spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትፖለቲካ ሐይማኖት አይደለም (አሰፋ አበበ)

ፖለቲካ ሐይማኖት አይደለም (አሰፋ አበበ)

ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሃይማኖት
ከሌላ ጦማር ገጽ ላይ የተወሰደ

አሰፋ አበበ 

1. መግቢያ

ፖለቲካና ሐይማኖት አፈጣጠራቸውም፥ ዓላማቸውም፥ አሠራራቸውም ወይም አፈጻጸማቸውም የተለያየ ነው:: ሆኖም አንዱ በአንዱ ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል:: ለምሳሌ በአንዳንድ አገሮች የፖለቲካው ወይም የመንግስት አሰራር ከሐይማኖታዊ አስተምሮት ጋር ተጣጥሞ እንዲካሄድ ይደረጋል:: ለምሳሌ ሳዑዲ አረቢያንና ኢራንን እንድሁም ሌሎች የሙስሊም አገሮችን መመልከት ይቻላል:: ሐይማኖተኛው የሻሪያ ሕግ ተፈጻሚ እንዲሆን የመንግስት መዋቅርን መጠቀም ይፈልጋል:: ፖለቲከኛው ደግሞ በሐይማኖት ተቋማት አሰራር ላይ ተጽዕኖ በማሳረፍና የሐይማኖት አባቶችን ድጋፍ  በማግኘት ሕጉ፥ ደንቡና መመሪያው ተፈጻሚ እንዲሆለት ይፈልጋል:: እነዝህ ፍላጎቶች ፖለቲካውንና ሐይማኖቱን ቢያቀራርቡም አንድ ሊያደርጉ ግን አይችሉም:: ምክንያቱም ፖለቲካ የተፈጠረው ለምድራዊ (ከሞት በፊት) ላለው ሕይወት ሲሆን ሐይማኖት ደግሞ የተፈጠረው በዋነኛነት ለሰማያዊ (ከሞት ብኋላ ላለው) ሕይወት ነው:: በአሰራራቸውም ፖለቲካ እንደሁኔታው መተጣጠፍን (flexibility) የሚፈልግ ሲሆን ሐይማኖት ግን ቀኖናው(dogma)  እንዲጠበቅ ይፈልጋል :: በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 11 መሠረት መንግሥት (ፖለቲካ) እና ሐይማኖት የተለያዩ ናቸው:: አንዱ በአንዱ ጣልቃ እንዳይገባም ተካልክሏል::

ፖለቲካና ሐይማኖትን የሚያመሳስላቸው ደግሞ የፖለቲካ ደጋፊው በሚደግፈው መሪው: የሐይማኖት ተከታዩ ደግሞ በሚያመልከው አምላኩ ላይ የሚጥለው እምነት ነው:: ለምሳሌ እ.አ.አ. በኣፕሪል 2018 ዶ/ር አቢይ አህመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ አገሩንና ሕዝቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ይወስዳሉ በማለት የተለያዩ ቡድኖች የጣሉባቸው እምነትና ተስፋ ከፍተኛ ነበር:: ከመጽሐፍ ቅዱሱ ሙሴ ጋርም ያመሳሰሉአቸው ነበሩ:: በሐይማኖታዊው መንገድ ደግሞ የታመነው አምላክ ወደ ገነት እንደሚያስገባ የሚታመንና ተስፋ የሚደረግ ሲሆን  የእምነት ውጤት ግን እንደፖለቲካው ቶሎ ላይታይ ይችላል:: ስለሆነም አብዘኞቻችን እስከ ዕለተ ሞታችን  ድረስ በእምነታችንና ተስፋችን ጸንተን እንቆያለን:: የፖለቲካ እምነታችንን ውጤት ግን ቶሎ በአመትና ሁለት ዓመት እናያለን:: በመሆኑም ያመነው ሳይሆን ሲቀር፥ ተስፋ ያደረግነው ሳይፈጸም ሲቀር ከደጋፊነት ወደ ተቃዋሚነት ልንቀየር እንችላለን:: በመሆኑም በፖለቲካ ከደጋፊነት ወደ ተቃዋሚነት ወይም ከተቃዋሚነት ወደ ደጋፊነት መቀየር እንደ አሳፋሪ ድርጊት መታየት የለበትም:: ለምንወስደው የፖለቲካ አቋም መሰረት መሆን የሚገባው ያለው ተጨባጭ ሁኔታ: በሕይወት እያለን ማየት የምንፈልገው ውጤት እንጂ ይሉኝታ ወይም የማይጨበጥ ተስፋ መሆን የለበትም::

2. የፖለቲከኞች እንደ ሁኔታው መተጣጠፍ (Flexibility) የተለመደ ነው::

አቋምን ማስተካከል ወይም መለወጥ ወይም መተጣጠፍ በፖለቲካው የተለመደና አንዳንዴም እንደ የጥሩ መሪነት ችሎታ እንጂ እንደ ደካማነት ወይም አቋም የሌሽነት አይታይም:: አካሄዳቸውን ከሁኔታዎች ጋር እያስማሙ የሚሄዱና ዕቅዳቸውን ከሚፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች ጋር እያጣጣሙ የሚሄዱ መሪዎች በብዛት ስኬታማ መሪዎች ናቸው ይባላል:: የአዋቂዎችን ምክር ሰምቶ ወይም ያለውን ሁኔታ ገምግሞ በቀደመው አካሄድና ባሕሪ ልፈታ ያልተቻለውን ችግር በአዲስ አካሄድና ባሕሪ ለመፍታት መታጠፍ ጥንካሬ አንጂ ድክመት አይደለም:: “መካር የሌለው ንጉስ አለአንድ አመት አይነግስ” የሚለው የአማርኛ ብሂልም ይህንኑ ምክር ሰምቶ ተጨባጭ ሁኔታን አገናዝቦ አካሄድ የማስተካከልን አስፈላጊነት የሚገልጽ ነው:: የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ሜይ 30, 2024 በኬኒያ ብሔራዊ የጸሎት ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው “አሁን የኢትዮጵያ መሪ ቢሆን ኖሮ የሚሰራውን ሥራ ከድሮው በተለየ መንገድ እሰራ ነበር” ብለው  የተናገሩት ንግግር እንደ ሁኔታው  የአስተሳሰብና የአካሄድ ለውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያሳይ ነው:: እውቁ ሳይንትስት አልበርት አነስታይን እንዳለው “ተመሳሳይ ድርጊትን ደጋግሞ በማድረግ የተለየ ውጤት መጠበቅ እብደት ነው”:: ስለዝህ  ነገሮች እንደተፈለጉት አልሄድ ስሉ አስተሳሰብንም አካሄድንም ለውጦ መሞከሩ ተገቢ ይሆናል:: 

በኢትዮጵያ ፖለቲካ መተጣጠፍ የተለመደ ነው:: ደርግ  ከሶሻሊዝም ወደ ቅይጥ ኢኮኖሚ ታጥፏል፥ ኢሐዴግም ከሶሻሊዝም ወደ ልማታዊ መንግሥት ከዝያም ወደ ካፒታሊዝም ታጥፏል:: መተጣጠፍ ባይኖር ኖሮ ፕሬዝዳንት መንግሥቱ  ኃይለማሪያም አንድ ጥይትና አንድ ሰው አስኪቀር ወያኔንና ሻዕቢያን እዋጋለሁ ብሎ ስፎክር የነበረውን ትቶ  መንግሥትና አገር ጥሎ ወደ ዝምባቢዌ አይፈረጥጥም ነበር፥ ጠቅላይ ሚኒስትር  ኃይለማሪያም ደሳለኝ የኦሮሞ ቄሮን አመጽ በኃይል አቆማለሁ ብሎ መፎከሩን ትቶ በቃ ሥልጣን እለቅላችኋለሁ ብሎ ሥልጣን አይለቅም ነበር፥ ወያኔና ብልጽግና ፓርቲ ያን ሁሉ ፉከራ ትተው ፕሪቶሪያ ሄደው አይታረቁም፥ ናይሮቢ ሄደው አይተቃቀፉም፤ አዲስ አበባ ላይ አይሸላለሙም ነበር:: እስክንድር ነጋም  የሰላማዊ ትግል አቋሙን ለውጦ መንግስትን በጠመንጃ ኃይል አስገድዶ ለመለወጥ ወደ ትጥቅ ትግል አይገባም ነበር::

አንዳንድ ሰዎች ‘ዶ/ር አቢይ ከዝህ ቀደም ወለጋ ከሄድኩ ይገሉኛል ብለው ነበር፤ ታዲያ በሚያዝያ ወር 2016 ለምን ወለጋ ሄዱ? ቀደም ሲል ሲያደርጉት የነበረውን የማስፈራሪያ ንግግርስ ቀይረው ለእርቅ የሚጋብዝና የለሰለሰ ንግግር  ለምን አደረጉ’ ብለው ለመተቸት ይሞክራሉ::የአቢይ አህመድን ማዕከላዊ  መልዕክት ለማግኘት ስዝት በቀጥታ በጎ ነገር ወይም የተለሳለሰ ነገር ስናገር ግን ግልብጦ በመስማት ተቀራኒውን ለማድረግ የተዘጋጀ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል ብለው ጥሪውን በአሉታዊ መልኩ ይመለከታሉ:: ይህም ካለመተማመን የመንጨ ነው:: እነዝህ ሰዎች የሁኔታዎች መለወጥና ጊዜ የውሳኔና የአካሄድ ለውጥን ሊያስከትል እንደሚችሉ ይረሳሉ:: ዶ/ሩ ነቀምቴ የሄዱት ቀደም ስል ልገለኝ ይችላል ብለው የጠረጠሩት ኃይል ልገላቸው እንደማይችል በማረጋገጣቸው ሊሆን ይችላል:: ይህም ወይ ያ ኃይል ተዳክሞ ስጋት በማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል ወይ  ደግሞ የእርሳቸው ኃይል ተጠናክሮ ስጋቱ እንዳይኖር በሚያደርግበት ደረጃ ላይ ደርሷል ማለት ነው:: በመሆኑም ዶ/ር አቢይ አንደ ከአፋቸው ለወጣው ቃል ተገዥ ሁነው ይኑሩ የሚለው መከርራከሪያ ሊያስከድ አይችልም:: ግፋ ብል ከእርሳቸው የሚጠበቀው ቀደም ስል የያዙትን አቋም ወይም ቃል ለምን እንደለወጡ ማብራራት ይሆናል::

አቶ ጀዋር መሃመድም በበኩሉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ታሪክና ማንነት የላቸውም ከሚለው አቋሙ ወደ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የጋራ ታሪክ አላቸው፥ ኢትዮጵያ በስብሳለች መፍረሷ አይቀርም መጠንቀቅ ያለብን ስትፈርስ እኛ ላይ ወድቃ እንዳትጎዳን ነው  ከሚለው አቋሙ ኢትዮጵያ የቀነጨረች አገር ስለሆነች በቀላሉ አትፈርስም ወደሚለው ዞሯል:: ይህንን የአቶ ጃዋር መሃመድን መተጣጠፍ ወይም መገለባበጥ አስመክተው ዶ/ር ዮናስ ብሩ ስጽፉ እንዲህ ይላሉ “ፖለቲካ ተለዋዋጭ ነው:: የፖለቲካ ሁኔታ ስለወጥ ፖለቲከኛው እንድለወጥ ያስገደዳል:: የሰው ልጆች ለመኖር ከተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር ራሳቸውን ያስማማሉ:: ጀዋርም ያደረገው ይህንኑ ነው”:: 

በአጭሩ የሰው አስተሳሰብ ይለወጣል፥ አዲስ መረጃ ባገኘና ግንዛበው በተለወጠ ቁጥር ደግሞ የፖለቲካ አቋሙን ወይም አካሄዱን መለወጥ ይችላል:: ይህንን የኦነግ መሪ የነበሩት አቶ ገላሳ ድልቦ: አቶ ሌንጮ ለታ፥ ዶ/ር ዲማ ነገዎና ሌሎች ስያደርጉት አይተናልና:: አቶ አንዳርጋቸው ጽጌና ሌሎች ብዙ ፖለቲከኞችም አድርገውታል:: በመሆኑም ግለሰቦች የፖለቲካ አቋማቸውን በመለወጣቸው ሊተቹ ይችላሉ ግን ሊወገዙና ሊዋከቡ አይገባም::

3. በፖለቲካ አንድ ቦታ ተቸክሎ መቅረት ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል

የፖለቲካ ገበያ ልክ እንደኢኮኖሚው ገበያ ትርፍና ኪሣራን በማመዛዘን የሚነገድበት ገበያ ነው:: በዝህ አሰራር ባወጣው ይውጣ እንጂ የጠየኩትን ሳላገኝ ከተቸከልኩበት አልነቃነቅም ያሉት የሚከስሩ ሲሆን ፍላጎትና አቅርቦትን አይተው ጥያቄያቸውን የሚያሻሽሉ፥ የኃይል ሚዛኑን አይተው አሰላለፋቸውን የሚያስተካክሉ፥ እንደተጨባጭ ሁኔታው ሚዛን ጠብቀው የሚጓዙ በገበያው ያተርፋሉ:: ይህንን ያላደረጉ ግን ኪሣራ ይገጥማቸዋል::

ለምሳሌ፥ሕወሐት መራሹ የትግራይ ኃይሎች  የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥትን ለሁለት ዓመት (ከኖቨምቤር 2020- ኖቨምቤር 2022 ) ከተዋጉ በኋላ የኃይል ሚዛኑንና አሰላለፉን በመገምገም ሸብረክ በማለትና የማሪያም መንገድ (graceful exit) የሆነውን የፕሪቶሪያ ስምምነት በመጠቀም በኢትዮጵያ የፖለቲካ ገበያ የሚፈልጉትን ለማግኘት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ:: እስከ አሁን ድረስም በትግራይ ጦርነት እንዲቆም፤ የተቋረጡ የመብራት፤ የስልክና የኢንተርኔት አገልግሎቶች መልሰሰው ሥራ እንዲጀምሩ፥ ትግራይን በጦርነት ለማንበርከክ ገንዘብና የሰው ኃይል ስያዋጡ የነበሩ ክልሎችና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለትግራይ ግንባታ ከበጀታቸው ቀንሰው እንዲሰጡአቸው በማድረግ፥ የታሰሩ የትግራይ ተወላጆች እንዲፈቱ፥ ከመንግሥት ሥራ የተባረሩም ወደየሥራቸው እንዲመለሱ ማድረግ ችለዋል:: በኃይል ተይዞብናል የሚሉትን የትግራይ መሬቶችንም የፌዴራሉ መንግሥት አስመልሶ እንዲያስረክባቸውና በሽብርተኝነት ተፈርጆ ሕጋዊ ሰውነቱ የተገፈፈው ሕወሐት ሕጋዊነቱ እንዲመለስለት በመጠየቅ ላይም ይገኛሉ:: በዝህ አካሄዳቸውም እስከ አሁን አትራፊዎች ናቸው:: ‘ቆጥሮ መልሶ የመረከቡ’ የሕወሐት ስትራቴጂ እስከ አሁን ውጤታማ ነው::

በፖለቲካ ገበያው የቡድን ንግድ ሌላው መጠቀስ ያለበት አዋቂ ነጋዴ የጉራጌ ማህበረሰብ ነው:: የጉራጌ ፖለቲከኞች አፕሪል 20, 2024 ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ  ወልቂጤ ላይ ትልቅ የድጋፍ ሰልፍ አዘጋጅተው “ዶ/ር አቢይ የተምቢ”: “ልጃችን” እያሉ የተቀበሉትና አምና ወደ ወልቂጤ በመጡበት ጊዜ ተገቢውን አቀባበል ስላላደረግንልዎ ይቅርታ ይደረግልን ብለው ይቅርታ የጠየቁት አካሄዳቸውን አሳምረው በፖለቲካው ገበያ ትርፍ ለማግኘት እንጂ ፖለቲካ ባለማወቃቸው አይደለም:: የጉራጌ ተወካይ ተብለው የቀረቡት  ሰው “አምና ወደ ወልቂጤ በመጡበት ጊዜ ተገቢውን አቀባበል ስላልተደረግልዎ መላው የጉራጌ ማህበረሰብ አዝኗል፥ ቆስሏል፥ ተምሮበታል” ያሉት እውነት ሊሆንም ላይሆንም ይችላል:: ነገር ግን የሥልጣን: የውሳኔ ሰጪነትና የበጀት ምደባ ማዕከል የት እንደሆነ አውቀው እርስዎ ከሚያሰሩት እንደጎርጎራ፥ ሃላላ ኬላ፥ ወንጪ፥ አድዋ ዜሮ ዜሮ፥ የአንድነት ፓርክና የጫካ ፕሮጄክቶች እኛም አንድ ቀን ተቋዳሽ እንሆናለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን ብለው መጠየቃቸው ለተወካዩ ከፍተኛ ጭብጨባ ማስገኘት ብቻ ሳሆን ፖለቲካ አውቂነታቸውንም አስመስክሯል::

በተቀራኒው በፖለቲካ ገበያው ያልተሳካላቸው ከብልጽግና ውጪ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ናቸው:: ከብጽግና ውጭ ያሉ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ወይ እንደ ትግራይ ፖለቲከኞች ሸብረክ ብለውና የማሪያም መንገድ ፈልገው ራሳቸውን ከእስራትና ከመታደን፤ ሕዝባቸውን ከመቀጥቀጥና ከመከራ አላዳኑም ወይ ደግሞ እንደ ጉራጌ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩን “ልጃችን” ብለው አባብለው ሰላምና ልማት ማግኘት አልቻሉም:: አንድ ቦታ ተቸክለው ከማማረርና አንድ ቀን መብታችንን በኃይል እናስከብራለን ብለው ከመፎከር ውጭ የራሳቸውንም፤ የጠቅላይ ሚስትሩንም አካሄድ መለወጥ ባለመቻላቸው የኦሮሞ ሕዝብ ለመከራ ተዳርጓል:: የኦሮሞ ሕዝብም በተለይ የወለጋው “እህል የሚደርሰው በፍልሰታ: እኔ የሚሞተው ዛሬ ማታ” የሚለውን  ተረት እየተረተ ላያስችል አይሰጥ ብሎ መከራውን ሁሉ ተሸክሞ እንዲኖር ተፈርዶበታል::

በራሱ ተነሳሽነት የኦሮሞን ሕዝብ እስራት፥ ግርፋት፥ እርዛት፥ረሀብ፥ግድያና መከራ መቀነስ ወይም ማስወገድ ያልቻለው ከብልጽግና ውጪ ያለው የኦሮሞ ፖለቲከኛና ኤሊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሚያዝያ 30, 2016 ነቀምቴ ላይ ባደረጉት ንግግር ያቀረቡትን ሐሳብ (offer) መርምሮ ከመቀበል ወይም አማራጭ ሐሳብ (counter offer) ከማቅረብ ይልቅ በደፈናው ሐሳቡን በማጣጣል በፖለቲካው ገበያ ከሣሪነቱን ይዞ ተኮፍሶ በመቀመጥ የሕዝቡ መከራ እንዲቀጥል አስተዋጾኦ እያደረገ ነው::

ከብልጽግና ፓርቲ ወጪ ያሉ የአማራ ፖለቲከኞችና ኤሊቶችም በፖለቲካው ገበያ ያላቸው ሚና የኦሮሞ ፖለቲከኞችና ኤሊቶች ካላቸው ሚና ጋር ተመሳሳይ ነው:: የመንግሥትን ሥልጣን የያዙት እነርሱ እንዳሰቡት እፍ ብሉ የሚጠፉ አረፋዎች አለመሆናቸውን፥ መንግሥትን ለማዋረድ መሞከርም እንዳሰቡት ዕዳው ገብስ አለመሆኑን በተግባር እንዲያዩ ቢደረግም በማጥ እንደተያዘ አሮጌ ከብት እዝያው ሁኖ እንቧ ከማለት ውጭ  በፖለቲካው ላይ ለውጥ ማምጣት አልቻሉም:: 

4. ማጠቃለያ

ከላይ እንደተገለጸው ፖለቲካ ሐይማኖት አይደለም:: ዛሬ ተሰቃይተን፥ ዛሬ ሞተን፥ በትንሳኤ ከሞት ከተነሳን በኃላ ጥሩ ሕይወት እንኖራለን ብለን ተስፋ አድርገን የምንገባበት ሳይሆን ዛሬና ነገ በምድር ላይ እያለን የተሻለ ኑሮ ለመኖር የምናደርገው እንቅስቃሴ ነው:: ይህም ማለት እንደ አህያዋ “እኔ ከሞትኩ ሣርዶ አይብቀል” ብለን ሕልውናችንን ሽጠን ለግል ድሎታችንና ምቾታችን ስንል የማይገባውን አስነዋሪ ድርጊት እንፈጽም ወይም የተጫነብንን ሁሉ መሸከም አለብን ማለት ሳይሆን  ትርፍና ኪሳራውን እያየን አንድ ትክክለኛ ሰው ማድረግ ያለበትን ‘prudent person rule’ ተጠቅመን እናድርግ ለማለት ነው::  የትግራይ መሪዎች ሕዝባችን እያለቀ ከሆነ የምንዋጋበት ምክንያት የለም በማለት እ. አ. አ. በ1985 ረሃብም በ2022 ጦርነትም የትግላቸው ማዕከል የትግራይ ሕዝብ ኑሮ መሆኑን አረጋግጠዋል:: የኦሮሞ አማጽ መሪዎች ግን የኦሮሞ ሕዝብ ነጻ መውጣት አልፈልግም ብል እንኳ ጫካውንና የዱር እንስሳትን ነጻ እስክናወጣ መዋጋት አናቆምም፥ ትጥቅም አንፈታም ብለው ስላመረሩ የትግራይ ሕዝብ ያገኘውን እፎይታና አገልግሎት አንዳንድ የኦሮሚያ አከባቢዎች ማግኘት አልቻሉም::

 የትግራይ የፖለቲካ መሪዎችና ኤልቶች የትግራይ ተወላጆች ከማዕከላዊው መንግሥት ጋር በሚያስማሙን ጉዳዮች ላይ አብረን እየሰራን፤ በሚያለያዩን ጉዳዮች እየተወዳደርን፥ እዝህ አገር ውስጥ አብረን እስከኖርን ድረስ በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ድርሻችንን ማግኘት አለብን፥ በውሳኔ ሰጪነት ውስጥም መሳተፍ አለብን እንጂ ያልተሳተፍንበት፥ ያልከራከርንበት፥ ሐሳባችንን ያልሰጠንበት ውሳኔ አስፈጻሚ መሆን የለብንም ብለው ለመካተት ስታገሉ ተቃዋሚ ኦሮሞዎቹ ግን በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን በራሳቸው ከኢትዮጵያ ፖለቲካ እያገለሉ ሌሎች የወሰኑት ውሳኔ ተገዥና ፈጻሚ መሆንን መርጠዋል:: ተቃዋሚ የኦሮሞ የፖለቲካ መሪዎችና ኤሊቶች ይህንን ራስን በራስ የማግለል የፖለቲካ ባሕል ካልለወጡ እንታገልለታለን የሚሉት ሕዝብ የበለጠ ተጎጂ ይሆናል::

እንደ ብልጥ ልጅ የተገኘውን እየበሉ/ይዞ ለቀሪው ማልቀስ እንጂ የጠየኩት ሙሉ በሙሉ በአንዴ ተሟልቶ ካልተሰጠኝ በፖለቲካ ጫወታው ውስጥ ገብቼ አልጫወትም ብሎ ራስን ማግለልና የዳር ተመልከች መሆኑ አይጠቅምም:: እነርሱ ተሳተፉበትም አልተሳተፉበትም ተመረጥኩ ያለው መንግሥት ያስተዳድራቸዋል፥ የወጣው ሕግ ይፈጸምባቸዋል:: ባለፉት ስድስት ዓመታት ያየነው እውነታም ይኼው ነው:: አፖርትይድ የተለወጠውና የኮሚንዝም ካምፕ የተበተነው በአብሮ መሥራት ዜዴ (constructive engagement) እንጂ በማግለልና በመገለል አለመሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል:: “ብርሃን ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው?” ተብሎ በ2ኛ ቆሮንቶስ 6:14-15 የተጻፈው ለሐይማኖታዊ ጉዳይ እንጂ ለፖለቲካ ጉዳይ አይደለም:: በፖለቲካው በሚያስማማው ላይ ተስማምቶ፥ ተቻችሎ መሥራት የግድ ይላል:: ፖለቲካ ማለት ራሱ መቻቻል (compromise) ነው:: የአሜሪካ አምባሳደር በኢትዮጵያ ኢርቪን ማሲንጋ ሜይ 15, 2024 ባደረጉት የፖሊሲ ንግግር የኢትዮጵያ ውስብስብ የፖለቲካ ችግር በጦር ሜዳና በጸጥታ ላይ ባተኮረ አካሄድ ሊፈታ ስለማይችል መመካከር ያስፈልጋል ማለታቸው የዝህኑ የመቻቻልና የመተባበር (compromise and cooperation) አስፈላግነትን ያስረዳል:: በመጨረሻም የፖለቲካ ፈላስፋው ፕላቶ “በፖለቲካ ውስጥ ባለመሳተፋችን ከሚደርሱብን ቅጣቶች ውስጥ አንዱ በዝቅተኛ ሰዎች መገዛት ነው” (One of the penalties for refusing to participate in politics is that you end up being governed by your inferiors) ያለውን ማስታወስ ያስፈልጋል::

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

1 COMMENT

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here