Homeነፃ አስተያየትብልጽግና ያበለጸገው የመፈንቅለ መንግስት መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ የጎንዮሽ ጉዳት በወታደራዊ ዘመቻዎች ውድቀት እየተንጸባረቀ ነው

ብልጽግና ያበለጸገው የመፈንቅለ መንግስት መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ የጎንዮሽ ጉዳት በወታደራዊ ዘመቻዎች ውድቀት እየተንጸባረቀ ነው

Advertisement
World Wide Travel Group
ብልጽግና ያበለጸገው የመፈንቅለ መንግስት መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ

አበራ ገረመው 
ከሰሜን ዕዝ 

“የመከላከያ ሰራዊት ኩዴታ እንዳይሞክር አድርገን ሰርተነዋል”  አለ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባገባደድነው አመት በአንድ ስብሰባ ላይ በይፋ ለፓርላማ ሲገልጽ፡፡ ፓርላማው የዚህ አባባል  አደገኝነት፣ምንነትና አንድምታ  ምን ማለት አንደሆነም ሳይጠይቅ ተቀብሎት አልፎታል፡፡ ሰራዊቱም ምንነቱን ሳይረዳ  በየቦታው መስወአትነት እየከፈለ ነው፡፡ አንዳንድ ሚዲያዎችም ምንም አይነት መሰረተ ሃሳብ ላይ የተመሰረተ ትንተና ሳይሰጡ በደፈናው ሲተነትኑና ሲያሞካሹ ከረሙ፡፡ እውነታውን ለህዝብ ለማሳወቅ  በንድፈ ሃሳብና   በመረጃ የተደገፈ ትንታኔ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ይህ መጣጥፍ ተዘጋጅቷል፡፡ 

የአባባሉን ትርጉም በመረጃ አስድገፌ በኋላ እተነትነዋለሁ፡፡ የዚህ አባባል አንድምታው ግን በሀገር ውስጥ በተጋጋሉ ግጭቶች  መከላከያ ሰራዊታቸው  አሸናፊ እንዳይሆን ያደረገውን  ምክንያት  ጠ/ሚሩ በራሳቸው አንደበት  በተዘዋዋሪ መንገድ ለፓርላማውም ሆነ ለህዝብ መናገራቸውን ልብ ይሏል፡፡ ይህንን ለማብራራት በኩዴታ የተደረገ ንድፈ ሃሳብ መነሻ ላድርግ! 

በኩደታ መቆጣጠሪያ  ስልት ላይ የተደረገው ጥናት አንደሚያሳየው ሁለት መሰረታዊ የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስልቶች አሉ፡፡ የመጀመሪያው በዴሞክራቲክ መንግስታት የሚተገበር  ሰራዊቱን ፕሮፌሸናል ሰራዊት አድርጎ መገንባት ሲሆን፤ ሁለተኛው በአምባገነን መንግስታት ስራ ላይ የሚውል   የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡  ጠ/ሚሩ  ከእነዚህ የትኘውን ተጠቅመው ነው ሰራዊቱ ኩዴታ አንዳይከጅል ያደረጉት ተብሎ ብጠየቅ ፕሮፌሸናል ሰራዊት በመገንባታችን ነው  ብለው  እንደሚያብራሩን ከባህሪያቸው ተነስተን በርግጠኝነት መናገር  እንችላለን፡፡ ነገር ግን ፕሮፌሸናል ሰራዊት ግንባታ ከዴሞክራሲያዊ ስርአት ግንባታ ጋር በቀጥታ የተሳሰረ  በመሆኑ አሁን በኢትዮጵያ ባለው የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ መቀልበስ ሲታሰብ የእሳቸው ማብራሪያ  ሙልጭ ያለ ማደናገርያ አንደሚሆን ለማወቅ የነቃ አእምሮ ያስፈልጋል፡፡   ስለሆነም  ጠ/ሚሩ ሰራዊቱ ኩዴታ እንዳይከጅል አድርገን ሰርተነዋል ሲሉ  ሁለተኛውን አመክኒዩ( የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ)  ተግባራዊ ማድረጋቸውን እየነገሩን አንደሆነ  ገልጽ  ነው፡፡ 

ዴሞክራት መንግስታት ኩዴታ አያስጨንቃቸውም፡፡ ምክንያቱም ወታደሩ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ እንዲገባ የሚጋብዙ የፖለቲካ ችግሮችን በሚዲያ ነጻነት እና በሶስቱ የመንግስት አካላት (ህግ አውጪ፣ህግ አስፈጻሚና ህግ ተርጓሚ አካላት መካከል ባለው ቼክ ኤንደ ባላንስ ) እርስ በርስ ቁጥጥር በመኖሩ ምክንያት እልባት ያገኛሉ፡፡ ይህ ሁኔታ ሰራዊቱ ፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ የማይገባ ፕሮፌሸናል ሰራዊት  ሆኖ  ስለሚገነባ  የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስልት መተግበር አያስፈልገውም፡፡ ማለትም ዴሞክራሲያዊ ስርአት ሲኖር ዴሞክራሲ  ራሱ በራሱ ኩዴታን ይቆጣጠራል ማለት ነው፡፡ 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

አምባገነን መንግስታት ግን  ኩዴታ ያስጨንቃቸዋል፡፡ ምክንያቱም የሚዲያ ነጻነት፣የሃሳብ ነጻነትና የመንግስት አካላት መካከል ያለው ቼክ ባላንስ የላላ በመሆኑ አስፈጻሚው አካል ፈላጭና ቆራጭ ብቻ ሳይሆን አፋኝ በመሆኑና በህብረተሰቡ ዘንድ ያሉ የፖለቲካ ጥያቄዎች ስለማይፈቱ ችግሩ ተባብሶ ይቀጥልና የወታደሩን ጣልቃ ገቢነት ይጋብዛል፡፡ ስለሆነም አምባገነን መንግስታት ኩዴታ ስለሚያሰጋቸው የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂዎችን ይተገብራሉ፡፡ 

አምባገንን መንግስታት የሚተገብሯቸው የኩዴታ መጣጠሪያ ስልቶችን ማብራራቱ ለተነሳንበት ጥያቄ መልስ ይሰጠናል፡፡  አምባገነን መንግስታት የሚተገብሯቸው የኩዴታ መቆጣጠሪያ  ስልቶች  ምን ምን ናቸው? 

አንዱ ስልት የሰራዊቱን ከፍተኛ አዛዦች በጥቅም መያዝ(spoills) ነው፡፡ የሰራዊቱ  ከፍተኛ አመራሮች በተለይም ጀኔራሎች ለኩዴታ ሊውል የሚችል ሀብትና የሰው ሀይል ማነቃነቅ የሚያስችል ስልጣን ስላላቸው በጥቅማጥቅም አፋቸውን ሸብበው ይይዛሉ፡፡ ኩዴታ ልጠነስሱ ይችላሉ  ተብለው የሚሰጉ አዘዦችን ደግሞ በስለላ መረባቸው አማካይነት ይለዩዋቸውና ዕድሜያቸው  ለጡረታ ሳይደርስ በጡረታ ማሰናበትን ጨምሮ  በልዩ ልዩ  ምክንያቶች ከሰራዊቱ ማግለል፣በዲሞሽን በማይረባ ቦታ ላይ መመደብ፣ ከመዋቅሩ እንዲወገዱ ማድረግና መሰል እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ 

 ሁለተኛው ስትራቴጂ ማህበረሰባዊ ትስስር/Communal tie ነው፡፡ በብሄር፣ በጎሳ፣በሀይማኖትና በርዕዮት ዓለም ትስስር  ለአገዛዙ ታማኝ ሊሆኑ የሚችሉ መኮንኖችንና ጀኔራሎችን በከፍተኛ እና ቁልፍ ቦታዎች ላይ መሾም፤ጥቅማ ጥቅም መስጠትና ሞራላቸውን  በመገንባት ለገዢው ፓርቲ ታማኝ ሎሌ አድርገው ያስቀምጣሉ፡፡  ከማህበረሰባዊ ትስስር ውጪ የሆኑ  መኮንኖችን  ታማኝ የሆኑ አባላትን በውስጣቸው በመሰግሰግ እየሰለሉ  ከገዢው ፓርቲ ያፈነገጠ አስተሳሰብ ያላቸውን መኮንኖች መፈናፈኛ ያሳጡና በማሸማቀቅ የአገዛዙን ዕድሜ እንዲራዘም ያድርጋሉ፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ሶስተኛው ማሸጋገር/Diversion ስልት ነው፡፡ አምባገነን መንግስታት በሀገር ውስጥ የፖለቲካ ውጥረት ሲነግስ  ወይም መንግስታቸው በህዝብ ዘንድ ያለውን ቅቡልነት ሲያጣ  ወታደሩ ይህንን ተጠቅሞ ኩዴታ እንዳያካሂድ ውጫዊ ጠላት ይፈጥራሉ፡፡ ውጫዊ ጠላት ተፈጠረ ማለት ሰራዊቱ ጸጥታውን ለማስከበር ያስባል አንጂ ኩዴታ ለመጠንሰስ   ፍላጎቱ ይኮላሻል የሚል እምነት አላቸው፡፡ የህዝቡም ትኩረት ከውስጥ ይልቅ ወደ ውጪ  ስለሚሆን በገዢው አምባገነን መንግስት ላይ በየ አቅጣጫው የሚያሳርፈው ጫናና ውጥረት ያርግባል የሚል አስተሳሰብ ያሰርጻሉ፡፡ በዚህን ግዜ የውስጥ ፖለቲካ ውጥረት ይረግብና ስልጣናቸው ይራዘማል፡፡  

ሰራዊትን  በአለም አቀፍ ሰላም ማስከበር ተልኮ  ማሰማራት ሌላኛው   የማሸጋገር ስትራቴጂ አካል ነው፡፡ ድህነት ያቆረቆዘው   ወታደር  ወደ ሰላም ማስከበር ዘምቶ ከሰላም ማስከበር የሚገኘውን ጥቅም አግኝቶ ኑሮን ለማሻሻል  ያልማል እንጂ ኩዴታ አካሂዶ ከኩዴታ እጠቀማለሁ ብሎ አያስብም፡፡ 

አራተኛው ስልት ተጓዳኝ ወታዳራዊ አደረጃጀት መፍጠር Parllel military organization ነው፡፡ አምባገነን መንግስታት ከላይ የተጠቀሱ የኩዴታ ስትራቴጂዎችን ተግባራዊ አድርገው አንኳ ሰራዊታቸውን አያምኑም፡፡ ሰራዊቱ እነዚያን የኩዴታ አጥሮችን ጥሶ ኩዴታ ሊያካሂድባቸው ይችላል ብለው ስለሚሰጉ  ከመደበኛ ሰራዊት በተጓደኝ ለርዕሰ ብሄሩ ብቻ የሚታዘዝ ልዩ ኤሊት ሀይል ያደራጃሉ፡፡ ይህ ኢሊቲ ሀይል ለመከላከያና ለጦር ሀይሎች ጠ/ኢታማዦር የማይታዘዝ፣በርዕሰ ብሄሩ ትዕዛዝ ብቻ የሚንቀሳቀስ፣የስልጣን ቀበኛ የሆነ ማንኛውንም ሀይል ለመደፍጠጥ የሚዘጋጅ ሀይል ነው፡፡ ይህ ቅልብ ሀይል ከሌላው ሰራዊት የተለየ ስልጠና፣የተለየ ጥቅማጥቅምና የተለየ ክብርና ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ከሌላው መደበኛ ሰራዊት ጋር በአይነ ቁረኛ ይተያያል፡፡ ኩዴታ መጠንሰሱ ሲያቅ ወዲያው ተወርውሮ ጠንሳሹን ሐይል ድባቅ  አንድመታ አድርገው ያደራጁታል፡፡ 

ጠ/ሚሩ  “መከላከያ ሰራዊት ኩዴታ አንዳይሞክር አድርገን ገንብተናል” ሲሉ ከላይ የተጠቀሱ የኩዴታ መቆጣጣሪያ ስልቶችን መተግበራቸውን እየነገሩን ነው፡፡ ፓርላማውም ይህ ምን ማለት አንደሆነ ሳይጠይቅ አጨብጭበውለታል፤ ደጋፊ ሚዲያዎችም አንደ ጀብዱ ቆጥረው ተንትነውታል፡፡ 

- Advertisement -

የብልጽግና መንግስት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት፤የዜጎች ደህንት መፍጠር ባለመቻሉ ሀገሪቱ በማያባራ የግጭት አዙሪት ውስጥ በመግባቷ  አገዛዙ ህዝባዊ ቅቡልነት  አጥቷል፡፡ ዕድሜውም እያራዘመ ያለው   በሶስት ነገሮች ነው፡፡ በሰራዊቱ መስዋትነት፣ አፋኝ የመረጃና ስለላ መረቡ እና ፕሮፖጋንዳ በሚያራግቡ ሚዲያዎች ህዝቡን በማደናገር  ነው፡፡ ለዚህም ነው  የብልጽግናው ጠ/ሚር ሰራዊቱ አንድ ቀን እንዳይነሳበት  በመስጋት የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂዎችን ያበለጸገው፡፡ 

የብልጽግና መንግስት ኩዴታ ለመቆጣጠር በሚል ለስርአቱ ታማኝ ለሆኑ ጄነራል መኮንኖች በአዲስ አበባ ከተማ ከ400-1000 ካሬ መሬትና አስር ሚሊዮን ብር ለያንዳንዳቸው በመስጠት  የስርአቱ ምሽግ አንዲሆኑ አፋቸውን ሸብቧል፡፡ሌሎችንም በዚህ ጽሁፍ  የያልተገለጹ በርካታ ጥቅማጥቅሞችን በችሮታ በመስጠት ዕድሜውን እያራዘመ ይገኛል፡፡ የጥቅም ተጋሪ ጀኔራሎች  የጠ/ሚሩ አመራር ሰራዊቱ በውስጥ ግጭት እስከቀበሌ ተበትኖ አቋሙ እየተልፈሰፈሰ እንዳለ እያዩ ትንፍሽ እንኳ ብለው ምክረ ሃሳብ መስጠት አቅቷቸዋል፡፡  ምስኪኑ ወታደር ግን በረሃ ለበረሃ እየተንከራተተ ዱር ቤቴ ብሎ ዕድሜውን ይገፋል፡፡ ልጆቹና ቤተሰቡ የረባ መኖርያ ቤት አጥተው በስቃይ ህይወታቸውን ይገፋሉ፡፡ አዲስ አበባ ጃን ሜዳ ፈረሰኛ ግቢ ተብሎ የሚታወቅ ግቢ  ውስጥ በፈራረሱ ቤቶች፣ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰራ፤ እንኳን የሰው ልጅ አይጥ ይኖራል ተብሎ በማይታሰብ መጠለያ ውስጥ የሚኖሩ ወታደሮች ህይወት ይዘገንናል፡፡   በሌላ በኩል ታማኝ አይደሉም ላሉዋቸው ጄነራሎች በአዲስ አበባ የሚሰጠውን መሬት መስጠትን በመከልከል ኮንዶሚኒየም እንዲሰጣቸው አድርጓል፡፡ የሚገርመው ነገር ይህንን የጥቅማጥቅም ልዩነት በሰራዊቱ አባላት መካከል ለመፍጠር የመከላከያ ሰራዊት አዋጁን ሁለት ጊዜ በሁለት አመት አሻሽለዋል፡፡ ይህ ነው በጥቅማጥቅም መደለል ማለት፡፡ 

 በበልጽግና የኩዴታ መቆጣጠሪያ ፓኬጅ ውስጥ ከተካተቱ የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስልቶች ውስጥ በርዕዮተ ዐላምና በብሄር ትስስር  ሰዎችን በቁልፍ ቦታ ላይ መሾም አንዱ ነው፡፡ ከለውጡ በፊት የነበረው የብሄር ብሄረሰብ ስብጥር እንድፈርስ ተደርጓል፡፡ የኦሮምኛ ተናጋሪዎች ስብጥር ከፍ እንድልና ቁልፍ ቦታዎች በእነሱ ስልጣን ስር እንዲሆን ተደርጓል፡፡ ለምሳሌ ጠቅላይ ኢታማዞር ሹምን ጨምሮ  የሎጄስቲክ፣የመረጃ ፣የመገናኛና ኮሙኒከሽን፣የሰው ሀብት አመራር  ዋና መመሪያዎችና በስራቸው ያሉ መመሪያዎች በሙሉ በእነዚያ ታማኝ በሚባሉ ሰዎች ተይዘዋል፡፡  ለስርአቱ ታማኝ ናቸው የተባሉ ከፍተኛ መኮንኖችና ጄነራሎች የጡረታ እድሜ ቢደርስ እንኳ ያለ ገደብ እየተራዘመላቸው ስርአቱን አንዲያገለግሉ ይደረጋል፡፡  በሌላ በኩል የአናሳ ብሄሮች ስብጥር በጄነራል መኮንንና በከፍተኛ መኮንነን ደረጃ እንድመናመን ተደርጓል፡፡  የሶማሌ፣የቤንሻንጉል፣የደቡብ ህዝቦች…ወዘተ ስብጥር ጭራሽ ጠፍቷል፡፡ ይህ ማለት ግን አናሳ ብሄሮች የወታደር ገባሪ አንጂ በመከላከያ ሰራዊት የአመራር ሚና እንዳይኖር ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል መከላከያንና ጠ/ሚኒስትሩን በደህንነትና በወታደራዊ ጉዳዮች የሚያማክሩት የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ሳይሆኑ የቀድሞ ሰራዊት አባላት መሆኑ በተቋሙ የባህል መጣረስ አንዲከሰት አድርጓል፡፡  ጠ/ሚሩ የሰሜኑን ጦርነት ለማሸነፍ በወያነ ላይ ከፍተኛ ጥላቻ ያላቸውን የቀድሞ ጦር መኮንኖችና የደህንንት አማካሪዎችን ወደ ስርአቱ አስገብቶ አስካሁን እያማከሩት ይገኛሉ፡፡ የሚያማክሩትም ዘመኑን በሚዋጅ ዴሞክራቲክ አስተሳሰብ ሳይሆን በነበራቸው የደረግ ዘመን መርሆ ላይ ተመስርተው ነው፡፡ በዜጎች ላይ በመረጃና ደህንነት አባላት የሚፈጸም ግድያ፣አፈናና  አስገድዶ ገንዘብ መመንተፍ የእነሱ ማማከር ውጤት ነው፡፡ በዚህ የተነሳ በሰራዊቱ ዘንድ ከለውጡ በፊት በመጠኑም ቢሆን ተገንብቶ የነበረው ዴሞክራሲያዊ ባህል ተሸርሽሮ ዴሞክራሲያዊ ያልሆኑ ልምምዶች፣ ብልሹ አሰራርና ስንፍና በመዋቅሩ ውስጥ ሰፍኗል፡፡ በጥቅም ተሳስሮ የመንግስትን ሀብት ወደ ግል ኪስ ማስገባት፣የመንግስትን ሪሶርስ ለተገቢው ክፍል ከመመደብ ይልቅ ጠቅልሎ  ኢታማዞር ሹሙ እንደፈለገ ለሚወዷቸው ይመድባል፡፡ መከላከያ ሚኒስትሯ ምንም ዐይነት ሚና የላትም፡፡ ክፍሎች ተገቢ በጀት አይመደብላቸውም፡፡ የዛሬ ሶስትና አራት አመት  የሚመደብ በጀት ኮፒ እየተደረገ ይመደብላቸዋል፡፡ በጀት ሲፈቀድ ግን በአሁናዊ ገበያ ተስልቶ ለመከላከያ ይመደባል፡፡ በጀቱ በማዕከል እንደቀመጥ ተደርጎ ባለስልጣናቴ እንደፈለጉ ያባክኑታል፡፡ 

ሪፓቢሊካን ጋርድ ብልጽግናን   ሺ አመት ለማንገስ  የተፈጠረ  የዐቢይ ሌጋስ ነው፡፡ በልዩ ሁኔታ  በውጭ ሀይሎች ድጋፍና ስልጠና የተደራጀው ይህ ሀይል በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ  ደናማ ተራሮች ውስጥ ማንም በማያይ ሁኔታ በሰውር ካምፕ ሰርቶ  ቤተ-መነግስቱን የሚያልሙ ሀይሎችን  በአይነ ቁረኛ ይከታተላል፡፡  እንደ አስፈላጊነቱ ከበድ ያሉ ኦፕሬሸኖች ሲኖሩ እየተወረወረ  ተቀናቃኝ ሀይሎችን  ለማስወገድ ተልዕኮ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ሀይል የተደራጀው ኩዴታን ጨምሮ ለጠ/ሚሩ ስልጣን አስጊ የሆኑ ንቅናቄዎችን ለማፈን ነው፡፡ 

ይህ ሁሉ የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስልት ተግባራዊ ሆኖም የብልጽግና መንግስት የሀገሪቱ ቀውስ እየተባባሰ መጥቶ የወታደሩን ጣልቃ ገብነት የሚጋብዝ ሆኖ ተሰምቶታል፡፡ ለዚህ የዘየደው መላ  ውጫዊ ጠላት መፍጠር ነው፡፡ እናም በአሁኑ ወቅት ግብጽ ምስራቅ አፍሪካ ላይ የጀመረችውን የዲፕሎማሲ እንቅስቃሴ እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው ለግብጽ ዲፕሎማሲ ዘመቻ  ዲፕሎማሲያዊ አጸፋ ከመመለስ ይልቅ ኢትዮጵያ በብጽ ተወራለች እያሉ  የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀምረዋል፡፡  በታሪክ ጦርነት ተለይቷት የማያቃትን ሀገርና ህዝብ ገና ከሰሜኑ ጦርነት ሳታገግም፤ገና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሰሜኑ ጦርነት ሰመአታት  ደማቸው ሳይደርቅ፣አጽማቸው አንኳ ተሰብስቦ ወደ አንድ ስፍራ ተሰብስቦ በክብር  አፈር ሳይለብስ ለምስራቅ አፍሪቃው ጦርነት ህዝቡን ለማነሳሳት እየሞከሩ ነው፡፡ 

በምድር ላይ እንደ ግብጾች ቆቅ የለም፡፡ ግብጾች ሞኝ አይደሉም ቀጥታ ወታደራዊ ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ ሰነዝረው ዲፕሎማሲያዊ ወግዘት የሚከናነቡት፡፡ ግብጾች መሃማን አይደሉም የጉንደትና ጉራ ሽንፈት ለመጎንጨት በእግረኛ ጦር ኢትዮጵያን የሚሞክሩት፡፡ ግብጾች ከሀገራቸው ተነስተው የሱዳንን 1250 ኪሎሜትር መሬት አቋርጠው እግረኛ ጦር እያንጋጉ ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ጥሰው  በመግባት በባዕድ ሀገር  ሀብት ንብረታቸውን የሚያወድሙት፡፡ ለዚያውም የኤርትራና የሱዳን ፖለቲካዊ ድጋፍ ማግኘቱ ሌላ ፈተና በሚሆነበት ቀጠና፡፡  ግብጾች ጅሎች አይደሉም የህዳሴ ግድብን በአየር አጋይተው በማፍረስ  መላውን የግብጽና የሱዳን  ህዝብ  በጎርፍ አጥልቅልቀው የሚያጠፉት፡፡ ግብጾች ግብዞች አይደሉም የሀያላንን ይሁንታና የጎረቤቶቻችን ዲፕሎማሲያወ ድጋፍ ሳያገኙ ጦርነት አውጀው በለኮሱት ጦርነት የሚለበለቡት፡፡ ግብጾች ሞኝ አይደሉም  እርስ በርስ የሚባላና የሚገዳደል የኢትዮጵያ ህዝብ  በቀላሉ ማንበርከክ እየተቻለ   (ድምጽ አልበ የጦርነት ስትራቴጂ እያለ) በ21ኛው ክፍለዘመን መድፍና ታንክ እያንጋጉ  አምጥተው  የሚዋጉት፡፡  

 ወደ ሶማሊያ ጦራቸውን ያስገቡት ለዲፕሎማሲያዊ ኩፈሳ፣ለስለላ እና ውስጣዊ ግጭት በማበባባስ  ኢትዮጵያን አንበርክከው በአባይ ወንዝ ላይ አሳሪ ውል ማስፈረም የሚያስችል ተጽዕኖ መፍጠር  ወይም ለዘላለም እንዳትነሳ አድርገው በውስጥ  የማበጣበጥ  ግባቸውን አንግበው ነው፡፡ ለዚህ ስትራቴጂያቸው ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት የጦርነት ነጋሪት መጎሰሙ  ሞኝ ጩሄት ከመሆን በምን ይለያል፡፡ ግብጾች ሶማሊያ ሆነው ትኩስና ተጨባጭ መረጃዎችን  ስለ ኢትዮጵያ በመሰብሰብ የኢትዮጵያን ወርድና ቁመት ስፋትና ጥበት…በመመረጅ ስትራቴጂያዊ መረጃ ይሰበስባሉ፡፡ ቀጥታ ጦርነት ግን  ዜሮ ነው ባንልም   ሎጀስቲክ፣ዲፕሎማሲያዊና.ፖለቲካዊ ሁኔታ እና ርቀት እንቅፋት ይሆንባቸዋል  ብለን ማሰብ አንችላለን፡፡

እነሱ በነበራቸው ተነጻጻር ሰላም  የተነሳ የስለላ፣የዲፕሎማሲና የኢኮኖሚ ሀይላቸውን አሳብጠዋል፡፡ አቅማቸውን አዳብረዋል፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን ደግሞ በውስጣዊ መከፋፈልና ግጭት አቅማችን ተዳክሟል፡፡ ውስጣዊ ችግሮችን መፍታት ቅድሚያ የሚሰጠው የፖለቲካ ስራ ሆኖ ፈጦ ይታያል፡፡ ግብጾች የሚዋጉን ውስጣዊና ከጎረቤት ሀገሮቻችን ጋር ባሉን ቅራኔዎች ተጠቅመው ነው፡፡  ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ላይ አሳሪ ውል እንድትፈርም  ካልሆነም  ለማዳከም በሶማሊያ የታላቋ ሶማሌ ካርድ በእጃቸው አለ፡፡ በሶማሊያ በሚሰማራው  ሀይላቸው አማካይነት ኢትዮጵያ በልታ ያደረችውን ጭምር ለመሰለል  አዲስ በሶማሊያ በሚያሰማሩት ጦራቸው አማካይነት   የአፍረካ ሰላም አስከባሪ ሀይል  በመቀላቀል የዲፕሎማሲ ክንዳቸውን ለማፈርጠም ቋምጠው የሶማሊያን ይሁንታ አግኝተው የአፍሪካ ህብረት ይሁንታ እየተጠባበቁ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚካደውን የውስጥ ግጭት ማባባስ የቆየ ስትራቴጂያቸውን ሀገራቸው ሆነው በርቀት ማሳካት ባለመቻላቸው  ሶማሊያ ሆነው በቅርበት ለመምራት መልካም ዕድል አግኝተዋል፡፡ 

የአሁኑ የግብጽ ጦርነት በፉከራና በሽለላ የምናሸንፈው ጦርነት አይደለም፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ደሙና ስጋው ተበልቶ አጽም ብቻ የቀረው ፤ብዛት ካልሆነ ጥራት የሌለው  የደከመ  መከላከያ ሰራዊት ግብጽ ቀጥታ ጦርነት ቢታውጅ እንዴት ተዋግቶ ሊያሸንፍ ይችላል? ደግሞስ የተፋፋመውን  የውሰጥ ግጭት አንዴት አስታግሰን ነው ከግብጽ ጋር የምንዋጋው? የብልጽግና መንግስት ለዚህ የተደራጀ መልስ እንደለለው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡  ዳሩ ግን ግብጾች የዲፕሎማሲ፣ የስለላና የቅልበሳ ጦርነት ካልሆነ ቀጥታ ጦርነት ሊያውጁ እንደማይፈልጉና እንደማይችሉ እየታወቀ ግብጽ ጦርነት አውጃብናለች ብሎ ማራገብ የውስጥ ቀውስ በውጭ ጠላት ለማላበስ መጣር ካልሆነ ሌላ ምን ልባል ይችለል፡፡ እንዲህ ዓይነት አካሁድ በጠብ ጫርነት ኢትዮጵያን አስፈርጆ መልሶ እንዳይበላን ምን ማደረግ ያስፈልጋል የሚለውን ማጤን አይሻልምን?

በቀጠናው የተጋጋለው የጂኦ ፖለቲካ ወበቅ እየተጋጋለ ሂዶ ወደ ቀጥተኛ ግጭት የሚመራ ክስተት ይፈጠር ይሁን ወይስ እንድያ ሞቅ ቀዝቀዝ  እያለ ይቀጥላል? የሚለው ወደፊት የሚታይ እንጂ አሁን በግልጽ የታወጀ ጦርነት በለለበት የጦርነት ጉሰማው አንዱ የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስትራቴጂ ሆኖ የህዝቡንና የመከላከያ ሰራዊት ቀልብ በውጭ ጠላት ላይ ለማሳረፍ የተዘየደ ስልት  ነው ከማለት ሌላ ምን ይባላል፡፡ 

ሲጠቃለል የጠ/ሚ ዐቢይ  የኩዴታ መቆጣጠሪያ ስልት ብዙ  የጎኒዮሽ ጉዳት አስከትሏል፡፡ ዋናውና ትልቁ ጉዳት የሰራዊቱ አዛዦች በችሎታና በእውቀት ደረጃቸው ተለክተው ሳይሆን ለአገዛዙ ባላቸው ታማኝነት ብቻ የሚሾሙ በመሆኑ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ብቃት ላይ ከፍተኛ መውረድ ተከስቷል፡፡   የሀገሪቱን የፖለቲካ ቀውስ  በፖለቲካዊ መንገድ ከመፍታት ይልቅ በሀይል ለመፍታት ካለው ፍላጎት የተነሳ  አገዛዙ በወታደሩ፣ በስለላ መዋቅሩና በፕሮፖጋንዳ ማሺኔሪዎች  መተማመን ተያይዞታል፡፡  የሰራዊቱም ሆነ የፖለቲካ አመራሩ በሀገሪቱ እንደ አሸን የፈሉ የታጠቁ ሀይሎችን ወይ በጉልበት አሸንፎ ካልሆነም በፖለቲካዊ መንገድ በሰላማዊ ትግል አንበርክኮ የሀገሪቱን ሰላምና ደህንነት ሊያረጋግጥ አልቻለም፡፡  ይህንን የውስጥ ቀውስ ማርገብ  ስለተሳነውም በአሁኑ ወቅት የውጭ ጠላት በመሳል የውስጥ ቀውስ ወደ ውጭ ለማላከክ ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

የፈረደበትን የደሃ ልጅ በጦርነት እሳት ለመማገድ ሽር ጉዱ፣ፉከራዉ የሴራ ትንተናው በኢትዮጵያ ሰማይ እያስገመገመ ነው፡፡ 

__

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ትዊተር ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News