spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየዶ/ር ዐብይ አሕመድ “ብልጭልጭ የልማት ሥራዎችና” አንድምታቸው

የዶ/ር ዐብይ አሕመድ “ብልጭልጭ የልማት ሥራዎችና” አንድምታቸው

Ethiopian News _ Abiy Ahmed

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ 
ሰኔ 27 2016

“ለአንድ ሰው አሳ ከሰጠኽው ለአንድ ቀን ትመግበዋለህ፤ አሳ ማጥመድ ካስተማርከው ግን እድሜ ልኩን ትመግበዋለህ” የቻይኖች ብሂል።

ከጥቂት ቀናት በፊት፤ የአቶ ታምራት ታረቀኝ የፌስቡክ ገጽ ላይ አቶ ስለሺ ፈይሳ ከተባሉ ሰው ጋር ባደረግኩት ውይይት በዚህ ርዕስ ላይ መጣጥፍ እያዘጋጀሁ መሆኑን ጠቁሜ ነበር። ይህንን ጽሁፍ እያዘጋጀሁ ባለበትም ወቅት ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከበርካታ ጉዳዮች በተጨማሪ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ አስመልክተው ማብራርያ የሰጡት። እሳቸው ከሰጡት ማብራርያም ለዚህ ጽሁፍ ይጠቅማል ያልኩትን ሃሳብ ወስጃለሁ። ከአቶ ስለሺ ጋር በነበረኝ ውይይት መነሻው ነጥብ፤በተለይም የሥራ አጥ ቁጥር በኢትዮጵያ ከመቼውም በላይ ጨምሯል በሚለው ሃሳብ ላይ ያተኮረና፤ እሳቸውም “ይህ ብልጭልጭ ሥራ ለተራበው ሕዝብ ምን ያደርግልታል” የሚል አንድምታ ያለው ሃሳብ ማንሳታቸው ነበር። 

ልክ እንደ አቶ ስለሺ በርካታ ሰዎች፤ ‘በጦርነት ውስጥ ሆነን፤ ሕዝብ እየተራበ፡ ሕዝብ ተፈናቅሎ፤ ወዘተ ወዘተ፤ ፓርክ መስራት፤ ከተማ ማሳመር ምን ይጠቅማል’ የሚሉ እሳቤ ያላቸው ትችቶች ሲስነዘሩ እየሰማን ነው። ብዙዎች እነዚህ የልማት ሥራዎች ያላቸውን ጠቀሜታ ካለመረዳት የሚያነሱት ሃሳብ ሲሆን፤ ሌላው ቀርቶ በዘርፉ እውቀት አለን ብለው “የሚኩራሩ ሰዎች” ይህንኑ ሃሳብ በመጠቀም፤ ሕዝብ በመንግስት ላይ ለማነሳሳት ስሜቱን መኮርኮርያ አድርገው ሲጠቀሙበትም አስተውለናል። ኢኮኖሚስት ነን ብለው እነዚህን የልማት ሥራዎች የፖለቲካ ቅብ ቀብተው በማጥላላት የራሳቸውን እኩይ ዓላማ ለማስፈፀም የሚተጉም ጥቂት አይደሉም። በተለይ የእነዚህ “ምሁራን” ቀናነት የጎደላቸው ውግዘቶች፤ የእነዚህን የልማት ሥራዎች ጠቀሜታ ካለማወቅ የሚነሱ አይመስለኝም፤ የአንዳንዶቹ የእውቀት ማነስ እንደተጠበቀ ሆኖ። 

መሰረታዊ ነጥቡ፤ ኢትዮጵያ የበርካታ ወጣቶች ሃገር ናት። በርካታ ወጣትም በሥራ አጥነት ኑሮው ማጠፍያው ያጠረበትና አብዛኛውም ለቤተሰብ ጫና ሆኖ ሕይወትን እየገፋ እንዳለ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። ይህንን የሥራ አጥነት ቁጥር ግን እንዴት መቀነስ ይቻላል ለሚለው መፍትሔ ከሚጠቁመው የበለጠ ተቺ የበዛበት፤ የሚሰሩ ሥራዎችን ማጣጣል የሚወደስበት የፖለቲካ አውድ ላይ እንገኛለን። የአንዳንዶቹ እሳቤም፤ መንግሥት በተለያየ መልክ የሚያሰባስበውን ገንዘብ፤ ለሕዝብ እንድያከፋፍል ወይም ሕዝቡን የተመጽዋችነት ኑሮ እንዲያኖር የሚጠቁም አይይነ በመሆኑ የአንዳንዱን ሰው ስለኢኮኖሚ ያለውን ግንዛቤ አነስተኛነት የሚያሳብቅ ሆኖ አግኝቸዋለሁ። 

በተለይ በገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ የመንግሥት ተቀዳሚ ተግባር ሥራ ፈጣሪዎችን ማበረታታትና ለሥራ ፈጣሪዎች በር የሚከፍቱ ፖሊሲዎችን መንደፍ እንደሆነ በርካታ ኢኮኖሚስቶች ጽፈውበታል። በዚህ ረገድ ሃገራችን ከደርግ የእዝ ኢኮኖሚ፤ ወደ ኢሕአዴግ “አብዮታዊ ዲሞክራሲ ኢኮኖሚ” ቅይጥ ኢኮኖሚ ተሸጋግራ፤ በተወሰነ ደረጃ የገበያ ኢኮኖሚውን ተለማምዳለች። አሁን ያለው የዶ/ር ዐብይ መንግሥት ደግሞ ሃገራችንን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር እየተውተረተረ ይገኛል። በየትኛውም የኢኮኖሚ ጽንሰ ሃሳብ፤ የመንግሥት ሚና ግን አይተኬ ነው። ለምሳሌ የገበያ ኢኮኖሚ ዋና ተምሳሌት ተደርጋ በምትታየው አሜሪካ፤የሃገሪቱ ትልቁ የሥራ ቀጣሪ፤ የፌደራል መንግሥቱ እንደሆነ ይነገራል። በተደጋጋሚ ጊዜ እንዳየነውም፤ የአሜሪካ ኢኮኖሚ የመዳከም አዝማምያ ሲያሳይ፤ መንግሥት የመሰረተ ልማቶች ላይ መዋዕለ ነዋዩን በማፍሰስ ነው ኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት የሚፈጥረውና የሥራ አጥነት ቁጥርን የሚቀንሰው። ይህ በበርካታ ሃገሮች ላይ የተለመደና ከፍተኛ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያለው ተግባር ነው። 

የዶ/ር ዐብይም “ብልጭልጭ” እየተባለ የሚተቸው የመሰረተ ልማት ግንባታ ጠቀሜታው ከዚህ የተለየ አይደለም። የዶ/ር ዐብይን የልማት ሥራዎች የተለየ የሚያደርገው፤ አብዛኛው መሰረተ ልማት እየተሰራ ያለው ከመንግሥት ባጀት በተመደበ ገንዘብ ሳይሆን፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ከሃገርና ከውጭ ሃገር ባለፀጎች በተለያየ መንገድ ከሚያሰባስቡት መዋእለ ነዋይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ የርሳቸውን ገንዘብ ሳይቀር ለእነዚህ የመሰረተ ልማት ሥራዎች ሰጥተዋል። ከቅርብ ጊዜያት ታሪካችን እንደምናውቀው፤ “ገዢዎቻችንና፤ አጋሮችቻው” ኢትዮጵያን ሲዘርፉ እንጂ ገንዘባቸውን ሲለግሱ አላየንም። “ባልና ሚስት ከአንድ ባሕር ይቀዳሉ” እንዲሉ፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ፤ በቂ ምስጋና ያልሰጠናቸው የቀዳማዊት እመቤት እንኳን በርካታ መሰረተ ልማቶችን ገንበተዋል። ከዳቦ ፋብሪካ፤ የእንጀራ ፋብሪካ፤ እንዲሁም ወደ 34 ትምሕርት ቤቶችን አስገንብተዋል። በቅርቡ ያስገነቡት የዓይነ ስውራን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንኳን በዓይነቱና በጥራቱ እጅግ አስደማሚ ነው። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንጦጦን ፓርክ፤ የአንድነት ፓርክን፤ የመስቀል አደባባይን እንዲሁም በርካታ መሰረተ ልማቶችን ሲያስጀምሩ፤ የነበረው ሁከትና ወጀብ ምን ያክል እንደ ነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። እነዚህ ፕሮጀክቶች ሲሰሩ በሺህ ለሚቆጠሩ ወጣቶችና እናቶች ጊዜያዊ የሥራ እድል ፈጥረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ሥራው ከተጠናቀቀ በኋላም፤ በሺሆች ለሚቆጠሩ ቋሚ የሥራ እድል ፈጥረዋል። እነዚህ ሥራ ያገኙ ዜጎች በአማካይ እያንድንዳቸው ቢያንስ ሶስት የቤተሰብ አባላትን የሚደጉሙ ናቸው። አንድ ሰው መጠየቅ ያለበት፤ እነዚህ መሰረተ ልማቶች ባይሰሩስ ኖሮ የሚጠቀመው ማን ነው የሚል መሆን አለበት። መሰረተ ልማት ሲገነባ፤ በቀጥታ የሥራ እድል ከሚያገኙት ሌላ በተዘዋዋሪ የሥራ እድል የሚያገኙ በርካቶች ናቸው። ሲሚንቶ አምራቹ፤ ብረት አምራቹ፤ ሚስማር የሚያስገባው፤ በአጠቃላይ ለመሰረተ ልማት ግብዓት የሚሆኑ ቁሳቁሶችን የሚያመርቱና ከውጭ የሚያስገቡ፤ በመጓጓዣ ዘርፍ የተሰማሩና መሰል ዜጎች በመሰረተ ልማቱ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ የሚሆኑ ናቸው። እነዚህን ሥራዎች የሚተቹ፤ የሚያወግዙና የሚያጣጥሉ ሰዎች እሳቤ ግን፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገንዘብ ሰብስበው ለሕዝብ እንዲመጸውቱ የመጠበቅ ያክል ነው።

እነዚህ መሰረተ ልማቶች በመገንባታቸው፤ አሁን ቋሚ የገቢ ምንጭ ማግኛ ሆነዋል፤ የአንድነት ፓርክ በዓመት በሚሊዮን የሚቆጠር ብር የሚያስገኝ ተቋም ሆኗል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የመሰረተ ልማት ግን በዚህ ብቻ አላቆመም። ዛሬ ኢትዮጵያ አፋር ውስጥ ጤፍ፤ ስንዴ፤ ፍራፍሬ፤ ሰሊጥ በሚያሰድምም ሁኔታ እያመረተች ነው። በሶማሊያም እንደዚሁ። እነዚህ አካባቢዎች በየትኛውም ቀደም የኢትዮጵያ መንግሥታት ለእርሻነት ለመታሰባቸው መረጃ የለኝም። በቅርቡ የቦረና አርብቶ አደር ሕዝብ በጠኔ ተጠቅቶ እንደነበር እናስታውሳለን። ዛሬ የቦረና አርብቶ አደር፤ የእርሻ ስልጠና ተሰጥቶት መሬቱን እያረሰ፤ በቆሎ፤ ስንዴ፤ ፍራፍሬ አብቅሎ፤ እራሱን ከመመገብ አልፎ፤ ወደ ገበያ ማቅረብ ችሏል። ትላንት ለከብቶቹ መና ማግኘት ይቸገር የነበር ሕብረተሰብ ነው፤ ዛሬ ትርፍ ምርት ማምረት የጀመረው። ይህም በመስኖ የእርሻ ልማት የተከወነ ነው።

በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደገለፁት ከ40 ሺህ በላይ የውኃ ፓምፖች ተዘርግተው፤ሃገራችን “የበጋ የመስኖ እርሻ” ተጠቃሚ ሆናለች። እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2015 ባሳታምኩት “እምባሽን ላብሰው” በሚልው የግጥም መድብሌ በ2010 ዓ.ም በከተብኳት “የረሃብ አለንጋ” የምትለውን ግጥሜን በገጽ 47 ላይ አስፍሬዋለሁ። በዚህ ግጥም እንዲህ የሚል ስንኝ ይገኝበታል

“…የሙጢኝ ብላችሁ በትረ መንግሥቱን፤
ሽቅብ አንጋጣችሁ ሳታዩ መሬቱን፤
ዝናብ ስትጠብቁ ፖሊሲ ይመስል፤
ወንዞቹ ሲፈሱ ያለምንም ደለል፤
ስለመስኖ ማሰብ ማለም ተሳናችሁ፤
ዛሬም እንደትላንት ጥርሱን ያገጠጠ ጠኔ መጣላችሁ።..”

የዶ/ር ዐብይ መንግሥት በመስኖ ልማት እየሰራ ሃገራችን ያልተጠቀመችውን መሬት በመጠቀም ያሳየችው የምርት እመርታ ለዚህ ፀሃፍ እጅግ አስደማሚና የመሪውን ለሀገር እድገት የሰጡትን ትኩረት የሚያሳይ ሆኖ አግኝቶታል። ይኸው ጽሃፍ በዚሁ የግጥም መድብሉ በ2015 ባካተተው ግጥሙ፤

“ሽንጣም ወንዞቻችን ከጥቅም ቢውሉ፤
መስኖው ቢዘረጋ ቢሰራ ደለሉ፤
በቅጡ ቢታረስ ጂማና ወላይታ፤
ማዕድን ቢወጣ ከአፋር ከአሳይታ
እንኳን ለኢትዮጵያ በበቃ ለአፍሪካ፤
የወገኔም ሆዱ በጥጋብ በረካ።”

ያለው ምኞቱና ሕልሙ እውን እየሆነ እየተመለከተ ነው። ይህ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕልምና ምኞት ነው።የጠቅላይ ሚኒስትሩ የ“ብልጭልጭ መሰረተ ልማት” ግንባታ በዚህ ብቻ አላበቃም፤ የሌማት ትሩፋት፤ ኢትዮጵያ ታምርት፤ መትከል በፅናት፤ ወዘተ በሚል መሪ ቃል በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን ለመስራታቸው የሥራቸው ውጤት በቂ ምስክር ነው። መቼም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በኢትዮጵያ ውስጥ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች፤ በመንግሥት ምገባ እየተደረገላቸው ነው። “የድሃ ድሃ” የተባሉ ዜጎች በተለይ በአዲስ አበባ በየክፍለ ከተማው በተዘረጉ የመመገቢያ ማዕከላት፤ የእለት ጉርስ እያገኙ ነው።የአንደኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በመንግሥት መማርያ ቁሳቁስና ዩኒፎርም እየተሟላላቸው ነው።የተጠናቀቁት በርካታ የቱሪስት መስህብ የሆኑ እንደ ጎርጎራ፤ ጨበራ ጩርጩራ ብሔራዊ ፓርክ፤ ኮይሻና መሰል መሰረተ ልማቶች፤ ለበርካታ ሰዎች የሥራ እድል የፈጠሩ ብቻ ሳይሆን፤ ለአካባቢው ነዋሪም መኖርያ ቤቱንና አካባቢውን እጅግ ያሻሻለ ለመሆኑ ነጋሪ የሚያሻው አይደለም። 

ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሩን፤ በዚህ ዓመት ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ ለ3.8 ሚልዮን ዜጎች የሥራ እድል ተፈጥሯል። ኢትዮጵያ ዛሬ የትልልቅ ኩባንያዎች Remote ሥራ የሚያሰሩበትና የብዙ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች Call center በመሆን ከሕንድ ጋር በመፎካከር ላይ ያለች ሃገር ሆናለች። ይህም ሊሆን የቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባዋቅሩት አዲሱ የክህሎት ሚኒስትር ባመቻቸው የሥራ እድል ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ አቧራ ያስነሳው የኮሪደር ልማት ነው። ፒያሳን ኖሬበታለሁ፤ዶሮ ማነቅያን አቀዋለሁ። ዶሮ ማነቅያ ድሮ መፍረስና መሰራት የነበረበት ሰፈር ነው። የደሃብ ሆቴል ትዝታ አለበኝ፤ እኔም እንደ በርካታ ሰዎች “የፒያሳ ትዝታ አለብኝ” ግን ሰው በትዝታ አይበለጽግም። አዲስ አበባ ውስጥ በርካታ ዜጎች የሚኖሩት አኗኗር ዘግናኝ እንደነበር ነጋሪ አያሻውም። ምእራብ ሃገር ተቀምጦ ትዝታዬ እያለ “ሙሾ የሚያወርደው” ወደ ሃገር ሲገባ እናቱ ቤት እንኳን የማያደር፤ ሆቴል የሚያጣብብ ነው። እሱ ሻወር የሌለበት ቤት ለጥቂት ቀናት እንኳን ማረፍ አይፈልግም፤ ጥሩ መፀዳጃ የሌለበት ቤት ውስጥ መኖር አይፈልግም። ይህ እንዲሻሻል፤ ፈርሶ መሰራት አለበት ሲባል ግን ያዙኝ ልቀቁኝ ይላል፤ ለፖለቲካ ትርፍም እነዚህን ወርቃማ ሥራዎች ያጠለሻል። 

ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ከፍተኛ ለውጥ እያመጣች ለመሆኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እየመሰከሩ ነው። በቅርቡ በዓለም ትልቁ ከሆኑት አንዱ የመዋእለ ነዋይ ፍስት አማካሪ ድርጅት የሆነው Goldman Sachs፤ ኢትዮጵያ ከ25 ዓመታት ገደም በኋላ የዓለማችን 17ኛዋ ትልቁ ኢኮኖሚ ትሆናለች ሲል ተንብይዋል። እንዲህ ዓይነት ትንቢት ዝም ብሎ የሚነገር አይደለም፤ ዛሬ የሚሰራውን ሥራ ወደፊት የሚያመጣውን ውጤት በመገመት የሚተነበይ ነው። ዛሬ እጅህን አጣጥፈህ ለሕዝብሕ መጽዋት እየሰጠህ በማኖር የሚመጣ ለውጥም የሚመጣ እድገትም አይኖርም። ብዙዎች የዶ/ር ዓብይ ነቃፊዎች አንድ የቻይኖች አባብል ነው ተብሎ የሚነገርለትን “አንድን ሰው አሳ ከሰጠኸው ለአንድ ቀን ትመግበዋለህ፤ አሳ ማጥመድ ካስተማርከው ግን እድሜ ልኩን ትመግበዋለህ” የሚለውን አባባል ያላጤኑ ናቸው። በሃገራችን እየተሰሩ ያሉት መሰረተ ልማቶች ለትውልድ የሚሸጋገሩ ናቸው እንጂ፤ ጊዝያዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ብቻ አይደሉም።   

         በአንድ ወቅት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነቡት መሰረተ ልማቶች ሃገራችን በውጥረት ላይ እያለች መሆኑ አስገራሚ መሆኑን ገልጸው ነበር። አዎ የሚገርመው፤ ኢትዮጵያ ይህን ሁሉ ያከናወነችው፤ በጦርነት ውስጥ ሆና፤ በምእራባውያን የማዕቀብ ጫና ውስጥ ሆና፤ በተለይም በዲያስፖራ ያለው ጽንፈኛ ኃይል፤ በውጭ መንግሥታት ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ አገዝ እንዳታገኝ ተግቶ በሚሰራበት ጊዜና፤ እግር ጎታቹ ጎልቶ በሚጮኽበት ወቅት መሆኑ አስደማሚ ነው። ሌላው የሚገርመው፤ በኢትዮጵያ ባልተለመደ መልኩ፤ የፕሮጀክት ሃሳቦች የሚመነጩት በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሆናቸው ብቻ ሳይሆን፤ በየፕሮጀክቱ እየተገኙ ሥራዎችን የሚገመግሙ ጠንካራ ሰራተኛ መሆናቸው ነው። 

እስካሁን ካነሳሁት ውስጥ የጫካውን መሰረተ ልማት አላነሳሁም። ብዙዎች ባለማወቅ፤ አንዳንዶች አውቀው በቅናት “የ7ኛው ንጉስ ቤተ መንግስት” ብለው ሊያኮስሡና ሊያጣጥሉ የሚሞክሩት የጫካ ፕሮጀክት፤ በሺህ ለሚቆጠሩ ወጣቶች የሥራ እድል የፈጠረ ከመሆኑም በላይ፤ ሥራው ሲጠናቀቅ በመቶ ሺህ ለሚቆጠሩ ዜጎች የስራ እድል የሚፈጥር፤ በከተማ ውስጥ እየተገነባ ያለ እራሱን የቻለ ከተማ ነው።የዶ/ር ዐብይ “ብልጭልጭ” መሰረተ ልማት፤ ብልጭልጭ ሆኖ ከተማን፤ ሃገርን ያሳመረ ብቻ ሳይሆን፤ ለሚልዮኖች የሥራ እድልን የፈጠረ፤ ሰው ተኮር የሆነ፤ የበርካቶችን ሕይወት የለወጠ፤ ሊታገዝና ሊበረታታ የሚገባው ነው። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደነገሩን፤ በኮሪደር ልማት ሥራው በየቦታው የተተከሉት መብራቶች፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተመረቱ ናቸው።እነዚህን መሰረተ ልማቶች ለሚያጥላሉ ጥያቄ አለኝ፤ ምን እንዲደረግ ነው የምትፈልጉት? ጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ እግራቸውን አጣምረው ይቀመጡ፤ ምንም ሥራ አይሰራ? ሰላም ይቀድማል ስትል፤ ሰላሙን እያደፈረሰ ያለው ማን ነው ብለህ ጠይቀሃል? አንተው እሳት እየለኮስክ፤ ጭሱ በረከተ ማለትስ ተገቢ ነው። ሰራ ሳይፈጠር፤ የሥራ አጡን ቁጥር መቀነስ ይቻላል? በነገሬ ላይ በርካታ ሰው የሚዘነጋው፤ የኢትዮጵያ መንግስት የሥራ ክፍፍል ያለው መንግሥት መሆኑን ነው።የፀጥታ መዋቅሩ፤ ሰላም የማስጠበቅ ሥራውን እየሰራ ነው፤ ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀን ተቀን ሥራ አይደለም።እያንዳንዱ የሚኒስትር መሥርያ ቤት ሥራውን ይሰራል፤ የሰራውን ሥራ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በዝርዝር ያቀርባል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሥራት ካለባቸው በላይ እየሰሩ ነው። ሃገራቸውን ወደፊት ለማራመድ፤ እንቅልፍ አጥተው እየሰሩ መሆኑን መካድስ ይቻላል?ሲሳሳቱ ማረም፤ ሲያጠፉ ማውገዝ፤ ሲሰሩ ደግሞ ማበረታታት የቅን ዜጎች ኃላፊነት የተሞላው ተግባር ነው። ጦርነት እንዲቆም ከልብህ ከፈልግክ፤ ቦምብ መግዣ ገንዘብ አታዋጣ። 

            ኢትዮጵያ ሰላሟ ይብዛ፤ ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።    

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

3 COMMENTS

  1. ይህን የጻፍከው ስንት ተከፍሎህ ይሆን? አብይ አህመድ መሠረተ ልማት እየሠራ ነው አልክ። መሠረተ ልማት ፓርክ መገንባት የሆነው ከመቼ ጀምሮ ነው? የአንድነት ፓርክ፣ ጨበራ ጩርጩራ፣ ጎርጎራ፣ እንጦጦ ፓርክ እና የጫካው ቤተመንግሥት መሠረተ ልማት የሆኑት ከመቼ ጀምሮ ነው? ባለሀብት ይመስል ፓርኮችን እየሠሩ ቱልቱላ መንፋት ከጠቅላይ ሚኒስቴር የሚጠበቅ አይደለም። አብይ አህመድን አግዝፈህ ሌላውን አሳንሰህ ጽፈሀል። ይሄ ስለአመራርነት ጥበብ ምናምንቴ ያልዘለቀህ እንደሆንክ ነው የሚያሳየው። ምርጥ መሪ ማለት ራሱ ከፕሮጀክት ፕሮጀክት እየዞረ የሚያስመርቅ በታይታ ፍቅር የተጠቃ ሰው ማለት አይደለም። ምርጥ መሪ በስሩ ያሉት ሰዎች ምርጥ ሠራተኛ እንዲሆኑ የሚያደርግ ነው። ይኸውም አንድም ምርጥ ሰዎችን በስሩ በመሰብሰብ፣ ሁለትም ሰዎች በሚመጥኑበት የሥራ መስክ ማሰማራት፣ ሶስትም የሠራተኞቹን ወይም የሚመራቸውን ሰዎች ብቃት ማሳደግ፣ አራትም ባለሙያዎች ነጻ እንዲሆኑ በማድረግ የሚመጣ እንጂ ራስን በማወደስ የሚመጣ አይደለም። ሁሌም የምትጽፋቸው ጽሑፎች ለአብይ አህመድ ውዳሴ የሚያዘንቡ ናቸው። ይኸውም ቅጥረኛ ጸሐፊ እንጂ እውነትን ፈላጊ ላለመሆንህ አስረጂ ናቸው። ሰላምን አናንቀህ አቀረብክ። ኢኮኖሚን ድምጥማጡን ከሚያጠፉ ቁልፍ ጉዳዮች ዋነኛው ጦርነት ነው። ጦርነትን ማስቀረት የማይችል መሪ ደግሞ የማይረባ መሪ ነው። ሰላምን የሚበጠብጡት ሌሎች ናቸው ልትል ሞከርክ። የብልጽግና ደቀመዝሙሮች መለያችሁ ሀፍረት የሚባል ነገር የማያውቃችሁ መሆናችሁ ነው። አማራ ላይ ጦርነት የከፈተው መከላከያ ተብዬው ጨፍጫፊ አይደለምን? አማራ ወደመከላከያ ተብዬው አልሄደ? ብልጽግና መውጣት እንደመግባት ቀላል መስሎት በሶስት ቀን ሱሪ እናስወልቃለን፣ እናጸዳዋለን ብሎ መግባቱን አጥተኸው ነው? ኦሮሚያ ልዩ ሀይል አይፈርስም የአማራ ልዩ ሀይል ግን ይፈርሳል ብሎ ተሾመ ቶጋ የለፈፈውን ረስተኸው ነው? ዝመት፣ ማረክ፣ ታጠቅ፣ የታጠቅኸው ንብረትህ ይሆናል የተባለውና በአብይ አህመድ ሀገሩ ከተነካችበት የማይመለስ እና የአብይን ውዳሴ የማይሻ ነው ተብሎ የተመሰከረለት ፋኖ ክህደት ተፈጽሞበት ትጥቅህን ፍታ መባሉን ሳትሰማ ቀርተህ ነው? ፕሪቶሪያ ላይ ህውሀት ትጥቅ ይፈታል የሚል ፊርማ አኑሮ በማግስቱ አማራ ትጥቅ ፍታ የሚል ከሀዲና ጭራቅ ፓርቲ ብልጽግና መሆኑን ነጋሪ ፈለግህ? ብትዘል ብትፈርጥ የሚሰማህ የለም። ኢኮኖሚ አድጓል እያልህ የምትዘላብደው ለራስህም ጠፍቶህ አይደለም። ኢኮኖሚ የሚያድገው ኢንፍሌሽን ሲቆም፣ ኢንደስትሪዎች ሲስፋፉ፣ ንግድ ሲሳለጥ፣ ኤክስፖርት ሲጨምር፣ የትምህርት ጥራት ሲሻሻል፣ ሥራ ፈጠራ ሲበራከት፣ ምርምሮች ሲስፋፉ፣ ሀገሪቷ ያላትን የማእድን፣ የውሀ፣ የእርሻ መሬት፣ የቱሪዝም ሀብት ወ.ዘ.ተ መጠቀም ስትችል፣ መንገድ ሲሠራ፣ የመጠጥ ውሀ፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ እና ኢንተርኔት ሽፋን ሲጎለብት፣ ቢሮክራሲ ሲቀንስ፣ ሙስና ሲገታ ነው። የአብይ አህመድ አገዛዝ በሁሉም ረገድ የወደቀ ቢሆንም የሀገሪቱን ሁነኛ እስታቲሺያኖች አባሮ ምንደኞቹን በመሾም የሚፈበረከው የሀሰት ዳታ ነው። የእርዳት ስንዴ እየሸጠ ስንዴ ኤክስፖርት አደረግሁ ብሎ የሚያታልል ዋሾ ነው። አብይ አህመድ ሳይነቀል ኢትዮጵያ መፍረሷ አይቀሬ ነው። አብይ እግሬ አውጪኝ ሲል አንተም ጉድጓዷ የጠፋባት አይጥ ሆነህ እናይሀለን።

  2. Nobody said that the PM should be idle. The main question is why there is no plan and involvement of the people in the decision making? If the current corridor project in Addis was done properly residents would have been given reasonable time to vacate and include them in the future development. I remember the discussion in Piassa district which was made after the Government already made the decision. Even then the old houses were demolition within few weeks of the announcement. Those who got replacement residence had to accept unfinished condominiums without proper infrastructure. Most renters became homeless too. It is shame to support Abiy blindly.

  3. ይህ ጸሀፊ እንደዚህ ብሎ ሲጽፍ ጭንቅላቱ የታመመ ብቻ ሳይሆን አረመኔ መሆኑን ነው የሚያረጋግጠው። በዛሬው ወቅት በአገራችን ምድር ፋሺሽታዊ አገዛዝ ነው ስልጣን ያለው። አቢይ አህመድ የሚባል ጭራቅ ሰው ህዝባችንን፣ በተለይም አማራውን እያረደው ነው። በየትኛው አገር ነው እንድ አገዛዝ የራሱን ከውጭ እንደመጣ በመቁጠር በድሮን የሚደበድብ? ለመሆኑ አቢይ አህመድ የሚሰራው ስራ ይታይሃል ወይ? አገሪቱን ምስቅልቅሏን እያወጣት ነው። እንደዚህ ብለህ ስተጽፍ የአንተንም ፋሺዝምነት ነው የሚያረጋግጠው።
    ስለ ኢኮኖሚ ሀሁ የሚገባህ ከሆነ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነታ ማለቂያ በኋላ አዲሱ የጀርመን አገዛዝ ፓርክ መስራት ላይ አይደለም ያተኮረው።ያለ የሌለውን ኃይል በመሰብሰብና በማደራጀት በአዲስ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ኢኮኖሚውን በሁሉም አቅጣጫ መገንባተና ህዝቡን ከረሃብና ከድህነት ማላቀቅ ነበር።

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here