spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየ 50 ዓመቱ ጉዞ (ክፍል አንድ)

የ 50 ዓመቱ ጉዞ (ክፍል አንድ)

ሲራክ  አስፋው  _ Ethiopia-Politics
ሲራክ  አስፋው

ሲራክ  አስፋው
ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓም ሮተርዳም

በእርግጥ ኢትዮጵያውያን ለመላው ኢትዮጵያ አልለፉም? አልታገሉም? አልታሰሩም? አልተሳደዱም ብሎም አልሞቱም?

እኔ የ1966 ዓ/ም አብዮት ሲቀጣጠል እና አሁን ኢትዮጵያ ያለችበን መቀመቅ በቅርብ ካዩ የዓይን ምስክሮች አንዱ ነኝ። የእድል ነገር ደግሞ ተክኖበት [ታክሎበት ] ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የተካሄደባትን ጥቃት በጥንቃቄ አይቻለሁ እያየሁም ነው።

እስኪ ከኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም እንጀምር

ከ1966 ዓ/ም አብዮት መቀጣጠል አስቀድሞ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም “ለትምህርት” በሚል ሽፋን (ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የእንግሊዝኛ ቋንቋ ችሎታው ትምህርት ለመከታተል በቂ እንዳልሆነ በጥብቅ መጠቆሙ አስፈላጊ ነው) ወደ አሜሪካ ሦስት ግዜ አቅንቶ ያውቃል። ከዚሁ በተያያዘ የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት መረጃ ተቋም የኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምን የጥፋት ተልእኮ በመንገዘብ በሞት እንዲቀጣ ቢበይንበትም በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ መንግሥት ውስጥ ሰርጎ ገብቶ የነበረው የውጪ ኃይል ከሞት አልፎ ሥልጣኑን በመሪነት እንዲቆጣጠር አድርጎታል። ይሄ እንግዲህ የኢትዮጵያን አንድነት የማዳከሙ ብሎም የመቀራመቱ የረጅም ጊዜ ዓላማ የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

እነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተታለሉት እነሱ እናያታለን የሚሏትን ኢትዮጵያን መገንባት የጀመሩ መስሏቸው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴን ጠቢብነት በመከተል ፋንታ ተቃዋሚ የመሰላቸውን በሙሉ በኃይል ለማጥፋት መነሳታቸው ነው። ይህም አሁን አብይ አህመድ የተከተለው መንገድ ነው። አብይ እንደነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ኢትዮጵያዊ ሳይሆን የጎሳ አክራሪ አዲስ መርዝ ነው።

እዚህ ላይ ማየት ያለብን የእነ ጀብሀ/ሻዕቢያ ወዘተ ብሎም በኋላ ላይ መንቀሳቀስ የጀመሩት ኢህአፓ/መኤሶን/ኦነግ እና ህወሃትን ነው። እነዚህን እንቅስቃሴዎች በኃይል ለማጥፋት መሞከሩ የእነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ትልቁ ስህተት ነው። እነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በግል አሰልጥነው እና መክረው ያነሳሷቸው ኃያላን ዓላማቸው ምን እንደሆነ መገንዘብና ቢያንስ መጠራጠር ነበረባቸው። ያንን ያደረጉ ግን አይመስለኝም። ምክንያቱም ከኢትዮጵያ አልፈው ሱዳንን ለመከፋፈል ለደቡብ ሱዳን “ነጻ አውጪ” በሚል ሽፋን ለሚቀሳቀሱ የጦር መሳሪያ በኢትዮጵያ ምድር ሲያሳልፉ ሱዳኖቹ ደግሞ በተራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ዓመጽ ለሚያካሂዱት እነ ጀብሀ/ሻዕቢያ/ኢህአፓ እና ህወሃት አገራቸውን ከፍተውላቸው ትጥቅ ብቻ ሳይሆን ስንቅም ብሎም የሱዳን መንግሥት፡ መናገሻ ከተማችን አዲስ አበባ ደርግን ለመጣል በስለላ ተግባር ዋና ተሳታፊ እንደነበረ አልባሽር መቀሌ ላይ በተላላኪው የሱዳን ዲፕሎማት ሲያስለፍፍ አይተናል። በጣም የሚያሳዝነው ኢትዮጵያውያን ወደ ሱዳን ሲሰደዱ ሱዳናውያኑ ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ ሲሰደዱ እያየን መንቃት እና ችግሮቻንን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍትሄ ማምጣት ተስኖን አገራችንን ለውርደት እና ለውድቀት አጋለጥናት። 

አሁን እዚህ ላይ መንገንዘብ ያለብን ሱዳንም ሆነች ኢትዮጵያ አገራቸውን ክፍት አድርገው አመጹ አንዱ የሌላው አገር ላይ እንዲፋፋም አስፈላጊውን የማቅረብ ሀብቱ እንደሌላቸው ግልጽ መሆኑን ነው። ከመጠቀሚያነት ውጪ ይኼ ነው የሚባል ሚናም የላቸውም። ይኼኛው ደግሞ የተፈጥሮ ሀብትን ለመቀራመት አፍሪካን የመከፋፈሉ አንዱ አጀንዳ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። አንድነት ‘እምቢ’ ለማለት ጉልበት ሲሰጥ መከፋፈል ለሁሉም ለመጋለጥና ለመጠቃት ያጋልጣል።

በመቀጠል ያየነው እኔ በደንብ ስለማውቀው የምእራቡ ዓለም የዜና አውታሮች ዘመቻ ነው። በምእራቡ ዓለም የዜና አውታሮች ኢትዮጵያን እንደ መንደር ኤርትራን ደግሞ እንደ አገር ተደርገው በፈረንጆቹ 70፣ 80 እና 90ዎቹ ዓመተ ምህረቶች በተጨማሪ ከደርግ መውደቅ ወቅት ጀምሮ ደግሞ መለስ ዜናዊ እና ኢሳያስ አፈወርቂ አዲሶቹ ድንቅ እና ብርቅ ዲሞክራቶች ተባሉ።

በምእራቡ ዓለም እስከዛሬ ድረስ አንድን ኢትዮጵያዊ የምእራቡ ሰው መጀመሪያ የሚጠይቀው ኤርትራዊ ነህ? በማለት ነው። ይኼ ያለማቋረጥ የምእራቡ ዓለም የዜና አውታሮች ለ40+ ዓመት ባካሄዱት ዘመቻ የምእራቡ ዓለም ሕዝብ ሳያውቀው በውስጡ ስለተቀረጸ ነው።

ታዲያ በተደጋጋሚ የምሰማውና እና የማነበው ኢትዮጵያውያኑ ምንም አልታገላችሁም ፤ ምንም አላደረጋችሁም ፤ የሚል ክስ ነው። እኔ በግሌ በወቅቱ አብረውኝ የነበሩ ወገኖቼም ሆነን የሆላንድን መንግሥት በተደጋጋሚ የጦር መሳሪያ ስጡን እና አገራችንን ነጻ እናውጣ። እኛ ለምጽዋት ተቀባይነት የመጣን አይደለንም ብያለሁ።

ላለፉት 46 ዓመታት በደንብ የማውቀው ተሰሚነት ብሎም እርዳታ የሚሰጠው ‘ኢትዮጵያዊ’ ለምንለው ሳይሆን ጎሰኝነትን እኛና እነሱን ለሚለፍፉ ቡድኖች ብቻ ነው። ይሄ ደግሞ ለጋሾቹ እንደሚሉት ‘በደንብ አልገባንም እኮ’ ሳይሆን ታስቦበት የሚደረግ ነው።

ከሞት የተረፍነው ኢትዮጵያውያን በፈረንጆችሁ በ1982 ዓ/ም አምስተርዳም ተሰብስበን ኢማሆ ‘የኢትዮጵያውያን ማህበር በሆላንድ’ በሚል ተሰባሰብን። በእርግጥ በወቅቱ መሃላችን የሃሳብ ልዩነቶች አልነበሩም ማለት ባይቻልም በኢትዮጵያዊነት የታነጸ በ”አንድ ኢትዮጵያ” የምናምን ከሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ማለትም ከኤርትራዉያንም ያሉበት ምንም አይነት የጎሳ የሀይማኖትም ሆነ የጾታ ልዩነት የሌለበት አንጋፋ ማህበር ተመስርቶ በወቅቱ ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ በዓለም ላይ የነበሩ የዉጪ እና የአገር ውስጥ ሊቃውንትን ፤ አንጋፋ ኢትዮጵያውያንን ፤ አባት እናቶችን ፤ ወጣቶችን በመሰብሰብ ትልልቅ ትርኢቶችና ሴሚናሮች፥ ስብሰባዎችን፥ ስነጽሁፎችን ‘አገራችንን እንዴት ብናደርግ ነው ከኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጀምሮ የተነሱባትን አመጸኞች የምናቆመው? በሚል መርሆ በማዘጋጀት ለፋን። በእነዚህ ሴሚናሮች ላይ የኢትዮጵያን ወዳጆች ብቻ ሳይሆን በወቅቱ የነበሩ የውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶቿንም እየጠራን ተከራክረናቸዋል ፤ አውግዘናቸዋል። የደርግ ተወካዮችንና የወቅቱ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶችን እንዲሁም ሻዕቢያን  ህወሀትንና በወቅቱ ትንሽ የነበሩ ቢሆንም የኦሮሞ አክራሪዎችን አውግዘናል። የለጋሽ አገራት ተወካዮችን ጆሮ ማግኘት ግን ምርጫቸው ስላልሆንን ማግኘት አልቻልንም። ኤርትራ ከተገነጠለች እና ህወሃት ኢትዮጵያን የመበከሉን ስራ ከጀመረ ከብዙ ዓመታት በኋላ የሁለቱም ዋና ለጋሻቸው ከነበሩት አንዱ ሚኒስትር ያን ፕሮንክ አፍ የሰማሁት እንደ “የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች ያጭበረበረን የለም” በማለት ዘ ሄግ ከተማ በየዓመቱ በሚዘጋጀው አፍሪካ ኮንፈረንስ ታዳሚዎች ሲናገሩ ነው።

በወቅቱ ታዲያ እንደ አቅማችን ትንሽ ብትሆንም 5×5 ሜትር የምትሆን ጽህፈትቤት አምስተርዳም “ነበረችን ነው የሚባለው?” ነበረችን!!! ያችን ጽህፈት ቤት ለማግኘት ብዙ ተለፍቶበታል። ኢማሆን ከእኛ የተረከቡት የደርግና የህወሀት ሰዎች ዛሬ ላለው ትውልድ እንኳን ጽህፈት ቤት ሊያስረክቡ የኢማሆን ደብዛውን አጥፍተው አጽሙን ብቻ ነው ያስቀሩት። ኢማሆ በአሁኑ ወቅት ኢሜል አድራሻ ብቻ ነው ያለው!!!

የኢትዮጵያውኑን በሆላንድ እዚህ ላይ ላቁምና እስኪ የሻዕቢያን ደግሞ እንይ።

በእርግጥ የእውቀትም ሆነ የችሎታ የበላይነት ኖሮ ነው በመጀመሪያ ሻዕቢያ በኋላ ደግሞ ህወሃት ዛሬ ደግሞ የኦሮሞ አክራሪዎች በተራ እያሸበረቁ የታዩት? በጭራሽ አይደለም። በላም አለኝ በሰማይ በመታለል የድብቁን አጀንዳ አራማጅነትን መገንዘብ ባለመቻል፣ በስሜታዊነት፣ የደርግና የህወሃት አገዛዝ ባደረሰው ሰቆቃ ቁጭት ብሎም ያንን ተጠቅሞ በያዘን የጎሰኝነት ስካር የመካረሩና የመከፋፈሉ ጎዳና እንዲሰፋ እነዚህ አገሮች የሚያቀርቡት የማያቋርጥ እርዳታ ነው። አንዳንድ ወገኖቼ ለምሳሌ እንደ እነ ጃዋር አይነቱን እንደልቡ ሲንቀሳቀስ ሲያዩ በደጋፊዎቹ ከሚለገሰው ገንዘብ ነው ሲሉ አዝናለሁ። ወገኖቼ እስኪ እጃችሁን ዘርጉ ስል ኢትዮጵያውያን ሲለግሱ ፤ ያላቸውን ሲያካፍሉ ነው ያየሁት እና የማውቀው። እነ ጃዋር ሌላ ከኋላ አይዟችሁ ባይ አሏቸው። ኢትዮጵያዊ ለአንድነት ለአብሮነት ለቅንነት ስለሚሰራ ያ ደግሞ ስልጣኔን እድገትን ስለሚያመጣ መገታት ስለአለበት የኢትዮጵያዊው እና የአክራሪው የገቢ ምንጭ በጭራሽ የሚወዳደር አይደለም።

እኛ አንዲት የዶሮ ምላስ የምታህል ጽህፈት ቤት ሲኖረን ሻዕቢያ አምስተርዳም እና ሮተርዳም ከተማዎች ባሉ ትልቅ መሰብሰቢያ፣ ለምሳሌ የማውቀውን የሮተርዳሙን ብንወስድ መሀል ከተማ ፤ ውዱ ቦታ ላይ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ጽህፈት ቤት ነበረው። እንደውም አንድ ወቅት ላይ የሮተርዳም ከተማ ከንቲባ ከእንግሊዙ ኒል ኪኖክ ወዘተ ጋር በማበር የመታሰቢያ ሀዉልት እስከማቆም ሄደውም ነበር።

በጣልያን ወራሪዎች ቅስቀሳ የተጀመረው ጥላቻ ኢትዮጵያዊነትን በተለይ አማራውን እንደ ወንጀለኛ የሚፈርጁ ብዙ ምእራባውያንም ነበሩ። ብዙ የስብዓዊ መብት ተቋም ጠበቃዎች ፤ ጋዜጠኞች ወዘተ ከደርግ ጭቆና አምልጦ የመጣ ኢትዮጵያዊ ላይ በይፋ አድልኦ ይፈጽሙም ነበር። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጅምላ ተቀባይነት አልነበረውም። ኢትዮጵያዊውም ከፍራቻ እና አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞች በተያያዘ መኖሪያ ፈቃዱን ካገኘ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ማህበር ብቅ አይልም ነበር። እንዲያውም ‘ፖለቲካ በሩቁ / ከፖለቲካ ነጻ የሆነ’ ወዘተ በሚል ዘይቤ ቤቱን ኢትዮጵያ አሰርቶ እያከራየ ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት ኖሯል። በሌላ በኩል ደግሞ ሻዕቢያ በዲስፕሊን የታነጹ ተወካዮቹን አሰማርቶ ማንኛውም ሰው የሚጠበቅበትን መዋጮም ሆነ ተሳትፎ እንዲያሟላ ያስገድድ ነበር። ታዲያ እኛ ኢትዮጵያውያኑ በዚህ ቀልጣፋ ስራቸው አልቀናንባቸውም ብል ውሸት ነው። 

እዚህ ላይ በወቅቱ እና ዛሬም ድረስ ፤  አንድ ኢትዮጵያዊ የአውሮፓ ማህበር ላይ ተሰሚነት የሚኖረው በጎሳው ማለትም የመገንጠል ዓላም ይዞ ከሄደ ወይንም የመገንጠል ዓላማ ካላቸው ጋር ተለጥፎ እንጂ በኢትዮጵያዊነቱ ሊያዩት የሚፈልጉ ብዙም የሉም። ይሄ ማለት ታዲያ ፍቅራቸውን ተቀባይነታቸውን ወሳኝ እርዳታቸውን ለማግኘት ያለማቋረጥ ሞራላዊ ጥያቄዎችን በማቅረብ እውነተኛ ማንነትን ለማሳየት መሞከር እንጂ በመቃወም እና በተለይ በዘለፋ የሚገኝ ምንም አለመኖሩን የመገንዘብ የኢትዮጵያዊነት ግዴታ አለብን። 

የዜና አውታሮቹ ሚና ከወቅቱ ጋር የሚሄድ ነው። ለምሳሌ እስከ ሻዕቢያና ህወሃት ሁለት ዙር ጦርነት ድረስ ድጋፋቸው ለሻዕቢያ ነበር። ወዲያውኑ ግልብጥ ብለው የህወሃት አፈቀላጤዎች ሆኑ። ዛሬ ደግሞ ፊታቸውን ህወሃት ላይ በከፊል አዙረውበታል። ምክንያቱም የታለመው ጥፋት እየተሳካ ነው። አሁን ደግሞ የአውሮፓ ማህበር አባላት ድጋፋቸው ለኦሮሞ አክራሪዎች ነው። ኤርትራን ልክ እንደ አፍጋኒስታን እና ሶርያ በጦርነት የታመሰ እና ሕዝብ የሚያልቅበት በማስመሰል የዛሬው የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ሱናክ ሳይቀሩ ስደተኛ ከኤርትራ እንደሚቀበሉ በአደባባይ አስታውቀዋል። ከሰብዓዊነት ከተነሱ ምነው ዛሬ የሩዋንዳው ፓውል ካጋሜ ባሰማሯቸው ገዳዮች ጎማ ላይ ለሚያልቀው የኮንጎ ሕዝብ ኑ ብለው ተቀባይነታቸውን ቢገልጹ? አንዲትን አገር ለመስበር ወጣት ልጆቿን ማስፈለስ (ወጣቱን ሀገር ጥሎ እንዲሰደድ ማድረግ)፡ ወታደር ከማዝመት የበለጠ ውጤት ያመጣል። ለመሆኑ ስንቶቻችን ነን ምእራቡ ዓለም ምነው እንደዚህ ምስራቅ አፍሪካ ላይ በፍቅር ተያዘ ብለን እራሳችንን የምንጠይቀው? ስንቶቻችን ነን እነ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በምእራቡ እርዳታ ወደ ዚምባብዌ ሄደው ያለምንም ተጠያቂነት በሰላም የሚኖሩት? ስንቶቻን ነን ሎንዶን ኢትዮጵያን ወክለው መጨረሻዋ ሰዓት ላይ ድርድር ተቀምጠው ሻዕቢያና ህወሃት አዲስ አበባ ይግቡ ተብሎ ሲለፍፉ የነበሩ ወዴት ሄዱ? ኑሯቸውስ እንዴት ነበር? ከነሄርማን ኮኸን ጋርስ አይታዩም ነበር? ስንቶቻቸንስ ነን ኢንቬስተር ቱሪዝም በሚል ማወናበጃ አገርና ሕዝባችንን ለማናውቃቸው በቋሚ አገልጋይነት እያጋለጥን መጤው ቤት ውስጥ ወገኖቻችንን በረንዳ አዳሪ እና የበይ የተመልካች የምናደርገው? ለዘመናት የተገነባ ግዙፍ እውቀትን እያፈረስን ወገኖቻችንን ከመሬታቸው እያሳደድን ከእጅ ወደ አፍ በሆነ ስራ መስክ እንዲሰማሩ በማስገደድ እውቀት ከማጥፋት በላይ ለሰቆቃ የምናጋልጠው? ወገኖቼ በዚህ 50 ዓመት ኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ያለውን ሰቆቃ ተገንዝበን ወደ አብሮነታችን ካልተመለስን ለወቅቱ አክራሪም ሳይቀር መኖሪያ አይደለም ኢትዮጵያ መቀበሪያችንም አትሆንም።

ወገኖቻችን ላይ የተጋረጠው ሰቆቃውና ችግሩ ኢትዮጵያ/ኤርትራ ውስጥ ብቻ ሳይሆን እዚህም አለ። እንደ ምሳሌ እስኪ ከኬፕቨርድ ደሴቶች በተራ የመርከበኝነት ስራ ተሰማርተው በአጋጣሚ ነዋሪነታቸውን ሮተርዳም ያደርጉ እና ልጆቻቸው ደግሞ እያደረጉ ያሉትን ላቅርብ። አስቀድሜ እነዚህ የኬፕቬርድ ሰዎች በፖርቱጋል ቅኝ ተገዢነት የኖሩ እና እንደኛ ከሃይማኖቱም ሆነ ከስነጽሁፉ ብዙም የቀሰሙ አልነበሩም። ዛሬ ሆላንድ ውስጥ ግን የእነዚህ የመርከብ ጠራጊ እና ቀለም ቀቢ ልጆች በትልልቅ የትምህርት ተቋሞች ትምህርታቸውን አገባደው በሳምንት አንድ ወይንም ሁለት ቀን የቋንቋ ፣ ከህግ በተያያዘ ፤ የትምህርት ፤ አጠቃላይ ለወገኖቻቸው ደራሽነት በመቆም በበጎ ተግባር ተሳትፈዋል። እኛ ማለትም ከኢትዮጵያ/ኤርትራ የመጣነው ግን እንደው ተከፋፍሎ በቤተክርስትያን እሱውም የተወሰነ ነው ይገናኝ እንጂ እንደዚህ ለወገን ደራሽነት አይታይብንም። በጣም ብዙ የተማሩ ልጆች አሉን ፣ ግን በበጎ አድራጎት አገልጋይነትና እውቀትን ማካፈል ላይ ይኼ ነው የማይባል ድክመት አያለሁ። አሁን በቅርቡ በቤትክርስትያን የአመለካከት ልዩነት ተነስቶ ስብሰባ ላይ ተካፍዬ መፍትሄው መሸማገል (ሚዲዬሽን) እንደሆነ ፤ መካረር ለማናቸውም እንደማያዋጣ አመለካከቴን ገለጽኩ። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የሆላንድን የሕግ እውቀት ያለው ሰው እንደሚፈለግ እና ኤርትራውያን ልጆች ብቻ ሆላንድ ውስጥ በሕግ ትምህርት እንደተመረቁ፡ ኢትዮጵያውያን እንደሌሉ ስሰማ ገረመኝ። አብረው የሚሰበሰቡት ሰዎች የሚያውቋቸው ፤ አብረዋቸው የሚበሉ ፤ በወዳጅነት የሚገናኙ ፤ ከዛም አልፎ ቤትክርስትያን እና በዝምድና ያሉ ሰዎች እዛ ስብሰባ ላይ እንዳየሁና “እከሊት የምትባል ወጣት የህግ ምሩቅ እዚህ እኛ አካባቢ ወደ አምስተርዳም ከተሄደ ደግሞ የእከሌ ልጆች—“ ብዬ ጠቆምኩ። ተገናኝተው ምክር ከተቀበሉ በኋላ በደስታ ሲደውሉልኝ አሁንም የገረመኝ መረዳዳት ሲቻል እንደማያውቅ በዝምታ ፤ ግን እዛ ስብሰባ ላይ እና ቅዳሴ አለመቅረታቸውን ሳስበው ወዴት እየሄድን ነው የሚለው ያስፈራኛል!!

በመጨረሻም የዛሬው ኮለኔል አብይ አህመድ አሊም አመጣጥ አካሄድ እና መጨረሻው ከኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተለየ አይደለም! አሁንም መፍትሄው መቻቻል አንድነት እና አብሮነት ብቻ ነው። 

ጸሃፊውን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማኘት ይቻላል ፡ siraksvoice@gmail.com 

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here