
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
በሁዳዴ ታላቁን ጦም
ልጡምልሽ፤ ልሳልልሽ
ላብራ ጥዋፍ፤ ላጢስ ዕጣን
እቤተ ክርስቲያን
በጉልበቴ ልሂድልሽ
ከፈጣሪ ልማልድሽ
ይህን ተኩላ፤ የቀን አውሬ
በሃይለ መለኮት
ፈጥኖ ደርሶ ቢነቅልልሽ፤
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
በረመዳን ታላቁን ጦም
አላህ ልበል፤ ልጡምልሽ
አዛን ልበል፤ ሃ ያ ሃ ለሶላት
ልሂድ መስጅድ
በግንባሬ ተደፍቼ ልስገድልሽ
ጦም ሶላቴን አላህ አይቶ
ይህን ጨካኝ አረመኔ
ከጫንቃሽ ላይ ቢያወርድልሽ።
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
የህዝብሽ መከራ እንግልቱ
መፍናቀል መሳደዱ
እንደዋዛ መገደሉ
መረሸኑ መታረዱ
በበራሪ መንኮራኩር
መጨፍጨፉ መረፍረፉ
በቃሽ ብሎ ቢያቆምልሽ
ይህን ዲያብሎስ አገር አፍራሽ
በሰይፈ መለኮት ቢመታልሽ።
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
ቤተ ክርስቲያን ገዳማትሽን
ቤተ ሙስሊም መስጅድሽን
በመድፍና በቡልዶዘር
አውድሞና ደረማምሶ
ቅርሶችሽን ከተሞችሽን
በጎሳ ጥላቻ አፈራርሶ
የህዝብሽን ድርና ማግ
አመሳቅሎና በጣጥሶ
በስድ አደግ ባልተገራ
ባለጌ አፉ ነጋ ጠባ
ተዘባብቶ ያዋረደሽ
ይህን ዲያብሎስ ከነግዋዙ ከስርዓቱ
በዙርያውም ከከበቡት
ሆድ አምላኪ እበላ ባይ
ማን ሊመጣ ከኔ በላይ
የይስሙላ “ፕሬዝዳንት”
የበር ምንጣፍ፤ በር ከፋች
“ሚኒስትር” ነኝ “አማካሪ”
“ከንቲባ” ነኝ ቀባጣሪ
እነ “አምባሳደር” ተብዬዎች
በራስ ቀርቶ በህሊና
በከርሳቸው አሳቢዎች
“ዲኮንስትራክት አደረግናት”
ብለው የተሳለቁብሽ
በጥራዝ ነጠቅ “ዕውቀታቸው”
ታሪክሽን ያጎደፉ
ከክብርሽ ማማ ያወረዱሽ
ያጠለሹሽ፤ ያዋረዱሽ
ይህን አውሬ ከስርዓቱ
ሁሉን ባንዴ ይንቀልልሽ
ከነቀርሳሽ ይፈውስሽ።
ፈጣሪ አምላክ ትንሳኤሽን
ፈጥኖ ያምጣልን
ሀሴት እናርግ፤ ደ ስ ይ በ ለ ን
ዕ ል ል እንበል፤ እንዘምር
ኢትዮጵያውያን ባንድ ቆመን
እጅ ለእጅ ተያይዘን።
አይ ኢትዮጵያ፤ አይ ሀገሬ
በትንሳኤሽ ልይሽ ልምጣ
በጢያራ ተሳፍሬ
ከወገን ጋር ልካፈለው
ዳግም ልደት ነጻነትሽን
ከመከራ መፈታትሽን
አረንጓዴ ቢጫና ቀይ
ሰንደቅሽ ፊት ቁሜ አብሬ
ያምላክ በረከት ትንሳኤሽን
ላወድሰው በዝማሬ።
ውዴ ኢትዮጵያ፤ ህይወት ነፍሴ
ማንነቴ ታሪክ ክብሬ
ሞገስ ግርማ ሸማ ልብሴ
የሀሴት ዕንባ ላፍስስልሽ
አምላክሽን ላመስግነው
ንሴብሆ፤ ንሴብሆ
አላህ ከቢር ልበልልሽ።
አስፋው ረጋሳ
መጋቢት፤ 2017
ክምድረ አሜሪካ
_
ድጋፍ ያድርጉ :- ቦርከና ከ13 ዓመታት በላይ ነጻ መድረክ በመሆን አገልግሏል ፤ ወደ ፊትም በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት እና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሰራ ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ በዓመት $5 ወይንም $10 የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም ካለዎት እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ https://borkena.com/subscribe-borkena/
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ





