spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየትየፕሬቶሪያው ስምምነት፣ የትሕነግና ብልፅግና እርጥበ ኩበት የማንደድ ሴራ፡ እኔ እንደሚገባኝ 

የፕሬቶሪያው ስምምነት፣ የትሕነግና ብልፅግና እርጥበ ኩበት የማንደድ ሴራ፡ እኔ እንደሚገባኝ 

ፕሬቶሪያው ስምምነት
የብልጽግና ተወካዮች በመቀሌ ከህወሓት ጋር ከመከሩ በኋላ (ፎቶ /ፋይል )


ከአበበ ኃብተሥላሴ
ግንቦት 27 2016  ዓ. ም.

ይህ ጽሑፍ በወርሃ ሚያዚያ 25 2016 (May 3 2024) ከሆራይዘን ነፃ የብዙሃን መገናኛ ባልደረባ ለተሰነዘርለት ጥያዌዎች የትሕነግ ሠራዊት ከፍተኛ አዝዥ አሁን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚደንት የሆነው ጄነራል ታደሰ ወረደ1 በሰጠው መልስ ላይ በተለይ ያጠነጠነ ነው። በተጨማሪም በግንቦት 4 2016 (May 12 2024) ላይ ደግሞ ከትሕነግ ቃል አቀባይ ጋር2 ከዚሁ የብዙሃን መገናኛ ጋር በተደረገ ቃለ ምልልስና ከሰሞኑ ከግራም ከቀኝም በሚናፈሱ ዘገባዎችና መነጋገሪያ በሆኑት ላይ በአጠቃላይ መሰረት ያደረገ እኔ የገባኝን በተመለከተ የተጻፈ ነው። እኔ እንደሚገባኝ ትሕነግ የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ ሕዝብ ሳይፈቅድ ከትግራይ ውጪ የነበሩና የበጌምድር ግዛቶች የሆኑትን ወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራን በጉልበት ወስዶ ምዕራብ ትግራይ ብሎ፣ ጠለምትንም እንደዛው ደግሞ ከሌሎች ጋር አድርጎ ሰሜን ምዕራብ ትግራይ ብሎ ከወሎ ደግሞ ራያን በመውሰድ ደቡብ ትግራይ በማለት የፌዴራል ክልሎች ሲመሰረቱ የትግራይ ግዛቶች አድርጎ ማካለሉን ነው። እነዚህ ምዕራብ ደቡብ አባባሎች ጉዳዩን በሚገባ የማያውቀውን የውስጥና የውጪ ወገን ለማደናገርና ቀስ በቀስም ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉ የወልቃይት፣ የጠገዴ፣ የጠለምት፣ የሁመራ፣ የራያ ግዛቶችን ስም በማደብዘዝና በማጥፋት ግዛትነታቸው የትግራይ ሆኖ እንዲቀር ያለመ እንደሆነ ነው እኔ የገባኝ ። 

በዚህ መሰረት ትሕነግ እነዚህን የአማራ ግዛቶች የትግራይ ክልል አድርጎ በሰራቸው ሥራዎች የግዛቶቹን ታሪካዊ ቦታና ይዞታ በሚገባ የሚገነዘቡ የሚባሉ ግለሰቦችን ሳይቀር በማስፈራራትና በጥቅም በመያዝ ዕውነቱን እንዲክዱ የደረሰ የድፍረትና ዓይን ያወጣ የማጭበርበር ሥራዎችን ለአመታት በትጋት ሲሰራ እንደኖረም ይታወቃል። ይህ ደግሞ ከምንም የመጣ ሳይሆን ትሕነግ የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመስረት እሳቤው አድርጎ ትግሉን የመጀመረ በመሆኑ ነው። ለዚህም ትሕነግ እንደ ፖለቲካ ድርጅት የሚመራበት፣ ሊተገብረው ያቀደውና ይፋ ያደረገው እ.አ.አ የ1976ቱ አቋም መግለጫ (manifesto) መሰረት እነዚህ ግዛቶችን በጉልበት ወደ ትግራይ ማካለሉ ለወደፊቷ የትግራይ ሪፑብሪክ ሉዓላዊነት ጥንካሬ እንዲረዳ፣ በሱዳን በኩል መውጫና መግቢያ ድንበር እንዲኖርና የሚታረስ ለም መሬትም ለማግኘት ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የበለጠ ሚዛን እንደሚደፋ ነው እኔ የሚገባኝ። 

ሲጀመር ትሕነግ ለኢትዮጵያ ችግሮች በአጠቃላይና የተለያየ ማንነት ላላቸው ዜጎች ችግር በተለይ አማራውን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ቢያወራም የበለጠ ሚዛን የሚደፋው ግን ከላይ በተገለጸው የትሕነግ የመመሪያና የትግበራ መግለጫ (manifesto) መሰረት በጉልበት ሊወስዳቸው ላሰባቸው ግዛቶች ግብዓት ሲባል ለማይቀረው ፍልሚያ ከአማራው ጋር ተጋብቶና ተስማምቶ የኖረው የትግራይ ሕዝብ በአማራው ላይ ያለውን ግንዛቤ ወደ ጠላትነት መቀየር አስፈላጊነቱ እንደሚጎላ ነው እኔ ከአምሳ አመታት ተመክሮ መረዳት የቻልኩት። ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ ገና ከጅምሩ ትሕነግ በትግል ዘመኑ ተዋጊ ጦሩ አማራውን እንደጭራቅ እንዲስለውና ጥላቻ እንዲያድርበት ያላሰለሰ ሥር መስራቱ3 ሲሆን በተጨማሪም የመንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላም ይላቸው የነበሩ አባባሎችና ይወስዳቸው የነበሩ እርምጃዎች ድርጅቱ ሲፈጥረው ፀረ-አማራ መሆኑን የመሰከሩ ተግባራት ናቸው። 

እንግዲህ ትሕነግ ይህን የመሰለ አቋሙን ተከትሎ ነው ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት ከትግራይ ወደ ሱዳን የፈለሰ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ሕዝብን የመንግሥት ሥልጣን እንደያዘ በጉልበት ከአማራው በነጠቃቸው ቦታዎች ውስጥ በተለይ በወልቃይት ያለውን የሕዝብ ስብጥር ለመቀየር ሲባልና የእነዚህን አምስት እጥፍ የሚያህል ቁጥር ያለው ሕዝብ ደግሞ ከትግራይ አምጥቶ በተመሳሳይ ጊዜ በእነዚያ ግዛቶች ውስጥ ማስፈሩ4 ይታወቃል። እንግዲህ እነዚህ ሰፋሪዎች ናቸው እራስቻውን ትግርኛ ተናጋሪ ‘ወልቃይቴ’  

የሚሉት። በተጨማሪም በጊዜው የመከላከያ ሠራዊትን ከሁሉም በተውጣጣ ለመገንባት በማለት የቀነሰውን የትሕነግ ተዋጊ በፈቃደኝነት በሁመራ ማስፈሩ5 ሁሉም የሚናገሩት ትሕነግ ቀደም ብሎ በያዘው አቋም መሰረት የኗሪውን ሕዝብ ስብጥር ለመቀየር የሰራው ሥራ የትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታን ግቡ ያደረገ እንደሆነ ለመረዳት የሚከብድ እንዳልሆነ ነው እኔ የሚገባኝ። 

አሁንም የትሕነግ ባለሥልጣናት በተለያዩ ጊዜ ከሚሏቸው አባባሎች አንፃር ምንም እንኳን የትግራይ ሪፑብሊክን መስርቶ በተለይ በዚህ አካባቢ ነጻ ሆኖ፣ በሰላምና ትብብር ከጎርቤት ጋር መኖር እንደሚወራው ቀላል እንደማይሆን ሲብስም እንደማይቻል የተለያዩ መከራከሪያ ሃሳቦችን (ለምሳሌ ነፃ ወጡ የሚባሉት ደቡብ ሱዳንና ኤርትራ ምን ያህ ከነበሩበት የባሰ ሁኔታ ላይ መገኘታቸውን)  በማንሳትና አድሏዊ ከሆነው ዓለም አቀፋዊ ግንኙነት ግንዛቤ አንፃር ሚዛን የሚደፋ ክርክር ማድረግ ቢቻልም ትሕነግ ከዚህ እሳቤ ግን የተላቀቀ አይመስልም። ስለዚህ የትግራይ ሪፑብሊክ እውን አይሆንም ብሎ ለመከራከር የሚያስችል ጭብጥ ነገር ማየትና መስማት አልተቻለምና ሃሳቡ እንዳለ ነው ማለት ይቻላል። 

ከ2010 ወዲህም የብልፅግና አገዛዝም ኦነግን በጉያው አቅፎና ደግፎ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለው በአግባቡ አገር ለማስተዳደር ሳይሆን በተመሳሳይ የጎሳ ፖለቲካ እሳቤ ፀረ-ኢትዮጵያ ለሆነ አላማ ሲል በመሆኑ ኢትዮጵያን ኦሮሚያዊት አድርጎ ለመፍጠር አጀንዳ አንግቦና ይህንንም ለመተግበር ሲባል አማራው የዘመን ጠላት ተብሎ በተቀነባበረ፣ በተደራጀና የመንግሥት ባለሥልጣናት ጭምር በሚሳተፉበት የፀር ማፅዳት ወንጀል ሲጨፈጨፍ ሊታደገው እንዳልፈለገ ነው እኔ የገባኝ። በመሆኑም የብልጽግናው አገዛዝ አማራውን በተመለከተ ከትሕነግ የተለየ ሳይሆን የባሰ መሆኑን ያስመሰከረበትና የነበረውን ችግር ማረኝ ያስኘ እጅግ ዘግናኝና አረመኔያዊ የዘር ማፅዳት ወንጀል ለአመታታ ሲፈጸምበት አንድም ቀን ሊታደገው አለመፈለግ ብቻ ሳይሆን ላነገበው አጀንዳ ስኬት እንቅፋት እንዳይሆን ጭራሽ ሊያጠፋው ባይችል ሊያዳክመው ሠራዊት አሰልፎ እየወጋው ይገኛል። የብልፅግና መሪዎች ይህንን የሚያደርጉት በአንደበታቸው ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ እያሉ ያነገቡትን ፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ ለመተግበር ‘እኛ ዝሆን ነን’፣ ‘የሰበረንን እንሰብረዋለን’ እያሉ ነፍጠኛ የሚሉትን አማራ መሬት ነጣቂ፣ ቋንቋ ደፍጣጭ፣ ጡት ቆራጭ በሚል የስሁት ትርክት ቅስቀሳ እየተጠቀሙ እንደሆነ ነው እኔ የሚገባኝ። አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ ለዚህ ሁሉ ጦስ ምንጭ የሆነው በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ በግድ የተጫነበት አድሏዊ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ሲሆን ካደረሰው ጥፋትና ውድመት አንፃር ሥርዓቱ መወገድ ሲገባው ችክ ተብሎ እንዲቀጥልና አገራዊ ችግሮችን እንዲያባባስ ጭራሽ ማን ወንድ ይነካውና መባሉ ነው። 

ሲጀመር ትሕነግና ብልፅግና አድሏዊ ለሆነ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ተገዢ በመሆናቸው በየፊናቸው ቆመንለታል ለሚሉት የሕብረተሰብ ወገን ጠላት መፈለግ ስላለባቸው አማራውን የዘመን ጠላት ያደረገ የሚስማሙበትና የሚጋሩት የስሁት ትርክት ያላቸው እንደሆነ ያለፉት ሰላሳ ሶስት አመታት ማስተባበልም መካድም በማይቻል ደረጃ ያረጋገጡት ነው። እነዚህ አማራውን በተመለከተ በስሁት ትርክት የሚስማሙት ድርጅቶች የቆሙለት የጎሳ ፖለቲካ አቃፊ ሳይሆን ገፊ፣ ፍትሃዊ ሳይሆን አድሏዎ በመሆኑ ሥልጣን ላለማጋራት ትሕነግ በዘመኑ ኦነግን ከሥልጣን ተካፋይነት እንዳባረረው ሁሉ አሁንም ኦነግ የሚዘውረው የብልጽግና አገዛዝም በተራው የኔ የሚለው አጀንዳ ስላለው ትሕነግን ከሥልጣን በመግፋት ቂም ሊወጣ በወሰደው እርምጃ ጦርነት እንደተለኮሰ ነው እኔ የገባኝ። በመሆኑም በጥቅምት ወር 2012 ላይ የተጀመረው የእርስ በርስ ጦርነት ለሁለት አመታት ተካሂዶ ዝሆኖች ሲጣሉ የሚጎዳው ሣሩ ነው እንደተባለው ከሚልየን በላይ የሰው ሕይወት፣ ከትሪልየን ብር በላይ የሚገመት ውድመትና የሚልየኖችን መፈናቀል አስተናግዶ፣ አገርን መቀመቅ ውስጥ ከቶና በተለይ በአማራው ላይ ከፍተኛ ቀውስ አስከትሎ ብልጽግናና ትሕነግ ተመለሰው እርጥብ ኩበት አንድደው ለአማራው ኢ-ፍትሃዊ የሆነ የፕሬቶሪያ ስምምነትን በፊርማ እንዳጸደቁ ነው ለእኔ የገባኝ። 

እንግዲህ አማራውን በተመለከተ ትሕነግና ብልፅግና ተመሳሳይ አቋም ይዘው፣ ሁለቱም ወገናት በጦርነቱ ወቅት ለፈጸሟቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ማንም ተጠያቂ ሳይሆንና አማራውን የሚወክል ሳይኖር ፀረ-አማራ የሆኑት ኃይሎች በደቡብ አፍሪካዋ ፕሬቶሪያ ከተማ ባካሄዱት ስብሰባ ጦርነቱ ቆመ መባሉና የእነዚህ ግዛቶች ጥያቄም በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ይፈታል መባሉ የአማራውን ጥቅምና ፍላጎት ማርካት እንደማይችል ለመረዳት ዲግሪ መጫን እንደማያስፈልግ ነው ለእኔ የሚገባኝ። በተጨማሪ ከአማራው ጥቅምና ፍላጎት አንፃር በዚህ የፕሬቶሪያ ስምምነት ላይ የትሕነግ ጋሻ ጃግሬ የሆነችው የአሜሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪነት ሚና ሌላው ስምምነቱ ፍትሃዊ መሆኑ ላይ አሉታዊ አሻራ እንደሚኖረውም መገንዘብ ይቻላል። ሲጀመር ከመሰረታዊ የፖለቲካ ሀሁ በመነሳት አሜሪካ ከጥንት ጀምሮ በአካባቢው ተጽዕኖ የመፍጠር ልምዷ፣ የራሷንና የግብረአበሮቿን ጥቅም ከማስከበር ስሌት አንፃር ከኢትዮጵያ ይልቅ የትሕነግ ወዳጅነት የበለጠባት መሆኑ፣ በተለይም ጦርነቱን ተከትሎና ከዛም በኋላ በኢትዮጵያ ኪሳራ ለትሕነግ ጥብቅና መቆሟና አሁን የተለየ አቋም ልትይዝ የሚያስችላት አዲስ የተፈጠረ ምክንያት አለመኖሩ የስምምነቱን ፍትሃዊነት እንዲጠየቅ ቢያደርጉ አግባብነት አላቸው። 

እኔ የሚገባኝ ከሁለቱ ፀረ-አማራ ድርጅቶች ባሻገር አሜሪካ በተለይ በጦርነቱ ወቅት ለትሕነግና ባለሥልጣናቱ ስታደርግ የነበረው ግልጽ ድጋፍና በአንድ ወቅት ጦርነቱ ተፋፍሞ መቀሌ ደጅ ላይ በደረሰበት ወቅት ከፍተኛ የትሕነግ ባለሥልጣናትን ከመቀሌ ወደ ጂቡቲ ማን እንዳጓጓዘ መታወቁ አሜሪካ ለማን እንደምታደላ ለመርዳት እንደማይከብድ ነው። በተጨማሪም በዚያን ወቅት ኢትዮጵያ ካለችበት ሁኔታ አንፃር አሜሪካ በጅቡቲ ያላትን ጦር ለማዝመት የነበራት ዝግጅት መታወቁ፣ ለፕሬቶሪያው ስምምነት ስኬትም ምን ያህል ስትጥርና ተጽዕኖ ስትፈጥር እንደነበር ግልጽ ከመሆኑ አንፃር አሁን በአገራዊ ምክክር ኑ ተሳተፉ ከሚለው አቋሟ ፍትህን መጠበቅ ድንጋይ ወደ ሰማይ ወርውሮ ወርቅ ለመቅለብ መሞከር ነው የሚያደርገው። በመሆኑም የግዛቶቹ ባለቤት እኔ ስለመሆኔ ታሪክ ይመስክር የሚለው የአማራው ሕዝብ ጥያቄና ግዛቶቹ የኔ መሬቶች ናቸው የሚለው የትሕነግ የሌባ ዓይነ ደረቅ ጥያቄ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ ግምት ውስጥ ከከተተ፣ ከታሪክና ሕዝብን ካሳተፈ እንጂ ከሕዝብ ጀርባ ከተፈጸመ የደባ ስምምነትና ፊርማ ብሎም ለፀረ-ኢትዮጵያ አጀንዳ እየተጋ ያለ አገዛዝ የፈጠረው ኮሚሽን አስተናባሪነት ከሚካሄድ ምክክርም ሆነ ውይይት አማራውም የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ፍትሃዊ፣ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሔ ማግኘት እንደማይችሉ ነው እኔ የሚገባኝ። 

እንግዲህ ትሕነግና ብልፅግናም የተሳተፉበትና ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ የሰጠ የተባለለት ነገር ግን በአሜሪካ ቡራኬ ሰጪነት የተፈረመው የፕሬቶሪያ ስምምነት አንዱና ዋናው አጀንዳ በግንቦትና ሰኔ እንዲጠናቀቅ ቀነ ቀጠሮ የተያዘለት ሥራ እኔ እንደሚገባኝ ከሆነ ከአማራው በጉልበት የተወሰዱበት ግዛቶችን በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ለትሕነግ ለማፅናት ነው። ይህ አንዲሆን ደግሞ አገዛዙ ደፋ ቀና ማለት የጀመረው ቀደም ብሎ ሲሆን ጦርነቱን ተከትሎ ታስረው የነበሩና በሕግ ሊጠየቁ የሚገባቸው ወንጀለኛ የትሕነግ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታቱ ለስምምነቱ እንደ ድርጎ የቀረበ መሆኑ ሚዛን የሚደፋ እንደሆነ ነው እኔ የሚገባኝ። በቀጣይም ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የፕሬቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ “እኛ አንድ እርምጃ ሄደናል ተወያይተናል ተስማምተናል ፈርመናል። ቀጥሎ የሚጠበቅብን የገባነውን ቃል በታማኝነት በመፈጸም ሰላሙን ዘላቂ ማድረግ

ነው”6ያለውን ንግግር ተከትሎ ለስምምነቱ ስኬት ተግዳሮት ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን አማራ የማዳከም ዘመቻዎች በአገዛዙ እየተፈጸሙ ይገኛሉ። 

አገዛዙ በጭንቅ ወቅት የምትማርከውን መሣሪያ አጸናልሃለሁ ብሎ ለጦርነቱ የማገደው የአማራ ሕዝብና ፋኖ ላይ የፈረመበት ፊርማ ቀለም ሳይደርቅ በሕግ ማስከበር ስም የከፈተው የእመቃ እርምጃና ይህንንም አጠናክሮ ጊዜያዊ አዋጅ አውጆና በከፍተኛ መሣሪያና በሰው አልባ አውሮፕላን የታገዘ የመከላከያ ሠራዊትን በማዝመት የከፈተው አመት ሊሞላው ትንሽ የቀረው እልም ያለ ጦርነትም ለፕሬቶሪያው ስምምነት ትግበራ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ተግባር ሆኖ እንደ ግብዓት የሚወሰድ እንደሆነ ለመረዳት ጠቢብ መሆን እንደማይፈልግ ነው እኔ የሚገባኝ;። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከትሕነግም ሆነ ከብልፅግና ፍላጎትና አቋም አንፃር አማራው የዘመን ጠላት ከመሆኑ ባሻገር አሁን ለፕሬቶሪያው ስምምነት ትግበራ ሲባል ግዛቶቹ ለትግራይ መፅናታቸው ላይ እንቅፋት እንዳይሆን አቅሙን ከወዲሁ ማዳከም አስፈለጊነቱ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ ስለሚገኝ ነው። 

ከላይ በተጠቀሰው ቃለ ምልልስ ላይ ጄነራል ታደሰ ወረደ ለቀረቡለት ጥያቄዎች ከሰጣቸው መልሶች እኔ የገባኝ ነገር በናይሮቢ  የስምምነቱን አተገባበር በተመለከተ በተደረገው ውይይት ላይ ብሎም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ስብሰባ ላይም የተንሳ አንድ ጉዳይ የፕሬቶሪያ ስምምነቱን ለመተግበር እንዲረዳ ታምኖበት የተዋቀረ በም/ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ሰብሳቢነት የሚመራ አገራዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራ መጀመሩን ነው። እንደ ጄነራል ታደሰ ከሆነ ይህ ኮሚቴ ሰብሳቢውን ም/ጠቅላይ ሚኒስትሩን፣ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንትና ምክትሉን፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንትና ምክትሉን ብሎም አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና የመከላከያ ሚኒስትሩን ያካተተ ነው። ይህ ኮሚቴ ከሚሰራቸው ሥራዎች በሁሉም ላይ መግባባት ባይችልም ግን በመግባባት ሊሰራቸው ያቀዳቸው የሚከተሉትን እንደሚያካትት ነው ጄነራል ታደሰ አጽንዖ ሰጥቶ የተናገረውና እኔም ከቃለ ምልልሱ የተረዳሁት። 

እነዚህም በግዛቶቹ ውስጥ ያለው የታጠቀ ኃይል ትጥቅ እንዲፈታ፣ ጦርነቱን ተከትሎ በግዛቶቹ ውስጥ የሰፈረው ሕዝብ መቶ በመቶ ከግዛቶቹ ለቆ እንዲወጣ፣ በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲፈርስ፣ ከጦርነቱ በፊት ትሕነግ ያሰፈረውና ጦርነቱን ተከትሎ የተፈናቀለው ‘ወልቃይቴ’ ደህንነቱ ተጠብቆ እንደገና እንዲሰፍርና ይህ መሆኑን ተከትሎ አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር በቀበሌ፣ በወረዳ ካስፈለገም በዞን ደረጃ ማዋቀር እንደሚገባ ትሕነግና የብልፅግና አገዛዝ የተግባቡባቸው ተግባራት ናቸው። በድፍኑ የእነዚህ ግዛቶች የይዞታ ሁኔታ ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት (status quo ante) ማለትም ወደ ትግራይ ክልል እንዲመለስ ለማድረግ ሲሆን ሕዝበ ውሳኔም ካስፈለገ ከዚህ በኋላ ብቻ እንዲሆን ነው ትሕነግና ብልፅግና የተስማሙት።  

ስለዚህ እኔ እንደገባኝ ከሆነ በዚህ መልኩ በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ያለው ሥራ የፕሬቶሪያው ስምምነት በትክክል እንዲተገበር ከላይ የተጠቀሱ ተግባራትን የመፈጸሙ ሃላፊነት ግን ያለምንም ብዥታ የፌዴራል መንግሥቱና የአገዛዙ መከላከያ ሠራዊት እንደሆነ ነው። ቃለ ምልልሱ በዚህ መልኩ ቀጥሎ ሳለ የጄነራል ታደሰ ወረደ ጠያቂ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አገዛዝ ለዚህ በአማራው ኪሳራ ለትሕነግ የሚጠቅም ተግባራትን የመተግበር ወሳኝ ሃላፊነት እንዳለበት ጥርት ብሎና ግልጽ እንዲሆን የፈለገች የሚያስመስልባት ቀጥላ የጠየቀችው ጥያቄ ነው። ይህም በአላማጣ ያለውን አስተዳደራዊ መዋቅር መፍረስ ተከትሎ የሚወሩ ወሬዎች ትሕነግ እንዳፈረሰው ነው እየተናፈሰ ያለውና በእነዚህ የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው ግዛቶች ውስጥ ያለውን አስተዳደር የማፍረስ ሃላፊነቱ የማን ነው እርሶም ይህን የማፍረስ ሥራ በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ ማለትም በግንቦትና በሰኔ ወስጥ ይጠናቀቃል ብለዋልና ይህን ለመፈጸም ሃላፊነት የተሰጠው ለማን ነው? የሚል ነበር። 

ጄነራል ታደሰም እንግዲህ ባደረግናቸው ስምምነቶች ውስጥ በቀዳሚነትና በተከታይ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ ብሎ የሚከተለውን ያካተተ መልስ መልሷል። ከእነዚህ ውስጥ በደንብ የተግባባንበት ከጦርነት በኋላ ትጥቅ እንዲታጠቁ የሆኑትን ትጥቅ ማስፈታት፣ ነገር ግን ከጦርነቱ በፊት ታጥቆ የነበረ ኃይልን ግን ትጥቅ ላለማስፈታት ተግባብተናል። ምክንያቱም በእነዚህ አካባቢዎች ይህን ኃይል ትጥቅ ማስፈታት ቀላል አይደለም ከግል የደህንነት አለመሰማት ጋር የተያያዘ እንደ ባህልም የሚወሰድ ነው ይህ ደግሞ በምዕራብ ትግራይ (በወልቃይት ላለማለት) የተለመደ ነውና ማን ነው ትጥቅ ሊፈታ የሚችለው? ከዚህ ውጪ አስተዳደር ማፍረስም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ነው። አስተዳደራዊ መዋቅር በሌሎች ግዛቶች በቀበሌና በወረዳ ደረጃ ነው ያለው በወልቃይት ግን አስከ ዞን ይደርሳል። በተያያዥም አስተዳደራዊ ምልክቶች አሉ የመንግሥት ሠራተኞችም ተፈናቅለዋልና እነዚህ ሁሉ ቀላል ሥራዎች አይደሉም። 

ይህንን የበለጠ ለማብራራት ጄነራል ታደሰ የመለሰው ሲጨመቅ የሚከተለውን ይመስላል። ጦርነቱን ተከትሎ በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ የኗሪውን ስብጥር የመቀየር በተቀጣሪነትና በሌሎችም ምክንያቶች የሰፈራ ፕሮግራም ተሰርቷል (በአማራው ለማለት ነው)። ይህ ደግሞ ምጣኔ ኃብታዊ ሳይሆን ሲጀመር ፖለቲካዊ መሰረት ያለው በመሆኑ ይህ መቀልበስ አለበት ብለን ባነሳነው መሰረት በዚህም ላይ ተግባብተናል። ታዲያ ማን ነው ይህንን የሚያደርገው የሚል ጥያቄ አለ። እኛ የምናደርገውን በተመለከተ ማለትም የትሕነግን ሃለፊነት በተመለከተ በዋናነት ጦርነቱን ተከትሎ ተፈናቅሎ የነበረና አሁን ወደነበረበት ሊመለስ የተዘጋጀውን ሕዝብ ዝርዝር ማዘጋጀት ነው። ይህም አዲስ ታጣቂ አናዘጋጅም ነገር ግን ድሮ ታጥቆ የነበረ የሚታወቅ ሕዝብ ከነትጥቁ እንዲመለስ ማድረግ ነው። 

በፌዴራል መንግሥት በኩል ደግሞ አስተዳደር ማፍረስና ታጥቆ ያለውን ትጥቅ የማስወረድ ሃላፊነት የመከላከያ ሠራዊት ይሆናል ማለት ነው። ይህንን ወታደራዊ ፕላን ደግሞ እሱ ምዕራብ ትግራይ በሚለው (ወልቃይት) ግዛት ውስጥ ያሉ አዛዦችና በደቡብ ትግራይ (በራያ) ያሉ አዛዦች ናቸው ያዘጋጁትና ፖለቲካዊ አንድምታም እንዳይኖረው ሲባል በሲቪሎች እንዳይሰራ ሲባል ነው 

ሃላፊነቱ የመከላከያ ሠራዊቱ የሆነው። ስለዚህ አስተዳደር ማፍረስ፣ ትጥቅ ማስፈታትና ተፈናቃዮችን መመለስ የመከላከያ ሠራዊቱ ሃላፊነት ሲሆን ይህንንም ከአማራ ክልል አስተዳደር ጋር ተባብረው እንደሚፈጽሙት ነግረውናልና እኛም ተቀብለነዋል በማለት ጄነራል ታደሰ መልሱን አጠቃሏል። 

ከዚህ ቀጥሎ ጄነራል ታደሰ የተጠየቀው ደግሞ ጦርነቱን ተከትሎ በግዛቶቹ ውስጥ ሰፍረው ያሉትና የታጠቁት ኃይሎች በጦር ወንጀለኛነት የተከሰሱ ናቸውና እነዚህን ወንጀለኞች ሸሽተው የተፈናቀሉት (‘ወልቃይቴዎቹን’ ለማለት ነው) ተመልሰው ሲሰፍሩ እንዴት ነው ደህነታቸውን ማስጠበቅ የሚቻለው ብሎም የእነዚያ ታጥቀውና የተፈናቃዮችን ንብረትና ቦታ ይዘው ያሉትስ መጨረሻ ምንድን ነው? የሚል ነው። የጄነራል ታደስ መልስ የሚከተለውን ያካትታል። ጦርነቱን ተከትሎ በእነዚህ ግዛቶች ውስጥ ያለው ንብረት አንዳንዱ ሙሉ ለሙሉ የወደመ አንዳንዶቹ ደግሞ ምልክታቸውም የጠፋ ብሎም የተፈናቃዮቹን ንብረት በባለቤትነት የያዙም አሉ። አሁን የተፈናቀሉትን ለመመለስ ስናስብ አዲስ ቦታ እንዲሰፍሩ አይደለም የምናስበውና የምንሰራው የነበሩበት ቦታ ተመልሰው እንዲኖሩ ነው። በተጨማሪም የተያዙ ንብረቶችና ቦታዎችም መቶ በመቶ እንዲለቀቁ ይደረጋል፣ የፈራረሱት ደግሞ መጠገን ስላለባቸው መከላከያ ነፃ ያደርጋቸዋል ማለት ነው። 

ተፈናቃዩ መጠለያ ያስፈልገዋል፣ የቤት ዕቃ የለውም፣ የእርሻ መሣሪያ፣ የእህል ዘር የለውም ማዳባሪያ የመሳስሉ የእርሻ ግብዓቶችም አይኖሩትም። ስለዚህ ለነዚህ ሁሉ የትግራይ አስተዳደር ሳይሆን የፌዴራል መንግሥቱ ሃላፊነት ይወስዳል ማለት ነው። እንግዲህ ይህ ተፈናቃይ ከተመለሰ በኋላ ቁጭ አይልም ማረስ አለበት ነገር ግን የእርሻ መሣሪያ ያስፈልገዋል ግን ለምሳሌ በሬ የለም በጦርነቱ ምክንያት ዘርም በሬም የለምና በበሬ ሳይሆን በትራክተር የሚታገዙ ይሆናል። ይህ አስፈላጊ በመሆኑ የማን ሃላፊነት እንደሆነ ግልጽ አድርገናል። ነገር ግን ተደጋግሞ የሚነሳው ተፈናቃዮች ሲመለሱ የጸጥታና የደህንነት ጥያቄን በተመለከተ በተልዕኮ የተቀመጡ ሥራዎች ሲሰሩ የሚከታተልና በተባለው መሰረት መሰራታቸውና አለመሰራታቸው መጣራት አለበት የሚልውን ያካተተ መልስ ነው ጄነራል ታደሰ የመለሰው። 

ስለዚህ ትጥቅ የማስፈታቱን ሥራ፣ በግዛቶች ውስጥ እንዲሰፍሩ የተደረጉና የተፈናቃዩን ንብረት ይዘው ያሉ አማራዎችን ሙሉ በሙሉ ከቦታው ማንሳትና አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማፍረስ የመሳሰሉ ተግባራት በተገቢውና በተጠበቀው ደረጃ መተግበራቸውን የሚከታተለው ዓለም አቀፋዊ አካል በመሆኑ የሚያቀርባቸው ዘገባዎች ታማኝ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከሁለታችንም ወገን ማለትም ከፌዴራልና ከትግራይ በኩል ይህንን ጉዳይ የሚያጣራና የተባሉት ሥራዎች መሰራታቸውን የሚከታተል የጋራ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተስማምተናል። ስለዚህ እነዚህ እንደ ተልዕኮ የተወሰዱ ሥራዎች በተባሉትና በሚገባው ደረጃ መፈጸማቸውን ማረጋገጥ ሲቻልና የተፈናቃዮቹ ደህንነት ሲረጋገጥ ነው ተፈናቅለው የነበሩት ‘ወልቃይቴዎች’ ወደ ድሮ ቦታቸው እንዲመለሱ የሚደረገው የሚለውን የሚያካትት ነው የጄነራል ታደስ መልስ። እንግዲህ ይህ እንዲሆን ነው ትሕነግና ብልፅግና ፊርማቸውን ያኖሩት ብሎም አፈራራሚዎቹም ያፈራረሙት ማለት ነው። 

ለጄነራል ታደሰ ቀጥሎ የቀረበለት ጥያቄ ትጥቅ ይፍቱ (ትሕነግን) ትጥቅ ይፍቱ የሚል በተደጋጋሚ የሚሰሙና ለጦርነትም እየተዘጋጃችሁ ነው የሚል ወሬ ይወራልና ትጥቅ አንፈታም ብላችኋል ወይ? የምትፈቱስ ከሆነ የአፈታቱ አካሄድ ምንድን ነው? ለጦርነትስ እየተዘጋጃችሁ ነወይ? ለነዚህ ጥያቄዎች ጄነራል ታደሰ የሰጠው መልስ የሚከተለውን የሚያካትት ነው። አንደኛ ጦርነት ለምን እንፈልጋለን? ጦርነት እኮ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው። አሁን ልዩነቶች ቢኖሩም በሰላም እየፈታን ነው ያለነው ያሉት ልዩነቶችም ወደ ጦርነት የሚወስዱን አይደለም ብለን ነው የምናምነው። ስለዚህ ለጦርነት እየተዘጋጃችሁ ነው የሚለው መሰረተ-ቢስ ነው ለጦርነት እንድንዘጋጅ የሚያደርግ ምክንያት የለም። ሁለተኛ ጥጥቅ ስለመፍታት ለተንሳው ትጥቅ አልፈታንም ትጥቅ መፍታት እኮ የራሱ ሥርዓት አለው እኛ ሠራዊት ይዘን ስንፋለም የነበርን ነን። አሁን በፕሬቶሪያው ስምምነት ሰላም ተፈጥሯል።DDR (Disarmament,  Demobilisation and Reintegration) ማለት ትጥቅ መፍታት አይደለም በማለት ጄነራል ታደሰ የተናገረውን ነው የትሕነጉ ቃል አቀባይም ከሆራይዘን ነፃ የብዙሃን መገናኛ ጋር ከቀናት በኋላ በነበረው ቃለ ምልልስ አጠናክሮ የመለሰው። 

ጄነራል ታደሰ በመቀጠል የመለሰው መልስ የሚከተለውንም ያካትታል። ትጥቅ እኮ ዝም ብሎ አይፈታም። ስለዚህ ትጥቅ ፍቱ ትጥቅ ፍቱ የሚባል ነገር አይገባኝም ዝም ብሎ እኮ አይበተንም ለምክንያት የሚታገል የነበረ ጦር ነው እኮ። ስለዚህ ተስማምተናል ሰላም ሰፍኗል ስለዚህ ና፣ ተመለስ፣ ትጥቅ ምናምን አይባልም። ትጥቅ ማስፈታት የሚባለው አስፈትተን ለመመታት ነው እንዴ? አላማው መፍታት ብቻ የሚሆነው። እኔም እሰማለሁ ስለትጥቅ መፍታት disarmament ሲባል disarmanet, demobilisation and  reintegration እኮ የተያያዙ ናቸው። ለምንድን ነው ስለትጥቅ ማስፈታት ብቻ የሚወራው? ስለዚህ የDDR አላማ ደግሞ ሰላም ለማስፈን እስከሆነ ድረስ በመጀመሪያ ለጦርነቱ ምክንያት የሆነውን ልዩነት የፖለቲካ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል። ያንን ነው እያደረገን ያለነው። በሰላም ይፈታል የሚል እምነትም አለን። 

ትሕነግ እንደተሸናፊ ትጥቅ እንደሚፈታ የብልጽግናው አገዛዝ ሕዝብን ያጭበረበረ ቢሆንም ጄነራል ታደሰ የመለሰው መልስ ግን የሚከተለውን የሚያካትትና ከሕዝብ የተደበቀውን ሃቅ ፍርጥ ያደረገ መልስ የሚከተለውን ያካተተ ነበር። ሁሉም ያውቁታል ትጥቅ ፍቱ የሚል ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ የመጣ የለም። ምክንያቱም ስምምነቱ ትጥቅ ለማስፈታት ሳይሆን disarmanet, demobilisation  and reintegration ነው። D ማለትም disarmament (ትጥቅ መፍታት) ብቻ አይደለም። ፍቱ አልተባልንም፣ እንዴት እንደምንፈታ ግን እናውቃለን አጀንዳው ግን አልተነሳም በማለት የብልጽግናን ዋሾነት እርቃኑን ያስቀረ መልስ መልሷል። እንግዲህ ወደጦርነት የሚወስደን ምንም ነገር የለም የሚል መልስ ጄነራል ታደሰ በመስጠቱ ቀጥሎ የቀረበለት ጥያቄ ደግሞ ስለዚህ ከአማራም ከሌሎች ጋርም ጦርነት የሚባል ነገር ከሌለ ከአማራ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዴት ነው የምታዩት? ምክንያቱም በአማራና በትግራይ መካከል የተፈጠረ ነገር አለና እናንተ ደግሞ ከአማራ መንግሥት ጋር ስለምትሰሩ እንዴት ነው? የሚል ነው። 

የጄነራል ታደስ መልስ እንደሚከተለው የተንጭቦ ቀርቧል። ከአማራ ጋር ያጋጠመው ያሳዝናል በጊዜውም መፍታት አለመቻሉ ልክ አይደለም። እስካሁን ድረስ የወሎ መንገድ ተዘግቷል የጎንደር መንገድም ተዘግቷል ምናልባት ወደፊት በታሪክ የሚወቀስ ወገን ሊኖር ይችላል። ግን መሻገር ያለብንን ነገር መሻገር አቅቶን ነው እንጂ ከአማራ ጋር ያለው ነገር መፈታት ይኖርበታል። እኛ የአማራን መንግሥት ለመጣል እሳቤ የለንም የአማራ መግሥትን ለመጣል ከዚህ ጋር ሆነን ከዛ ጋር ሆነን የኢትዮጵያን መንግሥት የመጣል አላማም የለንም። እኔ የሄድኩትን ርቀት የአማራ ልሂቃን ሲሄዱ አላይም። በጣም የሚያስፈራቸው ነገር አለ ስለምዕራብ ትግራይ (ወልቃይት ላለማለት ነው) ስለራያ ማንሳት ይከብዳቸዋል ለምን እንደሆነ እንጃ። ስለዚህ እነዚህን ግዛቶች በተመለከተ ድሮ ወደ ነበረበት ሁኔታ ይመለስ (stratus quo ante)፣ ለጦርነት መነሻ የሚሆን ነገርን እናጥፋ ከዛ በኋላ የሚነሳ ጥያቄ ካለ በሕዝበ ውስኔ እንዲታይ ማድረግ ነው በማለት ነው ጄነራል ታደስ ለጥያቄው ግልጽ የሆነ መልስ የሰጠው። 

እንዲህ ሲልም ይቀጥላል ጄነራል ታደሰ ጎጃምና ትግራይ በሁመራ ጉዳይ ለምን ይጣላል ጎንደርና ትግራይስ ለምን ይጣላል ሲጀመር ጥያቄው የልሂቃኑ ነው የነበረው እና ትንሽ ግልብነት አለ። ጦርነት የሚያስከትለውን መዘዝ እናውቃለንና በአማራ ላይ እየደረሰ ያለው ያሳዝናል ግን እዛ ያለውን ጦርነት (አገዛዙ በአማራው ላይ እያካሄድ ያለውን ጦርነት ለማለት ነው) ማስቀጠልና ከትግራይም ጋር ውጥረት እንዲቀጥል ማድረግ ለአማራው አይጠቅምምና መሆኑ ለማይቀር ነገር ትንሽ ብልህነት የጎደለ ይመስላልና በልሂቃኑ (ማለትም በአማራና በትግራይ) መካከል ስከን ብሎ መነጋጋር ያስፈልጋል። እነሱም ግማሽ መንገድ ይምጡ እኛም እንደዛው እንሂድና በንግግር እንፍታው። በሌላ መንገድ ሊፈታ እንደማይችል መታወቅ ይኖርበታል በማለት ትሕነግ በምንም ምክንያት ከአማራ ላይ በጉልበት የወሰዳቸውን ግዛቶች አሳልፎ እንደማይሰጥ እቅጩን ያሳወቀ መልስ መልሷል ጄነራል ታደሰ ወረደ። እንግዲህ የፕሬቶሪያውን ስምምነት ተከትሎ ለሕዝብ ሲደበቁና ሲዋሹ የነበሩ ሃቆች ጊዜ ደጉ አሁን እየጠሩ መምጣታቸውና በተግባርም መታየት መጀመራቸው አገዛዙ በአማራው ላይ ቀደም ብሎ የጀመራቸው የእመቃ ተግባራትና የከፈተበት እልም ያለ ጦርነት ሊተገበሩ ቀነ ቀጠሮ ለተያዘላቸው ተግባራት አንድ ግብዓት የሚቆጠሩ ናቸው የሚለው ክርክር ከዚህ አንፃር ሚዛን እንሚደፋ ለመገንዘብ ዲግሪ መጫን እንደማይጠበቅ ነው እኔ የገባኝ። 

ከዚህ በመነሳት ቃለ ምልልሱ ሲጠቃለል አንደኛ ትሕነግ በፍጹም ትጥቅ እንደማይፈታና ይህንም እንዳልተጠየቀ ትሕነግና ብልፅግና የተስማሙ ሲሆን በተፈራረሙት የፕሬቶሪያ ስምምነት አንቀጽ 6 ተራ ቁጥር (f) መሰረት ግን ስምምነቱ በተፈረመ በ30 ቀናት ውስጥ የትሕነግ ተዋጊዎች የታጠቁትን መሣሪያ ሙሉ ለሙሉ ቀላል መሣሪያን ጨምሮ መፍታት እንዳለባቸው7 በግልጽ እንደተቀመጠ መረዳት ይቻላል:: ሆኖም ግን ይህ አንቀጽ በዚህ መልኩ እንዳይተገበር ከአሥር ቀን በኋላ የስምምነቱን አተገባበር በተመለከተ በተለይ አንቀጽ 6 (f) ማለትም የትሕነግን ትጥቅ መፍታት በተመለከተ ትሕነግና ብልፅግና በናይሮቢ ባደረጉት ሌላ ስምምነት ተራ ቁጥር 2  

(d) የከባድ መሣሪያ ትጥቅ መፍታት የሚተገበረው የውጭ ኃይሎችና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ያልሆኑ ሌሎች ከክልሉ በተመሳሳይ ጊዜ እንዲወጡ ሲደረግ ነው8የሚል ስለሆነ ይህ የናይሮቢው የአተገባበር ስምምነት የፕሬቶሪያውን የትጥቅ አፈታት ስምምነት እንደሻረ ነው እኔ የገባኝ። 

ከዚህ የናይሮቢ የአተገባበር ስምምነት መረዳት የሚቻለው የውጭ ኃይል የተባለው የኤርትራ ጦር እንደሆነና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባል ያልሆኑ የተባለው ደግሞ በራሱ ግዛት ውስጥ የሚኖረውን አማራ ለማለት እንደሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ በአጠቃላይ ከቃለ ምልልሶቹ መገንዘብ የሚቻለው ትሕነግና ብልጽግና አነደኛ ከአማራው ላይ በግድ የተወሰዱት ግዛቶች የትግራይ አካል እንጂ የአማራው እንዳልሆኑ ፍርጥም ያለ አቋም እንደያዙ ነው እኔ የገባኝ። ሁለተኛው ከአማራ ላይ በኃይል በትሕነግ የተወሰዱ ግዛቶቹ  

በሕገ-መንግሥቱ መሰረት የትግራይ አካል ሆነው እንደሚጸኑ ነው። ሦስተኛው ትሕነግና ብልፅግና የተግባቡበት ጉዳይ ደግሞ አሁን በቦታው ላይ ሰፍሮ ያለው ኢትዮጵያዊ ትጥቁን ፈቶ ሙሉ ለሙሉ ከቦታው መነሳት እንዳለበትና ይህንንም የፌዴራል መከላከያ ሠራዊት የመተግበር ሃላፊነትና ግዴታ የተጣለበት መሆኑ ነው እኔ የገባኝ። አራተኛ ከፕሬቶሪያው ስምምነት ባፈነገጠ የናይሮቢ ስምምነት ትሕነግ ትጥቅ እንደማይፈታና ሊፈታ የሚችለው (የሚፈታም ከሆነ) አሁን በግዛቶቹ ውስጥ እየኖረ ያለው አማራ ተጠራርጎ ከወጣ በኋላ እንደሆነ ነው እኔ የገባኝ። ስለዚህ አማራው ዝም ብሎ ተግተልትሎ ለቆ ይወጣል ወይ? ወጣ ቢባልስ የትሕነግን ትጥቅ መፍታት ማን መረጋገጥ ይችላል? ይህን የመሰለ ዓይንህን ጨፍንና ላሞኝህ ጨዋታስ እንደ አገር ሲታሰብ ይበጃል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች እንዲጠየቁ ሁኔታው ግድ እንደሚል ነው እኔ የገባኝ። 

ከቃለ ምልልሶቹ እኔ የገባኝ አምስተኛ ጉዳይ ደግሞ የግዛቶቹ ጥያቄ የአማራ ሕዝብ ጥያቄ ሳይሆን የጥቂት ልሂቃን ጥያቄ እንደሆነ፣ ስድስተኛ አሁን በግዛቶቹ ውስጥ ያለው አስተዳደራዊ መዋቅር እንደሚፈርስ፣ ሰባተኛው ደግሞ፣ ከጦርነቱ በፊት በቦታው ሰፍሮ የነበረው ትሕነግ ያስፈረው ‘ወልቃይቴ’ ከነትጥቁ፣ ደህንነቱና ሰላሙ ተጠብቆ ተመልሶ እንደሚሰፍርና ለኑሮ የሚያስፈልጉ ከቤት ዕቃ አንስቶ አምራች መሆን እንዲችል የትራክተርም አቅርቦት እንደ ማቋቋሚያ እንደሚሰጠውና ይህም የአገዛዙ ሃላፊነት እንደሆነ ነው እኔ የገባኝ። ስምንተኛው ደግሞ እነዚህ ጦርነቱን ተከትሎ የተፈናቀሉ የተባሉ ትሕነግ በግዛቶቹ ውስጥ አስፍሯቸው የነበሩ ‘ወቃይቴዎች’ ከነትጥቃቸው ተመልሰው ከሰፈሩ በኋላ እነሱ የሚሳተፉበት አዲስ አስተዳደራዊ መዋቅር እንደሚዋቀር በቃለ ምልልሶቹ ግልጽ መሆኑ ነው። እንግዲህ ትሕነግና ብልፅግና በፕሬቶሪያ ስምምነት መሰረት በዘጠነኛ ደረጃ የተግባቡበትና የሚተገብሩት እኔ የገባኝ ጉዳይ አማራው ያለው ዕድል ነገሮች ሁሉ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት (status quo ante) ከተመለሱ በኋላ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ትሕነግ ባሰፈረው ‘ወልቃይቴ’ ሕዝበ ውሳኔ የሚበየነውን መቀበል ብቻ እንደሆነ ነው። 

በመጨረሻም በአሥረኛ ደረጃ ከቃለ ምልልሶቹ እኔ የገባኝ ጉዳይ ‘መሆኑ ለማይቀር’ የተባሉት ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉ እንዲተገበሩ ማለትም ነገሮች ሁሉ ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበሩበት (status quo ante) ከተመለሱና የሚፈለገው ሁሉ መልክ መልክ ከያዘ በኋላ ትሕነግ ያሰፈራቸውና አሁን ተፈናቃይ የሚባሉት ‘ወልቃይቴዎች’ የሚሰጡትን ሕዝበ ውሳኔ እንዲቀበሉ የአማራ ልሂቃን ‘ብልህ ሆነው’ና ታጋዥ ሆነው እንዲመለከቱ እየተመከሩ እንደሆነ ነው። እንግዲህ ይህ እንዲሆን ነው የፕሬቶሪያና የናይሮቢ ስምምነት ብለው፣ ትሕነግም፣ ብልጽግናም፣ የአፍሪካ ሕብረትም፣ አሜሪካም ሌሎችም ሌሎችም እንዲተገበር ደፋ ቀና ሲሉት የነበረው ማለት ነው። 

ሆኖ ግን በዚህ የፕሬቶሪያ ስምምነትና ቀጣይ ስብሰባዎች መሰረት ትሕነግና ብልጽግና ተግባባንበት ያሏቸውንና ከላይ ጄነራል ታደሰ ‘መሆኑ ለማይቀር’ ያላቸው ተግባራት ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸው በ2016 ወርሃ ግንቦትና ሰኔ ላይ ለማጠናቀቅ በተስማሙት መሰረት ትሕነግ ራያን ተቆጣጥሮ አስተዳደሩን እያፈረሰና 70 ሺ የሚሆኑ ዜጎችን አፈናቅሎ ይገኛል። በተጨማሪም ይህንን ተከትሎ የወልቃይት ሕዝብ በራያ እየሆነ ካለውና በወልቃይትም ላይ ‘መሆኑ ለማይቀር’ በተባለው መሰረት ከታቀደው አንፃር ተሰብስቦ ወደ ባርነት እንደማይመለስ በመማማል ግልጽ ባደረገበት ወቅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የተሰጠው የአሜሪካ መንግሥት የአቋም መግለጫ እጅግ በጣም አነጋጋሪ ሆኗል። እንግዲህ በተለይ አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታና በአጠቃላይ ላለፈው ሰላሳ ሶስት አመታት ያክል ጊዜ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ለከፍተኛ ቀውስ በመዳረግ ለችግሮች ምንጭ የሆነውና በሕገ-ሕዝብ ሊቀየር የሚገባውን አድሏዊ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት ለማስቀጠል አገዛዙ ሆነ ብሎ የፈጠረውና የሚዘውረው የምክክር ኮሚሽን በሚያካሂደው ውይይት ላይ እንዲሳተፉ አገዛዙን፣ ፋኖን (ያውም ተገቢ እውቅና ሳይሆን ፋኖ ነን የሚሉ በማለት የገለጸው) እና ሌሎችንም የጠየቀው የአሜሪካ አቋም መግለጫ ለምን አሁን ቢባል ተገቢነት እንደሚያንሰው ነው እኔ የገባኝ። 

ምክንያቱም አንደኛ አገዛዙ ያለውን አድሏዊ ሥርዓት ተገን አድርጎ አማራው በማንነቱ ተለይቶ በፖለቲካ አቋም፣ በሥርዓት የተደገፈ፣ የተለያዩ የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅሮችን በመጠቀም እየተጨፈጨፈ፣ ንብረቱ እየወደመና እየተፈናቀለ በመሆኑ ፋኖ ሥርዓቱንም አገዛዙንም ለመቀየር እምቢ ብሎ እንደተነሳና ይህ መሰረታዊ የሰው ልጅ የመኖር መብት የማስከበር ትግል መሆኑን አሜሪካ ከማንም በላይ እንደምታውቅ ነው እኔ የሚገባኝ። ሁለተኛ አገዛዙ የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጫና የአገር ሉዓላዊነትን ለመጠበቅ በሃላፊነት የተሰጠውን የመንግሥት ሥልጣን እየተጠቀመ በቀናት ዕድሜ ያሉ ሕፃናትና አረጋውያን ሳይቀር በአማራ ማንነታቸው እየመረጠ እጅግ አሰቃቂና አረመኔያዊ በሆነ መንገድ እንዲታረዱና በእሳት እንዲጋዩ የፈቀደና አሁን ደግሞ ሠራዊት አሰልፎ በድሮን ጭምር በመታገዝ የዘመን ጠላት ተደርጎ በስሁት ትርክት የሳለውን አማራ እየጨፈጨፈው እንደሆነ የአሜሪካ መንግሥት አሳምሮ ያውቃል። 

ሦስተኛ ይህ የፕሬቶሪያ ስምምነት ከአማራው በጉልበት የተወሰዱት ግዛቶች ትሕነግ ያወጣውን የ1976 መግለጫ የሚያፀና ማለትም ከጦርነቱ በፊት ወደ ነበረበት ለመመለስ (status quo ante) በሕገ-መንግሥቱ መሰረት ይፈጸማል መባሉ ከታሪክና መሬት ላይ ካለ ሁኔታ አንፃር በፍጹም ፍትሃዊ ሊሆን አንደማይችልና ትሕነግ ትጥቅ እንደማይፈታ ከብልፅግና ጋር መስማማታቸውን የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያዊያን የበለጠ እንደሚያውቅ ነው እኔ የሚገባኝ። ታዲያ የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ ሕግና ፍትህን ለማስጠበቂያነት የተሰጠውን ሃላፊነትና ሥልጣን በተቃራኒው አማራውን በተለይና የተቀረውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በአጠቃላይ ለማፈን፣ ለመግደል፣ የትምህርት፣ የጤና የእምነት አገልግሎት መስጫዎችን ለማፈራረስና ልማትን ለብዙ አመታት ለመጎተት በትጋት እየተጠቀመ ካለ አገዛዝ ጋር እንዴትና ምን ለማግኘት ነው ድርድሩም ሆነ ምክክሩ? ለዚህም ነው የአሜሪካ የተደራደሩ ጥሪ ለምን አሁን እንዲባል ግድ የሚለው?  

በመሆኑም ላለፉት ሰላሳ ሶስት አመታት ኢትዮጵያና ሕዝቧ የደረሰባቸው ችግር ሊደርስ የቻለው ፀረ-ኢትዮጵያ ጥቂት ባንዳዎችና አገር ገንጣዮች ተማክረውና አርቅቀው በግድ በሕዝብ ላይ የተከሉትና በተፈጥሮው ፍትሃዊ መሆን የማይችል የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓትን ተገን አድርጎ በመሆኑ ፋኖ የጀመረው በነፍጥ የተደገፈ እምቢታ ሥርዓቱንና ማን ወንድ ይነካውና ባይ አገዛዙን ለማስወገድና ሕዝብ በሚመርጠው ለመተዳደር እንዲቻል የአገዛዙን አስተዳደር እየሰባበረ ባለበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይህን የመሰለ የአቋም መግለጫ ከአሜሪካ መንግሥት መውጣቱ ከላይ እንደተገለጸው መሬት ላይ ካሉ ኩነቶች አንፃር ሲመረመር መፍትሔ ሰጪ ሳይሆን አደናቃፊ እንደሆነ ነው እኔ የገባኝ። ይህ አገዛዙን ከነሥርዓቱ ለማስወገድ በፋኖ የተጀመረው ሕዝባዊ የእምቢታ ትግል እየጋመ ባለበት ወቅት ላይ ለሥርዓቱ መቀጠል ተብሎ የተፈጠረ የምክክር ኮሚሽን ተብዬው በሚያዘጋጀው መድረክ ላይ ከአገዛዙ ጋር የሚደረግ ውይይት ሥርዓታዊ፣ መዋቅራዊና የአመራር ለውጥ ማምጣት እንደማይቻል መታወቁ ነው ዋናው የአሜሪካ መንግሥትን አቋም ለምን አሁን እንዲባል የሚያደርገው። 

ምክንያቱም የተጀመረው ትግል የኢትዮጵያ ሕዝብን በአጠቃላይ ለከፍተኛ ምጣኔ ኃብታዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ቀውስና አማራውን በተለይ ለህልውና አደጋ የዳረገ ሥርዓትን ለማስወገድ ሲሆን የምክክር ኮሚሽኑ ደግሞ ለአገራዊ ችግር ምንጭ በመሆን ወሳኝ የሆነውን አድሏዊ ሥርዓትና አገዛዙን ለማስቀጠል ግቡ ያደረገ በመሆኑ መደራደሩንም መመካከሩንም ትርጉመ-ቢስ ስለሚያደርገው ነው። እንግዲህ ቀደም ብሎ በብልጽግናም በትሕነግም ሲወሰዱ ከነበሩ እርምጃዎች ከሰሞኑ ደግሞ መሬት ላይ ከታዩትና ከተሰሙት ማለትም ትሕነግ ‘መሆኑ ለማይቀር’ እያለና ሰማይ ዝቅ መሬት ከፍ ቢል መተርጎሙ እንደማይቀር ከሚዝተው ዛቻ፣ ይህንንም እውን ያደረገ በራያ 70 ሺ ሕዝብ መፈናቀሉ ተደማምረው የሚነግሩት ነገር በዚህም ተባለ በዚያ ትሕነግ ከብልፅግና ጋር በተስማማው መሰረት እነዚህን ግዛቶች ድሮ ወደ ነበሩበት ሁኔታ (status quo ante) ለመመለስ እንደማይተኛ ነው እኔ የገባኝ። ታዲያ ይህ የአሜሪካ በጉልበት አይደለምና መፍትሔውም ውይይት ነው አቋም ሚዛን የሚደፋው ለማን ይሆናል? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ተገቢ ይሆናል። ምክንያቱም እነዚህ ግዛቶች ሕገ-መንግሥቱ ከመጽደቁ በፊት ወደ ትግራይ የተካለሉ በመሆኑ አሁን ያላቸው እጣ ፈንታ በሕገ-መንግሥቱ መሰረት እንዲፈጸም በፊርማ የጸደቀ በመሆኑና በዚሁ መሰረት ተፈጻሚ የመሆን ዕድላቸው “ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር፣ ቋንቋ፣ ማንነትና ፈቃድ ላይ በመመስረት ነው” በሚለው አንቀጽ 46 ተራ ቁጥር 29 መሰረት ትሕነግ በሚፈልገው መንገድ ሊወሰንለት ስለሚችል ነው። 

ስለዚህ እኔ የገባኝ ነገር እያስገመገመ ያለው የፋኖ ትግል ትሕነግ የፈረመውን ስምምነት በአስቸኳይ ለመተግበር እንዲሯሯጥ፣ ‘እኛ ዝሆን ነን’ በሚል እሳቤ ያበጡት ጽነፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች በመደናገጥ አማራው እየመጣብህ ነው ብለው ኃይል ለማስተባበር እንዲሯሯጡ ስላደረጋቸው ፋኖ የእምቢታ ትግሉን አጠናክሮና ሌሎችንም አስተባብሮ አገራዊ መልክ እንዲይዝ አድርጎ መቀጠል እንደሚገባው መሬት ላይ ያለው ሁኔታ እየጠየቀ እንደሆነ ነው። በተጨማሪም የአማራ ፋኖ የሚያካሂደው በመሣሪያ የታገዘ ትግል በአገዛዙ ላይ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከተጠበቀው በላይ በመሆኑ አገዛዙን ብርክ ብርክ እንዲለው እያደረገ በመሆኑ አማራው እየመጣብህ ነው የሚል ጦር ሰበቃ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል። ሌላ የፋኖ ትግል ያስበረገገው ወገን እንደዛው አማራው መጣብህ የሚል ጥሪ በዘፈን መልክ እንዲያወጣ መገደዱን አንድ ግለሰብ ከምንግዜም የብዙሃን መገናኛ ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ሃቁን ግልጽ አድርጓል10። 

ስለዚህ እኔ እንደገባኝ ከሆነ የፋኖ ሕዝባዊ ትግል የማይተካ የሕይወት መስዋትነት እየከፈለ ያለው አገርን ከመቀመቅ ለማውጣት፣ አድሏዊውን ሥርዓት ሽሮ አዲስ በሕገ-ሕዝብ ላይ የሚጸና ሥርዓት ለመትከልና የሚልየኖችን ሕይወት ለመታደግ በመሆኑ ነባራዊውን ሁኔታና ጊዜውን የሚመጥን እርምጃ መሆን ያለበት የተዋጊውን አደረጃጀት እንደተጠበቀ ሆኖ ፖለቲካዊ አደረጃጀቱን መፍጠርና በአንድ ወጥ አመራር እንዲመራ ትጉልን ማሳለጥ ነው። በተጨማሪ የትግሉን አቅጣጫና ግብ ግልጽ ማድረግ፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ማሳተፍና ትግሉን አገራዊ ደረጃ ማድረስ እጅግ አስቸኳይና ወሳኝ በመሆኑ ምንም የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ሰበብ እንደማይፈልግ ነው። አሁን ካለው መሬት ላይ ከሚታይ አገራዊ ሁኔታና ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይላት ከተሰለፉለትና ሊፈጽሙት ከተዘጋጁት ጥፋት አንፃር ይህ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የፈነጠቀ የፋኖ ተጋድሎ አሁን ካለበት የተለየ ደረጃ ላይ መገኘት እንዳለበትም ግድ ስላለ ነው ይህን ማለት ያስፈለገው። 

ስለዚህ የአማራውን እምቢተኝነት በመሣሪያ ትግል እያጧጦፈ ያለውና ከተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብም ተስፋ የሚሰጥ የትብብር መንፈስ እየተለገሰው ያለ ትግልን የሚመራው ፋኖ ብልጥ መሆን ካለበትም ብልጥ ሆኖ፣ ብልህ መሆን ካለበትም ብልህ ሆኖ በተፈጥሮ ፍትሃዊ መሆን የማይችል የጎሳ ፖለቲካን ተጠይፎ ዜጋውን ቂመኝነትና ጨካኝነት ወደሚነዳው ማንነት ደረጃ ባወረደ የጎሳ ፖለቲካ ሥርዓት መቃብር ላይ ማንኛውም ዜጋ ሰው በመሆኑ ብቻ ሰላሙና ደህንነቱ፣ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቹ መጠበቃቸውን አስተማማኝ ማድረግና በተቋም ደረጃ እንክብካቤ የሚያገኙበት ሕገ-ሕዝብ ላይ የጸና ሥርዓት ለመትከል ራዕይ ሰንቆ የሁሉንም ኢትዮጵያዊ ትብብርና ተሳትፎ ማግኘት ላይ አበክሮ መስራት የተቀረው ኢትዮጵያዊም የእምቢታ ትግሉን መቀላቀልና ለውጤት ለማብቃት እያደርገ ካለው በላይ መረባረብ እንደሚገባው ነው እኔ በቅጡ የገባኝ። ለዚህም ነው ይህ እንዲሆን በይቻላል መንፈስ መነሳሳት ሁለቴ የሚያሳስብ አይደለም ሊሆንም አይገባውም እየተባለ ያለው። 

ይሰማል ፋኖ?  
ይሰማል የአማራ ሕዝብ?  
ይሰማል የኢትዮጵያ ሕዝብ? 

ማስታዎሻዎች

1 Horizon Free Media, 2014 
2 Horizon Free Media, 2014a 
3 Bamlak Yideg & Peteti Premanandam, 2019 
4 Wosenyelew Tedla & Moges Kelklie. 2023 
5 The World Bank, 1996
6 አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን 2015
7Intergovernmental Authority on development (IGAD) 2022 
8 Chala Dandessa 2022
9የፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ 1987 
10 ምንግዜም ሚዲያ (2024)

ዋቢ ማጣቀሻ 

አማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን (2015) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚሰጡት ማብራራያ፣ የተለቀቀበት ቀን ሕዳር 6 2015፣ የተገኘው https://www.youtube.com/watch?v=nTmqCHOPqQw&t=8521s (የተሰማበት ቀን ግንቦት 12 2015). 

ምንግዜም ሚዲያ (2024) መስታወት- የአቶ ልደቱ መጣጥፍ ላይ የተደረገ ውይይት Megizem Media Mestawet-Discussion  on Lidetu Ayalew’s Document, የተገኘው፣ https://www.youtube.com/watch?v=UucdJDc_6zQ (የተሰማበት ቀን ግንቦት 17  2024). 

Horizon Free Media (2016) ቆይታ ከሌ/ጀኔራል ታደሰ ወረደ ጋር፣ የተለቀቀበት ቀን፣ ሚያዚያ 25 2016፣ የተገኘው ፣ https://www.youtube.com/watch?v=M5lqsM_KiWQ፣ (የተሰማው ግንቦት 11 2016). 

Horizon Free Media (2016a) የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ህወሃት ከአልቡራን ጋ ሆኖ እየወጋኝ ነው” ፣ጌታቸው ረዳ በ UAE  ቆይታ ከህወሃት ተወካይ ጋር፣ የተለቀቀበት ቀን ግንቦት 4 2016፣ የተገኘው፣ https://www.youtube.com/watch?v=VUp IaWrxZU፣ (የተሰማው ግንቦት 12 2016). 

ፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ 1987፣ “የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ-መንግሥት አዋጅ”፣ የታየው ግንቦት 20  2016፣ <https://www.ethioreaders.com/boksdwnlods/The%201995%20Ethiopian%20constitution English%20and%20Amharic%20version.pdf>. 

Bamlak Yideg & Peteti Premanandam 2019, “The 1976 TPLF Manifesto and Political instability in Amhara Region,  Ethiopia”, Viewed on May 21 2024, Accessed at ,<https://core.ac.uk/download/pdf/211831177.pdf>. 

Chala Dandessa 2022, Nairobi Agreement Between FDRE Defence Force and TPLF Military Commands,  <https://ethiopianstoday.com/2022/11/12/nairobi-agreement-between-fdre-defense-force-and-tplf military-commands/ >. 

Intergovernmental Authority on Development (IGAD) 2022, Agreement For Lasting Peace Throght a Permanent  Cessation of Hostilities Between The Government of the Federal democratic republic and the Tigray people’s  Liberation Front (TPLF), <https://igad.int/wp-content/uploads/2022/11/Download-the-signed-agreement here.pdf>. 

The World Bank 1996, Case Studies in War-to-Peace Transition: The Demobilisation and Reintegration of Ex Combatants in Ethiopia, Namibia and Uganda, Discussion Paper No 331, Viewed on May 21 2024, Accessed at, <https://documents1.worldbank.org/curated/en/385411468757824135/pdf/multi-page.pdf>. 

Wosenyelew Tedla & Moges Kelklie 2023, Welkait, Ethiopia: Geo Strategic importance and the Consequential Annexation by TPLF, viewed on 22 May 2024, Accessed at, <https://www.hornafricainsight.org/post/welkait ethiopia-geo-strategic-importance-and-the-consequential-annexation-by-tplf>.


__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here