spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየልደቱ አያሌው የዳያስፖራ ተልዕኮና በሰሜን አሜሪካ እየተጫወተ ያለው የፖለቲካ ቁማር

የልደቱ አያሌው የዳያስፖራ ተልዕኮና በሰሜን አሜሪካ እየተጫወተ ያለው የፖለቲካ ቁማር

ደረጀ አያኖ 

ይህን ፅሁፍ እንዳቀርብ ያስገደደኝ አቶ ልደቱ አያሌው ባለፈው ከመሳይ መኮንን ጋር ያደረገውን ውይይት ከሰማሁኝ በኋላና ክዚያም ቀደም ብሎ በሰጣቸው ሐገራዊ አስተያየቶች ላይ አበው “የላይ ለምጡን፣ የውስጥ እብጠቱን ባለቤቱ ያውቀዋል”  እንዳሉት፣ የሰውየውን አደናጋሪና አሳሳች ትንታኔና የመልዕክቱን የሰምና ወርቅ ይዞታ ለአንባብያን ለመግለፅ ነው። 

አቶ ልደቱ አያሌው፣ “እኔ የ31 ዓመታት የፖለቲካ አንጋፋ ነኝ። ለምን አትሰሙኝም?” በማለት አድማጮቹንም ተማፅኗል። ነገር ግን ይህ የ31 ዓመታት የፖለቲካ አንጋፋ ነኝ የሚለው ልደቱ አያሌው፣ ከኢሃደግ እስከብልፅግና ባሉት አሥርተ ዓመታት ውስጥ የአማራ ሕዝብ ወደገደል ሲወረወር፣ ሲፈናቀል፣ ሲቃጠልና ሲጨፈጨፍ መቼ ነበር የታገለለት? በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞችና (አርሲ፣ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ) በመተከል የአማራ ሕዝብ በቀስት በገጀራና በጥይት ሲበሳሳ የት ነበረ? “ወላሂ ከአሁን በኋላ አማራ አልሆንም ተውኝ” ስላለችው ህፃን የትኛወን የፖለቲካ ድረሰትና ትንተና ፃፈ? ለየትኛው ሕዝብ ነበር በፓርላማም ሆነ ከፓርላማ ከወጣ በኋላ ጥብቅና የቆመው? ለፓርላማ ለመረጠው የአማራ ሕዝብ ወይንስ ለእንጀራ አባቱ ኅወሃት? 

ይህ ፅሁፍ፣ የአቶ ልደቱ አያሌውን ሦስት ስልታዊ፣ የሰምና ወርቅ ይዘት የለበሱ፣ አሳሳችና አደናጋሪ የፖለቲካ ትንታኔዎቹን ለማጋለጥ ነው። አቶ ለደቱ አያሌው በየጊዜው የሚያቀርባቸው የፖለቲካ ምልከተና ትንታኔዎች፣ በመሰረቱ በዚህ ፅሁፍ እንደቀረቡት መሰረተ ቢስ አቋሞቹ የሀቀኛ የሕዝብ ትግል ማወናበጃዎችና የግል ጥቅምን ለንማስከበር የታለሙ ብቻ ናቸው። ልደቱ ይህ ነው የማይባል ሕዝባዊ መሰረት የሌለው፣ በግለሰብ እንጂ በኅብረት/አንድነት ፖለቲካ የማያምን (እሱ የሚመራው የፖለቲካ ፓርቲ ካልሆነ የማይቀላቀል)፣ ለራሱ ጥቅም ብቻ ይሚያስብ (egocentric) አስመሳይ ፖለቲከኛ ነው። የልደቱ አያሌው ሦስቱ አድናጋሪና አሳሳች ትርክቶች እነሆ። 

1ኛ) አደገኛው የአቶ ልደቱ አያሌው ትርክት፡ ኅወሃት “ኢትዮጵያ ለገባችበት ችግር አንዱ የመፍትሄ አካል ነው። ገንቢ ሚና  መጫወት ይችላል”  

ይህ የአቶ ልደቱ አያሌው ግልፅ የሆነ የአቋምና የድጋፍ መልዕክት “ህወሃት ኢትዮጵያ ለገባችበት ችግር አንዱ የመፍትሄ አካል ነው” የሚል የአጭበርባሪዎች ትርክት ነው። 

እንዴት ነው “እኔ ብቻ ያላልኩት ካልሆነ” የሚል አቋም ከደደቢት ብረሃ ጀምሮ ለስድሳ ዓመታት ድርድርንና አብሮ መሥራትን የሚጠላ ደርጅት ዛሬ የመፍትሄ አካል የሚሆነው?  

እንዴት ነው በዝባዡን ስርዓት ሳይሆን በማኒፌስቶው ላይ “የአማራን ሕዝብ እንደዋነኛ ጠላት በጅምላ የፈረጀ” ከዚያም ለዘመናት የኖረበትን ሐገር በጉልበት በመቀማት ዘር ያጠፋና ከቀየው ያባረረ፤ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱና በእኩልነት በየትኛውም አካባቢ በነፃነትና በሰላም ሀብት አፍርቶና የማህበራዊው አካል ሆኖ እንዳይኖር የዘር ፖለቲካን የሚያቀነቅን ሕገ መንግሥት የነደፈና ኢትዮጵያን ወደ ዘለአለማዊ ብጥብጥና የጦርነት ማእበል ወስጥ የማገደ አካል ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል? 

ለዚህ አቶ ልደቱ አያሌው ሲመልስ “ምክንያቱም ህወሃት ከፈረሰ የሰሜን ሕዝብ ለጥቃት ይዳረጋል” ይለናል። 

ተው እንጂ አቶ ልደቱ ወዴት ጠጋ ጠጋ። አንተ የምትለው፣ ህወሃት ከፈረሰ አማራም ለጥቃት ሊዳረግ ነው? በመጀመሪያ ደረጃ ኅወሃት አይደለም እንዴ የሰሜንን ሕዝብ ለአስከፊ ጥቃት ያጋለጠ? በአማራና በአፋር ሕዝብ ላይ ያደረሰው ወረራ፣ ያወደመው የኢንደስትሪና፣ የጤናና የመሰረተ ልማት ውድመት እንዴት ይረሳል? 

ትላንትና አንድ ሚልየን ተኩል የሚጠጋ የትግራይና የሌላ ክልል ሕዝብ ለራሱና የብልፅግና የስሥልጣን ፍልሚያ ያጋየበት ጦርነትን የቀሰቀሰ፣ ከጦርነት የተረፈውን የትግራይ ሕዝብ ደግሞ በረሃብና በመፈናቀል ያከሰመ፣ በጦር ወንጀል አለም ፍርድ ቤት መቀውብ የሚገባውን አሸባሪ ድርጅት እንዴ እንደ ችግሩ መፍትሄ ባሰብ የሚችል ግለሰብ ያቀርባል? ሕወሃት እኮ፣ እሱ አዲስ አበባ በቪላ ቤት እየኖረ፣ ማርሰዲስ ቤንዝ እየነዳ ከሁለት ተኩል ሚልዮን የበለጠን የትግራይ ሕዝብ ለ27 ዓመታት በስንዴ እርዳታ ያኖረ ዘራፊ ቡድን ነው። 

አቶ ልደቱ ኅወሃት ከፈረሰ የስሜን ሕዝብ ለጥቃት ይዳረጋል የሚለው ኅወሃት ዛሬ በአይንህ እያኡእህው ራያን ወርሮ የለም?  ጠገዴንና ወልቃይትን እስከ ሰኔ 30 እይዛለሁኝ ብሎ የለም? ቀደም ሲልስ መቀሌ ቁጭ ብሎ አይደለም እንዴ የአማራ ሕዝብ (የሰሜን ሕዝብ ማለት ነው) በድሮንና በአብይ ስልጣን አስጠባቂ ቅጥረኛ (መርሲነርይ) ሰራዊት የሚጨፈጨፈው? ይህ የኅወሃት ስብስብ የሰሜንን ሕዝብ ከጥቃት ሊከላከል ይቅርና፣ ዋናው የሰላም ጠንቅ ነው። በወልቃይት፣ በጠለምትና በራያ ለዘመናት አብሮ ቆፍሮ፣ በልቶና ተዋልዶ የኖረን ሕዝብ እርስ በእርሱ ደም ያቃባ፣ ዛሬም የጠብና የእልቂት ጠንሳሽ የሆነ አሸባሪ ድርጅት ነው። ዛሬ አንተና የአማራ ጠሉ የኅዋሃት ስብስብ (እንደ አሉላ ሰለሞን ያሉ) “የአማራና የትግራይ አንድነት” በሚል አጀንዳ እያወናበዱ ያንንው የአማራ መሬት ራያ፣ ጠገዴንና ወልቃይትን ከምስለኔው የብአዴን ተላላኪዎቻቻው ጋር አብረው ለመዝረፍ ነው። “ዶሮን ሲያታልሏት በመጫኛ ጣልዋት” እንዲሉ። አንተስ ትርፍህ ምን ይሆን አቶ ልደቱ? 

አቶ ልደቱ ማወቅ ያለብህ፣ የሰሜንን ሕዝብ፣ አማራውን፣ ትግሬውንም ሆነ አፋሩን ከጥቃት የሚከላከለው የራሱ ሕዝብ ነው። የራሱ ክንድ። ህዝብ ከጥቃት የሚድነው በኅወሃትም ሆነ በሌላ አምባገነንና “ሕዝብ ጠል” ድርጅት አይደለም። ይህ አመለካከት ኅወሃትን ወደ መድረክ ለመመለሰ የተቀነባበረ “የሎቢነት” ሥራ እንደሆነ የሚያሳይ ሃቅ ነው። ወይንስ ዛሬ በአሜሪካ ዳያስፖራ እየተዶለተ ካለው የአገዛዙ የቅደመ “ሽግግር መንግሥት” አጀንዳ ተቀንጭቦ እንደመንደርደሪያ የተወሰደ ነወ?

ቀድም ብለህ እንደፈተልከው አጀንዳ፣ “የሰሜንን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ሲል” ዛሬ ሕወሃት የተባለው አሸባሪ ድርጅት፣ በእንጀራ ልጁ የብልፅግና መንግሥት ቡራኬ ተሰጥቶት፣ ራያን እስከ አላማጣ ድረስ ወርሯል። ስለዚህ በእውነትም “ኢትዮጵያ  ለገባችበት ችግር አቶ ልደቱ እንዳልከው ኅወሃት አንዱ የመፍትሄ አካል ነው”። 

ኢትዮጵያ ለገባችበት ችግር ወሳኙ መፍትሄ ግን ኅወሃትን ከሆዳምና ከተላላኪ ባንዳዎቹ ጋር በተፋፋመው የሕዝብ ትጥቅ ትግል  ከነወዲያኛው ጨርሶ መደምሰስ ብቻ እንጂ፣ የመፍትሄው አካል አድርጎ ማቅረብ የ31 ዓመት የፖለቲካ አንጋፋ ነኝ ከሚለው ልደቱ  አያሌው አይጠበቅም። በሰሜን አሜሪካ ልኅወሃት የሎቢነት ሥራ እየሰራ ካልሆነ። ለዚህም ይሆናል በኅወሃት በሚዘወሩ ሶሽያል  ሚድያዎች የሚወደሰው። 

2ኛ) የልደቱ አያሌው ሰምና ወርቅ የተላበሰ የ ”ሰላማዊ ትግል” ትርክት።  

አቶ ልደቱ አማራጩ የሰላማዊ ትግል ነው ይለናል። እኔ ለሰላሳ አንድ አመታት የሰላማዊ ትግል አካሂጃለሁኝ ይላል። በኢሃዴግ ግዜ፣ የፓርላማ ወንበርና ከማሞቅና ለስልጣን ኮርቻ ከፓርቲ ወደ ፓርቲ መዋቅሮች ከመዝለል በቀር ያመጣው አንዳችም መፍትሄ የለም። የህወሃትን አምባገነን መንግሥት የጣለው በወጣቱ የተመራው የሕዝብ እንቅስቃሴ ነው እንጂ ልደቱ አያሌው የመራው የሰላማዊ ትግል አይደለም። 

ከህወሃት ወደ ብልፅግና በሰላማዊ ትግል የመጣው ለውጥ ምን አመጣ? እስከወረዳ በኢሃአደግ ግዜ የነበረውን የካድሬ መዋቅር እንዳለ ተሸክሞና የዳቦ ሥም ሰጥቶ አይደል እንዴ ወደ ብልፅግና የተሻገረው? በዚያን ግዜ፣ ይህ የአምባገነን የካድሬ መዋቅር በቅድሚያ መፍረስ እንዳለበት የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነበር የተነበየው? ከጊዜው ባለስልጣኖች ጋር ከማሸርገድ በቀር። 

አቶ ልደቱ አያሌው፣ እነዚህን እውን ምልከታዎች በሰከነ መልክ መገንዘብ አለበት  

አምባገነናዊ ስርዓት በነገሰበትና ገለልተኛ የሆነ የመከላከያና የሕግ ተቋም በሌለበት ሐገር እንዴት ሕዝብ በሰላማዊ ትግል ዘላቂ መብቱን ያስከብራል?  

ሰላማዊ ትግል የሚሰራው ሕግና ሥርዓት ባለበትና በሚከበርበት ሐገር ነው። የሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የአምባገነን መንግሥት የስልጣን ማስጠበቂያ ዱላና ጉልበት በሆነብት፣ ፖሊስ በዘፈቀደ ሰላማዊውን ሕዝብ በሚያስርበት፣ ዳኛ ሲፈታ ህግ አስከባሪው አልፈታም በሚልበት፣ የሕዝብ እንደራሴዎችን ከፓርላማ አውጥቶ የመከሰስ መብታቸው እንኳን ሳይነሳ ከርቸሌ የሚወረወር አምባገነን መንግሥት ባለበት፣ በየክልልሉ ከተሞች የንፁሃን ደም በግፍ በሚፈስበትና መንግሥት ጆሮ ዳባ በሚልበት፣ ገለልተኛ ሚድያዎችና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ትንፍሽ ካሉ እንዲታሰሩ እንዲደበደቡና እንዲገደሉ በሚደረግበት፣ ሕዝብ በደሉን በአደባባይ እንኳን ወጥቶ መግለፅ በማይችልበት፣ መናገር እንዳይችል አንደበቱ በታነቀበት፣ ሕዝብ ለዘመናት ከኖረበት ቤቱ ትላንትና ከበሻሻና ካርሲ በመጡ የ21ኛ ክፍለዘመን ናዚዎች እንደከብት እይተነዳ በየጎዳና በሚጣልበት ሐገር፣ በዚህ በአንድ መሪና አንድ ፓርቲ  ፈላጭ ቆራጭነት በሚዘውር ሥርዓት እንዴት ተብሎ ነው የሰላማዊ ትግል የሚካሄደው?  

ወይ አቶ ልደቱ? በሰላማዊ ትግል ካመንክ ለምን ሰሜን አሜሪካ ውስጥ መሽገህ ተቀመጥክ? ሰላማዊ ትግልም ቢሆን እንኳን  ከሕዝብ ጋር እንጂ በሪሞት ኮንትሮል አይካሄድም። ማርቲን ሉተር ኪንግ የሰላማው ትግል ያካሄደው እኮ፣ ዲሞክራሲ በሰፈነበት አሜሪካ በሕዝብ መሃል ተቀምጦ ነው። የማንዴላ የአፓርታይድም ትግል፣ የሰላማዊ ትግል አላማ ቢይዝም፣ በተመሳሳይ ረድፍ አፍሪካን ናሽናል በተሰኘው የፖለቲካ ፓርቲው የትጥቅ ትግል በአንፅሩ እያካሄደ ነበር። በመጨረሻም ወሳኝ ድል ያጎናፀፈው ይህው በብዙ የአፍሪካ መንግሥት የተደገፈው የትጥቅ ትግል ነበር። የብዙዎቹ የአፍሪካ ሐገራት የነፃነት ትግልም በድል የተጠናቀቀው በትጥቅ ትግል ሰለተደገፈ ነው። የትጥቅ ትግልን የሚያጥላሉት፣ ስርዓታቸውን ለማስቀጠል የሚፈለጉ አምባገነኖችና ትርፍ የሚያገኙ ደጋፊዎችና ካድሬዎች ብቻ ናቸው። 

ለምሳሌ አቶ ልደቱ አያሌው “ህዝቡ ከፈለገ እቤቱ ቁጭ በማለት ሰላማዊ ትግል በመድረግ ማሸነፍ ይችላል” ይለናል። ይህንን ማድረግ ከአቶ ልደቱ ለምን አልተጀመረም? የሥርዓቱ በየወረዳው ያለ የካድሬ መዋቅር በየቤቱ እየጋባ አይደለም እንዴ ሲያሰኘው ለድጋፍም ሆነ ለቅወማ ሕዝቡን ለሰልፍ አደባባይ የሚያወጣው? ሲፈልግስ በጭለማም ሆነ በጠራራ ፀሃይ ክየቤታቸው አውጥቶ እረሽኖ የለም እንዴ? ትላንትና በአቶ በቴ ኡርጎሳ ላይ የደረሰው ፅዋስ ይህ አይደለም፣ በሰላማዊ ትግል መክንያት? የትጥቅ ትግል  የሚያደርገው ጃል መሮ ግን ነገ በድል የመለሳል። እንዲያው ለነገሩ፣ አቶ ልደቱ አሁን እንድሚለው ሕዝብ እቤቱ ቁጭ ብሎ የሚያካሂደው ትግል ቢሳካ እንኳን፣ የትኛው የተደራጀና በሕዝብ ድጋፍ የተጠናከረ የፖለቲካ ፓርቲ ነው ሥልጣኑን የሚረከብ?  የልደቱ አያሌው ፖፑላር ፍሮንት? ኢዜማ? ኢሐፓ? እናት ፓርቲ? ባልደራስ? ማን? 

ነገሩ “የላይኛው ከንፈር ለክርከር፣ የታችኛው ከንፈር ለምስክር” እንዲሉ ትኩረቱ ስርዓቱን ለማስቀጠል ምክንያቱንም አተገባበሩንም ለመጠቆም ነው ። የተፈለገው፣ የሰላማዊ ትግልን ሰበብ አደርጎ “ከኢሃደግ ወደ ብልፅግና፣ ወይም ከአባት ወደ እንጀራ ልጅ”፣ ምንም አይነት መዋቅራዊ ለውጥ ሳይደረግ ከነተባዮቹ እንደተገበረው የሥልጣን እርካብክብ፣ አሁን ደግሞ ወደሌላ እንዚህኑ “አባትንና ልጅን የሚጦር” ሥራአት የማዋለድ እሩጫ ነው። “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ምሰናል” በትጥቅ ትግል ይህንን የጭቆናና ያምባገነን የትውልግ ሐረግ ክሥሩ መንቅሎ አዲሲቷን ኢትዮጵያን መገንባት ግድ ይላል። የሰላማዊ ትግል መፈክር፣ ጉልቻ ለማቀያየር እንጂ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት አይቻልም። በሰላማዊ ትግል የማያምን አምባገነናዊ ሥርዓት የሕዝብ ዋነኛ ጠንቅ ስለሆነ በሕዝብ የትጥቅ ትግል መፈንቀልና መውደም አልበት። ሌላ ምርጫ የለም። 

በአጭሩ፣ አቶ ልደቱ የትጥቅ ትግልን አልደግፍም ሲል፣ በግልፅ እየነገረን ያለው “የፋኖ ትግል ልክ አይደለም” ነው። ፋኖ ማለት ሕዝብ ነው። ለአመታት ሕዝቡ መፈክር ይዞ፣ አደባባይ ወጥቶ በሰላማዊ መንገድ ጥያቄውን አቅርቧል። ያገኘው መስልስ ግን ድብደባ፣ እስርና ግድያ ብቻ ነበር። ህልውና የአልሞት ባይ ተጋዳይ ጥያቂ ነው። እራስን ከሞት የማዳን ትግል በዓለማት ሕግ የሚደገፍ ተግባር ነው። ልደቱ አያሌው እሱ የሚዘውረው ህቡይ ሃሳብ ቢሳካና የፋኖ ትግል ባይሳካ፣ አሁን ህይወታቸውን አዲዘሩ ለሚታግልላቸው አለቆቹ “ይኸው ድሮ ብዬ ነበርኮ” ለማለት እንዲረዳው ማለት ነው። የልደቱ አያሌው የፖለቲካ ጨወታ ወርቅና ሰም አለው። እያንዳንዱን ጠርጥሮ ማየት ያስፈልጋል። 

3ኛ) የልደቱ አያሌው “በቶሎ ድርድር ካልተደረገ ሐገር ይፈርሳል” ትርክት  

ለአሥርተ ዓመታት የፖለቲካ አቆማዳውን እየቀያየረ የአማራንና የኢትዮጵያውያውያንን ትግል ሲያጨናግፍና ሲያደፍቅ የነበረው ልደቱ አያሌው፣ ዛሬ ደግሞ ሽጉጥ አስታጥቆ ሲንከባከበው ወደነበረው ህወሃት መራሹ የዳያስፖራ የግዞት ካምፕ ጠጋ ብሏል። የሐገሪቱን የፖለቲካ የአየር ሁኔታ ከጥግ ሆኖ እየሰለለ፣ ፋኖን እንደ አማራ፣ ህወሃትን እንደትግሬ፣ ኦነግን እንደ ኦሮሞ ሕዝብ ታጋይ፣ ሸኔን እንደተገላይ ሁሉንም እንድበሽታው እያስታመመ፣ አስተያየቱንና አቋሙን በጥንቃቄ ከሌላው ወገን እንዳይጋጭ እየፈተለና እያጠነጠነ፣ አጋጣሚው ሲመጣ ደግሞ ሚዛኑ ወዳመዘነው ወገን የሚለጠፍ አቆብቁቦ የተቀመጠና ሕዝብ ጠንቅቆ ያላወቀው ተናዳፊ ኮብራ ነው። 

አቶ ልደቱ አያሌው ዛሬ በአንከር ሚድያ፣ ነገ በኮምፓስ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በርዕዮትና በወያኔ አፈቀላጤው ኢትዮ ፎረም ሚድያዎች በየጊዜው ብቅ በማለት የሚደሰኩረው አሳሳች ትርክት፣ በተለይም ዛሬ በሚካሄደው የአማራ ትግልና ህልውና ላይ የተጠመደ ፈንጂ ነው። ፀሐይ ጠለቅ ስትል በጉያቸው አቅፈው ያኖሩትን የህወሃት አጎቶቹን እያማከረና እየዶለተ፣ ፀሐይ ብቅ ስትል ደግሞ “ሐገሪቱ 

ከመፍረሷ በፊት በቶሎ መደራደር ያስፈልጋል” ይለናል። “ኢትዮጵያ” ከማለት ይልቅ “ሐገሪቷ” ይሏታል፣ ሥም እንድሌላት ምናምንቴ ሐገርና 

ለመሆኑ ለስንት አሥርተ ዓመታት ነው፣ ዘወትር አምባገነናዊው ስርዓት ሊገረሰስ ሲቃረብ “ሀገሪቷን ከመፍረስ እናድን” ስትሉን የከረማችሁት? ለመሆኑ ሀገር ቢፈርስ ማነው ተጎጅው? የተፈናቀለውና የታረዘው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በእስር ቤቱ በግፍ ታጉሮ በበሽታ የሚሰቃየው እስረኛ ወይንስ እንደ መዥገር ከጀርባው ላይ ተጣብቆ ደሙን እየጠጣ ያለው ሌባና ዘራፊ?  

ሀገር ቢፈርስ ደሃው ገበሬ ምንም አይሆንም። ወዛደሩም ቢሆን ሲዘርፉት ከነበሩት ቀምቶ ይበላል። ሀገር ቢፈርስ፣ “ይብላኝለት  አሁን ሕዝብን እየዘረፈ ለሚንደላቀቀው የሌባና የአምባገነን ተረኛ መንግሥት፣ ለደጋፊዎችሁና ለካድሬዎቹ”። ስለዚህ አቶ ልደቱ አያሉኤው እባክህን “ሀገር ይፈርሳል” በሚል ማር የተየቀባ መርዛማ ትርክት እኛን አታደናግረን። ለመሰሎችህ ሥልክ ደወልላቸው። 

ለእኛ ለሰፊው ልጆች ሐገር ከፈረሰ ዓመታት አልፈዋል። ሀገር በምንላት ኢትዮጵያ ወስጥ መንቀአሳቀስ አልቻልንም። በቀያችን መኖር አልቻልንም። በማንነታችን እየተለየን፣ ከቤታችን እየተውሰድን፣ ከአደባባይ እየተለቀምን እንታሰራለን። እየተጨፈጭፍን ነው። ሕግና ሥርዓት ፈርሷል። ሀገር ፈርሷል። መንግሥት አለሁ የሚለው፣ አዲስ አበባ በቅጥረኞች እየትየጠባቀና በተቆጣጠረው የሚድያ ልሳን ቢነዛው ፕሮፓጋንዳ ብቻ ነው። 

ስለዚህ ከወጣለት ዐምባገነናዊና ፋሽስታዊ ሥራት ጋር እንዴት ድርደር ማሰብህ፣ እንኳን ድርጊቱ ሃሳቡም ይሰቀጥጣል። የተደራጀ ሃይል በሌለብት ድርድሩ ከማን ጋር ሊሆን ነው አቶ ልደቱ? ከህዋሃት፣ ኦነግ? ሸኔ? ኦፌኮ? ኢዜማ? አብን? ባልደራስ? ይህ አማራጭ አይደለም። 

መደረግ ያለበት 1ኛ) አብይ አህመድ ያቋቋመውን “ብልፅግናዊና ወገናዊ” ሀገራዊ የምክክሮ ኮምሽን ማፍራስ። 2ኛ) አሁን ያለውን የብልፅግና መንግሥት ማፍረስ። 3ኛ) የአፍሪካ ሕብረትና የተባበሩት መንግሥታት ያቋቋሙትና፣ ሁሉንም ክልልሎች በአግባቡ እንደ ሕዝብ ብዛታቸው ያካተተ፣ የጊዜያዊ መንግሥት ማቋቋም። 4ኛ) በመላው የኢትዮጵያ አካባቢዎች፣ የውጭ ታዛቢዎች በሚካፈሉበት ይሕዝብ ቆጠራ ማድረግ። 5ኛ) ሕገ መንግሥቱን ሕዝብ መሚፈቅደው መሰረት ማሻሻል። 6ኛ) ግልፅና አስተማማኝ የሆነ የሕዝብ ምርጫ ማካሄድ። 

ጊዜው የአሁኑ ትውልድ የራሱን ታሪክ የሚፅፍበት ወቅት ነው። “ለኛ ለ31 ዓመታት የፖለቲካ አንጋፋዎቹ መድረኩን ስጡን። እኛን ስሙን” ከማለት ይልቅ፣ የዛሬው ትውልድ የራሱና የመጪው ትውልድ ሚና ለመገንባት በሚያደርገው እርብርብሾች “ከመገዱ ገሸሽ” በማለት እንርዳው። አቶ ልደቱ፣ መልካም የጡረታ ጊዜ በአሜሪካ። ፊትህን አጠገብህ ባለው መስታወት ተመለከተው። ያንተን ጊዜ አልሰራህበትም። ጊዜው የአዲሱ ትውልድ ነው0። እሳት የላሰ ትውልድ መጥቷል። 

አዲስ ትውልድ፣ አዲስ አስተሳሰብ፣ አዲስ ተስፋ።  

የኢትዮጵያ ሕዝብ በፋኖ የትጥቅ ትግል ያሸንፋል።  

“ፋኖ” ማለት ለህልውናው “በትጥቅ” የሚታገል ሕዝብ ነው።  

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉt.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉBorkena

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here