Homeአበይት ዜናከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ወቅታዊ የአማራ ህልውና ትግልን አስመልክቶ የተሰጠ የአቋም መግለጫ   

ከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ወቅታዊ የአማራ ህልውና ትግልን አስመልክቶ የተሰጠ የአቋም መግለጫ   

Advertisement
World Wide Travel Group
ከዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ወቅታዊ የአማራ ህልውና ትግልን አስመልክቶ የተሰጠ የአቋም መግለጫ   

ነሐሴ 13 ቀን 2016 ዓ.ም. 

ውጫዊና ውስጣዊ ጥንተ ጠላቶቹ በሸረቡት ሴራና መርዘኛ የሆነ የሀሰት ትርክት የተነሳ የአማራ ህዝብ ላለፉት ሃምሳ አመታት ከፍተኛ ጭፍጨፋ እና መፈናቀል እየደረሰበት ቆይቷል። ይባስ ብሎ በ1983 ዓ ም በሃይል ስልጣን የተቆናጠጠው የትግራይ ህዝብ ነፃ አውጭ ግምባር በግልፅ አማራውን በጠላትነት የፈረጀና ያገለለ ህገ መንግሥት በመቅረፅ ለሃያ ሰባት ዓመታት የአማራውን አፅመ ርስቶች ወደ ትግራይ በመጠቅለል እንዲሁም ለሌሎች ክልሎችም በማቀራመት አማራውን ተሳዳጅ ከማድረጉም ባሻገር መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ/genocide/ እና ማፈናቀል ሲያደርስበት ቆይቷል። ህዝቡ በከፈለው መራራ ትግል የትህነግን ከስልጣን መውረድ ተከትሎ የለውጥ ጭምብል ለብሶ የመጣው የአብይ አህመድ አፓርታይዳዊ አገዛዝ እያደረሰበት እንዳለው መንግሥት መር የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ግን የአማራ ህዝብ በታሪኩ አጋጥሞት አያውቅም። ይህ አፓርታይዳዊ አገዛዝ በወለጋ፤ በመተከል፤ በአሩሲ፤ በባሌ፤ በሀረር እና በአዲስ አበባ  እያደረሰበት ያለው ጭፍጨፋ፤ ማፈናቀል፤ አፈና ማሳደድ፤ እስርና እንግልት አልበቃው ብሎ በእብሪተኝነት የአማራ ክልል ብሎ በወሰነለት አካባቢ በሚኖረው አማራ ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት ከከፈተ ይኸው ድፍን አመት አስቆጥሯል። 

የአብይ አፓርታይዳዊ አገዛዝና ተባባሪ ኃይሎች የከፈቱበት ጦርነት ህልውናውን የሚፈታተን መሆኑንን በመረዳት አማራው ራሱን ከመጥፋት ለመታደግ ውድ ልጆቹን በፋኖ አደረጃጀት በማዋቀር ወራሪውን ኃይል እየተፋለመው ይገኛል። የህልውና ትግሉን በስኬት ለማጠናቀቅም ወራሪውን ኃይል በወታደራዊ ዘመቻዎች ድል ከመንሳትና ከማሸነፍ ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ በፅኑ እናምናለን፤ እንደዚሁም የህልውና ትግሉ ከጠላት ጋር በሚደረግ ድርድር ግብ ሊመታ እንደማይችልም እንገነዘባለን። ድርድርን የትግል ስልት አድርገው የያዙ ኃይሎች የያዙት መንገድ ስህተት መሆኑን እና አማራ ጠል ከሆኑ ጨፍጫፊዎች ጋር የሚደረግ ድርድር የአማራዉን ህልውና የማያስጠብቅ መሆኑን በመረዳት ከዚህ ድርጊታቸውእንዲቆጠቡ ለማሳሳብ እንወዳለን። 

ዓለም ዓቀፍ የአማራ ህብረት የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል በስኬት እንዲጠናቀቅ የሚያግዙ ስራወችን እያከናወነ ይገኛል። በዚህም ረገድ በጦርነቱ ሰለባ የሆነውን ህዝብ ከማገዝ ባሻገር፣ ግፍ እየደረሰበት ላለው ህዝብ በውጭ ድምጽ መሆን፣ የህልውና ትግሉን ከሚመሩ አደረጃጀቶች ጋር በጋራ መስራት እና የትግል አቅጣጫ መጠቆም ይገኙበታል። ዓለም ዓቀፍ የአማራ ህብረት የህልውና ትግሉ በአጭር ጊዜ በስኬት እንዲጠናቀቅ ትግሉ በተደራጀ እና ሁሉንም ባሰባሰበ መልኩ መካሄድ እንዳለበት ያምናል። በመሆኑም በግንቦት 2015 ዓም የአማራ ህዝባዊ ግምባር የሚባል አደረጃጀት በአገር ቤት ሲመሰረት እና የውጭ አስተባባሪ ግብረ ኃይል ሲቋቁም የፋኖን የተበታተነ አደረጃጀት ወደ አንድነት ሊያመጣ ይችላል የሚል እምነት

አሳድሮ ከሁሉም ድርጅቶች በፊት ድጋፉን በመግለጫ አሳውቋል። ከግንባሩ የውጭ አስተባባሪ ግብረ ኃይል አመራሮች ጋር ሰፊ ውይይት ካካሄደ በኋላም አመራሮቹ በተለያዩ ጉዳዮች እገዛ እንዲደረግላቸው በጠየቁት መሰረት በፋይናንስና በሃሳብ ሰፊ እገዛወች በማድረግ ሲሳተፍ ቆይቷል። ነገር ግን ህዝባዊ ግምባሩ ስድስት ወር ሳይቆይ በህዝባዊ ሰራዊት ተተካ ሲባል ድርጅታችን ሂደቱ ላይ ጥያቄ የነበረው ቢሆንም ትግሉን ላለመጉዳት በሚል አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቦ ቆይቷል። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ሆኖም የፋኖ አደረጃጀት አንድ ወጥ ወደ ሆነ እዝ መጥቶ እና አንድ ማዕከላዊ ተቋም መስርቶ የአማራ ሰቆቃ እንዲያከትምና በኢትዮጵያ ፍትሃዊ ስርዓት እንዲመጣ ትግሉን ወደ መጨረሻ ግቡ ያደርሳል ተብሎ በሚጠብቅበት ሰዓት የፋኖን ወደ አንድነት መምጣት ያግዛል ብለን ተስፋ የጣልንበት ድርጅት የተወሰኑ የፋኖ አመራሮችን በመያዝ የአማራ ፋኖን አንድነት ያላስጠበቀ “የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት” መመስረቱን ስንረዳ እጅግ አዝነናል። ይህን አንድነት የማያመጣ ከፊል አደረጃጀት የማንደግፈው መሆኑን እና ከዚህ በፊት ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት ለህዝባዊ ግምባሩ እና ለድርጅቱ አመራሮች ሰጥቶት የነበረውን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ያነሳ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን። በተጨማሪም ድርጅታችን ከአማራ ህዝብ ህልውና በላይ የሚያስቀድመው አደረጃጀትም ሆነ ግለሰብ እንደሌለ ለማሳወቅ እንወዳለን። እንደዚሁም ለትግሉ የሚጠቅሙ አደረጃጀቶችንም ሆነ ግለሰቦችን መደገፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። በአንጻሩ ግን ትግሉን የሚጎዳ ይህን መሰል ከፋፋይ ድርጊት ስናይ የተቃውሞ ሃሳባችንን ከመግለፅ ወደ ኋላ አንልም። 

በእኛ እምነት የአማራ የህልውና ትግል ግብ መታ የሚባለው የአማራ ፋኖ ወራሪውን ኃይል በማሸነፍና ከስልጣን በማባረር ሃገራዊ ስልጣኑን ተረክቦ ህልውና የተነፈገውን ህዝብ ከመጨፍጨፍ፤ከመፈናቀል፤ከመታፈን፤ ከእስር እና ከመሳደድ መታደግ ብቻ ሳይሆን ሰላምና መረጋጋትን ሲያሰፍን እንዲሁም የህግ የበላይነትንና ፍትህን በመላዉ ኢትዮጵያ ማስፈን ሲችል እንዲሁም በ1983 ዓ ም የተተከለውን መርዘኛ አፓርታይዳዊ ስርዓት ከስሩ ነቅሎ በመጣል ፍትሃዊ ስርዓትን የሚተክል በሁሉም ኢትዮጵያውያን ውይይትና ይሁንታ የሚፀድቅ አዲስ ህገ መንግሥት ሲኖር ነው። ይህንን የህልውና ትግል ባልተራዘመ ጊዜ እውን ለማድረግ የፋኖ አደረጃጀቶች ወደ ተማከለ አንድ እዝ ወይም አወቃቀር መምጣት በፍጥነት መከናወን አለበት ብለን እናምናለን። 

ይህን የተማከለ የፋኖ አደረጃጀት እውን ለማድረግ የሚከተሉትን ምክረ ሃሳቦች እናቀርባለን፡- 

1. ሁሉም የየክፍላተ ሃገራት የፋኖ አደረጃጀቶች ወደ አንድ የአማራ ፋኖ አደረጃጀት ከመምጣታቸው በፊት የክፍላተ ሃገራት እዞችን አንድ አድርገው የሚመሩ ማዕከላዊ የፓለቲካና ወታደራዊ መዋቅሮች ሳይዘገዩ መመስረት፣ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

2. የአማራ ህልውና ትግል በድርድር መፍትሄ እንደማያገኝ በመገንዘብ በአማራው ላይ በዕብሪት የተከፈተበትን ጦርነት በማሸነፍ አገዛዙን በማውረድ አገራዊ ስልጣን ከመረከብ ውጭ ሌላ ምንም አማራጭ የለለ መሆኑን መተማመን ላይ መድረስ፣ 

3. በአገር ቤትም ሆነ በውጭ የምትኖሩ የማህበረሰባችን አባላት፣ የአማራ አደረጃጀቶች፣ የሚድያ ተቋማት፣ የማህበራዊ ሚድያ አንቂዎች፣ ምሁራን እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች የአማራ ፋኖ በአንድ ማዕከላዊ መዋቅር እንዲመራ ግፊት እንድታደርጉ ጥሪ እያቀረብን አንድነት እንዳይፈጠር እንቅፋት የሚፈጥሩ ኃይላትን በመለየት ድርጊታቸውን እንድታወግዙ እንጠይቃለን።

እንደ ማጠቃለያ ለትግሉ እንቅፋት የሚሆን እና አንድነት የማያመጣ አደረጃጀት ወይንም ግለሰብ ሲከሰት ያለ ምንም ይሉኝታ ለህዝብ ማሳወቅ ለትግሉ ስኬት እጅግ ጠቃሚና ነው ብለን እናምናለን። እንደዚሁም አንድ ወጥ የአማራ ፋኖ አለመመስርቱ በህዝቡ ላይ በየቀኑ የሚደርሰው ሰቆቃ እንዲራዘም እንዲሁም የህልውና ትግሉን በአስቸኳይ በአሸናፊነት ለመደምደም በሚደረገው የሞት የሺረት ተጋድሎ ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ እያደረሰ በመሆኑ ሁሉም የፋኖ ኃይሎች ተጠያቂነት እንዳለባችሁ በጥብቅ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን። የአማራ ፋኖ ወደ አንድ የእዝ ሰንሰለት እና ፖለቲካዊ አደረጃጀት በፍጥነት በመምጣት የአማራን የህልውና ትግል በድል በመደምደም አማራውን ከህልውና ስጋት ማውጣት ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ ፍትሐዊ ስርዓትን በማስፈን፣ እንዲሁም በኢትዮጵያና በቀጠናው ሰላምና መረጋጋትን ያመጣል በሚል በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየተጠበቀ ይገኛል። 

ዓለም አቀፍ የአማራ ህብረት መርህን የተከተለ እና በሁሉም የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች ስምምነትና መግባባት ላይ የሚዋቀርን አንድ የአማራ ፋኖ ተቋም በሙሉ አቅሙ ለመደገፍ እና የበኩሉን አስተዋጽዖ ለማበርከት ከወዲሁ ቃል ይገባል።  

- Advertisement -

ድል ለአማራ ህልውና ትግል! 

ድል ለፋኖ! 

ድል ሰላምና ፍትህ ለተጠማዉ ኢትዮጵያዊ ወገናችን!

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News