
ጠገናው ጎሹ
እጅግ ለከረፋ ፖለቲካ ሥርዓት
ለተጨማለቀ በጎሳ ደም ስሌት
እንተሳሰብ ባይ በአጥንትና ጉልጥምት
ለህወሃት መራሹ ኢህአዴግ ለሚሉት
ለእኩያን ስብስብ ለደደቦች ህብረት
አገርን ለተካው በመንደር ማንነት
መርዙን ለተከለው በአገር አፍራሽነት
ሲታጭ በካድሬነት
ለፖለቲካ ንግድ ተግባርና ስኬት
ቀብተው ሲሾሙት
ለስለላ መረብ ለጥላ ወጊነት
የሰው ሥጋ ለባሽ ሲሆን አሻንጉሊት
ያኔ እኮ ነበረ አብይ የለየለት
ቀውስ ውስጥ የገባበት
በሞራል ዝቃጭ ውስጥ የተዘፈቀበት
ሰለባ በመሆን የአስቀያሚ ልክፍት
እጅግ የወረደ የንግሥና ቅዠት
እውነትን አውልቆ ሲከናነብ ሃሰት
ራሱን ሃሰትን ሆኖ በመገኘት።
አዎ!ያኔ እኮ ነው ህሊናውን ሽጦ ለሃሰት ያደረው
መሆኑን ሲነግረን ጌታ/ፈጣሪ አማካሪው
የእኩይ ባህሪው
ብሎም የጭካኔው።
በእውን የሚቆጣ በመጥፋቱ አባት
እኛም እንደ አማኝ አቅቶን መቆጣት
“እመኑኝ በኢየሱስ” በሚል የሸፍጥ ስብከት
ፈጣሪን ጨምሮ ሲያወርደው ቁልቁለት
ተባባሪ አድርጎ የእኩይ ቤተመንግሥት
አዎ! ያኔ ነበር አብይ የለየለት።
የህወሃት/ የኢህአዴግ ሥርዓተ መቆሚያ
ክፉኛ ሲናጋ በሥልጣነ ሽሚያ
ህዝብ መሰለውና የለውጥ መጀመሪያ
አድሮ በማይፀና ነግ ከነገ ወዲያ
በስሜት ሲጋልብ በሌለው ማረፊያ
አብይና አብዮች አገኙና መግቢያ
በዚያው ባደጉበት የሸፍጥ መደለያ
ተቀባብተው ቀርበው በስመ ኢትዮጵያ
ቤተ መንሥት ገብተው በለቀቁት ቋያ
ምድረ ሲኦል ስትሆን አገረ ኢትዮጵያ
ድፍን ሰባት ዓመት አጥተን መጠለያ
ህይወትን ማቆያ ወይም መሸሸጊያ
አልሰምርልን ብሎን መፍትሄና ገበያ
ከራሳችን አልፎ ሆነን መሳለቂያ ።
የራሳችን ጉድፍ ለማየት ተስኖን
አይተንም ለማፅዳት ስንፍና ተጭኖን
ትውልዳዊ ታሪክ ለመሥራት ተስኖን
እንደ አብይ አይነቱን ጨካኝ ውሸታሙን
በቂ ጊዜ ወስደን መገምገሙ ከብዶን
ይበልጥ ይባስ ብለን “ሙሴያችን ነህ” እያልን
ከአድናቆትም አልፈን አምልኮ እየቃጣን
የለውጥን አቅጣጫ ሃዲዱን እየሳትን
የመከራን ዘመን እናስቆጥራለን።
እንዲህ በቀላሉ ጉዳችን መች ያልቃል
ልክፍተኛው አብይ “ተአምር” ያሰማናል
ወርደት መከራችን “ልማት ነው” ይለናል።
የሰባት ዓመታት የመከራ ዶፉን
ለመማን የሚከብድ የጭካኔ ሰይፉን
ለመስማት የሚቀፍ የግፍ አሟሟትን
የመፈናቀሉን የቁም ሰቆቃውን
ለማሰብ የሚከብድ የርሃብ ቸነፈሩን
የምፅዋዕት ልመና አሰቃቂነቱን
በፖለቲካ መርዝ ትምህርት መበከልን
እምነተ ሃይማኖትን የማጎሳቆልን
ትውልድ የመግደልን
እጅጉን የከፋ የፍትህ እጦትን
የዝርፊያ ግዝፈትን
የሙስና ልክፍት አደገኛነትን
እንዲያው በአጠቃላይ እንደ አገር መውደቅን
የመማሪያ ታሪክ ለማድረግ ከፈለግን
በቃ ማለት ያሻል ሥርዓተ አብይን
በመከራችን ላይ የሚጨፍረውን
ተአምር ሠራሁ በሚል የሚሳለቀውን ።
በቃን የሚል ትግል ትውልድ የሚያድነው
ትውልድ ተሻጋሪ መሠረት ሲይዝ ነው።
ይህ ደግሞ በተራው ከግብ የሚደርሰው
በአርበኝነት ትግል ሲታገዝ ብቻ ነው።
እናም ጥያቄያችን ከሆነ የእውነት
ለህልውና እና ብሎም ለነፃነት
የትኛው ሃይል ነው የቆመው በፅዕናት ?
መሆን ነው ያለበት ።
ከዚህ ጥያቄ ውጭ ሰላማዊ ትግል እያሉ መብከንከን
ወይም በደፈናው ድርድር እያሉ አጥብቆ ማላዘን
ፈፅሞ አይጠቅምም ያራዝማል እንጅ የግፍ አገዛዝን ።






