spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትአደጋ ላይ የወደቀው ሲኖዶስና ሲኖዶሳዊነት (ለውይይት የቀረበ ጽሑፍ)

አደጋ ላይ የወደቀው ሲኖዶስና ሲኖዶሳዊነት (ለውይይት የቀረበ ጽሑፍ)

መላከ ኤዶም ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ  _ ኤዶም ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ
ቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ


+++++
(ከቀሲስ ኤፍሬም እሸቴ)

ዛሬ “ሲኖዶሳዊነት ምንድነው? ሲኖዶሳዊነት ለምን ያስፈልጋል? በሲኖዶሳዊነት ላይ የተጋረጠው አደጋ ምን ያህል አደገኛ ነው? ካህናትና ምዕመናን ለሲኖዶሳዊነት ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው ለምንድን ነው?” የሚሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ግድ ነው። ጊዜው ነዋ!!!

መነሻ
++++
ቅዱስ ሲኖዶስ “በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ፣ የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ የመጨረሻው ከፍተኛ ሥልጣን ባለቤት” የሆነ፣ “ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን መዋቅር ሁሉ የበላይ አካል” ነው። ከዚህም ባሻገር “ሕጎችን፣ ልዩ ልዩ ደንቦችንና መመሪያዎችን የማውጣትና የዳኝነት ሥልጣን” ያለው አካል መሆኑን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ይደነግጋል። ይሁንና የቤተ ክርስቲያን የበላይ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ እንዲሁም በጠቅላላው በቅ/ሲኖዶስ የበላይነት የመተዳደሩ መንፈሳዊ እሳቤ በዘመናችን ሁነኛ አደጋ ላይ ወድቋል።

መጠነኛ ሐተታ
++++
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እንደማንኛውም በሐዋርያዊ ቅብብሎሽ ውስጥ እንዳሉ አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶሳዊት (Synodal) ቤተ ክርስቲያን ናት። ሲኖዶሳዊነቷ (Synodality) የሚጀምረው የራሷን ሀገር በቀል ጳጳስና ፓትርያርክ ከሾመችበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን ከሐዋርያት ጉባዔ እንዲሁም ቀዳሚ የመንበረ ማርቆስ አባት ከሆነው ከቅ/ማርቆስ ነው፡፡ “እስከንድርያ እናታችን፣ ማርቆስ አባታችን” በሚለው አባባል የቤተ ክርስቲያናችን ሲኖዶሳዊ ማንነት እና ምንነት በአጭሩ ይገለጻል።

በርግጥ ራስን ለመቻልና የራስን ሀገር አጠቃላይ መንፈሳዊና ሐዋርያዊ አገልግሎት ለማከናወን፤ “የሀገሩን ሰርዶ በሀገሩ በሬ” በሚለው ብሒል በተደረገው ጥረት፤ ሀገራችን የራሷ ልጆች ጳጳሳት ሆነው ማገልገል የጀመሩበትን ዘመን የሲኖዶሳችን መጀመሪያ አድርገን ብንናገርም፣ ሐዋርያዊ ቅብብሎሹን በሚያጠይቅ መልኩ ሲኖዶሳዊ ታሪካችንን ከቅ/ማርቆስ ዘመን ብሎም ከሐዋርያት ጉባዔ አለመጀመራችን በሌላ በኩል አሁን ለገባንበት ችግር አስተዋጽዖ አድርጓል።

“ሲኖዶስ የተመሠረተልን በቅርቡ ከሆነና ያለ ሲኖዶስ የኖርንበት ዘመን ለሁለት ሺህ ጥቂት ፈሪ ዓመታት ብቻ ከሆነ፣ አሁንስ ሲኖዶስ ለምን ያስፈልገናል፣ ምን ያደርግልናል፤ ይህንን ሁሉ ችግር ያመጣብን አሁን የመጣብን ይህ ሲኖዶስ ነው” የሚል አስተሳሰብ ሊያመጣ ችሏል።

እውነተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን ያለ ሲኖዶሳዊነት የኖረችበት ዘመን የለም። በዓለም አቀፍ ደረጃ ክርስትና ወንጀል ተደርጎ በሚቆጠርበት በዘመነ ሰማዕታትም ሆነ ክርስትና ሕጋዊ እምነት ሆኖ እንዲኖር በተፈቀደበት ዘመን የክርስትና ሕይወት ከአበው ጉባዔ (ሲኖዶስ) እና ከአበው ትምህርት (ሲኖዶሳዊነት) የተለየበት ጊዜ አልነበረም። ይህ ከሆነ ዘንዳ በጃንደረባው አማካይነት፣ በፊሊጶስ ትምህርትና ጥምቀት ወደ ሀገራችን የገባው የክርስትና እምነት ከሲኖዶሳዊነት የተለየበት ጊዜ የለም ብሎ መናገር ታሪክን ለራስ ትርጉም መለጠጥ አይሆንም።

አባ ፍሬምናጦስ ከሣቴ ብርሃን አክሱምን ከእስክንድርያ ሲያገናኝ እና ጵጵስናን ሲቀበል ሐዋርያዊ ሠንሠለቱ በማይበጠስ ሁኔታ መተሳሰሩን ያሳያል። ሶርያዊ እንደመሆኑ ወደ ሶሪያ ሳይሄድ ወደ እስክንድርያ መሔዱ የአጋጣሚ ጉዳይ ብቻ ሊሆን አይችልም። በመልክዓ ምድር ቅርበት ብቻ ነው ብሎ መውሰድም አይቻልም። እግዚአብሔር ባወቀ የተደረገ ከመሆኑም በላይ በአክሱምና በእስክንድርያ መካከል የቀደመ ግንኙነት መኖሩን መገመት የዋህነት አይሆንም። (በተጨማሪም ሁልጊዜ የሚደንቀኝን የእግዚአብሔር ጥበቃ እዚህ ላይ እንድጠቅሰው ያደርገኛል።)

ሶርያዊው አባ ፍሬምናጦስ ከእስክንድርያ ይልቅ በሥጋ ዘመዶቹ ወደሚሆኑት ሶርያውያን ቢሔድና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንም በሶርያ መንበርና ትውፊት የምትመራ ብትሆን ኖሮ ኋላ በሶርያውያን መካከል የተፈጠረው የምሥራቅና የምዕራብ ሶርያ የእምነት ክፍፍልና ቁርቋሶ ወደ ሀገራችንም ሊገባ ይችል ነበር። በሕንድ ኦርቶዶክስ ያለው ዓይነት ክፍፍልም ይወድቅብን ነበር። ቤተ ክርስቲያናችንም አሁን በምናያት መልክ በተዋሕዶ ጸጋዎቿ በልጽጋ ላናገኛት እንችል ነበር ብዬ አስባለሁ።

አባ ፍሬምናጦስ ከቅ/አትናቴዎስ ክህነትን ብቻ አላመጣም። የእስክንድርያ ሲኖዶሳዊነትም ገንዘባችን ሆኗል:: በዚህም የእስክንድርያ ብቻ ሳይሆን የሐዋርያት አንድነት አካል ሆነናል። ምክንያቱም የአባ ፍሬምናጦስ ክህነት እውነተኛ ክህነት የሆነው ከሐዋርያት ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ በመጣው አማናዊ የክህነት ሥርዓት ውስጥ ያለ ስለሆነ ነው። ያ ክህነት በሲኖዶሳዊነት ማዕቀፍ ውስጥ ያለ ነው። በሐዋርያት ቀኖና፣ በሐዋርያት ሥርዓት፣ በሐዋርያት ትውፊት፣ በሐዋርያት ትምህርት ላይ የጸና ሐዋርያዊ ክህነት በመሆኑ ነው እኛም ልጆቹ በአማናዊቱ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነን ብለን የምናምነው፣ የምንናገረው።

ከዚህ አፈንግጠው የራሳችን ጳጳስ፣ የራሳችን መንበር፣ የራሳችን ቤተ ክህነት ፈጠርን ያሉ ሰዎች ከዚህ ሐዋርያዊ ዛፍ ተገንጥለው የወደቁ የደረቁ ቅርንጫፎች ስለሆኑ ክህነታቸው ፍሬ አያፈራም። ቢቀድሱ፣ ቢያቆርቡ፣ ቢያጠምቁ፣ ክህነት ቢሰጡ ሁሉም ተራ ዕቃዕቃ ጨዋታ ነው::

ሲኖዶሳዊነት ኮሚቴነት አይደለም!!
++++
ኮሚቴ አንድን ተግባር ለመከወን በጊዜያዊነት የሚቋቋም የተግባር ቡድን ነው። ሲኖዶስ ኮሚቴ አይደለም። አስተዳደራዊ ሥራን ቢሠራም እውነቱን ለመናገር አስተዳደራዊ ሥልጣንም አይደለም። የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ዓላማ (ድኅነትን) ለመፈጸም የሚተጋ መንፈሳዊ ተቋም ነው። የቤተ ክርስቲያን ነገረ ሃይማኖታዊ፣ ቀኖናዊ፣ ትውፊታዊ እና ማሕበራዊ ጤንነት የሚጠበቀው በሲኖዶሳዊ ሥርዓት ነው።

የመጀመሪያው የሐዋርያት ሲኖዶስ ከተደረገበት ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚነሡ ሃይማኖታዊ ጦርነቶች (ኑቄዎች) መልስ እያገኙ የመጡት በዓለም አቀፍ ሲኖዶሳዊ ጉባዔዎች ነው። ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚመጡ ችግሮች በጊዜው መፍትሔ ሊበጅላቸው የሚገባው በሲኖዶሳዊ ጉባኤ ነበር:: እውነታው ግን ከዚህ በጣም እየራቀ ነው:: ሲኖዶሳዊነትም ዓይናችን እያየ በመናድ ላይ ይገኛል። ለዚህም ደግሞ ውጪአዊ/ አፍአዊ ምክንያቶች ያሉትን ያህል በራሳቸው በቅ/ሲኖዶስ አባላትም የሚፈጸመው ሐዋርያዊውን ሥርዓተ-ሲኖዶስ የመናዱ እንቅስቃሴ ከባድ ታሪካዊ ወቅት ላይ ደርሷል።

ሲኖዶሳዊነትን የሚገዳደረው ማን ነው?
++++++
ሀ/ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሳዊ ሕይወት ዋነኛ ተግዳሮት ፖለቲካ መሆኑን ካወቅን 50 ዓመት አለፈን። የሀገራችን ፖለቲካ ፓትርያርኳን ገድሎ፣ ጳጳሳቷን አሰድዶና አሥሮ፣ ንብረቷን ዘርፎ፣ ልጆቿን ጨፍጭፎ፣ ታሪኳን ጥላሸት ቀብቶ፣ ሲኖዶሷን ለሁለት ከፍሎ፣ ፓትርያርኳን አሰድዶ መከራ አጽንቶባታል። በዘመናችን ደግሞ አድማሱን እና ኃይሉን በመጨመር ሲኖዶስን በነገድ ደረጃ ለመሸንሸን ቆርጦ የተነሣ ፖለቲካ ገጥሞናል።

ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያት በዘር ሐረግ የሚመራ ፖለቲካ ቤተ ክርስቲያንም የዘር ሐረግን የእምነቷ መሠረት እንድታደርግ ለማስገደድ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ሲኖዶሳዊነትን በመናድና በመከፋፈል በጎችን ያለ እረኛ ለማስቀረት የሚተጋ ሲኖዶሳዊ ሥርዓት የሌለው የቀበሮ ሰብሰብ የሆነ የእምነት ቡድን የፖለቲካ ሥልጣንን እየተጠቀመ መሆኑ ነው።

እንደታሰበውም አገልግሎታችን የዘር ሐረግን የተከተለ በማድረግ ላይ እንገኛለን። ጳጳሳትን ሳይቀር በዘር ሐረግ ለይተን በመሾም ላይ ነን። ምእመኖቻችን የኔ አባት የሚሉት ከራሣቸው ወንዝ የተገኘውን ብቻ ወደ መሆን እየደረስን ነው። የምንደግፈውም የምንቃወመውም ትውልደ ነገዳችንን፣ ሀገር ሙላዳችንን እየተመለከትን ብቻ ነው። ስለዚህም ፖለቲካው ያቀደልን ሁለት ዓላማዎች እየተሣኩለት ነው ብንል ማጋነን አይደለም።

ለ/ ፖለቲካው የፈቀደውን ማድረግ የቻለው ዓላማውን ሊያስፈጽምባቸው የሚችልባቸው አበው ጳጳሳትና ካህናት በመኖራቸው ነው። ሰይጣን በእባብ አድሮ ገነት ገባ። ሰይጣን በአስቆሮቱ ይሁዳ አድሮ ከሐዋርያት ጉባዔ ገባ። ሰይጣን በነአርዮስ፣ ንስጥሮስ፣ መቅዶንዮስ አድሮ ከአበው ሲኖዶስ ገባ። የዘመናችንም ከዚህ የተለየ አይደለም። በራሳችን ሥጋዊ ድካም ሰይጣንን ወደ ጉባዔያችን አስገብተናል። መፍትሔውም ግልጽ ነው። “ሑር እምኔየ ሰይጣን”!!!!!

ሐ/ ከላይ የተዘረዘረውን የፖለቲካውንም የአበውን ድካምም በመረዳት ችግሩን ለመዋጋት የሚደረገው ትግል ደርዝ እና ፈር እየለቀቀ በመምጣቱ ትግሉ ሲኖዶሳዊነትን ወደመቃወም እያደገ ይመስላል። ለቅ/ሲኖዶስ ዓላማ ተጻራሪ ሥራ የሚሠሩ ጳጳሳትን ለመቃወም የሚነገሩ፣ የሚጻፉ፣ የሚደረጉ ተግባራት ጵጵስናንና ጉባዔቸውን (ሲኖዶስን) ጭምር ወደ መገዳደር ማደጉ በራሱ ተጨማሪ ተግዳሮት ይሆናል ብዬ እሰጋለሁ። “ሲኖዶሱ ይህንን የማያደርግ ከሆነ ይህንን አደርጋለሁ” የሚል ክፍል መበራከቱ አንድን ጳጳስ በመቃወም እና ሲኖዶሳዊነትን በመቃወም መካከል ያለው ቀጭን መስመር እንዲጠፋብን አድርጓል።

ምን ይሻላል ጎበዝ?!!!
++++
በዘር ሐረግ ማንነት ላይ የቆመው የዘመኑ የሀገራችን ፖለቲካ ከቤተ ክርስቲያናችን ትምህርት ጋራ የማይታረቅ ቅራኔ ነው ያለው። በምንም መልኩ ብናባብለው ዓላማውን ትቶ አይገራም። የቤተ ክርስቲያን መኖር ለዓላማዬ እንቅፋት ነው ብሎ የወሰነና ለዚህም ላለፉት 60 ዓመታት ተግቶ የሠራ እንደመሆኑ በዘመነ ወያኔም በዘመነ ብልጽግናም ያለው ጸረ ኦርቶዶክሳዊነት ይቀጥላል። መፍትሔው ቤተ ክርስቲያን ዘረኝነት ኢክርስቲያናዊ መሆኑን እንደምታምን ተግቶ ማስተማር፣ ለዚህም የሚፈለገውን ዋጋ መክፈል ብቻ ነው። ዘረኛ ሰው ሃይማኖት የለውም። “አሁን የፕትርክናው ተራ የእኛ ነው” የሚል ሰው ሃይማኖት የሌለው ሰው መሆኑን ማስተማር ነው መፍትሔው።

በተጨማሪም ይህንን በጎሳ (ዘረኝነት) ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ተጠግቶ የመጣውንና ሥልጣን የተቆጣጠረውን ፖለቲካ ለበስ እምነትም ከመቃወም ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም። በአፍም በመጣፍም መታገል ይገባናል። በየዘመናቱ ከዓላውያን ነገሥታት፣ ከግኖስቲኮችና ከሐሳውያን ወንድሞች (መን) ጋራ እንደተደረገው ክርስቲያናዊ ተጋድሎ በዘመናችንም በክርስቲያናዊ ጥብዓት ያንኑ መድገም ይገባናል።

በሌላ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን በመቆርቆር ስም የሲኖዶሳዊነታችን ተግዳሮት በመሆን ላይ ያሉ አካላትን ግን ለጊዜው ሃይ ባይ የተገኘ አይመስልም። ፍፁም ክርስቲያናዊነት በጎደለው መልክ እየተካሄደ ያለው ይህ ስመ-ለቤተ-ክርስቲያን-ጥብቅና መቆም ዞሮ ዞሮ የሚጎዳው ቤተ ክርስቲያናችንን ነው። እግዚአብሔር የማይከብርበት ፍጹም ዓለማዊ ፉክክር፣ ዘለፋ፣ የሰው ኃጢአት የመቆፈር ተራ ተግባር ስለሆነ ምንም ክርስቲያናዊነት የለበትም። ሰዎችን በማዋረድ ላይ ያተኮረ ዓለማዊ ሩጫ ስለሆነ ፍሬ የለውም። ፍሬ አለመኖሩ ብቻ ሳይሆን ሰዎች የቤተ ክርስቲያን የሆነውን ደጉንም ነገር እንዲጠሉ፣ እንዲጠራጠሩ፣ እንዲሸሹ ያደርጋቸዋል።

ቅ/ሲኖዶስ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሆኖ የግንቦት 2016 ዓ.ም ርክበ ካህናት ጉባዔውን ያደርጋል። ፓለቲካውም፣ አጽራረ ኦርቶዶክሱም፣ በዚህ መካከል ሥልጣን አገኝ ብሎ የሚተጋውም፣ የሲኖዶሱ አባል ሆኖ ልቡ ለሌላ ያደረውም ሁሉም የአቅሙን ያህል መፍጨርጨሩ አይቀርም።

የቤተ ክርስቲያን አምላክ ያውቃል!!!!!

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here