spot_img
Sunday, July 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሚድያው እሳት ውኃ ያስፈልገዋል!!! ወፍ በረራዊ ቀላል ቅኝት

የሚድያው እሳት ውኃ ያስፈልገዋል!!! ወፍ በረራዊ ቀላል ቅኝት

የሚድያው እሳት
ምንጭ ፡ ለምኪን ኢንስቲቲዮት

ክፍል አንድ

ባንተአምላክ አያሌው አባተ

ሚድያዎች አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ምን ማሰብ (what to think) ሳይሆን ስለምን ማሰብ (what to think about) እንዳለባቸው የሚነግሩ የመረጃማዕከላት ናቸው። ሰዎች ፈጥረው ተመራምረው እንዲያስቡ ሳይሆን ስለተፈጠረ ክስተት እንዲያስቡና እንዲጨነቁ ያደርጋሉ። እንዴት ማሰብ (how to think) እንዳለብንም በብዙው አያግዙንም። ያገኙትን መረጃ አንዳንዶች አጣርተው ሌሎች አበላሽተውዘርግፈውልን ይሄዳሉ። መረጃውን ማላመጥ፤ ማገላበጥና ማጥናት የአድማጩና አንባቢው ድርሻ ነው። በተለይ በዚህ ወቅት በሚድያ በኩል የሚመጣው የሐሳብና የአስተሳሰብ ለውጥ አሉታ ይበዛበታል።

ሚድያ ላይ ብዙሰዓት የሚውል ሰውም አምራችና አልሚ ሳይሆን በዝባዥና ተበዝባዢ እየሆነ ነው። አድራጊ ሳይሆንተደራጊ ነው። በተለይ አድማጩና ተቁለጭላጩ ሚድያው ተጽዕኖ ይፈጥርበታል እንጂ እርሱ ሚድያው ላይ ጫና የማድረስ አቅሙ እጅግ ዝቅተኛ ነው። ዐይኑእስኪቀላ ናላው እስቲፈላ አፍጥጦ ውሎ በመጨረሻ ጊዜውን፣ ገንዘቡንና ጉልበቱን አባክኖ እርሱም ባክኖ ይወጣል።

የሚድያ ጥገኝነቱም ከስንፍናው የመነጨ ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰው ስለ ሀገር፣ ስለፖለቲካ ስለ ትግል በራሱመርምሮ አንብቦና ዋጋ ከፍሎ የማወቅ ፍላጎቱም ጊዜውም የለውም። ስለነዚህ ነገሮች ብዙ ማሰብ አይፈልግም። ነገር ግን እርሱ ባይፈልግም እነርሱ የሕይወቱ አካል ስለሆኑ ስለ እነርሱ የሚነግረው አካል ደግሞ ይፈልጋል።

ሚድያ ከላይ ስላነሣናቸውና ስለሌሎችም ጉዳዮች መረጃዎችን አጠናቅሮ ወደ ሰሚው ወይም አንባቢው የሚያደርስ ነው። በዚህም ሚድያዎች አጀንዳ ፈጣሪዎች ባይሆኑም (በእርግጥ አሁን አሁን የሐሳት አጀንዳ እየፈጠሩ ቢሆንም) በዋናነት መረጃ አምጭዎችና ሰጪዎች ናቸው።

ድሮ ዛሬ ሬድዮ ምን አለ? ጋዜጣው ምን መልእክት ይዞ ወጣ እያሉ መጠየቅና ዓለም ወይም ሀገር ወይም ፖለቲከኞች የተጠመዱባቸውን አጀንዳዎች በዝርዝር ለሕዝብ ማቅረብ የሚድያ ዋነኛ አጀንዳ ነበር። ያኔ የነበረው ሚድያ በአንጻራዊነት ተቋማዊና ሙያዊ እንዲሁም በእውቀትና በስነ ምግባር የተገነባ ስለነበር የመረጃ አስተማማኝነቱና የአጀንዳው ማኅበራዊና ሀገራዊ እርባና የጎላ ነበር።

አሁን ላይ ያሉ ብዙ ሚድያዎች እውቀት፣ እውነት፣ ሞራል፣ ሀገራዊና ሕዝባዊ ኃላፊነት የጎደላቸው፣ በተራ ግለሰቦች የተያዙ ናቸው። እነዚህ ግለሰቦች በሚድያዎቻቸው እውቀትንና እውነትን ከመካድ አንሥቶ፤ የተፈጸመውን እውነታም ሙያዊ የኃላፊነት ስሜት በጎደለው አግባብ ማቅረብ ከዚህ አልፎም እጅግ ከፍተኛ ለሆነ የገንዘብ ማጋሰሻና የሕዝብ መከፋፈያ መንገድ አድርገው ይጠቀሟቸዋል። በዚህም ብዙዎች የጥፋትና የጥል የመለያየትና የሞት ምክንያቶች ሁነው ይገኛሉ።

በዋናነት በወቅቱ ከሚታዩ የሚድያ ክፍተቶች የተወሰኑትን ብንመለከት፦

  1. ቅድምናንና አስፈላጊነትን (Precedence and importance ) መርሳት፦ አሁን ላይ በየሚድያው የሚተላለፈው መልእክት በአይነት፣ በመጠንና በይዘት እጅግ የተወሳሰበና የበዛ ነው። ወቅታዊና አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችንና ሐሳቦችንመርጦና መጥኖ የሕዝቡንም ስነልቡና ተረድቶ በልኩ ስነልቡናዊ ቅድምና ያላቸውን መረጃዎች የሚያቀርበው ተቋማዊም
    ሆነ የግል ሚድያ በጣም ጥቂት ነው።

የሚረባውንም የማይረባውንም እያገበሰበሱ ሀገራዊና ሕዝባዊ እርባና የሌላቸውን ጉዳዮች እየደረቱ፣ አድማጭ ተመልካችን ማዘናጋት አንዱ የወቅቱ የሚድያዎች ችግር ሁኖ ይታያል። በዚያም ላይ መረጃው በግነት ርእሶች በውሸትና በአሉባልታ የተሞላ ስለሆነ፣ ብዙዎችን ወደ ስሕተት ጎዳና የሚመሩና የሚያሳስቱት በጎና ትክክለኛ መረጃ ከሚያቀርቡት በእጅጉ ይበልጣሉ። ታዲያ ምን እናድርግ?

መፍትሔው፦ አብዛኛው የሚድያ ተከታይ በተለይ ወጣቱ ዳሰስ ዳሰስ አድርጎ በቶሎ በቃኝ (satisfice) የሚመለስ ወይም ስድብና ንትርክ ዘለፋና ነቀፋ በበዛበት ውሎ የሚያድር ነው። ይህችን አጭር ጽሑፍ እንኳ መዝለቅ አይችልም። መረጃዎችን የሚፈልጋቸው በአቅሙና በሚመስለው ደረጃ እንጂ ሁሉንም አስፈላጊ እውነታዎች ከግንዛቤ አስገብቶ (by full consideration of all relevant information) ስላልሆነ ግልብና ስሑት ነው። ይህን ተገንዝቦ በሚቻለው መጠን አቅራቢው መረጃውን መንስኤውን ከውጤቱ አስተሳስሮ ባጭሩ ለመግለጥና የተወሰነ ግንዛቤ እንዲኖር ማድረግ ይኖርበታል።

ራሱ ተደራሲውም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከዚያም ከዚያም በመቃረም ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሐተታና ትችት ለማቅረብ፣ እውቅና (profile)፣ ብቃት (efficiency) እንዲሁም ልምድ (experience) ካላቸው እንዲሁም ከጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶችና የመረጃ ምንጮች (direct owners and sources) መረጃን ለማግኘት መጣር ይኖርበታል።

ራሱ ተደራሲውም መሬት ላይ ያለውን እውነታ ከዚያም ከዚያም በመቃረም ሳይሆን በጉዳዩ ላይ ሐተታና ትችት ለማቅረብ፣ እውቅና (profile)፣ ብቃት (efficiency) እንዲሁም ልምድ (experience) ካላቸው እንዲሁም ከጉዳዩ ቀጥተኛ ባለቤቶችና የመረጃ ምንጮች (direct owners and sources) መረጃን ለማግኘት መጣር ይኖርበታል። ይህን እንዲያደርግ ደግሞ ምሁራኑ በሚችሉት መጠን ንቃተ ሕሊና መፍጠር፣ ሚድያውን በዘርፉ አለመናቅ፣ “አይመጥነኝም አልገኝም” አለማለትና አስፈላጊ በሆነው ሁሉ ተገኝቶ ማስተማር ይገባል። ቲክቶክም ቢሆን። ከዚህ አልፎም ከዝብርቅርቅ ዘገባ፣ ከአልባሌ ቧልትና ሀሜት የተለዩ የሚድያ ተቋማትን መደገፍና ማደራጀት ያስፈልጋል።

  1. የመረጃና የሁነቶችን ትስስርና ቅደም ተከተልን ማዛባት (disordering coherence and chronology) ሌላኛው ችግር ነው። ይህ ከቅድምናና አስፈላጊነት ችግር የተለየ ነው። እዚህ ላይ የሚስተዋላእው ስሕተት ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ አስፈላጊ ጉዳዮች ወይም አጀንዳዎች ቢኖሩ የመጨረሻውን ወይም ሁለተኛና ሦስተኛውን ጉዳይ መጀመሪያ የማድረግና ወሳኙና መጀመሪያ ላይ መቅረብ የሚገባው ጉዳይ እንዲረሳ ወይም አትኩሮት እንዲነሣ ማድረግ ነው።

በዚያም ላይ የታሪኮችንና የሁነቶችን ሂደታዊ ትስስር (coherence) ሆን ብሎ ማዛባት በጣም የተለመደ ሁኗል። ለምሳሌ ወቅታዊ ጉዳዮችን ብንመለከት ከአንገብጋቢው የህልውና ትግል ይልቅ ነገ የሚመሠረተው ሀገር፣ የምንከተለው የፖለቲካ ርእዮተ ዓለም፣ የኢኮኖሚ ሥርዓት በሚሉ አዳሪ ጉዳዮች ላይ በመወዛገብና በመከራከር ወሳኙን ሕዝባዊ ትግል ከአጀንዳነት ማንሣትና አትኩሮት መንሣት ይስተዋላል።

ምንም እንኳ ሀገረ መንግሥት ምሥረታው አስፈላጊና ሊታሰብበት የሚገባ ቢሆንም ይህ የሀገረ መንግሥት ምሥረታ በፖሊሲ አጥኚዎች፣ በፖለቲካ ልሂቃንና ትግሉን መሬት ላይ በሚመሩ ሰዎች መሆን ሲገባው ያልተገባውን ጉዳይ ለማይገባው (“ገ” ን አጥብቅ) ብሎም የፖሊሲና የስትራቴጂ ንድፍ ለማያውቀው ብዙኀን አጀንዳ አድርጎ ማቅረብና በገንዘብ በጉልበት በወኔ አስተዋጽኦ ሊያደግበት ከሚችለው የህልውና ትግሉ ላይ ማንሣት እጅግ በሴራም ባለማወቅም ሚድያው ላይ ውለው ለሚያድሩ አካላት ዋነኛ ጉዳይ ነው።

መፍትሔው፦ በዋናነት እነዚህ ስሕተቶች አጀንዳ ባላቸው ሴራ እንዲያሴሩ በተመለመሉ የተማሩና አዋቂ ሊባሉ በሚችሉ አካላት የሚዘወሩ በብዛትም አገዛዙ የቀጠራቸው ቅጠረኞች ወይም እኛም ራሳችን የማናውቃቸው ቡድኖች ክንፍ ስለሆኑ እነርሱን የሚገዳደርና የሚያሳፍር አካሄዳቸውን የሚያስነውር ግብረ መልስና ተመሳሳይ የሚድያ አማራጭ ማዘጋጀት ይገባል።

ከዚህ ባለፈም እንዲህ ዐይነት ሥራ የሚሠሩ አካላትን በስምና በዘውግ (ብዙዎች ቡድኖች ስለሆኑ) ለይቶ ማወቅና በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በተደራጀ መልኩ በውጪም በውስጥም ያሉ ትግሉን በእውነትና በእውቀት ብሎም በቅንነት በሚመሩ አካላት እንዲወገዙ ማድረግ ስለ ስሑት አካሄዳቸው ሰፊ ገለጻ መስጠት፣ በሕዝቡ ዘንድ ያላቸውን ተቀባይነት ለማስለቀቅ እውነቱን በመግለጥ ማጋለጥ ይገባል።

  1. የጉዳዮች ቅንበባና (issue framing) መሠረት (spin) ላይ የሚስተዋሉ የሚድያ ተግዳሮቶችም እጅግ የበዙ ናቸው። በመሠረቱ ስለአንድ አዲስ ወይም ሂደታዊ ጉዳይ የሚቀርብ ዘገባ አቀራርቡ በጉዳዮ አረዳድ መፍትሔና ውጤት ላይ ትልቅ ሚና ይጫዎታል። አብዛኞቹ ድርጊቶች ባለዘርፈ ብዙ ባሕርያት ወይም ባለቅርንጫፍ ናቸው። ለምሳሌ ስለጦርነት ስናነሣ ሞት ዋናው ነው። ከእርሱ የማይለዩ መፈናቀል፣ ርኀብ፣ ውድመት፣ ውንብድና፣ ስነልቡናዊና ተላላፊ በሽታዎች ወዘተ አብረው ይኖራሉ።

እንዲህ ባሉ ሁነቶች ውስጥ በተለይ በእኛ ሀገር የሚድያው ዋና አትኩሮት ጦርነቱና በጦርነቱ የተደመሰሱ ተፋላሚ ኃይሎች ምርኮና ድል ሽንፈትና ገድል ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። ይህ ጦርነቱንና የጦርነቱን ሂደት በትክክል ለመረዳት አያስችልም። በንጹሐን ላይ የሚፈጸመውን አሰቃቂ ወንጀልም አያስቆምም። ስለዚህ በዋናነት የሚያዎች ድርሻ ማኅበርሰብ አቀፍ ሊሆን ይገባል።

በትክክለኛ የሚድያ ዘገባ አማካኝነት የሚደርሰውን የንጹሐን እልቂት ለውጪው ዓለም የማሳየትና ከተራድኦ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመሥራት አስገዳጅና ጋባዥ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። ስለዚህ የዜና ጥንቅሮች ሁሉን አቀፍ በተለይ ማኅበረሰባዊ ሊሆኑ ይገባል። ጦርነቱን ብቻ ሳይሆን በጦርነቱ እየተጎዱ ስላሉ አካላት አብዝተው መዘገብ ለሚጎዳው ሕዝብ ነን ከሚሉ ሚድያዎች የሚጠበቀው ተቀዳሚ ግዴታ ነው።

መፍትሔው፦ ይህም ከላይ እንደተባለው በራሱ ይህን ሊሠራ የሚችልን የሚድያ ተቋም ማበረታታና ማብቃት አዳዲሶችንም ማደራጀትና ለሚድያ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት በገንዘብና በሰው ኃይል መርዳትና ዘገባቸው ሁሉን አቀፍ እንዲሆን ማገዝ ይገባል።

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here