spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትእንደሰጎል ራስ ቀብሮ "ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም"

እንደሰጎል ራስ ቀብሮ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም”

Selam _ Ethiopia _

በእስያኤል ዘ ኢትኤል
ሰኔ 30/2016 ዓ.ም

በዓለማችን ላይ የሰላም ሚኒስቴር እያላት ሰላም ያጣች፣ የሰላም ባህልን ለማስፋፋት ተቋቋሞ ጦርነት የሚያውጅና የሚያስፋፋ፣ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በሀገሪቷ ውስጥ ሰላም እንደብርቅ የታየበት ሀገር ብትኖር የኛዋ ድንቋ ሀገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሲቋቋም ሰላም የሚል ቃል ኢዞ ስለነበር ያልተደሰተ ሰው አልነበረም፤ በተለይም በሀገሪቷ ላይ የነበሩ አንዳንድ ቅሬታዎችንና በደሎችን በዚህ ተቋም የሚፈታ መስሎን ተደስተን ነበር፡፡ነገሩ የገባን ግን ከተቋቋመ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ወደ እርስ በእርስ መባላት ውስጥ ስንገባና አሁን ላይ ሆነን ስናየው ግን ይህንን ሚኒስቴር መ/ቤት ያቋቋሙት በቀጣይ ፍዳችንን እንደሚያበሉትንና ሰላምችንን እንደሚያሳጡትን ታይቷቸው ይመስላል፤ ያው ጠቅላዩ ብዙ ጊዜ ንግርት አለኝ፣የሆነ ነገር ታየኝ ስለሚሉ ነው፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ተልዕኮይ “የዜጋውን፣ የቤተሰብንና የማህበረሰብን ሰላምን በማስጠበቅና በማስከበር፣ ብሔራዊ መግባባትንና አገራዊ አንድነትን በማሳደግ፣ የፌዴራል ስርዓቱን በማጠናከር፣ በቀድሞ ተገኝነት ግጭትን በማስተዳደር፣ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትብብርና ትስስርን በማጎልበት እንዲሁም ተቋማዊነትን በማሳደግ ሁለንተናዊና ዘላቂ ሰላም መገንባት ነው፡፡” የሚል ሲሆን በመሬት ላይ ያለው ሀቅ ግን የሰላም ሚኒስቴር “ጦርነት ያውጃል፣በሀገሪቷ ላይ ያሉ ሰላም የሆኑ ነገሮችን መጦ በብጥብጥና ረብሻ ይተካል፣ ሰላማዊ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ያጠፋል ግጭት ይጠነስሳል፣ ሀገራዊ የግጭት አፈታቶችን ያረክሳልና ማህበረሰቡ እንዲንቃቸው ያደርጋል፣ ማህበራዊ እሴቶችን ያረክሳል፣በቀጠና ጠብ ጫሪና ተቀባይነት የሌላ ሀገር በመገንባት አውንታዊና አሉታዊ ሰላም የሌላት ሀገር ይፈጥራል” ከዚህ አኳያ የተሻለ ተቋም መገንባት ተችሏል፡፡

ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሰሞንኛ ኢዞልን ከመጣው አጀንዳ መካከል በሰላም ሚኒስቴር የሰላም ግንባታና ብሄራዊ መግባባት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ከይረዲን ተዘራ(በአቶ ታዬ ደንደአ ቦታ ተተክተው የተሾሙት) “ሰላም ለሁሉም ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በተመሳሳይ ሰዓት የሚካሄደውን የሰላም ሩጫ አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ለጋዜጠኞች በሰጡት ማብራሪያ የሰላም ሩጫው ዋነኛ አላማ በሀገራችን የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም( ሰላም የሚለው ቃል ጦርነት የሚል ትርጉም ካለው)  የበለጠ እንዲያጠናክሩና ሁሉም ዜጋ ለሀገራችን ሰላም የባለቤትነት ስሜትን ለመገንባት ፤መላው ኢትዮጵያዎያን ለሀገራችን ሰላም በጋራ እንዲሰሩ መነሳሳትን መፍጠር እና መንግስታቸው ለሰላም (በሚኒስቴር መ/ቤቱ ተልዕኮ መሰረት ለጦርነትና ለብጥብጥ ማለታቸው ነው) የምንሰጠውን ዋጋና ለሰላም (ለጦርነት ተብሎ ይወሰድ) ያለንን ፍላጎት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ጥሩ ነገር ዓለም ሰላም የማይፈልግ ጦረኛ መንግስት እንደሆኑ አውቆ፣ ሰርዓቱን ጊዜና ጉዳት በማያመጣበት መንገድ ማስወገድ ይቻላል በሚልበት ሁኔታ ላይ እየመከረ ባለበት ጊዜ መሆኑ፣ የጦረኝነት ባህሪያቸውንና የጦርነት ፍላጎታቸውን እነሱም ከተረዱት በላይ ፍላጎታቸውን አውቆላቸው በሆነበት ሰዓት ነው፡፡ 

ሚኒስትር ዴኤታው አስከትለውም የተረጋጋ እና ዘላቂ ሰላም በመገንባት የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅ የመንግስት ተቀዳሚ ተግባር ነው ያሉ ሲሆን ማህበረሰቡም የሰላም ባለቤት እንዲሆኑ የሚያስችል ታላቅ የሰላም ሩጫ እንደሆነ ተናግረው ሩጫው በሁሉም ክልል ከተሞች እንደሚካሄድ በመግለጫውቸው የገለጹ ሲሆን የሳቱት ነገር ቢኖር የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና መጠበቅ ያልቻለው መንግስታቸው የእነዚህ ሁሉ ችግሮች መንስኤ መሆኑን የዘነጉት ወይም ጠቅላዩ እንደሚሉት ጥሩ ጥሩውን ለነሱ መጥፎን ደግሞ ባለማውራት አልፈውታል፡፡

አንድ ትልቁ ነገር ሰላምን ለማምጣት የመንግስት፣የማህበረሰቡና ሌሎች መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የጋራ ስራ የሚጠይቅ ሲሆን በተለይም አሉታዊ ሰላም ወይም የህግ የበላይነትን የሚያመጣው መንግስትና መንግስት ብቻ ነው፡፡ይህንን ለማድረግ ተስኖት ብዙ አማራዎች በዘር ሀረጋቸው ተቆጥሮ በየቦታው ሲገደሉና የዘር ጭፍጨፋ ሲደረግባቸው ሰላም ሚኒስቴር ግቡ እንደተሳካላቸው በዝምታና ተጠያቂነት እንዳይሰፋን ሆኖ ብሎ ሲያልፍ አማራው ህዝብ ድምጼን ስሙኝ ሲል ጆሮ ዳባ ተባለ፣ በተደጋጋሚ በጉልበቱ ሰልፍ ወጣ በመንግስት ሃይል እየተደበደበ የሚሰማ ጆሮ ግን አልነበረም፡፡ እንደውም በመከራውና በሞቱ የሚሳለቁ በዙ በስተመጨረሻም “ይሄ የመጨረሻይ ሰልፍ ነው” ብሎ ወጣ የሚሰማ ጠፋ በዚህም መፍትሄ ባለው ነፍጥ አንግቶ ዱር ቤቴ አለ፡፡በኦሮሚያም በተመሳሳይ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር በወለጋና በአንዳንድ አከባቢዎች የሚደርስብትን በደል በንግግር እንፍታ አለ፤ ሰሚ ጆሮ ጠፋ በዚህም ለኦሮሞ የነጻነት ሠራዊት ምስረታ በር ከፍተ፣ ትጥቅ ትግም ተጀመረ፡፡ በትግራይም የፌደራል መንግስቱና ክልሉን እያስተዳደረው ያለው ህውሀት አለመግባባቱን ለመፍታት ተብሎ ሽማግሌና የቀድሞዋ የሰላም ሚኒስቴር ሄዱ፣ አለቀሱ፣ ነገር ግን ከሽምግልናውና ድርድር ይልቅ ለሽምግልና የሄደው ኮሚቴ ውስጥ የሚከበሩ ዜጎች ሲፈተሹ በማሳየት ህዝቡን ለጥላቻና ለጦርነት አዘጋጁት፡፡ ጦርነትም ተካሄደ ከአንድ ሚሊዩን የሚበልጥ ሰው ህይወቱን አጣበት፡፡ ነገር ግን እስካሁን ማንም ተጠያቂ አልሆነም የብልጽግነሰው መንግስት ሀገሪቷ ላይ ሰላም ላመጣ እየሮጥኩ ነው ይለናል፡፡

መንግስት ራሱን እንደ ሰጎን ቀብሮ የዚህች ሀገር ሰላም የሚመጣው አባላቴን ሰብስቤና ቲሸርት አድይ በየክልሉ ከተሞች በእኩል ሰዓት ስሮጥ ነው ብሎ መጥቷል፡፡ የሰላም ሚኒስትር የሆኑት አቶ ብናልፍ አንዱአለም ባስተላለፊት መልዕክት  ”እኛ ኢትዮጵያዊያን ከሁሉም ነገር በላይ ምርጫችቸን እና ፍላጎታችን ሰላም ነው። ይህን ፍላጎታችንን እና ለሰላም ያለንን ቁርጠኝነት ለዓለም እናሳያለን።” ያሉ ሲሆን ሚኒስትሩ ያልተረዱት ነገር ቢኖር እኛ ኢትዮጵያን  እሳቸው እንዳሉት ምርጫችን ሰላም ቢሆንም የእሳቸው  መንግስት አጭበርብሮ ስልጣን እንደሚይዝበት ምርጫ ግን አይደለም፡፡የህዝቡ ፍላጎቱ ሰላም ነው፣ ለፕሮፖጋንዳና ለፖለቲካ ጥቅም ሲባል የሚደረግ ሳይሆን ሀቀኛና ከህዝብ ፍላጎት የመነጨ፣ ወንጀለኞች ተሰብስበው የሚሰብኩት ትርጉሙ ጦርነት የሆነ  ሰላም ሳይሆን ከምስራቅ እስከ ምዕራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን ያውለ ኢትዩጵያዊ በሰላም ውሎ ማደር ምን ማለት የሚገንዘበው ዜጋ  በሚፈልገው ደረጃ መሆን አለበት፡፡

ሰላምን ለማምጣት ያለው የተሻለው በሰላማዊ መንገድ ሲሆን በተለይም ጥያቄችን በሰላማዊ መንገድ አልሰማልን አለ ብለው ነፍጥ ወደ ማንሳት የሄዱትን አካላት ወደ ጠረጴዛ ለማምጣት በዳዬች ከልብ የመነጨ ይቅርታ ህዝብን በመጠየቅ፣ ለተፈጸሙ ወንጀሎች ወንጀለኞችን ለፍድር ማቅረብና በሀቀኛ የሆነ የሽግግር ፍትህ እንዲኖር በማድረግ፣ሀገሪቷ መጻይ እድል ለመወሰን የሚያስችል የሽግግር መንግስት በማቋቋም ሀገርቷ የተጋረደባትን አደጋ መቀልበስ ሲቻል ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ከእውነታው የራቁ እርምጃዎችን በመውሰድና ትልቁን ችግር ባላወቀና በልሰማ ማለፊ ብዙ ያስከፍለናል፣ እያስከፈለንም ይገኛል፡፡ አውንታዊ ሰላም ለማምጣት ጥረት የሚያደርጉትን መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የምዕራብያን ስላይ፣ የሸፍጥ መሳሪያና ጥቁር ሪፖርት አቅራቢ አድርጎ ማሰቡን በመተው ለሰባዓዊ መብት፣ መልካም አስተዳደር፣ ዲሞክራሲ፣ ፍትህና ሌሎች ማህበራዊ ጉዳዬችን የተቋቋሙ መሆኑን በመረዳት በነጻነት እንዲሰሩ ድጋፍ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡መንግስት ከቅዠት አለሙ ወጥቶ ከእውነታው ጋር መታረቅ ይኖርበታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ አለም በሀገራችን ላይ የሚሰራውን እያንዳንዷን ነገር ያውቃል፣ይከታተል፡፡ለዚህም ማሳያ ኢትዮጵያ ውስጥ የምትካሄደውን እያንዳንዱን ነገር በሪፖርት ይዘግባል፣ተጠያቂነት እንዲኖር ይጠይቃል፡፡ስለሆነም የሚታየውን ትልቁን ችግራችን ትተን በሽብርቅና ገጽታ ግንባታ ጊዜና ገንዘብ ማጥፋቱን ትተን ችግሩን ለመፍታት ቁርጠኛ በመሆን ወደ መፍትሄ መሄዱ ነገ ዛሬ የሚባል አይደለም፡፡

ሰላም ለሰው ዘር በሙሉ!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here