Homeነፃ አስተያየትአቶ ጀዋር መሀመድ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ እያሉ ይሆን ?

አቶ ጀዋር መሀመድ እንደ ጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ እያሉ ይሆን ?

Advertisement
World Wide Travel Group

በአልፀፀትም መፅሀፍ ላይ የተመረኮዘ የግል ምልከታ

የመፅሀፍ ርእስ ፡- አልፀፀትም
ፀሀፊ ፡- ጀዋር መሀመድ 
የህትመት ዘመን ፡- ታህሳስ 2017 
የገጽ ብዛት ፡ 455

የመፅሀፍ ርእስ ፡- አልፀፀትም
ፀሀፊ ፡- ጀዋር መሀመድ 
የህትመት ዘመን ፡- ታህሳስ 2017 
የገጽ ብዛት ፡ 455

በቶፊቅ ተማም 

በወቅቱ የኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ተጣቃሽ ከሆኑ የዘመኑ ፖለቲከኞች አንዱ የሆኑት አቶ ጀዋር መሀመድ በተለይ በኦሮሚያ ክልል ከተቀሰቀሰው ተቀውሞ ጀርባ በሚሊየን የሚቆጠሩ የአሮሞ ተወላጆችን ቅቡልነት አግኝቶ ቄሮ የተሰኘ ህቡእ አደረጃጀት ያደራጀ ከቲም ለማ ጋር አብሮ የሰራ በአሮሚያ ተወላጆች ላይ የደረሰው ግፍ አለም እንዲያውቀው መንግስታት ትኩረት እንዲሰጡት በማደረግ አርቆ አሳቢ ነው የሚባለው ጀዋር መሀመድ በሀገሪቱ ከታዩ የፖለቲካ ትእይንቶች ጀርባ ያለው ጉምቱ የፖለቲካ ሰው ከልጅነት እስከ እውቀት ያለውን የህይወት ጉዞውን የተረከበትን እና የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ ወደ ማረሚያ በወረዱበት ወቅት ባገኙት የፅሞና ጊዜ በመጠቀም አልፀፀትም የሚል መጽሀፍ  የፃፉ ሲሆን ይህን መፅሀፍ እንድጽፍ ያሥገደደኝም ሁለት ምክንያቶች ናቸው የሚሉት አቶ ጀዋር መሀመድ የመጀመርያው ከገባሁበት ወህኒ ቤት በህይወት እተርፋለሁ ብየ ስላላሰብኩ የተሳተፍኩበትን የትግል ጉዞ የማስታውሰውን ያህል ለቀጣዩ ትውልድ በመፅሀፍ መዝግቦ ለማኖር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ አንዲት ቀን የአመት ያህል የምትረዝምበትን የእስር ቤት ቆየታየን ለማሳጠር እና ለመጠቀም   በማሰብ መጽሀፉን ፅፎ ለአንባቢያን አቅርቧል ፡፡መፅሀፉ በአስራ አንድ ክፍሎች የተቀነበበ ሲሆን ትውሰታ በምስል የተሰኙ የፎቶዎች ስብስብ ያካተተው እጅግ እና ሰፋ ባለ መልኩ በ455 ገፅ የተቀነበበው መፅሀፍ በወፍ በረር እንደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክራለሁ ፡፡

የስለት ልጅ

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ስለ ልጅነት አስተዳደጉ ሰፋ ባለ እና ማራኪ በሆነ መልኩ በክፍል አንድ የተረከው ጀዋር መሀመድ የሰላሌ ተፈናቃይ እና  የአርሲ ቱጃር ከሆኑት አባታቸው  ከአቶ ሲራጅ መሀመድ ቱፋ  እንዲሁም ከወ/ሮ ፋንታየ በኋላም ሸምሲ በግንቦት 1978 የተወለዱ ሲሆን የስለት ልጅ ስለመሆናቸውም በዚህ መልክ አስፍረውታል ‹‹ እናቴ ዘምዘም የተባለች የመጀመሪያ ልጅ ወለደች፣ በዓመቱ ሌላ ሴት ልጅ ደገመች። ሁለት ሴቶች ተከታትለው መወለዳቸውን ቀልባቸው አልወደደውም። የሲራጅ አባትም ከሲራጅበሰተቀር ሌሎች ልጆቻቸው ሴቶች ስለሆኑ፣ ወንድ የልጅ ልጅ ለማግኘት ታለቅ ጉጉት ነበራቸው። ተፈላጊውን ወንድ ልጅ ለማግኘትም አባቴ ሌላ ሚስት በአናቴ ላይ ደርቦ አግብቶቢሞክርም አዲሷም ሚስቱ ሴት ወለደች። እናቴ አሁንም ሦሰተኛ ሴት ልጅ ወለደች፣ አባቴ ተጨማሪ ቢያገባም ውጤቱ ያው ሆነ። ይባስ ብሎ እናቴ አራተኛ ሴት ልጅ ደገመች። በዚህ”እድለቢሥነቷ” ያዘነችው እናቴ በአካባቢው ባሕል መሠረት ለሼኽ ሁሴን ተሳለች። “ፈጣሪ ሆይ፣ ቀጥሎ የምወልደውን ልጅ ወንድ አድርግልኝ፤ ወንድ ልጅ ካልሆነ ግን አምጥቼ በቀዬህ (ድሬ ሼኽ ሁሴን) እጥላለሁ” ብላ በዛቻ ተማጸነች። ሼኽ ሁሴን በ13ኛው ክፍለ ዘመን ባሌ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ታዋቂ የእስልምና ወልይ ናቸው። እርሳቸው በኖሩበት ቦታ ከበርካታ ዞኖች የተውጣጣ ሕዝብ አሁንም ድረስ ለጸሎት ወደ ሙዳ ይሄዳል። እናቴ ነፍሰጡር ሆና ከሼኽ ሁሴን ዚያራ የሚመለስ አንድ ሰው ጎራ ብሎ በሆዷ ያዘለችው ፅን  ወንድ መሆኑን በሕልሙ አንዳየ ነገራት። ለሚወለደውም ልጅ ከምንም ምግብ በፊት “ይህን ጀዋረ አጉርሺው” በማለት ከድሬ ሼኽ ሁሴን ይዞት የመጣውን ቋጠሮ ሰጣት። የልጁንም ስም ሙሐመድ ጅዋር ብዬ ሰይሜዋለሁ አላት። ጀዋረ ማለት ወደ ሼኸ ሁሴን ለሙዳ (መንፈሳዊጉዞ) የሚሄዱ ሰዎች ይዘው የሚመጡት ጥቁር አፈር ወይም አመድ ቢሆን ሕመምተኛን ለመፈወስ የሚበላ እና የሚቀባ ነው። በኦርቶዶክስ ክርስትና «እምነት» ከሚባለው የሚቀባ ነገር ጋር ተመሳሳይ ነው።አንደተባለውም እናቴ አምስተኛ ላይ ወንድ ልጅ ወለደች። ያንን ጀዋረ አጎረሱኝ፡ ስሜንም ሙሐመድ ጀዋር ብለው ሰየሙኝ። ትምሀርት ቤት ስመዘገብ መምህራኖቹ ሙሐመድን ጀዋር በሚለው አሳጠሩት። እናቴ ከእኔ በኋላ ሁለት ሴቶችን ብትወልድም ወንድ ልጅ ግን መድገም አልቻለችም። አባቴ ግን እናቴ አኔን ነፍሰጡር ሆና ካገባት ሚስቱ አሚን የተባለ ሌላ ወንድ ልጅ ወለደ። አኔም ወንድሙን አስከትሎ የመጣ ገዳም (‘ዳ’ ጠብቆ) ልጅ ተባልኩ። >> ገፅ (11-12) በማለት የስለት ልጅ ስለ መሆናቸው ያስረዳሉ ከዛ በላፈ  በገጠር ማህበረሰብ ጋር እንደመኖራቸው የልጅነት የመድረሳ  ቤት ህይወት እንዲሁም የኔታ ጋር ያሳለፏቸውን ጣፋጭ የልጅነት ጊዜም ያጋሩ ሲሆን በቀየው ስለሚከበሩት የአቴቴ ፤ቦረንቲቻ፤መስቀል እና መውሊድ አከባባር በተወሰነ መልኩ መዳሰስ ችለዋል  ፡፡

የሸጎየ ምሽቶች

ጀዋር መሀመድ ታዋቂ ፖለቲከኛ እንደመሆናቸው የሚፅፉት መፅሀፍ ውስጡ የፖለቲካ ብቻ ይሆናል ተብሎ ቢታሰብም ወደ ፖለቲካ ሕይወታቸው ከመግባታቸው በፊት ስለ እድገታቸው ስለ ቤተሰብ ኋላ ታሪክ ብሎም በአካባቢያቸው ስለሚከወኑት ባህላዊ ሁነቶች በመፅኀፋቸው ቦታ ሰጥተው ተርከዋል ፡፡‹‹ በሽዋ የኦሮሞ ማህበረሰብ የሚደረገው ባህላዊ ጭፈራ ሴቶች በአንገትና ጭንቅላት በሚደረግ እሽክርክሪት ሲከወን ወንዶች እግርን፣ ትከሻን አጅንና አንገትን መሰረት ያደረገ ውዝዋዜ ይከውናሉ። ሸጎየ በምስራቅ ኢትዮጵያ በኦሮሞ ማህበረሰብ የሚከወን ባህላዊ ጭፈራ ሲሆን የወገብ፣ የትከሻና የአንገትን እንቅስቃሴ መሰረት በማድረግ ሲሰራ ወንድና ሴት ጥንድ በመሆን ወንዱ የሴቷን ትከሻ ወደ ግራና ወደ ቀኝ አቅጣጫ በማንቀሳቀስ ሴቷ ከወገቧ ጎንበስ ቀና እያለች፤ አንገቷን ወደ ግራና ቀኝ በማዘንበል የሚሰራ ባህላዊ ጭፈራ ነው፡›› (ከዋኔ ጥበባት መማርያ  መፅኀፍ ገፅ  77) ይህን ባህላዊ  በድሙጋ የሚጨፈር ሲሆን የሸጎዬ ዓይነቶች ደዳይሳ፣ ሁሩምሱ፣ ኦኮይና፣ ገዲ ደዋ፣ ጂይሳ፣ ረገዳ፣ ወዘተ በመባል ይታወቃሉ።

የልጅነት ትዝታቸውን ቀደም ብለው እንዳካፈሉ ሁሉ በአካባቢው ወጣቶች ይዘወተር ስለነበረው ባህላዊ ጭፈራ የሸጎየ ምሽቶች በሚል ርአስ እንዲህ አሰፍረውታል  ‹‹ የወጣት ልጃገረዶች እና ጎረምሶች በምሸት ወጥቶ መዝፈን የሚታወቅ ቢሆንም በግልጽ ግን አይፈቀድም። ስለዚህ ላለመጋለጥ ሲባል ምሽት ከሰፈር ራቅ ተብሎ ይጨፈራል። ይህም ርቀት “ሽማግሌዎችን በእንቅልፍ ሰዓት ላለመረበሸ” የሚደረግ ጥረት አካል ነው ይባላል። እኩያማቾች የሆኑ ልጃገረዶች እና ጎረምሶች የሚጫወቱበትን ቀን፣ ቦታ አና ሰዓት ይቀጣጠራሉ። ምሽት ላይ ሴቷ ልጅ ቤተሰቦቿን እራት አብልታ ካስተኛች በኋላ ከእናቷ ጀርባ ትተኛለች። ወላጆቿ መተኛታቸውን ሰትገነዘብ፣ ቀሰ ብላ ትነሳና ማታውኑ አንዳይጮኽ ብላ በውኃ ያራሰችውን በር ከፍታ ወጥታ ከሌሎች ሴት ጓደኛቿ ጋር ትቀለቀላለች። እናቷ ለወጉ ያህል ዓይኖቿን ታዞራለች እንጂ ምሥጢሩን ታውቃለች። ይልቁንም ወደ ሸጎዬ ከሚሄዱ ወጣቶች መካከል ለአንዱ ዘመድ አደራ ትሰጣለች። ወጣቱ የሴቷን ደኅንነት እና ሥነ-ምግባር የመጠበቁን ኃላፊነት ይወሰዳል። በዚህም ምክንያት የሸጎዬ ቦታ አንዲት ልጃገረድ እና አንድ ወጣት የፍቅር ዘፈኖችን አብረው ቢዘፍኑም ከዚያ ያለፈ ፆታዊ ግንኙነት አይታሰብም። በእኛ ዘመን ጫካ ሄዶ ሸጎዬ የመጫወት ባሕል እየተዳከመ መጥቶ በዳንስ ተተካ›› (ገፅ 11) በማለት የሚገልፁት ጀዋር ከሸጎየ ባለፈ በአካባቢያቸው የነበሩ የጋብቻ ልምዶችን በከፊል  እንደሚከተለው አጋርተዋል ፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

<<በአካባቢያችን ብዙ የሰርግ ልማዶች ነበሩ። ከእነዚህ ውሰጥ በጣም የሚታወቁት ከጳ (መሪ)፣ ጨብሳ አና ቡታ ናቸው። ከሁሉም በክብር የሚታየው ወንዱ የልጅቷን ቤተሰብ ለምኖ አጭቶ የሚያገባው ነው። አንድ ወጣት ለማግባት ዝግጁ ሲሆን ልቡ የከጀላትን አይቶ ለአባቱ ይናገራል። አባትየውም ሽማግሌ መርጦ ወደ ልጅቷ ቤተሰቦች ይልካል። እነሱም ልጅቷ ከዚህ በፊት ካልታጨች “ተወያይተን እናሳውቃችኋለን” በማለት ለሌላ ጊዜ ይቀጥሯቸዋል። በዚያ ቀጠሮ ልጁ ጥሩ አማች አንደሚሆናቸው ካመኑ «ይሁን» ይላሉ። በመቀጠል የጉዱንፋ ሥነ-ሥርዓት ይከተላል። ይህም በልጁ ወገን ያሉት ሽማግሌዎች እንደ ትምባሆ ስኳር፡ ጀንፈል ቡና ወዘተ ይዘው በመሄድ ለሴቷ ወገን የሚሰጡበት ነው። የልጃገረዷ ወላጆች ቋጠሮውን ከፈቱ ልጅቷ ታጭታለች ማለት ነው። ከዚያም ልጁ ለአማቾቹ ጥሎሽ ይጥላል። ጥሎሹ እንደሌሎች አካባቢዎች ለአማቾቹ ገንዘብ ወይም ከብት ከመስጠት ይልቅ በሥራ ማገዝ ነው። ልጁ ደቦ ጠርቶ በቡና ቆፋሮ፣ እህል በማጨድ እና ቤት በመሥራት ያግዛል። ይህ ለአማቾች የሚሰጥ ነጻ አገልግሎት እነሱን ከመጥቀም ይልቅ ለልጁ ሠራተኛ መሆኑን ለመገምገም የሚከናወን ነው። ደቦ የጠራ ሰው በምላሹ ለጠራቸው ሰዎች ሄዶ መሥራት አለበት። ብዙ ሰዎችን ደቦ መጥራት ቻለ ማለት ከዚህ በፊት ሌሎችን አግዟል ወይም ወደፊት አፀፋውን አንደሚመልስ ይታመናል። ወጣት ሙሽሮች ለአማቾች ደቦ በሚጠሩት የሰዎች ብዛት ይፎካከራሉ። «የእከሌ አማች ለጠራው ደቦ ማሳው አልበቃ አለ» ተብሎ ይዘመርለታል። በዚህ መንገድ ልጅቷን አግብቶ ወደ ቤቱ ከማሰገባቱ በፊት ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያገለግላል። በዚህ ጊዜ ውሰጥ ለአማቾቹ ብቻ ሳይሆን ለራሱም በትጋት መሥራት አለበት። ቢያንስ አራሽ በሬ እና ሦሰት ጎተራ አንዲኖረው ይጠበቃል። ምክንያቱም አንዱ በድንገት ቢሞት፣ ሥራው እንዳይቆም ዋሰትና ለማግኘት ነው >>( ገፅ 22) በዚህ መልኩ ደቦ እየጠራ ምርቱን ሲያሳይ ሙሽራው ትጉህ ነው ተብሎ ቀጠሮ ይያዝለታል በተቃራኒው ይህን ማድረግ ካልቻለ ሌሎች አማራጮችን ይፈልጋል ፡፡

‹‹ሴት ልጅን ለምኖ ማግባት እንደዚሀ ዓይነት ውጣ ውረድ ስላለው አንዳንድ ወጣቶች በጨብሳ እና ቡታ ማግባትን ይመርጣሉ። እኛ ጋር ከቡታ በላይ ጨብሳ ይከናወናል። ጨብሳ የድንገቴ ጋብቻ ሲሆን፣ ሴትን ልጅ ወዲያውኑ ለምኖ የማግባት ሂደት ነው። ልጁ በማለዳ ጓደኞቹን ይዞ የልጅቷ ወላጆች ቀዬ በማድፈጥ ከእንቅልፍ እሰኪነቁ ድረስ ይጠባበቃል። ሴቶቹ አመድ ለመድፋት በሩን ከፍተው ሲወጡ፣ ካደፈጡበት ዘለው በመነሳት አለንጋ ወደ ፊት ወርውረው ገብተው ይቀመጣሉ። የልጅቷ አባት ነገሩ ሰለሚገባቸው ለጎረቤት ሽማግሌዎች ይናገራሉ አንድ ወጣት በጨብሳ ለማግባት የሚገደድባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው ምክንያት በሁለቱም በኩል ያሉት ቤተሰቦች ቂም ከተያያዙ፣ ልጁ ደሀ ከሆነና የልጅቷ ወላጆች ሀብታም ሆነው በወጉ ከጠየኩኝ አይሰጡኝም ብሎ የሠጋ አንደሆነ ነው። ከዚህ ውጪ በገንዘብ ከእሱ ሻል ያለ ሰው ልጅቷን ለመጠየቅ ማቀዱን ከሰማ ሳይቀደም ለመቅደም ነው። ያጫት ልጅ ሌላ ሰው አፍቅራ አብራው ከኮበለለች፣ አሊያም ከተጠለፈች ሞራሉን ለመጠበቅ በእልህ ተነሳሰቶ ወደ ጨብሳ ያመራል። በሌላ በኩል ጨብሳም አይሳካልኝም ብሎ የሠጋ ወጣት ቡታን እንደ አማራጭ ይወሰዳል። ሌላ ሰው ቀድሞ ካጫት ኮረዳ ከባድ ፍቅር ከያዘው፡ ልጅቷ ላይ ጠለፋ (ቡታ) ሊፈጽም ይችላል። ወኃ ቀድታ፣ እንጨት ሰብራ ወይም ገበያ ሄዳ ሰትመለስ ጓደኞቹን አደራጅቶ በግዳጅ ይዟት ከተሰወረ በኋላ የሀገር ሾማግሌ ልኮ በመታረቅ ኒካህ ያሥራል። ››( ገፅ 23) በማለት ሲገልጹ የገጠር ሰርግ ሲኖር ሁሌም አልቅሼ ከእናቴ ጋር እሄዳለሁ የሚሉት አቶ ጀዋር መሀመድ ካሳለፏቸው አስቂኝ ትእይንቶች እና ትዝታዎች መካከል ይህን አካፍለዋል ፡፡

‹‹ምሽቱ ሙሽሪት ልጃገረድ ሰለመሆኗ ለሚነሳው ጥያቄና ሀሜት ግምት መልስ የሚገኝበት ስለሆነ ሚዜዎች ምሥጢሩን ለመጠበቅ፡ ሌሎቹ ደግሞ ቀድሞ ለማወቅ ይፋጠጣሉ። ስለዚህ ሚዜዎቹ ቤቱን እና አካባቢውን አስሰው ያገኙትን ሰው ሁሉ በአለንጋ እየገርፉ ያባርራሉ። ምሥጢሩን ለማወቅ የሚፈልጉ ሰዎች እንደ እኛ ያሉ ልጆችን ይጠቀማሉ። ትንንሾች ስለሆን የቤቱ ግድግዳ ላይ ከተጋደመ ሳር ወይም በቡና ጆኒያ መሀል ይደብቁናል። ድምጻችንን አጥፍተን ከሚዜዎቹ ፍተሻ ካመለጥን በሙሽሮቹ የጫጉላ ክፍል ውስጥ የሆነውን እና የሰማነውን ሁሉ ላሰማሩን ትልልቅ ሰዎች እንተርካለን። ተደብቀን ከተገኘን ግን የዕድሜ ልክ ጠባሳ የሚያስቀር የአለንጋ ግርፋት ያጠብቀናል። እኔ በማሰታወስ ችሎታዬና የተከሰተውን አጣፍጩ በመተረክ ሰለምታወቅ፣ ብዙ ጊዜ ለዚህ ተልዕኮ እመረጣለሁ። በተደጋጋሚ አሰኪበቃኝ ድረሰ በአለንጋ ተገርፈያለሁ›› (ገፅ 24) በማለት በአስራዎቹ የእድሜ ክልል ያሳለፏቸውን አይረሴ ገጠመኞች  አስፍረዋል ፡፡

ከኦነግ ጋር ትውውቅ

- Advertisement -

ከፖለቲካ ትውውቅ በሚል ርእስ በሰጡት የመፅሀፉ  ክፍል ሁለት  እንዴት ገና በአፍላ እድሜአቸው ወደ ፖለቲካ እንደተሳቡ ብሎም ከኦነግ ጋር እንዴት እንደተዋወቁ እንደሚከተለው አስፍረዋል የመጀመርያ የሆነውና ከኦነግ ጋር ሊተዋወቁ የቻሉበትን ሁኔታ ያሰፈሩት አቶ ጀዋር በልጅነታቸው በቦረቁበት ድሙጋ ከአቻውቻቸው ጋር በመሆን የልጅነት ጨዋታ በሚከውኑበት ወቅት መሆኑን አንዲህ ሲሉ ገልፀውታል ፡፡

<<አንድ ቀን ከተንጠለጠልንበት ትራክተር ወርደን ፍራፍሬ ለመልቀም ወደ ጥሻ ስንገባ፣ ረጅም ጸጉር ያላቸው እና መሣሪያ ያነገቱ ሰዎች ጥላ ሥር ቁጭ ብለው ፍራፍሬ ሲበሉ አየናቸው። ከመደንገጣችን የተነሳ ሰውነታችን ተርበተበተ፡ እነሱ ግን በዝምታ ተመለከቱን። ከእኛ መሀል ጠና ያለና ሲያወራ የሚንተባተብ ሰቡሬ(አብዱልሰቡር) የምንለው ልጅ እነዛ ሰዎች «ኦሮሞ ናቸው፡ ሰው አይነኩም’!›» ብሎ አደፋፍሮ እነርሱ ጋር ወሰደን። የማን ልጆች አንደሆንን ጠይቀው፣ «የኦሮሞ ጦር» መሆናቸውን ከነገሩን በኃላ አንዳየናቸው ለማንም አንዳንናገር አሰጠንቅቀው ሸኙን። ይህ ክስተት ከዚያ በፊት ተመሳሳይ ሰዎች ማየቴን አሰታወሰኝ። አንድ ቀን ሼኻ (የአባቴ ጓደኛ) ማሳ ውሰጥ ዘይቱን አና ኮክ ለመልቀም ስሄድ ድምፅ ሰምቼ ወደ አቅጣጫው ሳመራ የቆምኩበት ከሙዝ ግንድ የወዳደቀ ቅጠል አንሸራቶኝ የሆነ ጉድጓድ ውሰጥ ወደቅሁ። የወደቅሁበት ገደል የምድር ሥር ቤት ሲሆን፣ ከአሥር በላይ ሰዎች ልብሰ አየሰፉ፡ አባቴ መሀከላቸው ባለ መቀመጫ ላይ ተፈናጦ ልብስ ይቀዳል። ልክ ሰወድቅ አባቴ ደንግጩ እንዳልጮህ ዘሎ አፌን ይዞ ልጁ እንደሆንኩ ነግሮ አረጋጋቸው። እኔንም ያየሁትን ነገር ለማንም አንዳልናገር አስማለኝ፤ ከረሜላና ናና የምገዛበትን ሃምሳ ሳንቲም ሰጥቶ ለቀቀኝ። በኋላ እንደተረዳሁት፣ አባቴ አና አብረውት የነበሩት ሰዎች ቱምቱ ፉርዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ላለው የኦሮሞ ነጻነት ጦር ልብስ እና የትጥቅ ቀበቶ ሲሰፉላቸው ነበር።››(ገፅ 29-30) በማለት የመጀመርያ የሆነውን ከኦነግ ጋር  ትውውቅ ያሰፈሩ ሲሆን የኦነግን ወታደሮች በዚህ መልኩ ቀደም ብዬ ማየቴ በኋላ ላይ በይፋ ሲመጡ አንድቀርባቸው አደፋፈረኝ። ቁቤ አፋን ኦሮሞን በአጭር ጊዜ ውስጥ በለገ ደርባ የሸንኮራ ማሳ ውሰጥ አሰተማሩኝ።ከቻርተሩ ተገፍተው ከወጡ ከጥቂት ዓመታት በኋላም አንዳንዴ የፍየል እረኛ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዘመድ ጠያቂ መስዬ የከተማ እና የገጠር ሕዋስ መካከል መልዕክት አንዳመላልስ ይልኩኝ ጀመር›› በማለት ገና በማለዳው ኦነግ የሰጣቸውን ተልእኮ ማስፈጸም እንደጀመሩ ይገልፃሉ ፡፡                                                              

ሲንጋፖር እንደምን ሰለጠነች

ጀዋር መሀመድ በመፅሀፉ በተለይ በክፍል አራት የመጀመርያ ስለሆነው የውጭ ጉዞ አስመልክቶ በተለይ ስለተማረበት ኮሌጅ ስለሄደበት ሀገር ሲንጋፖር ፤ዥንጉርጉር ስለሚላት እስያ ፤ስለተማረበት ዩናይትድ ወርልድ ኮሌጅ በስፋት የዳሰሰ ስሆን በዚህ ዳሰሳ በተለይ  እውቀት እና ብልሀት ያበለፀጋት ሚጢጢ ሀገር ስለሚላት ሲንጋፖር የብልፅግና ሚስጢር ያሰፈረውን  ከመመልከታችን በፊት በቅድሚያ ጀዋር መሀመድ እንዴት የትምህርት እድል እንደገኘ ያሰፈረውን እንመልከት  ‹‹አንድ ቀን አሥረኛ ክፍል የተማርኩበት የጎሮ ትምህርት ቤት ዳይሬክተር አበራ ደሳለኝ ጠርቶኝ «ለአንድ የውጪ የትምህርት ዕድል ባለፈው ዓመት ሀገር አቀፍ ፈተና ከወሰዱ ተማሪዎች መካከል የጎበዝ ተማሪዎችን ሰም ላኩ ሲባል ያንተን ሰም ሞልቼ ልኬያለሁ› አለኝ። «አኔ እዚሁ መኖር እና መታገል አንጂ፣ ወደ ውጪ የመሄድ ፍላጎት የለኝም አልኩት። መምህር አበራ በጣም የሚያሰብልኝ እና የሚረዳኝ ሰው ነበር፤ በትምህርቴ ከማበረታታት አልፎ ከዘመድ ቤት ወጥቼ ሰቸገር የቤት ኪራይ የከፈለልኝ እሱ ነዉ። ቀልቤ በትግል እንደተማረከ ጠንቅቆ ሰለሚያውወቅ፡ ወደ ውጪአልሄድም የሚለው ተቃውሞዬ ብዙም ሳያሰገርመው፡ «ለማንኛውም የመጣው ቅጽ ላይ ስምሀን ሰለሞላሁት፣ መልሳቸውን አይተን አንወስናለን› አለኝ። ከሁለት ወር በኋላ «ማጣሪያውን ሰላለፍክ ለቃለ-መጠይቅ አዲስ አበባእንድትመጣ የሚል ደብዳቤ ሲላክ በመምህር አበራ ውትወታ እና ወጪ ወደ ፊንፊኔ ሄድኩ።(ገፅ 65)በማለት የሚገልጹት አቶ ጀዋር መሀመድ አዲስ አበባ ሄደው በመላው ሀገሪቱ ከተወጣጡ ተማሪዎች ጋር ተወዳደረው የትምህርት እድሉን በማግኘት ሲንጋፖር በማቅናት እውቅት እና ብልሀት ያበለጸጋት ሚጢጢ ሀገር ናት የሚሏትን ሲንጋፖር የእድገት ሚስጥር ያሰፉሩትን ሀሳብ አንደወረደ እንመልከት ፡፡

‹‹ያች የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችን ደሀ ደሴት በሰላሳ አመት ውስጥ በተአምር ቀይሮ ካደጉት ሀገራት ተርታ ያሰለፋት ሊኩዋንይው ነው ፡፡ እኔ ሲንጋፖር ሰደርስ ሥልጣኑን ለቆ ስለነበር በቴሌቭዥን የሚተለለፍ ንግግሩን፣ በትምህርት ተቋማት እናየሕዝብ መሰብሰቢያ አዳራሽ የሚሰጠውን ትምህርት (lecture) በመካፈል ብዙ ነገር ተማርኩ። «ሲንጋፖር ሊ ኩዋን ይው የሠራት ተዓምር ናት› ቢባል ከእውነት የራቀ አይሆንም ሀገሪቷ ትንሽዬ ደሴት ብትሆንም በምጣኔ ሀብት ዕድገት ግን በመጀመሪያው ደረጃ ላይ ከሚገኙ የዓለም ሀገሮች ተርታ ትመደባለች። ይህንን ፈጣን ዕድገት ከማሰመዝገቧ በፊት ግን ብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ አልፋለች። በድሮ ዘመን የማላይ ሕዝቦች ዓሣ የሚያጠምዱባትደሴት፡ አቀማመጧ ለውኃ ላይ ንግድ አመቺ ስለሆነ የአንግሊዝ ቅኝ ገዢዎች እ.አ.አ በ1819 ተቆጣጥረዋት ትልቅ የጦር እና የንግድ ወደብ ጣቢያ አደረጓት። ወደቡ ላይ የሚያገለግሉ ሠራተኞችን ደግሞ ከቻይና ያመጡ ነበር። አቀማመጧ ለአጎራባች ሀገሮች እምብርት ስለሆነች የወደብ አገልግሎቱ ተሰፋፍቶ የቀጠናው ዋና የንግድ ማዕከል ሆነች።››(ገፅ 73) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጃፓን ለአጭር ጊዜ ተቆጣጥራ ካሰተዳደረቻት በኋላ እንግሊዝ ተመልሳ በመቆጣጠር የፓሲፊክ የጦር ወደብ አድርጋ ቀጠለችበት። በሂደት የሲንጋፖር ነዋሪዎች አብዛኞቹ የቻይና ዝርያ ቢሆኑም እንግሊዝ የታላቋ ማሌዥያ ቅኝ ግዛት አካል አድርጋ ሰታሥተዳድራት ቆይታለች። እ.አ.አ በ1939 ማሌዥያ ነጻነቷን ሰትጎናጸፍ ችግሮች ተፈጠሩ። ነጻይቷ ማሌዥያ በሀገሬው የማላይ ብሔር እና ከቻይና መጥተው በሰፈሩት መካከል በተፈጠረ ውጥረት ትታመስ ጀመር። በትልቋ ማሌዥያ (mainland) የቻይና ዝርያ ያላቸው በቁጥር ብዙ ሰለሆኑ በሲንጋፖር ያሉት ከተጨመሩ ከሀገሬው (Native Malay) ጋር በቁጥር ሊመጣጠኑ ሆነ። የሲንጋፖር ቻይኖች መሪ ሊ ኩዋን ይው በሁለቱ ጎራ ያሉ ቻይኖችን በማሰተባበር ያሳየው ችሎታ ሲጨመርበት በማላይ ብሔርተኞች ለተቋቋመው የማሌዥያ መንግሥት አስፈሪ ሆነበት። አንዲሁም የማሌዥያ እና የሲንጋፖር ቻይኖች አንድ ለይ ከተጣመሩ፣ የማላይ ብሔርን አብላጫ (majority) ኃይል ያሳንሳል። ይሀ ደግሞ በታሪክ፣ በባሕል እናበፖለቲካ ለተገፋው የማላይ ሕዝብ የሀገር ባለቤትነት ዓላማውን ለማሳካት አንቅፋት እንደሚሆን ተገነዘቡ። የቻይኖቹን ቁጥር ለመቀነስ በማሰብ ሲንጋፖርን ከዋናዋ ማሌዥያ አንድትገነጠል ገፏት። ሲንጋፖር ኦገስት 9 ቀን 1965 በዓለም ላይ ያለፍቃዷ ነጻነትን የተጎናጸፈች ሀገር ሆነች። የፖለቲካ ነጻነት የተጎናጸፈችዋን ሲንጋፖር በኢኮኖሚ እራሷን ማስቻል ከባድ ፈተና ደቀነ። ደሴቷ በባሕር በመከበቧ ለወደብ አገልግሎት አመቺ ቢያደርጋትም ከዚያ ያለፈ የተፈጥሮ ሀብት አልነበራትም። ለእርሻ የተመቸ መሬትም ሆነ ማዕድን ሰላልነበራት፣ አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረው ከእንግሊዝ የጦር ሰፈሮች አገልግሎት በሚያገኘው ገቢ ነው። ሲንጋፖር ነጻነቷን እንደተቀዳጆች እንግሊዝ የጦር ካምፗን ለቃ ለመውጣት ወሰነች። ይህ የሕዝቡን ዋና የገቢ ምንጭ በማድረቅ ከፍተኛ አደጋ ተጋረጠ። ፈጣሪ ሲረዳቸው ሊ ኩዋን ይው የተባለ ጠንካራ መሪ ሰጣቸውና ከተጋረጠባቸው የኢኮኖሚ ውድቀት መትረፍ ብቻ ሳይሆን በፍጥነት አንዲመነደጉም ረዳቸው። ሊ ኩዋን ይው እንግሊዝ በሚገኘው ታዋቂው የካምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ የተማረ የሕግ ባለሙያ ሲሆን፣ ማሌዥያ ከቅኝ ግዛት ወጥታ ሲንጋፖር ነጻ ሀገር እንድትሆን ሲወሰን ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ተመረጠ። ገና ሥልጣን እንደያዘ የሲንጋፖርን መፃዒ ዕድል ሊቀይሩ የሚችሉ ወሳኝ ሐሳቦችን በማፍለቅ በፍጥነት ተገበረ።<<ሲንጋፖር ብዙ የተፈጥሮ ሀብት የሌላት እና የገቢ ምንጯም በሀገሪቱ በሰፈረው የአንግሊዝ ጦር ላይ ጥገኛ ስለነበረ፣ ይህ ጦር ሲለቅ ሊያጋጥማት የሚችለውን የኢኮኖሚ እና የደህንነት አደጋ ቀልብሳ ለማደግ የምትችለው በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ነው ብሎ አሰበ። የመጀመሪያው የሀገሪቷን ሰለም በማረጋገጥ የአካባቢው የኢንቨስትመንት ማዕከል ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ እንደሌሎች ሀገራት ኢንቨሰትመንት ለመሳብ የሚሰያችል የተፈጥሮ ሀብት ስለሌላት ያላት አማራጭ ጠንካራ ሙያ እና ሥነ-ምግባር ያለው የሠራተኛ ኃይል መፍጠር ነበር። እሳቤው በጠንካራ ሥነ-ምግባር የታነጸ እና ብቃት ያለው ሠራተኛ ካለ በአቅራቢያው ካሉ ሀገራት የበለጠ ኢንቨስትመንት መሳብ ይቻላል የሚል ነው። በተጨማሪም ሕጎች እና አሠራሮችን የኢንቨስትመንት ሥራን ሊያቀላጥፉ በሚችሉ መልኩ በመቅረጽ የሀገሪቷን ተወዳዳሪነት የበለጠ ማጠናከር ይቻላል በማለት አቅድ ነድፎ ወደ ሥራ ገባ።>>(ገፅ 74) ወደ ስራ ከገባ በኋላም ላሰበው እቅድ ፈታኝ ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ የሀገሪቱ የሰላምና ፀጥታ ጉዳይ ነበር ከዚህም መከከል የመጀመሪያው ኮሚኒዝም ሲሆን፣ ሁለተኛው የብሔሮች ብዝጎነትና ግጭት ነው። ዘመኑ ኮሚኒዝም በአካባቢው ሀገራት ብሎም በዓለም ላይ እንደ ሰደድ እሳት የተሰፋፋበት ስለነበር፣ አብዛኞቹ የሲንጋፖር ዜጎች ቻይናውያን ከመሆናቸው ጋር፣ ቻይና ለምትተዳደርበት የኮሚኒዝም ሥርዓት ሊጋለጡ ይችላሉ የሚል ሥጋት ነበር። እንደተፈራውም የኮሚኒሰት ፓርቲ ሲንጋፖር ውስጥ ተቋቁሞ ከፍተኛ ድጋፍ እያገኘ መጣ ፡፡ ካፒታሊዝምን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አድርጎ ቢጠቀምም የገቢ ልዩነት (income disparity) እንዳይሰፋ መንግሥት ኢኮኖሚውን ለመቆጣጠር ያለው ድርሻ ጠንካራ አንዲሆን አደረገ። ለፖለቲካ ሥልጣንም ሆነ ለልማት ድርጅት አመራርነት ችሎታ (meritocracy) በብቸኛ መሰፈርትነት ተወሰደ። መሰፈርቱን ራሱ በሚሾማቸው ሚኒሰትሮች ላይ በመተግበር ምሳሌ ሆነ።፣በሀገሪቷ ውስጥ ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ ቁልፍ ጥያቄዎች በመመለስ ከኣካባቢው ሁሉ ሰላሟ የተረጋገጠ በማረግ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ እና የጃፓን ትልልቅ ኢንቨሰትመንቶችን በአጭር ጊዜ ውስጥ አንድትስብ ረዳት።ሊ ኩዋን ይው ሲንጋፖር እ.አ.አ በ1959 ራሰ-ገዝ ሰትሆን ሥልጣን ይዞ፣ ከ30 አመታት በኋላ በ1990 ለቀቀ። በራሱ ብቃት እና እሱ መልምሎ ባሰማራቸው መሪዎች ጠንካራ አመራር ለቀን ጉርሷ አንኳን በእንግሊዝ የጦር ወደብ ላይ ጥገኛ የነበረች፣ ማሌዥያ አልፈልግሽም ብላ ያባረረቻትን ትንሸዬ ደሴት፣ በሠላሳ ዓመታት ውስጥ ከበለጸጉ ሀገራት ምድብ አሰለፋት።›› በማለት የሲንጋፖርን አስደናቂ እድገት ወዝ ባለው እና ለኛም ሀገር ትምህርት በሚሆን መልኩ ግሩም አርጎ አስፍሮታል ፡፡

የኦሮምያ ሚዲያ ኔትወርክ / OMN/ ምስረታ 

የኦሮሞ ታጋዮች የሚዲያን አስፈላጊነት የተረዱት ገና በማለዳው ነው። አንድን ሕዝብ ነፍጥ ከማስታጠቅ ይልቅ ንቃተ- ጎሊናውን ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን በመረዳት የትጥቅ ትግል ኮመጀመራቸው በፊት ሚዲያን ለማግኘት ሲተጉ ነበር በማለት የሚዲያን አስፈላጊነት በጊዜ ተረድተው ዝግጅት ከጀመሩ ቀደምቶቹ አንዱ ዶ/ር መሀመድ ረሻድ ሲሆኑ በግብፅ አል አዝሀር ዩኒቨርሲቲ የአፋን ኦሮሞ ራድዮ ፕሮግራም ለመክፈት የተጀመረው ጥረት በ 1962 ሱማሊያ ላይ ፍሬ አፍርቶ በቀን ለአምስት ደቂቃ አየር ላይ መዋል ጀመረ  በማለት የሚገልፁት አቶ ጀዋር መሀመድ ይህም  ለመጀመርያ ጊዜ ትግል ወደ ሚዲያ የመጣበት መሆኑን ይገልፃሉ ፡፡

ከራድዮ ባለፈ በቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ያለው የሚዲያ አማራጭ የሆነውን ኢንተርኔት አስመልክቶ እንዲህ ብለዋል  ‹‹በውጪ ያለው የኦሮሞ ሚዲያ ይበልጥ መስፋፋት የጀመረው ከኢንተርኔት መምጣት ጋር ተያይዞ ነው። በተለይ ፓልቶክ (paltalk) የተባለው የድረ- ገጽ መድረክ (plat form) ውጪ ያለው የኦሮሞ ማኅበረሰብ መረጃ እንዲለዋወጥ እና ለኦሮሞ ትግል ድጋፉን እንዲያጠናክር ጉልህ ሚና ተጫውቷል። ይሁን እንጂ ፓልቶክ ጥቅሞች እንዳሉት ሁሉ የኦነግ አንጃዎችን ሽኩቻ በማባባስ ረገድ ጉዳትም ነበረው። ከፓልቶክ ቀጥሎ ፌስቡክ መጣና ኦሮሞ ለራሱም ሆነ ለሌሎች መረጃ የማድረስ ዕድሉን የበለጠ እንዲያሰፋ አስቻለው።››በማለት  ማህበራዊ ሚዲያ ያበረከተውን አዎንታዊ አስተዋፅኦ ሲጠቅሱ OMNን ያቋቋምን ሰዎች ቀደም ብለን እንደ ፓልቶክ እና ፌሰቡክ ባሉ የማህበራዊ ሚዲያዎች ገና ከጅምሩ ስንሳተፍ ስለነበረ የኢንተርኔት መስፋፋት ይዞ የመጣውን ፋይዳ በጠዋቱ ለመረዳት ችለናል። ኢንተርኔት እየተሰፋፋ መሄዱ የኦሮሞ ትግልን የሚዲያ ሸፋን እያሰፋ ቢመጣም በጥንቃቄ እና በጥበብ ካልተመራ ከጥቅሙ ጉዳቱ አንደሚያመዝን ከፓልቶክ ልምዳችን ሰለተረዳን ፌስቡክ ላይ የእርምት እርምጃ ወሰድናል። በፌስቡክ ላይ መረጃ በማጋራት የሚታወቁ ዋና ዋና ሰዎችን በቡድን በማደራጅት፣ መረጃን በዝግ በመለዋወጥ አና በመወያየት የማኅበራዊ ሚዲያውን አጀንዳ አቅጣጫ ማስያዝ ቻልን። በዚህ መልኩ በሚዲያ በኩል ከመንግሥት ጋር በነበረው ግብግብ በአጭር ጊዜ የበላይነቱን ተቆጣጠርን። ስናስበው እና ስንዘጋጅበት የነበረው የሰላማዊ ትግል ሰልትም ሚዲያን በብቃት መጠቀምን ሰለሚጠይቅ፡ ከ2005-2012 በማኅበራዊ ሚዲያ ቆይታችን ጥሩ ልምድ አና ብቃት አካብተናል።››( ገፅ 181)ይላሉ ‹‹ የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክን ለማቋቋም በማሰብ የጀመሩትን የዶክትሬት ትምህርት ማቋረጣቸውን የገለፁት አቶ ጀዋር መሀመድ ይህ ውሳኔቸው በአማካሪያቸው ዘንድ ተቀባይነት ባያገኙም ትምህርታቸው አቋርጠዋል ለዚህም ዋነኛ ምክንያታቸው  «ቃል የገባሁትን ዳር ካላደረሰኩ ለሕዝቤ ከባድ የሞራል ውድቀት፣ ለአኔም ውርደት ነው›› በማለት ሲናገሩ ፡፡ ከሌሎች አቻዎቻቸው ጋር በመሆን ኦኤምኤን/ OMN/ አየር ላይ እንዲውል ማስቻላቸውን ሲጠቅሱ ሚዲያ ማቋቋም አንዱ የሰላማዊ ትግል እቅዳችን ስለነበር ዓለማው እውን መሆኑ አንደ ግለሰብም ሆነ አንደ ሕዝብ ለሚቀጥለው ምዕራፍ በልበ ሙሉነት እንድንገሰግስ በር ከፈተ። የሚሉት አቶ ጀዋር መሀመድ ‹‹ሐሳባችን ለአንድ ዓመት የሚዲያ ዘመቻ አድርገን ሕዝቡን አንቅተን ከዚያ በኋላ ወደ ተቃውሞ እርምጃ መግባት ነበር። ያልጠበቅነው ነገር ቢኖር ሕዝቡ አሰቀድሞ በመንግሥት በመከፋቱ ትዕግሥቱ ተሟጧል። የሚዲያ ዘመቻውን በጀመርን በሁለት ወር ውሰጥ አመጽ ፈነዳ። OMN (OMN) ማርች 1 ቀን 2014 ሥራ ጀምሮ፣ አመጹ ኤፕሪል 25 ቀን 2014 (ሚያዚያ 17 ቀን 2009 አ.ም) በዩኒቨርሲቲዎች ውሰጥ ተቀሰቀሰ። OMN አመጹን በየዕለቱ በመዘገብ እንዲሁም እኔ ፣ነጌሶ ዱቤ አና ፕሮፌሰር ሕዝቅኤል ገቢሳ በየጊዜው ትንታኔ እያቀረብን አቅጣጫ አና ሞራል በመስጠት ተቃውሞውን አቀጣጠልነው።›› (ገፅ 189) በማለት ለተነሳው ህዝባዊ ተቀውሞ ሚዲያ በማቋቋም ብሎም የተለያዩ ተቃውሞዎችን በመምራት ደማቅ ብለው የሚጠሩትን አሻራ ማሳራፋቸውን ይገልፃሉ ፡፡

ትግል አና ድል

‹‹አንድን አምባገነን ሥርዓት በሰላማዊ የትግል ስልት ለመቀየር ወደ ሙሉ ግብግብ (full scale confrontation) ከመግባት በፊት፣ መጀመሪያ ሕዝቡን የማነቃቃት ሥራ መሥራት ያስፈልጋል። በመቀጠል ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት እና ትናንሽ ዘመቻዎችን (campaigns) ማካሄድ ተገቢ ነው። በሰላማዊ ትግል ለውጥ መጥቶ በማይታወቅበት ሀገር ውስጥ ሕዝቡ በሰላማዊ ስልት ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ ይኖረዋል። በቀላሉ ማሸነፍ የሚቻሉ ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን ማንሳት እና በአጫጭር ዘመቻዎች ማሰመለስ ሕዝቡ ከሰላማዊ ትግል ጋር እንዲለማመድ እና ውጤታማነቱን በማየት ተሳትፎውን እንዲያጠናክር አጋዥ ነው። እኛም በሙሉ አቅማችን ወደ ቄሮ ትግል ከመግባታችን በፊት፡ አነስ ያሉ ዘመቻዎችን በማካሄድ ሕዝቡን ከሰላማዊ ትግል ጋር እያዕተዋወቅን ሄድን >>(ገፅ 204) በማለት የሚገልፁት  አቶ ጀዋር  መሀመድ ቀለል ያለ ካሉት የመጀመርያው #boycottbedele( በደሌ ቢራ እንዳይሸጥ እና እንዳይጠጣ) የማድረግ ዘመቻ ሲሆን ምክንያቱም በጊዜው ሊካሄድ የነበረው የቴዲ አፍሮ ኮንሰርት ስፖንሰር የነበረው የሄኒከን ቢራ ምርት የሆነው በደሌ ቢራ በብዛት በሚሸጥበት ኦሮሚያ ክልል እንዳይጠጣ የእቀባ ስራ የሰሩ ሲሆን በዚህም ድል ተገኝቷል ይላሉ ፤ሌላኛው ትግል የነበረውና ድል የተገኘበት ጉዳይ የኦሮሚያ ክልል በ2008 እና 2009 የትምህርት ዘመን በኦሮሚያ ውስጥ ሕዝባዊ አመጽ በተከታታይ ስለሚደረግና ትምህርት ቤቶችም ስለሚዘጉ የመማር ማስተማሩ ሂደት በአግባቡ አልተካሄደም። ተማሪዎቹም በተቃውሞው በግንባር ቀደምነት ስለሚሳተፉና ልባቸው ትምህርት ላይ ስላልነበር፤የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና (Entrance Exam) ለመውሰድ በቂ ዝግጅት እንዳላደረጉ ግልጽ ነበር በዚህም ሳቢያ የፈተና ጊዜ በሁለት ወር ይራዘምልን ጥያቄ ቢያቀርቡም በመንግስት ዘንድ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ሳቢያ ግንቦት 22 ቀን 2008 ዓ.ም ሊሰጥ የነበረውን ሀገር አቀፍ ፈተናውን የማክሸፍ ዘመቻ በድል መወጣታቸውን፡ ከዚህ ባለፈ ሌላው ድል የተገኘበት በማለት የሚገልፁት በኦሮምያ የተጠራው ታላቁ ሰልፍ ሲሆን በ 350 ከተሞች ሰልፍ የተደረገ ሲሆን አላማውም ተቃውሞውን ሁለን አቀፍ ለማድረግ ታልሞ ነበር ይህም  ትግሉ ከተቃውሞ ወደ ንቅናቄ ደረጃ መሸጋገሩን ያሳየበትና ድል ያረግንበት ነው በማለት ሲገልፅ ከዚህ ባለፈ ሌላው ታግለው ድል ያመጡበት  የቄሮ እንቅሰቃሴ ለኦሮሞ ትግል ይጠቅማል ብዬ ያጠናሁትን አና የተመራመርኩበትን ሰልት ወደ ሥራ የቀየርኩበት፡ እንዲሁም በሕዝብ ዘንድ እውቅና እና ፍቅር ያሰገኘልኝ፣ በአንዳንድ የፖለቲካ ቡድኖች ዘንድ ጥላቻና ባላንጣ ያበዛብኝ ነበር በማለት ሲገልፁ 

«Qeeyroo mataa tuutaa,

Hin jarjartu suuta»

«ቄይሮ ጸጉሩ የተከመከመ፣

ይመጣል እያዘገመ።››

የተባለለት ቄሮ የተሰኘው የወጣቶች የተቃውሞ እንቅስቃሴ በስፋት ወደ ተግባር የገባው  በሚያዚያ 2006 ዐ.ም በተቀናጀ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ስም የመንግሥትን የመሬት ወረራ እቅድ በመቃወም የተማሪዎች አመጽ መቀስቀስ ነው። ተቃውሞው በፍጥነት ወደ ሁሉም የኦሮሚያ ዞኖች ተዛመተ። መሬት ላይ ከሚደረገው ተቃውሞ በተጨማሪ በማኅበራዊ ሚዲያ በተለይም በፌሰቡክ የመረጃ ልውውጥ እና ቅንጅት ተጀመረ። አመጹ ከመፈንዳቱ በፊት መንግሥት ማስተር ፕላኑን እያዘጋጀ እንደሆነ መረጃ ሲደርሰን፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻ በማካሄድ ስንቃወም ነበር። OMN ማርች 1 ቀን 2014 (የካቲት 22/2006 ዓ.ም) ሲጀመር ዘመቻውን በስፋት አጧጧፍነው። ሚያዚያ መጨረሻ አካባቢ ተቃውሞው በዩኒቨርሲቲዎች ሲፈነዳ በ#BoycottBedele ዘመቻ የተሳተፉ አንቂዎችን በማሰባሰብ የሀገር ውስጥ ተቃውሞውን በማኅበራዊ ሚዲያ እና በተለያዩ ሚዲያዎች በተቀናጀ መልኩ መደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመወያየት የማቀናጀት ሥራ ጀመርን። ተቃውሞው ዓለም አቀፍ ድጋፍ ማግኘት እንዲችል የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻው ዲፕሎማቶች እና የውጭ ሚዲያዎችን መሳብ በሚችል መልኩ #oromoProtests የሚለውን ሀሸታግ መጠቀም ጀመርን። በአጠቃላይ ትግሉን ለመግለጽ ደግሞ «የኦሮሞ ቄሮ ንቅናቄ› የሚለውን ለመጠቀም ወሰንን።>>(ገፅ 209) የሚሉት ፀሀፊው በአራት አመት ውስጥ ጦር መሳርያ ሳይዝ የመንግስት ለውጥ ማምጣት የቻለ የቄሮ እንቅስቃሴ ለኦሮሞ ህዝብ ይጠቅማል ብየ ያጠናሁትና የተመራመርኩበት የወጣት ንቅናቄ ነው በማለት ያሞካሹታል ፡፡

ኮማንድ ፖስት ያላዳነው ውድቀት

የአምስቱ ቀናት ዘመቻ በስኬት ከተጠናቀቀ በኋላ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አቋቁሞ መጠነ-ሰፊ ጥቃት ሊፈጽም እንደሆነ ስለደረስንበት አስተባባሪዎቹ ኅቡዕ (underground) እንዲገቡ ተደረገ። ይህም ብዙዎቹ ወደ ትላልቅ ከተሞች ሸሽተው እንዲደበቁ ማድረግ ነበር። መንግሥት ኦሮሚያን ኮማንድ ፖስት ሥር አስገብቶ የጅምላ እሥራት ጀመረ። እስሩ ደግሞ እንደቀድሞ ፖሊስ ጣቢያ ሳይሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች ሊወሰዱ መታቀዱን መረጃ ስለደረሰን፤ ይህን የመንግሥት እርምጃ ወደ መልካም ዕድል ለመቀየር የሚያስችል ሐሳብ ቀረበ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተወሰኑ አስተባባሪዎች በስተቀር ቄሮዎች ትግሉን ሲያቀናጁ የነበሩት በአካል ሳይተዋወቁ በማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ብቻ ነበር።>> የሚሉት አቶ ጀዋር መሀመድ ከኢሬቻ በአል አከባበር ጋር ታያይዞ በደረሰው የሰው እና የንብረት ጉዳት ሳቢያ ለ 5 ቀናት የነበረው የቁጣ ዘመቻ ባስከተለው ተጨማሪ ጉዳት ሳቢያ መንግስት የኮማድ ፖስት እንዲያቋቁም ያስገገደደው ክስተት ነበር ›› ከኮማንድ ፖስት መቋቋም በኋላ እጅጉን በተጠና መልኩ የተካሄደውን የገበያ እና የትራንስፖርት እቀባ ዘርዘር ባለ መልኩ አስፍረዋል ፡፡

‹‹መንግሥት ኮማንድ ፖስት እንዳወጀ በቄሮ በኩል ለጊዜው የትግል እርምጃዎችን ከመውሰድ ለመቆጠብ ተወሰነ። ለዚህ ብዙ ምክንያቶች ነበሩ። የመጀመሪያው መንግሥት በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ትልቅ ኃይል አሰማርቶ ሕዝብን ለመጨፍጨፍ ስላቀደ ይህንን ኃይል መጋፈጥ ከጥቅሙ ኪሳራው ይበልጣል። ሁለተኛው፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ቄሮ ለውስጥ ግንኙነትም ሆነ ለፕሮፓጋንዳ ሥራ ኢንተርኔት ላይ ጥገኛ ሆኗል። ከቁጣ ዘመቻው በኋላ ኢንተርኔት በመቋረጡ ሌላ ዘዴ እስክናዘጋጅ ድረስ ተቃውሞውን ማቋረጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኘ። ሦስተኛው፣ ከኅዳር 2008 ዓ.ም ጀምሮ ሕዝቡ ያለ በቂ ዕረፍት ለአንድ ዓመት ያህል ትግል ላይ ስለቆየ፤ በተፈጠረው አጋጣሚ ዕረፍት ወስዶ ለቀጣዩ ዙር ትግል በሙሉ ኃይል እንዲዘጋጅ ነው። አራተኛው፣ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በቄሮ እንቅስቃሴ ውስጥ የታዩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችን በመተንተን እና በመገምገም ለቀጣዩ ዙር ክፍተቶችን ለመሙላትና ጠንካራ ጎኖችን ይበልጥ ለማጠናከር በተረጋጋ መንፈስ ማሰብ እና ማቀድ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው።›› በማለት ስልታዊ በሆነ መልኩ ለምን በቄሮ በኩል እርምጃ ለመውሰድ እንዳልፈለጉ ምክንያቶችን በመጥቀስ ያብራራሉ ፡፡ በዚሁ መሠረት ለአሥር ወራት በቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በኅቡዕ ለገቡትም ሆነ ወደ ወታደራዊ ካምፖች ለተጋዙት ቄሮዎች የአቅም ግንባታ (capacity building) ተሰጣቸው በዚህ ሁኔታ ቄሮ ከዚህ በኋላ ሥጋት አይሆንም በሚል እሳቤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ሐምሌ ወር 2009 ዓ.ም ተነሳ፤ የኢንተርኔት ግንኙነትም ተለቀቀ። ሆኖም በቄሮ በኩል በፍጥነት ወደ እንቅስቃሴ ከመግባት ይልቅ በዝግታ መሄዱ ተመራጭ ሆነ። ምክንያቱም ለስድስት ወራት ዕረፍት ላይ የቆየውን ሕዝብ ቀስ በቀስ በማሟሟቅ ወደ ትግል መንፈስ እንዲመለስ ማድረግ ስለሚያስፈልግ ነበር። መንግሥትን በአንዴ አስበርግጎ ወደ ከባድ የኃይል እርምጃ ከመመለስ ቀስ በቀስ መሄዱ የተሻለ ነው ብለን አሰብን። በዚሁ መሠረት ቀለል ያሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ጀመርን የሚሉት አቶ ጀዋር ለዚህም በዋነኛነት የጠቀሱት የግብር ጉዳይ ሲሆን በሁከትና እና ብጥብጥ በከረመቸው ኦሮሚያ ስራ የቀዘቀዘበት ነጋዴ ግብር ቀንሱ ሲል በአንፃሩ  የግብር ገቢ የቀነበሰበት መንግስት ግብር ለመጨመር አሰበ ይህን ተቃርኖ እንደ ትግል መሳርያ በመጠቀም ነጋዴውን ወደ አመፅ በማስገባት የኢኮኖሚ አሻጥር ( economic sabotage ) መፍጠር ብሎም የትራንስፖርት እቀባ እንዲደረጉ በማድረግ ሁለቱን እቀባዎች በአግባቡ በመከወን እንዲሁም አዳዲስ የትግል ስልቶችን በመጨመር አድማሱን አስፍተን ሥርዓቱን የበለጠ መከፋፈል እና ማዳከም ቻልን። ከትግል ዘመቻዎች ጎን ለጎን ከመንግሥት ሰዎች ጋር ስናደርግ የነበረው ንግግር እና ድርድርም ወደ ውጤት እየተቃረበ መጣ።›› የሚሉት ጃዋር መሀመድ በፊት አውራሪነት  የመራው የተቀውሞ እንቅስቃሴ ውጤት ማፍራቱንተከትሎ ገና ከጅምሩ ለመንግሥት ቀረቤታ ባላቸው ሰዎች፣ በመንግሥት ባለሥልጣናት እና በውጭ ዲፐሎማቶች አማካኝነት ለድርድር ያለንን ፈቃደኝነት ስንጠቁም ቆይተን፡ በሂደትም ምሥጢራዊ ውይይት ወደ ማድረግ ተሸጋገርን የሚሉት አቶ ጀዋር ስላደረጉት ድርድር እንዲሁም ለውጡን ማን ይምራው በሚለው ላይ ሳፋ ባለ መልኩ በመጽሀፋቸው አብራርተዋል ፡፡

የለውጡ መንሸራተት

ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ተቃውሞየን በልቤ ይዤ ሽግግሩ እንዲሳካ ለማገዝ ወሰንኩ ‹‹ገና ከጅምሩ የአሮሞን የትግል የሚቃረኑ ትርክቶችን እና ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር ሊያደናቅፉ የሚችሉ እርምጃ እየወሰደ ስለነበር ከመተቸት ይልቅ ሂሳዊ ድጋፍ (Critical support ) እየሰጡ ሽግግሩን ለማሳለጥ ሞከርኩ መጀመሪያ አካባቢ በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የአመራር አካሄድ ላይ ያለኝን ትችት በይፋ (publicly) ከመግለጽ ብቆጠብም፤ በአጋጣሚ በቀጥታ ስንገናኝ ወይም በሰዎች በኩል ከመግለጽ ግን አልተቆጠብኩም። በተለይ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ እና ብርሃኑ ጸጋዬ ጋር ብዙ ጊዜ በመመላለስ መወትወቴን አላቆምኩም። በእኔ እና በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መካከል ያለው የሐሳብ መራራቅ ስላሳሰባቸው ለማጥበብ ብዙ ሞክረዋል፤ በኋላ ግን እነሱ ራሳቸው ከመንግሥት ተገፍተው ወጡ። (ገፅ 311) ሲሉ እኔንና   ጠቅላይ ሚኒስትሩን ካነታረኳቸው ጉዳዮች መካከል በዋነኛነት የለውጥ ሞተር የሚባሉት አንዱ የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ መስማታቸው  ከኦሮሚያ መነሳት ከራሱ ከአቶ ለማ መገርሳ መስማታቸው ሲሆን ይህን የተረዳው አቶ ጀዋር ከአቶ ሌጮ ባቲ ጋር በመሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሊያግባቡ ቢሞክሩም ሳይሳካ ቀርቷል ሌላው ኢህአዴግን ማክሰም ወቅቱን የጠበቀ አይደለም በሚል ውህደቱ አሁን የሚጠበቅ አይደለም በማለት ተሟግተዋል ፡፡ ኢህአዴግን አፍርሶ ወደ ብልፅግና መግባት ትግራይን ያስቆጣ እና በህወሀት ተቀባይነት አያስገኝም ከሚል ስጋት የነበረ ቢሆንም የአቶ ጀዋር መሀመድ ስጋት ትክክል ሆኖ ሀገሪቱን  ለሁለት አመታት ለዘለቀ የእርስ በእርስ ጦርነት ዳርጓታል ፡፡

ሀገር አልባ ባለ ሀገር

‹‹ያመንኩበትን ያለገደብ መናገር እና ያቀድኩትን በፍጥነት መሥራት ስለምወድ የፓርቲ ፖለቲካ አይመቸኝም። በፖለቲካ ድርጅት ማዕቀፍ የመንቀሳቀስ አቅድም ኖሮኝ አያውቅም። በሁኔታዎች አስገዳጅነት ወደ ፓርቲ ፖለቲካ ለመግባት ስወሰን ከሚቀናኝ እና ከለመድኩት አሠራር ለመውጣት ተገደድኩ።›› ከሄዱበት አሜሪካ ተመልሰው ኦፌኮ ፓርቲ ጋር የተጣመሩት ጀዋር መሀመድ ‹‹ዜግነቱ ኢትዮጲያ ያልሆነ ሰው አባል ማድረግ ህግ መጣስ ነው በሚል በምርጫ ቦርድ ለኢፌኮ ደብዳቤ ፃፈ በዘህ ምክንያት ፓስፖርታቸውን ለመመለስ ቢያስቡም ኢትዮጲያ የጥምር ዜግነት (Dual Citezenship) የሚፈቅደውን ህግ ልታወጣ በመሆኑ ሁለቱንም ትይዛለህ የሚል ቃል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተገብቶላቸው እንደነበር ይጠቅሳሉ የአሜሪካ ፓስፖርት እንዳለኝ እና ያንን መልሼ የኢትዮጲያን  ዜግነት መውሰድ እንደምፈልግ መጀመርያ በቀጥታ ለጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በኋላ  በሚዲያ በይፋ ለህዝብ የገለፅኩ ብቸኛ ፖለቲከኛ እኔ ነበርኩ እውነቱ ይሄ ሆኖ ሳለ ምርጫ ቦርድ እኔ ላይ ብቻ አተኮረ ››በማለት በምርጫ ለመወዳደር ማሟላት ያለብኝ ቅድመ ሁኔታዎች ለሟሟላት የማደርገውን ሂደት አጓተተብኝ በማለት ወቀሳ አቅርበዋል ፡፡

የኢትዮጲያ ዜግነት ድጋሚ እንዲሰጠኝ የአሜሪካ ዜግነት መመለሴን የሚያሳይ ሰርተፍኬት ተቀብለው ፓስፖርት የመለስኩት የምርጫ መስፈርት ለማሟላት ብቻ አልነበረም የሚሉት ጀዋር ከህዝቤ ጋር ደግ እና ክፉውን ለመቀበል የገባሁት ቃል ለመሙላት ነው ይላሉ ይሁንና ቶሎ ዜግነት የማግኘት ጉዳይ  በላማለቁ በተለይ የኢሚግሬሽን ሰዎች የኢትዮጲያ ዜግነት እንዳይሰጡኝ በቀጥታ ከበላይ አካላት እንደታዘዙ ስለሰማን  ነገሩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ቢታሰብም የኢትዮጲያ ዜግነት ሳያገኙ (state less) በሆኑበት ወቅት የኮሮና ቫይረስ ገባ እኔም ታሰርኩ በማለት በመፅሀፋቸው ሲያሰፍሩ ሀገር አልባ የሆኑት ባለሀገር ከሁለት አመት በኋላ ከእስር መልስ እንደገና ዜግነታቸውን  ለማግኘት ችለዋል ፡፡

ረጅሙ እረፍት

‹‹ለአንደኛው የዓለም ጦርነት የኦስትሮ-ሃንጋሪው ልዑል ፍራንዝ ፈርዲናንድ፣ ጋቭሪሎ ፕሪንሲፕ በተባለ የሰርቢያ አክራሪ መገደሉ ክብሪቱን ሊያቀጣጥል ችሏል። የልዑሉ ደም ቤንዚን ሆኖ አውሮፓን ጨምሮ መላውን ዓለምን ያዳረሰ ፍጅት እና ውድመት አስከተለ። የፈርዲናንድ መገደል ብቻውን ግን ለአንደኛው የዓለም ጦርነት መከሰት በቂ ምክንያት ሊሆን አይችልም።ከዚያ በፊት የአውሮፓ ፖለቲካ በመቃቃር፡ በወታደራዊ ፉክክር እና በድንበር ውዝግብ አብጦ ሊፈንዳ ተቃርቦ ነበር። ግድያው ያበጠውን ፖለቲካ አፈንድቶ በዝግጅት ላይ የነበሩ እና በዓይነ ቆራኛ ሲተያዩ የቆዩ ኃይሎችን ፊት ለፊት አላተማቸው።››(ገፅ 349) በማለት የፈርዲናንድ መገደል ለአንደኛው የአለም ጦርነት እርሾ መሆኑ የሚገልፅት አቶ ጀዋር መሀመድ ይህንኑ ክስተት ከኛው ሀገር ታዋቂው የኦሮምኛ ዘፋኝ ድንገተኛ ህልፈት ጋር አያይዞታል ከሀጫሉ ጋር ያን ያህል የቀረበ ግንኙነት ባይኖራቸውም የሀሉጫን ዘፈን ማዳመጥ ግን የሰርክ ተግባራቸው እንደነበር እንዲህ በማለት ይገልፃሉ ‹‹በቤቴ እና በዩኒቨርሲቲዬ መካከል በባቡር ስመላለሰ ዘፈኑን ደጋግሜ በማዳመጥ እመሰጣለሁ። ቤተ-መጻሕፍት ውሰጥ ሳጠና እና ስጽፍ በሀጫሉ ዘፈኖች እራሴን አነቃቃለሁ።የሰላማዊ ትግል ስትራቴጂ ለመንደፍ ብዙ እያብሰለሰልኩ እና እራሴን እያዘጋጀሁ የነበረበት ወቅት ስለነበር፡ “ኦሮሚያ ቲያ” እና ”ማሳን ገማ” የተሰኙ ዘፈኖቹ መነቃቃት እና ብርታትን አጎናጽፈውኛል። አወዛጋቢውን “Oromo First” አባባል የተጠቀምኩበትን የአልጀዚራ ቃለ-ምልልሰ ለመስጠት ከኒው ዮርክ ወደ ዋሸንግተን ዲሲ በባቡር ሰጓዝ “ማሳን ገማ” የሚለውን ዘፈን ደጋግሜ እየሰማሁ ነበር። ወደኋላ መለሰ ብዬ ሳስበው በቃለ-ምልልሱ ላይ ያንጸባረኩት ስሜት ውሰጥ የከተተኝ ዘፈኑ ይመሰለኛል።›› በማለት የሚናገሩት አቶ ጀዋር መሀመድ ‹‹የሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያም በኦሮሞ አና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሰጥ አየተባባሰ የነበርውን ውጥረት በማፈንዳት አሁንም ድረስ ሀገሪቱን በየአቅጣጫው አየናጠ ወዳለው የአርስሰ በእርሰ ግጭት የከተተ አሳዛኝ ክስተት ነው። ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት አንደነበረው የአውሮፓ ፖለቲካ፣ ከሀጫሉ ሁንደሳ ግድያ በፊት በኦሮሞ እና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውሰጥ በተለያዩ ወገኖች መካከል ያለው መቃቃር፡ዛቻ እና ቅራኔ ከቀን ወደ ቀን እየተጠራቀመ እና እየተባባሰ ሄዶ አብጦ ነበር። የሀጫሉ ግድያ ያበጠውን የፓለቲካ ቀዉስ አፈነዳው። የሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ መንግሥት በኦሮሞ ላይ የከፈተው እሥራት እና ግድያ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች የትጥቅ ትግል ለማድረግ ወደ ጫካ እንዲያመሩ ምክንያት ሆነ። በኦሮሞ ልሂቃን እና በሕዝቡ መካከል ከፍተኛ መሰንጠቅ ፈጠረ። በአጠቃላይ የሀጫሉ ግድያ የኦሮሞን ሕዝብ ለጥልቅ የልብ ስብራት ያጋለጠ ክስተት ነው ማለት ይቻላል። በዚሀ ሕዝብ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ እንደዚያች ዕለት የጋራ ድንጋጤ እና ሀዘን አጋጥሞ አያውቅም። ኦሮሞ በዚያ ቀን ከተፈጠረበት ድንጋጤ እና ቁጣ ዛሬም ድረስ ያገገመ አይመስለኝም በማለት የሀጫሉ ሞት የፈጠረውን ታላቅ ድንጋጤ ፤ሀዘንና ቁጣ ያመጣውን አሉታዊ ውጤት ገልፀዋል ፡፡

ሀጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ በፊት አነጋጋሪ የነበረው  ከ omn ጋር ያረገው ቃለ ምልልስ ብዙዎች የሚያስታውሱት እና ለህልፈቱ መንስኤ ይሆናል ተብሎ የተሳበ ሲሆን አቶ ጀዋር መሀመድ ባቋቋሙት ጣቢያ ኢንተርቪው እንዳይሰጥ ለሀጫሉ አስረግጠው መናገራቸውን ይገልፃሉ ‹‹ደውዬለት፣ ቤቴ ጋበዝኩትና በዚህ ሰዓት ሚዲያ ላይ ባይታይ እንደሚሻል ነገርኩት። እሱም በብስጭት በተሞላበት ድምፅ «ለምን ሁልጊዜ ከሚዲያ ልትከለክለኝ ትፈልጋለሀ?›› በማለት ሀጫሉ ሁንዴሳ እንደተቃወማቸው ገልፀዋል ብዙም ሳይቆይ ወደ OMN ቢሮ ሄዶ ቃለ-ምልልሰ እንደሰጠ ሰማሁ። ቃለ ምልልሱን ከሰጠ በኋላ እኔ ጋር መጥቶ መታገስ አቅቶት እንደተናገረ ነገረኝ። ብቻችንን ለሰዓታት አወራን። ኦሮሞ የትላንቱን አገዛዝ በአንድነት ገርስሶ ዛሬ ግን ተከፋፍሎ እርስ በእርስ መዋጋቱ እንዳስከፋው እና በኦሮሞ አመራር በጣም ማዘኑን አወጋኝ። «እንኳንም በሕይወት ያለን ሰው አወድሽ አልዘፈንኩ። በሕይወት ያለ ሰው አንድ ቀን ያኮራህና በሌላ ቀን ደግሞ ያሳፍርሃል። የሞተ ሰው ግን የሠራውን ጥሩ ታሪክ ለማጉደፍ ዕድል ስለሌለው እሱን ብታሞግሰውም ሪስክ የለውም» አለኝ። ንዴቱን ለማስረሳት በማሰብ «በቃ አታስብ የምትዘፍንለት ሰው አታጣም፣ በቅርቡ እኔን መግደላቸው ስለማይቀር ትዘፍንልኛለሀ›› ብዬ ቀለድኩ። ሀጫሉ ሊሄድ ሲንሳ የእሱ ደጎንነት ስላሳሰበኝ ሁለት ጠባቂዎቹን እንዲወስድ ተማጸንኩት። እሱ ግን ቴኳንዶ የተማረ ወንድሙ አብሮት ስላለ ችግር የለውም በማለት እምቢ አለ። ሀጫሉን ከዚያ ቀን በኃላ በአካል አላገኘሁትም። ከጥቂት ቀናት በኋላ በአሳዛኝ ሁኔታ ገደሉት በማለት  የእሳቸውና  እና  የሀጫሉን የመጨረሻ ሰአት ንግግሮች ከላይ ባለው መልኩ አስፍረዋል  ከሀጫሉ ሞት በኋላ ስላጋጣማቸው እስር ፤የቃሊቲ ክራሞት ፤ስለፍርድ ቤት ሂደት በማረሚያ ቤት ስላካሄዱት የረሀብ አድማ በመጨረሻው ምእራፍ ከእስር ስለመፈታታቸው የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት መንግሥት አንዲፈታቸው በተደጋጋሚ ስላደረጉት ጫና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እና የአጋድ ዋና ጸሐፊ ዶ/ር ወርቅነሀ ገበየሁ ጠ/ሚኒሰትር ዐቢይን አግኝተው፣ሰለትግራይ ጦርነት ሲወያዩ መፈታት አንዳለባቸው በግልጽ ስለመጠየቃቸው ፕሬዝዳንት ኬንያታም ከእስር ከተፈታሁ ለደህንነቴ ወደ ኬንያ ሊወሰደኝ እንደሚችል ቃል ስለመግባቱ ዶ/ር ወርቅነህም ከእስር መፈታቴ ሕይወቴን ከማዳን ባለፈ ለሀገሪቱ መረጋጋት እንደሚጠቅም ስለመናገሩ ጀዋር ከእስር  ወጥቶ ትግሉን ያቀጣጥላል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም በተቃራኒው የሰላም ሰባኪ ስለመሆኑ እና ነገሮችን ለማረጋጋት ሰለሞከሩበት ሁኔታ ፤ከውጭ ማህበረሰብ ጋር ስላደረጉት ውይይት እና ሌሎች ተግባራት በመጨረሻው ምእራፍ ሰፋ ባለ መልኩ አስፍረዋል ፡፡

እንደ መውጫ

በዚህ መጽሀፍ ውስጥ ከልጅነት ጀምሮ አመለካከቴን በመቅረፅ ረገድ ሚና የነበራቸው ማህበራዊ ኢኮኖሚያ እና ፖለቲካዊ ሁነቶች በትምህርት ቆይታ የቀሰምኩትን እውቀት እና  በአለም ዙርያ ባደረኩት ጉዞ ያካበትኩትን ልምድ በማጣመር የትግሉ ሂደት ፈር አስይዣለሁ የሚሉት አቶ ጀዋር መሀመድ በጠዋቱ በተጠናወታቸው የትግል መንፈስ ሀይል ተነሳስቼ የተወለድኩበትን ህዝብ ከጭቆና የማውጣት አላማ ለማሳካት በመትጋት ሂደት ውስጥ ከጫፍ ለደረሱ አደጋዎች ተጋልጫለሁ ለቅስም ሰባሪ የስም ማጥፋት ዘመቻዎች ተዳርጌአለሁ ሆኖም ማንኛውም ለከፈልኩት መስዋእትነት ትክክለኛነት ላመንኩበት አላማ የተከፈለ ተከፍሎም ውጤት ያስገኘ ስለሆነ አልቆጭም ለዚህም ነው ርእሱን ‹‹አልፀፀትም ›› ያልኩት ይላሉ ይህ ማለት ፖለቲካ ስራየ ሁሉ ምንም ስህተት አላገኙሁበትም ማለት አይደለም ቀላል ሊባሉ የማይችሉ መስዋአትነት ለከፈሉት ትግል ‹‹አልፀፀትም›› ቢሉም መፅሁፉን በጥሞና እንዳነበበ አንድ አንባቢ በእርግጥም አልፀፀትም ቢሉ ተገቢ የሚሆኑ ጉዳዮችን አንስቼ የግድ ሊፀፀቱበት የሚገባቸውን ጉዳዮች አንስቼ ላጠቃል ከልጅነት እስከ እውቀት በነበረ ትግል የ OMN ቴሌቭዥን ጣቢያ  ከጥንስስ ጀምሮ እስከ ምስረታ  ባደረጉት ስራ አልፀፀትም ቢሉ እንደ እኔ ተገቢ ይሆን ይሆናል የኢህአዴግ መክሰም በተለይ ህወሀትን  አስከፍቶ ወደ ግጭት ያመራል በማለት እንደ በሳል ፖለቲከኛ ያነሱት ሀሳብ ተግባራዊ ባይሆንም ይህን ሀሳብ አንስተው በመሞገቶ አልፀፀትም ቢሉ እንደእኔ ተገቢ ነው እላለሁ  ኦሮሚያ በሁከትና ብጥብጥ በነበረበት ወቅት በጊዜው የነበሩ የሀገር አቀፍ ማጠቃለያ ፈተና ተፈታኞች እንዳይጎዱ  በማሰብ ፈተና በማሰረዝ አልፀፀትም ቢሉ ተገቢ ይሆን ይሆናል የሚዲያ ሀይልን በመገንዘብ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክን ለማቋቋም በማሰብ ከአንድ ሁለት ጊዜ የዶክትሬት ትምህርቶን ለማቋረጥ በመገደዶ አልፀፀትም ቢሉ ተቀባይት ይኖረዋል የወቅቱን ሁኔታ በማጤን ሃጫሉ ኢንተርቪው እንዳይሰጥ እንዲሁም በቂ ጥበቃ እንዲያገኝ እና ከሞት አደጋ ለመከላከል ባደረጉት ጥረት ላይፀፀቱ ይችሉ ይሆናል በሀጫሉ ሞት  ምክንያት ወደ ማረምያ በመውረዶ የፅሞና ጊዜ በማግኘቶ ብሎም በረሀብ አድማ ሳቢያ የህክምና እርዳታ ታደርግሎ ከነበረችው ዶ/ር ኢሊሊ ጋር ተዋውቀው ትዳር መመስረቶ ብሎም  ይህን መፅሀፍ በማበርከቶ ላይፀፅቱ ይችሉ ይሆናል የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ከመንግስት ጋር እርቅ ይፈፅም ዘንድ ወደ ሰላም እንዲገባ ያላሰለሰ ጥረት በማድረጎ  ላይፀፀቱ ይችሉ ይሆናል በሺዎች የሚቆጠሩ ህይወት ሲቀጥፍ የነበረው በኦሮሞ እና በሱማሌ መካከል የነበረው ግጭት ረግቦ ወደ ሰላም እንዲመለሱ በማድረጎ አልፀፀትም ቢሉ  ተገቢ ነው  በተቃራኒው የአዲስ አበባ ማስተር ፕላን በመቃወም ወጥተው አምቦ ላይ ህይወታቸውን ስላጡ ንፁሀን ብሎም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከዚሁ ማስተር ፕላን ጋር  በተያያዘ ከ200 ባለይ ዜጎች ህይወት ማለፍ ፤ ታላቁ ሰልፍ ብለው በመፅሀፉ ስለገለፁት እና 200 ሰዎች ስለሞቱበት ሰልፍ  በ 2009 አ.ም  በተከበረው የኢሬቻ በአል ሕይወታቸውን ስላጡ በመቶዎች ስለሚቆጠሩ ዜጎች ህይወት ብሎም በአምስቱ ቀን ቁጣ ስለጠፋ የንፁሀን ንብረት እና ህይወት  ከግል ጠባቂዎ መነሳት ጋር ተያይዞ  በተነሳ ግርግር ነፍሳቸውን ስለተነጠቁ ንፁሀን እንዲህ ብዙ መስዋአትነት ተከፍሎበት ስለተንሸራተተው ለውጥ ብሎም ለአመታት የታገሉለት ህዝብ ከራሱ በወጡ አካላት ሰላሙን አጥቶ አሁንም ሙሉ ሰላም ማግኘት ተስኖት ‹‹ ላም እሳት ወለደች ስለሆነበት የኦሮሞ ህዝብ ‹‹አልፀፀትም›› ማለት በዚህ ሁሉ ለስርአት ለውጥ ተብሎ እርሶ መርተውት  በጠፋ ሕይወት እና ንብረት መሀል ሆኖ እንደ ጲላጦስ እጅን ታጥቦ ከደሙ ንፁህ ነኝ ማለት ይቻል ይሆን ?የሚል ጥያቄ እያቀረብኩ ከልጅነት እስከ እውቀት ያሎትን የትግል ህይወት ለቀጣይ ትውልድ ይማርበት ያለፈ ትግልን መለስ ብሎ ያይ ዘንድ ለህትመት በማብቃትዎ ምስጋናየ ይደረስዎ እያልኩ በዚሁ ላብቃ ፡፡

___

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ቦርከና ከ13 ዓመታት በላይ ነጻ መድረክ በመሆን አገልግሏል ፤ ወደ ፊትም በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት እና አስቸጋሪ  በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሰራ ስለሆነ  ችግሩን ለመቅረፍ በዓመት $5 ወይንም $10 የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም ካለዎት እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ድጋፍ ያድርጉ፡፡


ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡  በነጻ መድረክ ላይ የሚቀርቡ ጽፉፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን ሃሳብ አያንጸባርቁም!

የንግድ ድርጅትዎን ወይንም አገልግሎትዎን የንግድ ድርጂት ማውጫ ላይ ለማውጣት  
እዚህ ይጫኑ፡፡
የቴክኒክ ድጋፍ ካስፈለገዎ በሚከተለው ኢሜይል ይጠይቁ zborkena@borkena.com

Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ (የቀድሞው ቲዊተር) ፡ @zborkena

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News