spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትአብይ አህመድ   በአማራ ክልል ህዝብ ላይ አመት ሙሉ  ተደጋጋሚ ጦር አዝምቶ...

አብይ አህመድ   በአማራ ክልል ህዝብ ላይ አመት ሙሉ  ተደጋጋሚ ጦር አዝምቶ በድል ማጠናቀቅ ያቃተውን  እውን በአንድ ወር ያሸንፋልን? “የ7ኛው ንጉስ”  አብይ አህመድ  ስራዊትና የፋኖ ሃይሎች  የአማራ ክልል ወታደራዊ ሁኔታ- ሰባት ነጥቦች  

  ነዓምን ዘለቀ _ አብይ አህመድ
ነዓምን ዘለቀ

ነዓምን ዘለቀ 

“በጦርነት የደቀቀ ህዝብ ላይ ሌላ ጦርነት አትክፈቱ፣ አንጀቱ የበገነ፣ የቆረጠን ህዝብ አታሸንፉትም” ገና ከጅምሩ ተው አያዋጣችሁም፣ ተብሎ በብዙዎች ሲነገሯቸው ነበር። ወቅቱን ያላገናዘበ ፣ የአማራን ህዝብ የደህንነት ስጋቶች፣ የህዝቡንም ተደጋጋሚ ጥያቄዎች  ከቁብ ያልቆጠረ፣ “የክልል ልዩ ሃይልን ማፍረስ”  ሽፋን ለድብቅ አጀንዳ ሲባል  ቅዠታሙ አብይ አህመድ በአማራ ህዝብ ላይ የከፈተውን  ጦርነት ማሸነፍ እንዳልቻለ ግልጽ እየሆነ ነው ። እንደሚታወቀው በአለፈው አንድ አመት የአማራ ክልል ምስለኔዎችና የመከላከያ ጀኔራሎች፣ እንዲሁም ብልጽግና ያሰማራቸው ካድሬዎች ሃቁን ለመሸፋፈን ብዙ የሃስት ፕሮፖጋንዳ ሲያስራጩ ከርመዋል፣ “ክልሉን 97% ተቆጣጥረናል፣ ከፋኖ አጽድተናል፣ መለቃቀም ነው የቀረን፣ አከርካሪውን ሰብረነዋል ፣ ወዘተ” በሬ ወለደ ወሬያቸውን ነዝተዋል።  https://www.youtube.com/watch?v=zbknI3CvzP0&t=2s  ።  ሃቆቹ ግን  በተቃራናው መሆናቸውን ከበቂ በላይ  የመረጃ ምንጮች ያረጋግጣሉ። ዛሬ ላይ ደግሞ በሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች ወጣቶች ፣ ተማሪዎች እየታፈሱ በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ወታደራዊ ማስልጠኞዎች እየተላኩ መሆናቸውን በርካታ የመረጃ ምንጭች ዘግበዋል። https://www.youtube.com/watch?v=lFvmPSAORSI

1. ትልቁና ቁልፉ  ጥያቄ፥-የውጊያ  ልምድ የነበረውና ባሩድ ያሸተተው ነባሩ ስራዊት ያልቻለውን በለብ ለብ ስልጠና የሚላክ አዲስ ምልምል ሰራዊት ከፋኖ ጋር ገጥሞ ድል ያመጣልን በሚል ታስቦና ታቅዶ ነው በስርቱ ሺዎች አዲስ ምልምል ወደ ጦር ማስልጠኞዎችና ወደ አማራ ክልል የሚዘምተው? ለዚያውም  በአመዛኙ በአስገዳጅ ሁኔታ የተመለመለ፣ ከፋኖ ሃይሎች ጋር የሚካሄደውን ጦርነት  ውጤት  እንዴት ሊለውጠው ይችላል? ።  መልሱ ግልጽ ነው። በአማራ ክልል ሲደረግ የነበረውን ጦርነት በአብይ አህመድ አሸናፊነት ሊደመደም እይችልም ብሎ በእርግጠኛነት መናገር ይቻላል። ምንም እንኳን የተለያዪ ጊዜያትና አውዶች ቢሆኑም ለማነጻጻር ይረዳል።  በደርግ/ኢሰፓ መንግስት በስተመጨረሻዎቹ አመታት የሆነውን ወደ ኋላ ሄደን እናስታውስ።  የብሄራዊ ውትድርና በሚል አዲስ ፕሮግራም  በግዳጅ መቶ ሺዎችን በማስልጠን አገዛዙ አዲስ ዘመቻ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ግን  በሰሜኑ የሀገራችን ክፍሎች፣ በኤርትራና ትግራይ የነበሩትን የጦርነት ውድቀቶችና  ሽንፈቶችን   ሊቀይራቸው አልቻለም ነበር። በተመሳሳይ የአሁኑም አስገዳጅ  ምልመላ ለአብይ አህመድ ወሳኝ ድል ሊያመጣለት የሚችልበት ሁኔታ ዜሮ ነው ለማለት ይቻላል። 

2 ለምን ? ጦርነቱ መነሻ የፓለቲካዊና የደህንነት  ችግሮችና ስጋቶች ናቸው።  የአማራ ህዝብ እነዚህን ጥያቄዎች  በሰላማዊ መንገዶች ሲጠይቃቸው  የነበሩ ናቸው።  የፋኖ ሃይሎች ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኙትም እነዚህ የአማራ ህዝብ የህልው ጥያቄ  እንዲሁም ከወልቃይትና ራያ ጋር በተያያዘና በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት ህወሃት ትጥቅ አለመፍታት፣ በአማራ ህዝብ ላይ የደረሱ ተደጋጋሚ  ጭፍጨፋዎች፣ መፈናቀሎች፣ ሌሎችም  የደህንነት ስጋቶች በህዝብ ልብ ውስጥ የሚንቀለቀሉ እሳት ጉዳዮች በመሆናቸው ነው። እነዚህ ሰፊ ድጋፍ ያላቸውን የህዝብ ስጋቶችና ጥያቄዎችን ደግሞ  በወታደራዊ ሃይል ለመጨፍለቅ እንደማይቻል፣ አብይ አህመድና አቅመ ቢስ ጀነራሎቹ  እስከአሁን ሊረዱት እንዳልቻሉ ፣ ወይንም እንዳልፈለጉ ግልጽ ነው። እብይ እህመድና ግብረ አበሮቹ አሁናዊ ሁኔታዎችን በአግባቡና ሀቀኛ ሆኖ ለመገምገም የሚችሉ እንዳልሆኑ  በርክታ አገሪቱ የምትገኝባቸው ተደራራቢ ችግሮችና ቀውሶች ይመሰክሩባቸዋል።  ከታሪክም የመማር ፍላጎትና ፣ የአምሮ ክፍትነት ያላቸው ባለመሆኑ፣ በስህተት ላይ ስህተት በውድቀት ላይ ውድቀት እየከመሩ ውድቀታቸውን እያፋጠኑት ነው። 

3. በደረግ/ኢሰፓ መንግስት ዘመን የነበሩት ጀነራል መኮንኖች አብዛኞቹ (በደርግ አባልነታቸው ከአስር አለቃ፣ አምሳ እለቃ ማዕረግ ፣ በአንድ ጀምበር የጀነራልነት መኮንን የተደረጉትን በጣም ጥቂቶች ሳንጨምር) በአለም ወታደራዊ አካዳሚዎች የተማሩ፣ ወታደራዊ ሳይንሱ ፣አቅሙ፣ ብቃቱ፣ ወኔው፣ ቆፍጣነቱ፣ ዲሲፕሊኑ  የነበራቸው ምርጥ ጀኔራል መኮንኖች ኢትዮጵያ  እንደነበሩዋት ብዙ ተመዝግብአል፣ ተንግሮአል። ነገር ግን  በትግራይና በኤርትራ የነበረውን የህዝብ አመጽ በወታደራዊ ሀይል ማሸነፍ ያልቻሉበት ሁኔታ እንደነበር ግልጽ ነው። ዋናኛ  ምክንያቶች  ደግሞ ተፋላሚ ሃይሎች ህዝብ ውስጥ ስለነበሩ፣ ሰፊ ህዝባዊ ድጋፍ ስለነበራቸው፣ የውጊያ ስልቶቻቸው ለመደበኛ ሰራዊት በጣም አስቸጋሪ ስለነበርና፣ ሌሎችም የመልክአ ምድር አቀማመጥ/ቶፖግራፊ፣ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ጂኦፓለቲካዊ ምክንያቶች ሊቀርቡ ቢችሉም። ቁንጫዎች ዝሆኑን ወይንም አንበሳውን ከመቶ አቅጣጫ የመተግተግ/(War of the Flea)  ስልቶች ለማንኛውም መንግስት ፣ ለሃያላኑ ሀገራት ጭምር እጅግ አዳጋችና የመደበኛ ሰራዊትን ሞርል ገዝግዘው የሚያፍረከርኩ መሆናቸውን በርካታ ታሪኮች ያረጋግጣሉ።  አሜሪካ በቬትናም፣ በአፍጋኒስታ፣ የቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት በአፍጋንስታን የደረሰባችውን ውርደትና ውድቀት ያጢንኡአል።  

የዛሬዎቹ የአብይ አህመድ ጀኔራሎች አብዛኞቹ፣ የቀድሞቹ ጀኔራሎች፥ አጃቢዎች፣ መኪና አሽከርካሪዎች፣ አንጋቾችና ፣ የባለሌላ ማእረግተኖች ፣ እንዳንዶቹ  መስመራዊ  መኮንንኖች ሆነው በቀደምቶቹ ስር ያገለገሉ ነበሩ። በህወሃትና ሻቢያ ተማርከው በብሄር ኮታ ጀነራልነት ማእረግ የታደላቸው፣ ነገር ግን በወታደራዊ ሳይንስ፣ በአቅም፣ በክህሎትና፣ በልምድ አሁንም በጣም የወረደ ደረጃ ላይ የሚገኙ ስለመሆኖቸው ብዙ ዝርዝር መረጃዎች በየግዜው ወጥተዋል። ስለዚህ እነዚህ  ምንም አይነት ለውጥ በአማራ ክልል ጦርነት ላይ ማምጣት እንደማይችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው።  

4 አሁን ላይ ለምን ይህ አስገዳጅ አዲስና ሰፊ ሀገራዊ ምልመላ አስፈለገ? ምክነያቱ ግልጽና ብዙ ዝርዝር መረጃዎች የወጡበት ነው። የአማራ ክልል ለአብይ አህመድ ሰራዊት ረመጥ ሆኖ ቆይቷል፣ እነሱ ያቀዱትና መሬት ላይ ያለው እውነታ ሰማይና ምድር ነው።  በተለያዪ ጊዜያት የመጨረሻ ዙር ዘመቻ አቅድው ቢያንስ 10 ዙር ዘመቻዎች ከሽፈዋል፣ 7 ቀን፣ 15 ቀን የግዜ ገድብ ለፋኖዎች ስጥተናል የሚሉ አዋጆችና መግለጫዎች እየሰጡ በነበሩበት ሁኔታ አብይ አህመድ ወደ ክልሉ ያሰማራው ስራዊት ላይ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል ። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ለጋ ወጣት የመከላከያ ሰራዊቱ አባላት ሙት ሆነዋል፣ በአስርቱ ሺ የሚቆጠሩ የመከላከያ ስራዊት አባላት በፋኖ ተማርከዋል።  በሺዎች የሚቆጠሩ ቁስለኛ ሆነዋል። ቁጥሩ ለማወቅ የሚያስቸግር እጅግ ብዙ ቁጥር ያለው  የመከላከያ ስራዊቱ አባላት ምድባቸውን ጥለው ጠፍተዋል/ከድተዋል። ሬጅመንቶች ፣ ክፍለ ጦሮች ሙሉ በሙሉ የተደመሰሱበት ፣ የተበተኑበት እውደ ውጊያዎች በርክታዎች ናቸው።   ከመላው ኢትዮጵያ፣ ከልዩ ልዩ እዞች (ከምስራቅ፣ ከደቡብ፣ ከማእከላዊ) አብይ አህመድ በየግዜው ወደ አማራራ ክልል ያዘመተው ስራዊት ተምናምኗል፣ ተሸርሽሯል፣ ተበትኗል። ከፋኖ ጋር በተደረጉ ውጊያዎች  እጅግ ከባድ ኪሳራ ደርሶበታል። ይህን ሀቅ በርካታ የመረጃ ምንጮች ዘግበዋል።

5. ከፍተኛ የሆነ ቁጥር በውጊያ፣ በምርኮ፣ በመጥፋት/በመክዳት  የተመናመነው ስራዊት አሁናዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ ፣ የግዳጅ ምልመላ ብቸኛው አማራጭ ሆኖ የታየበትም ዋነኛ ምክነያት ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። አማራ ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ክልሎች፣ ዩኒቨስቲዎችን ጨምሮ የምልመላ ዘመቻዎች እየተካሄዱ ናቸው። የዛሬውን ምልመላ  ደግሞ የባሰ የሚያደርገው፣ የዘመኑ ወጣት የአማራን ህዝብ ለምን እንደሚወጋ፣ ለማን እንደሚያዋጋ አያውቅም።  በአብይ አገዛዝ ያሰማራው ሰራዊት ድንበር ከመጠበቅ ይልቅ ህዝብን እንዲወጋ ተልእኮ የተሰጠው አንዱ መሰረታዊው ችግር  ፣ የጠራ አላማ የለውም ።  ሊኖረውም አይችልም።  በየጊዜው ለስራዊቱ በአዛዦቹ የሚነገሩት/የሚሰጡት የተምታቱ ተልእኮዎች እንደነበሩ የተማረኩ የመከላከያ ስራዊት አባላት በልዩ ልዩ አካባቢዎች ለፋኖ ሃይሎች ላቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ገልጸዋል።

6 የመከላከያ ስራዊቱ የመዋጋት ሞራል እጅግ የተመናመነ ነው። በአብዛኛው ውጊያ አውዶች የመከላከያ ስራዊቱ ከ 15 እስከ 30 ደቂቃ በኋላ ተዋግቶ እንደሚሸሽ፣ እጅ እንደሚሰጥ ከልዩ ልዩ  አካባቢዎች የፋኖ መሪዎችና ፣ ቃል አቃባዮች ተናግረዋል። ከባድ መሳሪያዎችን በብዛት መጠቀም ባይችል ኖሬ ስራዊቱ ከእነአካቴው ባዶ ሊቀር የሚችልበት እድል ከፍተኛ ነው። የአብይ አገዛዝ የተማመነባቸው ሌሎቹ ሃይሎች ለምሳሌ አድማ ብተና እና  ሚሊሺያ በብዛትና በልዩ ልዩ  የክልሉ አካባቢዎች እጃቸውን ለፋኖ ስጥተዋል። በፋኖ ሃይሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የሰራዊቱ አባላት ፣ ከፍተኛና መስመራዊ መኮንኖች በፋኖ ሃይሎች ተማርከዋል። የሪፓብሊካን ጋርድ፣ የኮማንዶ አባላት ተማርከዋል፣ ሙትና ቁስለኛ ሆነዋል። በርካቶች ፋኖን ተቀላቅለዋል። መከላከያ ስራዊቱ በሺ የሚቆጠሩ ከባድና ቀላል መሳሪያዎች ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተተኳሶች፣ በአስርቱ ሺዎች የሚቆጠሩ የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች (ኤኬ 47) ፣ ስናይፐሮች በፋኖ እጅ ወድቀዋል። የፋኖ ሃይሎች ሞራል ከፍተኛ መሆኑ፣ ሞራል፣ ዲሲፕሊን ጠንካራ መሆን  በየግዜው የወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ። 

የፋኖ አደረጃጀትና አቋም ፣ ከጋንታና ሻለቃ ወደ ብርጌድ፣ ክፍለ ጦሮች፣ እዞች አድጓል፣ ከአብይ አገዛዝ ስራዊት ከባድ መሳሪያዎች በብዛት ማርኳል፣ ዙ 23, ዲሽቃ፣ ብሬን፣ ሞርታሮች ፣መድፎች፣  በብዛት በምርኮ መታጠቁን በልዩ ልዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች ያረጋግጣሉ፡ ከድሮን በስተቀር የፋኖ ሃይሎች ሙሉ በሙሉ  በሚባል ደረጃ ከባድ መሳሪዎች በምርኮ ለመታጠቅ ችለዋል።  ለዚህም ነው ፌልድ ማርሻሉን “አስታጥቄ’ በሚል ስላቅ የሚጠሩት።  በአጭሩ በአለፈው አንድ አመት የተደረገው ጦርነት የፋኖ ሃይሎችን ያሳደገና ያደራጀ በተቃራኒው ደግሞ በመክላከያ ሰራዊቱ ላይ ከባድ ኪሳራ አድርሶ፣ ስራዊቱን በእጅጉ  ያመናመነ፣ የስራዊቱን ሞራል ይብሱኑ የገደለው  ሂደት ነበር ለማለት ይቻላል። 

7 የአብይ አገዛዝ ስራዊት በሸዋ፣ በጎጃም፣ በጎንደር፣ በወሎ ፣ በልዪ ልዩ አካባቢዎች በፈጸማቸው የድሮን ጥቃቶች፣ በከባድ መስሪያ በደቦ በሚያርሱ ገበሬዎች ላይ፣ በት/ቤቶች፣ በጤና ጣቢያዎች፣ በንጽሃን ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች፣ በስራዊቱ አባላት ሽንፈት ሲደርስባቸው በሲቪል ዜጎች ላይ በሚደረጉ ጭፍጨፋዎች፣ ሴቶችና ህጻናትን አስገድዶ መድፈር ሳቢያ በአስር ሺ የሚቆጠሩ ወጣቶ የፋኖ ሃይሎች በገፍ ተቀላቅለዋል። በ 15 ቀን እንጨርስዋለን፣ “ፋኖን ትጥቁንም ሱሪውንም  እናስፈታለን” በሚል እብሪትና ትዕቢት አብይ አህመድና ብርሃኑ ጁላ የጀመሩት ጦርነት አንድ አመት ሞላው። ድል የራቀው ቅዠታሙና አረመኔው የበሻሻ ደላላ ሰፊ አስገዳጅ ምልመላ በማድረግ፣ በለብ ለብ ስልጠና የጦርነቱን ይዘት ለመለወጥና በድል አድራጊነት ለመውጣት  መሞከር ጉም መዝገን ማለት  ነው። የአብይ አህመድ የብልጽግናው መንግስት በውድቀት ላይ ውድቀት፣ በክሽፈት ላይ ክሽፈት፣ በእልቂት ላይ እልቂት፣ በውድመት ላይ ውድመት እየከመረ ወደ አይቀረው ውድቀቱና ውርድቱ እየተጓዘ ያለበት ሂደት ነው ለማለት ይቻላል።

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here