Homeነፃ አስተያየትአብዮቱ፤ መስከረም 2/1967 እና የኦዲት ግኝቱን በጨረፍታ

አብዮቱ፤ መስከረም 2/1967 እና የኦዲት ግኝቱን በጨረፍታ

Advertisement
World Wide Travel Group

በ ሙሉዓለም ገ/መድኀን

ከ አብዩቱ በፊት…

የአውሮፓ ‹ስቴቶች›ን ቅርጽ እና አቅጣጫ የነደፉት ሩሶ እና ጆን ሎክ እንደሆኑት ሁሉ፣ በኢትዮጵያም የአገሪቱን ቅርጽ እና አቅጣጫ የቀየሱት ቤተ-መንግሥት እና ቤተ-ክህነት ነበሩ፡፡ ባለቤትነቱ የግዕዝ ሥልጣኔ የሆነው የአክሱም ሥልጣኔን ይዞ፣ ክብረ-ነግሥት የአገሪቱ ሥነ-መንግሥታዊ ፍኖተ ካርታ ሆኖ አገልግሏል፡፡

በይበልጥ በመካከለኛው ዘመን እ.አ.አ ከ1528-1543 ድረስ የቀጠለው የአሕመድ ኢብን ኢብራሂም (ግራኝ አሕመድ) እስላማዊ ሱልጣኔት ለመመስረት የተነሳው ጦርነት፣ እሱን ተከትሎ የተፈጠሩ የውጭ ኃይሎች ሚናና አሰላለፍ፤ ቀጥሎም በጦርነት በተዳከመ ሕዝብ ላይ የታየው የኦሮሞ ወረራ (ምኒልክ ዳግም እስኪሰበስባቸው ድረስ በወረራው ስፋት ተጠፋፍተው ነበር)፣ … እነዚ ግዙፍ ክስተቶች የአገሪቱን ቀጣይ አሰፋፈር ያመላከቱ፣ ቅራኔን ያሻገሩ፣ ከመሆኑ ባለፈ የኃይል ምንጭ ሆነው ታይተዋል፡፡ 

ይህም ሆኖ የሥነ-መንግሥቱ ፍኖተ ካርታ እንደየጊዜው ሁኔታ ቅቡልነቱ እየሳሳም ሆነ እየበረታ እስከ ዘውዳዊው ሥርዓት ማክተም መስከረም 2/1967 ዓ.ም ድረስ ዘልቋል፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በዚህ ሁሉ ሂደት የብሔረ-ኢትዮጵያ ግንዛቤ በክርስቲያናዊ፣ እስላማዊ ሱልጣኔቶች (የአዳል፣ የሐረር ሥልጣኔ፣…) አስተምህሮ ተመርታለች፡፡ ምዕተ ዓመታትን በሚያስቆጥረው በዚህ ሁሉ ሂደት ኃይማኖት እንጅ ብሔር የሥልጣን መወጣጫ አልነበረም፡፡ የአካባቢ ገዥነት እንደሕዝብ ስብጥሩ (ሙስሊም፣ ክርስቲያን፣ ዋቄ ፈና፣…እንዳለበት) ይሾማል፤ የላይኛው ገዥነት ደግሞ እንደ ፍኖተ-ካርታው አመጣጥ የሚወሰን እንጂ በብሔር ማንነት የሚገኝ አልነበረም፡፡ (የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰን ተዋሕዶን የሚጠሉ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች መነሻቸው ቤተክርስቲያኗ የአገር ዘብ ሆናባቸው እንደሆነ ሚገለጠው ፍኖተ ካርታውን ስናጤን ነው)

ዘግይቶ በደረሰው ትውልድ ‹የደብተራ ፖለቲካ› የሚል የፍረጃ ስም የተሰጠው ፍኖተ-ካርታው ለምዕተ-ዓመታት የንጉሣዊ ሥርዓት የባህላዊ አስተዳደር ምልክት ሆኖ አገልግሏል፡፡ አገር አንፆል፤ ዘብ አቆሞ መርቷል። ከዚህ ርዕይ፣ ከአገር-ግዛት አንድነት እና ግንባታ ሂደት ጋር በተያያዘ በተፈጠሩ አንዳንድ ‹ቅራኔዎች› የኢትዮጵያን ሐገረ-መንግሥት በተመለከተ የተለያየ አተያይ ተፈጥሯል፡፡

የኢትዮጵያ ሺህ ዘመናት የታሪክ ባለቤትነት፣ Civilization State ተክዶ ፤  ‹‹ከመቶ ዓመታት ያልተሻገረ ዕድሜ›› ያላት የሳር ጎጆ መስላ ተሰብኳል፡፡ አሁን ድረስ ገዥነታቸውን ማመን አቅቷቸው ስድስት ዓመታት ሙሉ በሚበረግግ ህሊናቸው እየባተቱ ያሉ ኃይሎች፣ ዛሬ የኢትዮጵያን ታሪክ ወደሺሕ ዘመናት ሲያሳድጉት፣ ኢትዮጵያን በቅኝ ገዥነት የበየኑባቸውን ሐሳዊ ‘ቴክስቶች’፣ የኪነ-ጥበብ ስራና ሃውልት፣ …ታዳጊዎች በሚደርሱበት ቦታ አስቀምጠው፤ ያውም እያስተማሩበት ጭምር ነው፡፡

የሆነው ሆኖ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ‘ሰዋሰዋዊ መግባቢያ’ ለመጥፋቱ በሐገር ምስረታ ስር ቅራኔን ሲፈለፍል ውሎ የሚያድር፣ ተራማጅ ሀሳብ ያረጠበት፤ ታሪክን በጠባቡ ማየት እና ከፖለቲካ ሥልጣን ጋር የሚያቆራኝ (የሀሳብ ጥገኛ) ኃይል ከመበርታቱ ጋር ይገናኛል፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

አንዳንድ ነጥቦች ስለቅድመ-አብዩቱ

ስለ1966ቱ የኢትዮጵያ አብዩትና የአብዩቱ መሪ ተዋናይ ስለነበረው ያ-ትውልድ በየፈርጁ እና የኃይል አሰላለፉ ብዙ ተብሏል፡፡ ለአብዮቱ መፈጠር እና ስለትውልዱ ሥር ነቀልተኝነት ባህሪያትም እንደፀሐፍቱ የፖለቲካ ዝንባሌ እና የጀርባ መደብ የዕይታ ልዮነቶች ቢኖሩም፤ ስለጉዳዮ ትንታኔዎች ከየአቅጣጫዎች ተሰጥተዋል፡፡ 

ለኢትዮጵያ አብዩት መፈንዳት እና ለትውልዱ ሥር ነቀልተኝነት ባህሪያት ይህን ተከትሎ አገሪቱ ለገባችበት የአዙሪት ፖለቲካ የቅድመ-አብዮት ታሪካችን የራሱ ድርሻ አለው፡፡ 

ፀረ-አማራ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የገቡበት ቀዳዳ አለ።

- Advertisement -

በዚህ ዕይታ፣ ኢትዮጵያን የታሪክ ፈተና ላይ ከጣሏት ሂደቶች ሁለት ወሳኝ ሁነቶችን እንመልከት፡-

አንደኛ፡- የተገባደደው (የመልሶ ማቅናት) የግዛት አንድነት ምስረታው እና የአገር ግንባታ ጅምር ሂደቱ ያስከተላቸው ለውጦችና አንዳንድ ቅራኔዎች በማህበረ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች ሳይታረቁ፣ ሂደቶቹ በሚፈለገው ፍጥነት ቀጣይነት አለማሳየታቸው፤ በተለይም ከዓድዋ ድል በኃላ የአገሪቱ ሁነኛ መሐንዲስ የሆኑት ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከነበሳል አመራራቸው የአንድ ትውልድ (ሃያ አመት) ቆይታ ቢኖራቸው ሁኔታዎች የመቀየር ዕድል ነበራቸው፡፡ 

ሆኖ ግን የዓድዋ ድል በዓለም ፖለቲካ ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ በዲፕሎማሲና ሌሎች መስኮች የድሉን ትሩፋት በደንብ ለማጣጣም የሚያስችል የዕድሜ በረከት ለንጉሣችን አልተገኘም፡፡ ከድሉ ማግስት በነበሩ 13/14 ዓመታት ያ ሁሉ የዘመናዊነት መሠረት ቢጣልም በዙፋኑ ላይ ተጨማሪ ዕድሜ የሚጠይቁ ጉዳዩች ነበሩ፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ የምኒልክን የአልጋ ቁራኛ መሆን ተከትሎ ለአጭር ጊዜም ቢሆን አገሪቱ በሦስት ማዕዘን ፖለቲካ ታምሳለች (ንግሥት ጣይቱ Vs ራስ ሚካኤል Vs ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ በየራሳቸው ቡድን ፍትጊያ ውስጥ መግባታቸውን ያስታውሷል) ይሄው ትርምስ የአገር ግንባታና ማዘመን ሂደቱ ላይ ቀጣይ ተጽዕኖ ማሳደሩን መካድ አይቻልም፡፡ ኃይል ተበትኗልና። 

ይህን ተከትሎ የልጅ እያሱ ዘመነ-መንግሥት፣ በእንቆቅልሽ የተሞላ መሆኑ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ አለኝታን ለማጠናከር የሞከረበት አካሄድ፣ በተለይም የኢትዮጵያን የዳር አካባቢዎች በማህበራዊ ግንኙነት ወደመሀል አገር ለመቀላቀል የተጓዘበት መንገድ በውስጠ ተቃርኖ ቀጣይነት ማጣቱ፤ በቀጣዩ የኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ ተጽዕኖ አልነበረውም ማለት አይቻልም፡፡ በዚህ ያኮረፈ፣ ያሴረ፣ ያደባ፣… ቀን ይጠበቅ ነበርና።

ቀጥሎም ዘውዲቱን ንግሥተ ነገሥት፣ ተፈሪን አልጋ ወራሽ ያደረገው የፖለቲካ ለውጥ ትኩረቱ የግዛት አንድነት ምስረታው እና የአገር ግንባታ ሂደቱ ያስከተላቸውን ለውጦችና እዚህም እዚያም የነበሩ ቅራኔዎች በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎች የሚያስታርቅ ሳይሆን የተፈሪን ፍጹማዊ የሥልጣን ጎዳና የሚጠርግ ሆኖ መገኘቱ ከአርባ ዓመት በኃላ ለመጣው ውጥንቅጥ እርሾ አልነበረውም ማለት አይቻልም፡፡ ይሄኛው ጊዜ ደግሞ ለአገር ውስጥ የርስ በርስ ጦርነት የመጀመሪያው የጦር ጀት ጥቅም ላይ ሁሉ ውሎበታል። (አንቺም-1923)

በሌላ የታሪክ ሁነት፦ በያ-ትውልድ ውስጥ የፀረ-አማራ፣ የፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች የሴራ ሜዳ ሰፊ እንደነበር ሳይዘነጋ፣ አንዳንዶች ታሪክን እያጣቀሱ፣ የማህበረ-ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን መሪ አጀንዳ በማደረግ ዘውዳዊ ሥርዓቱን የተፈታተኑበት ሁኔታ አንድም ባህላዊ አስተዳደሩ በተለይም ከፋሽስት ጣሊያን በኋላ ንጉሡ አርበኞችን የያዙበት መንገድ፣ የተከተሉት ጠቅላይ የሆነ የአስተዳደር ዘይቤ፣  እዚህ እዚያም ቅራኔ ፈጥሮ ለሁኔታው ገፊ-ምክንያት ሆኗል፡፡ 

(በነገራችን ላይ ከዓድዋ ድል በኋላ በዳግማዊ ምኒልክ የንግሥና ዘመን ኢትዮጵያ 42 ግዛቶች ነበሯት፡፡ አከፋፈላቸውም የራሳቸውን ታሪክና ባህል በመመርኮዝ  የተከናወነ ነበር [Bahru Zewde, 2014] የአጼ ኃይለሥላሴ የድኀረ-ጣሊያን የአስተዳደር ዘይቤ፦ ጥርስ ውስጥ በገባች አገር፣ ዙሪያዋን በሦስቱ ሾተላዩች ጣሊያን፣ እንግሊዝና ፈረንሳይ ለተከበበች፤ የአረብ አገራት ስውር እጆች ለሚፈትኗት አገር ‘አማራጭ የሌለው መፍትሔ ነበር’ ቢባል እንኳ ያ ጠቅላይ የአስተዳደር ዘይቤ ኢትዮጵያን የጠላቶቿ ሜዳ ከማድረግ አላስቀራትም)

ሁለተኛ፡- ከአገር ግንባታ ሂደቶች ጋር ተጣምሮ አትዮጵያን የማዘመኑ ሂደት አፄ ኃይለሥላሴ በጎ አሻራቸው ሳይዘነጋ አንድ የአደጋ በር ተከፍቶ ነበር። በተለይም በትምህርቱ መስክ ነባሩን በማበስበስ እንጅ አዲሱን ከነባሩ (አገር በቀሉ) ጋር በማስማማት ማለምለም አለመቻሉ፤ ከአገሪቱ ታሪክ ጋር መታረቅ የማይችል ሥር-ነቀልተኛ (ያ) ትውልድ እንዲፈጠር በር ከፍቷል፡፡

በዚህ ረገድ በተለየ መልኩ በድህረ-ጣሊያን ወረራ በስፋት ወደአገር ውስጥ ያስገባነው የባህር ማዶ ሥርዓተ ትምህርት (Imported Curriculum) ትውልዳዊ ዝንፈቱን አስከፊ አድርጎታል፡፡ 

በእርስ በርስ ጦርነት እና የውስጥ ሽኩቻ የታሪክ ፈተናዋን መሻገር አቅቷት በውስጣዊ ሁኔታ የጠላቶቿ ሜዳ ለመሆን የተገደደች አገር፤ በትምህርት ሥም ዘመናዊነትን ከነ አሰስ ገሰሱ መቀበል ስትጀምር፣ በትውልዱ ላይ የባህል መነጠሉ (Cultural dislocation) እና ከነባራዊው አውድ የማፈንገጡ ነገር እየበዛ፣ ከአዳሽ ምሁርነት ይልቅ ለሥር-ነቀልተኝነት አንገቱን የሚሰጥ ትውልድ ወደፊት መስመር ወጣ፡፡ ሀሳብ ተበድሮ አገር ላጥፋ ባይ ሆነ። 

ትምህርት አዳኝ ብቻ ሳይሆን ገዳይ ጭምር የሚሆነው የጊዜውን የኢትዮጵያን ሁኔታ ስናይ ነው፡፡

የሥር-ነቀልተኝነት ንቅናቄው ባለቤትና ተዋናይ መሠረቱ በጣም የጠበበ ቢሆንም የአገሪቱን ተሰርታ አለማለቅ (የኤርትራ፣ ኡጋዴን፣ ባሌ፣… ሁኔታዎች ያጤኗል) እና የቅራኔዎችን አለመለዘብ ተከትሎ ንቃቃቱ በማየሉ መሠረተ ጠባቡ የትውልዱ ተዋናይ ራሱን ለእንግዳ ብሔራዊ ግብ እንዲያጭ የልብ ልብ እንዲሰማው አድርጎታል፡፡ 

‹‹መሬት ላራሹ››፣ ‹‹የኃይማኖት ነፃነት››፣… ወዘተ ህዝባዊ ጥያቄዎች አገሪቱንም ሆነ ያን ዘመን የሚመጥኑ አጀንዳዎች እንደነበሩ አይካድም፡፡ ችግሩ የነበረው፣ ‹‹የብሔረሰብ ጥያቄ›› ትርጉም፣ ብያኔና ድምዳሜ ላይ ነው። (ማስፈንጠሪያ ሊንኩን ዳብሰው ያድምጡ)

በደፋር እርግጠኝነት የሚታበየው ያ-ትውልድ ቆዳውን ዘልቆ ባልገባው ጥራዝ ነጠቅ ማርክሳዊ ርዕዮተ ዓለም እየተመራ፣ ያለበትን ህብረተሰብ ፦ ማኀበራዊ ዕድገታቸውንና የለውጥ ሁኔታዎችን ቀድመው ከጨረሱት ሀገራት ጋር እያነፃፀረ፣ በችኩል ግንፍልተኝነት ባህሪው የመዘመን/የመለወጥ ዕድል የነበረውን አስተዳደር ነቅሎ ለመጣል ተጣደፈ፡፡ 

የያ-ትውልድ ጥንተ-አብሶ (Original sin) መጠገን ይችል የነበረውን የአገሪቱን የተዋረሰ ማህበራዊ ህሊና ማናጋቱ እና ቅጥ ያጣ ሥር-ነቀላዊነቱ ነው። ያ ቅጣ ያጣ ሥር ነቀላዊነቱ ኢትዮጵያን ዛሬም ድረስ ለዘለቀው ተንከባላይ የትውልድ ዕዳዳርጓታል። 

ማርክሳዊ ሌኒናዊ ርዕዮት የአስተሳሰብ ዘይቤ መሆኑ ቀርቶ የእምነት ያህል የአስተሳሰብ ልዕልና በያዘበት በዚያ ዘመን፣ መፈክር የንድፈ ሐሳብ ቦታን ከመያዙም ባለፈ የትውልዱ ፉክክር ከግራም በላይ የበለጠ ግራ ለመሆን እንደነበር የትውልዱ የታሪክ ድርሳናት ህያው ማስረጃዎች ናቸው፡፡ 

ዛሬም ድረስ ያለንበትን ፖለቲካዊ ሁኔታ ቅርጽ የሰጠውና በተቃርኖ የተሞላውን አብዩት ካዋለዱት ውስጣዊ ሁኔታዎች አኳያ ያ-ትውልድ የታሪክ ፈተናችን ውጤት አልነበረም ማለት ይቻል ይሆን?!

(ያ) ትውልዱ በተጓዘበት የትግል መስመር ሁሉ ሥር-ነቀላዊ ረብሸኝነት፣ ባህሪ-ድርጊት ከመፍጠሩ ውጭ የአገሪቱ የታሪክ አቅጣጫ በአንድ ጀምበር ማስተካል የሚችል መስሎት ነበር፡፡

የኢትዮጵያ ፓራዳይም ሽፍት የተመዘገበው እዚህ ላይ ነው። ክብረ-ነግሥት ሥነ መንግሥታዊ ፍኖተ ካርታ ሆኖ ባገለገለበት አገር ቀዩን መፅሐፍ አምጥተው ሕዝቡ ላይ ጫኑበት። ለመሸጋገሪያ የሚሆን ‘ማኀበራዊ መላ’ እንኳ ቦታ እንዳይሰጠው አገር በቀሉን እሳቤ ‹የደብተራ ፖለቲካ› እያሉ በፍረጃቸው አራከሱት። 

እነዚያ ተመፃዳቂዎች በሰፊ አገር በቀል ዕውቀት መሀል ተፈጥረው፣ ምድረበዳ እንደበቀለ ባይተዋር ከራሳቸው አገር እውነት ጋር ተጣልተው ኢትዮጵያን ወደገደል ገፏት፡፡

ዛሬ አባትና ልጅ የማይግባባበት ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥ የቆምነው በዚህ መንገድ ነው። ይህን ትውልድ፣ ተንከባላይ የትውልድ ዕዳ ነው የተጫነው።

ዛሬ መስከረም 2/2017 50ኛ ዓመቱን የደፈነው ‹‹የኢትዩጵያ አብዮት›› ሲጠና ከፖለቲካ ብቻ ሳይሆን ከማኀበራዊ ሁኔታዎቹ አኳያ ጭምር ቢሆን ለኦዲት ያመቻል፡፡ 

የድኀረ-አብዩት ፖለቲካዊ ተላምዷችን በደም ግብር የታጀበ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የነገሥታቱ ‹‹መለኮታዊ›› ሥልጣን ያበቃበት፣ ዘመናዊ እና ምድራዊ ፖለቲካ ተጀመረ የተባለበት  አግባብ፦ መጠፋፋትን መታያው በማድረጉ ዛሬም ድረስ የፖለቲካ ትርጉሙ ከደም ግብር ያለፈ በጎ ምስል የለውም፡፡ 

ፖለቲካችን አንድ ገጹ፦  ‹‹አማራንና ኦርቶዶክስን መጥላት፤  ኢትዮጵያን ማራከስ››  ሲሆን፤ በሌላኛው ንባቡ ደግሞ ‹‹ለሥልጣን ደም መፋሰስ›› በሚል የትርጉም ማዕቀፍ እንዲጠቃለል አድርጓል፡፡ 

ይህን የሃምሳ ዓመት “እውነት” የሚጋፋ የዚህ ዘመን ሀቅ ቢኖር የአማራ ሕዝብ እያደረገ ያለው ትግል ነው፡፡ ትግሉ የሕልውና እንጂ የሥልጣን አይደለም፡፡ ሥልጣን ሁለተኛ ዕድል እንጂ ቀዳሚው የትግሉ አምድ ሕልውና ነው፡፡ 

ይህ በ50 ዓመቱ የድኀረ-አብዩቱ ጉዞ ግዘፍ የሚነሳ ሀቅ ነው፡፡ አለመንተንተኑ ግን ለባለጌዎች ስላቅ ተመችቷል፡፡

የአማራ ልሂቅ ከበዛ አርምሞው ወጥቶ ይህን ግዜ ካልተጠቀመበት ሌላ ዙር ሃምሳ የስቃይ ዓመታት በልመና እንኳ አያገኝም፤ ኢትዮጵያ በዚህ ሁኔታ ልትቀጥል አትችልምና፡፡

የኦዲት ግኝቱን በጨረፍታ…

ኢትዮጵያ የዛሬ 50 ዓመት ያስተናገደችው አብዩት የአገሪቱን የታሪክ ጉዞና አቅጣጫ የለወጠ ለመሆኑ አያከራክርም፡፡ ይህ ፓራዲየም ሽፍት (ከክብረ-ነገሥት ወደ ቀዩ መጽሐፍ) ያልተሟላ ቢሆንም መጠገን ይችል የነበረውን የኢትዮጵያን የተዋረሰ ማህበራዊ ህሊና አናግቶታል። ቅጥ ያጣ ሥር ነቀላዊነቱ የዛሬውን ‘የኢትዮጵያ አዕምሮ’ እንዳዋለደ ከፍ ሲል ለማመላከት ተሞክሯል፡፡ 

አሁን አብዩቱን አጠር ባለመልኩ ኦዲት ለማድረግ እንሞክራለን፡፡ 

መስከረም 2/1967 አበሰረ ከተባለው ነገር አንዱና ዋናው ሥልጣን ከ ‹‹መለኮት›› ወደሕዝብ ባለቤትነት ዞረ የሚል ነበር፡፡ በተግባር የተመለከትነው ደግሞ ያለፈውን እጅግ የሚያስናፍቅ ነው፡፡ 

የአብዩቱን ኦዲት አጠር ባለመንገድ ለመመልከት የተደራጀ ፖለቲካ እና ማኀበራዊ ህሊና ላይ ያሳረፈውን ተፅዕኖ (ማኀበረ-ፖለቲካዊ ጉዳዩችን) አለፍ ገደም እያልን እንመልከት፡-

ዛሬ ኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲ የሚባል የላትም፡፡ ይህ የበሻሻው ማንጁስ Abiy Ahmed Ali  የብቻ ጥፋት ሳይሆን የራሱ የሆነ ቅድመ-ታሪክ አለው፡፡ ቀድሞውንም ቢሆን የፓርቲ-ፖለቲካ እንቅስቃሴ በሚያፈርሰው ላይ እንጂ በሚገነባው ላይ ስምምነት ባልነበረው ያ-ትውልድ የተጀመረ በመሆኑ መሠረቱ የተበላሸ ነበር፡፡

የፓርቲ-ፖለቲካ እንቅስቃሴ መለያ ባህሪው ዛሬም ድረስ ተሻግሮ የመጣውን አሉታዊ ጎኑ ጎልቶ የሚታየውን የአገሪቱን ፖለቲካ ባህሪ በመቅረጽ ረገድ ተፅዕኖው ከፍ ብሎ ይታያል፡፡ 

ለውይይት በር መዝጋት፣ የጥላቻ እና ቂም በቀል ፖለቲካ፣ ሃሳብን እና ግለሰብን ማቆራኘት፣… መነሻቸው ከመጀመሪያዎቹ የፓርቲ-ፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ጋር በጽኑ የተሳሰረ ሆኖ ይታያል፡፡

በያ-ትውልድ ውስጥ ፍትሃዊ ማኅበረሰብ እና ፖለቲካዊ ሥርዓት ለመገንባት የታገሉ ግለሰቦች ቢኖሩም  እንደትውልድ የተመዘገበው ውጤት ለፖለቲካም ሆነ ለሥልጣን ሊኖር የሚገባውን ትርጉም ያዛባ ሆኖ ታይቷል፡፡ በተለይም ከከተማ እንቅስቃሴ ወደ ፓርቲ-ፖለቲካ የተሻገሩት ኢህአፓ እና መኢሶን፤ መጨረሻቸው ይታወቃል፡፡ 

አመፅን የአብዩት ተጠባቂ ክስተት አድርጎ ለሚያየው ትውልድ ከግምት በላይ መከራን ሲያሸክመው የቀጣዩን ጊዜያት የአገሪቱን ፖለቲካ ደግሞ ይበልጥ አወሳስቦታል፡፡ (ይህን ነው የ50 ዓመቱ የኢትዮጵያ አዕምሮ ምለው)

አብዮቱን ጠልፎ ወደሥልጣን የወጣው ደርግ፣ ሥልጣኑን ለማጽናት የከፈተው የቀይ ሽብር ዘመቻ እና በዛኛው ጽንፍ የታየው መልሶ ማጥቃት ቀድሞውንም ልዩነቶችን በጉልበት የመፍታት የአመፅ ባህል ባዳበረች አገር ተጨማሪ ዕዳ መሆኑን በተግባር አሳይቷል፡፡

ለተደራጀ የፓርቲ ፖለቲካ እንቅስቃሴ እንግዳ በሆነችው ኢትዮጵያ የልዩነት መፍቻ መንገዱ ከነባሩ ባህል አለመለየቱ የመደራጀት ትርጉም አሉታዊ ምስል አንዲይዝ አድርጓል፡፡

የቀዩም ሆነ የነጩ ሽብር ድርጊቶች ድምር ውጤት የአገሪቱን የፓርቲ-ፖለቲካ እንቅስቃሴ በአጭሩ የገታ፣ ለህብረ-ብሄራዊ ኃይሎች መበታተን እና ለዘውግ ተኮር ነፃ አውጭ ኃይሎች እንቅስቃሴ መበረታታት በር ከፋች ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡

የአማራ ክሬም ጭንቅላቶች ከግራና ከቀኝ እንዴት መበላት እንደጀመሩ ከሕዳር 14/1967 የስድሳዎቹ ግድያ ጀምሮ ትራጀዲውን መቁጥር ነው፡፡ 

በነገራችን ላይ አብዩቱን ኦዲት ስናደርገው፡- በዜጎች ማኅበራዊ ግንኙነቶች ላይም ሆነ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ አሁን ድረስ ለሚስተዋሉ አድርባይነት እና አስመሳይነት፤ ፅንፈኝነት እና ተነጣይነት የሽብሮቹ መዘዝ ስለመሆናቸው በማኅበራዊ ሳይንስ መምህራኑ በተደጋጋሚ የተወሳ ጉዳይ ነው፡፡ 

ባለፈው ሃምሳ ዓመት የኢትዮጵያ ዘመናዊ ፖለቲካ ያሳለፋቸው በጎም ሆነ በጎ ያልሆኑ ምዕራፎች፣ በፖለቲካ ኃይሎች ላይ በአሰላለፍ ብቻ ሳይሆን በአመለካከት እና በባህሪ ደረጃ የራሳቸውን ተፅዕኖ ሲያሳርፉ ታይቷል፡፡

በዚህ ረገድ ጎላ ብለው የሚጠቀሱት በአብዮቱ ማግስት የታየው የሽብር ድርጊት፣ ድህረ-ደርግ የተሞከረው የሽግግር መንግሥት መጨናገፍ፣ የምርጫ ዘጠና ሰባት መኮላሸት፣ የ2010ሩ የለውጥ ዕድል የተጨናገፈበት መንገድ በየራሳቸው አንጓ የሚታዩ ቢሆንም የፖለቲካ ኃይሎች ላይ የአሰላለፍ (የትግል ስትራቴጂ)፣ አመለካከት እና ፖለቲካዊ ባህሪ ለውጥ አስከትለዋል፡፡ የፖለቲካ ባህላችንም በእነዚህ ምዕራፎች ተፅዕኖ ስር የተቀነበበ ሆኖ ይታያል፡፡

በነገራችን ላይ የመጋቢት 2010 የፖለቲካ አመራር ለውጥ፣ የኢሕአዴግ ፍርሰትና ወራሾቹ ይዘውት የመጡት የፖለቲካ ባህል (ኦሮ-ማራ – ኦሮ-ሴራ- ) የገዥው ፓርቲ ልዩነትን በኃይል የአፍታት ባህል የወለደው የወያኔ ጦርነት፣ … እነዚህ ልቃቂቶች ስለአብዩቱና ያሳደረብን ተፅዕኖ ብዙ የሚነግሩን ቁምነገር ያለ ይመስለኛል።

ወደኋላ ስንመለስ፣ በ1960ዎቹ መጨረሻ የታዩ የሽብር ድርጊቶች (በጥፋቱ ላይ እጃቸው የተነከረ መሆኑን ሳንዘነጋ) ህብረ-ብሔራዊ ድርጅቶቹን በመዋቅር ደረጃ እንዲከስሙ አድርጓል፡፡ በአንፃሩ ወያኔ፣ ሻቢያ፣ ኦነግ፣ ኦብነግ፣ አርዱፍ፣… የመሳሰሉ ዘውግ ተኮር ነፃ አውጭ ኃይሎች እየተበራከቱ እንዲሄዱ የትግሉን ሜዳ አስፍቷል፡፡

የ1983 ደርግን ውድቀት የ1966ቱ አብዩት ክሽፈት የወለደው አድገው የሚያቀርቡ ምሁራን ዓላማቸው ፖለቲካዊ ስለሆነ ዝርዝር ማለት ባያስፈልገውም አብዩቱ የከሸፈው ሕዳር 14/1967 ነው፡፡

ደርግ፣ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት አገራቸውን በአርበኝነትና በዓለም አደባባይ በዲፕሎማሲ ያስጠሩትን እነ ራስ መስፍን ስለሺን፣ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድንና ሌሎችን ‹ክሬም› የሆኑ በትምህርት ዝግጅትም በተሞክሮም የበሰሉ ሊቃውንት መጨፍጨፉ ሳያንሰው ተተኪውን ብሩህ አእምሮ የነበረውን ወጣት ያለ ርህራሄ ጨፍጭፎ፣ ከሁሉም በላይ አማራውን እስከዛሬም ድረስ ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል፡፡

በነ ጸሐፊ ትእዛዝ አክሊሉና ሌሎች ሊቃውንትና መሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ የፈጠረው ከፍተኛ ድንጋጤ ሳይሽር፣ በዚያው ላይ ቀይ ሽብር መጥቶ ከአዲስ አበባ እስከ ጎንደር፣ ከደሴ እስከ ማርቆስ፣ …ወዘተ በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ልጆች በግፍ ተጨፍጭፈዋል፡፡

ኢህአፓን ከሰመሉ የደርግ ተፋላሚ ኃይሎች ጋር ‹ወገናችሁ› የተባሉ የጎንደር ሃሙሲት፣ የበለሳ፣ የሰቆጣ አካባቢዎች በአየር ደብደባ ንጹሃን ረግፈዋል፡፡ መስከረም 2/1967 በይፋ  የጀመረው የደርግ ረግጠህ ግዛ አገዛዝ አማራውን በህይወቱም በክብሩም ሥርዓታዊ በደል አድርሶበታል፡፡

ይህ ተከታታይ ጭፍጨፋ በሕዝባችን ሥነ-ልቦና ላይ የፈጠረው ጠባሳ እስከዛሬም አልሻረም ማለት ይቻላል፡፡ የአማራ ሕዝብ ለብዙ ጊዜያት በአንገት መድፋት ቆፈን (trauma) ውስጥ እንዲገባ ያደረገው ደርግ ቢሆንም፣ የአማራ ምሁራን በዚህ ላይ እምብዛም ሲጽፉበት አይስተዋልም፡፡ (ብዙ ሊተነተን፤ በስፋት ሊጻፍበት የሚገባው የጥናት ዘርፍ ነበር)

በሰደድ፣ ኢጭአት፣ ወዝሊግና ሌሎችም ድርጅቶች ውስጥ በአመራርነትና በአባልነት የተሳተፉ፣ ግን ደግሞ አክራሪ ፀረ አማራ አቋም የነበራቸው አካላት አማራውን በጨቋኝነትና አድኃሪነት እየፈረጁ ከያለበት ማሳደድ የጀመሩት በዘመነ ደርግ ነበር፡፡ 

እነ ኢብሳ ጉተማ ወለጋ ላይ አማራውን በገፍ ያፈናቀሉት የደርግን የመሬት አዋጅ በመጠቀም እና የራሱን የአገዛዙን የፀጥታ መዋቅር በመጠቀም እንደነበር አይዘነጋም፡፡ የኢትዮጵያን አንድነት በሚያቀነቅን ድርጅት ውስጥ በአባልነት እየተሳተፉና ከፍተኛ ሥልጣን አግኝነተው እነሱ የሚሠሩት ሥራ ግን አማራውን ማፈናቀል ነበር፡፡

በደርግ/ሰደድ እና በኋላም በኢሕድሪ መንግሥት ውስጥ በከፍተኛ ኃላፊነት የተሳተፉ የአማራ ተወላጆች ቢኖሩም፣ ሥርዓቱ እንደ-ሥርዓት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ የአማራን ሕዝብ በእጅጉ የጎዳ ሥርዓት ነበር፡፡

አሳዛኙ ነገር የአማራ ልሂቅ ይህ የገባው ዘግይቶ መሆኑ ነው፡፡ የማህበራዊ ሳይንስ መምህራን “Threat Activates Identity, non activated identity is irrelevant” በሚል ብያኔቸው ያስተማሩትን እውነታ ተግደርድሮም ቢሆን ተቀብሎታል፡፡

ስጋትን እንደቡድን ለመቀበል ሲቸገር የኖረው ልሂቁ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን ምንያህል እንዳስቸገረ አይዘነጋም፡፡ ዛሬ ተመስገን የሚያስብለው ሀቅ ለጥቃት የወል ስሜት (sensitivity) የያዘ አማራ በመላ አገሩ ተነስቷል፡፡ ይህ ግን ከነ ግለቱ እንዲቀጥል የ50 ዓመቱን መከራ በትክክል የተረዳና አዲስ የታሪክ አቅጣጫ ማምጣት የሚችል የትግል ስትራቴጂ ቀይሶ መምራት ይጠይቃል፡፡  

__

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena 


ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News