ማሳሰቢያ ፤ በነጻ አስተያየት አምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከና አቋም አይንጸባርቁም፡፡

ጥሩነህ ግርማ
የአማራ ኢትዮጵያ ትቅደም በአማራ ደም መሰረቱ ፍርሃትም አድር ባይነትም ነው። ከጎኑ ካለው አማራ ብሄርተኛ ለኢትዮጵያ የላቀ ፍቅር የለውም፣ሊኖረውም አይችልም። አለኝ ብሎ ከታበየ ደግሞ ከፍርሃት የመነጨ የአድኑኝ ጥሪ ነው። ወገኑን ለማዳን በመዋደቅ ላይ ባለው ታጋይ ላይ በፍርሃት ቆፈን ተኮድኩዶ ታስሮ ኢትዮጵያዊነት በሚል ድንኳን ስር ተጠልሎ ድንጋይ ሲወረውር ይውላል።
ፍርሃት የአእምሮም የስሜትም መታወክ ነው፣ በራሱ በሽታ ባይሆንም ማዳን የማይቻል ተፈጥሯዊ እንከን ነው። ፍርሃት ሰዎች ከአስፈሪው ሁኒታና ጊዜ ለመሸሽ ወይም ለመደበቅ ከስብእናችው ውጭ የሆኑ ነገሮችን ያሰራል። ፍርሃት ለአደጋዎች ምላሽ ለመስጠት እና እራስን ለመጠበቅ የሚረዳ ስሜት ነውና በአማራ ደም እትዮጵያ ትቅደም አፋሽ አጎንባሽች በኢትዮጵያዊነት ጋቢ ውስጥ እንዲወሸቁ አድርጓቸዋል/እረድቷቸዋል።
ሌሎች ተፈጥሯዊ ችግሮችን ሰዎች መዋጋትና ማስተካከል ይችላሉ፣ የውሃ እጥረትን፣ የአየር ጸባይ መፋለስን፣ ርሃብንና የመሳሰሉትን ማቃለል፣ ማስወገድ ይቻላል፣ ፍርሃት ግን መድሃኒት የለውም።
ዛሬ በአብይ አህመድ ጉያ ገብተው ኢትዮጵያዊ ካባ አጥልቀው የሚወራገጡት ከአማራነታቸው ኢትዮጵያ በልጣባቸው አይደለም፣ በአማራነታችው ኢትዮጵያን እንደማያጧትም የማይገነዘቡ ሆነውም አይደለም። የፋኖ ትግል የቅደም ተከተል ጉዳይ እንጂ ኢትዮጵያና አማራ ተጋጭተውበት እንዳልሆነም ያውቁታል። ነገር ግን ይህች የቀውጢ ጊዜ ሆነችና በፍርሃት እያነከሱ በዚያውም ከኢትዮጵያዊነት ድንኳን ውስጥ የምትገኘውን ፍርፋሪ ለመልቀም መደበቂያ ስላደረጉት ነው በአማራ ሞት ስለኢትዮጵያ የሚሰብኩት።
ተመስገን ጥሩነህም ሆነ ዳንኤል ክብረት፣ ብርሃኑ ነጋም ሆነ በለጠ ሞላ፣ ጋሻው መርሻም ሆነ ፈላስፋው ዳኛቸው አሰፋ የአእምሮ ድሁራን ሆነው አይደለም አድርባይነትና ፍርሃት እጂ ከወርች ቀፍደደው ይዘዋቸው እንጂ።
ቀደም ሲል ደግ ደጉን ይናገረ የነበረው ዳኛቸው አሰፋ የአብይ አይን ሲጉረጠረጥበት ቅኝቱን አስተካክሎ ለአብይ እንዲጥም አድርጎ የገዘገዘው ማሲንቆ የሚረሳ አይደለም። የፋኖ መሪዎችን አባት ካነሳ በኋላ ከሁሉም የአህመድ ልጅ ይሻለኛል ብሎ ሲያቀነቅን ብዙወች እንደሚያዝኑለት ትቂቶችም እንደሚያለቅሱለት ይሰማኛል። ይህ ሰው ዝም ብሎ መኖር እንዳልቻለ የሚያሳይ የፍርሃትና ጭንቀት ኑዛዜ ካልሆነ ወይንም ስቷል ካለተባለ ጭራቁ አብይ አህመድ በአማራ ህዝብ ላይ የሚያወርደውን እሳት ትክክል ነው ብሎ ባልተቀበለ ነበር። የአማራን ህዝብ ደም የእጅ መንሻ አደረገው። ዳኛቸው ዛሬ አልሞተም የሚል ሞትን ሊተራል/ቀጥተኛ ትርጉም የሚሰጥ ብች ነው።
እነተመስገን ጥሩነህና እንዳናኤል ክብረት ህይወት የሲቃ ሰቆቃ እንደሆነች መገመት ችግር ያለባቸው አይመስለኝም፣ አድርባይም ፈሪም ስለሆኑ ከአብይ ተጣብቀው ከዘሬ ነገ ይሰይፈናል ብለው እንድ አይናቸውን ከድነው የሚያንቀላፉ ከሞቱት በላይ ሙታን ናቸው። አብይ አህመድ የሚያምነውም የሚወደውም ሰው የለውም። አብይ ሃይማኖትም ዘርም የለውም። ፕሮተስታንታት ሃይማኖትና የኦሮሞ ዝርያ ለሰያጣናዊ ተግባሩ መፈጸሚይ መሳሪያወቹ ናቸው።
እነ ብርሃኑም ሆነ በለጠ፣ ተመስገንም ሆነ ዳነኤል አስበውበት ሳይሆን በትንሽም ስህተት ከአገልጋይነታቸው የሳቱ ሲመስለው ይሰየፋሉ። ይህንንም ስለሚያዉቁ ከሰዎ በላው መሪያቸው ባልተናነሰ በአማራ እልቂት ላይ ሰፊ ተሳትፎ አድርገዋል እያደረጉም ነው።
በታሪካችን ብዙ ባንዳወች ነበሩ ይኖራሉም፣ ትልቁ ባንዳ ደጃዝማች ሃይለስላሴ ጉግሳ እንኳ ከከዳ በኋል ዞሮ አርበኞችን ባንዳ ብሎ አልተሳደበም ስራውን ያውቅልና ፣ በአሚሪክ የነጸንት ትግል በወታደራዊ አመራሩ ውስጥ የነበረው ቤኔዲክት አርኖልድ(Benedict Arnold) ወደ እንግሊዝ ሲከዳ፣ ባንዳ ፣ከሃዲ ሲባል ዞሮ የአሜሪካን የነጻነት ተዋጊወች ባንዳ አለ አልተባለም ያደረገውን ያውቃልና። ብዙ የባንዳ ታሪኮች በየሃገሩ ነበሩ፣አሉ፣ ይኖራሉም። የባንዳ ትርጉም ግን አልተቅየረም ለሌላውም አልተሰጠም።
በእኛ ዘመን የኢትዮጵያን ህዝብ አሳልፈው ለአብይ የሰጡት የነሱ ገባርነት አንሶ አርበኞቻችንን ባንዳ ሲሉ ይሰማሉ። መስታውት ፊት ለፊት ቆመው ጭንቅላታቸውን የሚበጠብጠውን ለመወጣት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ባንዳ ስለሚሉ ስድቡን በአማራ ህዝብ ላይ አድረገውታል። ይታያችሁ እነብርሃኑ ነጋ በኢዜማ ታጅቦ ቤት መንግስት ገብቶ ፓርቲውን እንደ አሮጌ ጣሳ አሽቀንጥሮ ጥሎ ባንዳ የሚለው ቃል ከአፉ ሲወጣ፣ በለጠ ሞላና ጋሻው በአብን ትክሻ ላይ ተፈናጠው ስልጣን ከያዙና ስኳሩናም ከቀመሱ በኋላ እንደ አለቃቸው(ጌታቸው) በአማራ ህይወት ላይ ሲቀልዱ ባንዳ ሲሉ ትርጉሙ አይጠፋባችሁም? እኒህ እራስ ወዳድም ፈሪዎችም ስለሆኑ ነው ነገ በሚፈርሰው የውሽት ኢትዮጵያዊ ድንኳን ውስጥ ተወሽቀው የሚልከሰከሱት፣ እውነተኛው ኢትዮጵያዊው ህንጻ ሲገነባ እዚያ ፍርስራሽ ውስጥ ይቀራሉ። ነፍስ ይማር።
የአማራ ህዝብ ያጠላበትን የሞት አደጋ ለመቀልበስ በግንባር እየትዋደቁ ካሉ ልጆቹ ጋር አብሮ እየተዋደቀ ነው። ለአብይና ለፈሪ ባንዳወች ጆሮ የሚሰጠበት ጊዜም ፍላጎቱም የለውም። አብይ ነግቶ እስከሚመሽ የውሽት ድሪቶውን ሲተረትር ከዳሚዎቹ ዙሪያውን ተሰልፈው ሲያጭበጭቡ ቢውሉ፣ ለአማራ ህዝብ ከክንዱ በስተቀር ሌላ መፍትሄ የለውም። አብይ የሁሉም ፈጣሪ በሆነበት ሃገር፣ሞትና ሽረት ወሳኙ አብይ በሆነበት ሃገር አሁንም የሚያዋጣው ጠንካራ ክንድ ብቻ ነው።
ትናትን ነዳጅ ሲያስቆፍር፣ ቀጥሎም ዝናም ሲያዘንብ፣ እንኳን ደስ አላችሁ ወደብ አመጣሁላችሁ፣ ስንዴ አምርቸ ወደ ውጭ ገበያ አድርሻለሁ( ምን ያህል የሀገሪቱ ህዝብ በረሃብ እንደሚያልቅ አይነግርንም)፣ ሃገሪቱን ዛፍ በዛፍ አድርጌታለሁ( ያፈረሰውን ቤት አይነግረንም) የጥይት ፋብሪካ ሰራሁላችሁ፣ ድሮን እያመርተን ነው ( የአማራ መጨፍጨፊያ መሆኑን ባይናገርም) እያለ በዚች ስድስት አምት ውስጥ አይኑን በጨው አጥቦ ሲዘላብድ ምንጣፍ ጎታቾቹ የኦሮሙማ ቡድንም ሆነ በአማራ ደም እትዮጵያ ትቅደሞቹ ለማጭበጭብና ኖት ለመውሰድ ሲገፋፉ ይታዩ ነበር ዘሬም እንዲሁ። ንጉስ አብይ ሲናገሩማ ኖት የሚውስደው ፈተና ያለበት ተማሪ ነው የሚመስለው። ምን አልባትም ከስብስባውና ከውሸቱ በኋል ማን በትክክን መልዕክቱን እንደመዘገብ ይፈተሽ ይሆናል። ተከታዮቹን አዋርዶ፣ እንደ ህጻን ልጅ የሚያያቸው እኒህ ተራ አሽከሮቹ አንገታቸውን አቀርቅረው ቀና ብለው ስህተቱን ሳይነግሩት እንዲያውም የስህተቱ ተባባሪ ሆነው ሃገራችንን ከሱ እኩል ይዘዋት እንደወረዱ መታየት አለበት። ከዚህ በላይ ሞት?
ለዚህ ሁሉ ውርደትና አገር አልባነት ኢትዮጵያውያን ቢችሉ በየአካባቢያቸው እራሳቸውን ችለው ካልሆነም ከፋኖ ጋር ወግነው መታገል አለባቸው። አሁንም መፍተሄው ጠንካራ ክንድ ነውና።
ፋኖ ትግሉን ለማፋጠን በተለይም በመካከሉ ያሉትን ችግሮች እልባት ሰጥቶ ወደ እንድነት መምጣቱ የነገ ሳይሆን የዛሬው አጣዳፊ ስራው ነው። በአካባቢ ሃይሎች ጋር አብሮ ለመስራት መጀመሪያ ፋኖ አንድ መሆንና በአንድ ድምጽ መናገር መቻል አለበት። ከዚያ በተረፈ ግንባርም ሆነ መረዳዳት ከማን ጋር እንድሚያደርግ ወሳኙ እራሱ ፋኖ እንጅ ማንም ሊሆን አይችልም።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ስለግንባርና በተለይም ስለኤርትራ የጻፈውን አይቻለሁ፣ ትክክለኛ ትንታኔ ነው ብየ አምናለሁ። የኤርትራ ህዝብ ለአማራ ህዝብ በጆግራፊም፣ በታሪክም፣ በባህልም፣ በሃይማኖትም የሚገናኝ ህዝብ ነው። ሁለት ሀገራት ከመሆናቸ በቀር ከትግራይ ህዝብ የሚለዩበት የለም። ፋኖ ከኤርትራ ጋር በግንባር መተሳሰሩ ተፈጥሯዊ ነው። ዛሬ ሁለቱም ህዝብ በአብይ አህመድ እብሪት እየታመሱ ነው፣ ይህን ለመመከትና ልኩን እንዲያገኝ ለማድረግ ግንባሩ ወቅታዊ ነው። ይህ መሰባሰብ፣ በጋራ መቆም ጥቅሙ ለሁለቱም ህዝቦች መሆኑ ግልጽ ነው። አብይ አሰብን እይዛለሁ የሚለው ፉከራው ተጨባጭነቱ አጠያያቂ ቢሆንም በቀጠናው አለመረጋጋትን መፍጠሩ እውን ነው።
የአማራ ህዝብ ይቅርና ጠቅላላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለአሰብ የሚሞትበት ምንም አይነት ምክያትት የለም። የሚያሰውጣውም ሆነ የሚያስገባው ምንም ሸቀጥ የለውም። የሚበላው ያጣ ‘እየየም ሲዳላ ነው።’ እነ አብይ በህዝብ ገንዘብ በቁንጣን ተይዘው ሚሊወኖቹ በራሃብ እያለቁ መሬት አይብቃን ባሉ ቁጥር ህዝቡ ለጦርነት የሚዳረግበት ምክንያት የለም። ለነአብይ ጦርነት የስልጣን ማቆያ ዘዴያቸው ነው፣ ህዝቡ ለዚህ እብደት በጦርነት አይማገድም።
በተለይ አማራው አዲስ አበባን አስርክቦ፣ በወለጋ፣ ባሩሲ፣ በሃረር ወዘተ አገርህ አይደለም ተብሎ እየታረደ አሰብን እናምጣ ጦር ይዘህ ተከተልኝ ማለት የንቀትም ንቀት ነው አለዚያም ከታመመ ጭንቅላት የሚወጣ ጩህት ነው።
ለነገሩ የአብይ የአሰብ ድንፋታ ከልብ ነውን? ብሎ መጠይቅም ያስፈልጋል። ዙሪያውን ተከቦ በለብለብ ያመረተው ወታደር በየቀኑ እየተገደል፣ እየተማረከ አዲስ የጦር ግንባር መክፈት አቅሙ እንደሌለው ግልጽ ነው፣ ቢሆንም እብደቱን ከሂሳብ ውስጥ ማስገባት አይከፋም።
በኔ እምነት አብይ እየደነፋ ያለው የፋኖ ግፊት እያየለ ስለመጣ በዙሪያው ያሉትን በአማረ ደም ኢትዮጵያ ትቅደሞችን እያየ አማራ ለአሰብ ሲል ይተባበረኛል ሊል ይችላል። የአብይ እውነተኛ አለምና የቅዥቱ አለም እንደተምታቱበት ናቸውና አያስደንቅም። ማንም ሊረዳው የሚገባው ግን የአማራ ህዝብ በዙሪያው ካሉት አጎብዳጆቹ በስተቀር አብሮት የሚቆም እንደማይኖር ነው፣ ማንም በራሱ ላይ ሞትን አይፈርድም። ገፍቶ ከመጣ የአማራ ህዝብ መቆም ያለበት ከኤርትራ ህዝብ ጋር ነው። ከላይ እንደተነሳው ለአማራ ህዝብ መዳኛውም ቀጠናዊ መረጋጋትም የሚመጣው የአብይን ውምብድና ለአንዴና ለመጨራሻ ማባረር ሲቻል ነው።
ግንባሩ ይህ ብቻ አይደለም፣ የትግራይ ህዝብ በደም የጨቀየውን የወያኔን አመራር ከትክሻው ላይ አራግፎ ጥሎ የመኖር ያለመኖር እጣ ፈንታው ከአማራ ጋር መሆኑን ተረድቶ በጋራ የአብይን ወንበዴ ከኢትዮጵያ ምድር ላይ ማጥፋት ታሪካዊ አላፊነት አለበት። ወያኔ ከእብሪቱ ሊወጣ የሚችል ስብስብ አይመስልም። አሁንም እንደገና በትግራይ ህዝብ ላይ መከራ ከማምጣት የሚቆጠብ መሆኑን ማመን አስቸጋሪ ነው፣ ባህሪው ጦርነት ነውና። አሁን ባለው ለትግራይ ህዝብም ሆነ በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያደረሰውን በደል፣ የፈጸመውን ግፍ በከፊል እንኳ ለመካስ ስልጣኑን ለኢትዮጵያውያን ትግሬዎች አስርክቦ እነሱም ከኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው ጋር አብረው በጋራ ይህን የደም መንግስት መጣልና የጋራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት አላፊነታቸውን ይወጡ እላለሁ።
አንዳርጋቸው ግንባርን በሰሜን ኢትዮጵያ ላይ አስቀርቶታል፣ እኔ እንድ እርምጃ እወስደዋለሁ። ጌታቸው እረዳ ባማራ ላይ በነበረው የከረረ ጥላቻ( ዛሬ እንዲህ እርስበርሳቸው ሊሻኮቱ) የአማራን ሂሳብ ለማወራረድ ወደ ሲዖል እንወርዳለን ብሎ ነበር፣ ወርዶ መመለሱን ማረጋገጥ ባይቻልም ጥላቻውን አሰምቶናል። ፋኖም ከአብይ በላይ ጠላት የለምና እንዲመለስ ሆኖ ሲዖልም ግብቶ የሚያገኘውን ድጋፍ መፈለግ የኖርበታል።
አንድ ልጨምር ፋኖ ያለምንም ማወላወል ከግብጽ ጋር ግንኙነት ፈጥሮ ማግኘት የሚችለውን ሁሉ የመጠየቅ ሃላፊነት አለበት። ለአብይና እስክስታ ወራጆቹ ይህች ትልቅ ዝማሬ ትሆናቸዋለጭ ከጠላት ሃገር ጋር ወዳጅነት፣ ባንዳነት የሚል መዝሙር ይዘምራል፣ በዲጂታል ሰራዊቱ ይለቀሳል፣ በአማራ ሞት ኢትዮጵያ ትቅደሞች ክንፋቸውን እያራገፉ ሙሾ ይወርዳሉ። አሁንም እላለሁ በአሁኑ ሰዓት ለኢትዮጵያ ከአብይ አህመድ በላይ ጠላት የላትም። ግብጽ ነገ ጠላት ትሆናለች ብሎ ዛሬ እንሙት የሙታን ብሂል ነው።
“ እኔ የምሞት ዛሬ ማታ እህል የሚደርስ በፍልሰታ “
የሚለው የሀገሬ አባባል እውነትነቱ አንዱ እዚህ ላይ ነው። ዛሬ መውጫና መግቢይ አጥቶ ሞት ሽረቱን እየጠበቀ በሰቀቀን ለሚኖረው ህዝብ የነገው የግብጽ ችግር ጉዳዩ ሊሁን አይችልም። በእርግጥ ችግር ትሆናለች ወይ? የሚለውን ለአሁኑ በይደር እንተወው።
__
ድጋፍ ያድርጉ :- ቦርከና ከ13 ዓመታት በላይ ነጻ መድረክ በመሆን አገልግሏል ፤ ወደ ፊትም በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት እና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሰራ ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ በዓመት $5 ወይንም $10 የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም ካለዎት እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ድጋፍ ያድርጉ፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ







ወንድም ጥሩነህ፦
ግሩም አስተያየት ለቀረበበት ድርሰትህ አመስግኛለሁ። የአማራ በቸኛው መድህኑ ጠንካራ ክንዱ ነው ያልኸው ምንም እንከን የለበትም። ለሆዳቸውና በፍርሀት ቆፈን ተቀፍድደው የኣቢይ አሽከር ሆነው በሚኒስትሮች ም/ቤትና በፓርላማውም የሚያጨበጭቡለትና ወደ ገደል ሲወርድ ገደል ከፊቱ መኖሩን የማይነግሩት ሁሉ የመጀመሪያዎች ሆዳሞችና ፈሪዎች አይደሉም። ጃንሆይ በዕውቅት ማነስ አልሰሟቸውም እንጂ እንደ እነ ክቡር አቶ ሀዲስ ዓለማየሀሁ፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደ ሐዋርያትና ደጃዝማች ወልደ ሰማያት ገብረ ወልድ ያሉ ብሩህ አገር ወዳዶችና ደፋሮችም ነበሩ። በዉሏቸው ሁሉንም አይተናቸዋል ።
በአንጻሩ፣ መንግሥቱ ኃይለ ማርያምን ተሳስተሀል የሚል፣ በፍርጠጣው ዋዜማ ከታየው ከዶ/ር ኃይሉ አርዓያ ውጭ፣ አንድም ጉብል እብዮተኛ ወይም ወታደር አልነበረም። አንድ ሰው እስኪቀር እንታገላለን ይል የነበረው ደናቁርቱ “አገር ወዳዱ መንጌ” የሚሉት ሰው ኢትዮጵያን ቀርቶ የምስራቅ አፍሪቃን ቀጣና ሊጠብቁ የሚችሉትን ጀግና ጀኔራሎች አርዶ ቀብሮ፣ አርበኞችንና የአገር ባለውለታዎችን ሰይፎ ጨርሶ፣ አንድም የአገር መሪና ጠባቂ እንዳይኖር አድርጎ፣ መሬትም ለአራሹ ሳይሆን ለሆዳም አስረክቦ አገር በሙሉ ጭሰኛ አድርጎ፣ ኤርትራን አስገንጥሎና ለጅብ አስረክቦን መሄዱን አሁንም ባግባቡ አላጤንነውም።
የደርግ ወራሽ የትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅትና አሽከሩ ኦነግ ነፃነት ምን እንደሆነ ስለማያውቁና ለትግሬም ሆነ ለኦሮሞ ያልቆሙ ተራ ዘራፊዎች በመሆናቸው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(1) ላይ ለ83 ጎሣ ቢበዛ 9 ጎሣ የሚገዛበት 9 ክልል “የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ረፐብሊክ አባላት …” ናቸው ብለው ፈጥረው፣ የቀሩትን 74 ጎሣዎች ፣ አዲስ አበባንና ድሬዳዋንም ከሪፐብሊኩ ውጭ አድርገው፣ ለባለክልሎች 74ቱን አሽከር አድርገው፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 8(1) “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው።” ብለው ለ30 ዓመታት ሲያታልሉንና ሲዘላብዱብን ከመለስ ዙሪያ የተኮለኮሉት ሆዳሞች ቃል አልተነፈሱም። ችግራቸው ሆዳምነታቸውና ፍርሀት ናቸው።
እንዲያውም፣ ዛሬም ይህን የአምባገነን ሕገ መንግሥት፣ ሌላው ጎሣ ይቅርና፣ ትግሬና ኦሮሞም ሲወድሙ እንድ ፕሮፌሶር ሕዝቅየል ያሉ የታሪክ ምሑራን ሳይቀሩ እያዩ ሕገ መንግሥቱ እንከን የለሽ ነው ሲሉ፣ ምሑር ነን ባይ ወንድሞቻችን ምን ቢነካቸው ነው እንዲህ የደነዙት የሚል ቁጭት ይፈጥራል። ደግነቱ እንደ ፕሮፊሶር መሐመድ ሐሰን ያሉ እውነተኛ ሊቃውንትም ስላሉ ደግሞ ሀቀኛ አስተማሪም አላጣንም። የፕሮፌሶር ሕዝቅየልና የሌሎችም ጭፍን ኦነጎችና የዛሬም አውዳሚ የሕወሀት መሪዎች ችግር ግን ከሆዳምነት ጋር ጭፍን ደንቆሮነት ነው። እዚህ ላይ ፍርሀትን ስግብግብነትና ራስ ወዳድነት ያሸነፉት ይመስላል።
የደርጉን መንግሥቱም ሆነ የወያኔውን መለሰ ያገለገሉ ሁሉ ዋናው ለባርነት ያበቃቸው ሆዳቸውን ማስቀደማቸውና ፍርሀት ነበሩ። ከሌሎቻችንም ጥፋት አለ፦ ለዚህ አምባገነን ሥርዓት ያበቃውን ሥርዓተ መንግሥት ለ30 ዓመት ፈርተን መቀበላችን ትልቅ ጥፋት ነው። “እናቴን ያገባ አባቴ ነው።” አስጠቃን። ይህን ተማርን የምንለው ሁሉ እናውቃለን። ግን አቅመ ቢስ ሆነን የአምባገነን ውዳቂ አሽክር በመሆን ይኸው 50 ዓመት ተገዛን፣ ተዋረድን፣ ተሰቃየን። ይህ ሥርዓት እንዳይለወጥ፣ እነ ፕሮፌሶር ሕዝቅየል ብቻ ሳይሆኑ፣ የሕወሀትን ቢሊየነሮች የፈጠረው ዘራፊው ሕወሀት፣ ተረኛው የኦሮም ቡድንና ደንቆሮ ፍርፋሪ ለቃሚዎች ሁሉ በቂ አልዘረፍንምና ሥርዓቱ አይቀየርም እያሉ ዛሬም በመከላከያ ወጣቶች ደም፣ ከጥቅም ተካፋዮች ጀኔራሎች ጋር በማበር፣ እየነገዱ ነው ማለት ስሕተት አይሆንም። መብቴን አክብራችሁ ግዙኝ ያለን ሰላማዊ ወገኑን መውጋትን፣ ማውደምና ማሰቃየት የመከላከያ ሠራዊት ተግባር አይደለም። ታዲያ የወደፊት መፍትሔው፣ የወቅቱን ደናቁርት እብሪተኞች የፈጠሩትን ችግር ከማስወገድ ሌላ፣ የደርግንና የወያኔን የደንቆሮ ስሕተት ላለመድገም ወንድም ጥሩነህና እኔም በአዲሱ መንግሥታዊ ሥርዓትና ሕገ መንግሥት ዳግመኛ የአምባገነን መፈንጫ እንዳንሆን አድርገን መቅረጹ የዜግነትና የተማረ ምሑር ግዴታ ነው።
ወንድም ጥሩነህ፦
አንድ ከአንተ ጋር የማልስማማበት ጉዳይ ከግብፅም ጋር እንወዳጅ የምትለው ነው። ከገነገነ ጠላት ጋር፣ ጀብሐን የመሠረተና ኤርትራን ያስገነጠለ፣ አባይን የእኔ ብቻ ነው ከሚል ጠላት ጋር፣ በሃይማት ሳይቀር ከሚረብሽ ጠላት ጋር፣ ኢትዮጵያን ብዙ ጊዜ ወርሮ ግምባር ግምባሩንና እየተባለና አንገቱን እየተቀላ ከተባረረ ጠላት ጋር (የአፋር ወንድሞቻችንም ይቀየሙሃል።)፣ በሺ የሚቆጠሩ ጀግኖች የግብፅን ወራሪ ለማባረር በዱሩ በገደሉ መውደቃቸውን ረስተህ፣ ዛሬም ጠላትነቱን እየነገረንና እያየንም እንደ ደርግ ደናቁርት በማንነታችን ላይ ራሳችን መዝመትማ አይሆንም። አባቶች “ጠላትማ ምንጊዜም ጠላት ነው፣ አስቀድሞ መግደል አሾክሿኪውን ነው።” እያሉ ነው ኢትዮጵያን ከድፍን አፍሪቃ፣ እስያና አሜሪካ በተለየ አኩሪ ነፃነት ያቆዩን። ይህን ቅርስ አሳንሰህ አትየው። እንደ ደርግና ወያኔ፣ የአባቶች ውለታና ደም የምንረሳ አይደለንም። ባንዳውንና ሆዳሙን ተወውና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ጀግኖች እያሉን፣ ከጠላት ጋር ሳናብር፣ እኛነታችንን ማስከበር መቼ አቃተን ? ይልቅስ መሰዳደቡንና ንትርኩን ለትናንሽ ሰዎች ትተን፣ የዜግነት ገንቢ ድርሻችንን መሥራት አለብን።
ወንድም አንድነት
በመጀመሪያ ዘግይቸ ስለመጣሁ ይቅርታ እንድታደርግልኝ እጠይቃለሁ: ፅሁፍህን አላየሁትም ነበርና ነው::
ስለአስተያየትህ በጣም አመሰግናለሁ: ስለግብፅም ያነሳኸውን እረዳዋለሁ ግን የእኔን አመለካከት ለማሳየት ልሞክር:
በዛሬይቱ ኢትዮዽያ ከአብይ በላይ ጠላት የለም ግብፅንም ጨምሮ: ሃገራችንን እያፈረሰ ያለው አብይ ነው: ይህ በምንም ምክንያት አያወላውልም: በሃገር አንጡራ ሃብት መሳሪያ እያስገባ የሚጨፈጭፈውን ህዝብ ለመታደግ ኢትዮዽያውያን ከማንም እርዳታ ለማግኘት መጣጣር ይኖርባቸዋል: ከግብፅም ቢሆን: ግብፅ ሃገራችን ትግባ ማለት አይደለም በምንም መልክ እርዳታ ካገኘን ግን በመፈራረስ ላይ ያለችውን ሃገራችንን ለመታደግ መሽኮርመም የለብንም: ይህ ሲባል ሃሀራዊ ነፃነታችንን አጥተን አይደለም : ገና ግብፅ ነገ ይህን ታደርግ ይሆናል ስንል ዛሬ ሃገራችንን ማጣት የለብንም: ሃገራችንን አትርፈን ነገን እንደአመጣጡ እንቀበለዋለን:: ሌላው የመንግስት የተጋነነ የግብፅ የጠላትነት ስብከት አመለካከታችንን እንዳያዛባው ያስፈልጋል: የአባይን ጉዳይ ግብፆችም ለሃገር ውስጥ ፍጆታቸው ይቧርቁበታል: በተመሳሳይ እነአብይም የህዝብ ማደንዘዣ ለማድረግ እየታከቱበት ነው: ለህዝቡ አጀንዳ እየፈጠሩለት ነው: የምንጠራጠራት ግብፅ ከዚህ የበለጠ ምን ልታደርግ ትችላለች? ሃገራችንን በጦር ወግታ ልትይዝ አትችልም : የምታደርገው ስታደርግ የኖረችውን አንዱን ከአንዱ ማጋጨት ነው: ይህን የምንፈታው ደግሞ እኛው ኢትዮዽያውያን በአንድነት ለሃገራችን ስንቆም ነው: የግብፅም እርዳታ ተጨምሮበት( ከረዳች) ሃገራችንን አድነን አንድ ሆነን ጣልቃ ገብነትን ማስቆም እንችላለን:
አሁንም በድጋሜ አመስግናለሁ