
ያሬድ ኃይለመስቀል
ዘሬ ያለወትሮዬ ለሊት ነቃሁና ስልኬን ስከፍት አንድ ኢሜል አነበብኩ። ነገሩ ስለከነከነኝ ነቃሁና መመለስ ገባሁ። ይህ ጥያቄ በብዙ ሰው ይነሳል። አሁን ደግሞ የብልጽግና መንግስት እንደ እውነታ ቆጥሮት ወደ ፓሊሲ አሳድጎታል። እንደውም ማክስ ዊበር በመደመር መጽሀፍ ሳይቀር ስለተጠቀሰ ስህተቱ እንደ እውነት እያደገ መምጣቱን አልወደድኩትም።
በኢሜል የደረሰኝ ክስ ኢትዮጵያ ያላደገችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአል ስላበዛች ነው የሚል ነው። በእርግጥ ይህ እውነት ነውን? እድገትስ የሚመጣው በማሰብና በመፍጠር እንጂ 365 ቀን መሬት በመቆፈር ይሆን ብዮ መጻፍ ጀመርኩ?
ለምን ከነከነህ ካላችሁ ይሄንን ለመጀመሪያ ግዜ አይደለም የምሰማው። እንቅልፌን ያስጠፋው ማንበብና መጻፍ ይችላል ብዬ የማስበው ሰው ሌሊት ላይ ይሄንን ክስ መሰል ጽሁፍ ስላጋራኝ ነው።
ክሱ አዲስ አይደለም። እኛ ስናድግ በኮሚኒስቱ ካድሬዎችና፤ ተራማጀ ነን የሚሉ በየኢትዮጵያ ተማሪዎች ሳያላምጡ የዋጡት እውነት መሰል መርዝ ነው። አሁን ደግሞ ጭራሽ የመንግስት የብልጽና ወንጌል አስተምህሮ ሆኖ የኦፒዲኦ በፕሮቴስታንት እምነት ፓለቲከኞች ደግመው ደግመው ሲሉት ይሰማሉ።
በእርግጥ ኢትዮጵያ ደሀ የሆነችው የኦርቶዶክስ እምነት በአል ስላበዛች ይሆን?
ከደርግ በኋላ ለተወለዳችሁ 70% የምትሆኑት ኢትዮጵያውያን እንዲረዳ ያደኩበትን ዘመን ላስረዳ። እኔ ወጣት እያለሁ የኢትዮጵያ አብዮታዊ ወጣቶች ማህበር (አኢወማ) የሚባል የወጣቶች ማህበር ነበር። ሁሉም ወጣት በየቀበሌው መደራጀት ግድ ነበር። የዚህ የወጣቶች መሀበር አላማ በአጭሩ ኮሚኒስት ወጣት መፍጠርና አብዮት ለሚባልው ጣኦት የመስዋዕት በግ ማዘጋጀት ነበር። እኔም ማትሪክ አልፌ ዮኒቨርሥቲ ባልገባ ኖሮ ብሄራዊ ውትድርና ተወስጄ ዘምቼ አጥንቴ ናቅፋ፤ አፋቤት ወይን ከረን ኮረብታ ላይ ይገኝ ነበር።
ደጋግሞ የተባለ ነገር እውነት ይመስላል። አሁን መለስ ብዬ ሳነብ ማርክሲስቶች ሰውን ለማሳመን ከፈለክ አንደኛ ቃሉን ብልግና (vulgarization) አድርገው ይላሉ። ሁለተኛ ደግሞ ደጋግመው (repetition) ይላሉ። ለምሳሌ በአይናችን በቅርብ በተግባር እንደ ሰደድ ሲቀጣጠል ያየነው ቮልጋራዜሽን “ጁንታ” የሚለው ቃል ነው። በምን ያህል ፍጥነት እንደተዛመተና ተቀባይነት እንዳገኘ ሁላችንም ያየነው ነው። ጁንታ ማለት ትግሬ እንደማለት ሆኖ ነበር። ሌላው ህወሓት አዲስ አበባ ሲቆጣጠር የተጠቀመበት ተመሳሳይ ቃል “ነፍጠኛ” የሚለው የብልግና ቃል (vulgarization) ነበር። ነፍጠኛ ማለት ዐምሓራ ማለት ነበር።
ይሄንን ያመጣሁት የድግግሞሽ ሁላችንም ሰላባ እንደሆንን ለማሳየት ነው። እኔመ ወጣት እያለሁ በአል በዝቷል ተብሎ ስለተነገረኝ በእርግጥ ሀገሬ ደሀ የሆነችው በአል በማብዛትዋ ይሆን ብዬ ነበር።
ይህ ውሸት መሆኑን የገባኝ እንግሊዝ ሀገር ስሄድ ነው። እንግሊዝ ሀገር ሄጄ የሰራሁባቸው ካንፓኒዎች በኢሮፕም ፋብሪካዎሽ ስለነበራቸው ድጋፍ ለመስጠት እጓዝ ነበር። ፈረንሳይ፤ ስፔን፣ ቼክ እና በእንግሊዝ መሀከል ተመላልሼ ሰርቻለሁ።
ያየሁት ነገር ፈረሣይ ሀብታም ሀገር ናት ይሁንና በሳምንት 35 ሰአት ነው ሰው የሚሰራው።በዛ ላይ ወደ 25 የስራ ቀናት ወይንም 5 ሳምንት የዓመት እረፍት አላቸው። ይህ ለጀማሪ ተቀጣሪ ሲሆን በአመት 1 ቀን ይጨምራል። በተጨማሪ 11 የሀይማኖትና የህዝባዊ በአል የእረፍት ቀናት አሉዋቸው።
እንግሊዝ ደግሞ 37.5 ሰአት በሳምንት እንሰራ ነበር። ቅዳሜ በየትኛውም የኢሮፕ ሀገር የእረፍት ቀን ነው። እኔም አርብ ግማሽ ቀን ወይንም ዘጠኝ ሰአት ስራ እንጨርስ ነበር። የአመት እረፍትም ከ25 ቀን ነው በያመቱ አንድ ቀን ይጨምራል። በዚህ ላይ 8 ቀናት ባንክ ሆሊዴ ተብለው ሰኞ ሰኞ የእረፍት ቀን ይባላሉ። ሰኞ እረፍት የሚሆንበት ምክንያት ሰው ረዘም ያለ የዕረፍት ቀን እንዲኖረው ነው። እኔ ኢትዮጵያ እያለሁ ደግሞ 46 ሰዓት ነበር የምሰራው። ቅዳሜ ግማሽ ቀን የስራ ቀን ነው ግን በጣም ደሆች ነን።
ረጋ ብዮ ሳስብ የኢትዮጵያ ገበሬ ደግሞ በሳምንት 70 ሰአት ነው የሚሰራው። የእንግሊዝና የፈረንሳይ ገበሬ ደግሞ ግማሽ አመት ምንም አይሰራም። መሬቱ በረዶ ይለብሳል ቀኑም ያጥራል። እሳቱን አንድዶ እየሞቀ፤ ሲኒማ እየየ፤ስፖርት እየሰራ ወይኑንና ኮኛኩን እየጠጣ ጨለማውን ያሳልፋል።
ታድያ ገበሬው 70 ሰዓት የሚሰራበት ሁገር ለምንድነው የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የምንከሳት ብዬ ማሰብ ጀመርኩ።እውነታው የኢትዮጵያ ገበሬ ቢያንስ ቢያንስ 70 ሰአት እየሰራ ማለትም የፈረንሳዩን እጥፍ ሰርቶ እንደ ሰነፍ ይሰደባል?
አሁን ደግሞ ትላልቆቹ የብልጽና የፕሮቴስታንት መሪዎች ይሄንን ሲደጋግሙ፣ ስለ ማክስ ዌበር የፕሮቴስታንት ኢቲክስ ሲጽፉ ሳይ አልሰሜን ግባ በለው እላለሁ። ስለዚህ እነዚህን የስማ በለው ምሁራንን ቦታቸው ማስቅውመጥ ግድ ይላል።
80% በሆነው በገበሬው ህይወት
የኢትዮጵያ ገበሬ ከለሊቱ 11 ሰአት ተነስቶ ማታ አይን እስኪይዝ ድረስ ነው የሚሰራው። ቢያንስ ቢያንስ 12 ሰአት በቀን ይሰረል። ቤቱም ቢገባም ስራው አይቆምም። ከብት ይጠብቃል፤ እንጨት ይፈልጣል፤ ላም ያልባለ፤ በረቱን ይዘጋጋል፤ መኖ ለከብቶቹ ተሸክሞ ያስገባል። ከዛ እግሩንን ታጥቦ ያገኘውን በልቶ ጥዋት ለመነሳት ይተኛል። ከዛ ደግሞ ከለሊቱ 11 ተነቶ ዳቦውንና ቆሎውን ቋጥሮ ከብቱን አሰማርቶ ሞፈሩን ተሸክሞ ጥማዱን እየነዳ ወደ እርሻው ይሄዳል። አንግዲህ በወር አንድ ቀን በሰፈሩ ገብርኤል፤ ማርያም፡ መድሀኒያልም የሚነግስ ከሆነ ታጥቦ ነጭ ለብሶ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል።
ይህ ገበሬ በዋዛ ፈዛዛ ጊዜ ያጠፋል እንዳይባል በሰፈሩ ሲኒማ ቤት የለ፤ ቴሌቭዥን አያይ፤ የዘፈን ኮንሰርት አይካሄድ፤ ጋዜጣ አያነብ፤ ኳስ አይጫወት ጂም አይሄድ። ከስራ ውጪ ህይወት የለው ታድያ ክሱ እንዴት መጣ?
ሙሉ ሰዓት ስራ ላይ ነው የሚያሳልፈው። ሚስቱም እንዲሁ። ልጆቹም የህጻናት መብት ተሟጋች የለ 18 ዓመት አልሞላውም አይባል በእግሩ መሮጥ ከጀመረበት ቀን ጀምሮ ስራ አለው። ረጅም ሰአት በመስራት ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ እነ ጃፓንን ታሰለጥን ነበር።
ገበሬው የሚያርፍባት ቀን ብትኖር ይቺ ታቦት የሚወጣባት ቅዳሴ የሚቀሰስባት ቀን ናት። ከተገኘም ስጋም፤ ጥሩ ወጥም የሚበላብት ጠላም ጠትቶ ትንሽ አካሉን የሚያሳርፍባት ቀን ናት። ይህ ማለት ግን በዛን ቀን ስራ አይሰራም ማለት አይደለም። በዛ ቀን የሚስቱና የልጆቹ ስራ እንደውም ይጨምራል።
ታድያ ኮሚኒስት ተማሪዎቹ እና የብልጽግና ካድሬዎች ይሄንን ሀሳብ ከምን አመጡት ብዬ ማፈላለግ ጀመርኩ። ምንጩ ኢሮፕ ነው። አንደኛው ዳርዊን ነው፤ ሁለተኛ የቅን ገዢዎች ጽሁፍ ነው ሶስተኛው እራስ ማሞገሻ Max Weber /ማክስ ዌበት/ የሚባል ጸሀፊ The Protestant work ethic የሚለው ነው።
ቻርልስ ዳርዊን (1809-1882) ምን አለ?
የ19ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያው እሳቤ ቻርልስ ዳርዊን የዝግመተ ለውጥ ሀተታ አሳተመ። አፍሪካውያን ከዝንጀሮና ከሰዎች መሀከል ያሉ ፍጥረታት ስለሆኑ ለማሰብ፤ ለመፍጠር’ ለመስራትና ለማደግ መነሳሳት የላቸውም ስለዚህ አያድጉም የሚል ድምዳሜ ነበር። እንደውም ከዛ አልፎ በኢቮሊሽን ፉክክር ውስጥ መቋቋም ስለማይችሉ ይጠፋሉ ነበር ያለው። ዋሸህ አንዳትሉ የጻፈውን አንብቡ።
“At some future period, not very distant as measured by centuries, the civilized races of man will almost certainly exterminate, and replace the savage races throughout the world.” – Chapter 6 of “The Descent of Man,” Charles Darwin።
ይሄንን ዳርዊን የጻፈው 1871 ዓመተ ምህረት ነው። ዳርዊን ይሄንን ሲጽፍ ኢትዮጵያ የምትባል ጽሁፍ፤ ሳይንስ፤ ስነ ጥበብ፤ ስነ ህንጻ፤ ስነ ጠፈር፤ ስነ መንግስት፤ ስነ ፍልስፍና ያለት የጥቁር ሀገር መኖር የተረዳ አይመስልም። ከ25 አመታት ቦሀላ የዳርዊን ዝንጀሮ የተባለው ጥቁርና የጣልያን ጦር አድዋ ላይ ተሸነፈ። የዳርዊን ዝግመተ ለውጥ አፈር በላ። ዳርዊን ወታደራዊ ጥበብ፤ሰነ ጥበብ፤ ስነ ፍልስፍ፤ ስነ መንግስት ያለው ጥቁር ሰው መኖሩን ያወቀ አይመስለኝም። ዳርዊን ተመልሶ መጥቶ ቢሆን እሱ ይጠፋል ያለው ጥቁር የአሜሪካን ፕሬዚዳንት ሆኖ ቢያይ መጽሀፉን ሰብስባችሁ አቃጥሉልኝ ባለ ነበር።
የቅኝ ገዢዎች ሰነፉ ጥቁር ትርክት
አፍሪካ ያላደገው ሰነፍ ስለ ሆነ ነው የሚለው ትንታኔ ነው። ስለዚህ ነጩ ሄዶ ቅኝ ገዝቶ እየገረፈ ማሰልጠን ያለበት ብለው አስተመሩ። ይህ ደግሞ በታዋቂው ጸሀፊና ገጣሚ Rudyard Kipling ተቀምሞ ታተመ። የነጭ ዘር ሸክም ብሎ በ1899 ይህም ከአድዋ ጦርነት 7 ዓመት ቀደም ብሎ የጻፈው ነው። The White Man’s Burden” ሙሉእን ግጥምን ፈልጎና አንብቡ በአጭሩ ነጩ ሰው የተጣለብህን የነጭነትህን ሸክም ተሸከም፤ ላክ ጥሩ ዝርያህ፤ ሂድ የተጣለብህን ግማሽ ህጻን ግማሽ ሰይጣን የሆነውን ያዝ አሰልጥን ነው። በአጭሩ
Take up the White Man’s burden —
Send forth the best ye breed —
Go bind your sons to exile
To serve your captives’ need;
To wait in heavy harness
On fluttered folk and wild —
Your new-caught sullen peoples,
Half devil and half child.
ግማሽ ሰይጣን ግማሽ ህጻን የሆነ ሰው በራሱ ስለማያስብ በቅኝ ተይዞ በጅራፍ እየተገረፈ ስራ ይልመድ ነበር። ይህም እንግዲህ የአፍሪካና የኤሽያ ሀገሮች ነጻ በመውጣትና እራሳቸውን ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ትላልቅ ስልጣኔ እያስመዘገቡ ትርክቱ ሀሰት እንደሆነ አስመስክረዋል።
የፕሮቴስታንት የስራ ባህል የሚለው ነው
አሁን የብልጽግና ሰዎች ሳይቀር የተንጠለጠሉበት የማክስ ዌበር አስተምህሮ ነው። The Protestant Ethic and the Spirit of Capitalism. የሚለስ ጽሁፍ ነው።
ይሄም እንግዲህ የስራ ባህል የፈጠረው የፕሮቴስታንት እምነት ነው የሚል የሀሰት አስተምሮ ነው። ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ባይኖር ተበለጽግ ነበር የሚል ትርከት ነው። ወለጋ በአመዛኙ ፕሮቴስታንት ነው ይሁንና የምናየው ቅርስ፤ ስነጽሁፍ ሳይንስ ስነ ጥበብ፤ ስነ ህንጻ አልተወለደም። ትልቁ ስህተት የሚጀምረው በአል ማለት ስራ አይሰራም የሚለው ውሸት ነው። እርሻ አይታረስም እህል አይታጨድም ማለት ነው እንጂ ሌላ ስራ አይሰራም ማለት አይደለም። በጥዋት ተነስቶ ከብት ያልባል፤ ያሰማራል፤ መኖ ተከኽሞ ያመጣል፤ ከብት ይጠብቃል። እሁድ ደግሞ ጠበል ጠዲቅ ይዞ ለደሀ ሊያላል ተሸክሞ ይሄዳል፤ ያበላል፤ ያጠጣል፤ ተሸክሞ ይመለሳል። ይሁንና የብልጽና ፕሮቴስታንቶቹ ደግመው ደግመው የሚነግሩን የኢትዮጵያ ገበሬ እንደማይሰራ ነው። ይህ ውሸት ነው። ስራ አይሰራም ማለት እንደ ይሁዳውያን ከአርብ ማታ እስከ ቅዳሜ ምሽት ያለው ሰንበት ነው።
እንደ ይሁዳውያን ስራ የማይሰራበት በአል በኢትዮጵያ የለም። እየሩሳሌም ሄዳችሁ ማየት የቻላችሁ ቅዳሜ ወደ ቤታቸው ሲገቡ ወይንም ሲወጡ እንኳን የሊፍት ቁጥር አይጫኑም። እንደ ስራ ስለሚያስቡት። ስለዚህ ባለ 30 ፎቅ ሰው ሲውጣ ቁጥሩን አይጫንም በሩ በራሱ ይከፈታል፤ ከዛ ሊፍቱ በየ እያንዳንዱ ፎቅ እየቆመ በር ይከፍታል ከዛ ይዘጋል። ሰውዬው ሊፍቱን ሳይነካ ቤቱ ይገባል። እንዲህ የሚያደርገው ሀገር ደግሞ በጣም የበለጸገ ነው። ታድያ የኞ ጥራዝ ነጠቆች ኢትዮጵያ የደሀየችው በአል ስለበዛ ነው የሚለውን ትርክት ከየት አመጡት።
የሀገር ውስጥ መረጃን
በአል የሚያከብረው የኢትዮጵያ ክፍል እና በአል ከሌለው ጋር እናወዳድር።
የመጀመሪያው በአል የሚያከብረው ነው ወይስ በአል ያማያከብረው ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የበለጸገው። አንድ ሰው እኮ ላሊበላ ሊሂድ ይችላል። የኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታይ የበዛበት ቦታ ነው ህጉም ይጠበቃል። እዛ ብዙ የስራ ውጤት የሆኑ ቅርሶች፤ የስነጽሁፍ ክምችቶት፤ ትምህርት ቤቶች፤ ስነ ጥበብ እናገኛለን። አንድ ሰአት ወደ ቆላው ብንወርድ ደግሞ ኦርቶዶክስም አይደለም በአልም የለውም። ይሁንና የገነባውም ቅርጽ የጻፈውም የስነጽሁፍ ክምችት አይታይም። ጎንደር መሄድ እንችላለን፣ ከዛ ደግሞ ወደ ታች ወደ ቆላው ወደ ቤንሻንጉል ወይንም ወደ ወለጋ። ልዩነቱን ማስተያየት እንችላለን። መሀል ኢትዮጵያም አዲስ አበባን ይዘን ወደ አርሲ ወይንም በአብዛኛው ፕሮቴስታትን የተሰበከነት ወለጋም መሄድ እንችላለን። ታድያ በአል ማክበር የድህነት ምንጭ ከሆነ ለምን በአል የማያከብሩት ቦታዎች በልጽግና መአከል አልሆኑም። ሰልጥነው የስብሁት የፈጠራ መአከል አልሆኑም?
ትንሽ ፊደል ለቆጠረ ሰው መቼም በአይኑ አይቶ ማወዳደር ይችላለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የድካም፤ የልፋት፤ የሀሳብ፤ የስራ ውጤት ክምችት ያለው እዛው ሰነፍ ሆነ በአል አበዛ በሚባልው ቦታ ነው። አፍሪካውያኑም የሚኮሩት እኛም ከነጩ እኩል ነን የሚሉት ብዙው ነገር እነዚህ ሰነፍ በአል ያበዛሉ ተብለው በሚከሰሱት ሰዎች የሰሩት ነው።
ኢትዮጵያና አፍሪካ
እስቲ ይሄንን ሀሳብ ሰፋ እናድርገውና ወደ ሱማልያ፤ ኬንያ፤ ዩጋንዳ እያልን አፍሪካን እናሥስ። በአብዛኛው ገብሬልን አያውቁ በአል የላቸው ታድያ ለምን ሰልጥነው ጥለውን አልሄዱም? መላው አፍሪካ በአል ስለማያከብር ከኛ የተሻለ መበልጸግ ነበረበት። እኛ እምነታችን ስራ እንዳንሰራ ያደረገን ከሆነ እነሱንስ ምን ያዛቸው?
እድገት ምንድነው
እድገትን ወስብስብ ምክንያቶች ያሉት ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያውያን እድገት በአል የማክበርና ያለ ማክበር ጥያቄ አይደለም። እድገት የሀሳብና የፈጠራ ውጤት እንጂ ለረጅም ሰዓት ዶማ ይዞ መሬት የመቆፈር ውጤት አይደለም። ተምሮ ፒኤች ዲ ተሰጥቶት ቁጭ ብሎ አሉባልታ የሚያወራው ምሁር ብረትና ብሎን አገኛኝቶ የሰራው ነገር የለም። ድንጋይ አቃሎ ሲሚንቶ፤ አሸዋ ጠብሶ የክምፒተር ፕሮሰሰር ሲሰራ አልታየም።
አንድ መምህር ፋንታሁን ዋቄ ያሉት ትዝ አለኝ። ከአላማያ እርሻ ኮሌጅ በእርሻ በዲግሪ ተመርቆ ገበሬው አባቱ ግብዣ አድርገው መሬታቸው ምርት እየቀነሰ መሆኑን ይነግሩታል። አዲሱ ምሩቅም መፍትሄም ማዳበሪያ መጠቀም ነው ይላቸዋል። እሰይ ጎሽ እሱን ትሰራልናለህ ይሉታል። እይ እኔ መስራት አልችልም ዮርያ የሚባለው ማዳበርያ ከፈረንጅ ሀገር ነው የሚመጣው ይላቸዋል። ከዛ ሄዶ መግዛት ነው ይላቸዋል። ግራ የተጋቡት አባትም ከሎሌጅ የመጣው ልጃቸው መስራት አልችልም ሲላቸው። አሀ ታድያ ያስተማሩህ መስራት ሳይሆን የት እንደሚገኝ እንድትጠቁምላቸው ነው አሉት። የኢትዮጵያ ትምህርት እንግዲህ ጠቋሚ እንጂ ችግር ፈቺ አልሆነም።
አሁን ኢትዮጵያ የምትኮራነበት ለቱሪስት የምታሳየው ነገር ሁሉ በዘመናዊ ትምህርት የተመረቁ የሰሩት ሳይሆን በአል ያከብራሉ፤ ስራ አይሰሩም፤ ሰነፎች ናቸው ብለው እነ ማክስ ዌበር፤ዳርዊንና ኪፕሊንግ የሚንቋቸው ሰዎች ናቸው።
ስልጣኔ የፕሮቴስታንት የስራ ትጋት ውጤት ነውን?
ይህቺ ቀልድ የመጣችው የፕሮቴስታንት ኢቲክስ የምትል የባሪያ አሳዳሪ ፍልስፍና ነች። ግሪክ፣ ሩስያ፣ ሮም፣ ፐርሽያ፣ ጃፓን፣ የፈርኦን ግብጽ፣ የቻይና፣ የእየሩሳሌም ስልጣኔ የመጣው በፕሮቴስታንት ኢቲክስ አይደለም። ስልጣኔ ድምር ውጤት ነው። በግብጽ ወደ ግሪክ፤ ከግሪክ ወደ ሮም እያለ ነው ወደ መጨረሻው የእንግሊዝ የሄደው። የትኛዎቹም ሀገራት የፕሮቴስታት ኢቲክስ ተከታዮች አይደሉም። ዛሬም ፈረንሳይም፤ ጣልያንም፤ ሩስያም፤ ቻይናም፤ ጃፓንም፤ ኮርያም ህንድም ፕሮቴስታት አይደሉም። ማክስ ዌበር እንግሊዝና ሆላንድ የባህር ላይ የባርያ ንግዱን በተቆጣጥረው በከበሩበት ዘመን ነው ወደ ሗላ እያየ የጻፈው። ከዌበር ቦሀላ ይሄው ቻይናና ጃፓን ሩስያ አሁን ህንድ ኮርያ ሰልጥኗል።
እንግዲህ ሁለቱ በፕሮቴስታንት ኢቲክስ የሚሞካሹት ሆላንድና እንግሊዝ ናቸው። የሚገርመው ነገር ደግሞ እነዚህ በባርያ ንግድና በቅኝ ገዢነት ነው የከበሩት እንጂ 70 ሰዓት እንደ ሀበሻ ገበሬ መሬት ቆፍሮ አይደለም። የፕሮቴስታንት ኢቲክስ በአርያ ስላሴ የተፈጠረውን ጥቁር ሰው አጋሰስ አድርጎ በማሰራቱ ነው።
ባርያ ነጋዴዎቹ ግን የአለምን እስፓርት ሁሉ ቁጭ ብሎ ይፈለስፉ ነበር። እንግሊዝ እግር ካስ፣ ራግቢ፤ ቴኒስ፤ ሆኪ፤ ጎልፍ፣ ባድሜንተን፤ ስካሽ፣ ዳርት፤ ስኑከር፤ ክሪኬት የሚባል ግዜ ማጥፊያ ሲፈለፍ ነው የኖሩት።
ብዙ ኢቲዮጵያውያን ስለ ክሪኬት ጨዋታ አያውቁም። እንደ የአሜሪካኖቹ ቤዝቦለ ጨዋታ ይመስላል። የእንግሊዞቹ የክሪኬት በሁለት ቡድን መሀከል የሚደረገው ውድድር ግን 5 ቀን እንደሚፈጅ ታውቃላችሁ? (Test Matches: These are the longest format and can last up to five days. Each day typically involves around six hours of play, divided into three sessions.)። ህንድን እየገዙ እነሱ ኳስና ዱላ ሰርተው ለአምስት ቀን ሙሉ ተጫውተው በአምስተኛው ቀን መጨረሻ አሸናፊው ይታወቃል። አሁን ለንደን ስትሄዱ ትኬት ቆርጣችሁ ማየት ትችላለችሁ። ፈጣኑ የአንድ ሙሉ ቀን ጨዋታ ተደርጎ ያጠረ አለ።
ታድያ ይህ ቀኑን ሙሉ ለ 5ቀን ህንድ ላይ ቁጭ ብሎ ሳይሰራ በሰው ብዝበዛ የከበረው እንግሊዝ ይመጣና ጥቁር ያልከበረው ስራ ስለማይወድ ነው፣ የፕሮቴስታንት የስራ ባህል የለውም ይላል። ይሄንን ሳያላምጥ ደግሞ ይዞ የሚሮጥ ኢትዮጵያዊያን እየበዛ ነው። በጠቅላይ ሚኒስቴራች አልፎ እነ ዲያቆን ዳናኤል ክብረትም የማክስ ዌበር ደቀ መዝሙር ሆነው ብቅ እያሉ ነው።
የገበሬው ልጅ አባትና እናቱ ምንያህል ደክመው እንዳስተማሩት ይረሳና እውነት ነው እኛ የደሀየነው በአል ስላበዛን ነው ይላል። ኢትዮጵያ ውስጥ የማይሰራበት ቀን የለም። የማይታረስበት የማይወቃበት ወይንም የማይፈጭበት ቀን እንጂ በበአልም ከብት ይታለባል፤ ከብት ይጠበቃል፤ ከብት ይታረዳል፤ ይገፈፋል፤ ምግብ ይሰራል፤ ሰው ተሸክሞ ይሄዳል፤ ሰው ይጓጓዛል፤ መኪና ፈረስ ጋሪ ይነዳል፤ ቤት ይጸዳል፤ የተበላበት ይታጠባል ወዘተ። በበአል ቀን ዘመድ ይጠየቃል፤ ሽምግልና ይቀመጣል፤ ልጅ ይታጫል፤ ልጅ ይዳራል ወዘተ። መጽሀፍ ይነበባል፤ መጽሀፍ ይጻፋል፤ ትምህርት ይሰጣል፤ ጸሎት ይደረጋል ሀጥያትን ይቀታ ይጠየቅበታል፣ ደሀ ይመገባል፤ ሀሳብ ይታሰባል በጎ ነገር ሁሉ ይሰራል።
ስለዚህ እባካችሁ እኛ ያልበለጸግነው በአል ስላበዛን አይደለም። ወይንም እንደ እንግሊዝ ለአምስት ቀን ቁጭ ብለን ስለተጫወትን አይደለም። እኛ ያላደግነው የሚያስብና የሚፈጥር ምሁር መፍጠት የሚያስችል የትምህርት ስርአት ስላልፈጠርን ነው።
ይልቁንም ለምን የኢትዮጵያ ትምህርት የሀሳብ ሰዎች መፍጠር አቃተው ብለን ብንጠይቅ ብልጽናን ማምጣት እንችላለን።
የተማረው ሁሉ አዲስ ሀሳብ የለውም። ያው ተራኪ እንጂ ፈጣሪ አይደለም። የፋንታሁን ዋቄ አባት ያስተማሩህ ማዳነሪያ የት እንደሚገኝ እንድትጠቁመን ነው ያስተማሩህ እንዳሉት ነው።
ለ50 ዓመታት ሌኒን እንዳለው፤ ስታሊን እንዳለው ማርክ ዌበት እንዳለው ብሉ አሉባልታ ሲያገላብጥ እንጂ አዲስ ሀሳብ ሲያፈልቅ ወይንም የአባቱን ቅርስ ሲያበለጽግ አይታየም። በአል በዝቶ ነው አዲሱ ሌኒን እንዳልው አሉባልታ ነው።
የፕሮቴስታንት ሀብት የተፈጠረው በሶስትዮሽ ንግድ ነው። ባርያ ከአፍሪካ ወደ አሜሪካ፣ ከአሜሪካ ጥጥና ስኳር ወደ ኢሮፕ፣ ከዛ ሸቀጥ ወደ አፍሪካ በመውሰድ በሰው በመቀየር ነው። ሌላው የሰውን ሀገር በመውረር ቅኝ በመያዝ ቀይ ህንዶችን፣ አበርጂኒሶችን በማጥፋት፣ ጥቁሩን በአርአያ ሳላሴ የተፈጠረውን ክቡር ሰው ወደ የጋማ ከብትነት ዝቅ በማድረግ እስኪሞት በመጫን እንጂ የእንግሊዝ ፕሮቴስታንት ኢቲክስ ብሎ እራሱ ተሸክሞ አርሶ አይደለም። ባርያ አሳዳሪዎቹማ ክሪኬት ለአምስት ቀን ቁጭ ብለው እየተጫወቱ ነው የከበሩት።
እድገት ለረጅም ሰአት መሬት መቆፈር አይደለም። የሀሳብ ውጤት ነው። ሀገር የሚያሳድገው የሚቆፍር ሳይሆን የሚያስበው መሀበረስብ መፍጠር ሲቻል ነው።
ፊደል የቀረጸው፣ ብራና ፍቀው፤ የቀለም ኬሚስትሪን አንጥረው ቀምመው ታሪኩን፤ መዋዕሉን፤ ሀይማኖቱን፤ ስነ ፍጥረቱን፤ ስነ ህይወትን፤ ስነ ከዋክብትን፤ ስነ ጥበብን፤ ስነ ቀመርን ጽፈው ሰንደው አንብቡት በዚህ ላይ ገንቡበት ብለው ከ300 ሺ በላይ የብራና ጽሁፍ ትተውልን ያለፉት በአል እያከበሩ እሁድ ተረጋግተው አስበው ጽፈው ነው። ፒኤችዲ ፈረንጅ ሰጥቶት ወረቀትና እስክሪብቶ አገናኝቶ አንድ ገጽ መጻፍ ያልቻለ ምሁር ፈረንጅ የሰጠውን አሉባልታ ሲያወራ ጊዜውን ያጠፋል።
ሀገር ምስረታ፣ ስረወ መንግስት ማቆም፣ ላሊበላን፤ ጉንደርን፤ አክሱምን፤ ደብረ ዳሞን፤ ደብረ ሊባኖስን፤ እንጦጦን፤ አዲስ አበባን መገንባት፣ ቤተ ክርስቲያን ማነጽ፣ መስጊድ ማነጽ፤ የነጻነት ስነልቦና ፈጥሮ ለጋራ ነጻነት የግል መስዋዕትነት መክፈል ፣ማስተማር በአልን ባከበሩ ሰዎች እንጂ አሉባለታ ባጠኑ ሰዎች አይደለም።
እስከ ቅርብ ግዜ እውቀት ማመምጫ፤ ማከማቺያና ማስጠበቂያ የሆነችው በአል አባዛች ተብላ የተከሰሰችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ነች። ታድያ ይህቺን ካላጠፋን ሞተን እንገኛለን ያሉ ምንም ውጤት ያላመጡ እሳቤዎች በዝተዋል።
መጻፍ ማንበብ፣ ቀመር መስራት፣ ህንጻ የሚያንጽ፣ ስነ ከዋክብትን፣ ስነ እጽዋት ያጠና ጥቁር የነበረው እዚህ ሀገር ነው። የሄንን የምንጻጻፍበትን ፊደል እንኳን ያስተማረችን እቺው ቤተ ክርስቲያን ነች። ያልከበርነው የሚያስብ የሚፈጥር ሰው ስላልፈጠርን እንጂ የሚቆፍር ሰው ስለጠፋ አይደለም። ስለዚህ የማክስ ዌበርን ይታችሁ ስራ ስሩ።
__
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት እዚህ ይጫኑ፡፡ የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com
Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ







ውድ ወዳጄ ነገሩ በጣም የተወሳሰበ ስለሆነ አንተ ያቀረብከውን ጥያቄ ለመመለስ የብዙ ዓመታትን ምርምርና ጥናት ይጠይቃል። የኢትዮጵያ ሀይማኖት በራሱ የድህነት ምንጭ ወይም ምክንያት ሊሆን በፍጹም አይችልም። እንደዚህ ብለው የሚያወሩ አንዳንድ የፕሮቴስታንት ሀይማኖት ተከታዮች የካፒታሊዝምን አፀናነስና ዕድገት በፍጹም የሚያውቁ አይደሉም። የፕሮቴስታንት ሀይማኖት በራሱ ብቻውን ለፈጠራ ስራ በር የከፈተ አይደለም። ከፕሮቴስታንት ሀይማኖት በፊት በጣሊያን ምድር የተከሰተው ሬናሳንስ የሚባለው የመንፈስ ተሀድሶ አብዮት አነሰም በዛም በአውሮፓ ምድር በፊዩዳሉ ስርዓትና በካቶሊክ ሀይማኖት ተቆልፎ የነበረውን፣ በጦርነት ይታመስና በረሀብ ይሰቃይ የነበረውን የአውሮፓ ህዝብ ዐይኑን እንደከፈተለት የማይታበል ሀቅ ነው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ነው ለቴክኖሎጂ መሠረት የሆነው ሳይንሳዊ ግኝት ሊያብብ የቻለው። ማርቲን ሉተር ሲነሳ በመሠረቱ ሀይማኖትን ለመከፋፈል አልነበረም። በካቶሊክ ሀይማኖት መሪዎች ዘንድ የነበረውን የቅንጦት ኑሮ ስለተመለከተ ነው። መሪዎቹ ውሃ ጠጡ እያሉ እየሰበኩ ራሳቸው ግን ወይን ይጠጡ ነበር። ይህንን በመገንዘብ ነው ማመጽ የጀመረው። ህዝቡም ከዚያ በኋላ ነው መጻፍና ማንበብ የጀመረው። ይህም ማለት የፕሮቴስታንት ሀይማኖት የተወሰነ ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል። በዛሬው ወቅት ያለውን ሁኔታ ስንመለከት የፕሮቴስታንት ሀይማኖት ከፋፋይና የጦርነትም ምንጭ ነው። ሰላምን ከመስበክ ይልቅ የአንድ ሀገር ህዝብ ምክንያቶችን እየፈለገ እንዲጠላላ የሚያደርግ ነው። ከስለላ ድርጅቶችም ጋር የሚሰራ ነው።
ወደ አገራችን ስንመጣ የኦርቶዶክስ ሀይማኖት እንደ ካቶሊክ ሀይማኖት ፀረ ሳይንስ አልነበረም። የነበረው ችግር መንፈስን የሚያድስ ምሁራዊ እንቅስቃሴ አለመኖሩ ነው። በዚህ ምክንያትና በመንግስት ላይ ጫና የሚያደርግ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ባለመኖሩ አጠቃላይ የሆነ ዕድገት ሊመጣ አልቻለም።
ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ