ጸሃፊው ኢትዮጵያ ያሉ በመሆናቸው ስማቸው እንዳይወጣ ጠይቀዋል

የደርግን ውድቀት ከረዥም ጊዜ አንጻርና ከርቀት ስናየው
ግዙፉና በወታደራዊ ቁመናው በኢትዮጵያ ታሪክ በጦር አደረጃጀት፤ በስልጠና ብቃት፤ በውጊያ ስረዓትና በአስፈሪነቱ በቀላሉ ይወድቃል ተብሎ የሚገመት አልነበረም። “የደርግ ሽንፈት እና የአዲሲቷ ኢትዮጵያ እና የኤርትራ መመስረት” በሚል ርዕስ ፖል ቢ ሄንዜ በ1992 እ.አ.አ እንዳሰፈረው የደርግን ውድቀት ያፈጠኑት የሶስት አበይት ሁኔታዎች መገጣጠም ነው ይላል። እነዚህም፦
- የሁለቱ ዋና ዋና አማፂ ንቅናቄዎች ከዶግማቲክ ማርክሲዝም ወደ ዲሞክራሲያዊ ተግባራዊነት መሸጋገር እና በሁለቱ አማፂ ቡድኖች መካከል ያለው ትብብር ዝግመተ ለውጥ
- የዩናይትድ ስቴትስ አስተዋይ ዲፕሎማሲያዊ ጣልቃገብነት
- የሶቪየት ኅብረት ውድቀት ነው።
የእነዚህ ሶስት እድገቶች ተጽእኖ እርስ በርስ የሚደጋገፍ ነበር እንጂ ማንም በራሱ በግንቦት መጨረሻ እና በ1991 እ.አ.አ ላይ የተከሰቱትን እድሎች ሊያመጣ አይችልም ነበር ይላሉ ጸሀፊው።
በመጨረሻም ደርግን እንዲወድቅ ካደረጉት ስትራቴጂካዊ ጦርነቶች መካከል በ1989 እ.አ.አ የሽሬ ጦርነት ትህነግ የመንግስት ሃይሎችን ያሸነፈበት እና በ1988 ዓ.ም የአፋቤት ጦርነት ሻዕቢያ በመንግስት ወታደሮች ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶ የሃይል ሚዛኑን ባዛባበት ጦርነት ነው። እነዚህ ጦርነቶች የደርግን የስልጣን ጥንካሬ በማዳከም ለአማጺ ሃይሎች ተጨማሪ ግስጋሴ መንገድ ጠርገዋል። ከዚህ ኤርትራ ህዝባዊ ነጻነት ግንባር (ኤ.ህ.ነ.ግ) ድል በኃላ ሁለቱ ግንባሮች ማለትም የኤ.ህ.ነ.ግ እና ት.ህ.ነ.ግ ግልጽ ወደ ሆነ የግንባር ትብብር ተሸጋግረዋል።
በተለይ ት.ህ.ነ.ግ በመጋቢት 1989 እ.አ.አ የደርግ ጦርን በማሸነፍ ከሽሬ እንደ ስላሴ ካስወጣ በኃላ ከትግራይ ርዕሰ ከተማና ከሰሜን ደቡብ ያለውን የክልሉን መስመር ዘግቶ መያዝ ችላል፡፡ በ1990 እ.አ.አ ኤ.ህ.ነ.ግ የምጸዋን ወደብ ሲቆጣጠር የኤርትራ ደጋማ ክፍሎች በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ችሏል። በዚህ አስመራን ጨምሮ የኤርትራ ወሳኝ አካባቢዎች በሻቢያ ከበባ ስር ወድቋል ማንኛው ለጦርነት የሚሉ ሎጂስቲኮች በአየር ካልሆነ መግባት አይችልም ነበር።
እነዚህ ድሎች ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ቢሆኑም ት.ህ.ነ.ግ የፖለቲካ ስልቱን ባያሻሽል ኖሮ በሰሜን መካከለኛው ኢትዮጵያ የደርግ ሃይል በፍጥነት እንዲወድቅ ማድረጋቸው አጠራጣሪ ነው። በአልባኒያ ቀኖናዊ መነጠል የተነሳ የት.ህ.ነ.ግ መሪዎች በጠባብ የተመሰረተውን ክልላዊ ማርክሲስት ሌኒኒስት አመጽ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ሰፊው የኢትዮጵያ ብሄራዊ የነጻነት ንቅናቄ ቀየሩት።
እ.ኤ.አ. በ1989 መጨረሻ ላይ ህወሓት የፈጠራቸውን እንቅስቃሴዎች በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በማዋሃድ ግንኙነት የሌላቸውን ታጣቂ ቡድኖች እንዲቀላቀሉ ጋብዟል (ፖል ቢ ሄንዜ: በ1992)።
በሌላ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ ዶ/ር ወርቁ ደረደ “እድገት ብሎ ውድቀት የወታደር ሶሻሊዝም” በሚል መጽሐፋቸው የደርግን ጦር መፈታት (መውደቅ) ሲገልጹ ከጦር ስልት አንጻር የተፈጠረ መሆኑን አንስተዋል። ደርግ የገጠመው ጦር (ት.ህ.ነ.ግ ማለታቸው ነው) የሽምቅ የጎሬላ ስልትን የሚከተል ጦር ነበር። ከደርግ በተቃራኒ ያሉት አማጺያን ሽምቅ ተዋጊ ነበሩ። በዚህ በደፈጣ አጥቅቶ የመሸሽ ወይም የመሮጥ ስልት ነበራቸው። እንዚህ አማጺያን ከሽምቅ ውጊያ ወደ ፊት ለፊት ውጊያ የገቡት በኃላ ሃይላቸውና ጀርባቸው ሲደላደል ወደ መጨረሻ አካባቢ ነው። እንደ ዶ/ር ወርቁ በደፈጣ ውጊያ ላይ ያለን ሃይል በመደበኛና በፊት ለፊት በሚዋጋ ጦር መግጠም አግባብነት አልነበረውም። መደበኛ ሰራዊት ለመደበኛ ጦርነት እንጂ ለጎሬላ አይሆንም፤ ስልጠናውም ትጥቁም እንቅስቃሴውም የተለየ ነው። ለሽምቅ ውጊያ የተለየ ስልጠናና ትጥቅ ያስፈልጋል ያሉት ዶ/ር ወርቁ በንጉሱ .ቀ.ኃ ስላሴም ጊዜ የኤርትራ ገንጣይ ንቅናቄዎች ከቁጥጥር ውጭ እንዲሆኑ አድርጎ የነበረው መደበኛው ሰራዊት ሳይሆን በሽምቅ ተዋጊው አምሳል ትጥቁ ቀላል ጓዙም ጥቂት በነበረው ሃይል እንደሆነ እየታወቀ ደርግ ይህንን ችላ በማለት አብዛኛው ትጥቁ ከባድ ጓዙ ብዙ በሆነ በመደበኛ ጦር የተዋጋው ለምን ነበር በማለት ይጠይቃሉ። ከዚህ አንጻር ደርግ ለገጠመው ጦር ተመጣጣኝ የጦርነት ስልት አለመከተሉን እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ።
በሁለተኛ ደረጃ የጦር ክፍል ውስጥ ውስጡን በደርግ ሃሳብ እና እርምጃ የተማረሩት መኮንኖች ደርግ በመጨረሻ የገነባው ግዙፉ የኮማንዶ ጦር በእንጭጩ እንዲቀር አድርጎታል ይላሉ።
በ1983 ዓ.ም በእንግሊዝ ሀገር በተደረገ ድርድር (በኢህዲሪ [ደርግ]፤በትህነግ፤ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) እና የኤርትራ ሕዝብ ነጻ አውጭ ግንባር (ህግሓኤ) ኦነግን የወከሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የደርግን መውደቅ ምክንያት ሲያነሱ ደርግ በ1981 ዓ.ም በነበረው መፈንቅለ መንግስት በኋላ ጦሩ “አልነበረም” ማለት ይቻላል ብለዋል፡፡ በመፈንቅለ መንግስቱ ጄነራሎች ሲያልቁ ጦሩ በጣም መድከሙንና ይህም ለደርግም መውደቅ ትልቁ መንስኤ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የኢህዲሪ ፕሬዝዳንት የነበሩት ኮ/ል መንግስቱ ሀገር ጥለው መሄዳቸውም ጦሩ አመራር እንዳይኖረው አድርጎታል ያሉት ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) አሁን ያለው ሁኔታ ያኔ ከነበረው ጋር እንደሚለያይ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ አንስተዋል፡፡
በሶስተኛ ደረጃ ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ ማተኮር፤ ደርግ የሰሜኑ ጦርነት እያየለ ሲመጣ የወቅቱ የደርግ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ፕሬዛዳንት ጓድ መንግስቱ ሃ/ማሪያም “ወታደሩን ስድስት (6) ሚሊየን አድርሰነው ልናጥለቀልቀው እንችላለን” በማለት የኤርትራን ተገንጣይ ሃይሎች አስፈራርተው እንደነበር ይታወሳል። በዚህም ደርግ ከጥራት ይልቅ ብዛት ላይ ያተኮረ የወታደር ምልመላ ውስጥ ገብቶ ነበር።
ዶ/ር ወርቁ ልክ እንደ ፖል ቢ ሄንዜ (1992) ደርግ በተከተለው የፓለቲካ ርዕዮት ዓለም በሶሻሊዝም ካምፕ ውስጥ መሆኑ ብዙ ጠላቶችን በዙሪያው የቀሰቀሰ ሆኖል ብለዋል።
በአራተኛ ደረጃ ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች ተያይዘው ግዙፉ የጦር ሰራዊት ቀስ በቀስ ከእዝ ሰንሰለት እየተበጣጠሰ በትክክል ትዕዛዝ ማድረስና መቀበል ችግር እየሆነበት መጣ። ወታደሩ ቀርቶ አዛዥም እርስ በርስ በማይተዋወቅበትና በማይተማመንበት ደረጃ ደርሶ ጠላት በቀላሉ መሃላቸው በመግባት ሲያተራምሳቸው ታይቷል። ወትሮ የወታደሩ ምደባ በችሎታና በወኔና በሀገር ፍቅር መሆኑ ቀርቶ ለግለሰብ ታማኝነት ላይ የተመሰረተ ሆነ፤ አድርባይነትና አጎብዳጅነት ታየ። በመጨረሻም በተለይም ከሽሬው ሽንፈት በኃላ ጎልቶ የታየው ክስተት ቢኖር ከፍተኛ ስልጣን የነበራቸው ሰዎች ሃላፊነታቸውን በመዘንጋት ለማፈግፈግና ለሽሽት ግንባር ቀደም መሆናቸው ነው። በተለይ ከመቀሌ የአካባቢው አዛዥ የነበሩት ለገሰ አስፍው ተጠቃሽ ናቸው፤ ቀድመው አዲስ አበባ በመግባት።
ሁለቱ ለጋራ ጥቅም የስትራቴጂካዊ ጥምረት የፈጠሩት ሃይሎች በተለይም ትህነግ ከትግራይና አስመራ መጽዳት በኃላ ከፍተኛ ተጋድሎና ትንቅንቅ የገጠማቸው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋና በባህር ዳር ነው። በደርግ ጦር ጀርባ ሆነው ከፍተኛውን ቅስቀሳና ሞራል ሲሰጡ የነበሩ የጦርና የሲቪል ባለስልጣናትና ሃላፊዎች በባህር ዳር በነበረው ውጊያ ቤተሰቦቻቸውንና ጓዞቻቸውን አስቀድመው ወደ አዲስ አበባ በመላክ የአባይን ድልድይ በማበላሸት ጦሩንና ህዝቡን ጥለው ወደ ዳንግላና ደብረማርቆስ ፈርጥጠዋል። ከዚህ በኃላ ወታደሩ የቻለ መሳሪያውን ይዞ ያልቻለ እየጣለው ወደ አዲስ አበባ እና ወደ መጣበት ተበትኖል። ወታደሩ ቀድሞውንም ከመፈንቅለ መንግስቱ በኃላ ያለመሪና በቂ ወታደራዊ ስነስረዓት ባለመቆየቱ ወደ ልቅነት ተሸጋግሮ እንደነበር ዶ/ር ወርቁ ወረደ ይናገራሉ።
የጦርነቱ መክበድ የደርግ መውደቅ አይቀሬነት የተረዱት ጓድ መንግስቱ ደርግ ባያድነውም አንዳንድ የስልጣን ሽግሽግ አድርገው ነበር። የደርግ የመጨረሻው የባብቂያው ሳምንት ላይ የአመራር ለውጥ ማድረጋቸውን የመጨረሻው የደርግ የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹሙ ሌ/ጄኔራል አዲስ ተድላ ተናግረዋል። በዚህ ጓድ ፈይሳ ደስታን ከምክትል ፕሬዚዳንትነት አንስተው ወደ ጡረታ በመስደድ ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳንን ተክተዋል። በመቀጠልም የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቦታ ለጓድ ተስፋዬ ዲንቃ በመስጠት እሳቸውን የራሳቸውን ካቢኔ መርጠው እንዲያቀርቡ ተደርገዋል። በመስኮም አጎታቸውን አስራት ወልዴን በመሾም በዛ ልጆቻቸውን ወደ እዛው ጠጋ አድርገዋል።
አይቀሬው ሽሽት እየተቃረበ ሲመጣም መደላደያቸውን ለማመቻቸት አንድ የዙምባቤ ተወካይ መጥቶ መንግስቱን አናግሮቸው ነበር፤ በማለት የመሸሹ ነገርን የሚያሳዩ ምልክቶች ነበሩ እኔም ይህንን ተረድቻለሁ ያሉት ሌ/ጄኔራል አዲስ ተድላ ግን ምንም እራሳቸውን ለማዳን ሳይችሉ 30 ዓመታትን በአዲስ አበባ የጣሊያን ኤምባሲ ተጠልለው ቆይተዋል፤ ከዚህ አንጻር አውቀው ነበር የሚያስብል ነገር አልተገኘባቸውም።
ሌፍተናንት ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ “አብዮቱና ትዝታዬ” በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደሚተርኩት ግንቦት 10 ቀን 1983 ዓ.ም ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም በመኖሪያ ቤታቸው ለከፍተኛ ባለስልጣኖቻቸው የእራት ግብዣ አደረጉ::
ግብዣው ሲጠናቀቅ ፕሬዚዳንቱ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ሁሉንም ተጋባዥ እንግዶች በራፋቸው ላይ በመሆን አንድ በአንድ እየጨበጡ ሸኙዋቸው። ግንቦት 12 ቀን 1983 ዓ.ም ፕሬዚዳንት መንግስቱ መሉውን ቀን የተለያዩ ወረቀቶችን ቢሯቸው ውስጥ ሲቀዱ ዋሉ:: አመሻሽ ላይ ወደ ዘመቻ መምሪያ በማምራት ለከፍተኛ የጦር አዛዦቻቸው ንግግር አደረጉ።
ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉት ክልሎች በተለይም በትግራይና አማራ የጦርና የሲቪል አመራሮች የተጀመረው የሽሽት ነገር ዋናው ጋርም ደርሶ ግንቦት 13 1983 ዓ.ም የወቅቱ የደርግ ሊቀመንበርና የሀገሪቱ ፕሬዛዳንት ጓድ መንግስቱ ሃ/ማሪያም የደርግን ሽሽት አሳርገውታል።
ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን ወደ ኬንያ ለመሄድ አውሮፕላን እንዲዘጋጀላቸው አዘዙ:: የጉዞ ምክንያታ ቸውም ወደ ብላቴ ማሰልጠኛ በመጓዝ ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ ያሉ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን እጎበኛለሁ የሚል ነበር:: ስለዚህ አውሮፕላኗ ከብላቴ ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ የሚበቃ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ::
ግንቦት 13 ቀን 1983 ከቀኑ 6 ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ሬዲዮ ጣቢያ ስርጭት “ጦርነቱ ያስከተለውን ሁኔታ እንዲለወጥ በልዩ ልዩ ወገኖች በልዩ ልዩ መልክ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል:: ሆኖም ችግሩ አልተቃለለም:: ስለዚህ ደም መፋሰስ እንዲቆም፣ ስምምነት እንዲሰፍን በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም ከስልጣን መውረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም በዛሬው ዕለት ከስልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ውጪ ሄደዋል:: ፕሬዚዳንቱ ከስልጣን በመውረድ ሀገር ለቀው በመሄዳቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ሌፍተናንት ጀኔራል ተስፋዬ ወልደ ኪዳን ተክተው ይሰራሉ::” የሚል እወጃን አስደመጠ::
በሌላ በኩል ግንቦት 19 ቀን 1983 በእንግሊዟ ዋና ከተማ ሎንዶን የኢሕዲሪ መንግሥት ተወካዮች ከኢሕአዴግ ፣ ከሕዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ሻዕቢያ)፣ ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦ.ነ.ግ) እና ከተለያዩ ፓርቲዎች ጋር በአሜሪካ መንግሥት አማካይነት ድርድር ተቀምጠው ነበር:: አደራዳሪው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ምክትል ሚኒስትር ሄርማን ኮኸን ነበሩ:: ከኢሕዲሪ መንግሥት ተወካዮች ጋር ለመደራደር ሎንዶን የተገኙት ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊ ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦ.ነ.ግ) ምክትል ዋና ጸሐፊ አቶ ሌንጮ ለታና የህዝባዊ ግንባር ሓርነት ኤርትራ (ህ.ግ.ሓ.ኤ) ዋና ፀሐፊ አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ነበሩ::
ማንንም ማትረፍ ያልቻለው የደርግ የተስፋዬዎች መንግስት
ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያም የሀገሪቱን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ጓድ ተስፋዬ ዲንቃን አድርገዋ፤ ም/ፕሬዝዳንታቸውን ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳንን ወክለው፤ የውጭ ጉዳዪን (የደህንነቱን ነገር) ለኮለኔል ተስፋዬ ወ/ስላሴ ትተው ተስፋ የሌለውን ደርግ ለተስፋዬዎቹ አስረክበው ለአንድ ሳምንት ሀገሪቱን በግራም በቀኝም ተስፋዬ በማድረግ ከደርግ ወደ “የተስፋዬዎቹ መንግስት” አሸጋግረውት እንደ ነበር ታሪክ የመዘገበው ሃቅ ነው። ቀድሞውኑ በፈረሰ የመንግስት ጦር ላይ ምንም አይነት ውጤት እንደማይመጣ የተረዱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ጄኔራል ተስፋዬ ጦሩ በተለይም በአዲስ አበባ ዙሪያ ምንም መከላከል እንዳያደርግ አሳስበዋል።
እዚህ ጋር ሁሉ ነገር ካከተመና ብዙ ዘመናት ካለፈ በኃላ በህይወት የተረፉት ሌ/ጄኔራል አዲስ ተድላን ጨምሮ ብዙዎች በተለያዩ ሚዲያዎችና መጽሐፎቻቸው እራሳቸውን በህይወት ከሌለው ደርግ አንጻር የሚገልጹበት መንገድ እጅግ ለሰሚም ታሪክን ለሚያውቅም አስተዛዛቢ ነው። ብዙዎቹ እራሳቸውን ንጽህና የተለየ አስተዋይ አድርገዋል። ይህ ስህተት እየታረመ ባለመሄዱ ሰፊውና ጨዋ የኢትይዮጵያ ህዝብ ዝምታን ስለመረጠ ይህ ባህል በእኛም ዘመን ደርሶ ለት.ህ.ነ.ግ መራሹ ኢ.ህ.አ.ዴ.ግ ምንጣፍ ሲጎትት የነበረ በብሄሩ ላይና በሌላ ብሄር ላይ ጥላቻን ሲነዛ ጥላቻን ሲያስግት የነበረ ሁሉ ዛሬ በግርግር ቤተ-መንግስት በገባው በኦሮሙማ መንግስት ቀሚስ ስር ተደብቆ ቀድሞ ከገጠር አምጥቶ አዲስ አበባ ያስቀመጠውን ትህነግን ሲኮንን ያልነበረውን ሆንኩ ሲል ተስምን ታዝበናል።
ደርግ ውስጥ ውስጡን እየተገዘገዘ በግንባር ከፍተኛ ሽንፈትን እየገጠመው ከህዝቡም ልብ እየራቀ ባለበት ወቅት እንኮን ዋና ዋና የጦሩ ሃይል አዛዥዎች እና ባለስልጣናት እለት እለት ከሚደረግ የቤተ-መንግስት ግብዥና ድግስ መውጣታ ተስኖቸው ታይቷል። መሪያቸውን ጓድ መንግስቱ ኃ/ማሪያምን በማሞገስና በማድነቅ የቃላት መረጣ ላይ መክረማቸውን በተለያዩ መንገዶች ተገልጽዋል። ለአብነትም አብረሃም በየነ “Ethiopian Uprising” በተሰኘ ድህረገፅ ላይ የመንግስቱ ኃይለማርያም የመጨረሻ ቀኖች በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሁፉ ላይ የመንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የተፈጸመውን ስንገመግመው እስከ አሁን በኢትዮጵያ ታሪክ የሃገሪቱ መሪዎች አሳይተውት የማያውቁት ክህደት እንደሆነ እንረዳዋለን ብሏል። የክህደቱ መፈጸም ብቻ ሳይሆን በአሁኑ ወቅት የደርግ ደጋፊዎች ይህንን አሳዛኝ ታሪክ በፈጠራ ተረት ተረት ለመቀየር የሚያደርጉት ጥረት ደግሞ የበለጠ የሚያሳዝን ነው። ምንም እንኳን መንግሥቱን “እንደ ቆራጥ መሪ ፣ እንደ አፄ ዮሐንስ፣ እንደ አፄ ቴዎድሮስ” ለመሳል ትልቅ ጥረት ቢደረግም በምንም መስፈርት መንግሥቱ ከከሃዲነት የሚያልፍ ስም ሊኖረው አይችልምም በማለት ይሞግታል።
የዓሣ ግማቱ ከአናቱ እንዲሉ ይህ ንቅዘት ምንም እንኳን በሁሉም የመንግሥት መዋቅሮች ውስጥ ቢከሰትም የመንግሥቱ ቤተሰባዊ ስብስብ ውስጥ ጎልቶ ይታይ ነበር። በተለይ የመጨረሻው ሰዓት በደረሰ ጊዜ ተራ የሆነ ንግድ ውስጥ እንደተገባ አብረሃም በየነ በተለያዩ መረጃዎች በማንሳት ሞግቷል። ይህ የቤተሰብ ኃይል ስለ ሃገር ደህንነት ከመደራደር ይልቅ ለግል የሚገኝ ንዋይን ማካበት ላይ አተኩሮ ነበር። ውሸት ቢጋነን እውነት አይሆንምና ዛሬ እውነቱ አደባባይ ላይ ሲቀርብ ለዛ መልስ ከመስጠት አሁንም እንደበፊቱ ምክንያት እየተፈለገ በየቃለ መጠይቁና በሚጻፉ መጽሐፍት ከእውነት ሊሸሸ ይሞከራል። የመጨረሻው ሃገራዊ ክህደት በጣት የሚቆጠሩ ቤተሰባዊ አባላት ባሉት ቡድን ብቻ በድብቅ የተፈጸመ ነበር። ለዚህ ማስረጃው ብዙዎቹ የደርግ ባለሥልጣናት የመንግሥቱን ፕሮፖጋንዳ አምነው “ቆራጡ መሪያችን ጥለውን አይሸሹም” በሚል መፈክር ሥር በመሰባሰባቸው እየተንጋጉ በትህነግ እጅ ላይ የወደቁት እና ለእስር ተዳርገው ከእድሜ ልክ እስከ ሞት የፍርድ ቅጣት የተላለፈባቸው። መንግስቱ ኃ/ማሪያም ውክልና የሰጦቸው የሪፐብሊኩ ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን፤ ይሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ (የደህንነት ሃላፊው) ተስፋዬ ወ/ስላሴ ከዚሁ ቅጣት ማምለጥ አልቻሉም።
በሰፈሩት ቁና መሰፈር አይቀርምና ደርግ በስልጣን ዘመኑ አንዳች የፖለቲካ ለውጥ አድጎ ወጣቱን ከእልቂት ምሁሩን ከስደት እንዲያድን ከማድረግ ይልቅ በየመድረኩ መሪያቸውን ሲሞካቹ የጦር መሳሪያቸውን መለኮታዊ ሃይል አድርገው ሲቆጥሩ ለነበሩ ጉምቱ የጦር አዛዥና ባለስልጣናት መጨረሻ የእድሜያቸውን ግማሽ ዘመን በእስር እንዲያሳልፉ አድርጎቸዋል። መሪያቸውንም እራሳቸውን በትክክል በማይመሩበት እና ማንም በማያምኑበት ሀገረ-ዙባቤይ ቀሪ ህይወታቸውን የመምራት ግዴታ ውስጥ ጥሏቸዋል።
የኦነግ-ኦሮሙማ መንግስት ሰሞነኛ ሁኔታ፡ የብረሃኑዎች መንግስት
ንጉሱ .ቀ.ኃ ስላሴም የኤርትራ ገንጣይ ንቅናቄዎችን ለማስቆም በሄዱበት የጦር ስልት በተመሳሳይ ደርግም ሄዶበታል። በዚህ ከኤ.ህ.ን.ግ ጋር ህብረት ለፈጠረው የት.ህ.ነ.ግ ሃይል ደርግ ያንን የሚያክል ግዙፍ ጦር አስበሎቶት እራሱን ለማዳን ከሀገር እንደኮበለለ በቀደመው ርዕሳችን አይተናል። የኦሮሙማ መንግስት ከቀድሞ የደርግ የመጨረሻ ሳምንት ጋር (ግንቦት 13-20; 1983 ዓም) በተለምዶ የተስፋዬዎች መንግስት ከተባለው ጋር ምን አገናኘው? ኮለኔል አብይ አህመድ ከኮለኔል መንግስቱ ጋር ሀገሪቱን ለመምራት በሄደበትና ብሚሄድበት መንግስት ምን አይነት ተመሳስሎሽን እየፈጠሩና እየደጋገመ ሄደ? የሚለውን ጥቂት የሚባሉ ጊዜያት በቀሩት የኦሮሙማ መንግስት የስልጣን ዘመን ላይ ሆነ ይህንን ለታሪክ የሚሆን ሃሳብን እናነሳለን።
በተመሳሳይ የታሪክ መስመር እና እጥፋት ላይ በተገኛው የኦነግ ኦሮሙማ መንግስት ርዕሳችን ላይ ለዚህኛ መንግስት የመውደቅ ማዘንበልና ማንጋደድ ምክንያት ከሆኑትን ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ፦ ሁሉንም የህዝብ ጥያቄ በሃልና በማደናገር ለማፈንና ለመፍታት መሞከሩ፤ ከደርግ የምስራቁ አለም ርዕዮትና ጥገኝነት የተፋታው ይህኛው የኦሮሙማ መንግስት በአረብ ሀገራት ርዕዮት አልባ እና መርህ አልባ ጥገኝነት ላይ የተመሰረተ መሆኑ፤ ኢትዮጵያዊነትን የተላበሰ የመንግስት አሰራርና መዋቅርን ከመከተል ይልቅ በፍጽም የአማራ ብሄር ጥላቻና በቀል ላይ መመስረቱና ሁሉም የእኛ ነው በሚል የመንደር ፈሊጥ ላይ መቸንከሩ፤ ከምዕራቡ አለም ጋር የተፋታ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ማራመዱ ይገኝበታል።
ሁሉንም የህዝብ ጥያቄ በሃልና በማደናገር ለማፈንና ለመፍታት መሞከርና ያስከፈለው ዋጋ
የአማራው ሃይል ትጥቅ ይፈታል አይፈታም የሚለው ወሬ በኦሮሙማው ጓዳና በተላላኪው ብአዴን በተለያየ መንገድ መገለጽ የጀመረው ባለፈው ዓመት ሚያዚያ 2015 ዓ.ም ነበር። የኦሮሙማው መንግስት እና ተላልኪ አክራሪ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የአማራ ልዩ ሃይል ይበተናል ወይም በተሰጡት አማራጭች ይሰማራል፤ ሁሉም በክልሉ የታጠቁ ሃይሎች ትጥቃቸውን ያወርዳሉ ሲሉ የወቅቱ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ይልቃል ከፋለ ይህን ለማስተባበል እና ጉዳዩን በድብቅ እንዲከናወን ቢጥሩም ሳይሳካላቸው ቀርቷል፤ እሳቸውንም ለሽሽት ዳርጎ ለኦሮሙማ መንግስት ውስጥ የሳሎን ውሻ ሆነዋል፤ አይናገሩ መድረክ የላቸው ሲሰጣቸው ይበላሉ ተኙ ሲሎቸው በሚተኙበት የሀገር ውስጥ ስደት አዲስ አበባ ይገኛሉ።
በዚሁ በሚያዚያ ወር 2016 የኦሮሙማው መንግስት በአማራ ክልል ያለውን ልዩ ሃይል ከማፍረስና በገንዘቡ እና ከትህነግ ጋር በተደረገው ጦርነት በደሙ የያዘውን ማንኛውንም ትጥቅ ለማስወረድ እየተደረገ ካለው ስራ ጋር የሚመጋገብ ደግሞ በመሀል ሀገር አዲስ አበባ አማራው ላይ ያተኮረ ዘመቻ ተከፍቶም ነበር።
ከእነዚህ ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች መካከል የጅምላ እስር፣ ማፈናቀል እና ወደ መዲናዋ አዲስ አበባ እንዳይገቡ መከልከል ይገኝበታል። በአዲስ አበባ የአማራ ብሄር ተወላጅ የሆኑ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና ባለሃብቶችን በሰፊ የማሰር ስራ ተከናውኖል። ከዚህ ጎን ለጎን በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያ አሁን ከአዲስ አበባ ተገምሶ ለኦሮሚያ ክልል ከተማ ሸገር ሲቲ በተሰጠው ቦታ ላይ ይኖሩ የነበሩ ከአምስት መቶ ሺህ (500,000) በላይ የአማራ ብሄር ተወላጆችንና ሌሎችን ቤታቸን በላያቸው ላይ በማፍረስ ንብረታቸውን በማውደም እንዲፈናቀሉና ለከፋ ችግርና ጉስቁልና እንዲዳረጉ አድርገዋል። በዚሁ ሰሞን በተለያየ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያቶች ወደ መዲናቸው አዲስ አበባ የሚገቡ የአማራ ብሄር ተወላጆች በኦሮሚያ ክልል ድንበር ከተሞች ላይ እየጠበቁ እንዳይገቡ ከማድረግም በላይ ድብደባና እስር ዳርገዋቸዋል። በዚህም ዜጎች በሀገራቸው ዉስጥ በነፃነት የመኖር እና የመንቀሳቀስ ሰብዓዊ መብቶቻቸውን በአደባባይ እንዲጣስ፡ እንዲዋረድ አድርገዋል። የማህበረሰቡን ሃይማኖታዊና ሞራላዊ ክብርን በሚያዋርድ መልኩ የሃይማኖት አባቶችን ሳይቀር በጥፊ በመታት በእግር በመርገጥ ለኢትዮጵያና ለአለም ህዝብ በአማራው ብሄር ላይ ያላቸውን ጥላቻና በቀል በገሃድ አሳይተዋል።
በዚህ መርካት ያልቻለው የኦሮሙማ መንግስት በድብቅ ሲወያይበት የነበረውንና ቀድሞ የአማራ ጀግኖች ጆሮ የደረሰው ትጥቅ የማስፈታት ዘመቻ ጅማሮ ገሃድ መውጣት ሲጀምር ከሀገር ውስጥ እስከ ውጭ ያሉ የብሄሩ ተወላጆች አንድ አቋም በመያዝ የሚመጣውን ለመጋፈጥ ወሰኑ፡።
መጋቢት 2015 ዓ.ም ከዓለም አቀፍ የአማራ ንቅናቄ በተሰጠ መግለጫ የአማራውን ትጥቅ መፍታት በተለያዩ ግልጽ በሆኑ ምክንያቶች ተቃውመዋል፤ በተለይም የአማራ ፋኖን ትጥቅ ለማስፈታት እና የአማራ ልዩ ኃይልን ለማፍረስ የተነሳበትም ጊዜ፦ትህነግ ከነሙሉ ትጥቁ ተጨማሪ ሠራዊት እያሰለጠነ ባለበት፣ የኦነግ ኦሮሙማ መንግስት አማራውን ፈጽሞ ለማጥፋት አቅደው እና ሰንደው በተነሱበት፣ የሱዳን የጦር ሀይል የኢትዮጵያ እና የአማራ ክልልን ዘልቆ በወረረበት፣ አማራውን በኦሮሚያ ክልል መጨፍጨፉ እና ማሳደዱ በቀጠለበት፣ አማራውን አዲስ አበባ እንዳይገባ እንዲውያም ከአዲስ አበባ ማፈናቀሉ በተፋፋመበት፣ ከ25 ሽህ በላይ የፋኖ፣ እና የአማራ ህሩያን በታሰሩበት እና በታፈኑበት፣ ዓለም አቀፍ መንግስታት በአማራ ህዝብ ላይ የሚካሄደውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ጆሮ-ዳባ ልበስ ባሉበት እና የአማራ ህዝብ በታሪኩ ከፍተኛ የህልውና አደጋ እና አጣብቂኝ በገጠመው ወቅት ነው።
የኦነግ ኦሮሙማው መንግስት በእነ ብረሃኑዎቹ (ብረሃኑ ጁላ እና ብረሃኑ በቀለ) በኩል እየፎከረ በተላላኪው እና በባንዳው ብአዴን እያደናገረ ቢቆይም አማራን ማጥፋት የቆመለት አለማ ነው እና ቀኑ ደርሶ ትጥቅ የማስፈታት እምጃዎችን በልዩ ሃይሉ በኩል ጀምሮት ነበር።
በፍራቻና በጥላቻ ላይ መንግስታቸውን የገነቡት የኦሮሙማ ሃይሎች በእነ ምርኮኛው ብረሃኑ ጁላ እና ለዘረፈው የህዝብ ሃብት እስከ መጨረሻው በታማኝነት ለማገልገል ቃል የገባው ጄኔራል ብረሃኑ በቀልና አበባው ታደሰ የአማራን ህዝብ በመሀል ሀገር በሚደረግ ግድያና ማፈናቀል አንገት ማስደፋት እንደማይቻል በማመን የአማራ ብሄር ባህሉ ባልሆነው ቋንቋ በመጠቀም እንኮን ትጥቁን ሌላውንም ነገሩን እንፈታለን ብለው ወደ ክልሉ ገቡ። መግባት ግን የፈለጉትን ሰርቶ እንደመውጣት ቀላል ስላሆነ መግባት ግን የአዲስ አበባን መሬት እንከሚበቃው ለክቶ መውሰድ ቀላል ስላልሆነ ይልቁኑ ይባስ ያስታጥቀው ያዘ።
ደርግ በግዙፉነቱ በምስራቅ አፍሪካ ተስተካካይ አልተገኘለትም በተባለው የጦር ሃይላቸው በሰማይ፤ በምድርና በባህር ጠምደው በተሸነፉበት የጦር ስልት በሞያና በማዕረግ የሚመስሏቸው የኦሮሙማው መንግስት መሪ አብይ አህመድ አሊ የአማራን ፋኖ ገጥመው በኢትዮጵያ ተሰምቶ በማይታወቅ የድሮን ጥቃትንም ጨምረውበት ያለ እውነተኛ አላማና ወኔ ለበቀል ያሰማሩት ሰራዊታቸውን በደፈጣ ውጊያ አስለቅመው ትጥቃቸውን አራግፈው ፊታቸውን ወደ መጡበት እንዲያዞሩ አስደርገዋቸዋል። ፎክሮ የሄደ ሁሉ ለምኖ መመልስ ተስኖታል። ልክ ዶ/ር ወርቁ ደረደ እንዳሉት ሁሉ የኦነግ ኦሮሙማውን የገጠመው ጦር (የአማራ አርበኛ ፋኖ) የሽምቅ የጎሬላ ስልትን በሚገባ የተካነ ነው። በደፈጣ ውጊያ ላይ ያለን ሃይል በመደበኛና በፊት ለፊት በሚዋጋ ጦር ገጥመውታል። የሽምቅ ውጊያን በመደበኛ የጦር ስልት መግጠም አግባብነት አልነበረውም ብለው እንደሚያምኑት ዶ/ር ወርቁ ደረደ ሁሉ የኦሮሙማ መንግስት ይህንን የመገምገም እድል እንኮን ማግኘት እንዲሳነው ተደርጎል። ከዚህ ይልቅ በቂ የግንባር የጦርነት ልምድ የሌለው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ሃይል ሁሉ እንዲገባ ተደርጎል፤ ወታደርነት የወታደር ዩኒፎርምን ወጣጥሮ መልበስና ሹሩባ መሰራት ባለመሆኑ የዝግጅታቸውን ያህል አግኝተዋል።
ዋናው ትግል ጎጃም ላይ ነው የሚጠናቀቀው እንዳለው አርበኛ ፋኖ ዘመነ ካሴ፤ አሁን ዋናው ትግል በጎንደር፡ በጎጃም፡ በወሎ አድርጎ ሸዋ ላይ እየተጠናቀቀ ነው። በኢትዮጵያ ታሪክ ትግል በሰሜኑ ተጀምሮ እዛው በሰሜኑ እንደሚያልቀው ሁሉ ይህም ታሪክ እዛው እያለቀ ነው። ሸዋ (አዲስ አበባ) ወትሮም የነገስታት መቀመጫ ነው እንጂ የጦር ሜዳ ሆኖም አያውቅም።
ቀድሞውኑ በባንዳው ብአዴን፡ በሁለት ምላሱ አብይ አህመድ፤ በምርኮኛው ብረሃኑ ጁላ በዘመቻ መሪ ጄኔራል ብረሃኑ በቀለ ንግግር መደናገር ያልቻለው የአማራው ፋኖና ልዩ ሃይል ማደናገሪያው እስኪያልቅ ጠብቆቸው ነው እብሪታቸውን ለማስታገስና እራሱን ለማቆየት እዚህ የህልውና ትግል ውስጥ የገባው። አሁን የአማራ ፋኖ የህልውና ትግሉ የመጨረሻው የብስራት ችቦ ለማየት ለጓጓውና እረፋት ላጣው ሰፊ የኢትዮጵያ ህዝብ ወደ ብስራት ዜና እየተቃረበ ሲመጣ በሽንፈት ላይ ሽንፈት የተደራረበበትና የህልውናውን ድል ዜና መስማቱ እንደማይቀር የተረዳው የኦሮሙማ መንግስት አሁን ጨዋ ጨዋ ልክ ልክ ያጫውተው ይዟል፤ ቋንቋውንም አስተካክሎ ከጽንፈኛ ወደ እውነተኛ ስሙ ፋኖ በማለት በጥላቻ ዜናና ፕሮግራሞቻቸው በሚያደነቁሩን የመንግስት ልሳን ሳይቀር ሰምተናል። አማራን ያጓጓሉ ብለው ባሰቦቸው ጥያቄዎች እራሳቸው ጠያቂ እራሳቸው መላሽ በሆኑበት የባህርዳር ሰሞነኛ መድረክ፤ ህገ መንግስትን ማሻሻል፤ የተዛባ ትርክት ማረቅና ማስተካከል፤ የወሰን እና ማንነት ጉዳይ፤ ፍትሃዊ የኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ውክልና ጉዳይ፤ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ የአማራ ህዝብ ጉዳይ፤ የአዲስ አበባ የመልካም አስተዳደር እና አድሏዊ አሰራር ችግር አለመቀረፉ እና በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ንጹሃን የአማራ ተወላጆች ለሚደርስባቸው ግድያ እና መፈናቀል ተጠያቂነት አለማስፈን ጉዳይ አንስተዋል።
እዚህ ጋር የኦሮሙማ መንግስት እየሰራ ያለውን የማደናገር ተመሳሳይ ባህሪውን ትተን አልፎ አልፎም ቢሆን በንጽህና ለምን ጉዳዩ በውይይት አይፈታም፡ የአማራ ፋኖ ጥያቄዎቹን ለምን መጀመሪያ ለፌዴራል መንግስቱ በግልጽ አይቀርቡም ለሚሉ እጅግ የዋሆች ግን ንጽሃን ለሆኑት ወገኖቻችን አንድ እውነተኛ አማራ ባልተወከለበት ሰብሳቢና ተሰብሳቢ የቀረቡት እነዚህን ጥያቄዎች ያዘጋጀው እራሱ የኦሮሙማ መንግስት መሆኑ እያደረገ ያለውን በአደባባይ ከማመንና ለሌሎች ጉዳዩ ላልገባቸው ጥቂቶችም ቢሆኑ የማስረዳት ስራን መስራቱ የኦሮሙማውን መንግስት አለማመስገን ንፉነት ውስጥ መግባት ጥሩ አይደለምና ማመስገን ይገባል፤ የተዘረፈብህን እቃ ዝርዝር ከአንተ በላይ ዘራፊው ሌባው ያውቀዋል ነው ነገሩ።
ስለዚህ የአሮሙማው መንግስት በደንብ ለተከታተለው የመንግስት ልሳን ከሆኑ ሚዲያዎች ላይ አይኑን ለነቀለው እና የመንግስት ድራማ ሰለቸኝ ላለው በተለይ አማራው ብሄርና ሌሎች ሊዋጡ ለተዛተባቸው በግራ በቀኝ እየሆነ ያለውን በድንብ ያስተዋለ ይህ ወቅት ግንቦት 13፡ 1983’ ን ይመስላል። ልክ እንደ ተስፋዬዎች መንግስት ሁሉ የአንድ ሳምንት የብረሃኑዎች መንግስት እየመጣነው፤ በንቃት መጠበቅና መከታተል ለጠላትም ለወዳጅም ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ ነው። ኢህዴግ ሊወድቅ አካባቢ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአዲስ አበባ ማኪያቶ እየጠጡና አይን ያዝ ያዝ ሲያደርግ በድራፍትና ቢራ ላይ ፖለቲካውን ያሰለጠኑትና የሚያስኬዱት ከተሜ ፖለቲከኞቹ “የኢህዴግ መውደቅ አይደለም ስጋታችን እላያችን ላይ እንዳይወድቅ ነው” በማለት እንደሚያፌዙት አይነት ፖለቲካ ሳይሆን የኦነግ ኦሮሙማን በደጁ በቀየው በማይቀበርበት ማንም ላይ በማይፈርስበት መንገድ በምስጥ ተቦርቡሮ እንደሚወድቅ ታዛ እየወደቀ ነው።
የኦሮሙማው መንግስት አወዳደቅ ልክ በግንባር ለህልውናቸው እንደሚዋደቁት እና በንቃት እንደሚከታተሉት ሰፊ የአማራ ህዝብ ሁሉ የአሜሪካና የአውሮፖ ህብረት ዲፕሎማቶች በደንብ ተረድተውታል፤ በዚህም በቀጣይ በሀገሪቱ ስለሚኖራቸው እጣ ፋንታ ለመለየት ከውጭ ሀገር ጀምሮ እስከ መዲናይቱ አዲስ አበባ ድረስ በኢትዮጵያ ቀጣይ ስለሚኖረው የሽግግር መንግስት በይፋ ከተለያዩ መንግስታዊም መንግስታዊ ካልሆኑት አካላት ጋር መክረዋል። ይህ የታላላቅ ሀገራት አቋም እና ስራ በድብቅ የተደረገ ስላሆነ እራሱ የኦሮሙማው መንግስት መሪ አብይ አህመድን ሳይቀር የጎበኘ ነበር። ባለቤቱን ካልደፈሩ አጥሩን አይነቀንቁ ነውና ይህ መንግስት እየወደቀ ያለ በመሆኑና በቀጣይም በሀገራቸው ግንኙነት ላይ የሚፈጥረው አንዳች ችግር የሌለ በመሆኑ ለአደባባይ ቀድመው አስጥተውታል። ይህንን ጉዳይ ለመሸፈን በብዙ ድራማዎች፡ አትክልቶችና የመንገድ ዳር መብራቶች ላይ የተጠመዱት አብይ አህመድ የማይደበቅ መሆኑን በተረዱት መጠን ባገኙት መድረክ ሁሉ ምንም ከአጀንዳ ጋር ባልተገናኘ አጀንዳ ዘለል በሆነ መንገድ “የሽግግር መንግስት በኢትዮጵያ እስከ ወዲያኛው አይኖርም” ይላል፤ እኛ ደግሞ ከአጀንዳ ውጭ “አልበላሽምን ምን አመጣው” እንላለን። ደርግም እንዲህ ነበር “አንድ ዛፍና አንድ ሰው እስኪቀር እዋጋለሁ” እያለ ያ ሁሉ የደርግ ባለስልጣናት እና የመንግስት ወታደር እንዲሁም ያ ሁሉ በትህነግ ተጨፍጭፎ የተሸጠው ዛፍ (ጫካ) እያለ ከ40 ሚሊዮን የሚልቅ ህዝብ በሀገሪቱ እያለ ጥለው የኮበለሉት።
ሌ/ኮሎኔል ፍሥሐ ደስታ በመጽሐፋቸው እና ሌሎች እንደገለጽት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም የግል ውሳኔያቸውን በራሳቸው ይዘው እስከመጨረሻው ጊዜ ለሎሌዎቻቸው የቤተ-መንግስቱን ግብዥ ከነ ሙሉ ፈገግታው ሳያቋርጡባቸው እስመጨረሻው ዘልቀዋል፤ የአሁኑም ኮሎኔል አብይ አህመድም እንደ’ዛው ናቸው በዘመን ልዩነት የግብዥው ዓይነትና ሁኔታ ከመለያየቱ ውጭ ለአሁኑ የኦሮሙማ ሎሌ ሚኒስትሮችና በስመ ተቃዋሚ የተለጠፉ ሆድ አደር የኢዜማ እና የአብን መሪዎች ድግሱ አልተቋረጠባቸውም። የአሁኖቹ ከደርግ ጄኔራሎችና ባለስልጣናት ትምህርት ወስደው በደጉ ዘመን እጃቸው የገባውን የውጭ ሀገራት ቪዛ ተጠቅመው እንዳያመልጡ ልክ የደርጉ መንግስት መሪ እንዳመለጡትና ወኪላቸው ጄኔራል ተስፋዬ ወ/ኪዳን ለጄኔራል አዲስ ተድላ ብቻ በማሳወቅ ሌሎቹን የጦር አዛዥዎችና የሲቪል ባለስልጣናትን ደብቀው ኤምባሲ ለኤምባሲ ተራርጠው ብቸኛ ፍቃድ ባገኙበት የኢጣሊያን ኤምባሲ እራሳቸውንና ወዳጃቸውን ከእስር እንዳዳኑበት፤ ሌሎቹ ከሀገር እንዳይወጡ አከላክለዋል ተብለው ከታሙበት በላይ የኦሮሙማ መሪ አብይ አህመድ እየተካሄደ ያለው ይበልጣል፤ አፍ የሚያሲዝ ነው። የኦሮሙማው መንግስት መሪ የሎሎዎችን (የሚኒስትሮችን) ፖስፖርት በብቸኝነት መቆጣጠር ብቻ ሳይሆን ማንም ዜጋ ወደ ውጭ ሀገራት መሄድና መከልከልን ሙሉ ስልጣን ካለው ፍርድ ቤት ነጥቀው ፖለቲካው ተቋም ለሆነው ለብሄራዊ የደህንነት መስሪያ ቤቱ በአዋጅ አስረክበውታል፤ አሁን እንኮን ባለስልጣናቱ በኦሮሙማ በበጎ አይን የማይታይ ሁሉ ከአለም አቀፍ በረራ ሊከለከል ይችላል።
በጣሊያን ኤምባሲ የተጠለሉት የደርግ ባለስልጣናት ወደ’ዛ ከመሄዳቸው በፊት የሌሎች ሀገራትን አሜሪካን ጨምሮ ኤምባሲዎች ተማጽነው እንደነበር በተለያዩ አካላት ተገልጾ ነበር። ጣሊያን ኤምባሲ ለመሄድ ከመወሰናቸው በፊት በአዲስ አበባ የአሜሪካን ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚ ለነበረው ሮበርት ሁዴክ ጥገኝነት እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርበው እንደነበር ፖል ሄንዝ የተባሉት የፀጥታ አማካሪና ፖለቲካ ተንታኝ ተናግረዋል። ነገር ግን ጉዳይ ፈፃሚው አዲስ ከሚመጣው መንግሥት ጋር ያቃቅረኛል በሚል ጥያቄውን ውድቅ እንዳደረገባቸው እኚሁ ሰው አስረድተዋል። ጄኔራል አዲስ ተድላ ከ30 ዓመት የጣሊያን ኤምባሲ ቆይታቸው በኃላ በአንድ የሀገር ውስጥ ቴሌቪዥን (ኢሳት) እንተናገሩት አሜሪካንን ጨምሮ ወደ ሌሎች ኢምባሲዎች ለመጠለል ያቀረቡት ጥያቄ በጎ ምላሽ አላገኘም።
ፖል ሄንዝ እንደገለጽውና በደርግ የፖለቲካ አካሄድ ባህሪ አንጽር የተነሳ ማንም የደርግ ባለስልጣን መጠለያ እንደተከለከለ መረዳት ተችሏሎ አሁን የአማራው የህልውና ትግል በድል መጠናቀቅና ለቀሪው የሀገሪቱ ዜጋ የብረሃን ጮራ በሚፈነጥቅበት በጣም ቅር ጊዜያት እነዚህ በዘር ማጽዳትና ማጥፋት ወንጀል ለረዥም ዓመታት ለተነከሩት የኦሮሙማ ባለስልጣናት እና ሎሌዎቻቸው የትኛ የኤምባሲ ቅጥር ግቢ ሊያስጠልላቸው እንደሚገባና እንደማይገባ ሳይታለም የተፈታ ነው። ገና ከአሁኑ ስለ መጪው የሽግግር መንግስት አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ የተለያዩ ምክሮችን ለያዘው የአሜሪካና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ይህ የኦሮሙማ መንግስት የጦር መሪዎችንም ይሁን ባለስጣናት የመጠለያው ቦታ የመስጠቱን ነገር የማይቻል መሆኑን ከወዲሁ የታወቀ ሆኖዓል።
ታዲያ በከፍተኛ የጦር አዛዥዎች በእነ ብረሃኑዎች ላይ ተስፋውን ያደርገው የኦሮሙማው መንግስት እንደ ጨዋ ቁጭ ብሎ የመደራደር እድሉስ አለ ወይ? ቀድሞውኑ ለተፈታው የኦሮሙማ መንግስት ስልጣን ወታደሮች ተዋጉ አትዋጉ የሚል ትዕዛዝ የሚሰጥበት ዘመንስ እንቁጠረው ብንል ስንት ቀን ነው? ስንት ሳምንት ነው? ስንት ወር ነው? አሁን በየጊዜ በአራቱም የአማራ ፋኖ ተጋድሎ ቦታዎች በየጊዜ የሚሰማውስ ዜና ሁሉም የመንግስት ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሰ ሁሉ የኦሮሙማ መንግስት ጠባቂ ነው ወይ ብለን በድፍረት የምንናገርበት ደረጃ ላይ ነን ወይ? የትኛው የመንግስት ከፍተኛ የጦር አዛዥ ጄኔራል ነው በስሩ ያሉትን መሪዎች ኮሎኔሎች፤ ሌተናል ኮሎኔሎች፤ ሻለቃዎች እና ሻምበሎች እስከ መጨረሻ ከእሱ ጎን እንዳሉ መናገር የሚችለው? የአማራው ሚሊሻና አድማ ብተናውማ ድሮም በስህተት ነበር መለጠፉ፤ አሁን የሰሞኑ የግንባር ዜናዎች ግማሽ ያህሉ የእነሱን ፋኖ መቀላቀል ሆኖዓል። አሁን ለነገሩ እራሱን ለማዳን እና የትግሉን ጊዜ በቀናትም ይሁን በሳምንታት ለማሳጣር የሚረዳ ካልሆነ በስተቀር ፋኖ የሀገሪቱ እውቅ የሽምቅ ውጊያ መሐንዲስ የሆኑትን ጄኔራል ተፈራ ማሞን ጨምሮ በርካታ የጦር ልምድ ያላቸው መሪዎችን ፈጥሮዓል።
በ1983 ዓ.ም እንደ ት.ህ.ነ.ግ እና ኤ.ህ.ነ.ግ ወታደሮች ከመቀሌ እና አስመራ ተነስተው አዲስ አበባ ለመድረስ በፈጀባቸው ርቀት ያህል የሚለካ የጊዜ ሰሌዳን ለአማራ ፋኖዎች እንለካላቸው ብንል መነሻውን የት ነው የምናደርገው? ጎንደር፤ ጎጃም፤ ወሎ፤ ሸዋ ነው ወይስ አዲስ አበባ ቦሌ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ። የዚህን ያህል ርቀት በሚመጣ ወታደር የሚለካ ውጤትስ ዛሬ በተደረሰበት የትግል ምዕራፍ እየተጠበቀ ነው ወይ?
የአማራው የመጨረሻው የግፍ ጽዋ ሞልቶ በጀግናው ኮሎኔል ደመቀ ሐምሌ 5, 2008 ዓ.ም ላይ የነፃነት ትግል አብሪ ጥይት ጎንደር ላይ ሲተኩስ እነ ወጣት ናሁሰናይ የጎንደርን ወጣት እያደራጁ ሕዝባዊ እምቢተኝነቱን ያቀጣጥሉትን ትግል አብቦና አፍርቶ ባለፈው አዲስ አበባ ላይ የለኮሱት የድል ብስራት ዜና እዚህ ጋር በአባሪነት ማንሳቱና ማስታወሱ ተገቢ ነው። ታድያ ይህ ጀግና ልክ ጎንደር እንደ ተለኮሰችው አብሪ ጥይት መሃል አዲስ አበባ ላይ አዲስ የነፃነት ችቦ ለኩሶ ለተሰዋለት የአማራ የነጻነት ትግል፤ ሌላ ችቦ ሌላ ዜና አዲስ አበባ ላይ ይጠበቃል ወይ? የሚጠብቅ አለ ወይ?።
በመሆኑም ከጎንደር አዲስ አበባ ከ700 ኪሜ በላይ የሚርቀውን መንገድ በሻለቃ ፋኖ ናሁሰናይ አንዳርጌ እና አርበኛ ፋኖ አቤኔዘር ስለተጠናቀቀ የአማራ ፋኖ በጎንድር፤ የአማራ ፋኖ በጎጃም፤ የአማራ ፋኖ በወሎም ይሁን የአማራ ፋኖ በሸዋ አዲስ አበባ ለመድረስ በኪሎ ሜትር የሚለካና የሚሄደው መንገድ የለም።
የአማራ ፋኖ በአዲስ አበባ የሚባል ስም መስጠት ስላልተፈለገ ነው እንጂ ፋኖ በአዲስ አበባ ላይ አዲስ ምዕራፍና ታሪክ በጀግናው በሻለቃ ፋኖ ናሁሰናይ አንዳርጌና አርበኛ ፋኖ አቤኔዘር ሚያዝያ 4, 2016 ጀምሯል። ስለዚህ አዲስ በአዲስ አበባ የሚጀመር የለም፤ የተጀመረ ነገር እንደገና አይጀመርም። ውጤት ነው የሚሰማው እንጂ።
የእነ ጄኔራል ብረሃኑ ጁላ፤ ጄኔራል ብረሃኑ በቀል፤ ጄኔራል መሐመድ ተሰማ እና ጄኔራል አበባው ታደሰ መሰል ከሆኑ ከደርጎቹ ጄኔራሎች አንጻር የእነሱን መንገድ ይከተሉ እንደሆነ ባናውቅም ሀገሪቱ እራሱን ለማስመለጥ ወይም ለማደናገር ከሚሞክረው አብይ አህመድ ይልቅ በእነዚህ ጄኔራሎች እጅ ናት፤ እንደ ፈለጉት ባልሆነላቸው ትግል ውስጥም ሆነው ቢሆን እንደ ግመል ሽንት ወደ ኃላ በሚሄደው የወታደር አቋም ላይም ሆነ ቢሆን የኦሮሙማው መንግስት የመጨረሻ እጣ ፋንታ ከሰሜን በሚመጣ ዜና ላይ ብቻ የተመሰረተ ሆኖዓል። በእየለቱ እያሽቆለቆለ በሚመጣው፤ በሚሞተው፤ በሚከዳው፤ በሚሸሹው፤ ውጤት በራቀው፤ ከትህነግ ጋር በአማራ ሃይል ትከሻላይ ሆነው ዛሬ ይህንን ቦታ ያዝን ነገ ያንን ቦታ እንይዛለን በማለት ሰላም ቀጣና ላይ ሆነው ሲያደናግሩ እንደነበሩት አብይ አህመድ ሳይሆን፡ ፈቅ ባላደረጉት ማመን በከበዳቸው የአማራው ጀግነት ላይ ሆነው፤ በፋኖ እጅ ላይ ከፍተኛ የጦር መሳሪያ መግባት፤ ከ110 በላይ የፋኖ ወታደራዊ ማሰልጠኛ መፈጠር እና በርካታ የአማራ ልጆች እየሰለጠኑ መሆናቸውን የግምገማ ውጤታቸው ላይ ሆነውም ቢሆን የሀገሪቱ የአንድ ሳምንት የስልጣን ዘመን በእነ ብረሃኑ ላይ ወድቋል። ቀጣይ የመጨረሻው የትግል ማጠናቀቂያ ላይም የምናገኛቸው “ብረሃን በሌለው የብልጽግና ጉዞ” ውስጥ የእነ ብረሃኑዎች መንግስትን ነው። እጅግ ጥቂት በሆኑ ቀናት ውስጥም ቢሆን ሊሆን የሚችለው እንደዚህ ነው።
የአማራውን የድል ዜና የህልውና ትግል ምዕራፍ ማጠናቀቂያ ግን እስከ ለንደን ሄደው ደርግን እንዳላዳኑት የተስፋዬ መንግስቶች ሁሉ የኦሮሙማው መንግስት የሚያድነው ድርድርም፤ ምክክርም፤ ሽግግርም የለም።
ድል ለአማራው
ድል ለኢትዮጵያ
ሐምሌ 2016
__
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com
Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ






