
ሙሉጌታ ቢያዝን
እነሆ ሀገሩን ጥሎ ሊበር ነው፡፡ መሔዱ እርግጥ ሲኾን ሆዱን ባር ባር አለው፡፡ ከአጥሩ ማዶ ቆመው እጃቸውን ጭራሮ አስመስለው የሚሰናበቱትን ቤተሰዎቹን ሲያይ እንባ በዐይኑ ሞላ፡፡ በቀኝ እጁ የያዘውን የጉዞ ሻንጣ ወዲያ ውርውርና ዘመዶችህን ተቀላቀል የሚል ስሜት ያፍነው ጀመር፡፡ ወድያው ግን የአባቱን ፊት ለርቀት ሲያይ እንደመጨከን ቃጣው፡፡ በኾነ አጋጣሚ እንደመልፈስፈስ ሲሠራው ከአባቱ አፍ የማትጠፋ ቃል አለች፡፡ ለምሳሌ ሊመረቅ አንድ ዓመት ሲቀረው ወላጅ እናቱ (መላ ቤተሰብ አቫዬ የሚላት) ይሄን ዓለም ትታ የሔደች ቀን ከልጆች በተለየ መጽናናት አቃተው፡፡ ይሄኔ ነው ወላጅ አባቱ እንባ ያረገዘ ፊታቸውን እንደመሸፈን አድርገው “ጨከን በል እንጂ ወንድ ልጅ አይደለህም?” ሲሉ የገሰጹት፡፡ የአባቱን ፊት ከርቀት ሲመለከት ትዝ ያለው ቃል ይህ ነበር፡፡
ዐይኑ ላይ ተንቸርፍፎ የነበረውን እንባ ውጦ (ዞርም ሳይል) ወደ አውሮፕላኑ ሆድ ለመግባት ተጣደፈ፡፡
“ጨከን በል እንጂ ወንድ ልጅ አይደለህም?!… ጨከን በል እንጂ ወንድ ልጅ አይደለህም?! ጨከን በል እንጂ ወንድ ልጅ አይደለህም?!” ይህ ቃል ደጋግሞ ጆሮው ላይ ደወለበት፡፡ ስለወንድ ልጅ ምን ያልተባለ አለ?ወንድ ልጅ የሚያለቅሰው እልፍኙን ዘግቶ ነው፤ የምን መነፋረቅ ነው?… እልፍኝ አላደርሰው ካለስ? እንባ ሲታቆር ደግሞ ደግም አይደለ ብለው አስተምረውናል፡፡ “…የወንድ ልጅ እንባ ጡር አለው” ይባላል፤ ሲያለቅስ ማን ዐየው? ወንድ ልጅ ተወልዶ ካልኾነ እንደአባቱ … አባቱ ሌባ የኾነስ እንደሁ?
በር ላይ ቆማ በማይረግብ ደማቅ ፈገግታ ሁሉንም “እንኳን ደኅና መጡ” የምትለዋን የበረራ አስተናጋጅ አልፎ ጓዙን እንደነገሩ ካደረገ በኋላ ወንበሩ ላይ ዘፍ አለ፡፡ሁልጊዜ ለምን መጨረሻ ወንበር ላይ እንደሚደርሰው ይገርመዋል፡፡ ከጎኑ ያለው ነጭ ተሳፋሪ ከያዘው መጽሐፍ ጋር ይጫወታል፡፡ ለአፍታ ፈገግ እንደማለት አለለትና ወደ መጽሐፉ ተመለሰ፡፡ አውሮፕላኑ ምድርን ሊለቅ ሲል ሁልጊዜ መልመድ ያቃተው የልብ ዝቅታ ጎበኘው፡፡ ልክ ውጭ ጉዳይ አካባቢ አንዲት ዳገት አለች(ወይም ነበረች)፡፡ ያቺን ዳገት ለአፍታ ወጥቶ ሲመለስ እንዲሁ ልቡ እንደማምለጥ ይልበታል፡፡ ሲያስነጥሱ ብቻ ሳይኾን የዚህ ጊዜም ‘ይማርህ’ ሳያስፈልግ አይቀርም፡፡ ‘ይሄ ነገር ግን ሁሉንም ሰው ይገጥመዋል ወይስ እኔን ብቻ?….አውሮፕላን ባይኖር በምን እሔድ ነበር?’ እያለ ከራሱ ጋር ወግ ጀመረ፡፡
‘ተፈሪ ተወልዶ ባያስገባ ንስር፣
ይሄንዜ ሐበሻ ክንፉ በቅሎ ነበር’ ማለት ዳዳው፡፡
ሰማዩን ለአፍታ ገረመመና የመስኮቱን መስታወት መለስ ሲያደርግ አስተናጋጇ እንደማይቻል በትኅትና ገልጣ መስታወቱን እቦታው መለሰችው፡፡ ‘እኔ የከፍታ ፍርሃት አለብኝ’ ሊላት አስቦ ምንም ለውጥ ስለሌለው ከአፉ ላይ መለሰው፡፡ የበረራ አስተናጋጇ በምትኩ ‘ካስከፋሁ ይቅርታ’ ለማለት ይመስላል ‘ምን ላምጣልህ?’ ስትል ጠየቀችው፡፡ምንም እንደማይፈልግ በደከመ ፈገግታ ከነገራት በኋላ የሐሳብ ማጉን ያመናትል ገባ፡፡
ከዛሬ ስንት ዓመት በፊት ሴት ልጁን (ሚጣን) ይዞ ወዳንዱ የኢትዮጵያ ክፍል ይዞ ሲበር፣የጠየቀችው ጥያቄ ትዝ አለው፡፡
“አባ ?”
“አቤት”
“ በአውሮፕላን ስንሔድ ለእግዚአብሔር ቀረብን ማለት ነው አይደል?”
“እግዚአብሔርማ ሁሉም ቦታ አለ፣ሽታዬ”
“ታድያ ‘አባታችን ሆይ በሰማይ የምትኖር…’ ለምን እንላለን?”
“…’በሰማይ የምትኖ’ር የምንለው ርቀትን ሳይኾን ከፍታውን ለመግለጥ ነው” አላት አንድ አባት ሲናገሩ የሰማውን አስታውሶ፡፡
ለሚጣ ዶክተር ማለት ሁሉንም ያውቃል፡፡ አባት መኾን ሲጨመርበት አስቡት፡፡ ስለዚህ አንድ አባት “ሁሉንም ዐዋቂ ነኝ” ከሚል መታበይ ካልወጣ፣ ልጁን ወደ አጓጉል መንገድ ሊነዳው ይችላል፡፡ አለያ እሱም ሲያድግ ‘ዐላውቀውም’ የሚለው እንዳይኖረው አንድም በርትቶ ያጠናል ወይም ይዋሻል አለያም ጥያቄን ይሸሻል፡፡ ሥልጣን በጁ የገባ ቀን ደግሞ ጠያቂን እግር በእግር እየተከተለ ያወድማል፡፡ የቻለውን (የሚያውቀውን) መመለስ ያልቻለውን በትሕትና ‘ዐላውቀውም’ ማለት የአባት ወጉ መኾን አለበት፡፡ አንድ ሌላ አማራጭም አለ፤ ጥያቄን ማስጣል/ማረሳሳት፡፡ “ሰማይ ከምድር ምን ያህል ይርቃል?” የሚጣ ጥያቄ ነው፡፡ ስንት ይበላት? ስንትስ ቢላት በዚህ ዕድሜዋ ምን ይፈይድላታል? ‘እግዚአብሔር ሁሉም ቦታ አለ’ ያላት ረቅቆባታል፤ወይም አልተዋጠላትምና “ከእግዚአብሔር ይህን ያህል ኪ.ሜ ርቀናል ወይም ርቆናል ብላ” ለማሰብ እንደኾነ ስለገባው፣ ለዚህ ጥያቄ የመጨረሻውን አማራጭ ወስዷል ፤ ማስጣል “ …ዐየሽው ያንን ጉም? እንዴት ያምራል! ጥጥ አይመስልም? ጥያቄን ማስጣል 101፡፡
“የቱን?” ብላ ወደ መስኮቱ ተጠጋች፡፡ ሕፃን መኾን እንደምን መልካም ነገር ነው! ፡፡ ያ…ሰው ሲሉት መለኮት፣ መለኮት ሲሉት ሰው፣ ያለነገር “…ወደኔ ይመጡ ዘንድ አትከልክሏቸው” አላለም፡፡
ጸሎት ትዝ የሚለኝ አውሮፕላን ስሳፈር ነው ያለው ማ ነበር? ጸሎት አማረው፡፡ አንድስኳ ያልተቆራረጠ ጸሎት ማድረግ ግን አልቻለም፡፡ ቪክቶር ፍሬንክል “Man’s search for meaning” በሚለው መጽሐፉ “… bird’s eye view “ ሲል ይሄን ዕይታ መኾን አለበት እያለ፣ ፍርሃት የወረሰው ልቡን ታቅፎ ፣ ለአፍታ ዐይኑን ቀልቁል ላከ፡፡ የመርቲ ጣሳ የሚመስሉ ቤታቤቶች ተቀበሉት፡፡
አንድ ሰው ከራሱ ጋር ሲያወራ ድምፁ ከተሰማ ‘ጀማመረው’ ይባላል፡፡ ሁሉም ሰው ግን ድምፁን አጥፍቶ ከራሱ ጋር ማውራቱ የታወቀ ነው፡፡ እና አብደታችንን ደበቅን ወይስ ድምፃቸውን አሰምተው የሚያወሩት እብድ አይደሉም?
ሐሳብ ያነሣል፤ይጥላል፡፡ አንዱን ሐሳብ ጀምሮ ሳይጨርስ ወደሌላው እንደፌንጣ ይዘላል፡፡ ከራሱ ጋር ያወራል፡፡ ይቁነጠነጣል፡፡
ከጎኑ ያለው ነጭ ሰው በሁኔታው ሳይረበሽ አይቀርም፡፡ መጽሐፉን አጥፎ ፈገግ በማለት ተመለከተው፡፡ በዚያ “Where are you from?” በሚል ጥያቄ ሊያዝገኝ ነው ብሎ ሲጠብቅ፡- “Do you mind if I ask why?”፡፡ ‘ከየት ነሽ/ህ?’ ጥያቄ እንደአስቴር ዐወቀ ሆዱን አያስብሰውም፡፡ ቶሎ ሆድ የሚብሰው ሰው አይደለም፡፡ “እሱኮ እንባ አይወጣውም፤ ደንጋይ ነው” ይሉታል አንዳንዶች፡፡ አለመኾኑን ግን በእናቱ ሞት (ጥሩ ማሳያ ባይኾንም)አሳይቷል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተርሚናል ላይ ቤተሰቦቹ እጃቸውን ሲያውለበልቡ ታይቷል፡፡ አይበቃም? (ካልበቃ ዕየታየ ይጨመራል፡፡) በርግጥስ ተገቢው ቦታ ሲነካ፣የማይነካ ያለ ይመስል ምንድነው ግን ማሟረት! እርግጥ ነው፡፡ ኃይሌ ገ/ሥላሴ በአንድ ወቅት አሸንፎ ባንዲራው ሲወጣ…ያነባው እንባ ብዙዎቹ ጓደኞቹን አስነብቷል፡፡እሱ እንባ ስላላዋጣ ሀገሩን ይጠላል ማለት ነው?
ይቺ ‘ዋይ’(why) የሚሏት ጥያቄ ግን ከባድ ናት፤ ‘ዋይ ዋይ’ ልታስብል ትችላለች፡፡ ፊቱን ቅጭም አድርጎ “What do you mean…why?”ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰ፡፡
“Why do you travel to Canada? I mean ….is that work stuff or vacation?”
“ Vacation?…. are you kidding ?” ሊለው አማረው፡፡ ከዛ ይልቅ አጠር አድርጎ፡-“Work” አለው፡፡
“Permanently?” ሰውየው የሚፋታው አይመስልም፡፡
“Yes”
ነጩ ሰው ይበልጥ ፈገግ ብሎ፡፡ “Then you must be a medical doctor?” ሲለው ብልጭ አለበት፡፡ ፊቱ ተለዋወጠ፡፡ ንዴት፣ጥቃት በመላ አካሉ ሲሰራጭ ታወቀው፡፡ የሀገሩ ገመና ደጅ መሰጣቱ፣በተለይ ደግሞ በባዕድ መታወቁ አንገበገበው፡፡ “No I’m not” ሲል ምላሽ ሰጠው፡፡
ከስሙ ፊት ቀድሞ የሚመጣው፣ የክብርና የመማር ፣የብዙ እንቅልፍ ማጣት ምልክት የኾነው ዶክተር የሚለው ቃል ለመሳለቂያ የታጨ መኾኑ ሲገባው ‘አይደለሁም’ (“No I’m not” ) ሲል ካደ፡፡ጴጥሮስ አምላኩን ቢክድ መከራን ፈርቶ ነው፡፡ የዚህ ሰው ክህደትስ …ክብርን ላለማስነጠቅ?
ሰው ግን እውነት ሲነገረው የሚናደደው፣ ያደፈጠው አንበሳ ኢጎው ብቅ ስለሚል?
ይህ ምላሹ የማይፈልገው ገጠመኝ ጋ ወስዶ አላተመው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ አንድ አውሮፕላን ተሳፋሪ በበረራ አስተናጋጇ የተሰጠውን ቸኮሌት ከነወረቀቱ ሲያጭድ ከጎኑ ያለው አንድ ነጭ ሰው ይመለከታል፡፡ ያም ነጭ አክብሮ “ጌታዬ የሚበሉት ቸኮሌት በስስ ወረቀት ተሸፍኗል፤ ዐይተውታል?” ይለዋል፡፡
“ኦ አመሰግናለሁ፣ዐላየሁትም ነበር” ይለኛል ብሎ ሲጠብቅ፣ ሰውየው “ዐይቸዋለሁ፤ኾን ብየ ነው”
ብሎ ቼኮሌቱን ከነልባሱ ያዳፍቅ ገባ ፡፡
ወጣቱን ሐኪም እንደዚህ ሰው መኾኑ ደግሞ ይበልጥ አቃጠለው፡፡ ቆይ “ጥላችን ከአመሰግናለሁ ጋ ወይስ ከይቅርታ ጋ?” ሲል ራሱን ጠየቀ፡፡ “ምናልባት ከሁለቱም ይኾናል” ሲል ለራሱ ምላሽ ሰጠ፡፡
ያ ነጭ ሰው ወጣቱን ሐኪም ስሜት መዳመን ለማለዘብ ይመስላል፡፡ “let me tell you one story” አለና ከጥቂት ዓመታት በፊት በአውሮፕላን ከተዋወቃት ወጣት ሐኪም የሰማውን ነገረው፡፡ እንዲህ፡-
….የተሰደደችበት ሀገር ትልቅ ሰው ለሕክምና እሷ ወደምትሠራበት ታላላቅ ሰዎች ወደሚታከሙብት (VIP) ሆስፒታል ይመጣል፡፡… ሰውየው አልጋው ላይ እንደተንጋለለ ሐኪሟን ሲመለከት ፊቱ ይለዋወጣል፡፡ ሜዲካል ዳ/ሩን ጠርቶ፡- በተሳበበረ እንግሊዝኛ she looks Angolan …then no operation ብሎ ልብሱን መለባበስ ይጀምራል፡፡ ሜዲካል ዳ/ሩ በእርጋታ፡- “Sir, you are right she looks like Angolan because she is originally from Angola.”
“I told you that I can’t do operation by Angolan! … you broke your promise.”
“No I didn’t break my promise, sir, because the surgeon is now Canadian.”
“Change her!”
“Sorry sir, (with due respect) I can’t do that. Because she is one of the few brilliant and skilled surgeons I can count on. Our number one priority in here is to save lives, sir.”
መቼ እንደኾነ በውል በማያስታውሰው አንድ ቀን፣ ስለሐኪም ጉዳይ ተነሥቶ ሲጨዋወቱ አንድ ወዳጁ “…ከሐኪም ጋ የሚሳፈጥ ከብረት የተሠራ ብቻ ነው” ያለው ሽው አለበት፡፡ ‘ገንዘብ ካለ በሰማይ መንገድ አለ’ የሚለውን የዘነጋ ነው በሚል ይህን የወዳጁን አስተያየት ከጅልነት ቆጥሮት ነበር፡፡ ሳይሳሳት አይቀርም፡፡






