spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየፖሊሲ ወይስ የአቋም ለውጥ - ከተጨባጭ እውነታ አንጻር 

የፖሊሲ ወይስ የአቋም ለውጥ – ከተጨባጭ እውነታ አንጻር 

ፖሊሲ ወይስ የአቋም ለውጥ

ታዬ ብርሃኑ 

በዚህ ርዕሰ ጉዳይ በቀጥታና በተዘዋዋሪ በርካታ ጽሑፎችን ያቀረብኩ ቢሆንም ይችን አንስተኛ ጽሑፍ ለመጻፍ ያነሳሳኝ ግን የጀርመኑ ዶቼቬላ ሬዲዮ እሑድ ገንቦት 18 ቀን 2016 ዓ.ም ከእኔ ጋር ሦስት እንግዶችን  ያወያየበትን ምክንያት በማድረግ ነው። በዚህ አጋጣሚ ከ45 ዓመታት በላይ በፊት የ10ኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በስሜት እና በፍቅር እከታተለው ለነበረው ዶቼቬላ ሬዲዮ ከኪጋሌ በሚተላለፍ መሰለኝ የአየር ሞገዱ ይረብሸን ስለነበር ማዳመጣችን እንዳይቆራረጥብን በጊዜው በ10 ሳንቲም ኤሮግራም አስተያየት ልኬ ነበር። ማበራታቻ ይሆነኝ ዘንድ እስካሁን የማትረሳኝ ልዩ የማስታወሻ ደብተር ተላከልኝ። ለሁለተኛ ደረጃ ሳይሆን የምትመጥነው ለዩኒቨርሲቲ ነው ብየ በማቆየት የተጠቀምኩባት ዩኒቨርሲቲ ስማር ነው። ያ የረጅም ጊዜ ትዝታ በድንገት በተደረገልኝ የውይይት መድረክ ላነሳ ብፈልግም ከጊዜ አንጻር አላደረግሁም። ታዲያ ዛሬ ለዚያች ውብ መጻፊያ እና የወጣትነት ትዝታየን ለቀሰቀሰው ለውይይቱ አዘጋጅ እና ጋባዥ ከፍ ያለ ምስጋናየን ከአክብሮት ጋር ይድረሳችሁ እላላሁ። 

ወደፍሬ ነገሩ ስገባ ትኩረት ላደርግ ያሰብኩት በውይይቱ ጊዜ ሆነ ከዚያ ውጭ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ባደረጉት ንግግር ለመንግሥት እና ለመንግሥት ተፋላሚዎች ያስተላለፉትን የሰላማዊ ውይይት ጥሪን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓም ወያኔ አዲስ አበባን ከመቆጣጠሩ ጋር ተያይዞ በመንግሥት እና በወያኔ መካከል ውይይቱ ያለመደረጉን በማጣቀስ በዚሀ የሬዲዮ ውይይት እና በሌሎች በርካታ መድረኮች የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የፖሊሲ ለውጥ አደረገ የሚለውን አባባል በግሌ ለመቀበል እንደሚያዳግተኝ በውይይቱ በቁንጽልም ቢሆን መግለጼ ይታወሳል። 

መጀመሪያ የፖሊሲ ለውጥ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ክርክር ልዩ ትኩረት ቢሰጠውም ባይሰጠውም፥ አሜሪካ በዓለም ፖለቲካ ያላት አዎንታዊ ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ በቀላሉ የማይገመት በመሆኑ ከራስ አመለካከት አኳያ ግልጽ ማድረጉ አስፈላጊና ጠቃሚም መስሎ ስለታየኝ በቃል ያልኩትን በጽሑፍ ማቅረቡን ወይም መድገሙን ወደድኩ። ሁለተኛ የአሜሪካ አምባሳደር ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለአማጽያን ያስተላለፉት የሰላም ውይይት መልዕክት እንደተባለው የፖሊሲ ለውጥ ይሁን አይሁን ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውም በበርካቶች አነጋጋሪ ሆኖ በመገኘቱ በዚህ ረገድ የግሌን ሃሳብ ፈንጠቅ ለማድረግ ፈለግሁ።

የቅርቡ የአሜሪካ አምባሳደር ንግግር የፖሊሲ ለውጥ ነውን? 

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ሚስተር ኤርቪን ማሲንጋ ግንቦት 7 ቀን 2016 ዓ̦ ም በአሜሪካ ግቢ በድሮው የአሚሪካን ሌጋስዮን ጽ/ቤት በመገኘት በአሜሪካ ኤምባሲ ድጋፍ የተደረገውን የሕንጻ ዕድሳት መጠናቀቅን ምክንያት በማድረግ በተዘጋጀ ልዩ ስብሰባ ንግግር አድርገዋል። ይህ ንግግራቸው በሦስት መሠረታዊ ፍሬ ነገሮች ላይ ያተኮረ ነበር። አንደኛው ስለየካቲት 12 የሰማዕታት ዕለት߹ ሁለተኛው ስለኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ እና ሦስተኛው ለኢትዮጵያ ችግር መወገድ ምን መደረግ እንዳለበት እና ስለሁለቱ አገሮች ግንኙነት የሚዳስስ ነበር። በንግግራቸው ከፍተኛ ትኩረት ከሰጡት መካከል የየካቲቱ 12 ሰማዕታት ቀን ትውስታ ነው ። ከትውስታም አልፎ ድርጊቱን ካለንበት ሁኔታ እና ከመፍትሄ ጋር በማያያዝ ነው። 

እ᎐ኤ᎐አ በ1937 የፋሽስቱ ጣልያን ወራሪ ኃይል በአዲስ አበባ በሦስት ቀናት ውስጥ ከ20,000 በላይ ንጹሐንን ግፍ እና ጭካኔ በተመላበት ኢትዮጵያውያንን በገደለበት ወቅት የአሚሪካ ሌጋሲዮን ጽ/ቤት ኃላፊ – ጉዳይ ፈጻሚው ሚስተር ኮርሚልስ ቫን ኤንገርት 750 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያንን በግቢያችው በማስጠለል ከሞት ማዳናቸውን እና ይህም የሆነው የዛሬ 87 ዓመት መሆኑን እና የአሁኑ ትውስታ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት 120 ዓመት ባስቆጠረበት ወቅት መሆኑን ገልጸዋል። በዚሁ ንግግራቸው አሜሪካኑ ጉዳይ ፈጻሚ በቆራጥነት ለኢትዮጵያውያኑ በሕይወት መኖር ሰብዓዊ መብታቸው እና ለክብራቸው መጠበቅ ያደረጉትን ተጋድሎ በአድናቆት በማስታወስ ሁሉም ከዚህ ከየካቲቱ 12 የሰማዕታት ዕለት ትምህርት መቅሰም አስፈላጊ እንደሆነ በአጽናኦት አሳስበዋል። 

አምባሳደሩ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታን በተመለከተ በአገሪቱ ያለውን የእርስ በርስ ግጭቶችና ጦርነቶች፡ የዜጎች ሰብዓዊ መብት መጣስ፡߹መገደል߹ያለፍርድ መታሰር߹መሰወር ߹ ጾታዊ ጥቃቶች እና ሌሎች ችግሮችና ተግዳሮቶች መኖራቸውን በመጥቀስ መንግሥት እና ተፋላሚ ኃይሎች ማለትም የኦሮሞ ነጻ አውጭ ሠራዊት߹ ፋኖ እና ሕውሃት ወደ ሰላማዊ ውይይት መምጣት አስፈላጊነትን በማንሳት እና ከየካቲቱ 12 ሰማዕታት ውጤት መማር አስፈላጊነትን አስረግጠው ተናግረዋል። ለ120 ዓመታት የፈተና እና የደስታ ጊዜያትን የተሻገረው የሁለቱ አገሮች ግንኙነትም እየተጠናከረ እንደሚቀጥልና የሚመለከታቸው አካላት ለሰላማዊ መፍትሄ መገኘት የአሜሪካ መንግሥት የበኩሉን ድጋፍ እንደሚያደርግ አሳውቀዋል። 

ከዚህ መሠረታዊ ሀሳብ መነሻነት እና የዛሬ 33 ዓመት ግንቦት 1983 ዓ᎐ም የተከሰተውን ክስተት ምክንያት በማድረግ የዶቼቬላ ሬዲዮ አወያዩ እንደመንደርደሪያ ያቀረቡት ሃሳብ ለመረዳት እንደሞከርኩት በአጭሩ በወርሃ ግንቦት 1983ዓ᎐ም የአሜሪካ መንግሥት አማጽያኑን ቀጥታ ወደ አዲስ አባባ እንዲገባ አድርጎ አሁን ደግሞ አማጽያኑ ከመንግሥት ጋር እንዲወያዩ በአምባሳደራቸው አማካኝነት አስነገሩ። ይህም የአሜሪካ መንግሥት የፖሊሲ ለውጥ ማድረገን የሚያሳይ ነው የሚል ነበር። እውን ይህ የፖሊሲ ለውጥ ያሰኛልዎይ? የሚለውን ለመመለስ ፖሊሲ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን በአጭሩ መዳሰስ ያሻል። 

የአገራት የውጭ ፖሊሲ ከራስ ብሔራዊ ጥቅም አንጻር በሁለትዮሽ፡ በአሕጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሊኖር ስለሚገባ ግንኙነት መስፈርት እና የተግባር መመሪያ የሚሆኑ አጠቃላይ መርሆዎችን የያዘ ማለት ነው። የውጭ ግንኙነት መርሆዎች በአሕጉራት ደረጃ ለምሳሌ በአፍሪካ ሕብረት እና በዓለም አቀፍ ደርጃ ደግሞ በዋናነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባላት ስምምነት የተደረገባቸውን የሚያመላክት ሲሆን በአገራት ደረጃ ደግሞ በዋናነት በጥቅሉ በየአገራቱ ሕገ መንግሥታት እና በዝርዝር በውጭ ግንኙንት ፓሊሲዎች በመርህነት ስልታዊ ዘዴን አቀናጅቶ በብሔራዊ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ከአጭር߹ ከመካከለኛ እና ከረጅም ጊዜ አንጻር ከስልታዊ ፍላጎት አኳያ ተተንትነው የሚቀርቡ ናቸው። 

ከአንደኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጀመሮ እና በተለይም በቀዝቃዛው ጦርነት መፋፋም በተያያዘ እና አሁንም ዓለማችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አኳያ የትናንቶች ኃያል አገራት አሜሪካ እና ሶቭዬት ሕበረት ዛሬ ደግሞ ተፎካካሪ አካላት አሜሪካ߹ሩሲያ߹ ቻይና በዋነኝነት እና በኃያሏ አሜሪካ ቁጥጥር ያሉ የተላያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በዓለም አቀፍ የጋራ ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ በሰብዓዊ መብት መከበር߹በስደተኞች߹በአካባቢ ጥበቃ߹በኑከሌር ጦር ማምረት ቅነሳና ዕቀባ እና በተለያዩ ጉዳዮች ያሉ እንቅስቃሴዎች መደበኛ የአገሮችን የግንኙንት የፖሊሲ አተገባበር ፈተና ላይ የጣሉ ለመሆናቸው አሌ የማይባል ሀቅ ነው። 

ወደርዕሰ ጉዳዩ ስንመለስ አሜሪካ የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት߹ ነጻነት እና የግዛት አንድነት እንደምታከብር በየጊዜው የምትገልጸው አንደኛው የቋሚ ፖሊሲዎ መገለጫ ነው። ሌላው ሁሉም በአገራት ደረጃ እና በጋራ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል አገሮች ጋር የሚጋሩት የውጭ ፖሊሲ አንዱ በሌላው የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት እና በአገራት ውስጥ ሆነ በአገሮች መካከል የሚነሱ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ መደገፍ በዋናነት ከሚጠቀሱት የፖሊሲ መርሆዎች መካከል ይገኙበታል። አሜሪካ በዋናነት የኢትዮጵያን ሕዝብ አንድነት߹ነጻናትና የግዛት አንድነት የማክበር ፖሊሲዋን የጠበቀች ሲሆን፤ ከቀዝቃዛው ጦርነት እና ከራስ የበላይነት ስሜት አንጻር በተለያዩ ጊዜያት ፖሊሲዋን የሚጻረሩ አቋሞችን ማሳየቷ የማይታበል እውነታ ነው። 

በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በመላ የአፍሪካ ቀንድ በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና በአንድ ወቅት የዓለም መሪዎች ኮሚቴ ሰብሳቢ በነበሩት በሄኒሪ ኪሲንጀር አማካኝነት አገራቱ በራሳችው እንዳይቆሙ እና ከጥገኝነት እንዳይላቀቁ ለማድረግ እና አሜሪካ በማትፈልገው የሶሻሊስት ርዕዮተዓለም መግቢያ ምቹ እንዳይሆኑ እርስ በርስ በጎሳ እየተናቆሩ ድህነታችውን እያጣጥሙ – ድህነት ይጥም ይጣጣም ይመስል እንዲቀጥሉ ማድረግ አንደኛው ሥልታዊ ዘዴ እንዲሆን ያቀረቡት ጥናት በአሚሪካ ፖሊሲ ላይ ከፍተኛ ጥያቄ ማስከተሉ እና በአሜሪካ እና በአገሮች መካከልም የግንኙንት የጥርጣሬ ሳንካን መፍጠሩ አልቀረም። እንዲያም ሆኖ አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት ያደረገችው ጣልቃ ገብነት እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰብዓዊ መብት አስከባሪነት ቆሜያለሁ እያለች በሰብዓዊ ጥሰት ሰበብ በኢትዮጵያ ላይ የጣልቃ ገብነት ተግባር እና ብድር እና ዕርዳታን በመከልከልና በማስከልከል ኢትዮጵያን የሚጎዱ ሥራዎችን ፈጽማለች፤ አስፈጽማለችም። 

እዚህ ላይ ሊጠቀሱ ከሚገቡ ክስተቶች መካከል በደርግ ጊዜ ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት ጊዜ የቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት የከፈለበትን የጦር መሣርያ መከልከሏ፤ የአገሪቱ መንግሥት ከተከተለው የሶሻሊስት ሥርዓት ምክንያት ከሰብዓዊ ዕርዳታ በስተቀር ለልማት የሚውል ብድር እና ዕገዛ መከልከሏ እና ማስከልከሏ፤ የአማጽያን ኃይሎችን መደገፏ እና በእራሷ እና በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት እና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ድጋፍና ዕገዛ ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ የመንግሥት ሥልጣንን የተቆጣጠረው ሕውሃት በየትኛውም ሥርዓት ይሁን ለሰው ልጅ እና በፖለቲካ አምክኗዊ አመለካከት ዘመኑን የማይመጥን ጸረ ዲሞክራሲ እና ኢሰብአዊ የጎሣ ፌዲራሊዝምን ሥርዓት ዘርግቶ በኢትዮጵያውያን ላይ መጠነ ሰፊና ግዙፍ ግፍና በደል ሲፈጽም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዓመታዊ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ላይ ከማንጸባረቅ በስተቀር በራሱ ሊተገብር ያወጣውን ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊነት የማስጠበቅ ፖሊሲ ወደ ጎን ትቶ ዕርዳታና ዕገዛውን ለገዥው መቀጠሉ በዋናነት የሚጠቀሱ የአድልኦ እና የጣልቃ ገብነት አቋማዊ ተግባሮች መሆናቸው እሙን ነው። 

ከላይ እንደተጠቀሰው ኢትዮጵያን በቀጥታ በተመለከተ የአሜሪካ መንግሥት በጣልቃ ገብነት߹ በአድሎአዊነት እና ከዲሞክራሲያዊ እና ሰብዓዊ መብት ከማስከበር ዓላማ ርቆ መታየቱ ቢያንስ በታሪክ ተጠያቂ መሆኑ አከራካሪ አይደልም። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ ከመቀየር የመጣ አይደለም። የአሜሪካ መንግሥት እንደ ፖሊሲ የኢትዮጵያን አንድነት እና በፈለገችው የፖለቲካ ሥርዓት የመመራት መብትን ማክበሯን እና የውስጥ ችግሮች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ የመፈለግን እና በሂደትም ተግባራዊ ተሳትፎ የማሳየት ጥረትን ከመግለጽ ቦዝናለች ማለት አይቻልም። ግን የፖሊሲ ለውጥ ሳይኖር የተገበረቻቸው ሥራዎች ማለትም የወሰደቻቸው አቋሞች ፖሊሲ ተጻራሪ ሆነው መገኘታቸው የሚያከራክር አይመስለኝም። አቋሞች አልፎ አልፎ ከአገራዊ ብቻ ሳይሆን ከአሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፖሊሲ ጋር ተጻረው መገኘት የተለመደ ነው። ይህም የሚሆንበት ምክንያት ልዕለ ኃያላን መንግሥታት በአንድ በኩል የግል ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር ሲባል በራስ በሚደረግ ጥናት በኃይል ሆነ በአጠቃላይ ቁመናዊ ግምገማ በመንግሥት ሥልጣን የወጣ ወይም ሊወጣ እና ሊቀጥል የሚችል እና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ቅንና ሥልጡን ታዛዥ የሚሆንን በመምረጥ የሚወሰድ የተዛነፈ አቋም ነው። በሌላ በኩል ከዓለም አቀፋዊ የፉክክር ሁናቴ አንጻር በየአገራቱ እና በየአካባቢው በፖለቲካዊ߹ ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እሳቤ የበላይነትን ይዞ ከመቀጠል ፍላጎት ጋር የተዛመደ የልዕለ ኃያልነት ሥልታዊ ዘዴ ውጤት ነው ማለት ይቻላል። 

ከዚህ አጠቃላይ ሥዕላዊ ዕይታ በመነሳት የአሁኑ የአምባሳደሩ ንግግር ካለፉት አቻዎቻቸው ለየት ብለው የተገኙበት አንደኛውና ትልቁ ነገር ወይም የአሜሪካ መንግሥትን አተያይ የለወጠ ነው የሚያሰኘው የአገሪቱን ችግር በስፋት መገንዘቡ እና በተለይም በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ የአማራውን ሰቆቃ እና ከሰቆቃው አንዲላቀቅ ትግል ለሚያደርገው ኃይል ፋኖ ዕውቅና መስጠቱ እና ብሎም እንደሌሎቹ አማጽያን ለሰላማዊ ውይይት መጋበዙ ነው። ይህ የነበረን ውስን እና የአድልኦ አመለካከት ያስወገደ ችግርንና ፈተናን ለአንድ አካባቢ አድርጎ የነበረን እሁን ለሁሉም አድርጎ መገኘቱ ነው። አምባሳደሩ እራሳችሁን ፋኖ የምትሉ ቢሉም በመሠረቱ ሌሎችም የሚጠሩት እራሳቸው ባወጡት ስም ስለሆነ አጠቃቀሙ ባላስፈለገ ነበር። ይልቁንስ እንኳንም “ፋኖ ተባዮቹ” አላሉ። ግራ ነፈሰ ቀኝ የአሜሪካ መንግሥት የፋኖን አገራዊ ሚና ማወቁ ከፍተኛ የአቋም ለውጥ ማምጣቱን የሚያሳይ እንጂ የፖሊሲ ለውጥ ማምጣቱን አይደለም። 

ከዚህም በተጨማሪ በ1983 ዓ᎐ም ውይይት ከልክለው (ከልክለው ባያሰኝም) አሁን ውይይት መጋበዛችው የፖሊሲ ለውጥን የሚያመላክት ሳይሆን የተጨባጭ ሁኔታን መሠረት ያደረገ የአቋም ለውጥ ነው። በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ የሶሻሊዝምን ጎራ የተቀላቀለችውን ኢትዮጵያ ከሶቭይት ሕብረት መዳፍ ውስጥ ለማላቀቅ የሥርዓቱን ቁንጮ ማውረድ ዋንኛ ዓላማ በማድረግ ለዚሁ ዓላማቸው መሳካት ከአገራዊ ወይም ብሔራዊ ስሜት ውጭ እናራምደዋለን ያሉትን የሶሻሊስት (የሕውሐት የአልባንያ ኮሚኒዝም ጭምር) ርዕዮተ ዓለም በቀላሉ ለማስወገድ እርግጠኛ ለሆኑባቸው ሻዕቢያ እና ሕውሀት ሁለገብ ድጋፍ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወቃል። በቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ እና የሶሻሊዝም ሥርዓት መፍረስ በኋላ አሜሪካ እነዚህን ድርጅቶች ካላንዳች ተገዳዳሪ እየረዱ߹ እያፈረጠሙ ሲሄዱ የኢትዮጵያ መንግሥት እራሱን እየበላና እያዳከመ ሲመጣ የዓለም ሁኔታ ለሻዕቢያ እና ለሕውሀት ሠርግና ምላሽ ሆነላችው። ድል በድል ሰተት ብለው የማዕካላዊውን መንግሥት ለመጣል በተቃረቡ ጊዜ ቢሆንም ሽምግልናው ቀደም ተብሎ ተጀምሯልና እስከ ሎንዶኑ ቀጠሮ ተደረሰ። የሎንዶኑ ቀጠሮ ሁኔታዎች ሁሉ ምስቅልቅል የሆነበት አገሪቷ ያለመሪ የቀረችበት ጊዜ በሚያሰኝ ሁኔታ ላይ ነበረች። ፖለቲካው እየተወራ ቀደም ብሎ ሻዕቢያ ኤርትራን ሙሉ በሙሉ ሲቆጣጠር ሕውሀት ደግሞ አዲስ አበባ ሰተት ብሎ ገባ። ጨዋታው ፈረሰ አባይ ደፈረሰ ሆነና ነገሩ ሕውሀት አዲስ አበባን ተቆጣጥሯልና የስብሰባው ፋይዳ ምን ላይ ነው በሚል የታሰበው ውይይት ሳይደረግ ቀረ። እውነታው ይህ ነው። 

የትግሉ ፍልሚያ እና የውይይት ጨዋታው ያለቀው ቀድሞ ነውና የአሜሪካ መንግሥት ለህውሃት አዲስ አበባን እንዲቆጣጠር መከረ ሳይሆን ፈቀደለት አንዳንዴም አደረገ የሚለው አባባል ከአገራዊ ዕይታ እና ከተጨባጭ ሁኔታው አንጻር አባባሉ ውሃ አይቋጥርም። ያኔ የመንግሥት ኃይል የመገዳደር አቅም ቢኖረው እና ለትንሽ ጊዜም ቢሆን ኃይሉ እንደቀላል የማይታይ ሆኖ ቢገኝ ኖሮ ውይይቱ ከዚያም ድርድሩ በተካሄደ ነበር። 

የያኔውን ሁኔታ በአጭሩ ስንቃኝ የምንረዳው ሻዕቢያ ለመገንጠል የበቃው እና ኢትዮጵያ ከወገኗ ከአካሏ የተለየችው እና ወደብ አልባ የመሆን ድምር ውጤት የአሜሪካ የፖሊሲ ውጤት ሳይሆን ሻዕቢያ ከሕውሃት ጋር ባደረገው በጋራ የተቀናጀና የተጠናከረ ፍልሚያ፤ በአገር ውስጥ ሌሎች ተመሳሳይ የእርስ በርስ ጦርነቶች እና ውስብስብ የተፈጥሮ እና ሰው ሠራሽ ችግሮች በስፋትና በግዙፍ ሁኔታ መስፈን፤ የቀዝቃዛው ጦርነት መገባደድ ያስከተለለት ዕድል፥ ከቅርብና ከሩቅ የኢትዮጵያ ‘ወዳጆች’ የተባሉ ጭምር ሳይቀሩ ያልነጠፈ የውጭ ድጋፍ፤ ሕውሀት መንግሥት ሆኖ ከሜዳው ትግል ባሻገር በአሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ መድረኮች እንዲሁም በአገር ውስጥ ውሳኔ ሕዝብን በማመቻቸት የሰጠው ሙሉ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በባለቤትነት በአመራር ያደረገው የማስገንጠል የማስፈጸም ተልዕኮ እና በአጠቃላይም የኢትዮጵያ መንግሥት የሕዝብን ድጋፍ አጥቶ የተጓዘበት የድካም እና ውድቀት ድምር ውጤት መሆኑ መዘንጋት የለበትም። የሕውሀት/ኢሕአዴግ ወደመንግሥት ሥልጣን እርከን መውጣትም ከዚህ አጠቃላይ ሁኔታ የተለየ አይደለም። በዚህ ሂደት ልዩ እና መሪ የነበራቸው ኸርማን ኮኸን እራሳቸው በሰጡት ምስክርነት በወቅቱ ለሕውህት]ኢሕአዴግ መሪ መለስ ዜናዊ የአሰብ ወደብን እንዲያስቀሩ መምከራቸው እና ተቀባይነት ያለማግኘታቸውም መዘንጋት አይኖርበትም። 

ከላይ በአጭሩና በጥቅሉ እንደተመለከተው አሜሪካ የደርግ መንግሥትን ለመጣል የወሰደውን አቋም እና የተለያዩ እርምጃዎችን እንደፖሊሲ አድርጎ መመልከት ይከብዳል። ወደ አሁኑ ሁኔታ ስንመለስ ላለፉት አምስት ዓመታት ሕውሀት በፌዴራሉ መንግሥት ላይ አምጾ ያልተጠበቀ እርምጃ ከመወሰድ አልፎ በአማራ እና በአፋር ግልጽ ወረራ በፈጸመበት ወቅት ፋኖ በግብታዊነት መልኩ ተደራጅቶ ከመከላኪያ ኃይል ጋር የተቀናጀ የመከላከል እርምጃ ወስዶ በመንግሥት በጀግንነት ተግባሩ ዕውቅና ማግኘቱ ይታወሳል። ይሁንና ብዙም ሳይቆይ መንግሥት ፋኖ በትግሉ የታጠቀውን መሣሪያ ለማስፈታት የወሰዳቸውን ቆስቋሽ እርምጃዎችን ተቃውሞ ተነሳ። የትግል አድማሱን አስፍቶ የወጣው ፋኖ ስሙ ገኖ ቢገኝም የአሜሪካን መንግሥት ጆሮ ሳያገኝ ቆይቷል። ፋኖ ዛሬ በጥንካሬው የታወቀና ለኢትዮጵያ መጭ ዕድል ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ ሲታወቅ ከሌሎች አማጽያን ጋር የመጠራት እና ተሳትፎው አስፈላጊ መሆኑ በአሜሪካ መንግሥት መታመኑን ያሳያል። በተጓዳኝ የአሜሪካ መንግሥት ከአንድ ክልል ትኩረት ወጥቶ በመላ አገሪቱ ያለውን ችግር ታሳቢ በማድረግ በሁሉም ቦታ የታጠቁ አማጽያን ከመንግሥት ጋር ለሰላማዊ ውይይት እንዲቀራረቡ ጥሪ መደረጉ በነበረ ፖሊሲ ላይ የአቋም ለውጥን እንጂ የፖሊሲ ለውጥን የሚያሳይ አይደለም። በመሆኑም፤ የአምባሳደሩን ንግግር የፖሊሲ መግለጫ ያሰኘው የኢትዮጵያ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያለውን የቆየ ፖሊሲ በማሰማታቸው ነው። 

ለዚህ አባባል ማረጋገጫዎች በርካታ ቢሆኑም በጥቂቱ ለመጥቀስ ያህል ሚስተር ማሲንጋ ከአሁኑ የአሜሪካ ግቢ ንግግር ቀደም ሲል አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ችግር በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ አድርገዋል። ከዚህም ሌላ አሜሪካ በቀድሞ ፕሬዚዴንት ካርትር ሽምግልና በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሻዕቢያ መካከል በአትላንታ የካርተር ማዕከል ውይይቶች ተካሂደዋል። ካለአሜሪካ ተጽዕኖ ተደረገ የማያሰኝ በጣሊያን መንግሥት ሸምጋይነትም በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕውሐት መካከል አንዴም ቢሆን በሮማ ውይይት ተካሂዷል። ይህ ሁሉ የሚያሳየው አሁንም የአሜሪካ መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ ለውጥ ማድረጉ ሳይሆን የአቋም ለውጥ ማድረጉን ነው። 

የዚች አጭር መግለጫ ዓላማ ለክርክርነት ሳይሆን በዚህ ዙሪያ የተጣራ አቋም ይዞ መገኘት ለተሻለ ውይይት እና መግባባት ብሎም የተሻለ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ለመሥራት ያስችላል የሚል እምነት ስላለኝ ነው። 

ቀጣዩ ሥራ ምን ሊሆን ይገባል? 

ለሁሉም ስኬት ሆነ ድክመት ወይም ኪሳራ ወሳኙ በአገር ውስጥ የሚሠራው ሥራ ወይም ትግል ሲሆን በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ወዳጆች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ ነው። ከዚህ አኳያ ትኩረት ሊሰጣቸው የሚገቡ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ። አንደኛው የአምባሳደር ማሲንጋን ንግግር በአውንታዊ መልኩ መመልከት ሲሆን፤ ሁለተኛው ለውይይት ተሳትፎ የተጠሩት ሁሉ ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ ጥንካሬን ይዘው እንዲገኙ ማድረግ ነው። ሦስተኛው እና ዋናው በሁሉም ወገን የውይይቱ መቋጫን ገዥ ዓላማን ለይቶ እና አንጥሮ መገኘት ነው።

እነዚህ ከላይ የተጠቀሱትን እንደሚከተለው ለመዳሰስ ይሞከራል፤ 

1.የአምባሳደር ማሲንጋን መልዕክት በተመለከተ – አምባሳደር ማሲንጋ በአዲስ ዓመት ያስተላለፉትን የሰላም ጥሪ እና እንዲሁም ከየካቲት 12 መስዋዕትነት ጋር በማዛመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ በበጎ መመልከቱ ፖለቲካዊ ሆነ ዲፕሎማሲያዊ ጠቀሚታው የላቀ ነው። አሜሪካ ያላትን ተደማጭነት እና ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ከፍርሃት ሳይሆን ከመርህ አኳያ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስጠበቅ እንዲቻል ከመርህ አኳያ ጥሪውን ከአንድ ወዳጅ አገር ተወካይ እንደሚጠበቅ አድርጎ መቀበሉ ተገቢ ይመስለኛል። ይህም ሲባል ያሉትን ሁሉ እንደወረደ መቀበል ሳይሆን አጠቃላይ ይዘቱን በሚዛን በማስቀመጥ ሊሆን ይገባል። ከላይ እንደተጠቀሰው አንዳንድ የጠቀሷችውን አባባሎች እና ለመፍትሄ በሚል የጠቀሷቸው እንደሽግግር ፍትህ እና የአገራዊ ምክክር ዓይነቱን በራስ መንገድ ማየት እና የሚበጀውን መያዝ የራስ ሥራ እንጂ ሁሉንም የምንፈልገውን እና የሚመቸንን ይጥቀሱልን ብሎ መጠበቁ ተገቢ አይሆንም። 

2.ለውይይት ተጠናክሮ መገኘት – ለአንድ አገር ችግር ሰላማዊ መንገድ ለመሻት በመንግሥት ወይም በውጭ ኃይሎች የሚደረግ የውይይት ጥሪ ተግባራዊ ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። የውይይት ጉዞ ቦታው ላይ ሳይደረስ በአንደኛው ወገን የኃይል የበላይነትን በማግኘት በእምቢተኝነት ሳይደረግ ሊቀር ይችላል። ለምሳሌ በሎንዶን የጨነገፈው የመንግሥትና የወያኔ/ሻዕቢያ ውይይት በምሳሌነት ሊጠቀስ ይቻላል። በአንድ ወቅት በላይቤሪያ የውይይት ጉዞ በግልበጣ የተጨናገፈውን ማንሳት ይቻላል። ከተፋላሚዎች መካከል አንደኛው ወገን ሲዳከም የይስሙላ የሰላም ውይይት እና ድርድር ሊደረግ ይቻላል። ይህ ደግሞ ውይይት ሆነ ድርድር ሳይሆን ተሸናፊን አሸናፊው ወገን ያቀረበውን ስምምነት ሳይወድ በግድ ማስፈረም ማለት ነው። በአንደኛው እና በሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች በናዚ ጀርመን እና በእነ አሜሪካ ወገን የተደረጉት ስምምነቶች ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው። በደቡብ አፍሪካ በኒልሰን ማንዴላ መሪነት የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግሬስ እና በዴ.ክሌርክ የሚመራው የመንግሥት አካል የተደረገ ውይይት በመልካም ውጤት ተጠናቋል። ብሎም በአፓርታይድ የዘረኝነት የፖለቲካ ሥርዓት ለዘመናት የቆየን ጦርነት፥ ግጭት፥ ዕልቂት እና ስደት ለማስቆም አስችሏል። በሌላ መልኩ ደግሞ የአገርን እና የሕዝብን አንድነት߹ ጥቅም እና ፍላጎት ለሚያሳጣ  ውይይት እና ድርድር ተቀባይነት ያለመኖሩን በሂደት በመረዳት ወሳኝ እና ቆራጥ ውሳኔ በመውሰድ ሂደቱን በማቋረጥ የአሜሪካ መንግሥት ለአምስት ዓመታት ያህል በኮንፌዴራሊስቶች ላይ የወሰደው እርምጃ በታሪካዊነት እና በአስተማሪነት የሚወሰድ ትልቅ ተግባር ነው። በአጭሩ በዓለማችን ሌሎች በርካታ ውይይቶች በአስገዳጅ ሁኔታዎች የተደረጉ ውይይቶች በስኬትም በውድቀትም የተመዘገቡ አሉ።

ትልቁ ቁም ነገር ግን ጦርነት እና ግጭቶች በአብዛኛው የብሶት እና የቁጭት፤ የነጻናት እና የህልውና ማስከበር ፍላጎት ውጤቶች መሆናቸው ከግንዛቤ ሊወሰድ ይገባል። በአብዛኛው ጦርነቶች አማራጭ በመታጣቱ ያለውድ በግድ የሚገባባቸው አላስፈላጊ አረንቋዎች ናቸው እና ችግሮችን በቀና ልቦና ይሁን በመሠሪነት ወይንም በመዳከም ምክንያት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት ለሚቀርብ ጥሪ ከየትኛውም ወገን ከመርህ አንጻር መቀበሉ ጉዳት የለውም። በመሠረቱ፤ ከድክመት ሳይሆን ከጥንካሬ በሚመነጭ እና ጥንካሬውም ለውይይት ጥሪ ምክንያት መሆኑን የተረዳ ወገን ለውይይት ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ መስጠት ፖለቲካዊ ብስለትን ያመለክታል። 

ውይይት ይደረግ ስለተባለ ተንደርድሮ ይገባበታል ማለት አይደለም። ለውይይት ምንጊዜም ዝግጁ መሆን እና የውጭ መካሪዎችን ሀሳብ መቀበል ለበለጠ መተዋወቅ እና እምነት ማሳደር ይጠቅማል። እዚህ ላይ ትልቁ ቁም ነገር በውይይት በአሽናፊንት ለመውጣት በሚያስችል መልኩ ተጠናክሮ መገኝትን ይጠይቃል።  ለመወያየት በቅድሚያ በሁሉም ፈርጅ ሳይዘናጉ ተጠናክሮ መገኘትን የሚጠይቅ እና ዝም ብሎ የሚገባበት አይደለምና ለውይይት በምን መልኩ? በምን አጀንዳ? ፋይዳው? እንዴት? መቼ? እና የት? የሚሉትን እና የመሳሰሉትን እያብሰለሰሉ ለውይይት ከመቅረቡ በፊት ሊነሱ የሚገቡ ቅደመ ሁኔታዎችን ማዘጋጀትን ይጠይቃል። ለዚህም የእራስን ፖለቲካዊ አመለካከትና አቋምና ድርጅታዊ አደረጃጀት ከዓላማ እና ከመዋቅራዊ ብቃት አንጻር መዘጋጀት ግድ ይላል። ተጠናክሮ የውይይት ብሎም የድርድርን ጥያቄ መቀበል ደግሞ የድክመት ምልክት ሳይሆን የጥንካሬ ምልክት መሆኑን በሚያረጋግጥ መልኩ ሊሆን ይገባል። ይህም ማለት ባጭሩ አገራዊ ተጨባጭ ሁኔታን በሚገባ ተገንዝቦ እና የተቃራኒ ወገንን ጠንካራ እና ደካማ ጎንን ገምግሞ በአንጻሩ የራስን ፖለቲካዊ እና ዲሞክራሲያዊ ጥንካሬን ማጎልበት ብሎም ዓለም አቀፋዊ ሁኔታን በሚገባ ማጤን ያስፈልጋል። 

3.ገዥ ዓላማን እና መቋጫን መለየት – ኢትዮጵያ ከተዘፈቀችበት አስከፊ እና አደገኛ ሁኔታ እንድትላቀቅ ገዥ አጀንዳን ይዞ መገኘት ወሳኝ ነው። ለውይይት የሚቀርቡ አካላት ከግል ፖለቲካዊ ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ተላቀው በአገራዊ ራዕይ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በቁርጠኝነት ለገዥ ዓላማ እና የመፍትሄ አቅጣጫን ይዞ መገኘት ወሳኝ ነው። ይህም እዚህ እዚያ የሚያሰኝ አይደለም። ውይይትን እና ድርድርን በዘፈቀደ ለማድረግ ሳይሆን ችግሩን በዘለቄታዊነት ለመፍታት የሚያስችልን በሕዝብ ዘንድ ቅቡልነት ያለውን የትግል ዓላማ አንግቦ መገኘት ወሳኝ ነው።

በመሆኑም ፥ በስመ ዲሞክራሲ ሁሉንም ባሳተፊ በሚል መልኩ ወንዝ ያማያሻግሩ ሀሳቦችን ይዞ ጊዜን ማባከን ሳይሆን የውይይቱ ሆነ የድርድሩ ዓላማ ለችግሮች ቋሚ እና ዘላቂ መፍትሄ ከመሻት ጋር የተገናኘ መሆን አለበት። በዚህም፤ ለአገራችን ውስብስብ ችግሮች ዋንኛ መንስዔ የጎሳ ፖለቲካ- የጎሳ ፌዲራሊዝም ስለሆነ በዚህ ዙሪያ የተጠናከረ ሃሳብ߹ ሀተታ እና አቋም ይዞ መገኘት እና መታገል ያስፈልጋል። በስመ ዲሞክራሲ ያለ የሌለ ሀሳቦችን በማንሸራሸር እና አላስፈላጊ መወሳሰብን በማምጣት ወሳኝ እና አስተማማኝ  

መፍትሄ ማግኘት አይቻልም። ስለሆነም፤ በዚህ ዙሪያ ተጠናክሮ መገኘት ግድ ይላል። በምንም ዓይነት ለአገር እና ለሕዝብ ዘለቄታዊ ጥቅም ለማይሆን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በተግባር ወደላቀ ከፍታ ለማያደርስ ዓላማ መሰለፍ በታሪክ የሚያስወቅስ ግዙፍ ስህተት እና በሕዝብ እንደመቀለድ ያስቆጥራል። ከጠረጴዛ ዙሪያ የሚገኝ ውጤት የኢትዮጵያን አንድነት߹ ነጻነት እና የግዛት አንድነትን የሚያስጠብቅ እና ብሎም ገናና ታሪኳን የሚያድስ መሆን አለበት። የውይይት መዳረሻ ምንነትም የሚገለጸው በዚህ መልኩ ነው። 

እንደማጠቃለያ – ለኢትዮጵያ ችግር መወገድ ከውጫዊው ግንኙንታችን እና ከውስጣዊ ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በጣም ባጭሩ መቃኘቱ አይከፋም። 

የውጭ ግንኙነታችን በተሻለ መነጽር ዕይታ እንዲቃኝ ማድረግ መልካም ነው። አንዳንድ የውጭ አገራት መንግሥታት እና ኃይላት በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ፖሊሲ ሳይቀየሩ ግን የየራሳቸውን እና ዓለም አቀፍ ፖሊሲዎችን በሚቃረን መልኩ ኢትዮጵያን በተሳሳተ አቋም ለኢትዮጵያ መዳከም አሉታዊ አስተዋጻኦ የሚያደርጉትን ድርጊታቸውን እንዲያቆሙ በተቻለ መጠን የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፖለቲካዊ እና ዲፐሎማሲያዊ ሥራዎች መሥራት ያስፈልጋል። እንዲሁ በተለመደ አነጋገር እነሱ ያወቁታል፤ መች አጥተውት ነው! ከማለት ይልቅ ከራስ የሚጠበቅን መወጣት ያሻል። 

ለምሳሌ ለዓመታት በጥቂት የተወሰኑ የአሜሪካ ባለሥልጣኖች አሳሳችነት የአሜሪካ መንግሥት የሚያሳየውን የተሳሳተ አቋምን እንዲያስተካክል መወትወቱ ተገቢ ነው። እ,ኤ.አ ከ1860 እስክ 1865  የተካሄደው የአሜሪካ የርስ በርስ ጦርነት ለሚሊዮኖች ሞት እና ለሚሊዮኖች የጦር ጉዳተኝነት ያደረሰው ምክንያት ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር ተመሳሳይ ነው። ጦርነቱ በዋናነት በአንድ ወገን ባርነትን ለማስወገድ እና የአገሪቱን አንድነት ለማስቀጠል በተነሳው የአንድነት ኃይል – የአሜሪካ ማዕከላዊ ወይም ፌዴራላዊ መንግሥት – እና በሌላ ወገን ደግሞ ባርነትን ለማስቀጠል በፈለጉ ተገንጣይ ኮንፌዴራሊስቶች መካከል ነበር። በኢትዮጵያድ ያለው ሁኔታም ችግሩ ከአሰላለፍ አኳያ ዝብርቅርቅ ያለ ቢሆንም “በአንድ ጥቁር ሕዝብ-

በአንድ ወገን- መካከል የዘረኝነት” ፖሊሲን በመዘርጋት እና በመደገፍ መገንጠልን ዓላማ ባደረጉ በአንድ በኩል እና በሌላ በኩል ደግሞ በአንድነት ኃይሎች መካከል ያለ ፍጥጫ እና ግጭት ነው። ለአሜሪካ ልዕለ ኃያልነት ያበቃት አንድነቷ እንደሆነ ሁሉ አሜሪካም በኢትዮጵያ ላይ ያላትን ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ረገድ ኢትዮጵያን ለመከፋፈል የተነሱ ኃይላትን የመደገፍ አቋሟን እንድትተው እና በሚስተር ማሲንጋ የየካቲት 12 ሰማዕታት ቀን ጋር በተገናኘ ያደረጉት ንግግር እና የአዲስ ዓመት መልዕክታቸው መንፈስ መሠረት ኢትዮጵያ በአንድነቷ ሰላሟን አግኝታ ተጠናክራ እንድትቀጥል ለማስቻል የሚመለከታቸው ሁሉ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። 

ጀርመን ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ምሥራቅ ጀርመንን ወደእናት አገሯ መመለሷ እና አውሮፓውያንም የአውሮፓ ሕብረት ከኢኮኖሚያዊ አንድነት ወደተጠናከረ እና የተሟላ ፖለቲካዊ አንድነት እንዲሸጋገር አዝወትረው የሚጥሩት እና የሚገሰግሱት የአንድነትን ጥቅም ጠንቅቀው ስለሚያውቁ ነው። ስለሆነም፤በዚህ አጋጣሚ ለዚህ ጽሑፍ ማነሳሻ የሆነኝ ዶቼቬላ ሬዲዮ እና ሌሎችም ጀርመንና የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊያገኝ የሚችለው እንደራሳቸው ፖሊሲ ሁሉ የኢትዮጵያ የሕዝብ እና የግዛት አንድነት ሲጠበቅ ነውና እንደራሳቸው ሁሉ ትኩረታቸው እና አቋማቸው በዚሁ እንዲቃኝ ጥረት ቢያደርጉ እላለሁ። የኢትዮጵያ አንድነት፥ ጥንካሬ እና ዕድገት ለራሷ ብቻ ሳይሆን በታሪክ እንዳስመሰከረችው ሁሉ ለአፍሪካም ለዓለምም የሚበጅ ነው። 

በአጠቃላይ አገራችን ካለችበት የውድቀት አዘቅት እንድትወጣ፥ ከድህነት አዙሪት እንድትላቀቅ ወደ ትክክለኛው መፍትሄ መግባት አገራዊ እና ሕዝባዊ ሚና እና ግዴታ ወሳኝ ነው። በመሠረቱ፤ ከውጭ የሚቀርቡ ሃሳቦችን ትክክለኝነት አረጋጋጩ߹ተቀባዩ ߹ መራጩና ወሳኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በመሆኑም፥ ከመንግሥት፥ ከተፋላሚ ኃይሎች እና ከምሁራን ሆነ ከማናቸውም ዜጋ ሆነ ለአትዮጵያ ተቆርቋሪ የሚጠበቀው ለሕዝብ የሚቀርብ ገንቢ አማራጭ ሀሳቦችን በአግባቡ አጢኖ ማቅረብ እንጂ የምንፈልገውንና የምንወደውን ብቻ ካላቀረብክ ብሎ ከውጭ ኃይል ጋር አላስፈላጊ አንጃ ግራንጃ መፍጠሩ ጠቃሚነት የለውም። ግን በመርህ ላይ የተመሠረተ ትግል የማድረግ አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው። ለምሳሌ ያህል የአሜሪካ አምባሳደር በአዲስ ዓመት የደስታ መግለጫ እና ካለይ በተጠቀሰው ንግግራቸው እኛ ባለፉት 30 ዓመታት በላይ ከተጠናወተን ጭፍን “የብሔሮች፥ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” የአገላለጽ አባዜ በተለየ መልኩ ኢትዮጵያን እንደ አንድ አገር፤ እንደ አንድ ሕዝብ በመግለጽ እና ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በአካታችነት እና በግልጽነት የሚመለከታቸው አካላት እና ዜጎች ውይይት እንዲያደርጉ ያቀረቡትን ጥሪ በአዎንታዊ መልኩ መቀበል መልካም ነው። ከሃሳቦች መካከል የሚጎራብጥን ደግሞ በራስ መንገድ መፈተሽ እና በጥልቀትና በጥራት የራስ የቤት ሥራን ማከናወን ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል። ይህ በነበረ እና ባለ ፖሊሲ የተገኘን የአቋም ለውጥ አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ይበጃል። 

በየትኛውም መልክ ይሁን ከየትኛውም አቅጣጫ ከውስጥ ሆነ ከውጭ የሚኖር ተጽዕኖ እና ግፊት ቢቀጥልም ብቸኛ እና ዋናው መፍትሄ የሚገኘው በኢትዮጵያ እና በኢትዮጵያውያን ነው። ስለሆነም፤ የሕዝብን ሥልጣን በምርጫ ውክልና የያዘው መንግሥት፥ ውክልናውን በሚገባ አልያዝክም የሚሉ ተቃዋሚና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እና በትጥቅ ትግል የተሰለፉ ኃይሎች߹በተደራጀና ባልተደራጀ መልኩ የሚታገሉ የነጻነት፥የሰብዓዊ መብት እና የዲሞከራሲ ሥርዓት አራማጅና ተሟጋች ኃይሎችና ግለሰቦች እንዲሁም ሃይማኖታዊ፥ ባህላዊ እና ግብረገባዊ እሴትን ተላብሰው የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ በተስፋ የሚጠባብቁ እና የሚጸልዩ እና በሁኔታው ተሰላችተውና ተንገፍግፈው ተስፋ የቆረጡ ዜጎች ጭምር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ እና በሰከነ ሁኔታ በቅንነትና በተቆርቋሪነት ስሜት መነሳት ይኖርባቸዋል። የሕዝብን መከራ ለማስቆም ብሎም ሰላምን ለማስፈን እና ዕድገትን ለማምጣት በአንድነት፥ በወንደማማችነት፥ በእህተማማችነት መንፈስ ከሥልጣን እና ከግል ጥቅም ይልቅ አገርን እና ሕዝብን ማስቀደም አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን ግዴታ መሆን ይኖርበታል። 

በዚህ ዙሪያ ሁሉም ከአጓጉል የእርስ በርስ ንትርክ ተላቆ በየአቋሙ ተከባብሮ ለአገራችን ወደሚበጀው አቅጣጫ መጓዝን መምረጥ ያሻል። እርስ በርስ መነካከስ፤ መወነጃጀል፤ በፖለቲካ ሊቅነት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ከሚል አባዜ ተላቀን የድህነት߹ የድንቁርና እና ሕዝብ ከፋፋይ የሆነን ኋላ ቀር እና አደንዛዥ የጎሳ ፖለቲካን አሽቀንጥሮ መጣል ቀዳሚ ትኩረት የሚሰጠው አጀንዳ ሊሆን ግድ ይለናል። ለትምህርት፥ ለንቃት እና ጥቃትን ለመከላከል ሳይሆን ዕድሜ ልክ እንዲሁ የእነኪሲንጀርን የኃያላንን ሥልታዊ የፍላጎት ማራመጃ ዘዴን እየኮነን ብቻ ግን በወጥመዳቸው እየተጥመለመልን እና የማይዋጡልን አንዳንድ ሀሳቦች ብቅ ሲሉ ደግሞ በእነዚህ ላይ ተጠምደን በጠላቶች ሴራ ተውተብትበን መሽከርከር አይጠቅምም። 

በቅድሚያ የራስ ድክመት ካልተወገደ ከመጠለፍ እና ከመጠላለፍ መዳን አይቻልም። አሁንም፥ ዛሬም߹ ነገም በአገራዊ ራዕይ ዕይታ አንድነትን߹ነጻነትን፥ፍትህን߹ ርትዕን እና ዕኩልነትን ማስፈን የችግሮቻችን መፍትሄ ቁልፍ ነው። ቁልፍ የምንለውም የረጅም ዘመን የነጻነት እና የሥልጣኔ ባለታሪክ የሆነችው አንዲት አገር ኢትዮጵያ፤አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ አንድ የኢትዮጵያ መንግሥት፤ ለሁሉም ዜጋ ዕኩል የሆነች አንዲት እናት ሀገር እና ባለአንድ ታሪካዊ እና የነጻነት አርማ ምልክቷን ባለአረንጓዴ፥ ቢጫና ቀይ ሕብረ ቀለም ሰንደቅ ዓላማ ባለቤት ማለት ነው። የአፍሪካ እናት፥ የአፍሪካ የነጻነት ጮራ ወ.ዘ.ተ ተብሎ በዓለም በውጭ ዜጎች የተዘመረላትን፥ የተዘከረላትን እና የተመሰከረላትን አገራችንን እኛው በእኛው ታሪኳን ማጉደፍ ይብቃ!  ለዚህ ከበቃን በየትኛውም ጉዞ ከጥንታዊ የነጻነት ታሪካችን እና እንዲሁም የአገራቸውን አንድነት ካስጠበቁ ግን ለታዳጊ አገሮች ግድየለሽ ከሆኑ ልዕለ ኃያላን መንግሥታት ትምህርት መቅሰም እና ከስህተቶቻችን መማር ሊሳነን አይገባም። እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here