spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeነፃ አስተያየትየብር የመግዛት አቅምን የማዳከም ዐቢይ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታዎች 

የብር የመግዛት አቅምን የማዳከም ዐቢይ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታዎች 

የብር የመግዛት አቅምን የማዳከም - Ethiopian Birr Devaluation
ከሌላ ድረ ገጽ የተገኘ

ከንጋቱ ወልዴ

መግቢያ  

የአንድ ሀገር ገንዘብ የመግዛት አቅም ማዳከም አንዱ የገንዘብ ፖሊሲ ማስፈጸሚያ ስልት ሲሆን ሀገሮች እንደሚፈልጉት የፖሊሲ ውጤት ገንዘባቸውን ሊያዳክሙም ጠንካራ እንዲሆን ሊያደርጉም ይቸላሉ፡፡ ለምሳሌ ማዕከላዊ ባንኮች የወለድ ምጣኔያቸውን ከፍ በማድረግ የአንድን ሀገር ገንዘብ ተመራጭ የእሴት ማስቀመጫ በማድረግ ከንግድ ሸሪኮች አንጻር ያለው ዋጋ ከፍ እንዲል ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በዋናነት ይህ ፖሊሲ ተግባር ላይ የሚውለው የንግድ ሚዛን በማስተካከል የውጭ ምንዛሪ ክምችት እንዲጨምር ለማድረግ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ሀገሮች የገንዘባቸውን የመግዛት አቅም ከፍ በማድረግ ወይም በማዳከም ከንግድ ሸሪኮቻቸው አንጻር ያላቸውን የንግድ ሚዛን ለማስተካከል ወይም ትርፍ የንግድ ሚዛን (ከፍ ያለ የውጭ ምንዛሪ ክምችት) እንዲኖራቸው የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲን ይጠቀማሉ፡፡ በተለይም ባደጉትና በፍጥነት በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች የራሳቸውን የገንዘብ አቅም ማዳከም ምርቶቻቸውን በገፍ ወደ ውጭ ለመላክ ስለሚያስችላቸው (የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ ስለሆነ) ይህን ፖሊሲ በብዙ ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ የአሜሪካና የቻይና የንግድ ጦርነት መንስኤውም አሜሪካ ቻይና ሆን ብላ ገንዘቧን በማዳከሟ የኔ ኩባንያዎች ተወዳዳሪነት እየጎዳች ነው፤ ገበያዬንም በሸቀጦቿ ታጥለቀልቅብኛለች፤ የአሜሪካውያንን ሥራ ወደ ሀገሯ ወስዳብኛለች…ወዘተ እያለች የምትከስበት ነው፡፡ እዚህ ላይ እነዓለም ባንክ እና የዓለም የገንዘብ ድርጅት ያሉ ዓለማቀፍ አበዳሪ ተቋማት ያላደጉ ሀገሮች ላይ የገንዘባቸውን የምንዛሪ አቅም እንዲያዳክሙ የሚያደርጉትን ያህል ጫና ቻይናን በተመሳሳይ መንገድ የገንዘቧ የመግዛት አቅም በማዳከሟ የማይደግፏት መሆኑን ሲታይ የነዚህ ተቋማት ሚና ምንድን ነው ብሎ መጠየቅ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ 

ጥናቶች ምን ይላሉ  

ይህ ባደጉት ሀገሮችና የማምረት አቅማቸው ከፍተኛ በሆነ እንደ ቻይና ባሉ ሀገሮች ያለውና ለቻይና ጠቀሜታው የጎላ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲ እንደኛ ላሉ መዋቅራዊ የአቅርቦት ችግር ዋነኛ ምጣኔ ሀብታዊ ተግዳሮታቸው ለሆኑ ሀገሮች ምን ያህል ይሠራል ለሚለው መሠረታዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ተቻኩለን ወደ ውሳኔ ከመሄዳችን በፊት እጅግ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህም ጥቂት በዘርፉ ባለሙያዎች የተደረጉ ጥናቶችን መመልከቱ ይረዳል፡፡ 

ጌታቸውና ሌሎች (2019) ‹‹የብር የመግዛት አቅም ማዳከም ዐቢይ ምጣኔሃብታዊ እና የገቢ ስርጭት እንድምታዎቹ (ተጽእኖዎቹ)›› በሚል ርእስ በተሠራ ጥናት1በአጭር ጊዜ (short run) የብር ምንዛሪ ግሽበት የወጭ ንግድን የተሻለ ተወዳዳሪ እንዲሆን ቢያስችልም እና የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ቢያያሻሽልም በረጅም ጊዜ (long run) ግን ምጣኔሀብታዊ መኮማተር ሊያስከትል ከመቻሉም በላይ ውጤቱ የዋጋ ንረት ሊሆን እንደሚችል ድምዳሜያቸው ያሳያል፡፡ ይህ ውጤት በአብዛኛው የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም ሊያመጣው ይችላል ተብሎ ከሚታሰበው በተቃራኒው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ 

በተጨማሪም ታከለ አብደላ እና ታከለ ጌታቸው (2019)2‹‹የብር ምንዛሪ ማዳከም ጥቅል ምጣኔ ሀብታዊ እንድምታዎች›› በሚል ርእስ የብር የምንዛሪ ተመን በ15 በመቶ ማዳከም፣ የወጪ ንግድ ሸቀጦችን ዋጋ በ15 በመቶ በመቀነስና ፣ የገቢ ንግድ ሸቀጦችን ዋጋ በ15 በመቶ በመጨመር በሠሩት የቢሆን ትንታኔያዊ ጥናት የመጀመሪያው ከሸማቾች ዋጋ መለኪያ (CPI) መጨመር በስተቀር ሁሉም የዐቢይ ምጣኔ ሀብት አመልካቾች ቅናሽ አሳይተዋል፡፡ ይህም የምንዛሪ አቅም ማዳከም የዋጋ ንረት የሚያስከትል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሁለተኛው የቢሆን ትንታኔ ውጤት ምንም እንኳን በብር የመግዛት አቅም መዳከም ወደውጭ የምንልካቸው ሸቀጦች የመግዛት ፍላጎት ቢጨምርም በመዋቅራዊ የአቅርቦት ችግር ምክንያት የፍላጎትን ያህል ማቅረብ የማይችለው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ፤ የሚጠበቀውን ያህል የውጭ ምንዛሪ ግኝት ጭማሪ ማሳየት አልቻለም፡፡ በሦስተኛው የቢሆን ትንታኔ፤ ማለትም የገቢ ሸቀጥ ዋጋ በ15 በመቶ ቢጨምር አጠቃላይ የዐቢይ ምጣኔ ሀብት አመልካቾች ከነበሩበት/base case scenario/ አሸቆልቁለው ተገኝተዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከውጭ በሚገቡ ግብአቶች ላይ ያለውን ከፍተኛ ጥገኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባቸው ሸቀጦች አብዛኛውን ምጣኔ የሚሸፍኑት (ነዳጅ፤ማዳበሪያ፤መድኃኒት፤ማሽነሪ…ወዘተ) መሠረታዊ ከመሆናቸው አንጻር የብር የመግዛት አቅም ማዳከም የንግድ ሚዛንን ያስተካክላል የሚለው መነሻ (assumption) ለኢትዮጵያ የማይሠራ መሆኑን ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም በሚፈጠረው የዋጋ ንረት ምክንት አጠቃላይ የማኅበረሰቡ ኢኮኖሚያዊ ደኅንነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያመጣ መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል፡፡ 

በአንጻሩ የብር የመግዛት አቅም ማዳከም በዋና ዋና ወጭ ምርቶች ማለትም ጫት እና ቡናን እንደማሳያ በመውሰድ ያለውን ሚና በሚመለከት በተደረገው ጥናት3፤ በረጅም ጊዜ የቡናና የጫት የውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ በጎ ተጽእኖ እንዳለው አመልክተዋል፡፡ ይህም በረጅም ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን የሚያሻሽል መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በተጨማሪም ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና የሀገር ውስጥ ምርት እድገትም የሚያሳይ መሆኑን ጥናቱ ያመለክታል፡፡ ይሁንና ይህ እውን የሚሆነው በፖሊሲው ምክንያት የሚፈጠረውን የዋጋ ንረት ጫና መቆጣጠር ከተቻለ ብቻ እንደሆነ ጥናቱ አመልክቷል፡፡ 

የብርን የመግዛት አቅም የማዳከም ተሞክሮዎች  

በሀገራችን እአአ ከ1992 በኋላ የውጭ ምንዛሪ ፖሊሲያችን ላይ ለውጦች ተካሂደዋል፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት የነበረው ቋሚ የምንዛሪ ፖሊሲ /fixed exchange rate regime/ ወደ ገቢር-ነበብ ማለትም በገበያው እንዲወሰን ማድረግ ሆኖም መንግሥት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጣልቃ የሚገባበት /managed  floating exchange rate regime/ ሲተገበር ቆይቷል፡፡ እአአ በ 2015 የብር የመግዛት አቅም በ 15% እንዲጋሽብ ሲደረግ ምክንያቶቹ ተመሳሳይ ነበሩ (የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነትን ማሻሻል)፤ በውጤቱም ጥናቶች የሚያሳዩት ይህ እርምጃ ተወዳዳሪነታችንንም አላሻሻለም፣ በረጅም ጊዜም የውጭ ምንዛሪ ክምችታችንን አልጨመረውም። የዓለም የገንዘብ ድርጅት ሊሰጠን ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠበት 3.6 ቢሊዮን ዶላር ከአጭር ጊዜ አኳያ የዶላር እጥረቱን በመቅረፍ ገበያውን ሊያረጋጋው ይችላል። ይሁንና ለውጭ ገበያ የምናቀርባቸው ምርቶች በገቢ ግብአት ላይ ያላቸው ጥገኝነት በአማካይ እስከ 60% (ግብርናንም ይጨምራል ምጣኔው ጥቂት ይቀንስ እንደሆነ እንጂ) የሚደርስ በመሆኑ ወደውጭ ልከን ክምችታችንን ለማሳደግ ያለን እድል ተግዳሮት ይገጥመዋል። 

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተከታታይ በዓለማቀፍ የገንዘብ ተቋማት ግፊት እየተዳከመ የሚገኘው የብር የመግዛት አቅም ወደ ውጭ የሚላኩ ሸቀጦችን ተወዳዳሪ በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡትን ደግሞ በማስወደድ የንግድ ሚዛን መዛባትን ያስተካክላል ቢባልም፤ የብር የመግዛት አቅም መዳከም ለዋጋ ንረቱ ቀጥተኛ አስተዋጽዖ ማድረጉን በቅርብ ጊዜ የተደረገ ጥናት ያመለክታል4፡፡ ይህ የሆነበት ምክንትም 80% የገቢ ንግድ ዋና ዋና ሸቀጦች በጣም አስፈላጊ በመሆናቸው (ማዳበሪያ፤ ነዳጅ፤ መድኃኒት፣ ለማምረቻ ግብአት የሆኑ የካፒታል እቃዎች…) ውድም ቢሆኑ መግዛት ግድ ስለሚሆን ነው (price inelastic)፡፡ በሂደቱም የገቢ ሸቀጦች ዋጋ በመጨመር የበጀት ጉድለት በማስከተል፤ ጉድለቱን ለመሸፈን በሚደረግ ጥረት የገንዘብ አቅርቦት እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል፡፡ ስለሆነም ዋነኛ የዋጋ ንረት መንስኤ የሆነው የምግብ እህል ምርት በበቂ ሁኔታ ማቅረብ እስኪቻልና ከወጪ ንግድ የምናገኘው ገቢ ከፍ አስኪል ድረስ የብር የመግዛት አቅም ማዳከም መቆም እንዳለበት ይመክራሉ፡፡ 

ይሁንና ከ 2018ቱ የጠቅላይ ሚንስትር አብይ ወደ ሥልጣን መምጣት በኋላ መንግሥት የብር የመግዛት አቅም በተከታታይ የማዳከም ፖሊሲ ተከትሏል፡፡ ይህም በወሳኝነት ይፋዊ አለማድረጉ ካልሆነ በስተቀር ፖሊሲውን እየተገበረው ነው ማለት ይቻላል፡፡ ታዲያ የሚፈለገው የውጭ ንግድ ተወዳዳሪነታችንን ጨምሮታል፤ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በሚፈለገው ደረጃ ለመሳብ አስችሏል፤ ይልቁንም ከፍተኛ የሆነ ምጣኔሀብታዊ እና ፖለቲካዊ እንድምታ ያለው የዋጋ ንረትንስ ለመቆጣጠር አስችሏል ለሚሉ ጥያቄዎች መልሳቸው አይደለም የሚል ነው፡፡ይህ በተደጋጋሚ የታየና በተደጋጋሚ የሄድንበትና ውጤት ያላመጣንበት ነው። ያልተሄደበት መንገድ መሞከር አለብን። ምናልባት ውጤታማ እንዳይሆን በሀገራችን ውስጥ በብዙ ስፍራዎች ያለው የሰላም እጦት እና ጦርነት እንደምክንያት ይቀርብ ይሆናል፤ ይሁንና ቅቡልነቱ ሊፈተሽ የሚገባው ቢሆንም ትክክል ነው ቢባል እንኳን ገንዘብን የማዳከም ፖሊሲ ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት ወደ ተረጋጋ ፖለቲካዊ ድባብ መመለስ እንደሚያስፈልግ የሚያሳይ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለዚህም መንግሥት ለሚዲያ ፍጆታ ከሚውሉ የዝግጁነት መግለጫዎች ባሻገር ለእውነተኛ ፖለቲካዊ መፍትሄ ከተፋላሚ ወገኖች ጋር ድርድር ቢያደርግ አሁን ለገጠመን የውጭ ምንዛሪ እጥረት መዋጥ የሌለብን ኪኒን እንዳንውጥ ሊያግዝ ከመቻሉም በላይ የሰላም አየር መተንፈስ ከተቻለ በቀጥተኛ ኢንቨስትመንትም መሳብ የሚቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል ብሎ መገመት ይቻላል፡፡ 

በአጠቃላይ ሲታይ የብርን የመግዛት አቅም ማዳከም የታለመለትን ግብ ከመምታት አንጻር አሁን ባለንበት ሁኔታ ለኢትዮጵያ የማይሠራ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን ኑሮ ከድጡ ወደ ማጡ የሚያስገባ፤ መዘዙም አሉታዊ 

የሆነ ምጣኔ ሀብታዊ እና ፖለቲካዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡ በመሆኑም ይህ የፖሊሲ ሃሳብ ወደ ትግበራ ከመሸጋገሩ በፊት መንግሥት ሊያስከትል ስለሚችለው ውጤት ቆም ብሎ ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ይመስላል፡፡ 

እንደ መውጫ  

ሀገራችን ከዚህ በፊት ከተገበረችው ተመሳሳይ ፖሊሲ ውጤቶች በመነሳት፤ አሁን ካለንበት የግጭት እና የጦርነት ድባብ ባልወጣንበት ሁኔታ፤ የማምረት አቅማችን በውጭ ግብአቶች ላይ ያለውን ከፍተኛ ጥገኝነት መፍትሄ ሳያገኝ ተግባራዊ የሚደረግ ፖሊሲ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝን በመሆኑ መንግሥት ባለድርሻ አካላትን በተለይም የዘርፉን ምሁራን ያካተተ ዘላቂ መፍትሄ ላይ ትኩረት ቢያደርግና ለሀገራችን የሚጠቅም እርምጃ ቢወስድ የተሻለው መንገድ ነው፡፡ ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን እርምጃዎች መውሰድ የተሻለ አማራጭ ነው፡፡ 

✍ አሁን ላለንበት የዐቢይ ምጣኔሀብታዊ መዛባትም ሆነ ሌሎች ችግሮቻችን ምንጭ በሀገራችን ውስጥ እየተካሄደ ያለው ግጭት/ጦርነት ስለሆነ፤ መንግሥት ቁርጠኛና እውነተኛ የሆነ ፖለቲካዊ መፍትሄ  ተፋላሚዎችን ጨምሮ ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ጋር ለመፈለግ ዝግጁ መሆን፤ 

✍ ከውጭ ምንዛሪ ግኝት አንጻር ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ዜጎች ለቤተሰባቸው የሚልኩት ሃዋላ እንዲጨምር ብሔራዊ ስሜትን ከሚያዳብሩ እርምጃዎች በዘለለ ኢኮኖሚያዊ ማበረታቻዎች በውጭ ለሚኖሩ ዜጎች መስጠት፤ 

✍ የአምራች ዘርፉ የሚታይበት ከአቅም በታች የማምረት ችግር ለመፍታት በዘርፉ ለሚሰማሩ አምራች ተቋማት ያለባቸውን ተግዳሮቶች በመፍታት (በመሬት አቅርቦት፤የጉምሩክ ቀረጥ እና ታክስ ማሻሻል፤ የፋይናንስ አቅርቦት፤ ተያያዥ ሙስናን መቀነስ፤ የመሠረተ ልማት አቅርቦት ማሻሻል፤ወዘተ) ምርታማነትን ለማሳደግ መሥራት የብርን የመግዛት አቅም ከማዳከም በፊት ሊወሰዱ ከሚገባቸው ተግባራት ይገኙበታል፡፡

_

1 Getachew A. Woldie , Khalid Siddig (2019)፡ Macroeconomic and distributional impacts of exchange rate  devaluation in Ethiopia: A computable general equilibrium approach

2 Takele Abdisa , 2Derese Getachew (2019). Economy-Wide Impact of Currency Devaluation in Ethiopia: A Recursive Dynamic Computable General Equilibrium Analysis 

3Abdelkaf Elias, Amsalu Dachito & Shabu Abdulbari (2023). The effects of currency devaluation on Ethiopia’s major export commodities: The case of coffee and khat: Evidence from the vector error correction model and the Johansen co-integration test

4 Alemayehu Geda & Kibrom (2020). The challenge of inflation and financing development in Ethiopia: A  Kaleckian approach with empirical result, https://www.researchgate.net/publication/346649752

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉt.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉBorkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here