spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትበአብይ አህመድ አገዛዝ  ለከባድ ብሄራዊ አደጋ የተጋለጠችው ኢትዮጵያ ፣ ፋኖ እና አሜሪካ 

በአብይ አህመድ አገዛዝ  ለከባድ ብሄራዊ አደጋ የተጋለጠችው ኢትዮጵያ ፣ ፋኖ እና አሜሪካ 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የፖሊሲ ንግግር ተብሎ በኢትዮጵያ ባቀረቡት ንግ ግር የኢትዮጵያን መንግስት በሰብአዊ መብት አያያዝ ከተቹ በኋላ ኢትዮጵያ ለገጠማት ላለችበት የተወሳሰበ ችግር የጸጥታ እርምጃም መፍትሄ አይሆንም በሚል ተናግረዋል

 

ነአምን ዘለቀ
 ቬርጂኒያ፣ ዩስ አሜሪካ

የአሜሪካ ባለሙሉ ስልጣን  አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በአዲስ አበባ በሰጡት ይፋዊ መግለጫ፣  ለፋኖ፣ ለኦነግና፣ ለአብይ አህመድ አገዛዝ ያቀረቡት  ጥሪ እና የሰጡት አስተያየት ዝም ብሎ የመጣ አይደለም።  የአሜሪካ መንግስት የሚደርሰውን ሁለገብ መረጃ (የሰው፣ የሳተላይት፣ የኤሌክትሮኒክ ወዘተ) በሚገባ በመዳሰስ እና በመተንተን ከደረሰበት መረዳት ተነስቶ የአብይ እህመድ ጦርነቱን  ማሸነፍ እንዳልቻለ እና እንደማይችልም ከአደረበት ስጋት የመነጨ መሆኑን መገመት ይቻላል፡  ይህም አረዳድ እና ስጋት፤ እንደ አብይ አህመድ እና በብዛት በኮታና ከካድሬነት ከሾሟቸው ጄነራሎቹ ባዶ ፉከራ ሳይሆን፤ በተቃራኒው የፋኖን ጠንካራ የወታደራዊ አደረጃጀት፤ ዲስፒሊን እና አንቅስቃሴን፤ የውጊያ ብቃትን እና የሞራልና የስነምግባር ብቃትን፣ እንዲሁም ያስመዝገባቸውን ተጨባጭ ወታደራዊ ተደጋግሚ ድሎች ከመገንዘብ ጭምር የመነጨ ነው፡፡

በመሠረቱ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተባባሰ የቀጠለው ህዝባዊ የትጥቅ አመጾችና ወታደራዊ ግጭቶች፡ ሀገሪቱን ወደ ከፍተኛ ትርምስና ምስቅቅል ሊከት የሚችል መሆኑ፣ ለቀጠናውም ለአካባቢውም ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አደጋ የሚዳርግ ሊሆን እንደሚችል  አሜሪካኖቹ ይገነዘቡታል። ይህ አረዳድ እና ስጋት የአሜሪካ መንግስት ብቻ ሳይሆን ሌሎች መሰል አገራትም ሆኑ፤ ለሀገራቸው ቅን የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚጋሩት ነው። ይህን በጣም አሳሳቢና አስጊ ሁኔታ  የአገዛዙ መክሸፍ መሆኑን ተረድቶ፤ ለሰላማዊ መፍትሔ በቁርጠኛነት ከመንቀሳቀስ ይልቅ፤ ቅዠታሙ አብይ እህመድ ና  በኦሮሚያ  ብልጽግዎች የሚዘውረው አገዛዝ የሀገሪቱ ዘርፈ ብዙ ችግሮች ዋናው አቀጣጣይ/multiplier ሆኖዋል።  በበርካታ እምዶችና በዚህ ጽሁፍ ለመዘርዝር የማይቻሉ ነገር ግን ከበቂ በላይ መረጃዎችና ማስረጃዎች የሚቀርቡባቸው ፓለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ በሰብአዊ ሁኔታዎች፣ በህግና ስርአት መጥፋት፣ ስርአተ አለበኝነት ቀውሶች ውስጥ የተዘፈቀች ሀገር እንደሆነች በርካታ ሂደቱን የሚከታተሉ የፓለቲካ፣ የኢኮኖሚም ሙያተኞች በጥናት ተኮር ጽሁፎቻቸውና ቃለ ምልልሶቻቸው፣ እንዲሁም የፓለቲካ ስዎች የሚስማሙበት መራርም፣ አሳሳቢው እውነታ ነው።  ከህወሃት ዘመን በባሰ ሁኔታ  የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ተባብሶ የቀጠለ ስለመሆኑ፣ የጅምላ ያላህግ አግባብ ማሰር፣ ስቆቃ መፈጸም፣ ልዩ ልዩ የሰብአዊ መብቶች የሚጥሱ እርምጃዎች አብይ እህመድ ወደ ስልጣን ሲመጣ ህወሃትን  “አሸባሪ” “ኢ-ህገ መንግስታዊነት” ናቸው በማለት የከሰሰባቸውን ወንጀሎች ፋሽስታዊውና አጭበርባሪው አብይ አህመድ አገዛዝ  ልቆና ፣ አጠናክሮ መገኘቱ ከበቂ በላይ መረጃዎችም ውጥተዋል። በቅርቡ የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት የሰብአዊ መብቶች፣ የሌበርና የዴሞክራሲ ቢሮ ያወጣውን አመታዊ የሰብአዊ መብቶች  ዘገባ ያጢኑዋል።  እነዚህና  ሌሎችም የአገራዊ ቀውሱ  መገለጫዎች ተደምረው ዛሬ ኢትዮጵያ ሀገራችን የገባችበት ከባድ የብሄራዊ ህልው አደጋ ጥልቀት ለመገንዘብ የሚያዳግት አይደለም። 

ከዚህ ጎን ለጎን አብይ አህመድ  ይህንን  ሀገራችን የምትገኝበትን አስከፊና ያፈጠጠና ያገጠጠ ሃቅ ዘርፈ ብዙ ቀውስ ለመደበቅ፤ እውነተኛ ስጋት በመካድ፤ ከፍተኛ በጀት መድቦ አጀንዳ ማስቀየስ የእለት ተእለት ተግባሩ ሆኖአል።  በእየለቱ ተውኔቶች መድረስ እና ንግግር በማድረግ፤ በተከፋይ ዲጂታል ካድሬ ሠራዊቱ አማካኝነት የሀሰት ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨትንም ስራዬ ብሎ ቀጥሎበታል፡፡ በመሆኑም ስልጣኑን በምንም ኪሳራ፣ በኢትዮጵያ የመበታተንም ኪሳራ ለማስቀጠልም የማይመለስ ፣ ሀገራዊ  ኃላፊነት የማይሰማው የቅዠታሙ የአብይ አህመድ እገዛዝ ከፍተኛ የህዝብ ዕልቂትን ያስከተለ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅልዎች እያሰፋፋ ቀጥሎአል። በመሬት ላይ ያሉ በርካታ ኩነቶች የሚያረጋግጡት  የብልጽግናው አገዛዝ በአማራና ኦሮሚያ አካባቢዎች ምንም ቁጥጥር ማደረግ እንዳልቻለ የማይታበል ሀቅ መሆኑን ነው። የፋኖ ፣ የኦነግ ስራዊት አማጺዎች ሰፊ የቆዳ ስፋት ያላቸውን ሁለቱን ትላልቅ ክልሎች መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ፣ በፈለጉበት ጊዜ ወደ ወረዳ፣ ዞን ፣ እና  ክልል ከተሞች ስርገው በመግባት አደጋ እንደሚያደርሱ፣ ፓሊስ ጣቢያዎችን የብልጽግና መዋቅሮችን፣ እስር ቤቶችን አጥቅተው እስረኛ አስፈትተው፣ መሳሪያና ተተኳሽ  ማርከው ወደ መጡበት እንደሚያፈገፍጉ ከበቂ በላይ ልዩ ልዪ መረጃዎች ወጥተዋል። የብልጽግና መሪዎች ወደ እነዚህ አካባቢዎች ሲጓዙ በድሮን፣ በጄት፣ በልዪ ኮማንዶዎች፣ በብረት ለበስ የጦር ተሽከርካሪዎች ታጅበው እንደሆነም አሜሪካኖች፣ በአጠቃላይ የአለም አቀፉ ማህበረስብ ያሚያውቀው እውነታ ነው። በቅርቡ የአገዛዙ ቁንጮ አብይ አህመድ ወደ ነቀምት፣ ባህር ዳር፣ ጎርጎራ በተጓዘ ቀናት እንዳደረገው።   የብልጽግናው አገዛዝ ከኦነግ ስራዊት መሪዎች ጋር ባደረገው  የተጨናገፈ የዳሬሰላም “ድርድር” ወቅት፣ የአሜሪካው አምባሳደር የተናገረው ሌላው ገላጭ ነው። “መኪና እየነዳሁ እንጦጦ ሄጄ መመልስ የሚያስጋኝ’ ሁኔታ ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የምንገኘው”  በማለት በተደራዳሪዎቹ ፊት መናገሩን ጃል መሮ በቅርብ ባወጣው መግለጫ ይፋ ማድረጉም የሚታወስ ነው።  የብልጽግና መሪዎች እንደ ሰጎኗ ራሳቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው፣ መራራውን እውነታ ከመዋጥ ይልቅ ፣  መሬት የረገጠ መፍትሄዎች ከመሻት  ይልቅ፣  ለራሳቸው በመዋሸት በሃሰት ፕሮፖጋንዳ ራሳቸውን አሳምነው ህዝብን ለማደናቆር ብዙ ይዳክራሉ።  ነገር ግን እነሱ ያልተረዱት የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ አለም አቀፍ ማህበረስቡ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ከባድ አደጋዎች ጠንቅቀው ይረዱታል።  

ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ሁኔታዎች በቅርበት ለሚከታተሉ እና ለሚረዱ፤ የሰው ህይወት ደህንነት ለሚያሳስበው   ሰብዓዊ ፍጡር ሆነ ተቋሟት ሁሉ የሚያስጨነቅ እና እንቅልፍ የሚነሳ መሆኑ ግልጽ ነው። የአሚሪካ ስጋት ከዚህ እሳቤ እና የሁኔታዎች ዳሰሳም ጭምር የሚመነጭ መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡ የሩቁን እንኳን ትተን የቅርቡን ብንመለከት፤ ታሪክ እንዳንዴ ራሱን ይደግማል እንደሚባለው በደርግ ዘመን የትግራይ የበላይ አዛዥ የነበረው የደርግ ኢሠፓ ከፍተኛ ካድሬ ሻምበል ለገሰ አፋው እንዳደረገው ሁሉ፤ “ሁሉም ተቆጣጥረናል፣ ደምስሰናቸዋል፣ ከተሞችን እያጸዳን ነው”  ባሉበት አፋቸው፣ ሶስት አራት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ   “የአንድ ወገን የተናጠል የተኩስ አቁም አደረኩኝ” የሚል የምንተ እፍረት ሰበብ ያወጀበት የሚታወስ ነው።  በህዝብ ውስጥ የተደረገውና  በህወአት ኃይሎች የተመራው የሽምቅ ውጊያ፤ በትግራይ ተልእኮ የተሰጠው የመከላከያ ስራዊትን ፋታ ነስቶት ገፍቶ ከትግራይ እንዳስወጣው  ከአሜሪካም፤ መላው አለምም ትወስታ ያልከሰመ የትላንት ጥሬ ሀቅ ነው፡፡  

በመረጃ አሰሳም፤ አደረጃጀትም፤ ትንተናም፤ በወታደራዊ ሳይንሳዊ ፣ ስትራቴጂካዊ አጥልቆና አርቆ በማሰብም እጅግ ጥቂቶች በስተቀር አብዛኞቹ ደካማ የሆኑት የመከላከያ የበላይ አዛዦች “ዱቄት አድርገናቸዋል” “ተበትነዋል” ፣”ጋንታም የላቸውም”፣ ወዘተ የሚል በተደጋጋሚ ህዝብን በሐሰት ፉከራ ያደንቁሩ እንጂ፤ እውነታው ሌላ እንደ ነበር የውጭ የመረጃ ድርጅቶች ዝርዝር መረጃ እንደነበራቸው  የአሜሪካው አሌክ ዲዋል፣ የእንግሊዙ ማሪትን ፕላውና ሌሎችም ከውጭ መረጃ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት ያላቸው ፈረንጆች ያወጧቸው መረጃዎችና ሰነዶች በወቅቱ ጠቋሚ ነበሩ።  የመከላከያ ጀነራሎች ፉከራ ከአየር ሳይወርድ  ህወሃት በጥቂት ግዜያት ውስጥ፤ ህዝብን እደራጅቶ፣ በደፈጣና በሽምቅ ውጊያ  በመላው ትግራይ አካባቢዎች በተሠማራው የመከላከያ ስራዊት ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሲፈጸምበት ነበር፡፡ ይህም ሁኔታ ተከትሎ የአብይ ብልጽግና ጄኔራሎች ከተሞችን በተነጣይና አነስተኛ ጦሮች ለተወሰነ ግዜ በማስጠበቅ፤ በረሃውን እና ገጠሩን ለህወሃት ተተወለት (እነ ሻምበል ለገሰ አስፋው በደርግ/ኢሰፓ ዘመን ካድረጉት እምብዛም ያልተለየ) ። በመደበኛ ውጊያ  ሽንፈት የደረሰበት ህወሃት ራሱን አደራጅቶና አጠናክሮ በመጨረሻም በየቦታው በተደጋጋሚ የተሰነዘረበት ጥቃት መቋቋም የተሳነው  የመከላከያ ስራዊት  ከመላው ትግራይ ገፍትቶ፣ ብዙ የህይወትና የማቴሪያል ኪሳራ ደርሶበት  እንዳስወጣው  የሚታወቅ መራር ሃቅ ነው። በሌላ ሀገር አንዳንዶቹ ጀነራሎች ኮር ማርሻል የሚያስደርጋቸው  ውድቅትና እልቂት የደረሰ ቢሆንም የመከላከያ ስራዊቱን ለዚያ ውድቀት ያደረሱትን ብሎም ህወሃት ወሎን፣ ጎንደርን ስሜን ሽዋን፣ አፋርን በመውረር ከፍተኛ ውድመትና እልቂት ለማድረስ የሚችልበት ቁመና እንዲገነባ ያስቸለው ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረጉ ጀነራሎች ናቸው ባኋላ በሹመት የተንበሸበሹት። 

በዚህ ሳይወሰን በአብይ አህመድና በሹመትና በሰፋፊ መሬት እድላ  ያንበሸበሻቸው  ሁሉም ባይሆኑ በብዛት ካድሬና  ጥቅመኛ ጀነራሎች አቅምና የስትራቴጂካዊ ኮማንድ ብቃት አለመኖር ሳቢያ፤ የህወሃት ኃይል በ2ኛ ዙር በ 3ኛ ዙር  ባካሄደው ውጊያ፤  ደብረ ሲና የደረሰበት፣ ደሴን የተቆጣጠረበት፣ የጂቡቲ – ኤትዮጵያ መንገድ ሚሌን ለመያዝ ኮሮችን ለውጊያ ያሰማራባት ከባባድ የአገር ህልውና አደጋዎች ተደቅነው እንደነበርም የሚታወስ ነው፡፡ እነዚህ የህልውና አደጋዎች፤ በአጭሪ ጊዜ ሊቀለበሱ የቻሉት በአመዛኙ የፋኖ ኃይልን ጨምሮ የአማራ፤ የአፋር፤ የሶማሌና የሌሎች ክልል ልዩ ኃይሎች በከፈሉት መራራ የህይወት መስዋዕትነት፤ በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ደጀንነት፤ በስንቅ፤ በሞራል፣ በማቴሪያል፣ በዲፕሎማሲ፣ በህዝብ ግንኙነትና ሁለገብ ጥረቶች እና በኤርትራ መንግስትም ድጋፍም ጭምርና የብዙ አቅሞች ድምር ውጤት በማስባሰብ  እንደነበር የሚረሳ አይደለም፡፡ ይህንንም አብይ አህመድና የብልጽግና መሪዎች ዛሬ ሊክዱት ቢዳዳቸውም በወቅቱ በየአደባባዩ የመስከሩለት እውነታ ጭምር መሆኑን እነሱም በደንብ ያውቁታል፤ ታሪክም መዝግቦታል። ይሁንና ክህደት እንደ ዋነኛ መለያ ባህሪውና ስልቱ ያደረገው  አብይ አህመድ ዛሬ ላይ በህዝብ ገንዘብ የገጽታ ግንባታ ዘጋቢ ፊልሞችን በመስራት የተገኘው አንጻራዊ ድል የአንድ አካል ፣ የእሱና የጥቂት ጀነራሎች እቅምና ጀግንነት አድርጎ ሌላ የክህደት  ትርክት በመፈብርክ፣ የዘጋቢ ፊልም በማስራት ውስብስቡም ብዙ ተዋንያን፣ ብዙ መስዋእትነት የከፈሉትን (የእማራ ፋኖን ጨምሮ) ለመፋቅ ሌላ ታሪክ/ትርክት  ሲስራም የኢትዮጵያ ህዝብ ታዝቧል፡፡ 

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ፣ ክህወሃት ጋር በፕሪቶሪያ የተደረገውን ስምምነት ተከትሎ ፣ ኢትዮጵያ እንደ ሀገር ከህወሃት መራሹ ጦርነት ሀገሪቱ ገና ሳታገግም፤ የአማራ ህዝብ ከደረሰብት ውድመትና እልቂት ሳያገግም፣ ቁስሉ ሳይጠግግ፣ አብይ አህመድ  በፋኖ ኃይሎች እና በአማራ ሰፊ ህዝብ ላይ የዕብሪት ጦርነት አወጀ።  ይህንንም ተከትሎ  የአብይ አህመድና ሹመኛ ካድሬ የበላይ ጀነራሎቹ በትዕቢት ተወጥረው “ትጥቅህን ብቻ ሳይሆን  ሱሪህንም እናስፈታህለን” በሚል ፉከራ በራሱ ቀዬ ዘልቀው ተኩስ በመክፈት ጦርነት ጀመሩ። በአማራ ክልል በራሱ ቀዬ መጥተው እንደ ህወሃት መራሹ ጦርነት በወራሪነት (offensiveness) ሳይሆን፤ ሰብዓዊ ባህሪ በሆነው በአልሞት ባይ ተጋዳይነት መንፈስ የአማራ ህዝብና የአብራኩ ክፍይ የሆነው ፋኖ አማራጭ አጥቶ የህልውና ማስከበር የምከታ (defensive) ጦርነት ውስጥ እንዲገባ እንዳስገደዱት የሚካድ  ሀቅ እይደለም፡፡ እነሱ የተገላቢጦሽ በየእለቱ ፕሮፓጋንዳ ህዝብን ለማደናገር ቢሞክሩም።  የጦርነትን አስከፊነት በንድፈ ሀሳብ ሳይሆን በተጨባጭ ተመክሮ የሚያውቀው ፋኖና ሰፊው የአማራ ህዝብ በትላንቱ ጦርነት ከደረሰበት እልቂትና ውድመት ሳያገግም ፣ መንበሩ እንዲጸና ፣ ሀገርንም ለመታደግ ከፍተኛ ድጋፍና መስዋእትነት በከፈለለት አብይ እህመድና በእሱ የሚታዘዙት የመከላከያ አዛዦች የክህደት ጦር ተሰበቀበት።  በመሰረቱ የአማራ ህዝብ እንደዚህ ዓይነት አስከፊ ጦርነት ውስጥ ላለመግባት ለግማሽ ምዕት ዓመት ግድም እየተፈጸመበት የቀጠለውን ዘመን ተሻጋሪ ዘር ተኮር  ድርብርብ፤ አካላዊ፤ ስነልቦናዊ፤ማህበራዊ፤ ሞራሊያዊ ፣ መዋቅራዊ ግፍና ጥቃት በትዕግስት እና በሰላማዊ መንገድ ሲታገል ቆየ።  ይህ ችግር በሰላም መፍትሄ እንዲያገኝ በሚል ለራሱ ለሚጨቁነው መንግስት በየወቅቱ ብሶቱን ሲያቀርብ፤ ሲቻልም ከመንግስት ጋር አብሮ በመስራት በደሉ ይቀር ዘንድ ያላሰለስ ጥረት አድርጓል፡፡የአብይንም መንግስትም ወደስልጣን እንዲመጣና የመንግስት ቁመና እንዲኖረው በመጀመሪያዎቹ አመታት ብሶቱን ውጦ ሲደግፍ የነበረው ከዚህ መንፈስ በተለየ አልነበረም፡፡ 

ይሁንና ትሻል ፈትቼ ትብስ አገባሁ ሆነ እና ነገሩ፤ የአብይ የአሮሞ ብልጽግና መንግስት ለአማራ ህዝብ ብሶት ጥያቄ  ጀሮ መንፈግ ብቻ ሳይሆን የአማራ ህዝብን ለህልውና አደጋ ያጋለጠ ጥቃት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በኦሮም የብልጽግና መሪዎች አመራርና ድጋፍ ጭምር የሚከወን ጥቃት ተባብሶ እንዲቀጥል ሆኗል፡፡ በኦሮሚያ ልዩ ልዪ አካባቢዎች የአማራ ነገድ ተወላጆች ሲጨፈጨፉ የዚህ ተባባሪ የሆኑ የመንግስትና የፓሪቲ መዋቅሮች እንዳሉ፣ በሸገር ዙሪያ በመቶ ሺዎችን የማፈናቀል፣ የአማራ ህዝብ በጅምላ ወደ አዲስ አባባ እንዳይገባ የተደረገበት ሁኔታ ከብዙዎቹ በደሎችና ጥቃቶች ጥቂቶች እንደ  ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።  ይህም ሁኔታ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ህወሃት ትጥቅ ባልፈታበት፣ ኦነግ ሸኔ ወደ አማራ ክልል በመዝለቅ ጭምር ከፍተኛ ውድመትና ጥቃት በሚያደርስበት እውድ፣ በዚህ ሳቢያ የደህነት ስጋትና የህልውና አደጋ ያለበትን የአማራን ዝህብ፣ እንድሁም ፋኖን እና በአጠቃላይ በመላው አገሪቱ የሚገኘውን አማራና አማርኛ ተናጋሪው ዜጋን ለባሰውን የህልውና አደጋ አጋልጠውት አረፉ።   ፋኖና ሌሎች የአማራ ኃይሎችን የህልውና ማስከበር፣ ራስን የመከላከል  ጦርነት ውስጥ አማራጭ አጥተው እንዲገቡ እንዳስገደዱት ሊካድ የሚችል እውነታ አይደለም። በዚህ ሳይወሰን፤ የህወሃት መራሹ ጦርነቱ አውድማና ቀጥትኛ ሰለባ የነበሩትን የአማራውን እና የአፋር ክልል ወገኖችን በማግለል ከህወሃት ጋር የተናጠል ስምምነት የፈጸመው ከሀዲው አብይ አህመድ፤ የስምምነቱን መንፈስ ሳይዛባ አንዳይተገበር ለማደናገር በማስላት፤ “ልዩ ሃይሎችና ኢ-መደበኛ ታጣቂን በትጥቅ የማስፈታት “ የሚል ህጋዊ ሽፋን በመስጠት የጦርነቱን አድማስ አሰፋው።  በአማራ ህዝብ እና የፋኖ ኃይሎች ላይ ያለ አቅሙ “በ15 ቀናት ውስጥ ትጥቁን ብቻ ሳይሆን ሱሪውንም እናሰወልቃለን” በማለት፤ ግልጽ ጦርነት ማወጁ ይታወቃል፡፡ አብይ አህመድ ይህ ጦርነት ያወጀበት ዋነኛ እና ድብቁ ምክንያት እና አጀንዳው ለምን አላማ እንደተፈለገ የሚያስገነዘቡ በቂ መረጃዎች ወጥተዋል። በሂደትም እየወጡም ናቸው፡፡ 

በአማራ ክልል ላይ በከፈቱት ጦርነት አብይ አህመድና ጀኔራሎቹ የመከላከያ ስራዊቱን ለከፍተኛ ኪሳራ እንደዳረጉት፣ በፊት ለፊት ውጊያ እንኳን በብዛት ቆሞ የመዋጋት ሞራል እና  አቅም እንደሌለው የውጭ የመረጃ ድርጅቶት ፣ አሜሪካን ጨምሮ ዝርዝር መረጃዎች ይኖራቸዋል። አሜሪካኖች በእያንዳንዱ ወረዳ ምን እንደሚሆን ዝርዝር መረጃ የሚያገኙበት መረብም እንዳላቸውም ይታወቃል። የመከላከያ ስራዊቱ ቁመና በርካታ ችግሮች የተጋራጠቡት መሆኑም ከእነሱ የሚሰወር አይደለም። በብሄር የተከፋፈለ፣ ለአንድ ስራዊት የሚያስፍለገው ቁልፍ መስፈርት ስፕሬት ዴኮር እጅግ የላላ መሆኑን ያውቁታል። የጠራ አላማ የሌለው፣ አብዛኞቹ አዛዦች የተዘፈቁበት  ዘረፋና ሙስና ጥልቅ መሆኑን  አያጡትም። የስራዊቱ ሞራል እጅግ የተዳከመ እንደሆነ፣ በከፍተኛ ቁጥር እጅ የሚሰጥ፣ ስራዊቱን ጥሎ የሚጠፋ፣ ሙትና ቁስለኛው ቁጥር እጅግ በርክታ እንደሆነ አያጡትም። እነዚህ ሁኔታዎች ደግሞ  የመከላከያ ስራዊቱን በክፍተኛ ደረጃ ማዳከሙን አያውቁትም ማለት የዋህነት ነው። በሰሜኑ ጦርነት በየአውደ ውጊያ በእግሩ አየተጓዘ ያበላውን፣ ያጠጣውን፣ ቁስሉን ያከመውን፣ በየግንባሩ እብሮት ደሙን ያፈሰሰውን፣ መስዋእትነት አብሮ የከፈለውን  የአማራ ህዝብ ላይ እንዲዘመት የተደረገ መሆኑ የሚረዳ፣ በመሆኑም በብዛት እጁን ለፋኖ የሚሰጡ የሰራዊቱ አካላት  (ኮሎኔሎች፣ ሻለቆች፣ መስመራዊ መኮንንኖችን ጨምሮ) እንዳሉ መረጃዎች ይኖራቸዋል። ድሮንን፣ ከባድ መሳራያዎችን በመጠቀም ሰላማዊ ዜጎች በሺዎች ከመጨፍጨፍ  በዘለለ የፋኖን ግስጋሴ በመጠኑም  ቢሆን  ለመግታት  የቻለ ቢሆንም፣ ፋኖ ከመከላከያ ስራዊት በሚያገኘው ሰፊ የመሳሪያና የተተኳሽ  ምርኮ ጉልበቱ እየተጠናከረ በመጣ ቁጥር ይህን የተዛባ ቁመና/Asymmetry፣ መሳ ለመሳ ሊሆን የሚችልበት   ሰፊ እድል ሊያድግ እንደሚችል አሜሪካኖቹ እያጡትም ።  ይህ ማለት ደግሞ የግጭቱን ፣ የውድመቱን፣ የአደጋውንም አድማስ በማስፋት የአገሪቱን ህልውና በከፍተኛ ደረጃ ሊፈታተን፣ አሁን ባለው ውስብብና በህዝብ ውስጥ የሚገኝ ሰፊ ብሄረተኝነት ውድመት፣ የእርስ በእርስ እልቂትና ፍጅት ሊያደግ ሚችልበት እድልም እንዱ ትልቅ ስጋት  እንደሚሆንም ግምገማቸው ሊያሳያቸው ይችላል። 

እንኳን የጦር ምርኮኛ ሆነው ህወሃት በኮታ (ያለበቂ ወታደራዊ ሳይንስ እውቀት፣ የአገልግሎት ዘመን፣ ልምድና፣ አቅም)  እስከ ብልጽግና በአመዛኙ በጅምላ ጄኔራል የተደረጉ  የቀድሞ መንግስት  ባለሌላ ማእረግተኞች የነበሩ  የሚመሩት ጦር፣ በአለማችን ትልልቅ ስም ካላቸው የሚሊታሪ ማሰልጠኛ ኮሌጆች  የተመረቁ  ከፍተኛ የውጊያ ልምድ ያካበቱ፣ ስትራቴጅካዊ ኮማንድ አቅም የነበራቸው ወታደራዊ መኮንኖች የሚመሩ የጦር ሃይሎች ከእነሱ በብዙ ወታደራዊ መለኪያዎች   በጣም ያነሰ አቅም በነበራቸው  ሃይሎች ተሸንፈዋል። ድሮኑ፣ የስለላው ቴክኖሎጂ፣ የላቀ ጦር መሳሪያ፣ ስልጠና፣ ወታደራዊ ሳይንስ ክህሎት አላዳናቸውም።  ከታንክ እስከ ሚሳይልና አውሮፕላን ድረስ የሚገኙ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች እራሳችው አምርተው የታጠቁ የአሜሪካና የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት ወታደሮች ዝቅተኛ ደረጃ ያለው የጦር መሳሪያ በታጠቀ ነገር ግን ከፍተኛ ህዝባዊ መሰረት ባለው ጦር ተሸንፈው ከቪየትናም እና ከአፍጋኒስታን ተባረው ወጥተዋል። ይህንን ጭምር  ስለሚረዱም ይመስላል አሜሪካኖች  ዛሬ ከፋኖ ጋር መዋጋት የማያዋጣ ነው “በጦርነትም  ማንም አያሸንፍም” ብለው የአቢይን አገዛዝ  ለመምከር የተገደዱት። ለነገሩ ከታሪክ ለመማር የማይችሉት፣ የብልጽግና የሲቪልና ወታደራዊ መሪዎች በደርግ ዘመን በኤርትራ ፣ በትግራይ ከነበረው ሁኔታ ብዙ መማር ይችሉ ነበር። ከሌላም ሌላም ተሞክሮ ብዙ ሊማሩ ይችሉ ነበር። እብሪት፣ ንቀት፣ ድንቁርና ሲዳመሩ የሚፈጥሩት የራስን ብቻ የመስማት  ቅዠት፣  ሰፋ አድርጎ፣ አርቆ ለማሰብና  ለማየት የታደሉ እንዳልሆኑ ተደጋጋሚ ሀገራችን የገባችባቸው ዘርፈ ብዙ መከራዎችና ቀውሶች አፍጥጠውና አግጥጠው ይመሰክሩባቸዋል።

የቅዠታሙ አብይ አህመድና የአቅመ ቢስ ጀነራሎቹ ፉከራ ገና ከጅምሩ ውሃ የበላው   በህወሃት ላይ የተገኘውን ወታደራዊ ብልጫ ዳግም በአማራ ክልል ለማግኘት እንደማይቻል አለመረዳታቸው ነው።  የአማራ ህዝብ ድጋፍ ባጣቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ ድጋፍ  ማግኘት እንደማይችሉ ግምት ወስጥ ለማስገባት አለመቻላቸው ፣ የራሳቸውን የማድረግ እቅም ትክክለኛ ግምገማ እንዳላቻሉ ያለፉት 10 ወራት የታዩት በርካታ ኩነቶች ይመስክርባቸዋል።  ትላንትን ዛሬ መድገም እንደማይቻል፣ የትላንቱን ጦርነት ፣ ደግሞ መዋጋት እንደማይቻል፣ ሲሞከርም ለወታደራዊ ክሽፈቶች እንዱ አምድ መሆኑን ለመረዳት አለመቻል(እንድ እውቅ ወታደራዊ ስትራቴጂ  እንደጻፈው)።  እንዲሁም ከስግብግብነት፣ ከመርህ አልባነት፣ ከአጭር ግዜ እይታ፣ ወይንም ራእይ አልባነት፣ የህዝብን እና የሀገርን ደህነነት ከማስቀደም ይልቅ በእብሪት የተወጠረው የአብይ አህመድ የክህደት እርምጃዎች የህዝብን ድጋፍና ልብ እንዳጡ ሃቀኛ ግምገማ ለማድረግ ሳይችሉና ሳይፈልጉ ቀርተው ዛሬ ለሚታየው ሰፊ ሀገራዊ ቀውስና አደጋ ኢትዮጵያንና ህዝቧን ዳርገዋል። 

አሜሪካኖች እና አውሮፓውያን አነዚህን  ሁኔዎች  በቅርብ ይከታተላሉ፣ በቀጠናው ላይ ያላቸውን ስትራቴጂካዊ  ጥቅም የሚመለከትም ስለሆነ በመረጃ አስደግፈው ይገመግማሉ።  እንደ  አብይ አህመድ፣  ካድሬዎቹ፣ ሁሉም ለማለት ባይቻልም እንደ  ብዙዎቹ ጀነራሎቹ በቀን ቅዠት፣ ምናባዊነት፣ የቀቢጸ ተስፋ ላይ የተመሰረተ፣ ከዘረፋና ከሌብነት የሚተርፋቸውን ግዜ “ደመስናቸው፣ አክርካሪያቸውን ሰብረናል” ዘወትር የሚነዙህ የሃስት ፕሮፓጋንዳዎች   ሳይሆን መሬት የረገጠ/Objective የሆነ ግምገማ ላይ የተመሰረቱ ትንተናዎች ያደርጋሉ። እነዚህ ጉዳዮች ሁሉ አሜሪካኖቹም፣ ሆነ አውሮፓውያኑ በሚገባ የሚረዱና ግምገማቸውም ልዩ  ልዩ ወታደራዊና ፓለቲካዊ መረጃዎች ያካተተ ሊሆን እንደሚችል ለመገመት ይቻላል። የአብይ የብልጽግና አገዛዝ፤ የሚወስዳቸው እርምጃዎች፤ በሀገር፣ በህዝብ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲ፣ ሊያስከትሉ የሚችሉትን ስጋቶች (Risks) በአማራጭ ቢሆኖችን (scenarios) የሩቁንም የቅርቡንም ሁኔታ በቅጡ ያልዳሰስ፣ ያልተነተነ፤ በዘፈቀደ እና በምን ግዴና፡ በድንቁርና (ignorance) እና  በአምባገነናዊ እብሪት(Arrogance) መር አሠራር የተመሠረተ፤ ሁሉም ጉዳይ አዋቂ፣  አድራጊና ፈጣሪ ሆኖ ለመቀጠሉ አይነተኛ ዋቢ ነው፡፡ አሰልቺ በሆኑ የአብይ የቀን ቅዠቶች እና ትርክቶች፣ በአብይ አህመድ ተጀምሮ በአብይ አህመድ የሚያልቁ አደናቋሪ ፕሮፖጋንዳዎች  መሬት ላይ ካለው እውነታ በተቃራኒው መሆናቸውን የአብይ አህመድ አጃቢዎችና አድርባዮች ካልሆኑ ቆም ብሎ በጥሞና ማሰብ ለሚችል የሚሰውር ሃቅ አይደለም። አነዚህ ግራ የተጋቡ እና ሲጠሩ አቤት ጌታዬ  ሲላኩ ወዴት ጌታዬ፤ ብለው ከማስፈጸም ውጭ ሌላ የማገናዘብ አቅምም አቋምም በሌላቸው የአብይ ግብረ በላ በሆኑ ጥቂት ሹመኛ የመከላክያ እና የሲቪል ባለስልጣናት ግለሰቦች ፊት አውራሪነት እየተካሄደ ያለው 10 ወራትን ያስቆጠረው እና ተባብሶ የቀጠለው የብልጽግናው አገዛዝ በአማራ ክልል የጀመረው ጦርነት ቀጠናዊ እና አለም አቀፋዊ ስጋት እየሆነ መምጣቱን ያረጋግጣል፡፡ ለዚህም የአሜሪካው አምባሳደር የሰጠው  ይፋዊ መግለጫ እንዱ ትልቁ ማሳያ ነው ብሎ በድፍረት መናገር የሚቻለው፡፡ 

_

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉt.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉBorkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
Ethiopia

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here