Homeነፃ አስተያየትየጠለምት ወረራ እና የህወሓት የስህተት አዙሪት 

የጠለምት ወረራ እና የህወሓት የስህተት አዙሪት 

Advertisement
World Wide Travel Group
ጸሃፊው

ደሳለኝ ቢራራ 

አማራ ክልል ባለዉ ዉጊያ የአገዛዙ ጦር ፋኖን መቋቋም አልቻለም። ከጅቡቲ መስመር ቀጥሎ የሀገር ዋና በር የሆነውን እና በልዩ ሁኔታ በከፍተኛ ወታደራዊ አቅም ጥበቃ የሚደረግለትን፡ መተማ ከተማ እና አካባቢውን ፋኖ ተቆጣጥሯል። ከእልህ አስጨራሽ ውጊያ በኋላ የአገዛዙ ጦር ተሸንፎ ወደ ጎረቤት ሀገር ተሰዷል። ትናንት በወጣው የሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ እንደተዘገበው መተማ አካባቢን ለቅቆ ተራ ስደተኛ የሆነው የኦሮሙማ ሰራዊት በሱዳን ጊዜያዊ መጠለያዎች እንደተጠጋ እና በመተማ እና በጋላባት መስመር ያለውን እንቅስቃሴ ሱዳን ማስቆሟን አሳውቋል። ይህንን መስመር በቁጥጥር ስር ማድረግ የሚሰጠው ወታደራዊና ፖለቲካዊ አንድምታ ከፍተኛ ሲሆን ተጽእኖውም በውጭ ግንኙነትና በዲፕሎማሲ ሁሉ የሚመነዘር ይሆናል።  

ይህ በእንዲህ እንዳለ፡ አገዛዙ ከሱማሊያ ጋር ዉጊያ ለመግጠም ዘመቻ ጀምሯል። ሰሞኑን በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር የቆየ፡ የኢትዮጵያ ንብረት የሆነ ተተኳሽ ሚሳይል የጫነ ተሽከርካሪ ወደ ሲማሌላንድ መጠጋቱ ታውቋል። ከትናንት በስቲያ አገዛዙ ባወጣው መግለጫ፡ ግብጽ ሶማሊያን ለማገዝ እያደረገችው ያለውን ወታደራዊ እንቅስቃሴ አውግዞ፡ እንቅስቃሴውን በዝምታ እየታዘቡ ያሉትን ሀገራት ጭምር በታጨቁ ኃይለ-ቃላት አስጠንቅቋል።  

ጅቡቲ በበኩሏ ‘የኢትዮጵያ ችግር ወደብ ከሆነ፡ 100% ኢትዮጵያ የምታስተዳድረው ተጨማሪ ወደብ እሰጣለሁ’ ብላለች። የጅቡቲ መግለጫ ሁለት ስለት ያለው ሾተል ሲሆን፡ አንደኛው ከሶማሊላንድ ጋር ያላትን የጥቅም ተቃርኖ በላጭ ሁና የምትገኝበት እና ለወታደራዊ ድጋፍ ስምምነት የተፈራረመቻትን ሶማሊያ በተዘዋዋሪ መንገድ መደገፍ ነው፤ ሁለተኛው ደግሞ “ኢትዮጵያ ቀጠናውን አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት እያመሰችው ነው” የሚል አንድምታ መፍጠር ነው። ምክንያቱም “የኢትዮጵያ ችግር የወደብ ጉዳይ ከሆነ ሙሉ በሙሉ ጥያቄዋን እኔ መመለስ እችላለሁ፤ ነገር ግን ከወደብ ያለፈ ፍላጎት ስላላት ነው ጠብአጫሪነቱን የፈለገችው” የሚል መልእክት አስተላልፋበታለች። በጅቡቲው መግለጫምላሽም፡ ኤርትራ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች። ጅቡቲ ለኢትዮጵያ እሰጣለሁ ያለችው የወደብ መገንቢያ ቦታ ላይ፡ የባለቤትነት ጥያቄ ከማንሳት በተጨማሪ በዚህ ቀጠና የሚገነባ ወታደራዊ አቅም የግል ስጋቷ መሆኑን አስገንዝባ፡ በጅቡቲ የተሰጠውን ምክረ ሀሳብ እንደማትቀበለው ኤርትራ ገልጻለች።  

በዚህ ዝብርቅርቅ መካከል ግብጽ 10ሺህ የሚጠጋ ሰራዊቷን ወደ ሶማሊያ በማስገባት ወታደራዊ ልምምድ ጀምራለች። የቀጠናውን ውጥረት ስንመለከት በኢትዮጵያና በሶማሊያ/ግብጽ መካከል ጦርነት መጀመሩ የማይቀር ይመስላል። ይህንን ነባራዊ ሁኔታ የተረዳው የአብይ አህመድ ኦሮሙማ አገዛዝ፡ ጦሩን ከአማራ ክልል ሰብስቦ ወደ ሀርጌሳ ለማስገባት እንደተገደደ የሚጠቁም ነገር አለ። የአገዛዙ ሰራዊት ከአማራ ክልል ከወጣ ደግሞ ለጥቆ የሚፈጠረው ዋና የፖለቲካ ክስተት ተገማች ይሆናል። ያለምንም ጥርጥር ፋኖ ከክልሉ አልፎም አ/አ የሚገባበት እድል ይፈጠራል። የአገዛዙ ስምሪት ወደ ቀይ ባህር ቀጠና ሲሆን፡ ፋኖ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርገው ስምሪት የተሳለጠ እንደሚሆን ግልጽ ነው። አገዛዙ በነዚህ ሁለት መቀሰቻዎች ተወጥሮ ሲያዝ፡ ከፋኖ ጋር እርቅ መፈጸም አልያም የሚያደርገውን ውጊያ ለሌላ አካል ሰጥቶ፡ በውክልና ማስቀጠል እንዳለበት ወስኗል። በመጀመሪያ ግን ድርድርና እርቅ ማድረግ የሚቻልበትን እድል ሞክሯል። ፋኖ ለድርድርና እርቅ መቅረብ እንዲችል ኃላፊነት ከተሰጣቸው ባለስልጣናት አንዱ የላኩልኝን መልእክት እንደወረደ እነሆ፡  

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

“ይህንን መረጃ አድርስልኝ!  

_________ //  

የፌደራል መንግስት በምስራቅ ኢትዮጵያ የገጠመውን ችግር እስኪፈታ ጊዜ እንዲያገኝ፡ አማራውም በዘመቻው እንዲተባበረን፡ በሚል ስልት ከፋኖ ጋር ታክቲካዊ ድርድር” ለማድረግ ወስኗል:: ለዚህ ድርድር በመንግስት በኩል ከታጨነው ዘጠኝ የአማራ ክልል ተወላጅ የፌደራል ባለስልጣን ውስጥ እኔም አለሁበት::ፋኖ ፈፅሞ እንዳይታለል! ይህንን ካደረጉ ታሪካዊ ስህተት ይሰራሉ። ህዝባችንንም እውነትም “ሾርት ሚሞሪ” ያስብሉታል:: እኔ የምመክረው ፋኖ የውጭጠላት የሚባሉትን ይደግፍ ወይንም ይቃወም የሚል ሳይሆን፡ በቃ ገለልተኛ ሆኖ ትግሉን ይቀጥል የሚል ነው::” 

ከተመረጡት ዘጠኝ ሽማግሌዎች አንዱ እንዳመለከቱት፡ አገዛዙ ከፋኖ ጋር መፍጠር የፈለገው ድርድር ታክቲካል ነው። ይህም የተለመደ የኦሮሙማ ፖለቲካዊ ቁማር መሆኑ ታውቋል። ለዚህም ነው ሽማግሌው ምክርም የለገሱት። ስለዚህ ፋኖን በድርድር እናቀርበዋለን የሚሉት ሀሳብ ውድቅ ተደረገ እና ሌላ ካርድ ወደ መሳብ ተሻገሩ። ሌላኛው ካርድ፡ ፋኖ ውጊያውን ሊያቆምልን የማይችል ከሆነ፡ እኛ ከፋኖም ከሶማሊያም ጋር በአንዴ መዋጋት ስለማንችል፡ ፋኖን በተወካይ ማዋጋት አለብን የሚለው ሀሳብ ሆነ።  

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በዚህ መሀል በደ/ፂ የሚመራዉ የህወሀት አንጃ “ጌታቸዉን አባረህ እኔን ከሾምከኝ ህወሀትን በትነን ብልፅግና እንሆናለን” እስከማለት ተንበርክኮ ባሪያ ለመሆን የሚማጸን ተላላኪ ተገኘ። በአገዛዙ ቤት ትልቅ ደስታን ከፈጠሩት ክስተቶች መካከል ትልቁም ሆኖ ተቆጠረ። ምናልባትም ወያኔን በጦርነት ድል ከተደረገበት ቀን በበለጠ የደስታ ምሽት የሆነው፡ አፈንግጫለሁ ብሎ የኮበለለው የህወሓት አንጃ በዚህ ደረጃ ተሽመድምዶ የመጣበት እለት ነበር። እንደዚያም ሁነው፡ አብይ አህመድ ወዲያውኑ መልስ አልሰጣቸውም። የእነ ደብረጺዎን ልኡክ ጥያቄውን ካቀረበ በኋላ አብይ አህመድ እሺም እምቢም ሳይል አሽቷቸዋል። መዋረዳቸውን በተግባር ነው የመለሰላቸው።  

በዝምታው ሰሞን ታዲያ፡ የተለየ የራሱን ሴራ ሾረበ። ከፋኖ ጋር መደራደርንም: ህወሀትን የብልጽግና አጋር ማድረጉንም ትቶ: ሁለቱ የሚጋጠሙበትን አዉድ መፍጠር መረጠ። ከዚህ ውሳኔው በኋላ፡ ወዲያዉኑ መልስ ሰጣቸው። የደብረጺዮን ቡድን “እኔ ፋኖን እይዝልሀለሁ” የሚል ታፔላ ለጥፎ እንደገና እንዲመጣ ታዘዘ። ህወኃትም “እንዴት አድርጌ?” የሚል ጥያቄ አነሳች። ኦሮሙማም “ህወሓት በጠለምት በኩል ገብታ አማራን ትዉረር፡ የተቀማችዉንም መሬት ታስመልስ” አለ። ህወኃትም በሽሬ በኩል ተከዜን ተሻግራ ጠለምትን ወረረች። ይህ “የህወሓት ወረራ የፋኖ ትግል የትኩረት ማእከል ይሆናል ወይስ አይሆንም?” የሚለው ጥያቄ በፋኖ አመራሮች ብስለትና ስትራቴጂክ ንድፍ የሚመለስ ሁኖ፡ በጊዜያዊነት ግን የአገዛዙ ስጋት የነበረዉ ፋኖ፡ ከወያኔ ጋር እየተዋጋ ስለሚቆይ: ከሶማሊያ ጋር ለመግጠም ወደ ተዘጋጀበት ጦርነት በሙሉ ልቡ እንዲዘምት ያስችለዋል።  

የኦሮሙማው አገዛዝ ከሶማሊያ ጋር የሚዋጋበት ምክንያት (cause) አሳማኝ ስላልሆነ ሰራዊቱ የዉስጥ እምነት አይኖረዉም፣ የቀጠናዉ ሀገራትና ኃያላን መንግስታትም ከዚህ በፊት እንዳሳወቁት ሁኔታዉ የሶማሊያን ሉአላዊነት የተጋፋ ጠብአጫሪነት ስለሆነ: በዲፕሎማሲና በመሳሪያ ሶማሊያን ይደግፋሉ። በመጨረሻም ኦሮሙማ የሶማሊያን ጦርነት ተሸንፎ ይመለሳል። አሁን ባለው የአገዛዙ እቅድ መሰረት፡ የሶማሌውን ጦርነት አሸንፎም ሆነ ተሸንፎ እስኪመለስ ድረስ፡ ፋኖ እና ህወሓት እየተፈሳፈሱ እንዲቆዩት ነው የሚፈልገው። ፋኖ ከትግራይ ህዝብ ጋር መዋጋት እንደማይፈልግ ቢታወቅም፡ በአገዛዙ ዘንድ፡ ሕወሓት የሀገር የመከራ እርሾ እንደሆነ ስለሚታወቅ፡ ፋኖን አስገድዶ ወደታቀደው ጦርነት ያስገባዋል ተብሎ ይገመታል።የተያዘው እቅድ ከሶማሊያ ሲመለሱ የሁለቱ አሸማጋይ መሆን ነው።  

ኦሮሙማ ተሸንፎ ከተመለሰም በኋላ፡ በሶማሊያ የሚከናነበዉን የሺንፈት ማቅ: “ለቀጠናው ሰላም ስንል የተሰነዘረብንን ጦርነት ትተን በመመለሳችን የተጎናጸፍነው የክብር ካባ ነዉ” ብሎ በኢትዮዽያን ህዝብ ንቃተ-ህሊና ላይ ድጋሜ ያላግጥበታል። በዚህ የጦርነት አዙሪት በዋናነት ህወሓት ከፋኖ ጋር እንዲገጥም በማድረግ፡ አገዛዙ “ከተሳካለት”፡ ከስልጣን የመዉረድ ስጋቱን ይቀርፋል። ኦሮሙማ ጦርነትን ማሸነፍ ወይም መሸነፍ አይደለም አላማው፡ የሚከፈለው ሁሉ ሀብትና የሰው ህይወት ተከፍሎ በስልጣን መቆየት ነው። የትኛውንም የፖለቲካ ስብስብ ለማቀፍም ፍላጎት የለውም። ህወሓትም ቢሆን ብልፅግና አይሆንም: ወልቃይትንም አያስመልስም። የአብይ አህመድ ካርድ ሁኖ ብቻ ያገለግላል። ይኸውም ምናልባት ፋኖ ስህተት ሰርቶ ትኩረቱን ወደ ህወኃት ካደረገ ነው። የኦሮሙማ ሰሞነኛ እንቅስቃሴ ሁሉ “የፋኖ ትግል ጊዜያዊ ትኩረቱ ይቀለበሳል” በሚል እሳቤ የተንጠለጠለ ነው። በጊዜያዊነትም ቢሆን የፋኖ ትኩረት ከአራት ኪሎ በመለስ መሆን ከቻለ ለአገዛዙ ፋታ ይሰጣል። ምክንያቱም ፋኖ ትግሉን እንደገና ተቀናጅቶ ሲጀምር: አገዛዙ ሌላ አጀንዳ ያመጣል። አጀንዳ በአጀንዳ ላይ እየደራረበ፡ የህልውና ተጋድሎውን ባለበት እንዲረግጥ ያደርገዋል። ይህንን ሁኔታ የፋኖ አመራሮች በሚገባ ይረዱታል የሚል እምነት አለኝ። ለአፍታም ዝንፍ የማይባልበት የትግሉ ትኩረት ማእከል 4ኪሎ ነው።  

- Advertisement -

ደሳለኝ ቢራራ (https://x.com/desalegn_birara) 

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News