spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ መንግሥት መሆን የለበትም

የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ መንግሥት መሆን የለበትም

የኤዲተሩ ማስታወሻ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

በአሰፋ አበበ

) መግቢያ   

ለዝህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ የኦሮሞዎች ለፍትሕ፣ ለደህንነት እና ለእውነት (ኦፍደእ) የተባለ ድርጅት “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት አይደለም” በሚል ሚያዝያ 22, 2016 ያወጣው የአቋም መግለጫ ነው:: መግለጫው በ2008 በኦሮሞ ፕሮቴስት መልክ የተክሰተው የኦሮሞ ህዝብ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት፣ የመሬት ባለቤትነት እና የማንነት መብቶችን በህገ መንግስታዊ ዋስትና ለማስጠበቅ የተደረገው የኦሮሞ ብሄራዊ ንቅናቄ ለአሁኑ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ አሊ በመጋቢት ወር 2010 ወደ ስልጣን መምጣት ምክንያት በመሆኑ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኦሮሞ የአገሪቱ መሪ ወደ ሥልጣን ወጣ” የሚል ትርክት ተፈጥሮ የኢትዮጵያ መንግስት “የኦሮሞ መንግስት” ነው የሚለው ተረት ተስፋፋ እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት አይደለም ይላል:: 

በመግለጫው መሰረት ተረኩ የተፈጠረው ሥልጣን በያዙ ኦሮሞች ሲሆን ወደ ላቀ ደረጃ የተወሰደው ደግሞ ኦሮሞ ጠል በሆኑ ግለሰቦች ነው:: ኦሮሞዎቹ ትርክቱን የፈጠሩት ኦሮሞ የመንግስት ሥልጣን ተረክቧል፥ የኦሮሞ ጥያቄ ተመልሷል: በማለት ከኦሮሞ ህዝብ ድጋፍ ለማግኘትና ኦሮሞ ካልሆኑ ኢትዮጵያውያን ሊነሳ የሚችለውን ተቃውሞ ለመከላከል ነው: ካለ በኋላ ኦሮሞ ጠሎቹ ደግሞ ተረኩን ያጦዙት ኦሮሞ የሀገሪቱን ሥልጣንና ሀብት በቁጥጥሩ ሥር አዋለ፥ ሌላውን አገለለ ብለው ኦሮሞ ላይ ጥላቻ ለመስበክ እንደሆነ ይገልጻል::

መግለጫው በዶ/ር አቢይ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት አለመሆኑን ለማሳየት ተቃውሞን የማጥፋትና ኦሮሚያን የመቆጣጠር ክንውኖች ናቸው ያላቸውን ብዙ ዝርዝር ጉዳዮችን አቅርቧል:: ዝርዝር ጉዳዮቹም በመብት ጥሰቶችና የሕግ የበላይነት ባለመከበሩ በደረሱ ጉዳቶች ላይ ያተኮሩ ናቸው:: የዝህ ጽሁፍ ዓላማ በዝርዝር ጉዳዮቹ ላይ አስተያየት ለመስጠት ሳይሆን “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት አይደለም” በሚለው ብያኔ ላይ የግሌን አስተያየት ለማቅረብና ሥልጣን ላይ ያለው የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት ነው ወይስ አይደለም በሚል ተደጋግሞ ለሚነሳው ጥያቄ የግሌን ሃሳብ ለመሥጠት ነው::

) መንግሥት ማለት ምን ማለት ነው?

በኢሳይክሎፒዲያ ቢርታንካ መሠረት መንግሥት ማለት አንድን አገር የሚያስተዳድር የፖለቲካ ተቋም ወይም ሥልጣን ባለው ቡድን የሚቋቋም ሥርዓት ነው:: ይህንን ተቋም ለመምራት ዕድል ያገኙ ቡድኖች ሕግ እያወጡ፥ ሕግ እየተረጎሙና ሕግ እያስፈጸሙ/ ሥራ ላይ እያዋሉ አገሩን ያስተዳድራሉ ፥ይገዛሉ:: ለዝህም እንዲያመቻቸው ራሳቸውን በሶስት ቡድን (ቅርንጫፍ) ይከፍላሉ:: እነርሱም 1) ሕግ አውጪ  ቡድን 2) ሕግ ተርጓሚ ቡድን/የደኝነት ሥልጣን ያለው ቡድን እና 3) ሕግ አስፈጻሚ ቡድን ይባላሉ:: በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 50(1) መሰረት የኢትዮጵያ መንግሥት በፌዴራልና በክልል የተዋቀረ ነው:: በሕገ መንግሥቱ ለፌዴራል መንግሥት በተለይ ወይም ለፌዴራል መንግሥትና ለክልሎች በጋራ በግልጽ ያልተሰጠ ሥልጣን የክልል ሥልጣን እንደሚሆን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 52 (1) ላይ ተደንግጓል:: ስለዝህም በኢትዮጵያ ክልሎች ከፌዴራል መንግሥቱ የበለጠ ሥልጣን (residual power) አላቸው ይባላል:: የፌዴራሉን መንግሥት የሚመሩት የሕግ አውጪ፥ የሕግ አስፈጻሚ እና የሕግ ተርጓሚ ቡድኖች  እንዲመሩ ሥልጣን የተሰጣቸው ግለሰቦች ናቸው:: ግለሰቦቹ ደግሞ የተላያዩ የኢትዮጵያ ብሔሮች: ብሔረሰቦችና: ሕዝቦች ተወላጆች ናቸው:: 

በአሁኑ ጊዜ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ሕግ አውጪ አካል) የጋሞ ተወላጅ በሆኑት አቶ ታገሰ ጫፎ ይመራል:: የፌዴራሉ መንግሥት የሕግ ተርጓሚ (የዳኝነት ሥልጣን ያለው) አካል  የአማራ ተወላጅ በሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከበደ ይመራል::  የፌዴራሉ መንግሥት የሕግ አስፈጻሚ አካል  የኦሮሞ ተወላጅ በሆኑት ዶ/ር አቢይ አህመድ አሊ ይመራል፥፥ አስራ ሁለቱ ክልሎች በራሳቸው ተወላጅ/ ተወካይ ይመራሉ:: ክልሎቹ የየራሳቸው ሕግ አውጪ፥ ሕግ ተርጓሚና ሕግ አስፈጻሚ አካላት መሪዎችም አሉአቸው:: የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር የአማራ ተወላጅ የሆኑት ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው:: ስለዝህ እነዝህ ግለሰቦችና ሌሎች የሚመሩት ተቋሞችና የመስተዳድር አካላት መንግሥት ይባላሉ::

) የኢትዮጵያ መንግሥት የማን ነው

ከኤርትራ መገንጠል  የተረፈችው ኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተመሰረተች መሆንዋ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ተገልጿል:: የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለበቶችም እነዝህ የኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆናቸው በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 8(1) ሥር ተደንግጓል (በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አመለካከት ግን ሕገ-መንግሥቱ ኢሕዲሪን ወደ ኢፌዲሪ ቀየረ እንጂ ኢትዮጵያን አልመሰረተም):: ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የመሰረቱትን የፖለቲካ ማህበረሰብ ወይም አገር የሚመራው መንግሥት በዴሞክራሲያዊ መርሆች ላይ ተመስርቶ ሕዝቡ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር የማድረግና በመካከላቸው እኩልነት እንዲኖር የማድረግ ግዴታ በሕግ መንግስቱ አንቀጽ 88 ሥር ተደንግጓል::

 ታዲያ የኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በጋራ የመሰረቱትን አገር የሚመራው መንግሥት የማን ነው? የአገሪቷ ርዕሰ ብሔር የአማራ ተወላጅ ስለሆኑ አገርቷና መንግሥቱ የአማራ አይሆንም:: የአገርቷ ከፍተኛ የሥልጣን አካል የሆነውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት (ፓርላማ) የሚመሩት የጋሞ ተወላጅ ስለሆኑ መንግሥቱ የጋሞ አይሆንም:: ከመንግሥት ሶስቱ ሞሶሶዎች ውስጥ አንዱ የሆነውና በሕግ የማሰርና የመፍታት ሥልጣ ያለው የሕግ ተርጓሚውን አካል የሚመሩት የአማራ ተወላጅ ስለሆኑ  መንግሥቱ የአማራ አይሆንም:: በፓርላማው የሚወጣውንና በዳኝነት አካሉ የሚተረጎመውን ሕግ የሚያስፈጽመውን ከመንግሥት  ሶስቱ ሞሶሶዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን የሕግ አስፈጻሚውን አካል የሚመሩት የኦሮሞ ተወላጅ ስለሆኑ  መንግሥቱ የኦሮሞ አይሆንም:: የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን የሚመሩ ባለሥልጣናት ጉዳይም እንዲሁ ነው:: የገንዘብ ሚኒስቴር በሱማሌ ተወላጅ ስለሚመራ የሱማሌ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አይደለም:: የመከላከያ ሚኒስቴር በትግራዋይ ስለሚመራ የትግራዋይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት አይደለም:: አገርና መንግሥት በዝህ ዓይነቱ እሳቤ ሊመራ አይችልም:: መንግሥቱም ሆነ መሥሪያ ቤቶች የሁሉም ኢትዮጵያዊ ናቸው::

በፌዴራልና በክልሎች (ከትግራይ በቀር) የመንግሥት ሥልጣን ይዞ የሚያስተዳድረው የብልጽግና ፓርቲ ነው:: ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ የብቻ ፓርቲ አይደለም:: በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የብልጽግና ፓርቲ የሚቆጣጠረው፥ የፓርቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር አቢይ  የሚመራው መንግሥት እንጂ የኦሮሞ የብቻው መንግሥት አይደለም:: የኢትዮጵያ መንግሥት የአንድ ብሔር ወይም ብሔረሰብ መንግሥት አይደለም: መሆንም የለበትም: መሆንም አይችልም:: የኢትዮጵያ መንግሥት የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መንግሥት ነው:: ኦሮሞዎች እንደማንኛውም የአገርቷ ዜጋ በመንግሥቱ ውስጥ ይሳተፋሉ፥ ከዝህ  ተሳትፎአቸው የተነሳም ይህ መንግሥት የእኔ ነው ብሉ ጥፋት አይደለም፥፥ ጥፋት የሚሆነው መንግሥቱ የእኔ ብቻ ነው፥ የአንተ አይደልም ከተባለ ነው፥፥ ማንኛውም በመግሥቱ ተቋምና ሥራ የተሳተፈ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብና ሕዝብ ተወላጅ ወይም አባል ይህ መንግሥት የእኔ ነው ብሎ ተስትፎውንና አካታችነቱን ቢገልጽ ጥፋት አይደለም::

) የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት ነው የሚለው ተረክ ከየት መጣ?

በኦፍደእ መግለጫ እንደተገለጸው የ2008-2010 ኦሮሞ ፕሮቴስት የወላይታው ተወላጅ አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ሥልጣን እንዲለቁና የኦሮሞው ተወላጅ ዶ/ር አቢይ አህመድ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ሥልጣን እንዲይዙ ዋና ገፊ ምክንያት መሆኑ አይካድም፥፥ ኦሮሞ በኢትዮጵያ በቁጥሩ ከሌላው ብሔር፥ ብሔረሰብና ሕዝብ አንደምበልጥም እሙን ነው:: ኦሮሞ በቁጥሩ አብላጫ ቢሆንም፤ የኦሮሞ ተወላጆች በተለያየ ጊዜ  በኢትዮጵያ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ ቢሆንም የኦሮሞ ድርጅትን ወክሎ፥ የኦሮሞ ጥያቄን እመልሳለሁ ብሎ፥ አፋን ኦሮሞን በአደባባይ ተናግሮ ዶ/ር አቢይ አሁን የያዙትን ሥልጣን የሚያክል ሥልጣን የያዘ የኦሮሞ ተወላጅ ባለመኖሩ “በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ኦሮሞ የአገሪቱ መሪ ወደ ሥልጣን ወጣ” ተብሏል፥፥ ይህ ደግሞ የተሳሳተ አባባል አይደለም:: 

በኦፍደእ መግለጫ ውስጥ “የነገስታት አገዛዝ በ1966 ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ [ቢያንስ] ስድስት የኦሮሞ ተወላጆች በፕሬዚዳንትነት ወይም በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገልግለዋል። ይሁን እንጂ አውነተኛ ታሪክ በውሸት ተረት ተሸፍኖ “የኦሮሞ መንግሥት” የሚለው ቅጥፈት ተስፋፋ” ተብሏል:: ሆኖም ግን በኦሮሞ ታሪክ በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የያዙትን ሥልጣን  የሚያክል ቁልፍ ሥልጣን የያዘ የኦሮሞ ተወላጅ የለም::  ይህንንም አንደሚከተለው በዝርዝር አሳያለሁ::

 1. ራስ ጎበና ዳንጬ (ዳጬ)– ራስ ጎበና ዳንጬ ከአጼ ምንልክ ጋር ኢትዮጵያን የመሰረቱና የታወቁ የጦር መሪ የኦሮሞ ተወላጅ እንደነበሩ ይታወቃል፥፥ አጼ ምንልክ ሁሉንም የአካባቢ ንጉሦችን አስገብረው ንጉሠ ነገሥት ዘ-ኢትዮጵያ ሆነው ሁሉንም የኢትዮጵያ ግዛት በማዕከላዊነት ለመግዛት የተቀቡት/ የነገሡት እ. አ. አ. ኖቬምቤር 3, 1889 ሲሆን ራስ ጎበና ግን የሞቱት ከዝያ ሶስት ወር ቀደም ብለው  በጁላይ 1889 ነው:: በመሆኑም ራስ ጎበና የንጉሥ ምንልክን ዓላማ በማስፈጸምና ኢትዮጵያን በመመሥረት ውስጥ ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም ኢትዮጵያ ከተመሰረተች በኋላ ሥልጣን አልነበራቸውም– ንጉሥም፥ ፕሬዝዳንትም፥ ጠቅላይ ሚኒስትርም አልነበሩም::
 1. ልጅ ኢያሱ ሚካኤል ልጅ ኢያሱ በአፄ ምንልክ ኑዛዜ መሰረት ከዴሴምበር 12, 1913 እስከ ሴፕቴምበር 27,1916 ለ 3 ዓመታት በንጉሠ ነገሥትነት ሥልጣን ላይ ተቀምጠው ነበር::ሥልጣኑ የተሰጣቸውም እናታቸው የአፄ ምንልክ ልጅ ስለሆኑ የወ/ሮ ሸዋረጋ ምንልክን የትውልድ ሐረግ ተክትሎ ነው፥፥ የተፈለገው ልጅ ኢያሱ የምንልክን የአማራ ሥርዓተ መንግሥት እንዲያስቀጥሉ ሲሆን እርሳቸው በአባታቸው ኦሮሞ ከመሆናቸው ውጭ በኦሮሞ ውክልና ወይም የኦሮሞን ጥያቄ እመልሳለሁ ብለው ሥልጣን ላይ አልተቀመጡም፥፥ የመንግሥታቸው ሥራ በራስ ተሰማ ናደው ሞግዝትነት የሚሰራ ስለነበረ ልጅ ኢያሱ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የነበራቸው ተጽዕኖ ያን ያክል የጎላ አልነበረም፥፥
 1. አጼ ኃይለሥላሴ (ተፈሪ መኮንን)–አጼ ኃይለ ሥላሴ በአባቱ በራስ መኮንን ወልደሚካኤል ጉዲሳ በኩልም ሆነ በእናቱ በወ/ሮ የሺመቤት አሊ በኩል ኦሮሞ ነበሩ:: ሆኖም የአፄ ምንልክ አክስት በሆነችውና የአባቱ እናት በሆነችው (በአያቱ) በወ/ሮ ተናኘወርቅ ሣህለሥላሴ በኩል ቀጭን የዘር ሐረግ መዞ አማራ ነኝ ብሎ አማራ ሁኖ ለሥልጣን በቃ::  ኤፄ ኃይለሥላሴ ኦሮሞ ቢሆኑም የኦሮሞን ጥያቄ እመልሳለሁ ብለውም፥ ራሳቸውንም እንደኦሮሞ ተወካይ አቅርበው አያውቁም:: ኢትዮጵያን ለ44 (1930-1974) በንጉሠ ነገሥትነት የገዙት አማራ ሁነውና “ሞኣ አንበሳ ዘእምነ ነገደ ይሁዳ” የሚል ማዕረግ ፈጥረው አይሁዳዊ/ እስራኤላዊ የዘር ሐረግ አለኝ ብለው ነው::
 1. / ጄኔራል ተፈሪ ባንቲብ/ጄኔራል ተፈሪ ከሌ/ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም ቀጥለው የደርግ ሊቀ መንበርና የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆነው  ለ3 ዓመት (እ. አ. አ. 1974-1977) የሰሩ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው:: እርሳቸው በደርግ (የወታደር ኮሚቴ) ተጠርተው የተሾሙ እንጂ የኦሮሞን ጥያቄ ይዘው ወደ ሥልጣን የወጡ አልነበሩም:: የሚወኪሉትም ወታደርንና ሶሻሊዝምን እንጂ ኦሮሞን አይደለም:: ዋናው ሥልጣንም በደርግ አባላቱ እጅ አንጂ በእርሳቸው እጅ አልነበረም::
 1. ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያምኮሎኔል መንግሥቱ እ. አ. አ. ከ1977-1991 የደርግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት የነበሩ ከፍተኛ ሥልጣን የነበራቸው ርዕሰ ብሔር ነበሩ:: ኮሎኔል መንግሥቱ ሥልጣን ለቀው ወደ ዝምባቡዌ ከሸሹ በኃላ በሰፊው እንደተነገረው በአባታቸው በኃይለማርያም ወልዴ አያኖ በኩል ኦሮሞ እንደሆኑ ነው:: መንግሥቱ የኦሮሞነት ስሜትም የለሌው በሥልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ኦሮሞነቱን ገልጾ የማያውቅ፤ የኦሮሞ ብሔርተኞችን በማሳደድና በመግደል የሚታወቅ ነው::
 1. አቶ ተስፋዬ ዲንቃ ያዴሳ ፡አቶ ተስፋዬ  እ አ አ  ከአስፕሪል 26-  ጁን 6, 1991  ከሁለት ወር ላነሰ ጊዜ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሁነው ያገለገሉ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው፥፥  በሥልጣን በቆዩበት ጊዜ በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ ያኔ የነበረው የኢትዮጵያ የመንግሥት ሥርዓት ፕሬዝዳንታዊ ስለነበረ ወሳኙ ሥልጣን በፕሬዝዳንት መንግሥቱ እጅ እንጂ በእርሳቸው እጅ አልነበረም፥፥ ሥልጣን ላይ የወጡትም የኦሮሞን ጥያቄ ይዘው አይደለም::
 1.   / ጄኔራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ገለቱ ጄኔራል ተስፋዬ እ. አ. አ.  ከሜይ 21-27, 1991 ለንድ ሳምንት የኢትዮጵያ ተጠባባቂ ፕሬዝዳንትና ርዕሰ ብሔር የነበሩ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው፥፥  በሥልጣን የቆዩበት ጊዜ እጅግ በጣም አጭር ከመሆኑም በላይ ሥልጣን ላይ የወጡት የኦሮሞን ጥያቄ ይዘው አልነበረም::
 1. / ነጋሶ ጊዳዳ ሶላን ዶ/ር ነጋሶ እ. አ. አ.  ከ1995-2001 ለ6 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትና ርዕሰ ብሔር የነበሩ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው::  እርሳቸው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የተባለውን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ወኪለው፤ የኦሮሞን የፖለቲካ ጥያቄ ይዘው  በዝያ የሥልጣን እርከን ላይ የደረሱ የመጀመሪያው ኦሮሞ ናቸው:: ሆኖም ግን የመንግሥት ስርዓቱ ፓርላሜንተሪያዊ በመሆኑና ቁልፍ ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠ በመሆኑ በያዙት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የኦሮሞን ጥያቄ ለመመለስ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽ አላበረከቱም::
 1. መቶ አለቃ ግርማ ወልድግዮርጊስመቶ አለቃ ግርማ እ. አ. አ.  ከ2001-2013 ለ12 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትና ርዕሰ ብሔር የነበሩ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው፥፥  እርሳቸው  በግል ተወዳዳሪነት ተመርጠው ፖርላማ እንዲገቡ ተደርገው የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የተሰጣቸው (የትኛውንም የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ያልወከሉና) ፤ የኦሮሞን የፖለቲካ ጥያቄ ያላነሱ ቦታው ላይ ተቀምጠው ያለፉ ግለሰብ (place holder) ናቸው፥፥ በያዙት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የኦሮሞን ጥያቄ ለመመለስ ያደረጉት እንቅስቃሴ ባለመኖሩ በአጭሩ አስተዋጽኦ የላቸውም ብሎ ማለፍ ይቀላል::
 1. / ሙላቱ ተሾመ ዊርቱ ዶ/ር ሙላቱ እ. አ. አ.  ከ2013-2018 ለ5 ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንትና ርዕሰ ብሔር የነበሩ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው::  እርሳቸውም እንደ ዶ/ር ነጋሶ የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) የተባለውን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ወኪለው፤ የኦሮሞን የፖለቲካ ጥያቄ ይዘው  ለዝያ ሥልጣን የበቁ ናቸው::  ሆኖም ካላይ እንደተገለጸው የመንግሥት ስርዓቱ ፓርላሜንተሪያዊ በመሆኑና ቁልፍ ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠ በመሆኑ በያዙት የፕሬዝዳንትነት ሥልጣን የኦሮሞን ጥያቄ ለመመለስ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽ አላበረከቱም::
 1. / አቢይ አህመድ አሊዶ/ር አቢይ አህመድ እ. አ. አ  ከአፕሪል 2018  ጀምሮ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና ርዕሰ መንግሥት/ መስተዳድር ሆነው በማገልገል ላይ ያሉ የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው::  እርሳቸውም ወደ ሥልጣን የወጡት የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) በኋላ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(ኦዴፓ) የተባለውን የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅት ወኪለው፤ የኦሮሞን የፖለቲካ ጥያቄ ይዘው ነው:: አንዳንድ የውጭና የአገር ውስጥ የዜና አውታሮች እንደገለጹት ዶ/ር አቢይ በኢትዮጵያ  ቁልፍ የመንግሥት ሥልጣን የያዙ የመጀመሪያው የኦሮሞ ፖለቲካ መሪና የኦሮሞ ተወላጅ ናቸው:: ከላይ ከተዘረዘሩት የኦሮሞ ተወላጅ ባለሥልጣናት ውስጥ ከዶ/ር ነጋሶና ከዶ/ር ሙላቱ በቀር የኦሮሞ ፖለቲካ መሪ ሆኖ የኦሮሞን ጥያቄ ይዞ ለክፍተኛ ሥልጣን የበቃ ኦሮሞ የለም:: ሁለቱ ፕሬዝዳንቶች ደግሞ የሥነ-ሥርዓታዊ ሥልጣን (ceremonial figurehead)  እንጂ ወሳኝ ሥልጣን (real political power) አልነበራቸውም:: ምክንያቱም ወሳኝ የሆነው ሥልጣን በሕገ መንግሥቱ መሰረት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሰጠ በመሆኑ ነው:: ይህንን ወሳኝ ሥልጣን የያዙት የመጀመሪያው የኦሮሞ ፖለቲካ መሪ ዶ/ር አቢይ ናቸው::  

በአጭሩ በኢትዮጵያ የንጉሣዊ አገዛዝ ከተወገደበት ከ1966 ጀምሮ እስከ ዛሬ 8 የኦሮሞ ተወላጆች የርዕሰ መንግስትነት/መስተዳድርነት ወይም የርዕሰ ብሔርነት ሥልጣን/ ቦታ የያዙ ቢሆንም በእነዝህ 50 ዓመታት ውስጥም ሆነ በኢትዮጵያ ታሪክ የዶ/ር አቢይን የሚያክል ወሳኝ ሥልጣን የያዘ የኦሮሞ ተወላጅ አልነበረም። በመሆኑም በኦፍደእ መግለጫ “የሀገር ውስጥ እና የዓለምአቀፍ መገናኛ ብዙሀን አርዕስተ ዜናዎች በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አንድ ኦሮሞ ስልጣኑን ተቆጣጠረ የሚለው ፍጹም ውሸት [ነው]” የተባለው ትክክል አይደለም:: የመገናኛ ብዙሀኑ አባባል ውሸት ሳሆን እውነት/ ትክክል ነው::

“የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለው ትርክት የተፈጠረው  የኦሮሞ ተወላጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ወሳኝ የመንግሥት ሥልጣን ተቆጣጠረ ብለው ባመኑና በተደሰቱ ኦሮሞዎች ሲሆን ትርክቱን አሳድገው የኦሮሞ ተወላጅ በሆነ ሰው በሚመራው መንግሥት ላይ ጥላቻ ለመፍጠርና ተቃውሞ ለማስነሳት የተጠቀሙት ደግሞ ኦሮሞ ጠሎች ናቸው:: “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለውን ትርክት ተቀብለው የሚያራግቡት ደጋፊዎች የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ግለሰብ ቁልፍ ሥልጣን ስለያዘ የኦሮሞ ጥያቄዎች እርሱ በሚመራው መንግሥት ይመለሳሉ፥ የኦሮሞ ሕዝብ  ይህንን በኦሮሞ ተወላጅ የሚመራውን መንግሥት መደገፍ እንጂ መቃወም የለበት ብለው የሚያምኑና በዝህ ፕሮፓጋንዳ ለመንግሥት የኦሮሞን ድጋፍ ለማሰባሰብና ተቃውሞን ለመቀነስ የሚጥሩ ናቸው:: “አብቹ የአባ ገዳ ልጅ” የሚል መፈክር ፈጠረውም ድጋፍ ለማሰባሰብና ተቃውሞን ለመቀነስ ተንቀሳቅሰው የተወሰነ ስኬት አግኝተውበታል::

በአሁኑ ጊዜ “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለው ትርክት በብዛት እየተራገበ ያለው ኦሮሞዎች ከሌላው ኢትዮጵያዊ በተለየ በዝህ መንግሥት የተጠቀሙ አስመስለው በማቅረብ ሌላው ብሔርና ብሔረሰብ በኦሮሞና በመንግሥት ላይ ተቃውሞ እንዲያስነሱ በሚቀሰቅሱ የኦሮሞ ጠሎች ነው:: በመሆኑም ትርክቱ በኦሮሞ ተፈጥሮ በኦሮሞ ጠሎች ተወስዶ ኦሮሞን እየጎዳ ያለና መንግሥትን በተንኮልና በውሸት ጠልፎ ለመጣል እያገለገለ ያለ እውነትነት የሌለው አደገኛ ትርክት ነው::

ሠ) መደምደሚያ

በደጋፊዎችም ይቅንቀን በተቃዋሚዎችም ይቀንቀን “የኢትዮጵያ መንግስት የኦሮሞ መንግስት ነው” የሚለው ትርክት ውሸተኛ እና አደገኛ ፕሮፓጋንዳ ነው:: ፕሮፓጋንዳ ሰውን ለማነሳሳት የሚያገለግል መሣሪያ ሲሆን ሕዝቡን አሳምኖ ለማስነሳት ይጠቅማል የተባለውን ሙሉ ወይም ግማሽ ውሸት ማሰራጨትን ይጨምራል፥፥ በፕሮፓጋንዳ ዋናው የሚታየውም መረጃው የሰውን አስተሳሰብ ወደተፈለገው አቅጣጫ ሊወስድ ይችላል ወይ የሚል ነው እንጂ እውነተኝነቱ አይደለም፥፥ በዓለማችን ብዙ እውነትነት የሌላቸው ፕሮፓጋንዳዎች ሕዝቡን አነሳስተው አጫርሷል: ጉዳት አድርሰዋል፥፥ ይህ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ  እየተካሄድ ያለው ውሸተኛና አደገኛ ፕሮፓጋንዳም የበለጠ ጉዳት ሳይደርስ መቆም ይኖርበታል:: ፕሮፓጋንዳውን የማቆምና ውሽትነቱን የማጋለጥ እንቅስቃሰም ድጋፍ ለማስገኘትና ተቃውሞን ለመቀነስ ብለው ፕሮፓጋንዳውን በጀመሩትና ባስፋፉት ወገኖች መጀመር ይኖርበታል::

የጥላቻ ንግግርና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣው አዋጅ ቁጥር 1185/2012 መሠረት የሐሰት መረጃን በብሮድካስት፣ በህትመት ወይም በማህበራዊ ሚድያ በጽሁፍ፣በምስል፣ በድምጽ ወይም በቪድዮ ማሰራጨት የተከለከለና ድርጊቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ነው፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 2(2) መሠረት “ሃስተኛ መረጃ” ማለት ውሸት የሆነና የመረጃውን ውሸት መሆን በሚያውቅ፣ ወይም መረጃውን የሚያሰራጨው ሰው ካለበት አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የመረጃውን ሃሰተኝነት ሊያውቅ ይገባ ነበር የሚያስብል በቂ ምክንያት እያለ የሚሰራጭ ሁከት ወይም ግጭት የማስነሳት፣ ወይም ጥቃት እንዲደርስ የማድረግ እድሉ ከፍ ያለ ንግግር ነው።

በመሆኑም የኢትዮጵያ መንግሥት የሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  መግሥት መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ስገባቸው “የኢትዮጵያ መንግሥት የኦሮሞ መንግሥት ነው” እያሉ ሐሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩ ሁሉ ከድርጊታቸው መቆጠብ ይኖርባቸዋል::

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉt.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉBorkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here