spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትየሽግግር ፍትሕ እና ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ (በዳዊት ወልደጊዮርጊስ )

የሽግግር ፍትሕ እና ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ (በዳዊት ወልደጊዮርጊስ )

Translated from the English version (https://www.africaisss.org) 

የሽግግር ፍትሕ እና ብሔራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ (በዳዊት ወልደጊዮርጊስ )

 በዳዊት ወልደጊዮርጊስ 

ጭምቅ ሃሳብ (Summary) 

የሽግግር ፍትሕ ማለት ሕዝቦች ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙባቸውን ሁለገብ ጥሰቶችን አርመው  ከአምባገነን አገዛዞችእና ከእርስ በርስ ውጊያዎች ወደ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚሽጋገሩበት የተሞከረ  የተመሰከረለት ስርአት ነው። የሽግግር ፍትሕ፤ ዕውነታ (እውነትን ማውጥት)፣ ፍትሕ እንዲሰጥ እና  ካሳዎች እንዲከፈሉ በማድረግ ሁሉንም ወገን ለእውነተኛ እርቅ ያዘጋጃል። እንዲሁም ወንጀሎች  እንዳይደገሙ፣ በመጨረሻም ሰላማዊ አብሮነት እንዲዳብር ዋስትና ይሰጣል። ይህ እንደ ኢትዮጵያ ላለ  በርስ በርስ ወጊያ የቆሰለ አገር፣ ተጨማሪ የዘር ማጥፋት እና የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይፈጠር  የሚያስፈልግ ሂደት ነው። የ120 ሚሊዮን ሕዝብ ደህንነት አደጋ እንዳይጋረጥበት ያደርጋል። ይህ  የሽግግር ፍትሕ እንዲመሰረትና ፣ ዓላማውም እንዲሳካ ለማድረግ ምን ዓይነት ትግል “ያስፈልጋል?”  የሚለውን ሃሳብ የሚያጭር ነው። አምባገነን ሲርአቶች ካልፈረሱ የሽግግር ፍትሕ ሊመሰረት  አይችልም። ይህ የመጀመሪያው ቅድመ ሁኔታ ነው። ይህ መንግስት ተብየው የግል ኩባንያ በውድ  ሰለማይለቅ እንደተጀመረው በሕዝቡ አመጽ ማስወገድ አማራጭ የለውም አለበት። በማንኛውም  አስፈላጊ መንገድ መብቶቹን ማስከበር እና ፍትሕ፣ ዕኩልነት እና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን  መብትን ማስጠበቅ የሚቻለው ለአዲስ ሰርአት የሽግግር ፍትሕ መዋቅር በአገራዊ ደረጃ ሲቕቕም ብቻ  ነው። የፋኖ ንቅናቄ ፍትሐዊ፣ አስፈላጊ እና ለውጥን ለመጎናጸፍ ብቸኛው መንገድ ነው። ይህ ጽሁፍ  ስለሽግግር ፍትሕ እና የተቀሰሙ ተመክሮዎች የሚያትት ነው። 

“ሰላማዊ አብዮት እንዳይካሄድ የሚያደርጉ ወገኖች፣ ነውጠኛ አብዮትን አይቀሬ ያደርጉታል”  – ጆን ኤፍ ኬኔዲ 

አምባገነኖች በገዛ ፈቃዳቸው ከስልጣናቸው ቢለቅቁ፣ ቀጣዩ የሽግግር ሂደት ያነሰ ደም አፋሳሽ እና  ውስብስብ እንዳይሆን መንገዱን ለመጥረግ ይቻል ነበር። ግና አምባገነኖች በፈቃዳቸው ስልጣናቸውን  ለመልቀቅ አይፈልጉም። ምክንያቱም የራሳቸው ሰብዕና በአመክንዮ እንዲያስቡ ዕድሉን  አይሰጣቸውም። ከእነርሱ ቀጥሎ ስልጣን የሚይዘው ግለሰብ አይቀጡ ቅጣት እንደሚቀጣቸው  አስበው እንዲፈሩ ያደርጋቸዋል። “ሊለወጡ ነው” ብላችሁ እያሰባችሁ ሳለ፣ አምባገነኖቹ ሁለት እርምጃ  ወደኋላ ይራመዳሉ። ይልቁንም ከቀድሞው በባሰ መጠን ጨካኞች ይሆናሉ።  

እጅግ በርካታ ሁነቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ፣ አምባገነኖች ስልጣናቸውን ለሌላ አሳልፈው ለመስጠት  ፈቃደኞች አይደሉም። ምክንያቱም አንድ ጊዜ መንበረ ስልጣኑን ከተቆናጠጡ መልቀቅ እንደማይችሉ  ራሳቸውን ያሳምናሉ። ለመልቀቅ ቢፈልጉ እንኳ አይሆንላቸውም። ወደ ስልጣን የመጡበት እና  በስልጣን ውስጥ የዘለቁበት መንገድ በዘር ማጥፋት፡በግድያ፣ በቶርቸር፣ በማፈናቀል እና በውድመት  የተሞላ ስለሆነ ከስልጣን ሲወርዱ ተጎጂዎቹ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ እንደሚችሉ ያውቃሉ። የሚፈጸሙ ወንጀሎች በየዓመቱ ቁጥራቸው እየተመነደገ ይመጣል። ለዚህ መንስዔው እንደዐቢይ  አሕመድ ያሉ በራሳቸው ፍቅር የተነደፉ እና የታመሙ አምባገነኖች በአመክንዮአዊ አስተሳሰብ አደብ  የተገዙ ሰላልሆኑ ነው። ስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ፣ ባለ በሌለ አቅማቸው ከፍተኛ ጭቆና መፈጸም  ብችኝ አማራጭ ይሆናል። 

“እስኪ፣ አስቡት! አንድ የአገር መሪ በየዓመቱ የሚጫወተው አንድ ጨዋታ አለ። በዚህ ጨዋታ  ላይ ‘አሁን ጡረታ ብወጣ ለእኔ ምን ጥቅም ይኖረዋል? ወይስ በሚቀጥለው ዓመት ጡረታ  ለመውጣት ከባድ የሚያደርግብኝን ሌላ ወንጀል ፈጽሜ ይሄኛው የአገዛዝ ዘመኔ አስተማማኝ  እንዲሆን ላድርግ?’ በማለት ያንሰላስላል። መልሱ ቀላል ነው። ከስልጣን የመፈንቀል ዕድሉን  አነስተኛ እንዲሆንለት በማሰብ ሌላ ወንጀል መፈጸሙን ይመርጣል። በየእያንዳንዱ ዓመት  ይህንን ጨዋታ ደጋግሞ ይጫወታል። በተጫወተ ቁጥርም፣ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ  ይደርሳል። እንግዲህ የመሪው ድምዳሜ ሙሉ በሙሉ ከምክንያታዊነት የተራራቀ ወይንም  ወጥ ያልሆነ አይደለም።”

የዕውቅ አምባገነን መሪዎች ፍጻሜ 

የሊቢያው ሙዓመር ጋዳፊ 

የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ተደብቆ ሳለ በሊቢያ ታጣቂዎች ተያዘ። ታጣቂዎቹ ከቱቦ  አውጥተው ከደበደቡት በኋላ፣ ጥይት ተኮሱበት፤ ገደሉት። ከገደሉት በኋላ ጸጉሩን በሳንጃ ቆራረጡት።  አስከሬኑን እየጎተቱ በመውሰድ ለሕዝብ ዕይታ አደባባይ ላይ አሰጡት። በመጨረሻም፣ አንድ የገበያ  ማዕከል ውስጥ ባለ ማቀዝቀዣ ውስጥ አስቀመጡት።  

የጣሊያኑ ሙሶሊኒ 

ናዚ ጀርመን ለዓመት እና የተወሰኑ ወራት ከመፈንቀል በማዳን መልሶ ስልጣኑን እንዲቆናጠጥ  አስችላው ነበር። ግና የኮሙዩኒስት አቀንቃኞች ሙሶሊኒ እና ባለቤቱ ወደ ስፔን ሊያመልጡ ሲሞክሩ  ያዟቸው። ሁለቱም በጥይት ተደብድበው፣ ሚላን ከተማ ባለው የነዳጅ ማደያ አስከሬናቸው ተዘቅዝቆ  ተሰቀለ።  

የኒካራጓው ሳሞሳ 

የሳንዲኒስታ ሶሻሊስት ፓርቲ መንበረ ስልጣኑን ሲቆናጠጥ፣ ሳሞሳ አብዛኛውን የአገሪቷ ሃብት  አግበስብሶ፣ ኒካራጓን ጥሎ ፈረጠጠ። በመጨረሻም፣ አይስንቲዮን ከተማ ውስጥ የግል መኪናውን  እያሽከረከረ ሳለ፣ ከተላከበት ገዳይ ቡድን ጸረ ታንክ (RPG) መሳሪያ ተተኮሰበት። ወዲያውኑ  የቀድሞው አምባገነን መሪ ከእነመኪናው ተቃጥሎ ሞተ። 

የሩማኒያው ኒኮላይ ቻውሼስኩ 

ለአንድ ሰዓት ንግግር ከተደረገ በኋላ፣ በአደባባይ የተሰበሰበው ሕዝብ ለንግግር አድራጊው መሪ  ተቃውሞውን ማዝነብ ጀመረ። አገር አቀፍ እምቢተኝነት ተጫረ። እርሱ እና ሚስት አገሪቱን ለቅቀው  እንዲወጡ ተገደዱ። ይሁንና በፖሊስ ተይዘው ለጦር ሰራዊቱ ተላልፈው ተሰጡ። ፍርድ ቤት ቀርቡ።  የኢኮኖሚ አሻጥር “ፈጽመዋል” በሚል የጥፋተኝነት ብይን ተላለፈባቸው። ከዚያም የጥይት ዶፍ ዝናብ  ዘነበባቸው፤ ተገደሉ። 

የዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎው ሞቡቱ ሴሴ ሴኮ 

ግንቦት 8 ቀን 1989 ዓ.ም.፤ በሎረን ዲዚሬ ካቢላ የሚመሩ ታጣቂ ሃይሎች አገሪቱን በሃይል  ተቆጣጠሩ። ሞቡቱ አገሪቱን ለቅቆ እንዲሰደድ አደረጉ። በሙስና ድርጊቱ እና ቅንጡ የሕይወት ዘዬው ይታወቅ ነበር። በከፍተኛ የካንሰር በሽታ ሲማቅቅ ቆይቷል። አውሮጳ እና ሞሮኮ ወደሚገኙ ምቹ  መኖሪያ ቤቶቹ እየተጓዘ ሳለ ሕይወቱ አለፈች። 

የዩጋንዳው ኢዲ አሚን 

ሚያዚያ 3 ቀን 1971 ዓ.ም.፤ የታንዛኒያ ጦር እና ሌሎች ታጣቂ ሃይሎች በተሳካ ሂደት ካምፓላን  ተቆጣጠሩ። አሚንን ከመንበረ ስልጣኑ ፈነቀሉት። በጭካኔው በጣም የታወቀ ነበር። በእርሱ የተነሳ  300 መቶ ሺህ የዩጋንዳ ሲቪል ዜጎች ለሞት ተዳርገዋል። አሚን ወደ ሳዑዲ አረቢያ ከተሰደደ በኋላ፣  በሕመም ምክንያት ሞቷል። 

የማዕከላዊ አፍሪካ ሪፑብሊኩ አጼ ቦካሳ 

የናፖሊዮንን ፈለግ በመከተል ራሱን “አጼ” ብሎ የሾመው ቦካሳ ከፈረንሳይ በስተቀር የሌሎች አገራት  ዕውቅና ተነፍጎት ነበር። ከሹመት ስነ ስርዓቱ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ከስልጣኑ ተፈንቅሏል።  የአውሮጳውያን በሆነ ነገር ላይ ሁሉ ፍላጎቱ ይንራል። በአንድ ታጣቂ ቡድን ስልጣኑን ተነጠቀ።  የተፈረደበት ፍርድ ግን በአገሪቱ አንዲት መንደር ውስጥ ደሃ እና ታማሚ ሆኖ እንዲኖር ነበር። በዚያም  ለሞት ተዳረገ። 

የሶማሊያው ዚያድ ባሬ 

የሶማሊያው የትጥቅ አመጽ ዚያድ ባሬን ወደ እርስ በርስ ጦርነት እንዲገባ አደረገው። አመጹ ባሬ  መጀመሪያ ወደ ኬንያ እንዲሰደድ አስገደደው። ግና የጥገኝነት ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ቀረ።  ከዚያም ወደ ናይጄሪያ ተጓዘ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ወደ ሆስፒታል እየተጓዘ በነበረበት ሰዓት ሊሞት  ቻለ። 

የላይቤሪያው ቻርለስ ቴይለር 

በሚያዚያ 18 ቀን 2004 ዓ.ም.፣ የቀድሞው የላይቤሪያ ፕሬዝዳንት ቻርለስ ቴይለር አስገድዶ  መድፈርን እና የሴት ልጅ ግርዛትን ጨምሮ፣ ሴራሊዮን ውስጥ አሰቃቂ የጦር ወንጅሎች እንዲፈጸሙ  በማነሳሳት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑ ተረጋግጦ ነበር። 

የሱዳኑ አል በሺር 

ከበርካታ ወራት አመጾች እና ሕዝባዊ ንቅናቄዎች በኋላ፣ አል በሺር በሱዳን ጦር ሃይሎች ከመንበረ  ስልጣኑ ወረደ፤ ሚያዚያ 3 ቀን 2011 ዓ.ም.። ወዲያውኑ በቁም እስር እንዲቆይ ተደርገና የሽግግር  ምክር ቤት ተቋቋመ። 

መንግስቱ ሃይለማርያም 

ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት በአምባገነንነት እና በአስከፊ የፖለቲካ ስርዓት ገዝቷታል። የህወሓት ሃይሎች  መዲናይቱን ከበባ ውስጥ ሲያስገቧት ወደ ዝምባብዌ ኮበለለ። በጅምላ ፍጅቶች ፍርድ ቤት  የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተላልፎበታል። በሌለበት የሞት ፍርድ ተፈርዶበታል።

የአቢይ አገዛዝ ፍጻሜ የሚጓዘው በየትኛውም አቅጣጫ ቢሆን፣ አገሪቱ በመጨረሻ የምትደርሰው  የሽግግር መንግስት ምስረታ ላይ ነው። ይህም የሚሳካው ረዥሙ አታካች የፈውስ እና የማረጋጋት ስራ  ወደ ጥሩ ሰዎች እጅ ገብቶ ከተጀመረ ነው። ይህ ጽሁፍ በዚህ ሂደት ሁለተኛው ክፍል ላይ ያተኩራል። (የሽግግር መንግስት መቕቕም የመጀመሪያው ሆኖ) የዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ ሂደት እንዲጀመር  ወይም በሌላ አባባል የሽግግር ፍትሕ ዓላማውን፣ ማለትም ሰላማዊ አብሮ የመኖር እሴት ማረጋገጥን  እንዲያሳካ፣ አገዛዙ እንደተወገደ ወዲያውኑ ተግባራዊ መሆን ይኖርበታል። ይህ ሂደት የሕግ እና ከሕግ  ባሻገር ያሉ አሰራሮችን የሚያካትት ይሆናል። 

ወደ ሽግግር ፍትሕ እና ዘላቂ ሰላም የሚመሩ ተከታታይ ሁነቶች እንደሚከተለው የቀረቡት ናቸው፦ 

1 የአቢይ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ ሁሉን-አቀፍ የሽግግር መንግስት ምስረታ 2 እነዚህ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገ ብሔራዊ ኮንፈረንስ ማቋቋም 

• የዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ ሂደት ምስረታ 

• የሕገ መንግስት አርቃቂ ኮሚሽን ምስረታ 

• የምርጫ ቦርድ ኮሚሽን ምስረታ 

• ሪፈረንደም 

3 አገሪቱን የማረጋጋት ሂደት 

4 ምርጫ 

እነዚህ አራት ጉዳዮች ናችው የሽግግር ፍትህ ተብለው የሚታወቁት። አንዱን ከአንዱ በተናጠል መመልከት  አይቻልም። 

ከእነዚህ ተከታታይ ክንውኖች በፊት አገዛዙን ለማስወገድ የሚያበቁ የተለያዩ ሁኔታዎች ይከሰታሉ።  የሂደቱ አጠቃላይ ክንውን ዘርዘር ባለ መልክ እኔ ካዘጋጀሁት ሌላኛው ሰነድ ውስጥ ይገኛል። ይህ ጽሁፍ  የሚያተኩረው በሽግግር ፍትሕ ሚና ላይ ይሆናል። ይኸውም፣ ከሕገ ወጥ መንግስት ጋር ጦርነት  በሚደረግባት አገር – ኢትዮጵያ ውስጥ፤ እልባት ሊኖረው የሚችለው የዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ  ኮሚሽን ሲመስረት ነው። በአራት ነጥቦች ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል፦ 

ዕውነትን መፈለግ (ወይም የዕውነታ ፍለጋ)  

ከስርዓቱ ውጭ (independent) የሆኑ አካላት የዘር ማጥፋት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ የጦር ወንጀሎች እና የገፍ ማፈናቀሎች ላይ ምርመራዎችን ይጀምራሉ። እውነታዎች ሁሉ ዪውጠሉ።እነዚህን ምርመራዎች በሚያካሂዷቸው የተለያዩ ክስተቶች፤ ውንጀሎች ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በያዟቸው ዓላማዎች ጭምር መመልከቱ ተገቢ ይሆናል። 

እጅግ አስከፊ በሆኑ ወንጀሎች ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸው ወንጀለኞች በፍትሕ በኩል ማለፍ አለባቸው። ተገቢዊን ቅጣት ያገኝአሉ። ባሕላዊ (አካባቢያዊ) የፍርድ ስርዓቶች ትንንሽ ወንጅሎችን ሊዳኙ ይችላሉ። 

ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚሰጡ ካሳዎች የተለያየ መልክ ያላቸው ናቸው፤ በግለሰብ፣ በቡድን፣ በቁሳዊ እና በተምሳሌታዊ መልኩ ማለት ነው። 

ይቅር ባይነት እና ብዝሃነትን አክብሮ በሰላም የመኖር ቁርጠኛ ፍላጎትን ጨምሮ፣ አብሮ ለመኖር ሲባል በዕርቅ ጣናቀቃል። እርቅ በትእዛዝ ሊሆን ሲለማይችል። ያልተማከለ የስልጣን ክፍፍልን ለማረጋገጥ ሲባል የፌደራል አደረጃጀትንም አይነት መምረጥን ያካተተ ዪሆናል።

ሁለንተናዊ የሕግ የበላይነት 

ሁለንተናዊ የሕግ የበላይነት ማለት ተጠያቂነት፣ ፍትሐዊ ሕግ፣ ግልጽና አሳታፊ መንግስት እና ገለልተኛ  የፍትሕ ስርዓትን የሚያካትት ነው። የሽግግር ፍትሕ እና የሕግ የበላይነት በግልጽ የሚታይ  ተመሳሳይነት አላቸው። እንዲሁም ለድሕረ ጦርነት ማሕበረሰቦች የሚሆኑ ተመሳሳይ የአስተሳሰብ  ማዕቀፎች እና ውጤቶች አሏቸው። በግጭት እና ድሕረ ግጭት ወቅቶች የሕግ የበላይነት መኖር  “አለበት” ሲባል፣ ያለፉትን ጨቋኝ መንግስታት ማፈራረስ፤ የጦር ወንጀሎች ከፈጠሯቸው ጠባሳዎች  መፈወስ እና የፍትሕ ተቋማትን መመስረት ማለት ነው። እነዚህም ከዓለምአቀፍ ሕጎች እና የሰብዓዊ  መብት ድንጋጌዎች ጋር ስሙም መሆን ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ ሁኔታ የሕዝብን አመኔታ ዳግም  መፍጠር እና የሲቪክ ማሕበረሰቡን ማጠናከር ከእነዚሁ ጋር ተካታች ናቸው። የሽግግር ፍትሕ ያለፉት፣  በጨቋኙ አገዛዝ የተፈጸሙ ወንጅሎች እና ነውጠኛ የፖለቲካ ስርዓት ላይ ትኩረቱን አድርጎ ይሰራል። የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እና አምባገነን ስርዓቶች ስልጣን ላይ እያሉ፣ ጦርነት እና ግጭቶች አይቀሬ  ናቸው። እንደእነዚህ ያሉ ጨቋኝ አገዛዞች ሲሸነፉ፣ የሚከተሉት ጥያቄዎች መነሳታቸው አይቀርም፦ 

• አገሪቷን እና ማሕበረሰቡን እንዴት መልሶ መገንባት ይቻላል? እና 

• እንዴት ያለፉትን ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶች ድግግሞሽ መከላከል ይቻላል? 

ለእነዚህ ጥያቄዎች ከሚሰጡ ምላሾች አንደኛው የሕግ የበላይነትን መልሶ ማቋቋም ነው። ይሁንና  በጦርነት፣ በግጭት ወይም በጨቋኝ አገዛዝ የደቀቁ ማሕበረሰቦች ውስጥ የሕግ የበላይነትን ማስፈን  ቀላል ስራ አይደለም። በቁጥር በርካታ የሚሆኑ ብዥታዎች እና ተግዳሮቶች በሂደቱ ውስጥ አሉ።  ከጦርነት ማብቃት ወይንም ከአንድ ጨቋኝ መንግስት ውድቀት በኋላ፣ ጠንቀኛውን የኋላ ታሪክ ምን  ማድረግ እንደሚቻል የሚነሳው ጥያቄ በጣም አስፈላጊ ነው። በተመሳሳይ ጊዜ እጅግ መራር ከሆኑ  ጥያቄዎች መካከል፣ አንዱ ነው። በዚህ አውድ ከሄድን የሚከተለው ጥያቄ ይቀርባል። የሕግ የበላይነትን  ወደ ቦታው ለመመለስ ጠንቀኛውን የኋላ ታሪክ መመርመር ምን ጥቅም ይሰጣል? ወይም  ማሕበረሰቡን ያለፈውን ታሪክ እንዲመለከት መግፋት ለአዲስ ግጭቶች እና ችግሮች መፈጠር ክፍተት  ይፈጥር ይሆን? ከጠንቀኛው የኋላ ታሪክ ጋር ሊኖር የሚገባው ግንኙነት የሕግ የበላይነት ለማስፈን  ከሚያስፈልጉ ቁልፍ ነጥቦች አንደኛው መሆኑን ልምዶች እና አመክንዮ በጋራ ያሳያሉ።  

የሽግግር ፍትሕ ከሕግ የበላይነት ጋር መሳ ለመሳ ላይሄዱ ይችላሉ። ምክንያቱም የሕግ የበላይነት ኋላ ተኮር ፍትሕ ላይ መሰረቱን የጣለ ይሆናል። ግን ይህን መሰሉ ፍትሕ ከአስከፊ ጦርነት እና ግጭት  ለወጡ ማሕበረሰቦች የወደፊቱን አቅጣጫ የሚተልም ብቸኛ መንገድ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። ያለፍትሕ ሰላም አይኖርም። እንደብቸኛ መንገድ የሚታሰበው አጠቃላይ የሆነ የሽግግር ፍትሕ  ስትራቴጂ የሕግ የበላይነትን መልሶ ወደ ማረጋግጥ ጉዞ አገሪቷን ሊያሳልጥ ይችላል። እንዲሁም  በተወሰነ መጠን ዲሞክራሲ እና ዘላቂ ሰላምን የማስፈን ዕድል አለው። 

ሕግ የፍትሕ ስርዓቱ አንድ አካል ነው። ይህም አስተማሪ ቅጣቶችን በመጠቀም፣ የመከላከል እና  የምርመራ ሒደቶች ላይ ያተኩራል። ሕጉ በራሱ ኢ-ፍትሐዊ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም የሕጉ  አርቃቂዎች ሕገ ወጥ ወይም ስሁት ዕይታ ያላቸው ከሆኑ፣ ፍትሐዊነት ይዛባል። ሰብዓዊነት እና  ሞራላዊ እሴት የሚፈልጉትን ያህል ፍትሐዊ ብይን የመስጠት ዕድሉ ዝቅተኛ ይሆናል። 

ማርቲን ሉተር ኪንግ እንዲህ ሲል ተናግሮ ነበር፣  

“የሰውን ልጅ ሰብዓዊነት ከፍ የሚያደርግ ማንኛውም ሕግ፣ ፍትሐዊ ነው። የሰውን  ሰብዕና የሚያቃልል ማንኛውም ሕግ ደግሞ ኢ-ፍትሐዊ ነው። ሁሉም ከፋፋይ ዓዋጆች ኢ ፍትሐዊ ናቸው። ምክንያቱም ከፋፋይነት የሰውን ስሜት የሚያዛባ እና ሰብዕናን  የሚደመስስ ነው። የክፍፍል ዓዋጆቹ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ላይ የተሳሳተ የበታችነት  ስሜትን ይፈጥራል። ሕጉ ኢ ፍትሐዊ ከሆነ፣ አንድ ሰው ሕጉን ያለማክበር ብቻ  ሳይሆን ለሕጉ ያለውን እምቢተኝነት የማሳየት መብት አለው።” 

ከኢትዮጵያ ጉዳይ ጋር አስተሳስረን ካየነው፣ ፋኖ የሚዋጋው ሕገ ወጥ የሆነን ሕግ የሚተገብረውን  አገዛዝ ነው። ስለዚህ ትግሉ ፍትሐዊ ነው። 

አጸፋዊ ፍትሕ (Retributive Justice) ማለት በአንድ ፍትሐዊ ሕግ ስር የሚከወን የፍትሕ ዓይነት  ነው። እንዲህ ያሉ ሕጎች ትኩረታቸው ወንጀለኞችን መቅጣት ላይ ነው። በኢ-ፍትሐዊ ሕግ ስር፣  የተወሰኑ ወንጀለኞች ያለምንም ቅጣት ታልፈው በሰላም እንዲኖሩ ይደረጋል። ሆኖም ግን በፍትሐዊ  ሕግ ስር፣ ወንጀለኞች በፈጸሙት የወንጀል ድርጊት ልክ ቅጣት ይሰጣቸዋል። ይህም “አጸፋዊ ፍትሕ” ይባላል። አጸፋ ማለት በምላሽ ወይም ብቀላ እሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በተጨማሪም፣ መጽሐፍ  ቅዱስ ወይም ቁርዓን ውስጥ እንደሚጠቀሱ የፍትሕ አባባሎች ሁሉ፣ በዕኩልነት እና ቀጥተኛ ምላሽ  ላይም መሰረቱን ጥሏል። ይኸውም “ዓይን ያጠፋ፣ ዓይኑ ይጥፋ” ዓይነት፣ የወንጀለኛን ዓይን  የሚጎለጉል ተግባር ነው። ለወንጀሉ ተጎጂዎች የሚያበረክተው አስተዋጽዖ እጅጉን አናሳ ነው። 

በአጸፋዊ ፍትሕ መሰረት፣ የወንጀል ድርጊት እና የወንጀል እሳቤ ለተመጣጣኙ ቅጣት አስፈላጊ ቅድመ  ሁኔታዎች ናቸው። አጸፋዊ ፍትሕ ብቸኛ ትኩረቱ ቅጣት ላይ ነው። ወደፊት ሊፈጸሙ የሚችሉ  ወንጅሎችን መከላከል ወይም ወንጀል ፈጻሚዎችን በቅጡ ማረም ላይ ያለው ትኩረት እምብዛም  ነው። ይልቁንም ወንጀለኞቹ ላይ የሚጣለው ቅጣት ሌሎች ሰዎች ወንጀሎችን ከመፈጸም ሊያቅባቸው  “ይችላል” የሚል ዕይታ አለው። ዘግይቶም የማገገሚያ ፍትሕ (Restorative Justice) ለአጸፋዊ  ፍትሕ አንድ አማራጭ ሆኖ ቀርቧል። 

የማገገሚያ ፍትሕ (Restorative Justice) 

የማገገሚያ ፍትሕ (Restorative Justice) ብዙውን ጊዜ የሚያገለግለው ለትንንሽ ወንጀሎች ነው።  በሰብዓዊነት ላይ ለተፈጸሙ ወይም በሕዝብ ላይ ለደረሱ የተለያዩ ወንጀሎች አያገለግልም።  የማገገሚያ ፍትሕ ተጎጂዎች እና ወንጀል ፈጻሚዎች እንዲወያዩ ያደርጋል። በወንጀል ድርጊቱ ሳቢያ  የደረሰውን ጉዳት፣ እንዲሁም የተጎጂዎችን ሁኔታ፣ ፍላጎት እና ዕይታ ግምት ውስጥ ያስገባል። ይህ  ሂደት ተጎጂ እና ወንጀለኛን በማስታረቅ ወይም ተጎጂዎችን፣ ወንጀል ፈጻሚዎችን፣ ቤተሰቦቻቸውን፣  ጓደኞቻቸውን እና ሌሎች የማሕበረሰቡን አባላት ያጠቃለለ የገጽ ለገጽ ኮንፈረንስ ማከናወንን  ይጨምራል። የማገገሚያ ፍትሕ የወንጅል ፍትህ ሂደት ውስጥ ሊኖር ይችላል። ከቅድመ እስር እስከ  ድሕረ ብይን ድረስ ይሳለጣል። በእስር ቤቶች እና ማሕበረሰቦች ባሉ ሁኔታዎች ውስጥ የሚከናወንበት  ዕድልም አለ። 

የማገገሚያ ፍትሕን ተከትሎ፣ የፍርድ ቤት ዳኞች የአንዳንድ ወንጀለኞች የቅጣት ብይንን ቀለል  ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለተጎጂው በወንጀል ድርጊት ምክንያት ያጣውን የሰውነት አካል  ተመላሽ ማድረግ የሚቻል አይደለም። ወይም በጣም ከሰብዓዊነት በራቀ መንገድ ክብረ ንጽህናዋ  ለተገፈፈባት ሴት ካሳ መክፈል ያዳግታል። ብልቱ ላይ የፕላስቲክ ውሃ መያዣ ለቀናት ያህል  የተንጠለጠለበትን፤ ወይም በጭካኔ ቶርቸር የተፈጸመበትን ሰው በካሳ ክፍያ እንዲያገግም ማድረግ  ይከብዳል። እነዚህን ሁለት ሁኔታዎች በማምጣት፣ ተጎጂው ወንጀለኛውን ‘ይቅር’ እንዲለው መሞከር  የማይታሰብ ነው። ያለምንም ፍትሕ እነዚህን ሁለት ማሕበረሰቦች አብረው እንዲኖሩ ማድረግ በራሱ  ወንጀል ነው። ምንም ዓይነት ነገር ቁስላቸውን፣ ሕመማቸውን ወይም ጥላቻቸውን ሊቀርፈው አይችልም፤ ያለፍትሕ። ሕዝብን ያለፍትሕ ስለይቅር ባይነት እና ምክክር መስበክ ተቀባይነት  አይኖረውም። ሕዝቡ በውስጡ የተሸከመው ጥላቻ አንድ ቀን መፈንዳቱ አይቀርም። በዚህም ሰዎች  ፍትሕን በራሳቸው መንገድ ወደማግኘት ሊሄዱ ይችላሉ። 

ከአጸፋዊ ፍትሕ ጋር ሲነጻጸር፣ የማገገሚያ ፍትሕ ወንጀልን በአንክሮ የሚመለከተው ሰዎች ላይ  ያተኮረውን ጥሰት እና ግንኙነታቸው ላይ ነው፤ የሕግ ጥሰትን በማስቀደም፣ የተጎጂውን ሁኔታ  ከመዳኘት ይልቅ። የማገገሚያ ፍትሕ ዓላማ ጥፋተኛን ለይቶ የቅጣት ብይን ማሳለፍ አይደለም።  ግዴታዎችን በመለየት እና በጉዳዩ ላይ ተሳታፊ የሆኑ ሰዎችን ፍላጎት አውቆ ፈውስን መፍጠር ነው።  በተጨማሪም፣ የማገገሚያ ፍትሕ በግጭቱ ውስጥ የተሳተፉ ባለድርሻ አካላትን በማካተት፣  ግዴታዎችን እና መፍትሔዎችን ለይቶ፣ ውይይት እና የጋራ ስምምነት እንዲኖር ይሰራል፤ የጋራ  አሸናፊነት እንዲሰፍንም ያደርጋል። ይህም የፍትሕ ሂደቱ ልክ በወንጀለኞች እና የአገሪቱ ሕግ መካከል  እንዳለ ግጭት (በአብዛኛዎቹ ጉዳዮች ይህ ሂደት የአንዱን አሸናፊነት፣ በሌላው ተሸናፊነት የሚያረጋግጥ  ውጤት ያመጣል) አስመስሎ ሳይመለከት ማለት ነው። በገንዘብ እና እስራት ቅጣቶች ወንጀለኞችን  ከመቅጣት ይልቅ፣ የማገገሚያ ፍትሕ ወደ ማሕበረሰቡ ተቀላቅለው መደበኛ ሕይወታቸውን  እንዲቀጥሉ መደላድል ይፈጥራል። አጠቃላይ ፈውስ እንዲመጣ ከተፈለገ፣ ሰዎች የራሳቸውን የጉዳት  ታሪኮች መናገር እና የሌሎችንም ታሪኮች ለማዳመጥ መቻል አለባቸው። የድርድር እና የንግግር  ዘዴዎችን ተጠቅሞ፣ የሕዝብን ይፋዊ የግለ ሂስ እና ይቅርታ ንግግሮችን የሚያስተናግድ ምሕዳር  መፍጠር ይቻላል። አሁንም ያልተፈቱ የግጭት መንስዔዎችን ለማወቅ፣ ብሎም በመጪው ጊዜ  የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል ዕድሉን ያመቻቻል። ግን አጽንዖት የሚሰጠው ጉዳይ ቢኖር፣  የማገገሚያ ፍትሕ የወንጀለኛ መቅጫ ፍትሕን ተክቶ ካገለገለ፣ ስሕተት መሆኑን ነው። ያለፍትሕ ይቅርታ ሊኖር አይገባውም፤ አያስፈልግምም። ፍትሕ ጥፋተኛውን ወይም ንጹሁን  የሚለየው በወንጀለኞች ቃላት ላይ ተንተርሶ አይደለም። በሕግ ሂደት ነው ነገሩ ተጣርቶ  የሚረጋገጠው። አንዴ ፍትሕ ከተረጋገጠ፣ አንደ አገር፤ እንደማሕበረሰብ እና እንደግለሰቦች ወደፊት  የመጓዙን ሂደት በሽግግር ፍትሕ በኩል ማስኬድ ይቻላል። 

የሽግግር ፍትሕ (Transitional Justice) 

የሽግግር ፍትሕ በውስጡ የሕግ እና ከሕግ ውጭ የሆኑ አካሄዶችን ያካተተ ነው። እነዚህም ክሶች፣  ፍትሕ፣ ካሳዎች፣ ዕውነት ፍለጋ፣ ተቋማዊ ለውጥ ናቸው። ወይም ከተጠቀሱት ጋር የሚመሳሰሉ  ጥረቶች ቅልቅልም ሊሆን ይችላል። የትኛውም ቅልቅል አካሄድ ይመረጥ፣ ከዓለም አቀፍ የሕግ  መመዘኛዎች እና ግዴታዎች ጋር ሳይቃረን መተግበር አለበት። የሽግግር ፍትሕ ከፖለቲካዊ ሽግግር  በኋላ ብቻ ነው ሊከወን የሚችለው። ለተፈጸሙ ወንጀሎች እና ኢ ፍትሐዊ ድርጊቶች ሃላፊነት  የሚወስድ የፖለቲካ ስርዓት በልለበት ሁነታ ይህ ሊተገበር አይችልም። ለተፈጸሙ ወንጀሎች ወይም  ወንጀሎቹ እንዲፈጸሙ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ተጠያቂ የሆነው አገዛዝ ከስልጣኑ ሲለቅ ነው አካሄዱ  ሙሉ በሙሉ የሚተገበረው። 

“የሽግግር ፍትሕ ማለት ለተቀናጁ ወይም መጠነ ሰፊ ለሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምላሽ  የሚሰጥ ሂደት ነው። ለተጎጂዎቹ ዕውቅና ይሻል። የሰላም፣ የምክክር እና የዴሞክራሲ ዕድሎች  እንዲስፋፉ ይጥራል። የሽግግር ፍትሕ የተለየ ቅርጽ ያለው የፍትሕ ዓይነት አይደለም። ግን  ከከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የመሸጋገሪያ ጊዜ ውስጥ ላሉ ማሕበረሰቦች ታስቦ  የሚተገበር ነው። በአንዳንድ አጋጣሚዎች እነዚህ ለውጦች በድንገት ዕውን ይሆናሉ። በሌሎች  ደግሞ ከበርካታ አስርት ዓመታት በኋላ ሊከሰቱ ይችላሉ።”2

ይህ አንቀጽ የተወሰደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ የሽግግር ፍትሕ እንዴት  መታየት እንዳለበት ካወጡት መምሪያ ነው፣

“የሽግግር ፍትሕ ሂደቶች እና ዘዴዎች በፖለቲካ ክፍተት ውስጥ ሊሰሩ አይችሉም። ነገር ግን  ብዙውን ጊዜ የሚታቀዱት እና የሚተገበሩት በድሕረ ግጭት ያልተረጋጋ እና የሽግግር መቼት  ባለባቸው አካባቢዎች ነው። ተመድ የፖለቲካ ሁኔታውን እና የሽግግር ፍትሕ ዘዴዎች  የሚያመጧቸውን ውጤቶች በጥብቅ ማጤን አለበት። ከቻርተሩ ጋር ስሙም በመሆን፣  ተመድ ተጠያቂነትን፣ ፍትሕን እና እርቅን በማንኛውም ጊዜያት ይደግፋል። ሰላም እና ፍትሕ  መረጋገጥ ያለባቸው እርስ በርስ የሚደጋገፉ አስፈላጊ ነገሮች እና በሂደቱ የሚያጋጥሙ  ተግዳሮቶች ታሳቢ በማድረግ ነው። ለተመድ የሚቀርበው ጥያቄ ተጠያቂነት እና ፍትሕን  ስለመሻት መሆን የለበትም። ይልቅስ መቼ እና እንዴት የሚለው ጉዳይ ነው መሆን ያለበት። እንደዚህ ያሉ እርምጃዎች የተፈጥሮ እና የጊዜ ጠገግ፣ ከሁሉም በፊት መጀመሪያ መቀየስ  ያለበት በዓለምአቀፍ የሕግ ግዴታዎች ውስጥ ታይቶ ነው። እንዲሁም ብሔራዊ ዓውዶችን እና  የብሔራዊ ባለድርሻ አካላት፣ በተለይም የተጎጂዎች ዕይታዎችን ከግምት ውስጥ ማስገባት  ይገባል። ብሔራዊ ሁኔታዎች ዕድል በማይፈጥሩ አጋጣሚዎች ወይም የሽግግር ፍትሕ  ዕርምጃዎቹ ውጤታማ እንዳይሆኑ በሚያደርጉ ምሕዳሮች፣ ተመድ ውጤታማ አሰራሮች እና  ሂደቶች መሰረት እንዲይዙ እና እንቅስቃሴዎችም እንዲጠናከሩ ድጋፍ ያደርጋል። እነዚህም  ብሔራዊ ባለድርሻ አካላት የሽግግር ፍትሕ ዕርምጃዎችን ተረድተው ፍላጎት እንዲያሳድሩ  የሚያስችል ውይይትን ያካትታሉ። ተመድ በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጀሎች፣  በሰብዓዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች እና የገፍ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች  ተጠያቂነትን ለሚያለባብሱ የሰላም ስምምነቶች ዕውቅና ሊሰጥ አይችልም።  ይልቁንም በድሕረ ግጭት እና የሽግግር ጊዜ ላይ ለተጠያቂነት እና ለሽግግር ፍትሕ  ዕርምጃዎች ቦታ የሚሰጡ የሰላም ስምምነቶችን መደገፍ ይኖርበታል።” 

ዕርቅ 

የማሕበረሰብ አቀፍ ዕርቅ እና ዘላቂ ሰላም ቀዳሚ ግብ ሊሳካ የሚችለው በስፋት “የዕውነት እና ዕርቅ  ኮሚሽን” በተባለው፣ በተግባራዊ አሰራሩ ደግሞ ከላይ የዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ ሂደት ተብሎ የተገለጸው ነው። የዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ ሂደት የሽግግር ፍትሕ አንደኛው አንኳር ክፍል  ሲሆን፣ ከአንድ የፖለቲካ ስርዓት ወደ ሌላኛው ሽግግር በሚፈጸምበት ወቅት ይከናወናል። አጸፋዊ  ፍትሕ የሚያተኩረው በወንጀል ድርጊቶች ተባባሪ የሆኑ ግለሰቦችን በመክሰስ ላይ ነው። የሽግግር እና  የማገገሚያ ፍትሕ ደግሞ በተጎጂዎቹ ፍላጎቶች፣ የግጭት መሰረታዊ መንስዔዎች እና ወንጀል  ፈጻሚዎቹ ከማሕበረሰቡ ጋር አዋሕዶ ዳግም እንዲቋቋሙ የሚያስችል ዕድሎችን ማመቻቸት ላይ  ያተኩራል። የዚህ ዓይነት ፍትሕ ወንጀሎች ዳግም እንዳይከሰቱ መከላከል ነው። የመከላከል ስልቱም  ወንጀለኞችን በመቅጣት እና የተወሰኑትን ደግሞ መልሶ ማቋቋም ነው። እንዲሁም ሕዝቡን  ስለሰላማዊ አብሮ መኖር ማስተማር ላይ የተንተራሰ ይሆናል።  

ቀዳሚ ዓላማዎቹ የሕጋዊነትን ወይም የሕግ የበላይነት ዕሴትን ማስተዋወቅ እና ጉዳዩን እንዲጠናቀቅ  ማድረግን የሚያካትት ነው። ተጎጂዎቹ እና ወንጀለኞቹ ከተስማሙ፣ ሁሉንም ዕውነት እንዲፈልጉ እና  የዕርቅ ሂደቱን እንዲጀምሩ ውይይት ማዘጋጀት ይችላሉ። ነገር ግን አገሪቱ የእርስ በርስ ሰላም  ተረጋግጦባት፣ በአንድነት እና በሕብር እንድትጓዝ፣ ከየትኛውም አማራጭ በፊት ፍትሕ መቅደም  ይኖርበታል። ማንም ዜጋ እንዲዋደድ እና እንዲታረቅ ሊገደድ አይገባውም። እነዚህ ግላዊ ምርጫዎች ናቸው። ነገር ግን የሕግ የበላይነት ሰዎችን በሌሎች፣ በፍቅር፣ በይቅር ባይነት እና በዕርቅ በማያምኑ  ወገኖች ከመጠቃት እንዲጠበቁ ያደርጋል። 

“ይቅር ባይነት ውስጣዊ ሂደት ነው። ሂደቱም በመጎዳት፣ ምን እንደተፈጠረ ግንዛቤ  በማግኘት፣ የደህንነት ስሜት ዳግም በመፍጠር እና ክሕደትን ንቆ በማለፍ የሚሳለጥ ነው።  አጥቂው ወገን በግድ የሂደቱ አንድ አካል መሆን አይኖርበትም።”

በሌላ በኩል፣ ዕርቅ የእርስ በርስ ሂደት ሆኖ፣ በአጥቂና በተጠቂ መሀከል ምን እንደተፈጠረ፣  ስላጋጠሙ ታሪኮች፣ ግለ ሂስን ማዳመንና መተማመንን ዳግም ስለቀጣይ አብሮ መኖር  ጅማሮ ዙሪያ ውይይት ይደረግበታል። በጣም ውስብስብ ሂደት ነው። ከይቅር ባይነት ተሻግሮ  የሚጓዝ ነው። “ይቅር ባይነት የብቻ ስራ ነው። ዕርቅ ደግሞ የጋርዮሽ ስራ ነው” ሰዒድ  ስሜዴስ አንድ ጊዜ እንደተናገረው፣ “ለይቅር ባይነት አንድ ሰው ይበቃል። እንደገና አንድ  ለመሆን ደግሞ ሁለት ሰዎች ያስፈልጋሉ” 

“ሕይወቱ ያለፈን ሰው ይቅር ማለት ይቻላል፤ ወይም ሌላ ጊዜ የማታየውን ሰው፣ ወይም ይቅርታ  ለማለት ምንም ፍላጎት የሌለውን ሰው ይቅርታ መጠየቅ መንፈሳዊ ካልሆነ ለኑሮ ትርጉም የለውም።  ስለዚህ ይቅርታዎች አስፈላጊ አይደሉም። ግን ዕድሉ ሲፈጠር፣ እንደ ሁነታው ረዳት ሊሆኑ ይችላሉ።”

ሕዝቦች የሚመሩት በሕግ የበላይነት እንጂ በሰዎች ምኞት አይደለም። ቅቡል የሆነ የሕግ የበላይነት  በሕግ ከለላ ስር፣ ማሕበረሰቡ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ዕሳቤ ላይ የተመሰረተ ነው። በግጭት እና  ረሃብ ውስጥ ያሉ፣ ትልቅ የፖለቲካ ለውጦችን በሚሹ እንደኢትዮጵያ ባሉ አገራት፣ ቅቡልነት ያለው  የሕግ የበላይነት የለም። የየአገራቱ መንግስት መሰረታዊ ለውጦችን ለመፍጠር ሕጋዊነት የላውም።  ምክንያቱም የችግሩ አንድ ተካፋይ እና ክፍል ነውና። መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን  

መከታተል ሃላፊነት አለባቸው። ግና ይህንን ለማድረግ አቅም ወይም ፈቃደኝነት ከሌለ፣ ብሔራዊ  ውይይትን መሰብሰብ እና የመከታተልና መሰረታዊ የሰብዓዊ መብት መርሆዎችን የማስጠበቅ ሃላፊነት  በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለተዋቀሩ ተቋማት ሊሰጣቸው ይገባል። ከእነዚህም ውስጥ ዓለምአቀፍ  የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (ICC) አንደኛው ሊሆን ይችላል። 

“ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት (ICC) ከዚህ በኋላ ተመስርቷል። ቋሚ ተቋም ሆኗል። እናም፣ በዚህ  ድንጋጌ እንደቀረበው፣ እጅግ ከፍተኛ እና ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የሚስቡ ወንጀሎችን የፈጸሙ ሰዎች  ላይ ብይን የማስተላለፍ ስልጣን አለው። ከአገራት የወንጀል ብይኖች ጋር የተስማማ መሆን አለበት።  

ብይን የማስተላለፍ እና የፍርድ ቤቱ አጠቃላይ እንቅስቃሴ የሚመራው በዚህ ድንጋጌ ውስጥ  በተቀመጡ መመሪያዎች ነው።” (2002) 

በዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ላይ ከነበሩ ልምዶች የተገኙ ተመክሮዎች 

በዚህ ሂደት ከተጓዙ አገራት መካከል፣ ሩዋንዳ፤ ዴሞክራትክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፤ የቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ፤  ሱዳን፤ ኬንያ፤ ላይቤሪያ እና ማያንማር ተጠቃሽ ናቸው። በተለይም፣ በነውጠኛው የድሮ ሁኔታ  መካከል ሆኖ የተከፋፈለ ማሕበረሰብ፤ የጥንት እና የአሁን ታሪኩን አበክሮ በማጥናት፣ ወደፊት  ለመጓዝ አቅጣጫ እንዴት ማስቀመጥ እንደቻለ ማሳያ የሚሆነው ከ25 ዓመታት በፊት የደቡብ  አፍሪካ የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን፣ በመቀጠልም ሩዋንዳ እና ላይቤሪያ ላይ በየአገራቱ የተካሄደው  ስራ ነው። በመላው ዓለም ሌሎች ጥረቶች እንዲደረጉም መነሻ ሆነዋል። እነዚህ አገራት ውስብስብ  በሆኑ ያለፉ ታሪኮቻቸው መሃል ተረማምደው፣ በጉዳዩ ላይ በመስራት በጊዜ ሂደት ትምሕርት ቀስመዋል። የወደፊቷ ኢትዮጵያ ዕጣ በእነዚህ እና ሌሎች አገሮች ባለፉበት ሁኔታ ጋር የተመሳሰለ  ይሆናል። ሂደቱ የሚመረኮዘውም በዕውነታ፣ በፍትሕ፣ በካሳዎች እና በዕርቅ ላይ ነው። የዚህ ሂደት  ረቂቅ ሰነድ በቅርቡ ባሳተምኩት መጽሐፌ ውስጥ የሚገኝ ነው። 

የደቡብ አፍሪካው የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን የሂደቱ ውጤት ነው። ይህም “አዝጋሚ ዲሞክራሲ  የማስፈን ሂደት” ወይም “የድርድር ስምምነት” ሊባል የሚችል ነው። ቀደም ሲል የነበሩት መሪዎች  ሰላማዊ ሽግግር እንዲደረግ የሚያስችል ዋስትና በማረጋገጥ ሚናቸውን ተወጥተዋል። ከዚሁ ጋር  በተያያዘ የወደፊት ሰላም እና መረጋጋት ለማረጋገጥ ሲባል አጸፋዊ ፍትሕ የሚቀርበት ዕድልም አለ።  ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም ፍትሕ እና ካሳ አለመሞከራቸው ተፈላጊውን ውጤት እንዳይገኝ አድርጓል።  የደቡብ አፍሪካ የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን፣ በሕዝቡ መካከል ሰላም እና ዕርቅ በማምጣቱ ረገድ  ውጤታማ እንዳልሆነ፣ እንደእኔ ዕይታ እና እዚያች አገር የመኖር ዕድል እንደገጠማቸው በርካታ ሰዎች፣  ቁጥሩ በማይናቀው የማሕበረሰብ ክፍል ዘንድ ዕምነት አለ። ደቡብ አፍሪካ በዓለም እጅግ በጣም  ዕኩልነት ያልሰፈነባት አገር እንደነበረች፣ አሁንም እንደዚያው አለች። ንዴት እና ተቃውሞ አደገኛ ደረጃ  ላይ ከደረሰባቸው እና ወንጀል ካገረሸባቸው አገራት መካከል አንዷ ነች። ነገር ግን ሕዝቡ ሃሳብን  በነጻነት የመግለጽ ሙሉ መብት አለው። እንዲሁም ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመጻፍ እና ቅሬታን  በተለያዩ መልኮች የመግለጽ መብት ተጎናጽፏል። መንግስት ቅሬታዎችን ሁሉ ያዳምጣል፤ ሆኖም  የተፈለገውን ለውጥ ማምጣት አልቻለም። ደቡብ አፍሪቻ በቅርቡ ደሞክራሲያዊ ሰላማዊ ብሂራዊ  ምርጭ አካሂዳለች፤፤ ሆኖም ስር የሰደደውን ከ አፕርታይድ የትወረስውን የእኩልነት ጥያቂ ለመምለስ  ባለመቻሉ ደቡብ አፍሪካ የፖልቲካ ቀውስ ላይ ትገኝአለች፤፤ ይህ የሆነው በተጠናከሩ የዕኩልነት  ዕጦቶች፣ ፖሊሲዎች እና የአድልዎ አመለካከቶች ሳቢያ ነው። የእርቅ ኮሚሽኑ ፍኖተ ካርታ ሊያዘጋጅ  ይገባው ነበር። በፍኖተ ካርታው መሰረት፣ ከላይ የተጠቀሱት፤ አስፈላጊ ለውጥ እንዲደረግባቸው ጥያቄ  የቀረበባቸው ችግሮች ትኩረት አልተሰጣቸውም። ያለምንም ፍኖተ ካርታ፣ ደቡብ አፍሪካ በተጠቀሱት  ችግሮች ላይ ተዓምራዊ ለውጦች እስካልተደረጉ ድረስ፣ ድንገት ሊፈነዳ የሚችል፣ የተበጣጠሰ  ዴሞክራሲ የሰፈነባት አገር ሆናለች። የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ፍትሕም ሆነ ዕርቅ አላሳካም። በዕርቅ  እና ፍትሕ መካከል ልከኛ የሆነ ሚዛናዊነትን ለማምጣት አልቻለም።  

ዊኒ ማንዴላ አንድ ጊዜ ስለ ደቡብ አፍሪካ የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን እንዲህ ብላ ተናግራ ነበር፣ 

“ይህን የዕውነታ እና ዕርቅ ጨዋታ ተመልከቱት እስኪ፤ ከዚህ ጨዋታ ጋር መስማማት  አልነበረበትም።’ ቁጣዋ ያተኮረው ማንዴላ ላይ ነበር። ‘ዕውነትን ማወቅ ብቻ ምን ጥሩ ነገር  አደረገ? ማንኛውም ሰው የሚወደው ወዳጁ እንዴት እንደተገደለ ወይም እንደተቀበረ ማወቁ  ብቻ እንዴት ይጠቅመዋል? ነገሩን ሁሉ ወደ ሃይማኖታዊ ሰርከስ የቀየረው ቄስ ዴዝሞንድ  ቱቱ ነው”6 አለ ፍርድና ካሳ እውነትን መናገርና ይቅርታ መጠየቅ ብቻ ለተጎዳው ህዝብ የሚፈይደው  የለም ለማለት ነው። 

“የሽግግር ፍትሕ” የሚለውን ቃል ወደ ዓለም መድረክ ያመጣችው ደቡብ አፍሪካ ነች። ይህም  የሚያሳካውን ግብ በእጅጉ የለየ የማገገሚያ ፍትሕ ዓይነት ነው። ግቡ ዘላቂ ሰላምን መፍጠር ነው።  የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ይፋዊ ትዕምርት ቄስ ዴዝሞንድ ቱቱ ናቸው። የማገገሚያ ፍትሕን ዕሳቤ  ለሚጠራጠሩ ወገኖች “ፍትሕ አለ. . .ወንጀለኞች ከቅጣት ነጻ አይደሉም. . .በይፋ መናዘዝ አለባቸው”  ሲሉ አረጋግጠው ነበር። ይሁንና መናዘዝ ብቻውን ምሕረት የሚያስገኝ አይደለም በማለት ተናዛዦች  በቅን መንፈስ ለሂደቱ አስተዋጽዖ ማበርከት እንዲአደርጉ ተድርጎአል። የሚያስፈልጉ አጠቃላይ  ወንጀሎች በተመልከተ መረጃዎችን እንዲአስረክቡ ተደርጎአል። 6 የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ያደረጋቸው የማገገሚያ ፍትሕ ጥረቶች ደቡብ አፍሪካውያንን በግለሰብ፤ አገሪቱን በአጠቃላይ ደረጃ ወደፊት እንዳራመደ አጠያያቂ አይደለም። ሰዎች ታሪካቸውን ተናግረው፣ ሕሊናቸውን ንጹህ  አድርገዋል። በዕውነታ ውስጥ ሰላምን ፈልገዋል። አንድ ደቡብ አፍሪካዊ የታሪክ ምሁር እንዳለው፣  “የትኛውም ዓይነት ተዓምር አገሪቱን ሊፈውስ አይችልም። ነገር ግን ለመጀመሪያ ጊዜ ያ ሁሉ ሰው  የማቀቀበት ሕመም ታልፎ ወደፊት መመልከት ተችሎ ነበር። እንደአገር ዕውነታው ባይነገር፣ በጣም  ደሃ እንሆን ነበር። የታሪካችን ወሳኙ ክፍል ይህ እንደነበር አምናለሁ”

በሺህዎች የሚቆጠሩ ተጎጂዎች እና ወንጀለኞች ሃሳቦቻቸውን አቅርበዋል። ሁሉም በአንድ ወገን የቆሙ  አልነበሩም። የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) ትግል ሕጋዊ እንደሆነ ተረጋግጦ ነበር። ግን በዚያ ትግል  ስም የተፈጸሙ አንዳንድ ድርጊቶች ግን ሕጋዊ አልነበሩም። አልቤ ሳክስ የተባለ የቀድሞ የANC አባል እና  ኋላ ላይ የፍርድ ቤት ዳኛ የሆነ ግለሰብ እንዲህ ያለ ምልከታ አለው፣  

“አፅያፊ ነገሮችን የሰሩ ሰዎችን በማጋለጡ በኩል፣ ለአገዛዙ ወግነው በነበሩ ሰዎች በኩል ብቻ መሆን  የለበትም። የANC – እኔ አባል የሆንኩበት ድርጅት ማለት ነው – አባላትም ጭምር መካተት አለባቸው።  መጥፎ ነገሮችን ፈጽመናል። እነዚያን ለማንጻት መጣር ነበረብን” 8 የኮሚሽኑ ስራ ምክረ ሃሳቦችን  በማቅረብ ተደመደመ። “ለተጎጂዎች የገንዘብ ካሳ ለመስጠት የሚያግዙ የተለዩ መመሪያዎች፣ ከ300  በላይ ሊከሰሱ የሚገባቸው የአፓርታይድ ተባባሪዎች ስም ዝርዝር እና በአገር አቀፍ ደረጃ አጠቃላይ  የሆኑ፣ ክብርን ለመመለስ የተጠኑ ዕርምጃዎችን መውሰድ በምክረ ሃሳቦቹ ውስጥ የተካተቱ ተግባራት  ናቸው። በተጨማሪም፣ በከፍተኛ የዕኩልነት ዕጦት የተመታው የአገሪቱን አጠቃላይ የመንቀሳቀሻ  ምሕዳር ዕኩል ማድረግ የምክረ ሃሳቦቹ አንደኛው አካል ነው።”

ግን ለዳኛ አልቤ ሳክስ “የዕውነት ኮሚሽኑ እጅግ አስፈላጊው ነገር ሪፖርቱ አልነበረም። በቴሌቪዥን  ዕንባዎችን፣ ሃዘኖችን፣ ታሪኮችን፣ ምስጋናዎችን ማሳየቱ ነው ወሳኙ ነገር። አንድ የፖለቲካ ሳይንቲስት  እንዳስቀመጠው፣ የዕውነት ኮሚሽን ያደረገው ነገር ዕውቀትን ወደ ምስጋና የቀየረ ነው”10 

ሁሉም ነገር መልካም እና ጥሩ ነበር። ነገር ግን በቅጡ አልሰራም። ኮሚሽኑ ሊወጣው የማይችል አንድ  ስራ ገጠመው። አጠቃላይ የምሕረት አሰጣጥን ከሕጋዊ ክሶች ጋር ማመጣጠን አቃተው። ማን ይቅር  እንደሚባልና ማን እስር ቤት እንደሚገባ ለመለየት አዳገተው። ከሁሉም ወገኖች ነቀፋ ሊኖር  እንደሚችል የታወቀ ነበር። ይህ ሁኔታ እስከ ዛሬ ድረስ መታወቅ አለበት። ማለትም ወደኋላ መለስ  ብለን ስንቃኘው፣ በርካታ ጉልህ ችግሮች እንደነበሩ መረዳት ያስፈልጋል። መጀመሪያ ችኮላ የተሞላበት  ሂደት ነበር። የኮሚሽኑ ትኩረት በጣም ምናባዊ የሆነ፣ እጅጉን የሰፋ እና የተለጠጠ፣ በዚያ ላይ ቀላል  ነበር። እንዲያውም አብዛኛውን የደቡብ አፍሪካ ሕዝብ ወጥሮ ለያዘው ውስብስብ ችግር ፈጣን  መፍትሔ ለመስጠት የሚሞክር ይመስል ነበር። የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን በደንብ አቅዶ  የሚንቀሳቀስ አልነበረም። አገሪቱ ወደፊት እንድትራመድ የተወሰኑ ሰዎችን በፍጥነት ተጠያቂ  የማድረግ የጥድፊያ ጉዞ ላይ ነበር። ኮሚሽኑ ከ1952 እስከ 1986 ዓ.ም. ድረስ የተፈጸሙ የሰብዓዊ  መብቶች ጥሰቶችን ለመመርመር ሞክሮ ነበር። ምርመራውን ለማጠቃለል የተሰጠው ጊዜ በጣም  የተገደበ ነበር። ምክንያቱም ይህ ኮሚሽን በዓይነቱ የተለየ ስለነበር እና በርካታ ሰዎች፣ በተለይም  በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ሰዎች የምርመራ ስራዎችን ለመስራት መሰልጠን ስላለባቸው፣ የጊዜ መጠኑ  በጣም አጭር ነበር። በኮሚሽኑ ስር የተቋቋሙ ኮሚቴዎች ስራዎችን እንዴት እንደሚሰሩ ግልጽ  የአሰራር ዘዴዎች የላቸውም። በመካከላቸው ያለው ቅንጅት በጣም ደካማ ነበር። በዕውነት እና ዕርቅ  ኮሚሽን ስራ ላይ የዋለው አሰራር በስህተት የተሞላ ነበር። 11 ከዚያም በርካታ የምሕረት ዓዋጆች  ነበሩ። አንዳንድ ተጎጂዎች ጥፋታቸውን የተናዘዙ ነፍሰገዳዮች በነጻነት ሲንቀሳቀሱ በሚመለከቱበት  ወቅት ስሜታቸው ይቀያየር ነበር። እንዲሁም ቃል የተገባላቸው ካሳ ስላልተሰጣቸው ቅሬታ  አድሮባቸው ነበር። የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን፣ የፍትሕ እና ዕርቅ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ስታን  ሄንክልማን አስተያየታቸውን ሲሰጡ፣ “የምሕረት ሂደቱ ለሕዝቡ ፍሬውን ሳያፈራ እንዲከሽፍ  መንግስትና በተለይም የወንጀል ዳኝነት ስርዓቱ ምክንያት ሆነዋል። አንድ በሌላ ግለሰብ ዘመዱ  የተገደለበት ሰው ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማሰብ ነው፤ ያ ወንጀለኛ ሰው በነጻነት ሲንቀሳቀስ  ሲመለከት።” 12 ኔልሰን ማንዴላ የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ለሰራው “አስደናቂ ስራ” ምስጋናቸውን  አቅርበው ነበር። በዚያውም የኮሚሽኑን ውስንነቶች አንስተዋል። ነገር ግን አንዳንዶች እንደሚያምኑት  ማንዴላ እና የዕውነትና ዕርቅ ኮሚሽን እጅግ በጣም ይቅር ባይነትን አስፍነዋል፤ ስለዚህም ነጮች  የአፓርታይድን ፍሬ እያጣጣሙ እንዲቀጥሉ አስችሏቸዋል።13 ኮሚሽኑ ካሳዎች እንዲፈጸሙ ምክረ  ሃሳብ አቅርቦ ነበር። ተግባራዊ አልሆኑም። የማንዴላ ተተኪዎች እንዴት የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽንን  ስራ “በቅጡ ሳይጠናቅቁት” እንደተዉት፣ ቄስ ቱቱ ጸጸት በተመላበት ስሜት ተናግረው ነበር። ቀጥለው  ሲናገሩም፣ “ባልተጠናቀቀው ስራ ምክንያት፣ በኮሚሽኑ የተወሰነው የካሳ ደረጃ ተግባራዊ ሳይደረግ  አልፏል። የሃብት ዝውውርን ለመቆጣጠር የሚጣል፣ የአንድ ጊዜ ቀረጥ ላይ የሚጣለው ቀረጥ ሃሳብ  ችላ ተብሏል። የምሕረት ዓዋጁን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች አልተከሰሱም።” 14 

ዕውነት እና ዕርቅ በላይቤሪያ፦ 250 ሺህ ዜጎችን ከገደለው፣ ሚሊዮኖችን ካፈናቀለው፣ አራት  ሚሊዮን ሕዝብ በሚኖርባት ትንሽ አገር ውስጥ ለ14 ዓመታት ከተደረገው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ፣  በነሐሴ 1995 ዓ.ም. አጠቃላይ የሰላም ስምምነት ጋና፣ አክራ ከተማ ውስጥ እንዲፈረም የዕውነት እና  የዕርቅ ኮሚሽን ተስማማ። 15 የኮሚሽኑ ግብ “ብሔራዊ ሰላም፣ ደህንነት እና ዕርቅ ማስፈን” ነበር።  በተጓዳኝም፣ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን የፈጸሙ ወንጀለኞች ተይዘው ተጠያቂ እንዲሆኑ  ዕድሉን ፈጥሯል። 16 ከ2000 እስከ 2002 ላይቤሪያ ውስጥ ኖሬያለሁ። ሒደቱንም በቅርበት  ተከታትያለሁ። እንዲያውም የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ባዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች  ተሳትፌያለሁ። የመጨረሻው ሪፖርት ሲወጣ፣ እኔ እዚያ ነበርኩ። በርካታ ፖለቲከኞች፣ የዓይን  ምስክሮች እና በ14 ዓመት የእርስ በርስ ጦርነት ተጎጂ የሆኑ በርካታ ሰዎችን ለማነጋገር ዕድል  አግኝቼአለሁ። የማየው እና የምሰማው ነገር የሚያሳየኝ፣ ማንኛውም የዕርቀ ሰላም ሂደት  የሚገጥሙት ተግዳሮቶች እንዳሉ ነው። የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን የተቋቋመበት ሂደት ልክ  እንደደቡብ አፍሪካ በተካለበ ሁኔታ አልነበረም። የኮሚሽኑ ዓዋጅ በ1997 ዓ.ም. ጸደቀ። ኮሚሽኑ  በመደበኛነት ስራውን የጀመረው ከሶስት ዓመታት በኋላ ነው። ምስክሮችን ሲያደራጅ እና የእነርሱን  የምስክርነት ቃል ሲያሰባስብ ቆይቶ ነው ሕዝባዊ የምስክርነት ቃሎችን መቀበል የጀመረው። ነገር ግን  የዕርቅ ሂደቱ ግልጽ ዓላማ አልነበረውም። ላይቤሪያውያን የጦርነቱ ስነ ልቦናዊ ጠባሳ፣ ከዚህም በላይ  አስከፊው ድህነት ተደርቦባቸው እየተሰቃዩ ነበር። አብዛኛው ሕዝብ ከሰላም ማዕድ እንዳይቋደስ  መገለሉ አንድ ችግር ነው። ለዕርቅ ሂደቱ የተመደበው ገንዘብ አልተለቀቀም። ምንም ነገር ይለቀቅ  እንደስድብ ይቆጠር ነበር። ራሳቸው ፕሬዝዳንት ሰርሊፍ እንዳመኑት፣ ዕርቀ ሰላም እና የጸረ ሙሰና  ዘመቻውን ማሳካት ባለመቻላቸው ከስልጣን ለቅቀዋል። 17 አዎ፣ ቻርለስ ቴይለር ፍርድ ቤት ቀርቦ  ነበር። ነገር ግን በላይቤሪያ በፈጸማቸው የጦር ወንጀሎች አይደለም የተከሰሰው፤ በሴራሊዮን እንጂ! 

የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ያቀረባቸው ምክረ ሃሳቦች ላይቤሪያ ውስጥ ቢተገበሩ ኖሮ፣ ፍትሕ በሰፈነ  ነበር። ነገር ግን ያ አልተደረገም። አንዳንድ ወንጀለኞች ከላይቤሪያ ውጭ በፈረንሳይ፣ በቤልጂየም፣  በታላቋ ብሪታኒያ እና በአሜሪካ ተይዘው ሲታሰሩ እና ሲፈረድባቸው ነበር። በሌሎች አገራት ያሉ  ባለስልጣናት በሁለንተናዊ የፍትሕ ስልጣን መርህ (Principle of Universal Jurisdiction) መሰረት የሚታዩ የወንጀል ጉዳዮችን ሲከታተሉ ቆይተዋል። ሁለንተናዊ የፍትሕ ስልጣን መርህ የየአገራቱ ፍርድ  ቤቶች የአገራቸው ዜጋ ያልሆኑ ሰዎች በሌሎች ዜጎች ላይ የፈጸሟቸውን ወንጀሎች የሚዳኙበት ነው።  ከስደት ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን በፍርድ ቤቶቻቸው ይዳኛሉ። ለአብነትም ላይቤሪያ ውስጥ  ስለተፈጸሙ ጥሰቶች ተሳታፊ መሆንን፣ አለመሆንን በተመለከተ የሚጠይቁ የስደተኛ መረጃ ቅጾችን  በሐሰተኛ መረጃ የመሙላት ወንጀሎች ይጠቀሳሉ። በዚህም ቸኪይ ቴይለር እና ሌሎች በርካታ ሰዎች  ተይዘው ክስ ተመስርቶባቸው፣ በአሜሪካ፤ በቤልጂየም፤ በታላቋ ብሪታኒያ እና በፈረንሳይ የቅጣት  ውሳኔ ተላልፎባቸዋል። ከዚህም የበለጡ ስራዎች መሰራት አለባቸው። ፍትሐዊ የሕግ ሂደት በሌለበት  ውስጥ ጉልበተኛው ሁሉ፣ ምንም ሳይሆን ከቆየ ችግር ይፈጠራል። ሌላውም ከፍትሕ ውጭ ወይም ዳር  ተገፍቶ እንዲቀመጥ ያደርገዋል። ለተጎጂዎቹ ያለፍትሕ ምንም ዓይነት ዕርቅ እንደማይኖር ግልጽ ነው።  ስለሆነም ያለዕውነታ ፍትሕ ሊሰፍን አይችልም። 

ያለፉ ታሪኮቿን አስማምታ ተረድታ ፊቷን የወደፊት ዕቅዷ ላይ ያደረገች አገር፣ ያለፈውን ጊዜ ዕውነታ  በይፋ አጠናቅራ መያዟ አስፈላጊ ነው። የተወሰነው የማሕበረሰብ ክፍል ያለፈው ታሪክ ላይ ስሕተት  መፈጸሙን ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ፣ “ዕርቀ ሰላም” ሊደረግ አይችልም። ሌላኛው ደግሞ፣ መጎዳቱን  ወይም እየተጎዳ መሆኑን የሚያሳውቅ ዕውቅና አላገኘም። ለዚያ መከራ የመጨረሻ ሃላፊነት ስለሚወሰደው አካል የሚያውቀው ምንም ነገር የለም። 18 

ያልተቋጩ ታሪካዊ ኢ-ፍትሐዊ ድርጊቶች ችግር እየፈጠሩ በቀጠሉ መጠን፣ የዕውነት ኮሚሽኖች ፍላጎት  እየጨመረ ሊመጣ ይችላል። እንዳለመታደል ሆኖ፣ እየቀጠለ ላለ ፍላጎት ምንም ዓይነት ማክተሚያ የለም። በመጨረሻም፣ በላይቤሪያው የዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን፣ ሁሉም ዕውነት አልተነገረም። ፍትሕ  አልሰፈነም። ካሳዎች አልተከፈሉም። በታሪክ ውስጥ ባርነት በቀመሱ እና በጨቋኞቻቸው፤ በጦረኞች እና  በጦርነት ተጎጂዎች መካከል፣ ምንም ዓይነት ዕርቀ ሰላም አልወረደም። የላይቤሪያው ኮሚሽን የከሸፈ  ነበር። 

ዕውነት እና ዕርቅ በሩዋንዳ፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ዓለም አቀፍ  የወንጀል ችሎት በሩዋንዳ አቋቋመ። የችሎቱ ዓላማ በሩዋንዳ ወሰን ውስጥ ከፍተኛ የዓለም አቀፍ  የሰብዓዊ መብት ሕጎችን የጣሱ፣ ብሎም በጎረቤት አገራት የሚገኙ በዚሁ ወንጀል ተጠያቂ የሆኑ ሰዎችን  ተጠያቂ ማድረግ ነው። ይህም ከታሕሳስ 23 ቀን 1986 ዓ.ም. እስከ ታሕሳስ 22 ቀን 1987 ዓ.ም. ድረስ  የተፈጸሙ ወንጀሎችን ይመረምራል። ከእነዚህ ወንጅሎች መካከል፣ የዘር ማጥፋትን በተለየ መልኩ  ጠቅሶታል። 19 ችሎቱ መቀመጫው ታንዛኒያ፣ አሩሻ ከተማ ነበር። ሩዋንዳ፣ ኪጋሊ ከተማ ውስጥም  ቢሮዎች ነበሩት። ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ ያለው ኔዘርላንድስ፣ ሄግ ከተማ ነው። 93 ግለሰቦች ክስ  ተመሰረተባቸው። 62ቱ ጥፋተኝነታቸው ተረጋግጧል፤ የቅጣት ብይን ተበይኖባቸዋል። 10 ሰዎችም በነጻ  ተፈትተዋል። 10 ሰዎች ወደ ብሔራዊ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ተመርቷል። ከተፈረደባቸው ግለሰቦች  መካከል፣ የጦር ሰራዊት አባላት፣ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ነጋዴዎች፣ የቤተ ክርስቲያን እና የሚዲያ  መሪዎች ይገኙበታል። እነዚህን ወንጀለኞች በመክሰስ ረገድ ካለው ውጤታማነት ባሻገር፣ ችሎቱ በርካታ  ወሳኝ ምክንያቶች አሉት። በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ዓለም አቀፍ ችሎት የዘር ማጥፋት ወንጀል በፈጸሙ  ግለሰቦች ላይ የቅጣት ብይኑን አስተላልፏል። በተጨማሪም፣ አስገድዶ መድፈርን እንደዘር ማጥፋት  ወንጀል መቆስቆሻ አድርጎ መጠቀምን ለመጀመሪያ ጊዜ ዕውቅና የሰጠ ተቋም ነው። ሌላኛው  የመጀመሪያ ነገር ደግሞ፣ ከሚዲያ ጋር የተያያዘ ነው። የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለማጋጋል ሕዝቡን  የሚቀሰቅሱ ይዘቶችን ባሰራጩ የሚዲያ አባላት ላይ ብይን የሰጠ የመጀመሪያው ችሎት ያደርገዋል። 20 

የብሔራዊ የፍርድ ቤት ስርዓት እና የጋቻቻ ማሕበረሰብ አቀፍ ችሎቶች በጋራ፣ የዘር ማጥፋት ወንጀልን  ያሴሩ ወይም የአስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ሌሎች አስከፊ ፍጅቶችን ያደረሱ ሰዎችን የሩዋንዳ ብሄራዊ ፍርድ ቤቶች ላይ እንዲቀርቡ ተደርጓል። በ1998 ዓ.ም. አጋማሽ ላይ ወደ 10 ሺህ የሚጠጉ በዘር ማጥፋት  ወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎች ብሔራዊ ፍርድ ቤቶች ላይ ቀርበው ተዳኝተዋል። በ1999ዓ.ም. የሩዋንዳ  መንግስት የሞት ቅጣትን አስቀረ። ይህ ቅጣት ለመጨረሻ ጊዜ የተተገበረው በ1990 ዓ.ም. ላይ ነበር።  22 ሰዎችን ከዘር ማጥፋት ጋር በተገናኙ ወንጀሎች የጥፋተኝነት ብይን ተሰጥቶባቸው በሞት  ተቀጥተዋል። ነገር ግን በመንግስት በኩል የተወሰደው ቅጣቱን የማስቀረት ዕርምጃ አንድ ትልቅ  መሰናክልን አስወግዷል። የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን በተመለከተ፣ ጉዳዮቹ ከችሎቱ ወደ ብሔራዊ ፍርድ  ቤቶች እንዲዛወሩ አድርጓል። ይህም ችሎቱ ወደ መዘጋቱ ሲቃረብ ማለት ነው። በማንኛውም አገር  ለጅምላ ፍጅቶች ፍትሕ መስጠት የሚያታክት ተግዳሮት ነው። በሩዋንዳ የዘር ዕልቂት ደረጃ፣ እንዲሁም  በደንብ ለተደራጀ የፍትሕ ስርዓት እንኳ እጅግ አስቸጋሪ ነው። ሩዋንዳ ውስጥ ስራው እጅግ በጣም ከባድ  ነበር። ምክንያቱም ብዙ ዳኛዎች፣ ጠበቃዎች እናም ሌሎች የፍትሕ ስርዓቱ አካላት በዘር ማጥፋት ድርጊት  ሳቢያ፣ ሕይወታቸው ተቀጥፏል። አብዛኛው የአገሪቱ መሰረተ ልማት ወድሟል። እነዚህ ተግዳሮቶች  እንዳሉ ሆነው፣ የሩዋንዳ መንግስት ፍትሕ ለመስጠት ተጨባጭ ያልሆነ እና ገደብ የሌለው አቀራረብ  እንዲጀመር ተደረገ። በመደበኛ የአገር ውስጥ እና ማሕበረሰብ አቀፍ የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች አማካይነት  አቀራረቡ ጥቅም ላይ ውሏል። 21 

ተራ የሚጠብቁ በርካታ የወንጀል ጉዳዮችን ለማየት የሩዋንዳ መንግስት “ጋቻቻ” የተሰኘ ባሕላዊ  ማሕበረሰብ አቀፍ የፍርድ ስርዓት ለማቋቋም ተገደደ። ይህም በ1997 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ገባ።  ጋቻቻ ጥሬ ቃሉ ሲተረጎም፣ “ንጹህ የተከረከመ ሳር” ማለት ነው። በጋቻቻ ስርዓት፣ ማሕበረሰቦች  በመንደራቸው ደረጃ ዳኞችን ይመርጣሉ። እነዚህ ዳኞች የዘር ማጥፋት ወንጀል ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ  ይዳኛሉ። ዘር ማጥፋትን ለመፈጸም ከማሴር ውጪ ባሉ ሌሎች ወንጀሎች የተከሰሱ ግለሰቦች ናቸው  ዳኞች ፊት የሚቀርቡት። ፍርድ ቤቶቹ አነስተኛ ቅጣት ያስተላልፋሉ። ማለትም ሰውዬው ንስሐ ለመግባት  ከፈቀደ እና ከማሕበረሰቡ ጋር ዕርቅ ማውረድ ከፈለገ ቅጣቱ ቀለል ይልለታል። ሁልጊዜ፣ ጥፋታቸውን  የተናዘዙ እስረኞች ያለምንም ተጨማሪ ቅጣት ወይም የማሕበረሰብ አገልግሎት ትዕዛዝ ወደ ቤታቸው  ይመለሳሉ። ይህ አገር በቀል የፍትሕ ስርዓት ነው። እንደሌብነት፣ የጋብቻ ጉዳዮች፣ የመሬት ክርክሮች እና  የንብረት ውድመቶች ዓይነት ውዝግቦች የሚፈቱባቸው ኢ-መደበኛ መንገዶች አሉ። የመንደር ጉባዔዎች  ጉዳዮቹን እንዲመለከቱ ይደረጋል። በዕድሜ የገፉ ወገኖች ጉባዔዎቹን ይመራሉ። እያንዳንዱ የዚያ  ማሕበረሰብ አባል ለመናገር ጥያቄ ያቀርባል። ችሎቶቹ ዕርቀ ሰላም እና ፍትሕን ለወንጀል ፈጻሚው  እንዲሰጥ የሚያስችሉ መድረኮች ናቸው። ይህ የሚደረገው በቤትሰብ እና ጎረቤቶች ፊት ለፊት ነው። “ኢንያንጋሙጋዮ” በመባል የሚታወቁ የተከበሩ የአገር ሽማግሌዎች ለማሕበረሰቡ አባላት ባላቸው  ታማኝነት ተመዝነው ይመረጣሉ። “ኢንያንጋሙጋዮ” በወንጅሉ ውስጥ ያሉ ሁሉንም ወገኖች  ይሰበስባሉ። ካሳዎች እንዲከፈሉ ወይም የተወሰነ የማበረታቻ ዕርምጃን ጨምሮ ሌሎች የማግባቢያ  መንገዶች በመተለም ዕርቅ እንዲፈጠር ይጥራሉ። 22 የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች በይፋ የተዘጉት ግንቦት 2003  ዓ.ም. ነበር። ጥር 22 ቀን 2004 ዓ.ም. በትንሹ 1 ሚሊዮን 951 ሺህ 388 የዘር ማጥፋት ወንጀል  መዝገቦች በፍርድ ቤት ታይተው ተዘግተዋል። 23 

ለሩዋንዳውያን ይህ የስኬት ታሪካቸው ነው። ለቀሪ የአፍሪካ አገራት በራሳቸው የሕግ ፍላጎቶች ልክ  ሊቀመር የሚችል አንድ ተመክሮ ነው። ምዕራባውያኑ ባቋቋሟቸው የመመዘኛ መስፈርቶች ልክ፣  ባሕላዊውን ስርዓት መለካት ስህተት ነው። ከፍተኛ አቅም በሚጠይቁ ጊዜያት፣ አስፈላጊ ዕርምጃዎችን  መውሰድ ያስፈልጋል። ሩዋንዳ ራሷን ባገኘችባቸው አውዶች ውስጥ ይህ እጅግ ፈጠራ የተሞላበት፣  ሁሉም ሩዋንዳዊ ያያቸውን መከራዎች የመመልከቻ ዘዴ ነበረ። ለሰላም ማስከበር እና ዕርቅ የሚያገልግል  የተዘጋጀ መመሪያ የለም። መርሆዎች ግን ተሰናድተው ተቀምጠዋል። ሕዝብን ከመቀመቅ አውጥቶ  እንደገና መልሶ ለማቋቋም፣ ለታላላቅ ዓላማዎች አንዳንድ ወሳኝ መብቶች እና ነጻነትን መሰዋት ይጠይቃል፤ ለሰላም እና ዕርቀ ሰላም። ሩዋንዳውያን እንደሚያምኑት የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች  ለእነርሱ የፍትሕ ጥማት የተሰጠ አገር በቀል መልስ ናቸው። ከተገለጸው የተጠያቂነት ዓላማ ጋር ዕርቀ  ሰላምን ያስማሙ ስለመሆናቸውም ያወሳሉ። 24 ለተጎጂዎቹ የገንዘብ ካሳ ከመክፈል ይልቅ፣  የጥፋተኝነት ብይን የተላለፈባቸው ሰዎች መንገዶችን እና ሕንጻዎችን ወደ መገንባት እና መጠገን ስራ  እንዲገቡ ነበር የተደረገው። “በዚህ ስልት መንግስት የሚያምነው ሕዝቡ የሚሰራው በአጠቃላይ  ሩዋንዳውያንን ለመጥቀም ነው። ተጎጂዎች ደግሞ፣ ወንጀለኞች በገነቧቸው መሰረተ ልማቶች  ይጠቀማሉ።” 25 

የጋቻቻ ሞዴል በሩዋንዳ መንግስት፣ በአጋሮቹ እና በአንዳንድ ምሁራን ዘንድ ፍትሕ እና ዕርቅን የገነባ  ስኬታማ ስልት እንደሆነ ተደጋግሞ ይወደሳል። ጋቻቻን ከሚደግፉ ዋና ምሁራን መካከል ፊል ክላርክ  አንዱ ናቸው። ክላርክ ሙሉ በሙሉ ፍጹም ባይሆንም፣ ጋቻቻ ለስኬታማ ዕርቅ የሚያስችሉ  አጋጣሚዎችን የሚያስተናግድ መድረክ መፍጠሩን ያመለክታሉ። ቀስ በቀስ የሚሻሻል፣ የድሕረ ግጭት  የሕግ ስርዓት በሩዋንዳ እንዲፈጠርም የመሰረት ድንጋይ መጣሉን ያወሳሉ። ይሁን እንጂ ሌሎች የጋቻቻ  ፍርድ ቤቶች ያመጧቸው ውጤቶች የተደበላለቁ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። የቦስተን ዩኒቨርስቲ ምሁሩ  ቲም ሎንግማን ሲናገሩ፣ የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች ሩዋንዳውያንን ወደ አንድነት ከማምጣት ይልቅ የጎሳ  ልዩነቶችን ማጠናከራቸውን ይገልጻሉ። በዘር ማጥፋቱ ሰሞን የተፈጸሙ ወንጀሎችን ብቻ እንዲዳኙ  መመስረታቸው ሌሎች ወንጀሎችን (በተለይ የብቀላ ግድያዎችን) እንዳይመለከቱ ገድቧቸዋል። እነዚህ  ግድያዎች በገዢው የሩዋንዳ አርበኞች ግንባር እና በሌሎች ቱትሲዎች በተከታታይ ዓመታት የተፈጸሙ  ናቸው። ሌሎች ምሑራን ከታች በተጠቀሰው ጽሑፍ ላይ ከሎንግማን ጋር ይስማማሉ። አክለውም፣ የጎሳ  ቅራኔዎች የሚባባሱት በጋቻቻ ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ምክንያት መሆኑንም ያትታሉ። 26 ሆኖም ግን  ሩዋንዳውያን ጠበቃዎች እና ምሑራን የተለያየ ዕይታ አላቸው፣ 

“የሩዋንዳው የሽግግር ፍትሕ ልምድ ከፍተኛ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው። ይህ የሚታየው  ከዋነኛ ግቦች አንጻር ከሆነ ነው። ማለትም የሩዋንዳውያንን ሰብዓዊነት፣ ሰላም፣ አብሮ  መኖር፣ አንድነት እና ዕርቀ ሰላም ዳግም መመለስን የሚመለከት ነው። [አጽንዖት፡  የደራሲያኑ]…የጋቻቻ ፍርድ ቤቶች መመስረት በአስር ዓመታት ውስጥ ወደ ሁለት ሚሊዮን  ተጠርጣሪዎችን ለመክሰስ መቻሉ እንከን የለሽ ብቻ አይደለም። ለሩዋንዳውያን የራሳቸውን  ችግር በራሳቸው መንገዶች መፍታት እንደሚችሉ መልዕክት ያስተላለፈ ነው። 27 

በእርግጠኛነት መናገር የምችለው ነገር ቢኖር፣ በሩዋንዳ የከፋ የጎሳ መቃቃር እንደሚኖር የገመቱ  ምሑራን ስሁት መሆናቸውን ነው። ከዓመት ዓመት ያለውን ለውጥ ተመልክቼያለሁ። ከዘር ማጥፋቱ  በኋላ ወዲያውኑ ወደ ሩዋንዳ ሄጄ ነበር። ግራ በተጋቡ፣ ስነ ልቦናዊ ጠባሳ ባረፈባቸው፣ የደህንነት ስሜት  በማይሰማቸው፣ በደነገጡ፣ በአዘኑ ሕዝቦች መካከል ስሰራ ቆይቼ ነበር። እንደቱትሲዎች እና ሁቱዎች  ሆነው ወደ መደበኛ ሕይወታቸው መመለስ እንደሚችሉ የሚያውቁት ግልጽ ነገር አልነበራቸውም።  እንደጎረቤት እና ጓደኛ የሚቀጥሉበትን መላ አልደረሱበትም ነበር። ሁለቱም እንደአገር ሩዋንዳ ብቻ ነች  ያለቻቸው። የሚሄዱበት ቦታም አልነበራቸውም። በየቀኑ ከሩዋንዳውያን ጓደኞቼ ጋር የምወያየው  እንዴት ሩዋንዳ ከዚህ ሁኔታ ልትወጣ “ትችላለች?” በሚለው ሃሳብ ላይ ነበር። ያኔ ጥያቄውን ለመመለስ  ከባድ ነበር። ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ሩዋንዳ ተመላልሼያለሁ። የተወሰኑ ተስፋ ሰጪ ለውጦችን  ተመልክቼያለሁ። ግን አሁንም መታገል ያስፈልጋል። በመጨረሻም፣ የዘር ማጥፋት ወንጀሉ ከተፈጸመ፣  ከ20 ዓመታት በኋላ ወደ ሩዋንዳ ሄጃለሁ። ማንም ሰው ያን ጊዜ በጥላቻ እና በአሰቃቂ ወንጀሎች  ልቦናቸው የታጨቀባቸው ሕዝቦች “ይለወጣሉ” ብሎ ላያስብ ይችላል። እንዲሁም ካለፉት አሳዛኝ የታሪክ  ሁነቶች ጋር ስሙም በመሆን፣ ሃላፊነቶችን በመውሰድ፤ ይቅር በማለት፤ ንስሃ በመግባት፤ ካለፉት ስሕተቶች በመማር፤ በጌታ እና በማሕበረሰቡ ፊት ሕሊናቸውን በማንጻት፤ ሰላማዊ እና የተረጋጋ  ማሕበረሰብ ሊፈጥሩ ችለዋል። 

ሩዋንዳ ለዕድገት ስትፋጠን ማየት ተዓምራዊ ለውጥ ነው። በመቻቻል እና በግልጽነት የተሻለ ኑሮ መኖር፣  ቤተቦቻችንን ማሳደግ እና ሕልሞቻችንን ማሳካት እንደምንችል ልምድ እየሰጡን ነው። ይህ ነው  በሩዋንዳ እየሆነ ያለው። ስለዚህ መላው ዓለም ይህንን ተመልክቷል። ጠንካራ አመራር የሚፈልግ ሂደት  ነው። ያለጠንካራ አመራር፣ በተስፋ መቁረጥ እና ግጭት ውስጥ መዘፈቅ ሊመጣ ይችላል። ጠንካራ  አመራር ሰላም እና መቻቻል ከሁሉም በላይ በማስቀደም ይፈጠራል። ፖለቲካን ሕዝቦችን ወደ አንድነት  የማምጫ መሳሪያ አድርጎ ይመለከታል። ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ተጠቃሽ ስራ ሰርተዋል። አንዳንዶች  እጅግ በጣም ጥብቅ “ናቸው” በማለት ይከስሷቸዋል። ነገር ግን ሊበራል ዴሞክራሲ በሁሉም  ማሕበረሰብ ውስጥ ሊሰራ አይችልም። በፖል ካጋሜ በኩል ካየን፣ ሽግግር ለመፍጠር እና የሚሊዮኖችን  የቆሰለ ልብ ቀስ በቀስ እንዲፈወስ ለማስቻል በቅተዋል። አለፍ ሲልም ለመቻቻል እና ግልጽነት ቦታ  ሰጥተዋል። በአፍሪካ አሕጉር ችግር ካለባቸው አገራት አንዷ የነበረችው ሩዋንዳ፣ አሁን በሁሉም ዘርፍ በአፍሪካ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘች ናት። ይህ ዕውን ሊሆን የቻለው ጥላቻ እና በቀል ቦታቸውን  ለመቻቻል እና ሰላማዊ አብሮነት ስለለቀቁ ነው። ሁቱዎች እና ቱትሲዎች ያለምንም ችግር አብረው  ይሰራሉ፣ ይግባባሉ፣ ያርሳሉ፣ ማሕበረሰብ አቀፍ ግዴታዎቻቸውን አብረው ይወጣሉ። የሩዋንዳ ሕዝቦች  የደህንነት ስሜት ይሰማቸዋል። እርስ በርስ የሚሰማቸው ጥርጣሬ ዝቅተኛ ነው። ሩዋንዳ ለሁሉም  ዓይነት ባለሐብቶች በሯን የከፈተች አገር ሆናለች። የአገሪቱ የኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍ በተወሰነ እና  በፈጠነ ልክ እያደገ ነው። የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ማዕከል ለመሆን ችላለች፤ ሩዋንዳ። ከቦትስዋና  በመቀጠል፣ ሩዋንዳ በአፍሪካ አነስተኛ የሙስና ወንጀል መጠን ካለባቸው አገራት አንዷ ነች። 28 ሕዝቦች  ትኩረታቸው በዕድገት እና ብልጽግና ላይ ነው። ወደ ኋላ ተመልሶ ለማየት ምንም ዓይነት ጊዜ የላቸውም።  ግና ከዩጋንዳ ጋር በሚያዋስነው ድነበር በኩል የሚንቀሳቀሱ የኢንተርሃምዌ ርዝራዦች አሁንም አሉ።  የታላላቅ ሃይቆች ቀጣና ውስብስብ የጸጥታ ችግሮች አሉበት። እነዚሁ ችግሮች በፍጥነት ዕልባት  ሊደረግባቸው ይገባል። ሩዋንዳ ከዴሞክራቲክ ሪፑብሊክ ኮንጎ፣ ዩጋንዳ እና ብሩንዲ ጋር ያጋጠማት እሰጥ  አገባ ትኩረት ያሻዋል። 

እነዚህ ፈተናዎች ቢደቀኑም፣ በፖል ካጋሜ አመራር ስር የምትገኘው ሩዋንዳ እየበለጸገች ነው። የእርሳቸው  አመራር ከውዝግብ የጸዳ አይደለም። አንዳንድ በከፍተኛ መጠን የሚደፈጥጡ ፖሊሲዎቻቸው  የወቀሳው ማዕከል ናቸው። ነገር ግን ያለምንም ጥርጥር በወጥነት ብርታታቸውን አሳይተዋል። ሌላ  ግጭት በአገራቸው እንዳይፈጠር መከላከል ቁጥር አንድ ዓላማቸው መሆኑን ገልጸዋል። ጥቂት መሪዎች  እንዲህ ያለ ውጤት ተኮር ባሕርይ እና ጥንካሬ አስመስክረዋል። ሕዳር 25 ቀን 2011 ዓ.ም. በታተመው  ፎርብስ አፍሪካ መጽሔት፣ እርሳቸውን የ2018 (እ.ኤ.አ.) “ምርጥ አፍሪካዊ” ሲል ሰይሟቸው ነበር።  በተጨማሪም፣ “ባለራዕይ” በማለት ገልጿቸዋል። ከዚህም ባሻገር፣ የመላ አፍሪካ የቢዝነስ መሪዎች  ሽልማት የዓመቱ አሸናፊ ነበሩ። በሩዋንዳ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች እንደሚያምኑት፣ ካጋሜ ላለፉት ሶስት  አስርት ዓመታት ያልተበገሩ መሪ ናቸው። “አሉታዊ ዜናዎችን እንድንሰማ የሰርክ ልማድ በሆነብን  አሕጉር፣ በፖል ካጋሚ አመራር የምተመራዋ ሩዋንዳ የትኛውንም መሰናክል በጥንካሬ እና በፈጠራ  እያለፈችው ነው።” 29 

ማጠቃለያ 

በደቡብ አፍሪካ እና ሩዋንዳ የነበሩትን የዕውነትና ዕርቅ ሒደቶች ካነጻጸርን፣ የተገኙት ትምሕርቶች ግልጽ  ናቸው። ሁለቱም ሒደቶች አነሰም በዛ ተመሳሳይ ዓላማዎች ነበራቸው። ግና ውጤቶቻቸው የተለያዩ  ነበሩ። በሒደቱ ከተስተዋሉት ስሕተቶች እና ከላይ ወደ ታች ሲሄድ በነበረው የዕርቅ ጥረት ላይ ከባባድ ወቀሳዎች ጋር አያይዘን ካነጻጸርን፣ ሩዋንዳ ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ሌሎች የአፍሪካ አገራት የተሻለ  ውጤትን “አግኝታለች” ብዬ አምናለሁ። በሩዋንዳ — ምናልባት በተሟላ ትክክለኛነት ባይሆንም — ዕውነት ሁሉ ተነግሯል። ነገር ግን ማሕበረሰቡ ውስጥ ተጎጂዎች እና ተጠርጣሪ ወንጀለኞች ባሉበት ነበር  የተነገረው። በጋቻቻ ስርዓት ፍትሕ ሲሰጥ ነበር። በተጨማሪም፣ በሩዋንዳ የፍርድ ቤት ስርዓት፣ በሩዋንዳ  ዓለም አቀፍ ችሎት እና በአሩሻ ከተማ በተቋቋመው ልዩ ችሎት ፍትሕ ለመስጠት ጥረት ተደርጓል። ከዚህ  ጋር ሊጠጋጋ የሚችል አንድም ክንውን በደቡብ አፍሪካ አልተከናወነም። እዚያ ሁሉም ዕውነታ  አልተነገረም ነበር። ሁሉም ወንጀለኞች እና ተባባሪዎቻቸው በዕውነት እና ዕርቅ ኮሚሽን ፊት እንዲቀርቡ  አልተደረገም ነበር። ምንም ዓይነት የካሳ ክፍያዎች ከፍትሕ ጋር የመስጠት ጥረቶች አልተከወኑም።  በአፓርታይድ የተከፋፈሉትን አራት ማሕበረሰቦች — ነጮች፣ ሕንዶች፣ ክልሶች እና ጥቁሮች – እርስ  በርሳቸው ዕርቅ እንዲያወርዱ አልተደረገም። ልክ በአፓርታይድ አገዛዝ ዘመን ተከፋፍለው እንደነበረው፣  አሁንም እንደዚያው ተከፋፍለው ቀጥለዋል። ዛሬ ለመናገር እንደሚቻለው የደቡብ አፍሪካ የወደፊት  ዕጣ ግልጽ አይደለም። በዓለም ዕኩልነት ካልሰፈነባቸው አገራት መካከል አንዷ እንደሆነች አለች። በሌላ  በኩል ሩዋንዳ የስኬት ጉዞዋን እያስመሰከረች ነው። የነበሩትን ዓውዶች እና ታሪኳን በመፈተሽ  መመልከት ይቻላል። ዓለም ይበልጥ ዕውነት እና ዕርቅ ይፈልጋል። ግን ይህ መደረግ ያለበት አሁኑኑ ነው። 

ላለፉት ሶስት አስርት ዓመታት፣ ከ40 በላይ አገራት የዕውነት ኮሚሽን አቋቁመዋል። ከእነዚህ አገራት  ካናዳ፣ ቺሊ፣ ኢኳዶር፣ ጋና፣ ጓቲማላ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ጋምቢያ፣ ላይቤሪያ፣ ሞሮኮ፣ ፊሊፒንስ፣  ሴራሊዮን፣ ደቡብ አፍሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ተጠቃሽ ናቸው። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በነበሩት  የኑረንበርግ ችሎቶች ከሚታወሰው የአጸፋዊ ፍትሕ ይልቅ የማገገሚያ ፍትሕ ከፍ ያለ ፈውስን  እንደሚሰጥ ተስፋ አለ።30 በወንጅሎች ብዛት እና በማሕበረሰቡ የተናጋ ሁኔታ ምክንያት እያንዳንዱ  ጥሰት በመደበኛ ጊዜያት እንደሚከወነው ላይመረመር ይችላል። ለእንዲህ ያሉ ጉዳዮች የሩዋንዳ ተመክሮ  ጠቃሚ ሆኖ የሚታይ ይሆናል። ለትንንሽ ወንጀሎች እና የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች በጎሳዎች የሚተገበሩ  ባሕላዊ ስርዓቶች ማሕበረሰብ አቀፍ የፍርድ ስርዓቶችን ዳግም ማቋቋም አያቅታቸውም። እነዚህ የፍርድ  ስርዓቶች ስህተቶችን የመመልከት፣ ወንጀለኞችን የመቅጣት እና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ሚና  ይኖራቸዋል። ይህ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ግን በጥልቅ ሊሰራበት የሚገባ አስፈላጊ ጉዳይ ነው። የሩዋንዳው  የጋቻቻ ስርዓት ስራውን ለማጠናቀቅ በአጠቃላይ 16 ዓመታትን ፈጅቶበታል። በዚህም ቆይታው ወደ  ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ የወንጀል መዝገቦችን ለመመለከት ሲሰራ ከርሟል።  

በብሔራዊ ምክክር (ዕውነት፣ ፍትሕ፣ ካሳ እና ዕርቅ ኮሚሽን) የሚቀርቡ ግኝቶች እና ምክረ ሃሳቦችን  ተከትሎ፤ የሕገ መንግስት ለውጥ፣ ሕጎችንና ፖሊስ፤ ፍርድ ቤት፣ ወታደራዊ እና ወታደራዊ ደሕንነትን  ጨምሮ ሌሎች ተቋማትን መለወጥ ሊደረግ ይችላል። በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚደረግ  ማንኛውም ሙከራ፣ ከላይ የተጠቅሱትን ሁሉንም ነገሮች መሬት ላይ መተግበር አለበት፤ የፈጀውንም  ጊዜ ይፍጅ። ይህንን ሁሉ ነገር ያላካተተ ሙከራ ወደ ሰላም አይመራም። ፤ በህዝቦች መካከል የሚነሱ  ቅሬታዎች እና ቅራኔዎች ምላሽ ካልተሰጣቸው፣ የህዝቦችን የእርስ በርስ ግንኙነት የማይጠገንበት ደረጃ  ላይ ያደርሳል። እንደሃገርም እንደ ህዝብም ኢትዮጵያ ላትኖር ትችላለች፤ይህም ነገር አስቀድሞ ጀምሯል። 

ግን ለመፍትሂው አልዘገየችም። መመለስ ወደማይቻልበት ደረጃ እንዳይደረስ፡ ግንዛቤ፡ እውቀት፡  ሃላፊነትና ጠንካራ አመራር በሁሉም ደረጃ ያስፈልጋል።  

የብሔር ፖለቲካ ታሪክ እና ሐሰተኛ ዜናዎችን ያመርታል። በርካታ ኢትዮጵያውያን በማንኛውም ጉዳይ ዙሪያ ኢትዮጵያ ላይ ያለውን ዕውነት አያውቁትም። የኢትዮጵያ ታሪክ ከማናቸውም የአፍሪካ አገራት  ታሪክ በበለጠ ተመዝግቧል። ይሁንና ከ30 ዓመታት በላይ ኢትዮጵያውያን ስለራሳቸው ለሚናገር፤  የተዛባ እና የፈጠራ ታሪክ ተጋላጭ ሆነዋል። በታሪክ ምክንያት እርስ በርሳቸው እየተፋለሙ ነው። ይህም  አንድን አጀንዳ ለማሳካት ሲባል በፖለቲከኞች የተፈጠረ ነው። እውነተኝ ታሪክ እየተለወጠ በመመዝገብ ላይ መሆኑን ብዙዎች የሚያውቁ አይመስሉም። ገሪቱን የሃሰት ታሪክ እያጥለቀለቃት ነው። አዲሱ  ትውልድ አያነብም፤ ማንበብ አይችልም ወይም ታሪካዊ ዕውነታዎችን የሚያገኝበት ክፍት የሆነ ዕድል  አላገኘም። የተለያዩ አንጃዎች የሚነግሩትን ሁሉ አምኖ ይቀበላል። አሁን ዕውነታ ጠፍቷል። ዕውነታው  እስካልተነገረ፤ እያንዳንዱ ብሔር በታሪክ ላይ የጋራ መግባባት ላይ እስካልደረሰ፣ ወንጀሎች  እስካልተጋለጡ እና ተጎጂዎችና ወንጀለኞች ፊት ለፊት እስካልተገናኙ ድረስ፣ ወደ ሰላማዊ  አብሮ መኖር መሸጋገር አይቻልም። ከዚያ በኋላ ነው ፍትሕ የሚሰፍነው፣ ካሳዎችን መክፈል  የሚቻለው። የዕርቅ ሂደቱ የሚጀምረው ካለፈው ታሪኳ ጋር ቁርሾ በሌላት፣ በተለወጠችው  ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። ሰላምን ለማምጣት እና ዕርቅን ለመተግበር፣ አገሪቱን እያመሱ ያሉ የኦሮሞ  ጽንፈኞች ሃሳቦቻቸውን ለማራመድ፣ ታሪካቸውን በግልጽ ለማተት እና ታሪካዊ ዕውነታዎችን  በአደባባይ፣ ማለትም ከፖለቲካ ስርአት በሁዋላ በሚቕቕመው ብሔራዊና ነጻ፡ የዕውነት፣ የፍትሕ፣  የካሳ እና የዕርቅ ኮሚሽን ፊት ለመጋፈጥ አምነው መቀበል ይኖርባቸዋል። የትኞቹ ጥያቄዎች እና  ታሪካዊ ማረጋገጫዎች ተቀባይነት እንደሚኖራቸው በሕዝቡ ይወሰናል፤ ሕዝቡ በአንዳንድ የታሪክ እና  የእውነታዎች አተረጓጎም ዙሪያ ጊዜ ለመስጠት መስማማት ይገባዋል። 

መጠኑ ከማይታወቅ ጊዜ ጀምሮ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በተለያዩ ብሔሮች እና የዕምነት ቡድኖች  የሚነሱ ቅሬታዎች እና ጥያቄዎች ላይ የሚያጠነጥኑ፣ ዕውነተኛ እና ታማኝ የሆኑ ሕዝባዊ ውይይቶች  ተደርገው እያውቁም። አሁን የጎሳ ውጥረቶች እዚህ ደረጃ ላይ በመድረሳቸው፤ የአገሪቱን አንድነት  ለመታደግ፣ የእርስ በርስ ጦርነትን ለመከላከል እና ወደ ሰላማዊ አብሮ የመኖር መንገድ ለመግባት  ብቸኛው መፍትሔ ታሪክ ውስጥ ምን እንደተፈጠረ በገለልተኛ የታሪክ ምሁራን አማካይነት ግልጽ  ውይይት ማድረግ ነው። ለዚህ ውይይት የስነ ልቦና ባለሞያዎች ያስፈልጉ ይሆናል። ምክንያቱም የወል  ስነ ልቦናዊ ችግሮች ያሉባቸው አክራሪዎች፤ ጤነኛ ሰዎች ወደሚነጋገሩበት የተግባቦት መንገድ እንዲገቡ  የቅርብ ክትትል ያስፈልጋቸዋል። 

የዕርቀ ሰላም ስነ ልቦናዊው ገጽታ ከግጭት ስሜት መውጣትን የሚጠይቅ ነው። በተለይም ስለቡድናዊ  ግቦች በሚያጠነጥኑ ማሕበረሰባዊ ዕምነቶች፤ ስለተቀናቃኝ ቡድን፣ ስለራስ ቡድን በሚኖር አመለካከት፤  ከሌሎችም ወገኖች ጋር በሚኖሩ ግንኙነቶች እና በሰላማዊ ድባብ በኩል ለውጥ ሊያስፈልግ ይችላል።  በመሰረቱ፣ ስነ ልቦናዊ ዕርቀ ሰላም የሚሻው ነገር የሰላም ስሜትን መፍጠር ነው። ግና ይህን ነገር ማባሪያ  ባጣ ግጭት መካከል ላይ መፍጠር በእጅጉ ይከብዳል። የፖለቲካዊ ስነ ልቦና ባለሞያዎች ስለዕርቀ ሰላም  ያለውን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ መስራት ይኖርባቸዋል፤ አለባቸውምም። ከግጭት መፍታት  ይልቅ ብዙም ትኩረት ያልተሰጠው ጉዳይ ይህ ነው። 30 ምንም እንኳ አሳማሚ ቢሆንም፣ የተሟላ  ዕውነት በሌለበት ዕርቀ ሰላም ሊኖር አይችልም፤ አሁን ያለውን ጥልቅ ሕመም አይሽረውም። አሁንም  ቀጥሎ የሚመጣውን መከፋፈል ለጊዚው ይሸፍነው ይሆናል። ግን ውሎ አድሮ ራሱን በከባድ ሁከት እና  ብጥብጥ የሚገልጽ ነው። ባለፉት ዓመታት ሃላፊነት በማይሰማቸው እና ዕውነትንም ሆነ መረጋጋትን  በማይፈልጉ ልሂቃን የተከማቸው ንዴት እና ፍርሃት ግጭት ብቸኛ የማስተንፈሻ ቦይ ሊሆን ይበቃል።  ኢትዮጵያ ውስጥ የምናየው ይህንን ነው። 

ይህ ቅንቀና የረዥም ጊዜ የፈውስ ሂደት ነው። በጥሩ ዕምነት እና በጠንካራ የአሰራር መዋቅር  ከተጀመረ፣ ሰዎችን የሚያቀራርብ ነው። በተጓዳኝም ለሕዝቦች ተጠያቂነትን፣ ዕኩልነትን፣ ነጻነትን እና  ፍትሕን ለማምጣት የሚተጋ የፖለቲካ ስርዓት የዚሁ አንድ አካል ነው። ዕርቀ ሰላሙ በፖለቲካ፣  በማሕበራዊ፣ በፍትሐዊ እና በኢኮኖሚያዊ መስኮች የሚስተዋሉትን መዋቅራዊ የፍትሕ መጓደሎች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። በእርግጥም፣ “ግጭት የሚቆሰቁሱ እና የሚያጠናክሩ፤ ካለፈው ጊዜ  የሚመጡ ልማዶች፤ሃሰቶች፤ ሳይለወጡ ከቀሩ፣ ወዲያውኑ ተመሳሳይ ውጤትን ይፈጥራሉ።  ስለሆነም በአዘጋሚ የስልጣን ማጋራት፣ የእርስ በርስ የፖለቲካ አቋሞችን በመከባበር፣  ለኢኮኖሚያዊ ፍትሕ የሚመች ምህዳር በመፍጠር እና ሕዝቡ በስፋት በሚቀበለው ደረጃ ባለፈው ታሪክ (እስከ ሚቻለው ድረስ) እና የወደፊት አካሄድ በመተማመን፣ ዕርቀ ሰላም  መደገፍ አለበት። ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍትሕ የጠንካራ ዕርቀ ሰላም  መሰረት ነው።” 31  

 ፍትሃዊ ሽግግር ይህ ነው። ረጂም እልህ አስጭራሽ ነው። ግን አስተማማኝ ነው።  

ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ  

AISSS Excuive Director. www.aisss.org  

https://branko2f7.substack.com/p/there-is-no-exit-for-dictators

1 https://www.psychologytoday.com/us/basics/empathy 

2 https://www.goodreads.com/author/quotes/56576.Lewis_B_Smedes 3https://www.pressreader.com/south-africa/the-star-south-africa-late edition/20100310/281505042387578 

4 https://www.un.org/ruleoflaw/files/TJ_Guidance_Note_March_2010FINAL.pdf *For details read my most recent book: What A Life! 

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

4 COMMENTS

  1. ሻለቃ ዳዊትን የምጠይቀው ነገር ለምን አንዳንድ ሰዎች አምባገነን ይሆናሉ? አብሮአቸው የተወለደ አስተሳሰብ ወይስ የተበላሸ ወይም ያልተገለጸለት የህብረተሰብ አወቃቀር ውጤት? እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች እንዴት ነው ስልጣን ላይ የሚወጡት? ስልጣን ላይ ከወጡስ በኋላ በምን ዘዴ ነው ቀድሞ የተዋቀረውን የሚሊተሪ፣የጸጥታና የፖሊስ ተቋማትን፣ በመሠረቱ የመጨቆኛ መሳሪያዎችን ለመቆጣጠር የሚችሉት? እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ብቻቸውን ወይስ በውጭ ኃይሎች በመደገፍ ነው ስልጣን ላይ የሚወጡት? አምባገነናዊ አገዛዝን ከዓለም አቀፍ ካፒታሊዝም ነጥሎ ማየት ይቻላል ወይ?

    • ጥያቄህ መልካም ጥያቄ ነው። ጡረተኛው የደርግ ሻለቃ ዳዊት ግን ጥያቄህን ለመመለስ ትክክለኛ ሰው አይደሉም። እርሳቸው የገቡበት ሲበላሽ እንጂ ሲለማ አላየንም። ከላይ የብዙ አምባገነኖችን ስም ጠቅሰው የራሳቸውን ስም መርሳታቸው ምልክት ይሁንህ።

  2. ወንድም ፈቃዱ፡ ጥያቄው ብዙ የሚያነጋግር ነው:: የሶስዯሎጂ ምሁራንን እስተዋፅኦ ይጠይቃል :: ስለዚህም እኔ ያነበብኮቸውን እኔ ዘንድ ያሉ ሶስት መፅሀፎችን ማንበብ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ:: ዞሮ ዞሮ ከእስተዳደግና ከእካባቢ ይጀምርና እምባገነን እዝማሚያ ያላቸውን የፓለቲካና ሌሎችም ጥቅም የሚጠብቁ ግለሰቦች ድርጅቶችና መንግስታት መልምለው ደግፈው መንበሩ ላይ ያስቀምጦእቸዋል:: Origins of Totlitatianism by Hannah Arendt Social Origins of Dictators by Jr Moore Barrington Dictatorship by Frank Dikotter
    የምእራባዊያን ትቅም ማስከበሪያ ትልቅ መሳሪያ ሆኖ ቆይቶአል
    ከምስጋና ጋር

  3. ወንድም ፈቃዱ: ጥያቄው ብዙ የሚያነጋግር ነው:: የሶስዯሎጂ ምሁራንን እስተዋፅኦ ይጠይቃል :: ስለዚህም እኔ ያነበብኮቸውን እኔ ዘንድ ያሉ ሶስት መፅሀፎችን ማንበብ ይረዳል ብዬነው:: ዞሮ ዞሮ ከእስተዳደግና ከእካባቢ ይጀምርና እምባገነን እዝማሚያያላቸውን የፓለቲካና ሌሎችም ጥቅም የሚጠብቁ ግለሰቦች ድርጅቶችና መንግስታት መልምለው ደግፈው መንበሩ ላይ ይስቀምጦእቸዋል:: Origins of Totlitatianism by Hannah Arendt Social Origins of Dictators by Jr Moore Barrington Dictatorship by Frank Dikotter

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here