spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeነፃ አስተያየት  ጠሚ አቢይ አህመድና አገራዊ ምክክር (ኤፍሬም ማዴቦ)

  ጠሚ አቢይ አህመድና አገራዊ ምክክር (ኤፍሬም ማዴቦ)

አገራዊ ምክክር

                  

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)

አገራዊ ምክክር ወይም ብሔራዊ ውይይት የሚለው ቃል በጽንሰ ሃሳብ ደረጃ ለኛ ለኢትዮጵያዊያን አዲስ ሃሳብ አይደለም። ደርግ “ብሔራዊ መግባባት” የሚል ጥያቄ በተከታታይ ሲጠየቅ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ተወው፣ ህወሓት መጣና “ብሔራዊ ዕርቅ” ተብሎ ሲጠየቅ ደሞ የተጣላ ህዝብ የለም ብሎ ጭራሽ በህዝባዊ ጥያቄ ላይ አፌዘ እንጂ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አንዴ “ብሔራዊ ዕርቅ”፣ አንዴ “ብሔራዊ መግባባት” ሌላ ግዜ ደሞ “ሁሉን አቀፍ ውይይት/ድርድር” የሚልና በጆሮ ሲሰማ የሚለያይ የሚመስል በይዘት ግን ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ከ1967 ዓ.ም. ጀምሮ ምኒልክ ቤተመንግስት የገቡ መሪዎችን ሁሉ ጠይቋል።

ባለፉት ሦስት አመታት በተለይ የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ወጥቶ ኮሚሺኑ ተቋቁሞ ስራውን ከጀመረ በኋላ፣ “አገራዊ የምክክር ጉባኤ” የሚል ቃል በየቦታው ይደመጣል።አንዳንዶች ኮሚሺኑን ገና ሳይቋቋም አይንህን ላፈር ብለውታል፣ አንዳንዶች ደሞ “ምክክር” ያልሞከርነው መንገድ ነውና እስኪ እንየው የሚል አቋም ይዘዋል። ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ከተማ ደረጃ የምክክር ጉባኤ መጀመሩን አስመልክቶ ጠሚ ንግግር ካደረጉ በኋላ፣ ብዙዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ደረጃ ቁጭ ብሎ መወያየትና ችግሮቻችንን መፍታት አስፈላጊ ነው ብለው ቢያምኑም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚካሄደው አገራዊ ምክክር ሂደት የብልፅግና ፓርቲን ፍላጎት ቢያሳካ እንጂ የኢትዮጵያን ችግር ይፈታል የሚል እምነት የላቸውም። ለመሆኑ አገራዊ ምክክር (National Dialouge) ሲባል ምን ማለት ነው?

አገራዊ ምክክር- በአገርና በአገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት (Nation-Building & State-Building) ስምምነት በሌለባቸውና በህገ መንግስታዊ ቀውስ በሚናጡ አገሮች ውስጥ፣ የእኩልነት ጥያቄ፣ የሥልጣን መጋራት ጥያቄ፣እራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ ወይም የመገንጠል ጥያቄ በተነሳባቸው አገሮች ውስጥ፣ ጥያቄዎቹ መልስ አልባ ሲሆኑ ወይም ጥያቄዎቹን ለማፈን ሙከራ ሲደረግ የሚቀሰቀሱ ግጭቶችን/ጦርነቶችን ለማቆም፣ ህዝብ ላነሳቸው ጥያቄዎች አግባብ ያለው አገራዊ መልስ ለመስጠትና ሁሉንም እኩል የሚያቅፍ ሠላማዊና የተረጋጋ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ ለመፍጠር የሚደረግ ሁሉን አቀፍ አገራዊ መድረክ ነው። አገራዊ ምክክር አንድ አገር ጥልቅ የፖለቲካ ቀውስ ሲገባ፣ በድህረ ጦርነት ሁኔታ ውስጥ ሲሆን ወይም ዘላቂ የፖለቲካ ሽግግር ሲያስፈልገው ስፋት ያለው አገራዊ ባለድርሻ አካላትን በማሰባሰብና በማወያየት የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ የሚረዳ ፖለቲካዊ ሂደት ነው፡፡

አገራዊ ምክክር ይህ ነው ተብሎ የሚነገር አንድ ብቸኛ አላማ የለውም፣ አላማው እንደየአገሩ ባህል፣የእድገት ደረጃ፣ፖለቲካዊ አውድና ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታ ይለያያል። አንዳንድ አገር ውስጥ ህገ መንግስት ለማሻሻል፣ አንዳንድ አገር ውስጥ አዲስ ማህበራዊ ኮንትራት ለመፈራረም፣ አንዳንድ አገር ውስጥ ግጭትና ጦርነት ቆሞ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ፣ አንዳንድ አገሮች ውስጥ ሰላም፣ዕርቅና መግባባት ለመፍጠር፣አንዳንድ አገሮች ውስጥ ደግሞ ከላይ በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ በሁሉም ወይም በከፊል የሚመክርና መፍትሄ የሚፈልግ ጉባኤ ነው። ለምንም ጉዳይ ይደረግ ለምንም- የአገራዊ ምክክር ባለቤት ህዝብ ነው። አገራዊ ውይይት የቀውስ ማስወገጃና የፖለቲካ ሽግግር ማድረጊያ መሳሪያ ነው (National dialogue is a tool for conflict resolution and political transformation)ይህ መድረክ ብዙ ግዜ የአንድን አገር የፖለቲካ መድረክ ከሚቆጣጠሩ የፖለቲካና የሚሊታሪ ልህቃን በተጨማሪ ሌሎችንም የተለያዩ ባለድርሻዎችን ማቀፍ ያለበት ትልቅ፣ሰፊና አካታች መድረክ ነው።

አገራዊ ምክክር ለምንድነው ያስፈለገን?

አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኘው በቀላሉ የማትወጣውና ከግማሽ ምዕተ አመት በላይ ባስቆጠረ የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ ነው።እንዴት እዚህ አዙሪት ውስጥ ገባን? ለምን ገባን? እንዴት ነው  የምንወጣው? ምን ብናደርግና ምን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት ብንፈጥር ነው ተስማምተንና ተከባብረን አገራችንን እንደ ስሟ ትልቅ አገር የምናደርጋት ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ የምናገኘው ከአገራዊ ምክክር ጉባኤው መድረክ ላይ ነው። ተመልሰን  የህልውና አደጋ ላይ ወደ ጣለን የፖለቲካ አዙሪት ውስጥ እንዳንገባ፣ የሰራናቸውን ስህተቶች እንዳንደግምና ያለፈውን ያጫቃጨቀንን፣ ያገዳደለንን እና በድለኸኛል፣ጨቁነኸኛል፣ ረግጠኸኛል ያሳኘንን የታሪክ ምዕራፍ ተማምነን እና በይቅር መባባል ዘግተን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ለመጀመር ነጻ፣ግልፅና ገለልተኛ የሆነ አገራዊ የምክክር መድረክ ያስፈልገናል። አገራዊ የምክክር ጉባኤ የአገራችንን የፖለቲካ አቅጣጫ የምናስተካክልበት፣ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የምንጥልበት፣ትላልቆቹን አገራዊ ተቋሞች አብረን ዲዛይን የምናደርግበት መድረክ ነው። 

አገራችን ኢትዮጵያ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄድ ትልቅ የዉይይት መድረክ ያስፈለጋት፣የብሔር ፖለቲካ ኃይሎችና ኢትዮጵያዊ ብሔረተኞች ሁለቱም የኔ ነው ከሚሉት ጠባብ ጎጥ ወጥተውና ጠረቤዛ ዙሪያ ቁጭ ብለው ምን አይነት ምን አይነት የፖለቲካ ሥርዓት ነው በሰላም አብሮ  የሚያኖረን? ምን አይነት የመንግስት መዋቅር፣ የመንግስት ቅርፅና ምን አይነት የምርጫ ሥርዓት ነው የሚያስፈልገን?  ኢትዮጵያዊ ማንነትና የብሔር ማንነት እንዴት ነው አንዱ በሌላው አውድ ውስጥ አብረው እየኖሩ የጋራ አገር የሚገነቡት? የሚሉ ትላልቅ አገራዊ ጥያቄዎችን ቁጭ ብለው ተወያይተው መመለስ እንዲችሉ ለማድረግ ነው። 

የኢትዮጵያ ህገመንግስት በምን መልኩ ይሻሻል፣የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት፣የፖለቲካ ሥርዓታችን መሠረት ምን ይሁን የሚሉ ጥያቄዎች መልስ አጥጋቢ የሚሆነው ህገመንግስቱን አሻሽለን ለአገራችን የሚስማማ የፖለቲካ ሥርዓት መምረጥ በመቻላችን ብቻ አይደለም። እነዚህ ትላልቅ ጥያቄዎች መልስ ያገኙበት ሂደትና መልሱን ያገኙት ሰዎች ወይም ቡድኖች ማንነትና ስብጥርም የመልሱን ያክል አስፈላጊ ነው። የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ አንድ መቶ ሃምሳ አመት ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ኢትዮጵያን እንደ አገር ያዋቀሩ ትላልቅ ውሳኔዎች የተወሰኑት በአንድ ፓርቲ ወይም በጥቂት ቡድኖች ነው፣ ዛሬ ደሞ በአንድ ሰው ነው። አገራዊ የምክክር መድረክ ያስፈለገን ትላልቅ አገራዊ ውሳኔዎችን ከግለሰቦችና ከጥቂት ቡድኖች እጅ አውጥተን አገራዊ መልክ ለመስጠትና የሃሳብ ልዩነቶችን በመሳሪያ የመፍታት የቆየ ባህላችንን ቀይረን አዲስ የምክክርና የውይይት ባህል ለመገንባት ነው።

የብሔር ፖለቲከኞች “አሃዳዊያን” ፌደራሊዝምን ሊያፈርሱ ነው እያሉ በአካልም በመንፈስም ከሌለ ጠላት ጋር ተፋጥጠዋል።  የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኞች ደግሞ የብሔር ፖለቲካና ብሔር ተኮሩ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ሊያፈርስ ነው እያሉ የብሔር ፖለቲካንና ብሔረተኞችን ይኮንናሉ። እኛ ኢትዮጵያዊያን ምን ብናደርግ ነው ኢትዮጵያም ፌዴራሊዝምም ሳይፈርሱ እንዲቀጥሉ ማድረግ የምንችለው? አገራዊ የውይይት መድረክ ያስፈለገን ይህንን ቁልፍ ጥያቄ በጋራ ለመመለስ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ የአገራዊ ምክክር ጉባኤው ያስፈለገው – የፖለቲካ ሥርዓታችን መሠረት ‹‹ዜግነት›› ይሁን ወይስ ‹‹ማንነት››? ኢትዮጵጵያ ውስጥ አዲስ ማህበራዊ ኮንትራት መፈራረም ያለባቸው ዜጎች ናቸው ወይስ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች? የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ማደሪያው ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ናቸው ወይስ የኢትዮጵያ ህዝብ? የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችን በጋራ ለመመለስና ለሁላችንም እኩል የሆነች ኢትዮጵያን በጋራ ለመገንባት ነው።

አገራችን ኢትዮጵያ የራሷ የሆነ ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ አኩሪ የአልገዛም ባይነት ባህል፣ የራሷ ፊደልና ስነጽሁፍ ያላት አገር ናት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ፍትህ፣ ነጻነትና እኩልነት ለረጅም ዘመን የራቃት አገር ናት። ኢትዮጵያ የጭሰኛ ሥርዓትን እስከ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ተሸክማ የኖረች አገር ናት፣ ቀይ ሽብር የተካሄደባት አገር ናት፣የፖለቲካ ልህቃኖቿ ጎራ ለይተው የተገዳደሉባት አገር ናት። ትናንት ከህወሓት ጋር ሁለት አመት የዘለቀ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ውስጥ ነበርን፣ ዛሬ ደሞ የኢትዮጵያ መንግስት አማራ ክልል ውስጥ ፍጹም ትርጉም የለሽ ጦርነት ውስጥ ገብቶ ኢትዮጵያን “እንዳትሄዱ” የሚል ማስጠንቀቂያ የሚሰጥባት አገር አድርጓታል። 

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል በተለይ በፖለቲካ ልህቃኑ አካባቢ የሚታየው ትልቁ ድክመት ቁጭ ብሎ፣ ተከባብሮና ተደማምጦ ልዩነቶችን በውይይት የማስወገድ ባህል የሌለ መሆኑ ነው። ይህ ደሞ ረጂም ታሪክ ያለው ባህል ይመስላል። በነገስታቱ ዘመን ከንጉሱ ወይም ከንጉሱ እንደራሴ ጋር ልዩነት ውስጥ የገባ ግለሰብ የመጀመሪያ ምርጫው መሳሪያ አንስቶ መሸፈት ነው እንጂ ቁጭ ብሎ መነጋገር አይደለም። ከንጉስ ስርዓት በኋላ የመጡት ሥርዓቶችም ቢሆኑ፣ በደርግ ዘመን ኢህአፓ፣ መኢሶንና ደርግ ተገዳድለዋል። በኢህአፓ በራሱ ውስጥ በፓለቲካ ልዩነት የተነሳ ጓዶች ተገዳድለዋል፣ ህወሓትም ገና ጫካ እያለም ሆነ አራት ኪሎን ከተቆጣጠረ በኋላ በፖለቲካ የሚለዩትን የራሱንም ከራሱ ውጭ ያሉትንም ሰዎች አስሯል፣ ከአገር እንዲሰደዱ አድርጓል ወይም ገድሏል። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልህቃን ይህንን እርስ በርስ ያጋደላቸውን ጨለማ ምዕራፍ ዘግተው አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ መክፈት አለባቸው። ይህ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ልዩነቶቻችንን ቁጭ ብለን ተወያይተን በሰጥቶ መቀበል ሂደት ማስወገድ ወይም ማጥበብ እንዳለብን መገንዘብና ይህንን ግንዛቤ በተግባር ማሳየት ነው። 

የአለማችን የቀውስ፣ያለመረጋጋት፣ የግጭትና የርስበርስ ጦርነት ምልክት የሆነችዉ አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ላይ የምትገኝበት ውስብስብና አደገኛ ቦታ ላይ እንድትደርስ፣ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግስት ጨምሮ ሦስት ተከታታይ መንግስታትና፣ በእነዚህ መንግስታት ውስጥ የነበሩ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣የፖለቲካና ወታደራዊ ልህቃን፣ የሲቪክና የሙያ ማህበራት፣ የእምነት ተቋማትና ማህበራዊ ስብስቦች በማድረግም ባለማድረግም የየራሳቸውን አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ዛሬ የገባንበት አገራዊ ቀውስ ምንጩ ባለፉት ሃምሳ አመታት አንዱ ሌላውን፣ ለማጥፋት፣ለማሸነፍ፣ ለማሳነስ፣ ለማንቋሸሽ፣ ለማውገዝና ለማሳደድ የሄድንበት የግራ ኃይሎች፣ የቀኝ ኃይሎችና ግራ የገባቸው ኃይሎች አፍራሽ የፖለቲካ ነው። አገራዊ ምክክር የሚያስፈልገን በአንድ ወይም በሌላ መልኩ እኛው የፈጠርነውን ችግር እኛው መፍታት እንድንችል ነው። መንግስት ብቻውን የኢትዮጵያን ችግር መፍታት አይችልም፣ ምክንያቱም መንግስት ትልቁ የችግሩ አካል ነው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ልህቁና ምሁሩ ሊፈቱ አይችሉም እነሱም የችግሩ አካላት ናቸው። የኢትዮጵያን ዋና ዋና የፖለቲካና ማህበራዊ ችግሮች የፈጠርነው ሁላችንም ነን፣ ችግሩን በጋራ ተወያይተን መፍታት ያለብንም ሁላችንም ነን። ችግሩ ዛሬ በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መሪ “እኔ” “እኔ” ብቻ እንጂ “እኛ” የሚለውን ማህበራዊ ቃል የሚጸየፉት ይመስል ይህ ቃል በፍጹም ከአፋቸው አይወጠም።  የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተብዬው አባላትና ጠሚሩን ያጀቧቸው ሰዎችም፣ ጠሚሩ የሚጸየፉትን ከሳቸው በላይ የሚጸየፉ፣ ጠሚሩ የሚወዱትን ከሳቸው በላይ የሚወዱ የጠሚሩ ተጎታች ፉርጎዎች ናቸው። 

አገራዊ የምክክር ኮሚሺኑን ከተቋቋመበት ግዜ ጀምሮ ገለልተኛ አይደለም በሚል በፍጹም ያልተቀበሉት ብዙ ሰዎች ነበሩ። የዚህ ጽሁፍ ጸሐፊ የምክክር ኮሚሺኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ሲወጣ፣ አዋጁ ፓርላማ ውስጥ ለትችት ሲቀርብ፣ ኮሚሺኑ ተቋቁሞ ስራውን ሲጀምርና በሂደት የደረሰበትን ደረጃ ለህዝብ ሲያሳውቅ፣ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ የነቃ ተሳትፎ አድርጓል። እኔ (ኤፍሬም ማዴቦ) የምገኝበት ቡድን በአንድ በኩል የኮሚሺኑን አባላት ከአምስት ግዜ በላይ ኢሳት ቴሌቪዥን ላይ ጋብዞ ሞግቷል፣ በሌላ በኩል ደሞ ኮሚሺኑን፣የፓርላማ አባላትን እና የሰላም ሚኒስቴር መ/ቤትን ጨምሮ ቁልፍ ናቸው የሚባሉ ባለድርሻዎችን ጋብዞ አገራዊ ጉባኤውን በተመለከተ ውይይት አድርጓል። 

የመንግስት ባለሥልጣናት፣የኮሚሺኑ አባላት፣የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ምሁራን  በተገኙበት በተከታታይ እንደተናገርኩትና፣ በተለያዩ ሜዲያዎች ላይ በጽሁፍና በቃለመጠይቅ መልክ እንዳቀረብኩት፣አገራዊ ጉባኤውን በተመለከተ የኔ ትልቁ ችግር ከኮሚሺኑ ጋር ሳይሆን ኮሚሺኑን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ላይ ነው። በኮሚሺኑ ስራ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት እንዳለ ሆኖ፣የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት አገራዊ ምክክር ጉባኤውን እጁ ውስጥ ያስገባው ገና አዋጁን ሲጽፍ ነው፣ ወይም እኔ የማየው ጣልቃ ገብነትን ብቻ ሳይሆን ኮሚሺኑ የሚያደራጀው አገራዊ ጉባኤ ሙሉ በሙሉ ጠሚ አቢይ አህመድ እጅ ላይ እንዳለ ነው። ግልጽና ገለልተኛ የሆነና በኢትዮጵያ ዋና ዋና ችግሮች ላይ መወያየት የሚችል አገራዊ ጉባኤ የምንፈልግ ከሆነ፣ ጩኸታችን ኮሚሺኑ ላይ ሳይሆን ኮሚሺኑን ያቋቋመው አዋጅ ላይ ወይም አዋጁን ያወጣው አካል ላይ ነው መሆን ያለበት።

በታህሳስ ወር 2014 ዓም የወጣው የአገራዊ ምክክር ኮሚሺን ማቋቋሚያ አዋጅ ውሳኔን በተመለከተ ምን ይላል? በአገራዊ ምክክር ጉባኤው ላይ የውሳኔ አወሳሰንን በተመለከተ  የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 1265/2014 በክፍል ሁለትና በክፍል አራት ላይ የተቀመጡ ሁለት አንቀጾች አሉት 

አዋጅ ክፍል 2 አንቀጽ 9 ንዑስ አንቀጽ 10

የአገራዊ ምክክር ጉባኤ አጀንዳዎችን፣ የምክክሮቹን ሂደት፣ በምክክሮቹ የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን እንዲሁም ምክረ ሃሳቦቹ በተግባር ላይ ሊውሉ የሚችሉበትን ሥልት የሚገልፅ ሰነድ በማዘጋጀት ለአስፈጻሚ አካሉ፣ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ያቀርባል፣ ለህዝብም ይፋ ያደርጋል

አዋጅ ክፍል 4 አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2

በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በሕዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለአስፈጻሚ አካሉ፣ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ሌሎች የሚመለከታቸው  የመንግሥት አካላት እንዲቀርብ ማፅደቅ ይህ ሁለተኛው አንቀጽ (አንቀጽ 21 ንዑስ አንቀጽ 2) ረቂቅ አዋጁ ለህዝብ አስተያየት ቀርቦ ከተሻሻለ በኋላ የወጣው ነው፣ ከመሻሻሉ በፊት ይህን ይመስል ነበር

“በኮሚቴዎች ተዘጋጅተው የሚቀርቡ እና በህዝባዊ ውይይቶች የተገኙ ምክረ ሃሳቦችን በዝርዝር በመፈተሸ እና በማጠናቀር ለመንግሥት እንዲቀርብ ማፅደቅ”

የምክክር ኮሚሺኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ፓርላማ ቀርቦ ህዝብ አስተያየት ሲሰጥበት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ፓርላማ ተገኝቶ ጥያቄ እንዲጠይቁ ወይም አዋጁ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ ዕድል ከተሰጣቸው ሰዎች ውስጥ አንዱ ነበር። አንተ ጥያቄህን “አምስተኛ” ተራ ቁጥር ላይ መጠየቅ ትችላለህ ብለው ዕድሉን የሰጡኝ በዕለቱ ስብሰባውን የመሩትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የህግ፣የፍትህና የዲሞከራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ እፀገነት መንግስቱ ናቸው። ወ/ሮ እፀገነት ዕድሉን ከሰጡኝ በኋላ አጠገባቸው ካለ ሰው ጋር በተደጋጋሚ እያዩኝ ከተነጋገሩ በኋላ፣ የሰጡኝን ዕድል ከልክለው ለሌላ ሰው ሰጥተዋል። እረፍት ላይ ሄጄ የሰጡኝን ቁጥር አሳይቻቸው ምነው አለፉኝ ብዬ ስጠይቃቸው፣ ከእረፍት በኋላ የመጀመሪያውን ዕድል እሰጥሃለሁ ብለው፣ ከእረፍት ስንመለስ ሴትዮዋ ጭራሽ ወደኔ ማየትም አልፈለጉም። በዕለቱ እንደኔ ዕድል ተሰጥቷቸው ከተከለከሉ ሰዎች ውስጥ አንዱ አቶ ሠለሞን ሹምዬ ነበሩ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ሲቪል ማህበራትና ሌሎችም የተለያዩ አካላት አዋጁ እንዲሻሻል በጽሁፍም በአካል ፓርላማ ቀርበውም ካነሷቸው ብዙ ሃሳቦች ውስጥ አንዱ ውሳኔን የሚመለከተው ካላይ የተቀመጠው አንቀጽ ነበር። ሆኖም እንደምትመለከቱት በመጀመሪያው ረቂቅ አዋጅና ተሻሽሏል ተብሎ በጸደቀው አዋጅ መካከል ውሳኔን አስመልክቶ ያለው ልዩነት የቃላት እንጂ የይዘት አይደለም። ለኔ ይህ የሚያሳየኝ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በአገራዊ ጉባኤው ላይ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከእጁ እንዳይወጣ መፈለጉን ነው። አሁንም ይህ አንቀጽ ተሻሽሎ ውሳኔ የመወሰን ሥልጣን ከመንግስት እጅ ወጥቶ ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ካልተሰጠ፣ከዚህ ለአመታት ከተጮኸለትና ብዙ ከተደከመለት አገራዊ ምክክር እንደ አገርና እንደ ህዝብ የምናገኘው የረባ ነገር አይኖርም! ለምንድነው የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ኮሚሺኑን ለማቋቋም ባወጣው አዋጅ ላይ “አካታች” የሚል ቃል በተደጋጋሚ እየተጠቀመ ውሳኔ መወሰንን በተመለከተ ግን አካታችነትን ረስቶ ውሳኔ የመወሰኑን ሥልጣን ለራሱ የወሰደው? ደሞስ ጠሚሩ በተለያዩ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ችግሮች የምንፈታው በአገራዊ ምክክር መድረክ ላይ ነው እያሉ፣ ለምንድነው ለዚህ ትልቅ መድረክ ወይም ለአገራዊ ምክክር ጉባኤው ምንም አይነት ሥልጣን (Mandate) በአዋጅ እንዲሰጥ ያልፈለጉት? 

ከሰሞኑ ጠሚ አቢይ አህመድ የተለመደ የቃላት ድርድራቸውን ሲደረድሩ፣ እነ ፕሮፌሰር መስፍን አና እነ ጋሽ ዘገየ ኢትዮጵያን አሳልፈው አይሰጡም እያሉ ሲዘባርቁ ተደምጠዋል። የፕሪቶሪያውን ስምምነትና አንድ አመት ያስቆጠረውን የአማራ ክልል ጦርነት ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ትላልቅ ጉዳዮች ላይ ክህደትና የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ መስጠት በግልፅ የታየው እነ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ መንደር ሳይሆን በራሳቸው በጠሚሩ መንደር ውስጥ ነው። አገራዊ የምክክር ጉባኤውን መጠበቅ ካለብንም፣ መጠበቅ ያለብን ከኮሚሺኑ ሳይሆን ዳቦውንም እንጄራውንም እኔው ካላቦካሁት እኔው ካልጋገርኩት ከሚሉት ከጠሚ አቢይ አህመድና ከፓርቲያቸው ከብልፅግና ነው።

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here