ማሳሰቢያ ፤ በነጻ አስተያየት አምድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከና አቋም አይንጸባርቁም፡፡

በሲሳይ ሙሉ
መግቢያ
በአማራ ፋኖዎች የሚመራው የአማራ ህዝብ የህልውና ትግል የዐብይ አህመድ አገዛዝ በአማራ ሕዝብ ላይ አያደረሰ ያለውን ግፍ፣ ጅምላ ግድያ እና መዋቅራዊ ጭቆና በመመከት ላይ ይገኛል። የህልውና ትግሉ መንስኤም ለረዥም ጊዜ የተንሰራፋው የአማራ ህዝብ መፈናቀል፣ በመንግስት የሚደገፈው አማራ ተኮር መዋቅራዊ ጥቃት እና የአማራን ህዝብ ከኢኮኖሚ እና ፖለቲካ የማግለል ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች እንደሆኑ በሁሉም የአማራ ፋኖ ታጋዮች ዘንድ መስማማት አለ ማለት ይቻላል።
አማራ ላይ የተቃጣውን ዘርፈብዙ መዋቅራዊ ትግል ለመመከት ብሎም ለማሸነፍ የተቀናጀ የትጥቅ ትግል እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው፡፡ ከተለያዩ የአማራ አካባቢዎች ለአማራ ህልውና ለመታገል የወጡ ፋኖዎች ከቀበሌያቸው ተነስተው ትልልቅ እዞችን እስከመመስረት ደርሰው ባለፉት 20 ወራት አስደማሚ የጦር ሜዳ ድሎችን ማስመዝገብ ችለዋል፡፡ ይሁንና ሁሉንም የአማራ ፋኖ ወታደራዊ ድሎችን በድርጂት ማእቀፍ ወደዘላቂ ድል ለመለወጥ እና አንድ አማራአቀፍ አደረጃጀት ለመመስረት የተደረጉ ሙከራዎች በተለያየ ጊዜ ተግዳሮቶች እየገጠሙት እስካሁን ቀጥሏል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ አንድ አማራአቀፍ አደረጃጀትን ለመመስረት የተደረገው ሙከራ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን (አፋህድ) ቢወልድም በአፋህድ ውስጥ አንካተትም ወይም ልዩነት አለን ያሉ የፋኖ አደጃጀቶች በክፍለ ሃገርና በየአካባቢው ራሳቸውን ችለው እየተንቀሳቀሱ ነው። አሁን ባለው ሁኔታ በአፋህድ ስር የተጠቃለሉ ፋኖዎች እና ያልተጠቃለሉ ወይም በአንድ አማራ አቀፍ ድርጂት ያልታቀፉ የፋኖ አደረጃጀቶች መኖራቸው ለአማራ ፋኖ ትጥቅ ትግል ትልቅ ፈተና ሆኗል፡፡ ከችግሮቹም መካከል የሚከተሉትን ማንሳት ይቻላል፡፡
- የተዋሃደ እና ሁሉንም ያቀፈ አንድ ወጥ አማራዊ ድርጅት እና ወታደራዊ እዝ አለመኖሩ የጋራ ጠላት ላይ የተበጣጠሰ እና መካለከል ላይ ብቻ ያተኮረ ትግል ላይ እንድንወሰን ሆነናል፡፡ ለጠላት ተገማች ሆነናል፡፡
- አንዳንድ የፋኖ አደረጃጀቶች ከአካባቢያቸው ፤ ቀጠናቸው፤ ክፍለሀገራቸው ጋር በጥብቅ እንዲተሳሰሩ በመሆናቸው ትግሉን በአሸናፊነት ለማጠናቀቅ እጅግ አስፈላጊ ከሆነው አማራዊ አስተሳሰብ በማራመድ ትግሉ አማራን እንደህዝብ ነጻ ከማውጣት ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀጠናዊነት ስሜት እንዲጎላ እና አልፎ አልፎም ቢሆን በተለያዩ የአማራ ቀጠናዎች ባሉ ፋኖዎች መካከል ትግሉን በእጅጉ ሊጎዳ ሚችል የጎንዮሽ መራኮቶች እንዲፈጠሩ አድርጓል።
- አሁን ባለው ሁኔታ ከቀጠልን ዛሬ አልፎ አለፎ ምንሰማቸው በፋኖዎች መካከል ሚከስቱ የርስ በርስ ግጭቶች ፤አለመግባባቶች፣ ሽኩቻዎች እና የትግሉን አጠቃላይ እድገት አደጋ ላይ ሚጥሉ ክስተቶች በብዛት የሚፈለፈሉበት እየሆነ ሊመጣ ይችላል።
- አሁን ያለው ሁኔታ አጠቃላይ ትግሉን ስትራቴጂክ ቅርቃር (Strategic Stalemate) ውስጥ እንዲገባ እና የአማራ ፋኖ ያለውን ውሱን አቅም በመጠቀም በአንድ አቀናጅቶ ዋናው ጠላት ላይ ትኩረት እንዳይሰኝ አድርጎታል፡፡
- ሁሉንም የአማራ ፋኖዎች ያካተተ አንድ ተቋም አለመኖሩ የኢትዮጵያው አገዛዝ እና እና ሌሎችም ጸረአማራ የፖለቲካ አጀንዳ ያላቸው አካላት እነዚህን የውስጥ ክፍፍሎች በመጠቀም የአማራ ትግል ውስጥ ሰርጎ ለመግባት ፤ ትግሉን ለመቆጣጠር ብሎም ለማኮላሸት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። አንዳንድ ሙከራዎችም እየታዩ ነው፡፡
- የአማራ ፋኖ ትግል በሀገር ውስጥም ሆነ በሀገር ውጭ ባሉ አካላት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቋማት ተገቢውን ትኩረት እንዳያገኝ ሆኗል፡፡
ይህ ህዝባዊ የፋኖ ትግል የትኛውም ህዝባዊ ትግለ የሚያጋጥመው አይነት ከላይ የተጠቀሱት የራሱ ተፈጥሯዊ ተግዳሮቶች ቢኖሩትም የአማራ ፋኖን ትግል ከሌላው ለየት የሚያደርገው ግን ከማሸነፍ ውጪ አማራጭ የሌለው መሆኑና ለየትኛውም አይነት ስህተት ቦታ የሌለው መሆኑ ነው፡፡ የአማራ ፋኖ ትግል ጥንካሬ ሚለካው በተዋጊዎች ጀግንነት ወይም ትግሉ ባለው ሰፊ ህዝባዊ ቅቡልነት እና ድጋፍ ብቻ ሳይሆን በድርጅታዊ አሰራሩ፣ በአማራዊ አንድነትና ትብብር ትግሉ ያለውን ውሱን ሀብቶችን በብቃት በመጠቀም ላይ የተመሰረተ ከሆነ ብቻ ነው። አሁን የማይካደው እውነት የአማራ ፋኖ ትግል መስቀለኛ መንገድ ላይ ነው፡፡ አፋጣኝ መፍትሄ ሚያስፈልጋቸው ከላይ የተዘረዘሩ ውስብስብ ችግሮች አሉ፡፡ የትግሉን አሸናፊነት እውን ለማድረግ እና አንድነት በተመለከተ ያሉትን ተግዳሮቶች መለየት እና አዋጭ መፍትሄ መጠቆም ለነገ ማይባል ጉዳይ ነው። የዚህ ጽሁፍ ዓላማም የአማራ ፋኖ ትግል ቀጣይ ጉዞዎች በተመለከተ አንዳንድ የፋኖ አመራሮችን ጨምሮ ፤ አክቲቪስቶች ፤ የሚዲያ ባለሙያዎችና በአማራ ትግል ውስጥ አስተያየት የሚሰጡ የተለያዩ አካላት የሚሰነዘሩ የመፍትሄ ሀሳቦችን ጥቅምና ጉዳታቸውን በመተንተን አሁን ካለንበት አጣብቂኝ ሁኔታ አንጻር ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ የመፍትሄ ሀሳብ መጠቆም ነው፡፡ የሚቀርቡት ሀሳቦች በአጠቃላይ በአራት ዘርፎች ሊጠቃላሉ ይችላሉ፡፡ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
1. ሁሉም የአማራ ፋኖዎች በአንድ አማራዊ ድርጂት እንዲታቀፉ ማድረግ
ሁሉም የአማራ ፋኖዎች በአንድ አማራዊ ድርጂት ቢታቀፉ እጂግ ተመራጩና የየትኛውም አማራ ፍላጎትና ህልም ነው፡፡ ሁሉም የፋኖ ኃይሎች በአንድ ማዕከላዊ አማራዊ ድርጅት ስር ቢጠቃለሉ የተደራጀ፣ የተቀናጀ፣ እና አስፈሪ አማራዊ ሀይል ለመፍጠር ከማስቻሉም በላይ ያለንን ውሱን ሀብቶችን በብቃት ለመጠቀም የሚያስችል መደላድል ይፈጥራል፡፡ “ለአንድ አማራ አንድ ትግል አንድ ድርጅት አንድ ድል” በሚል መሪ ቃል ሁሉም ሀይሎች በአንድ ድርጅት ስራ ለጋራ አላማ የጋራ ትግል እና መስዋእትነት እንዲነሳሱ ያደርጋል፡፡
አንድ አማራዊ ድርጅት ትግሉን ከማሳለጥ ባለፈ ያለንን የሰው ኃይል፣ የጦር መሳሪያዎች፣ እና የቁሳቁስ ድጋፍ በትግሉ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው መስኮች ውስጥ በብቃት እንዲሰራጭ በማድረግ ሁሉም የፋኖ ቡድኖች በቡድን የውሳኔ አሰጣጥ እየተካፈሉ፣ የጋራ መረጃን እኩል በማጋራት እና የተቀናጀ አመራር በመስጠት እና የሎጂስቲክስ አሰራሮችን እና ሌሎች ለትግሉ አስፈላጊ ግብዓቶችን በሚፈልገው ቦታና ጊዜ ቶሎ ለማድረስ ያመቻል፡፡
በተጨማሪም አንድ አማራዊ ድርጅት የአማራ ፋኖን አጠቃላይ ትግል የውስጥ እና የውጭ ድጋፍ አቅም ያሳድጋል፡፡ የአማራን ህዝብ ጉዳይ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የሚወክል ግልጽ እና አንድ ወጥ ድምጽ በማቅረብ የተቀናጀ መልዕክት እና የአላማ አንድነት ያለው መሆኑን በማስመስከር እና ተዓማኒነቱን በማሳደግ ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የሌሎች ሀገራት መንግስታት ፤ የዲያስፖራ ማህበረሰቦች፣ እና ሌሎች የሀገር ውስጥ እና ሀገር ውጪ አጋሮች ጋር ተቋማዊ ትብብር ለመፍጠር ያስችላል፡፡
በተጨማሪ በአንድ አማራዊ ድርጂት አሰራር መታቀፍ ያለንን የሠራዊት አቅም በተጠና መልኩ ትላልቅ ዘመቻዎችን በተመሳሳይ ጊዜ ለማካሄድ የሚያስችል አቅምን ያሳድጋል፡፡ ይህም የጠላት ጥቃትን ለመቋቋም፣ የሀብት እጥረት ሲያጋጥም ያለንን ውሱን ሀብት በማብቃቃት ትግሉን ወደፊት ለማስኬድ እና የተዋጊውን እና ደጋፊውን ሀይል ሞራል ለመጠበቅ ይረዳል፡፡ እንዲህ አይነቱ አንድነት የውስጥ መለያየቶችን ለመቋቋም፣ ውጫዊ አደጋዎችን ለመቅረፍ፣ እና የረጅም ጊዜ አላማዎችን ለማስፈጸም ጠንካራ መሰረት ይፈጥራል፡፡
በአጠቃላይ አንድ የተቀናጀ ሁሉን አቀፍ አማራዊ አታጋይ ድርጅት መፍጠር ቢቻል ለአማራ ህዝብ ትግል አንድ ትልቅ እመርታ ሊታይ ሚቻል ድል ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ሁሉን አቀፍ አንድነት በመፍጠር የአማራ ሕዝብን የወደፊት እጣ ፋንታ የሚያረጋግጥ እና አሁን ያለውን የተበጣጠሰ ትግል በአንድ ማእቀፍ የህዝቡን ሞራልም ድጋሜ በማነቃቃት ትግሉ የተለያዩ ሀይሎች ትግል ሳይሆን የአንድ አማራ ትግል ሆኖ እንደ አንድ የተደራጀ፣ የተስተካከለ ቁርጠኛ ኃይል የሚመራ መሆኑን ማረጋገጥ ቢቻል ተመራጭ ነው፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ይሄን ማድረግ ካልተቻለስ የለን አማራጭ ምን ይሆናል የሚለውን ደግሞ እንመልከት፡፡
2. አሁን ያለውን ሁኔታ ማስቀጠል
አሁን ባለንበት ሁኔታ ሁለት አይነት አድረጃጀት አለ ማለት ይቻላል፡፡ በአፋህድ የታቀፉ የፋኖ አደረጃጀቶች እና ያልታቀፉ ብለን ልንከፍላቸው እንችላለን፡፡ የአፋህድ የምስረታ ሂደት አንድ ማዕከላዊ አማራዊ ድርጂት ለመፍጠር በተደረገው ሂደት እንደ አንድ ትልቅ እመርታ የሚታይ ቢሆንም አሁንም በድርጂቱ ስር ያልታቀፉ የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች መኖራቸው አፋህድ ሁሉንም ፋኖዎች አቅፎ ትግሉን ማሳለጥ አልተቻለም፡፡ ይህ የተበታተነ መዋቅር የትግሉን አጠቃላይ አቅም እና ውሱን ሀብታችን በተገቢው ቦታና ጊዜ ጥቅም ላይ በማዋል በተቀናጀ ጠንካራ ዘመቻ ጠላትን ለመጋፈጥ አላስቻለም፡፡
አሁን ባለንበት ሁኔታ ዋና ተግዳሮቶች አንዱ በተለያዩ የፋኖ አደረጃጀቶች መካከል ውጤታማ ትብብር አለመኖር ነው። የተቀናጀ አመራር እና የጋራ ስልተ-ትግበራ አለመኖር የትግሉን ውጤታማነት ይፋታተናል። አሁን ያለው ያልተቀናጀ ትግል ስትራቴጂ ስህተቶችን፣ ድርብ ትግሎችን በማድረግ የሀብትና ሰው ሀይል ብክነት፤ እርስ በእርስ የሚጋጩ ሚመስሉ መልእክቶች ለደጋፊው ህዝብ እና ለውጪም ሆነ የውስጥ ወዳጅ በመድረሳቸው የህልውና ትግሉን በተመለከተ መደናገርን ፈጥሯል፡፡ ጠንካራ ትብብር አለመኖር በዚህ ከቀጠለ በጦርነቱ ላይ የሚሳተፉ በበጎ ፈቃድ መስዋእት ለመሆን የወጡ ተዋጊ ፋኖዎች እንዲሰላቹ ፤ ሞራላቸው እንዲወድቅ ፤ ተስፋ እንዲቆርጡ እና ከትግሉ እንዲሸሹ ሊያደርጋቸው ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪም አሁን ያለው ሁኔታ ከዚህ በላይ ከቀጠለ የአማራ ፋኖ የድጋፍ መሰረት የሆነው የሰፊው የአማራ ህዝብ ሁለገብ ድጋፍ መቀነስ ይጀምራል። አማራ ሕዝብ ምንም እንኳን በከፍተኛ ስቃይ፤ ድህነት እና ሰላም እጦት እየተሰቃየ ቢሆንም አሁንም ድረስ ለፋኖ ተዋጊዎች ያለማቋረጥ ድጋፍ ያደርጋል። ይሁን እንጂ ይህ ድጋፍ የማያልቅ እና የማይቋረጥ ነው ማለት አይደለም። የኢኮኖሚያዊ ችግር፣ የድህነቱ ጥልቀት እና እየመጣ ያለው ሰብዓዊ ቀውስ ተደማምሮ አሁን ያለው ሁኔታ ከተራዘመ ህዝቡ ለአማራ ፋኖ ያለውን ድጋፍ ሊቀንስ ይችላል። ህዝቡ መሰረታዊ ፍላጎቶቹን ለማሟላት በሚቸገርበት ጊዜ፣ ለተዋጊዎች ምግብ፣ መጠለያ እና ሞራላዊ ድጋፍ ለመስጠት ከባድ ሊሆንበት ይችላል። አሁን ትግሉ ካለበት ሁኔታ ለመውጣት መፍትሄ ማግኘት ካልተቻለ በጊዜ ሂደት ህዝቡ ድጋፉን ማንሳት ብቻ ሳይሆን ፋኖን ወደመቃወምም ሊዞር ይችላል። ይሄ የጠላት ፋሽስታዊ አገዛዝ እና ግብረአበሮቹ ፍላጎትም እንደሆነ መገንዘብ ያሻል፡፡
በትግሉ ከመሰላቸት በተጨማሪ ትግሉ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ማህበራዊ ቀውስ እጅግ ውስብስብ እና ከባድ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከአራት ሚሊዮን በላይ የአማራ ህጻናት ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል። ይህ ሁኔታ አንድ ተጨማሪ ዓመት ሲቆይ፣ በህዝቡ ላይ ሚደርሰው ኪሳራ መዘዙ ከባድ ይሆናል። አንድ ትውልድ ከትምህርት በራቀ ቁጥር ለወደፊቱ የህዝቡ አለኝታ ሚሆን የተማረ ሀይል በማሳጣት የአማራን ህዝብ በዘላለም ባርነት አንገት አስደፍቶ መግዛት ለሚፈለገው ፋሽስታዊ ሀይል ምቹ ሁኔታን መፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ ቤተሰቦችም የልጆቻቸው የወደፊት እጣ ፋንታ በጦርነቱ ምክንያት ፈተና ውስጥ ከገባ በትግሉ ተስፋ እንዲቆርጡ እና አሁን ያላቸው ድጋፍ ወደ ቁጣ እና በመጨረሻም ከትግሉ በተቃራኒ ወደመቆም ሊሄድ ይችላል። የህዝብ ቁጣ ከጨመረ፣ በፋኖ ትግል ላይ ያለው እምነት ሊጠፋ ይችላል፣ ይህም የትግሉን መሠረታዊ ፅንሰ-ሀሳብ ከሆነው ህዝባዊነት ለይቶ በማውጣት በእጅጉ ሊጎዳው ይችላል።
በአጠቃላይ አሁን ያለው የተበታተነ እና ዘላቂ ያልሆነ አድረጃጀት ከባድ አደጋዎችን ይዟል። ይህ ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ የትግሉን ግለት በመቀነስ የህዝብ ድካም እና የሰብዓዊ ቀውስ ተግዳሮቶች ጋር ተዳምሮ ትግሉን ሊያዳክመው ይችላል። ትግሉ አሁን ካለበት ቅርቃር ወጥቶ ወደፊት መራመድ ይችል ዘንድ አስቸኳይ እርምጃዎች ካልተወሰዱ፣ ለትግሉ የሚያስፈልገው ወሳኝ የህዝብ ድጋፍ ሊነጥፍ ይችላል።
3. አፋህድን ማፍረስና እና በክ/ሀገር ወይም ቀጠና ደረጃ እንደገና ማደራጀት
በአንዳንድ አካላት አሁን ካለንበት ቅርቃር እንደመውጫ ከሚቀርቡት መፍትሄዎች አንዱ በተለይም ከጎጃም እዝ ተወካዮች አካባቢ በተደጋጋሚ የሰማነው አፋህድ ፈርሶ በክ/ሀገር ወይም ቀጠና ደረጃ እንደገና ማደራጀት የሚል ነው። የዚህ ሀሳብ አቀንቃኞች በመጀመሪያ አፋሀድን ማፍረስ ፤ ከዛ በቀጠና/ክ/ሀገር ደረጃ አንድ ጠንካራ አደረጃጀት መፍጠር እና በሂደት አንድ አማራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር እንወያይ የሚል ነው። ይህ ሀሳብ ላይ ላዩን ሲታይ አሁን በሁሉም ቀጠናዎች አካባቢ ያሉትን በአፋህድ የታቀፉትን እና ያልታቀፉትን ፋኖዎች በቀጠና ደረጃ ወደአንድ መንገድ ለማምጣት አቋራጭ መፍትሄ ቢመስልም ትግሉን አማራዊ በሆነ ድርጂት አስተባብሮ ወደፊት ለመግፋት ግን የራሱ ከባድ አደጋ ያዘለ ነው፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ አፋህድን ማፍረስ ለአማራ ትግል ጠንቅ የሆነውን ቀጠናዊነት/ከባቢያዊነት/ጎጠኝነትን ክልላዊነትን ከመቅረፍ ይልቅ የበለጠ ሊያጠናክረው ይችላል። የአማራ ትግል ወደአንድ አደረጃጀት ለማምጣት እስካሁን ካጋጠሙት ዋና ዋና ፈተናዎች አንዱ የፋኖ ኃይሎች በጂኦግራፊያዊ እና በአካባቢያዊ መስፈርቶች መሰረት አድርገው እዝ የመሰረቱ መሆናቸው ነው። መፍትሄው ፋኖዎች ከዚህ አካባቢያዊ አደረጃጀት ወጥተው ወደአማራዊ አደረጃጀት መምጣት ነው አያልን ከዚህ አካባቢዊነት አልፈው በአማራዊ አደረጃጀት ስር ያሉትን አፋህድ ይፍረስ ሚለው እርስበርሱ ሚጣረስ አፍራሽ ሀሳብ ነው፡፡ አፋህድ ከፈረሰ እና አሁንም ቀጠናዊነት/ከባቢያዊነት/ጎጠኝነትን ክልላዊነትን ላይ የተቸነከሩ አደረጃጀቶችን አጠናክረን ይዘን ከመጣን እነሱን አክስሞ እና አዋህዶ አንድ አማራዊ አደረጃጀት ለመመስረት አዳጋች ይሆናል፡፡ ይህም የአማራ ፋኖዎችን በአንድ አማራነት ዙሪያ ከማሰባሰብ ይልቅ ለቀጠናዊነት/ከባቢያዊነት/ጎጠኝነት የበለጠ ታማኝ እንዲሆኑ በማድረግ ይሄን ትግል በአሸናፊነት ለመወጣት አስፈላጊ የሆነውን አማራዊ አንድነት ላይ ቀዝቃዛ ውሃ ሊቸልስበት ይችላል።
በተጨማሪም የሁሉንም የአማራ ፋኖዎች አንድነትን እውን ለማድረግ እንደቅድመ ሁኔታ አፍህድን ማፍረሱ ለምን አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ የለም። ምንም እንኳን ሁሉንም የአማራ ፋኖ አደረጃጀቶች ባያቅፍም አፋህድ አሁን ባለው ቁመናው ብቸኛው ቀጠና ዘለል አማራዊ አደረጃጀት ተብሎ ሊጠራ ሚችል ነው፡፡ ስለዚህ ይህን አማራዊ ቀጠና ዘለል መዋቅር በማጠናከር እና የበለጠ በማደራጀት ሌሎች ፋኖዎችን በማካተት ማስፋፋት ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል። በፋኖ አደረጃጅቶች መካከል ያለውን ልዩነቶችን እና ቅሬታዎችን ለመፍታት መቀራረብ ፤ መወያየትና መተማመን ለትግሉ ጠቃሚና አዋጭ አማራጭ ነው። በውይይቶች ቅሬታዎቻቸውን ሲፈቱ እና የጋራ ግብ እና የጋራ ጠላት ላይ ሲያተኩሩ ልዩነት እየጠበበ አንድነት እየጎላ ሊመጣ ይችላል።
ሌላው ይሄን ሀሳብ ሚያቀነቅኑ አካላት ልብ ያላሉት ጉዳይ ቢኖር አፋህድን አፍርሶ ፤ በቀጠና ደረጃ ያለውን አንድነት አጽንቶ እንደገና ሌላ አማራዊ አደረጃጀት ለመፍጠር (መፍጠር ከተቻለ) የሚወስደው ጊዜ ሊረዝም ይችላል። ይሄ ደግሞ ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች ትግሉን ሊፈትነውና በአጭር እንዲቀጭ ሊያደርገው ይችላል፡፡ በማንኛውም የህልውና ትግል ጊዜ እጅግ ወሳኝ ነገር ነው። አፋህድን ማፈራረስ እና መመስረት ከተቻለ አዲስ ድርጅት ከመሠረት እንደአዲስ ለመገንባት ተጨማሪ ብዙ ወራት ወይም አመታት ሊወስድ ይችላል። የአማራ ሕዝብ ከጦርነት፣ ድህነት እና ስደት ጋር በተያያዘ ከባድ ዋጋ እየከፈለ ያለ ህዝብ ስለሆነ በአላስፈላጊ መጓተት የሚመጣን ችግር ለመሸከም ጀርባው አይችልም። አነሰም በዛም አሁን ያለውን ቀጠና ዘለል ድርጂት አፋህድን አፍርሶ እና በቀጠና ከተጠናከርን በኋላ እንደአዲስ መምጣት ሚለው እሳቤ ሰዶ ማሳደድ ቢያምርህ ዶሮህን በቆቅ ለውጥ የሚለውን ብሂል ልብ ይሏል፡፡
በተጨማሪም አፋህድ ይፍረስ አይፍረስ የሚለው እሰጥ አገባ ባለፉት ብዙ ወራት የታዘብነውን የሚዲያ እና ማህበራዊ ሚዲያ ፍትጊያ ከማስቀጠል የዘለለ ትርፍ እንደሌለው ታይቷል፡፡ ባለፉት ጥቂት ወራት የነበረው አፍህድ ይፍረስ ዘመቻ በጠላት ላይ ውሎ ቢሆን ወይም ወንድሞች አንድ ሚሆኑበትን መንገድ መስበክ ላይ ውሎ ቢሆን ዛሬ ብዙ ለውጦች ማየት ይቻል ነበር፡፡ ያለንን ውስን አቅም ጠላት ላይ ማዋላችን ቀርቶ እርስበርስ መጓተቱ ላይ ማዋላችን ለጠላት ኃይል የበለጠ እንዲጠናከር ከማገዝ የዘለለ ፋይዳ የለውም። የያዘነውን አፍርሰን ሌላ እንገንባ የሚለው ላም አለኝ በሰማይ ወተቷን የማላይ አይነት እሳቤም እንደማይሳካ ተገንዝበን ተግባራዊ ሊሆን ሚችሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ማተኮር ያስፈልጋል ።
በአጠቃላይ ከላይ በተዘረዘሩት ከፍተኛ አደጋዎች የተነሳ አፋህድን ለማፈረስ ከመስራት አፋህድን ጨምሮ ሁሉም ከአፋህድ ውጭ ያሉት አሁን ባላቸው ቁመና እና በቅንነት ወደውይይት እና ወንድማዊ ምክክር ቢመጡና አብረው ቢዋሀዱ የተሻለው አማራጭ ነው። ይህ አሰራር ትግሉን በአማራዊነት መስመር ይዞ እንዲቀጥል ከማገዙም በላይ በተመሳሳይ ጊዜ ለበለጠ አማራዊ አንድነት እና ትብብር ለመገንባት እድሉን ይፈጥራል፡፡ ከዚህም በላይ አፋህድ ለአማራዊ አደረጃጀት እርሾ ይሆን ዘንድ እስካሁን የገነባቸውን ድርጅታዊ መሠረተ ልማቶችን እና አውታረመረቦችን እንደጠበቀ ማስፋትና ማጠናከር ይቻላል፡፡ አፋህድን ከማፍረስ ይቅል የበለጠ አጠናክሮ እና ሌሎችን አካቶ እንዲመጣ ማድረግ ካልተቻለስ ምን እናድርግ የሚለውን ሚመልሰው ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘረው መፍትሄ አማራጭ ነው፡፡
4. ከአፋህድ ውጭ ያሉትን ፋኖዎች ያቀፈ ሌላ አማራአቀፍ ድርጅት መመስረት
እስካሁን ካየናቸው አማራጮች በጣም ተመራጩ ሁሉም ፋኖዎች በአንድ አማራዊ መዋቅር ቢታቀፉ የሚለው ነው፡፡ ወደክ/ሀገራዊ አደረጃጀት መመለስ ወይም ለአንድነት እንደቅድመሁኔታ አፋህድን ማፍረስ ሚለው ከጥቅሞ ጉዳቱ የሚያመዝን ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ አፋህድንና ከአፋህድ ውጪ ያሉት ፋኖዎች በአንድ ለማዋሃድ ካልተቻለ ያለው ብቸኛ አማራጭ ከአፋህድ ውጭ ያሉት ሌላ ወንድም አማራዊ ድርጅት መስርተው እንዲመጡ ማገዝ እና ማበረታት ብቻ ነው፡፡ ይህ አዲስ ድርጅት በአሁኑ ጊዜ በአፋህድ ሥር ያልሆኑትን የፋኖ ክፍሎች ያቀፈ ይሆናል።
ሁለተኛ ወንድም አማራዊ ድርጅት መፍጠር ሚያስፈልገው የአሁኑ ሁኔታ ዘላቂ አለመሆኑን በመገንዘብ ነው። በአንድ አማራዊ ድርጅት ስር አንድነት ለመፍጠር የሚደረጉ ሙከራዎች እንደቀጠሉ ሆነው ሁለት ወንድማማች ትይዩ የድርጅታዊ መዋቅሮችን በመፍጠር የጋራ ጠላት ለመምታት ትብብር ማድረግ ይቻላል። ይህ አማራጭ ትግሉ አሁን ካለበት ቅርቃር ለማስወጣት ከማስቻሉም በላይ በክ/ሀገርኝነት መገንገን ሊፈጠሩ ሚችሉ አደጋዎች ያስወግዳል፤ እንደ መለያየት፤ የሀብት ብክነት እና ሌሎችም ለትግሉ ተግዳሮት ሊሆኑ ሚችሉ እንቅፋቶችን ይቀንሳል። ሁለተኛ ድርጅት በመፍጠር በሁለት ሀይሎች የተባበረ ክንድ ጠላትን ለመምታት ይቻላል።
ሌላኛው ድርጅት ከተፈጠረ በኋላ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የትብብር ፍኖተ ካርታ በማዘጋጀት ትግሉን ስትራቴጂካዊ በሆነ መንገድ መምራት አስፈላጊ ነው፡፡ አንድነትን በግድ መጫን የውስጥ ግጭት እና እምነት መሸርሸር ሊያስከትል ስለሚችል በወንድማዊ ትብብርን ያስቀደሙ ሁለት ወንድማማች ድርጅቶችም ትግልን ማቀላጠፍ እንደሚችሉ የተለያዩ ተመሳሳይ የትግል ታሪኮች ምስክር ናቸው፡፡ ሁለቱ ወንድማማች ድርጅቶች ስርነቀል ለውጥን ያማከለ የትግል ግብ ላይ ከተስማሙ የጦር ሜዳ ውሎና ክዋኔዎችን እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ መረጃዎችን በመጋራት ተደጋግፈው በጋራ ሊሰሩ ይችላሉ። ይህ አይነት የትብብር አሰራር ሁለቱንም ድርጅቶች የራሳቸውን ቁመና እንደጠበቁ የትግሉን የጋራ ራእይ እና ዓላማ እንዲያስቀጥሉ ያስችላቸዋል። በጋራ ዕቅድ እና ግንኙነት በኩል ሁለቱም ድርጅቶች የሚያደርጉት ጥረቶች እርስ በርስ የሚጋጩ ሳይሆን የሚደጋገፉ እንዲሆኑ ማድረግም ያስፈልጋል።
በተጨማሪም ሁለት ትይዩ ድርጅቶች መኖር ማለት በሂደት የሚፈልገውን አማራዊ አንድነትን መተው ማለት አይደለም። በተቃራኒው ይህ የሁለት ወንድማማች ድርጅቶች አካሄድ በተለያየ መልኩ የተሰበከውን መቃቃር ለማርገም ፤ እርስ በርስ እምነትን እና ወንድማዊ መግባባትን ለመገንባት የሚያስችል የሽግግር ደረጃ ሆኖ ሊያገለግል ይችላል። በጊዜ ሂደት ቀጣይነት ያለው ውይይት በማድረግና እና በትግሉ የሚገኙ የጋራ ስኬቶች ወደ አንድ የተቀናጀ ግንባር ለመሄድ መንገድ ሊከፍቱ ይችላሉ። ይህ የደረጃ በደረጃ አካሄድ አሁን የታካረሩትን ልዩነቶችን ለመቅረፍ፣ እርስ በርስ አክብሮትን ለመገንባት እና የወደፊት አንድነትን ለማዘጋጀት እድል ይሰጣል። በተመሳሳይ ጊዜ በጋራ ጠላት ላይ ያለው ትግልም ያለማቋረጥ እንዲቀጥል እድል ይሰጣል።
ወደ ፍጹም አማራዊ አንድነት የሚወስደው መንገድ ረጅም ቢሆንም የወቅቱ ትኩረት ጠንካራ እና የተቀናጀ ፤ የተናበበ ጠላትን ከህዝባችን ጀርባ ላይ ማራገፍ ግን ዛሬውኑ መሰራት ያለበት ነው፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች በጠላት ላይ የማያቋርጥ እና የተናበቡ ወታደራዊ ዘመቻወችን በማካሄድ ትይዩ መዋቅሮቻቸው የተቀናጀ ስራ መስራተቸውን ማረጋገጥ አለባቸው። በተለያዩ ድርጅቶች ቢሆኑም በዐላማና በተግባር አንድነትን በማሳየት የትግሉን ጥንካሬ እና ተጽዕኖ ፈጣሪነት ማሳየት አለባቸው። ይህም የህዝብ ድጋፍን ከመጨመሩም በላይ መነቃቃትን ይፈጥራል፡፡ እንዲሁም በሀገርቀፍና እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ትግሉን ከፍ ለማድረግ ያስችላል፡፡
የሁለት ወንድማዊ ድርጅቶች መፈጠር ምርጡና የመጨረሻው መፍትሄ ባይሆንም አሁን ካለንበት ሁኔታዎች አንጻር አስፈላጊ እና ተግባራዊ ምላሽ ነው። ይህ አካሄድ አሁን ያለንበትን ቅርቃር በመቀበል ትግሉ ጉልበቱን እንዳያጣ ወይም በውስጣዊ መለያየት እንዳይጎዳ ብቸኛው መፍትሄ ነው። ይህን በማድረግ የትግሉን ቀጣይነት አስጠብቀን የወደፊት አማራዊ አንድነትም ተስፋ አድርገን እንድንሰራ ከማስቻሉም በላይ እና የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግል በትክክለኛው መንገድ እንዲቀጥል መሰረት ይጥላል።
ማጠቃለያ
የአማራ ህዝብ ተስፋው ይሄ ትግል ብቻ ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ እንደህዝብ የመኖር፣ ክብሩ እና ነፃነቱ በዚህ ትግል ላይ ተንጠልጥሏል። የዚህ ትግል ውጤት የአማራውን ማህበረሰብ የዛሬ ብቻ ሳይሆን የነገ እጣ ፋንታውንም ይወስናል። ስለዚህ እያንዳንዱ የአማራ ፋኖ የሚወሰደው እርምጃ በጥንቃቄ እና በስልታዊ አስተሳሰብ ላይ መመስረት አለበት። ይህ ትግሉን የሚያዳክሙ ስሜትና አለማወቅ የተቀላቀለባቸው እና ያልተሰበባቸው ወደጠላት ወጥመድ የሚያስገቡ ውሳኔዎች የምንወስንበት ጊዜ አይደለም። አንድ አማራ አቀፍ ድርጅት መፍጠር ተመራጩ እና የመጨረሻ ግባችን ቢሆንም፣ አሁን ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት ያስገባ እና በመሬት ላይ ያሉ ተግዳሮቶችን ታሳቢ ያደረገ አማራጭ መፍትሄዎች ያስፈልጋል። ለዚህም ሁለተኛ አማራአቀፍ ወንድማማች ድርጅት መፍጠር፣ በተሟላ ሁኔታ ፍጹም ባይሆንም፣ የትግሉን ጥንካሬ ለመጠበቅ እና በጠላት ላይ ያለውን ግፊት ለማጠናከር አስፈላጊ እርምጃ ነው።
በዚህ ወሳኝ ጊዜ በሁሉም የፋኖ ክፍሎች መካከል ክፍት ውይይት አስፈላጊ ነው። ጥቃቅን ልዩነቶችን ወደጎን ብሎ በጋራ ግንባር ላይ በመተባበር፣ ትልቁን የትግሉን ዓላማ ታሳቢ ያደረገ የጋራ ራእይ በመፍጠር የአማራውን ሕዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ ለማረጋገጥ በጋራ ቁርጠኝነት መስራት አለባቸው። እያንዳንዱ የአማራ ፋኖ ድርጅት ስራው ሁሉ በትክክል የተሰላ፣ ያለውን ውሱን አቅም በጥበብ የሚጠቀም፣ እና እያንዳንዱ ትንሽ ጥረት ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት በሚያስችል መልኩ ታቅዶ የሚተገበር መሆን አለበት። በአንድ የተዋሃድ ድርጅትም ውስጥ ሆኑ ወይም በሁለት በቅርብ ትብብር ሚሰሩ ወንድማዊ ድርጅቶች ትኩረቱ በሙሉ በቆራጥነት ትግሉን ወደፊት ለመግፋት እና በድል ማጠናቀቅ ላይ መሰረት ያደረገ መሆን አለበት። ይህ እንደህዝብ ላለመጥፋት እና የመኖር መብትን ለማስከበር የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ጊዜ የማይናወጥ ቁርጠኝነት፣ የጋራ መስዋዕትነት እና ድልን የሚፈልግ ጽኑ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል። በአንድወጥ አማራዊ ድርጅት ባለመኖር ምክንያት መንገዱ አስቸጋሪ ቢሆንም በግብ አንድነት እና በስልታዊ ትብብር የተቃኘ ትግል የአማራው አሸናፊ መሆኑ አይቀርም።
__
ድጋፍ ያድርጉ :- ቦርከና ከ13 ዓመታት በላይ ነጻ መድረክ በመሆን አገልግሏል ፤ ወደ ፊትም በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት እና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሰራ ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ በዓመት $5 ወይንም $10 የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም ካለዎት እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ድጋፍ ያድርጉ፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ትዊተር ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ







ወንድም ሲሣይ፦
ጥረትህን አደንቃለሁ። ለአማራ ሕልውናም እንደቆምህ አያለሁ። ግን የተለያየ አደረጃጀት ይኑር ያልኸው አይሆንም። አንተ እንዳልኸው የተለያየ ድርጅት ይዘው አዲስ አበባ ቢገቡ፣ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ በማለት፣ የመኢሶንና የኢሓፓን የልጅ አስተያየት በመድገም፣ አዲስ አበባን የጦር ሜዳ ሊያደርጉ ነው ? ከብልፅግና የተረፉትን ወገኖቻችንን ተረዳድተው ሊፈጁ ነው ? ችግራቸው እኮ የሥልጣን ነው። እስክንድር እውነት ለአማራ ሕዝብ ሕልውና ሲል ብቻ ጫካ የገባ ቢሆን ኖሮ፣ ድሮ ገና ድሮ፣ ተመረጥሁ የሚለውን ቀልድ ጥሎ ከሁሉም ወንድሞቹ ጋር በአንድነት ይሰልፍ ነበር።
እኔ እስክንድር ምርጫው ተቀባይነት ባልማግኘቱ አኩርፎ እስከ ዛሬ “ተመርጫለሁ” እያለ የአማራ ፋኖን አደረአጀት ማሰናከሉ፣ ከነጋ ፈንታ መወለዱንም እጠራጠራለሁ። ለአማራ ሕልውና ሕይወቱን ለመስጠት ጫካ የገባ ወጣት፣ እንደ መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ መለስ ዜናዊና አቢይ አሕመድ ለሥልጣንና ለሀብት የመጣና ለአማራ ሕልውና ነው የመጣሁት ማለቱን ውሸት መሆን መረዳት ቀላል ነው። ለአገርና ለወገን ሕልውናናለአንድነት ቢመጣማ ኖሮ፣ 27 ዓመት በእሥር ቤት ሲማቅቅ እንደነበረው እንደ ኔልሰን ማንዴላ በእንብርክክም ሄዱ ሌሎችንም ወደ አንድነቱ ያመጣ ነበር። እንዲያውም፣ እንደ እርሱ በመንደር፣ በሸጥ፣ በክፍለ ሀገር የሚያምኑ የፋኖ መሪዎች ካሉ፣ እንደ ማንዴላ አገር ወዳድነታቸውን ለአማራ ብቻ ሳይሆነ ለመላ ኢትዮጵያውያን ማሳየትና መተግበር ካልቻሉ፣ የኢትዮጵያንና የአማራንም ሕልውና ማስጠበቅ አይችሉም።
የመኢሶንና የኢሓፓ የትግል ስልት ልዩነት በግርድፉ፣ ” አንዱ በባሌ ሲል፣ ሌላው በቦሌ” ማለቱ እንደሆነ ሲነገር ሰምተናል። እኒህ የፈረንጅ ምሑራን፣ አገራቸውንና ችግሯን የማያውቁ፣ የነበራቸው ዕውቀት የቤተ መፃሕፍት ብቻ ነበር። ሌላው ቀርቶ ስለ ሰባዊ መብትም ብዙ የሚያውቁት አልነበረም። ቢያውቁ ኖሮማ፣ ኃይሌ ፊዳ ከአውሮጳ አልጀርስ ድረስ ሄዶ ከመሰል ተማሪዎች ጋር ተወያቶ የጋራ አቋምና የትግል ሥልት አውጥተው ወደ አገር ቤት ይገቡና፣ ለውርደት ሳይሆን፣ ለዕድገት ያበቁን ነበር።
በዚህ በአንድነት ጉዳይ፣ በዛሬ ዘመን ተማርን፣ አወቅን ከሚሉት ይልቅ የቀድሞ መሀያም አርበኞቻችን ይበልጡ ነበር። በላይ ዘለቀ ጃንሆይ ደብረ ማርቆስ ሲደርሱ፣ ጦሩን አሰልፎ ከቢቸና መጥቶ ለንጉሠ ነገሥቱ ታዛዥ መሆኑን አሳይቷል። ሌሎችም አርበኞች በድፍን ኢትዮጵያ ያደረጉት ተመሳሳይ ነው። “ኢትዮጵያን” የተሻለ ከልብ ይወዷት፣ ያስቡላትና ያከብሯት ነበር። ሁሉም መንገሥ ቢፈልጉ ኖሮ፣ እንደ እስክንድርና መሰሎቹ ተከፋፍለው፣ የጃንሆይ መንግሥትና አብሮ የመጣው የዊንጌት ጦር ተደናቅፈው፣ ጣሊያንንም ከጎንደር፣ ክሞጣ፣ ከጅማ፣ ከአዲስ አበባም ለማስወጣት ብዙ መስዋዕት ይጠይቅ ነበር።
የፋኖ መሪዎች ሕይወታቸውን ለአማራ ለመስጠት ጫካ ከገቡ በኋላ በመንደር መከፋፈላቸው የሚገርም ነው። ቆራጥነታቸውና ያስገኙት ውጤትም አስደናቂ ሆኖ ሳለ፣ መንደርን ምን አመጣው ? ሥልጣን ፍለጋውንስ ምን አመጣው ? ሀብት ፍለጋስ ቢሆን፣ ምን አመጣው ? “ለወገን ሕልውና መቆም” ከሁሉም የላቀ ቅዱስና ወሳኝ ዓላማ ነው። ሕልውና ካለ፣ መልካም አስተዳደርና ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ከተቋቋመ፣ በሚሊዮን የሚቆጠር አማራ ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ ኢትዮጵያዊ ወገናችን በሰላም የሚኖርበትና የሚሠራበት አገር መገንባትና ኢዮጵያን ከሌቦችና ዘራፊዎች አጽድቶ ወደ ልማት በማዞር፣ አገራችን ፈጥና ወደ 21ኛው ክፍለ ዘመን እንድትገባ ማድረግ ይቻላል ፤ ከአልተደላደለ ሥልጣንና በቢሊዮን ከሚቆጠር ሀብት እጅግ ይበልጣል። በዚህ ላይ፣ መንግሥቱ ኃ/ማርያምና መለስ ዜናዊ የት እንደደረሱና እንዳደረሱን ተረሳ እንዴ? ወይስ ከታሪክ የመማር አቅም አጣን ?
መንግሥቱ ኃ/ማርያም በማያውቅበት ዘሎ ገብቶ፣ መሬትንም የአርሶ አደሩ ሳያደርግ፣ ኢርትራን አስገንጥሎ፣ የመከላከያ ቁልፍ መሪዎችን ገድሎ ጦሩን ያለመሪ አስቀርቶ፣ ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል እንደሚባለው ወያኔ የሚባል ጅብ ገብቶ 9 ክልል ለ83 ጎሣ ክልሎ፣ ዲሞክራሲያዊም ሆነ ሪፐብሊክ ያልሆነ ሥርዓት መሥርቶ፣ እርስ በርስ እንድንጋደል አመቻችቶን፣ አገር አስዘርፎ፣ ትግራይንም አራቁቶ ዛሬ የለም ። ፋኖ እንደ እነዚህ ጨቋኝ መሪዎች ልሁን ካለ፣ የአማራ ሕልውናና የኢትዮጵያም አንድነት አይኖሩም። እስክንድርና ጓደኞቹ ይህን ይረዳሉ ? ለሆድ መሥራት የአራዊት ባሕርይ ነው።
ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ብንመሠርት ግን፣ መሬቱ፣ ውሀው፣ ማዕድናት፣ በሚሊዮን የሚቆጠር ሥራ ፈት ወጣት፣ የዘመናት ተከባብሮ የመኖር እሤትና አኩሪ የአንድነት ታሪክ አለን። ከጥሩ መሪ ጋር፣ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ፣ ኢኮኖሚያችንን በ10 እጥፍ ማሳደግ ይቻላል። መለስና መንግሥቱ ያን ያታልሉት የነበረውን የዋህ አርሶ አደርና አርብቶ አደር ከዛሬ 2000 ዓመት ሞፈርና ቀንበር እንኳን ትንሽም ሳያሻሽሉት፣ ሲያስገድሉት፣ ሲገድሉትና ሲዘርፉት፣ ሲያዘርፉትም ኖረው ጠፉ። ፋኖ በመንደር ከተከፋፈለ ያንን ሥይጣናዊ አመራር ለመድገም ፈልጎ ነው። መከፋፈል፣ ለ1960ዎች “ተራማጆች”፣ ለ1982 መንግሥት ግልበጣ ሙከራና ለ1953 መንግሥቱ ንዋይም አልበጀም።
ወንድም ሲሣይ፣ አንድነት ምትክ-የለሽ ነው።