spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትበፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም ወይንስ “በሰላም” ሽፋን የአብይ አህመድ የተለመዱ ቧልቶች ?

በፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም ወይንስ “በሰላም” ሽፋን የአብይ አህመድ የተለመዱ ቧልቶች ?

በፍትህ ላይ የተመሰረተ ሰላም

ነዓምን ዘለቀ

የዛሬ አመት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በመቃወም በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ባደረገው ታሪካዊ ንግግር “የአማራ ሕዝብ ከብልጽግና ጋር ላይገናኝ ተፋቶአል” ብሎ ነበር። ዛሬ ያ እውነታ በእጥፍ ድርብ በጨመረበት ሁኔታ የአማራ ክልል ሆነ የኢትዮጵያን ችግሮች በዋዛ ፈዛዛ፣ በግርግር፣ በድለላና ፣ በሽንገላ ለመፍታት መሞከር ሌላ ክሽፈት ነው። የአብይ አህመድና የአማራ ብልጽግና ሌላ የቀን ቅዠት። የአማራ ህዝብ ያነሳቸውን በርካታ አንገብጋቢ የፓለቲካና የደህንነት ችግሮችና ጥያቄዎችም ሆነ የኢትዮጵያ ዛሬ የምትገኝባቸውን ዘርፈ ብዙ ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ የደህንነትና የኢኮኖሚ ችግሮች ሊፈታ የሚችል አቅም እንደሌልው በባህር ዳሩ “የሰላም ኮንፈረስ” የወጣው በለአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ ጠቋሚ ነው። ለምን ቢባል በድቡሽት ላይ የተመሰረቱ የሰላም ኮንፈረሶች፣ ከልብ ያልመነጩ፣ አሁናዊ አውነታን ያልተቀበሉ፣ ሀቅን ያልተጋፈጡ ናቸው። ቅንነት የሌላቸው የሃስት ትርክቶችና ዲስኩሮች፣ ከዚያም አልፎ ሌላ ዙር የእብሪትና የትብኢት ፉከራዎች (ጀ/ል አብባው ከአመት በፊት በእብሪት በፋኖ ላይ የፎከረውን በሌላ ቋንቋ እንደደገመው) ዛሬ ላይ ኢትዮጵያን ስነገው የያዙ ዘርፈ ብዙ ፓለቲካዊ ችግሮች ሊፈቱ አይችሉም።

ባለፉት 11 ወራት በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ሲደርስ የነበረው ግፍና በደል፣ ከሰላምና ከፍትህ ጋር የማይተዋወቀው የብልፅግና አገዛዝ በአማራ ህዝብ ላይ የጫነው የህልውና አደጋ ነው። በኦሮሚያ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በአማራው ላይ በተደጋጋሚ ሲፈጸም የቆየው ጭፍጨፋ እና ማፈናቀል አልበቃ ብሎ፣ በሸገርና በአዲስ አበባ ማንነት እየተመረጠ የሚደረጉ ጥቃቶች፣ ወከባዎች፣ ማፈናቀሎች፣ የጅምላ እስራቶች አልበቃ ብሎ፣ አማራውን “ሱሪህንም ትጥቅህንም እናስፈታለን” ብለው ክልሉን የጦርነት ቀጣና ያደረገው የአቢይ አህመድ መንግስት ያሰበውን እውን ማድረግ አቅቶች ተከታታይ ሽንፈትና ውርደት ሲደርስበት፣ “ሰላም” “ሰላም” የሚል ያልተቃኘ ዘፈን መዝፈን ጀምሯል። አማራ ክልል የተጀመረው ጦርነት የአብይ አህመድን እውን ለማድረግና የኦሮሞያ ብልጽግናን የበላይነትለማረጋገጥ የተጀመረ ጦርነት ነው። አንዳንድ የኦሮሞያ ብልጽግና መሪ ካድሬዎችና የኦሮሞ ተወላጅ የሆኑ እንዳንድ ጄነራሎች ሲዝቱ እንደተደመጡት፣”ትግሬውን ጥርስ አስውልቀናል፣ አሁን ደግሞ አማራውን ልክ እናስገባለን” በሚል እብሪትና የሴራ ፓለቲካ አማራውን አንገት ለማስደፋት የጀመሩት ጦርነት ነው።

አብይ አህመድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትህና ሰላም ያስፈልገዋል ብሎ ቢያምን ኖሮ በቅርቡ በባህር ዳር እንደተናገረው የአማራ ህዝብ ባልመረጠውና እሱ በሾመው “በአረጋ ከበደ ስር ለክልላችሁ ስሩ” እያለ በአማራ ህዝብ ቁስል ላይ እንጨት በመስደድ አያላግጥም ነበር ። አሁንም ብልፅግናዎች “በሰላም” ስም የሚሰሩት አደናጋሪ ስራ አማራ ክልል ውስጥ የሚታየውን መሰረታዊ ችግር የሚፈታ አይደለም። አማራ ክልል ዉስጥ እርስ በርስ የተጣላ የማህበረሰብ ክፍል ያለ ይመስል ሽማግሌና ቄስ እየላኩ የፋኖን ኃይሎች ከተሰማሩበት የህልውና ማዳን ዘመቻ ተዘናግተው እጅ እንዲሰጡ ለማድረግ የሚሸረበው ሴራ የአማራን ክልል ችግር ያባብሰዋል እንጂ ሌላ ምንም የሚፈይደው ፋይዳ የለም። ብልፅግናዎች ከሰሞኑ የጀመሩት የሰላም ጩኸት የአማራ ህዝብ ለበርካታ አመታት በሰላማዊ መንገዶች ጭምር የጠየቃቸውንና ከክልሉ አልፎ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ የሚደርሱ ጥቃቶችና በደሎች ጋር የተያያዙ እና መሰረታዊ የፓለቲካ፣ የህልውና፣ የደህነነት ጥያቄዎችን ምላሽ የሚሰጥ አካሄድ እንዳልሆነ በርክታ ማሳያዎች ማቅረብ ይቻላል።

የዛሬ አመት የአብይ አህመድ የግል ጀነራሎች፣ እነ ብርሃኑ ጁላና እነ አበባው ታደሰ “ፋኖን ትጥቁንም ሱሪውንም በ 15 ቀን እናስፈታለን” በማለት በእብሪትና በትእቢት ተወጥረው ተነስተው ነበር። “የአማራ ህዝብ ብዙ የፓለቲካ ጥያቄዎች አሉት ፣ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ጥያቄዎች አሉት፣ የፖለቲካና የኤኮኖሚ መገለል ጥያቄዎች አሉት።ደሞም አነዚህን ጥያቄዎች ለብዙ አመታት በሰላማዊ መንገድ ሲጠይቃችሁ ነበር። የአቢይ አህመድ መንግስት ግን ለዚህ በሰላማዊ መንገድ መብቱን ለጠየቀና ኢትዮጵያ ችግር ውስጥ ስትገባ የተደረገለትን አገራዊ ጥሪ አክብሮ ከፍተኛ መስዋኦትነት ለከፈለ ህዝብ የሰጠው ምላሽ “ትጥቅህን ካልፈታህ” አጠፋሃለሁ የሚል ዕብሪት የተሞላበት ምላሽ ነበር። ይህንን በሰሜኑ ጦርነት የደቀቀን ህዝብ፣ በተለይ ከመከላከያ ሠራዊ ጎን ቆሞ ከፍተኛ መስዋእትነት በከፈለህዝብ ላይ እባካችሁ ጦርነት አትክፈቱበት በማለት እኔን ጨምሮ በርካታ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያውያን ሲያሳስቡና ሲማጸኑ ነበር።

ነገን አሻግሮ የመመልከት ችሎታ የሌለው አቢይ አህመድ በእብሪት ተወጥሮ “በአፍሪካ ውስጥ እኛን የሚወዳደር መከላከያ የለም አትጠራጠሩ” በማለት ወራሪ ሠራዊቱን ወደ አማራ ክልል አስገባ። ዛሬ ይህ ሠራዊት ገሚሱ ሞቷል፣ ገሚሱ ቆስሏል፣ ገሚሲ ተማርኳል፣ ገሚሱ ፋኖች በገዛ ፈዋዱ ተቅላቅሏል፣ ገሚሱ መሳሪያውን እየሸጠ ኮብልሏል። ኤኬ 47 ብቻ ታጥቆ የነበረው ፋኖ ዛሬ ላይ ከስራዊቱ በማረከው ሞርታር፣ ዲሽቃ፣ ብሪን፣ ዙ 23ና መድፎች ለመታጠቅ ችሎአል። በሻለቃ በሻምበል ደረጃ የነበረው አቋም ዛሬ የፋኖ ሃይሎች ክፍለ ጦሮች እና እዞችን መስርተዋል። ይህ የሆነው በዋነኝነት ደግሞ ጦርነቱ ህዝባዊ በመሆኑ እና አብይ አህመድ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ የከፍተው ጦርነት ኢ-ፍታሃዊ በመሆኑ ነው።

በመሰረቱ በሀገራችን ኢትዮጵያ የሀገርና የህዝብ ችግሮች ሀቀኛ ውይይቶችና ልዩ ልዪ አማራጭ መፍትሄዎች ቀርበው የጋለ ውይይትና ክርክር አይደረግባቸውም፣ ጥናቶችም አይቀርብባቸውም። የአማራም ሆነ ሌሎቹ የብልጽግና መሪ ካድሬዎች አብይ አህመድ አድርጉ ያላቸው ማድረግ ብቻ ነው። ምንም አይነት ሃቀኛ ውይይት፣ የተለያዩ ሃሳቦች ያለምንም ፍርሃትና መሸማቀቅ የሚንሸራሸሩበት ሁኔታዎች የሉም። የምንወስነው ውሳኔ፣ የምንወስደው እርምጃ ነገ ምን ሊያመጣ ይችላል፣ መዘዙ ምን ሊሆን ይችላል የሚሉ ጥያቄዎች በአብይ አህመድ ተላላኪዎች እይነሱም። ከሀገርና ከህዝብ ጥቅምና ደህንነት አኳያ ለማየት ፍላጎቱም አቅሙም የላቸውም። ይህ ስለሆነ እንወክለዋለን በሚለው ህዝብ ላይ ጦርነት ሲታወጅበት፣ህፃናት፣ አናቶችና አረጋውያን ሲገደሉና ሲፈናቀሉ፣መሰረተ ልማት ሲወድምና የመኖሪያ ቦታዎች ሲደመሰሱ እጃቸውን አጣጥፈው ይመለከታሉ። አብይ አህመድና ብልጽግና በአማራ ህዝብ ሲያደርጉ የቆዩት እንዲህ አይነቱን እንኳን በወገን ላይ በባዕዳን ወራሪዎችም ላይም የማይሰራ ግፍና በደል ነው።

ዛሬ የ”ኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት” ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበትና ቁጥሩ በመመናመኑ የጠሚ አቢይ አህመድ ካድሬዎች ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልደረሰ ወጣቶችን ጭምር በስፋት እየመለመሉ ነው። ትምህርት ቤቶች ወይ በመውደማቸው ወይም ወደ ወታደር ካምፕ በመለወጣቸው በበዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ተፈናቅለዋል፣ ሆስፒታሎች ወድመዋል፣ የእርሻ ቦታዎች በከባድ መሳሪያ ተቃጥለዋል፣ በሺ የሚቆጠሩ ሲቪሎች ብድሮን ህይወታቸው ተቀጥፏል። በቢሊዮኖች የሚቆጠር የህዝብና የግል ንብረቶች ወድሟል። የብልፅግና መሪዎች እንዲህ አይነት ትልቅ ጥፋት በገዛ ወገናቸው ላይ ከፈጸሙ በኋላ፣ የችግሩ ባለቤቶች እነሱ መሆናቸውን ተገንዝበው የመጸጸት ወይም ወደኋላ መለስ ብሎ እራስን የመፈተሽ ምንም አይነት ምልክት አይታይባቸውም። እንዲያውምይህን ሁሉ መከራና ግፍ በህዝብና በሀገር ላይ ፈጽመው አሁንም የህዝብ ሀብትና ገንዘብ ከፕሮፖጋንዳ የዘለለ ፋይዳ በሌላቸው መድረኮች ያባክናሉ። ከልብ ያልመነጨ “ሰላም” ይሰብካሉ ፣ ብዙ ሚሊዮኖች ወጪ ወጥቶ ሃቀኛ መፍትሄ የማይሰጥባቸው፣ የብልጽግና ኮንፍረንሶች ያካሂዳሉ፣ እርስ በእርሳቸው ከመነጋገር በዘለለ ዘላቂ መፍትሄ የማያመጣ የህዝብን ሀብትና ግዜ ከማባክን ውጭ ምንም ለውጥ የማያመጣ ከግርግር የማይዘል፣ መሰረታዊ ችግሮችን የማይፈታ የኮንፈረንሶች ጋጋታ። በደርግ ዘመን የኮሜቴ ጋጋታ፣ የብልጽግና ዘመን ውጤት አልባ የኮንፈረንስ ጋጋታ። ለምን ? ችግሩን ሀቀኛና ከልብ የመነጨ መፍትሄ ለመሻት ቅንነት እና ቁርጠኝነት ፣ ስልጣናቸውን ከማስቀጠል ውጭ ሌላ አላማ የሌላቸው ክፉና፣ ጨካኝ፣ አጭበርባሪ፣ እና አቅመ ቢስ ገዥዎች ሰለተጫኑብን ነው ።

በመሰረቱ ሰላም የሰው ልጆች ሁሉ የሚፈልጉት መሰረታዊ እሴት ነው። ሰላም የሰው ልጆች በህይወት ለመኖርም ፣ እንደ ማህበረሰብ ለማደግም ከሚፈልጓቸው መሰረታዊ ፍላጎቶች ውስጥ እንዱ መሆኑ ግልጽ ነው። ለኢትዮጵያችን ሰላም ከምንም በላይ የሚያስፈልግ መሆኑ ለማንኛውም ጤነኛ ዜጋ አጠያያቂ አይደለም። ትልቁ ጥያቄ እንዴት ነው እንደ አገርና እንደ ህዝብ ሰላም የምናገኘው፣ አገራችን ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን ምን ማድፈግ አለብን የሚለው ጥያቄ ነው። በየትኛውም ማህበረሰብ ውስጥ ሰላምና ፍትህ በቅርብ የተቆራኙ እሴቶች ናቸው። አንድ ማህበረሰብ ሰላማዊ ማህብረሰብ ነው የሚባለው፣ በማህበረሰቡ ውስጥ ሰላምና ፍትህ አንድ ላይ መኖራቸው ሲረጋገጥ ነው። አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም ትናንትም በግልጽ እንዳየነው አምባገነንነት በነገሰባቸው አግሮች ውስጥ ፍትህ እና ሰላም አንድ ላይ አብረው መሄድ አይችሉም። የአምባገነኖች ፍላጎት፣ ባህሪይ እና የስነልቦና ከሰላምና ከፍትህ ጋር አብሮ የሚሄድ አይደለም።ለአምባገነናዊ አገዛዞች ሰላም ማለት ህዝብን እንደ ባሪያ ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ማድረግ ነው፣ ለአምባገነናዊ አገዛዞች ሰላም ማለት እንዳሻቸው በህዝብ ላህ መጫን ሲችሉ ብቻ ነው። ፍላጎታቸው ሁሉ ህዝብ እነሱ አድርግ ወይም ሁን ያሉትን ሁሉ አሜን ብሎ እንዲቀበላቸው ብቻ ነው ። በሀገራችንም በኢትዮጵያ እየሆነ የሚገኘውም ይሄው ነው።

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ  በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here