
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
የአደጋው መሰረት ምንድን ነው?
የአማራው ሕዝብ፤ መንደር፤ ጎጥ፤ ክፍለ ሃገር፤ የኑሮ ወይም የትምህርት ደረጃ፤ እምነት፤ ገጠር ወይም ከተማ ውይም ሌለ መለያ ሳይበክለው በአማራነቱ ብቻ እየተለየ ኢላማ ሆኖ ሲወገዝ፤ ሲገደልና እንደ በግ ሲታረድ፤ ሲቆስል፤ በጅምላ ሲታሰር፤ ሲገረፍ፤ ከቀየው ሆነ ተብሎ እንዲራብ ሲደረግ፤ ልጆቹ እንዳይማሩ የትምህርት ገበታቸው ሙሉ በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ሲዘጉበት፤ መተኪያ የሌላቸው መሪዎቹ በተከታታይና ስልታዊ በሆነ ደረጃ እየተለዩ ሲገደሉበት፤ አምባገነኑ ስርዓት፤ የአንዱን የአማራ አካባቢ ከሌላው ለይቶ፤ ድጎማ እየስጠ እርስ በርሱ እንዲናከስና እንዲገዳደል ሲያደርግ ይታያል፡፡ ይህንን አንድን ዘር ከያለበት ማጥፋት ጀኖሳይድ ይሉታል፡፡ እኔ ሙሉ ድምሰሳ (Total Annihilation) እለዋለሁ፡፡
የአማራ ፋኖን እንቅስቃሴ የማጤነውና የምደግፈው በዚህ ደረጃ መዝኘ ነው፡፡ የዘር ማጥፋት ሆነ ሙሉ ድምሰሳ ወንጀል ነው፡፡ ራስን በአንድነት ሆኖ መከላከል አስፈላጊ፤ ህጋዊና ክብር ነው፡፡ የአማራው ሕዝብ ምኞትና ተስፋ በፍትህ፤ በሰላም፤ በመከባበር፤ በፍቅር በመሰረታት አገሩ መኖር ነው፡፡፡ የአማራ ፋኖ መንፈስም ይኼው ነው፡፡ ይህ መርህ ከሆነ አማራ ፋኖን ማን ያፈርሰዋል?
የአማራ ፋኖ መሪዎችና የውጭ ደጋፊዎች በአማራው የህልውና ትግል ላይ ብቻ ከማተኮር ባሻገር፤ ጎራ ለይተው አሁን የሚከተሉት የአሸናፊና የተሸናፊ ግብግብ ወደ የት ያመራል? ብየ ራሴን ስጠይቅ፤ መልሱ እርስ በእርስ ወደ መገዳደል ነው፡፡ በዚህ ሁሉም ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ የሚሆንበት ሁኔታ አይታየኝም፡፡ አምባገነኑ መንግሥት ያሸንፋል፤ የአማራው ሕዝብ ለባሰ ጥቃት ይጋለጣል፡፡
እመኑኝ፤ የአማራው ዋና ጠላት ራሱ የአማራው ልሂቅና ምሁር፤ አክቲቪስትና ማህበረሰባዊ ሜድያ Hኦኗል፡፡
የአማራ ፋኖን የምናፈርሰውም ራሳችን ተምረናል ብለን የምንናገረው አማራዎች ነን፡፡ የአማራ ፋኖ እንደ እምቧይ ካብ እየፈረሰ እያየን መፍትሄ ስናቀርብ አላይም፡፡ “ተባበሩ አለያ ትሠባባራላችሁ” ብለን ለመናገር አልደፈርንም፡፡ እናስታውስ፤ መኢአድን፤ ቅንጅትን ወዘተ አፍርሰናል፡፡ ብንቀበልን ባንቀበልም፤ እርስ በርሳችን እየተናከስንና እየተካሰስን አማራ ፋኖንም እየናድነው ነው፡: በሜድያ እየወጣን አንዱን ወደ ላይ፤ ሌላውን ወደ ታች፤ አንዱን ሰላይ ሌላውን ጀግናና መሪ ወዘተ የምንል እኛው ነን፡፡ ይህ ሂደት አማራውን አይመጥንም፤ አይወክልም፡፡
አማራውን ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵዊነት የመስበክ ሞራል ብቃት የለንም፡፡
በኢትዮጵያ ረዢም የፖለቲካ ታሪክ እንደ አማራው ሕዝብ፤ በተለይ እንደ አማራው ፋኖ ባጭር ጊዚ ውስጥ ራሱን በራሱ አቅም ገንብቶና በራሱ ተማምኖ፤ በራሱ የአካባቢ መሪዎች አመቻችነት ተራውን ሕዝብ ደጀን አድርጎ፤ በጎጃም፤ በጎንደር፤ በወሎና በሸዋ የአማራውን ሕዝብ ለመታደግ ከፍተኛ መስዋእት የከፈለና አመርቂ ውጤት ያሳየ ሃይል የለም፡፡ ይህንን የአማራ ፋኖ የፍትህ ጦርነት ጀብዱ የዓለም ህዝብ እውቅና ሰጥቶታል፡፡ ይህንን ወርቃማ እድል ስኬታማ ካላደረግን የአማራው ሕዝብ የባሰ አደጋ እንደሚደርስበት አምናለሁ፡፡
አምባገነኑ ስርዓት ይህንን የአማራ ፋኖን 21ኛ ክፍለ ዘመን ጀብዱ ሊቀበል አይችልም፡፡ አምባገነኑ አገዛዝ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ “የድሮን ጥቃት አላከሄድኩም፤ አማራውን አላፈናቀልኩም፤ አላስራብኩም፤ ከሺብርተኞች ውጭ አላሰርኩም” ወዘተ እያለ ያስተጋባል፡፡ ይህ ትርክት ፋይዳቢስ መሆኑን አምነስቲ ኢንተርናሺናል 14 April 2025 ለመላው ዓለም ባሰራጨው ዘገባ ብቻ ማየቱ በቂ ነው፡፡AFR 25/9098/2025 ETHIOPIA: “FEDERAL GOVERNMENT MUST PAUSE THE CORRIDOR።” እስካሁን ድረስ “በቀጠና ልማት” ምክንያት” በአዲስ አበባ ብቻ በብዙ መቶ ሺህዎች የሚገመት ሕዝብ ሌላ ተመጣጣኝ መኖሪያ ቤት ወይም መካካሻ ሳይስጠው ከቀየው ተባሯል፡፡ አንዲት የተጎዳች ወጣት ሴት ልጅ እንዲህ እያለች አልቅሳ ተናግራለች፡፡ “ከቤታችን ከተፈናቀልን በኋላ የሚከራይ ቢት ስንፈልግ፤ አከራዮቹ ለተፈናቀሉት እንዳታከራዩ” ብለውናል ያለችው ሊቀሰቅሰንና እምቢ፤ በቃን ሊያስብለን ይችላል፡፡ በሃገር ደረጃ ሲገመገም አምነስቲ እንደሚለው በብዙ ሚሊየን የሚገመት ሕዝብ ተፈናቅሏል፡ ለዚህ ሕዝብ ደንታ የሌለው ስርዓት ነው፡፡ አማራውን በሚመለከት ስገመግመው ይህ ስርዓት ብዙ ሚሊየን አማራ ቢጨፈጨፍ፤ በረሃብ ቢሞት፤ ቢፈናቀል፤ ቢሰደድ ደንታ የለውም፡፡ የሚፈልገው ስለሆነ፡፡ ተጨማሪ መረጃ ከፈለጋችሁ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚካሄደውን በመንግሥት የተቀነባበረ ጭካኒ፤ የድሮንና ሌላ ከባድ መሳሪያ ጭፍጨፋ በሚመለከት World Council of Churches ያወጣውን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ April 25,
2025, “WCC condemns drone attack in Ethiopia….World Council of Churches general secretary Rev. Prof. Dr Jerry Pillay expressed deep concern and sorrow over the tragic loss of civilian lives resulting from a recent drone strike in the town of Gedeb, Amhara region, Ethiopia.”
ይህ በተከታታይ በመንግሥት ደረጃ በማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄድ ጭካኔ የተሞላበት ጭፍጨፋ አያቆምም፡፡ የድምሰሳው አካል ነው፡፡ ለኔ ዛሬ እንቆቅልሽ የሆነብኝ፤ ለሁለት ዓመታት ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመለው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተስፋ የሰጠውና ተአምራዊ ለውጥ ለማሳየት የቻለው የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ ለምን ተበረዘ? በማን ተበረዘ? እንዴት? ምን ይደረግ? የሚለው መሰረታዊ ጥያቄ ነው፡፡
በምንም ልንክደው የማንችለው ሃቅ የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴ ባስቸኳይ መስተካከል ያለባቸው ድክመቶች አሉበት፡፡
አንደኛ፤ የአማራ ፋኖ ሁሉን አማራ አቀፍ የሆነ ተቋምና ድርጅት አልመሰረተም፤ መመስረት አለበት፡፡
ሁለተኛ፤ የአማራ ፋኖ ጀግኖች ቢኖሩትም ቅሉ፤ የመላው አማራ ፋኖ አታጋይ መሪ አልሰየመም፤ መሰየም አለበት፡፡ በአሁኑ ፈታኝ ወቅት፤ የአማራው ፋኖ ኢላማ አፋኙና አምባገነኑ ስርዓት አይደለም፡፡ የስልጣን የበላይነት፤ የርስ በርስ ፉክክርና ግብግብ፤ መወነጃጀልና አርፈህ የኔን አመራር ካልተቀበልክ ወዪልህ ማለት ሆኗል፡፡ “የፉክክር ቤት ሳይዘጋ ያድራል” እንዲሉ፤ ዋናው ኢላማ ተረስቷል፡፡ ይህ ከድንቁርና በላይ ድንቁርና ነው፡፡ የመንደርተኛነት አባዜ ለምን? ለማን?
ጎንደሬውም የኔን፤ የእኛን፤ ጎጃሚውም የኔን፤ የእኛን፤ ወሎየውም የኔን፤ የእኛን፤ የሸዋውም የኔን፤ የኛን” አትንኩብኝ አያለ ከቀጠለ የአማራውን የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ሊመልሰው አይችልም፡፡ ይህ አደገኛ ሂደት መቆም አለበት፡፡ አለያ ሁሉም መስዋእት ይሆናል፡፡ ይህ ጉዞ የሚጠቅመው ለአማራው ሳይሆን ለፈላጭ ቆራጩ አገዛዝ ነው፡፡
አምባገነኑ አገዛዝ ካሸነፈ ደግሞ የአማራው ሕዝብ እንኳን በሰላም፤ ባሪያም ሆኖ የሚኖርባት ኢትዮጵያ አትኖርም፡፡ የአማራ ፋኖ በአንድነት ሆኖ የአማራውን ሕዝብ የመኖር ወይም ያለመኖር ጥያቄ ለመመለስ ካልቻለ የአማራው ሕዝብ ሙሉና የማይመለስ ድምሰሳ (Total Amhara Annihilation) ሊካሄድበት ይችላል፡፡ ማንም የውጭ ሃይል አይደርስለትም፡፡ የአማራውን ልሂቃን፤ ምሁራውን፤ ሜድያ የመንደርተኛነትን፤ የጎጠኛነትን፤ የግለስባዊነትን፤ የጉረኛነትን፤ የሆዳምነትን፤ የግል ጥቅመኛነትና የግል ሥልጣን ተጠሚነትን ወዘተ መዘዝ ማየትና መተቸት ያለብን በዚህ መልክ ነው፡፡ ማንም ግለሰብ ከአማራው ሕዝብ የፍትህ ፍላጎት በላይ ሊሆን አይችልም፡፡
ሶስተኛ፤ ጀግንነቱና ጀብዱ እንዳለ ሆኖ፤ የአማራ ፋኖ እስካሁን የተጓዘበት መንገድ የዳበሳ ጉዞ መሆኑ አይካድም፡፡ ይህ ክፍተት ባስቸኳይ መፍትሄ ሊኖረው ይገባል፡፡
በመርህ የማይመራ ትግል የትም አይደርስም፡፡ አስቡት፤ ህወሃት/ትህነግ አማራውን ዋና ጠላት ያደረገ ፍኖተ ካርታ ተከትሎ ስኬታማ ሆኗል፤ አሁንም አልቅየረም፡፡ ኦነግ ተመሳሳይ ፍኖተ ካርታ ተከትሏል፡፡ ኢሃዴግን የተካው አምባገነን አገዛዝም የሚከተለው መርህ ተመሳሳይ ነው፡፡ ሶስቱም የአንድ ሳንቲም ግልባጭ ናቸው፡፡
አራተኛ፤ የአማራ ፋኖን የሚደግፈው የአማራ ዲያስፖራ ለአንድ ዓላማ በአንድነት ሲሰራ አይታይም፡፡ የአማራ ፋኖን “አንድ ሁን” ማለት ቀላል ነው፡፡ የአማራን ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ጫና ፈጣሪዎች ፤ ሜዲያ ወዘተ አንድ ሁኑ ለማለት አልደፈርነም፤ አልሰራነም፡፡ ይህንን ባስቸኳይ ካላደረን የሞራል ብቃት ሊኖረን አይችልም፡፡ እስኪ ተምሳሌት እንሁን!!! አንድ እንሁን፡፡
የአማራው “ምሁራን፤ ልሂቃንና ጫና ፈጣሪዎች ነን” የምንለው ሁሉ ከመንደርተኛነት፤ ጎጠኛነትና ግለሰባዊነት ምሽጋችን ወጥተን ታሪክና ህሊና የሚያስገድደንን ሃላፊነታችን ለመወጣት፤ በመደጋገፍ፤ በመከባበር፤ በመተማመን ይህንን ለመላው የአማራ ሕዝብ የሚረዳ ክፍተት መሽፈን አለብን፡፡ የአማራው ምሁር፤ ልሂቅ፤ ጫና ፈጣሪ፤ ሜድያና ሌላው “በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት” ሽፋን ተጠግቶ እያመኻኘ፤ ለአማራው ሕዝብ ያለውን ግዴታ አልተወጣም፡፡ ሌላውን ክመተቸቱ በፊት ራሱን ይገምግም፡፡ ራሳችንን እንተች እስኪ፡፡
የኢትዮጵዊነትን መንፈስ ለአማራው ልናስተምረው አንችልም፡፡ እኔ እስክማውቀው ድረስ አማራው ለኢትዮጵያ ደጋፊና ደጀን እንጅ ስጋትና ከሃዲ ሆኖ አያውቅም፡፡ በአማራነቱ የተደራጀበት መሰረታዊ ምክንያት ራሱን ከተጋረጠበት ስርዓት ወለድ የህልውና አደጋ ለመከላከል ብቻ ነው፡፡ ሁሉም የአማራ ምሁር፤ ልሂቅ፤ ጫና ፈጣሪ፤ ጋዜጠኛና ማህበረሰባዊ ሜድያ ተሟጋች “እኔም ፋኖ ነኝ” ብሎ ቢነሳ የዳበሳውን ጉዞ ለማስተካከል የሚቻልበት እድል አለ፡፡
ስድስተኛ፤ የአማራ ፋኖና ደጋፊዎቹ ጠላታቸውንና ወዳጃቸውን አልለዩም፡፡ ለምሳሌ፤ በአሁኑ ወቅት የአማራው ጥያቄ የመኖር አለመኖር ነው ካልን፤ የባህር በር ጉዳይ፤ የኤርትራ ጉዳይ፤ የሶማሌና የጅቡቲ ጉዳይ፤ የፍልስጤም ጉዳይ፤ የዩክሬን ጉዳይ ወዘተ ያገባናል ብለን የምንከራከርበት ነው? ሊሆን አይችልም፡፡ ይህ ሁሉ ማዘናጊያ ነው፡፡ ማዘናጊያውን በየቀኑ የሚወረውርልን አካል ለምን ይሆን? ብለን እንጠይቅ፡፡ የዳበሳ ጉዞን እንድንከተል ነው፡፡
የጠለፋው አደጋ
ፕሮፌሰር አስራት “ሆዳም አማራ” ያሉት ትክክል ነው፡፡ ዛሬ በረቀቀና ስልታዊ በሆነ ደረጃ የስርዐቱ የበላዮች ብዙ ሚልየን የሚገመት ብር ፈሰስ አድርገው የአማራውን ፋኖ በግል ጥቅም በመያዝ ላይ ናቸው፡፡ ይህ ለግል ጥቅሙ ተገዢ የሆነ ግለሰብ ሆነ ቡድን ተአመኔናነቱ ለአማራው የህልውና ትግል ሳይሆን ለራሱና ለሚለገሰው አካል መሆኑ አያጠጣጥርም፡፡ ወገኑ እየተጎዳ እያየ ጦርነቱ እንዲራዘም ይፈጋል ማለት ነው፡፡ የደም ነጋዴ የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ ወንድሙን እንዲገድል ሲጠየቅ “ስንት ብር ይከፈለኛል?” የሚል አማራ ለሆዱ አዳሪና ከሃዲ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የተባባሰው በጎንደር ነው ተብሎ ይነገራል፡፡ ጎንደሬው ምን ይላል? ዝምታን ለምን መረጠ?
የጦር ቀጠናው ጎንደር የነገው “ዳርፉር” እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡
ሰባተኛ፤ እንደ ቀጠና ስመለከተው ጎንደር ስትራተጂክ ቦታ ነው፡፡ ለሱዳን፤ ለኤርትራ አዋሳኝ ነው፡፡ ይህ አካባቢ ስርዓት አልባ ከሆነ ቀስ በቀስ የኢትዮጵያ “ዳርፉር” መሆኑ አይቀርም፡፡ ጎንደሬው ሌላውን ከመተቸት ይልቅ የራሱን አካባቢ ሁኔታ ቢመራመርና መፍትሄ ቢፈልግ፤ ባንድነት ቢሰራና ቢነሳ ይመረጣል፡፡
ስምንተኛ፤ የአማራው ምሁራን አስቸኳይ ስራው/ስራችን የተበታተነውን የአማራ ፋኖ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ ባስቸኳይ አዘጋጅቶ ለአማራው ሕዝብና ለፋኖ መሪዎች ማቅረብ ነው፡፡ ባለቤትነቱ ሲረጋገጥ ፍኖተካርታውን ወደ እንግሊዝኛ ተርጉመን ለመሚመለካታቸው አካላት እንልካለን፡፡
የአማራውን የፍትህ ትግል ልንወጣውና ስኬትማ ለማዳረግ የምንችለው በአንድ መርህ ወይም የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ፤ በአንድ ርስ በርሱ የተቆራኘ፤ የተደጋገፈና የተናበበ የሚሊታሪ እንቅስቃሴ አመራር፤ በአንድ የሕዝብ ግንኙነትና ዲፖሎማሲ መርህ፤ በአንድ ቋት ለአማራው ሕዝብ ትግል የሚደርስ ቁሳቁስ ለመሰብሰብ ስንችል ነው፡፡ የተበታተነው ሂደታችን የትም አያደርሰንም፡፡ ለአላማና ለተቋም ተገዢ እንሁን፡፡
ዘጠኝኛ፤ እኔ የምፈራው የአማራው ድሃ ሕዝብ አቅም መጎዳቱ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ ሸክሙን ወደማይችልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ከሸክሙ ላይ ተጨማሪ ሸክም አያዋጣም፡፡ ህሊና ቢስነት ነው፡፡ ይህንን ሸክም የሚያባብስ ሁሉ የአማራ ጠላት ነው ብል አልሳሳትም፡፡ የአማራው ልሂቅ/ምሁር፤ አክቲቪስት ወዘተ ማን ወዳጁ፤ ማን ጠላቱ እንደሆነ አያውቅም፡፡ የሚለይበት ወቅት አሁን ነው፡፡
አስረኛ፤ የአማራ ፋኖ መሪዎችንና ደጋፊዎችን የማሳስበው አማራ ፋኖ አታጋይ መሪ ያስፈልገዋል፡፡ ችሎታ ያለው ይምራን፡፡ “እኔና እኛ” የሚለው መንደርተኛነት ለአምባገነኑ ስርዓት እንጅ ለአማራው ሕዝብ ትግል አይበጅም፡፡ የአማራ ፋኖ አንድ አማራ ወጥ ተቋም እንጅ በጎጠናኘትና በመንደርተኛነት መዋቀር መዋኘት አያዋጣውም፡፡ እንዲያውም ይህ አይነት የከፈፍለህ ግዛው ሂደት እያማከነው ነው፡፡ ለዓላማ ጥራትና ባለቤትነት፤ ለድርጅት ጠንካራነት፤ ለአመራር ብልህነት፤ ብቃትና ቁርጠኛነት አማራጭ ለማግኘት አልችልም፡፡
ተግዳሮቱ እንዳለ ሆኖ፤ ተስፋ መቁረጥ አንችልም፡፡ ይህ ለአማራው ሕዝብ አማራጭ ሊሆን አይችልም፡፡ ማድረግ ከሚገባን ላይ እናተኩር፡፡ አንድ ምሳሌ ላቅርብ፡፡ በውጭ የሚኖረው የአማራ ተቆርቋሪ ቁሳቁስ እየሰበሰበል ሁሉም ነው ባይባልም፤ አብዝኛው ለተወለደበት አካባቢ እያዋጣ ይለግሳል፡፡ ይህ መጥፎ ነው አልልም፡፡ ሆኖም ልዩነቶችን አባብሷል፡፡ ጎንደሬው ለጎንደር ፋኖ ብቻ፤ ከዚያም ለግለሰብቦች ከለገሰ፤ ጎጃሜውም፤ ወሎየውና ሸዋየውም ተመሣሳይ መዋጮ ካደረገ የአማራ ፋኖን በአንድነት ለማደራጀትና እንዲታገል ለማድረግ እንቸገራለን፡፡ በሌላ አነጋገር “እኔ ይገባኛል” (Entitlement mentality) የሚል ስሜት ይፈጥራል፡፡ ለዚህ መፍትሄው ቁሳቁሱን በአንድ ቋት አስገብቶ ለተገቢው ስራ እንዲውል ማድረግና ለተባለው መዋሉን ማረጋገጥ ነው፡፡ ከእነዚህ ላይ ማተኮርና መስራት የሁሉም ባለድርሻዎች ሃላፊነት ነው፡፡ ምክንያት አንፍጠር፡፡ አምባገነኑ ስርዐት በየወቅቱ ለሚወረውርልን አጀንዳ ተገዢ መሆናችን እናቁም፡፡ የሚወረውርልን ሁሉ ማዘናጊያ ነው፡፡ አፈቀላጢዎቹ ብዙ ናችው፡፡ ተጨማሪ ምሳሌ ላቅርብ፤
አስራ አንደኛ፤ የአማራ ክልል የበአዴን ተተኪዎች በቅርቡ ለጎንደሬው ትንሽ ነገር ሲወረውሩለት ፈገግ እንደሚል ወጣት ሁሉ “ጎንድርን እንሞሽራት” የሚል ማዘናጊያና አማራውን ከአማራው የመከፋፈል ትርክት ወረወሩልን፡፡ ለመሆኑ ጎንደርን ሞሽረው ለማን ሊድሯት ነው? ጎንደሬውን የምመክረው ጎንደር ለማንም አትሸጥም በሉ ነው፡፡
አበው “አያሌው ሞኙ ሰው አማኙ፤ ሰው አማኙ” እዲሉ አንዳንድ ጎንደሬዎች ታሪካዊዋን ጎንደርን በሚመለከት የተሰጠውን ማዘናጊያ አወንታዊ ትርጉም ስጥተውታል፡፡
ጎንደር ውሃ በጀሪካ ሲቀዳ አልደረሱለትም፡፡ የጎንደርን ፋሲል ሃውልት “በሞራ ቀለም ቀብተው አደስንላችሁ” ሲሉም ፍንጥዝያ የገባን ነበርን፡፡ ጎንደሬው እንደዚህ ሞኝና ተላላ ሊሆን አይችልም፡፡ አታዘናጉት፡፡
ጎንደሬውን ላሳስብ የምፍለልገው ጎንደር ከአማራው ህልውና ውጭ መኖሪያና ሚና የለውም፡፡ ጎንደሬው፤ እንደ ወሎየው፤ ወሎየው እንደ ጎጃሜው፤ ጎጃሜው እንደ ሸዋየው የአማራው የህልውና ትግል የራሱም መሆኑን የመቀበል ግዴታ አለበት፡፡ ጎንደር ከሌላው አማራ ሕዝብ አስጨናቂ ሁኔታ የሚለይበት ጉዳይ አለ ቢባል አንደኛ፤ የጦር አውድማ መሆኑ፤ ሁለተኛ ዘረኛውና አፋኙ መንግሥት በጎንደር አንዱን የጎንደር ጀግና ከወንድሙ እየለየ በራሱ ሆዳሞችና ከሃዲዎች መግደልን ተከታታይ ስልት ማድረጉ ነው፡፡ “የራሱን በራሱ ማገዳደል” ዘዴ መሆኑ ነው፡፡
ጎንደሬውን የማሳስበውና የምመከከረው (መካሪ የሚሰማ ጎንደሬ ፈልጌ አላገኘሁም) የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ታየ አ/ሥላሴ ለስርዓቱ ያለውን ተአመኔታ ለማጠናከር በማሰብ “ጎንደርን እንሞሽራት” ብሏል፡፡ ይህንን ማዘናጊያ ከመስጠት ይልቅ፤ በጎደር የሚካሄደው ክፋፍለህ ግደለውና እልቂት ካላቆመ ጎንደር እንደ ዳርፉፍ መና ትሆናለች ቢል ታሪክ ያከብረው ነበር፡፡ ሞኙና ተላለው ጎንደሬ ግን የስማውና የሚያስተጋባው ጎንደሬውን በጅማል ተጠያቂ እያደረገን ነው፡፡ የቴዎድሮስ አገር ለራሱ ታሪክና ለራሱ ህዝብ እንደዚህ ዝቅ ያለ አመለካከት ያለው ነው? የሚል ግምገማ እየተናፈሰ ነው፡፡ የከፋፍለህ ግዛውንና ከፋፍለህ ብላውን አሉታዊ ውጤት ለማየት የሚከተለውን ሰንተረዢ ተመልከቱት፡፡ ስንት ጀግኖች መስዋእት ሆነዋል? ጎንደር እስከ መቸ የጦር አውድማ ሆና ትቆያለች? ለምን ጀግኖቿን ትገብራለች?
በመጨረሻ የማሳስበው እባካችሁ ሰከን ብላችሁ አስቡ፡፡ የጎንደር ሕዝብ የወደፊት እጣ ፋንታ ከመላው አማራ ሊለይ አይችልም፡፡
በተመሳሳይ፤ የአማራ ፋኖ ትግል ስኬታማ ሊሆን የሚችለው መጀመሪያ የተከሰቱትን ልዩነቶች በመወያየት መፍታት፤ ሁለተኛ አማራ ካልሆኑ ተቃዋሚ የውጭና የውስጥ ኃይሎች ጋር ጠንካራና ስትራተጂክ ትስስር መመሰረት ነው፡፡
አመራርና መሪዎች የሌለው ትግል ስኬታማ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ዝርዝር ከተካተቱት በተጨማሪ እነ ዶር አምቸው፤ እነ ብርጋዴር ጀኔራል አሳምነው፤ እነ አርበኛ ከፍያለውና ሌሎች ስማቸው መጨር ያለበትን ወገኖቻችን ለአማራው የመኖር ወይም ያለመኖር ትግግል ሲሉ መስዋእት የሆኑትንና ቤተሰቦቻቸውን እንድናስባቸው አደራ እላለሁ፡፡ በመጨረሻ አደራ የምለው የአማራ ፋኖ ያሉትን ልዩነቶች በስአቸኳይ ለመፍታት ከቻለ ተአምርን በተአምር እንደሚተካ አምናለሁ፡፡
አለያ ታሪክ ይፈርድበታል፤ ተከታታይ የአማራ ትውልድ ሲወቅሰው ይኖራል፡፡
ፍትህ ለአማራ ሕዝብ!
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!
__
ድጋፍ ያድርጉ :- ቦርከና ከ13 ዓመታት በላይ ነጻ መድረክ በመሆን አገልግሏል ፤ ወደ ፊትም በተሻለ ሁኔታ ለማገልገል ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የሰው ኃይል እጥረት ስላለበት እና አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ እየሰራ ስለሆነ ችግሩን ለመቅረፍ በዓመት $5 ወይንም $10 የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ አቅም ካለዎት እዚህ ገጽ ላይ በመሄድ ድጋፍ ያድርጉ፡፡ https://borkena.com/subscribe-borkena/
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ






