
ጭር ሲል አንወድም?
በሙሉጌታ ቢያዝን
“እንዴት አደራችሁ፣ቅድምም አሁንም፣
ያለንበት ዘመን አያስተማምንም”፡፡
ታክሲ ውስጥ ነኝ፡፡ በአንድ ወንበር ላይ ለሦስት ኾነን እንደ ሰርዲን ታጭቀን ወደምንሔበት እንጓዛለን፡፡ ዳር ላይ ነበር የተቀመጥኩት፡፡ ወንበሩን የተጋሩኝ ሁለቱ ሴቶች የኾነ ወግ ይዘዋል፡፡ በወጋቸው መሃል አንዳች የሚያስደነግጥ ፣የሚያስደስት አለያም የሚያስገርም ነገር ሳትሰማ አትቀርም፣ አንደኛዋ “በኢየሱስ ስም” አለች፡፡ብዙም ሳትቆይ ‘ወራጅ’ ብላ እንደወረደች ከጎኔ ያለችው አፏን ሸርመም አድርጋ “ማተቡን ለጌጥ ኖሯል ያሰረችው?” አለች፡፡
ኢየሱስ የተሰኘው ስም ከኾነ ሃይማኖት ጋር ብቻ እንዲቆራኝ ተፈርዶበታል ወይም ተፈርዶለታል፡፡ “በኢየሱስ ስም” በማለቷ ምክንያት የተወረወረ ቃል መኾኑን የተረዳው ጆሮውን ቀስሮ ሲሰማ የነበረው ሰው “ኢየሱስን ለ’ነሱ ብቻ የሰጠው ማነው?” አላት ፊቱን አዙሮ ፡፡ ጥቂት በዝምታ ከተዋጠች በኋላ “እረ እሱስ ልክ ነው” አለች ፡፡ “ገመዱን ወዲያና ወዲህ ስንጓተት ሳይታወቀን ለምን ዋናችንን እንደምንጥል አይገባኝም፡፡ አንቺ ብቻ እኮ አይደለሽም፡፡ ብዙው ሰው እንደዛ ማሰቡ ይገርመኛል”፡፡ መልስ የለም፡፡ መስኮት መስኮቱን ታይ ጀመር፡፡ ወዲያው አንድ ስፍራ ላይ ታክሲው ቆመና አንዲት ነፍሰ ጡር ገባች፡፡ ወንበር ይለቀቅልኛል ብላ ብትቁለጨለጭ ወፍ የለም፡፡ ቢጨንቃት ከበሩ ትይዩ ባለው ወንበር የተቀመጠውን ወጣት “ጠጋ በልልኝ” አለችው፡፡ ከመጠጋት ይልቅ “እራስሽ ተጠጊ” በሚል መታበይ እንድታልፍ እግሩን አንፈራጥጦ “ቅርብ ወራጅ ነኝ” አለ፡፡
ከኋላ የተቀመጡ ሽበት የወረሳቸው ሰው ብድግ ብለው “ሁሉም ቅርብ ወራጅ ነው፡፡ ማን የሚቀር አለ?” አሉና “ነይ የኔ ልጅ” ብለው ወንበራቸውን ለቅቀው ኩርሲው ላይ ተቀመጡ፡፡ ልጅቱ ‘እምቢ’ ብላ ብትግደረደርም ሲቆጧት ተቀመጠች፡፡ ወጣቱ አፍሮ (ሼም ይዞት) ወንበሩን ለኚህ ሰው ይለቃል፣ ያ ቢቀር ይቅርታ ይጠይቃል ብየ ጠብቄ ነበር፡፡ አልኾነም፡፡ ሰውየው እጅግ አዝነው “ኑሮውም ያሻቀበው፣ ሰላምም ያጣነው፣ እርስ በርሳችን ስለማንተዛዘን እኮ ነው፣ ምንድን ነው የኾንነው? እረ ወደ ልባችን እንመለስ ጎበዝ!” ካሉ በኋላ “በኛ ዘመን … “ እያሉ ትውልዱን ይወቅጡ፣ይከሸክሹት ጀመር፡፡ በዚያ ታክሲ የተሳፈረው በሞላ የሳቸው ትውልድ አባል አንድስ እንኳ አልነበረም፡፡
እዚህ ታክሲ ውስጥ ከመግባቴ በፊት ሌላ ታክሲ ተጠቅሜ ነበር፡፡ እና ከሾፌሩ ጀርባ አንድ መልእክት አንብቤ ገርሞኝ “እንደ አንተ ያለውን ያብዛልን!” ብየው ነበር፡፡ መልእክቱ፡- “ደም ለሚለግሱ ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንሰጣለን” የሚል ነበር፡፡ ይህ ወጣት የዚህ ትውልድ አባል ነው፡፡ የእናት ሆድ ሽንጉርጉር አትሉም?
ጨዋታን ጨዋታ ያነሣዋልና አንድ ወዳጄ በአውቶብስ ሲሔድ የገጠመውን እንዲህ አጫውቶኝ ነበር፡፡
[ወንበር ይዤ በአውቶብስ እየተጓዝኩ ነበር፡፡ ቀና ስል ጠና ያሉ ሰው ቆመው ስመለከት፣ ከወንበሬ ተነሥቼ “አባት ይምጡ እዚህ ይቀመጡ” ስላቸው “ምን አሉኝ መሰለህ? ምነው ቆሜ አልተመቸውህም?” ሃሃሃሃ…
“እውነት አላቸው እኮ ግን…” አልኩት ፊቱን ቅጭም አድርጎ “እኮ እንዴት?” አለኝ፡፡
ፈገግታየን ሳልቀንስ “ፊትህ የሌባ ነዋ የሚመስለው”
“አንተ ምናለብህ? ቀልድ!” ቀጠለና “የእውነት ግን ከዛ ወዲህ ወንበር መጋበዝ አቁሚያለሁ” ሲለኝ ሆዴን ይዤ ነበር የሳቅኩት ፡፡]
ይኹንና እኔን ጨምሮ ትውልዱን ለሚወቅሱት አባት ምላሽ የሰጣቸው ሰው አልነበረም፡፡ እውነት አላቸዋ!፡፡ በደምሳሳው ‘አንድን ትውልድ መውቀስ ልክ አይደለም’ ብሎ መከራከር ግብዝነት ስለሚኾን ድምፃችንን አጥፍተን ወቀሳውን ተጋትን፡፡
በዚህ ታክሲ ውስጥ ሁለት ጠንካራ ርእሰ ጉዳዮች ተነሥተዋል፡፡ ይህን ጽሑፍ ለመጻፍ የገፋኝም ይህ ነው – ሰላምና ሃይማኖት!
ሰላምና ሃይማኖት ምንና ምን ናቸው? የሰው ስሞች ናቸው? ሰላም ምንድር ነው? ሃይማኖትስ?፣ ሰላም ሃይማኖትን ያመጣል ወይስ ሃይማኖት ሰላምን? አንዱ የሌላው ሳቢያና ውጤት ነው? ከሁለቱ የቱ ይበልጥ ለሰው ያስፈልገዋል? ለምንስ አስፈለገን? ማን ፈጠረው? ከየት ተነሥቶ፣ የት ይደርሳል? ያለ ሰላም መኖር ይቻላል? ያለ ሃይማኖትስ?’ ወደሚለው ዝርዝር አልገባም፡፡ወረቀት የሚመክተው፤ በ’ኔ ዐቅምም የሚሞከር አይደለም፡፡
በሀገረ አሜሪካ አንድ ዘግናኛ ነገር ሲፈጸም፣ አንዳንድ ወግ አጥባቂ ፖለቲከኞችና ምሁራን “ሃይማኖት ስለቀዘቀዘች፣ እግዚአብሔርን ከት/ቤቶቻችን ስላስወገድን ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ ኦክቶበር 30/2015 (እኤአ) የ“Living the Secular Life” ደራሲና የማ/ሰብ ምሁሩ ፕሮፌሰር ዙከርማን (Phil Zuckerman) በሎስ አንጀለስ ታይምስ “ሕዝብ ሃይማኖትን ችላ ባለ ቁጥር፣ ከሰውነት መውረዱ አይቀሬ ነው፡፡ …ወንጀል ይጨምራል፣ነውጥና ቀውስ ይነግሣል …” ይላል፡፡ ይቀጥልና “ይሄ ሲባል የኖረ ነው፤ በመረጃ የተደገፈ ግን አይደለም፡፡ በመረጃ አለመደገፉ ብቻ ሳይኾን ሐቁ ተቃራኒውን መኾኑ” ያስደነግጣል፡፡ እንዴት?
በብዛት አማኝ ባለበት ማ/ሰብ ሙስና፣ ድህነት፣ የሕፃናት ሞት፣ ወንጀል ማሻቀቡ፣ ‘እንዴት ነው ነገሩ?’ ያስብላል፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይ “የተጠላው እንዳልተጠላ”ን ለመጻፍ የገፋው ይሄ ሐቅ ሳይኾን ያቀራል?
‘ሴኩላሪዝም’ (secularism) ብቻውን የሰላም ምንጭ ነው’ ብሎ መደምደም ባይቻልም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የ2011 (እኤአ) ሪፖርት “ግድያ የሚበዛባቸው ዐሥር ሀገራት፣ ‘አማኝ በብዛት ያለባቸው ናቸው’ ሲል አስደንጋጩን እውነት ይግተናል፡፡ ‘ቪዥን ኦፍ ሁማኒቲ’ (Vision of Humanity) የተሰኘው ድርጅት ያወጣው ሪፖርትም “ሰላማዊና ለኑሮ ምቹ ሀገራት፣ ብዙ አማኝ የሌለባቸው ናቸው” ሲል ይህንኑ ሐቅ ይነግረናል፡፡
ይህ ሐቅ ልእለ ኃያል በተባለችው አሜሪካም የተለየ አይደለም፡፡ ሉዚያና፣አርካንሶ፣አላባማ፣ሚሲሲፒ፣ጆርጅያ፣ደቡብና ሰሜን ካሮላይና፣ኬንተኪ፣ቴኑስና ኦክላሆማ የተሰኙት የአሜሪካ ግዛቶች በንጽጽር አማኝ ሳሉ ግድያ የሚበዛባቸው ሲኾኑ ሜይን፣ቬርሞንት፣ኮኔክቲከት፣ሮድ አይላንድ፣ኒውዮርክ፣አላስካ፣ኦሬገን፣ኒው ሃምሻየር ማሳቹሴትስና ካሊፎርኒያ ሃይማኖት የቀዘቀዘባቸው ግዛቶች ቢኾኑም የግድያ መጠን ግን በአንጻሩ አነስተኛ መኾኑን ፔው የምርምር ማእከል (Pew Research Center) አጋልጧል፡፡
አውስትራሊያ መቀመጫውን ያደረገው ‘ግሎባል ፒስ ኢንዴክስ’ (The Global Peace Index -GPI) በሰላምና የኢኮኖሚ በተሰኘው ተቋም (Institute for Economics and Peace) አማካኝነት ከ2008 (እኤአ) ጀምሮ በየዓመቱ የሀገራትን የሰላም ሁኔታ አጥንቶ ሪፖርት ያወጣል፡፡ ይህ ድርጅት “በ2024 (እኤአ) ለኑሮ ምቹና ሰላማዊ በመኾን ለ14 ዓመታት የመሪነቱን ስፍራ የያዘችው አይስላንድ ናት” ሲል አሳውቋል፡፡ (አይስላንድ 9ኛዋ ኢአማኚ (Convinced Atheist) ሀገር መኾኗ ደግሞ ይገርማል)፡፡ ይህ የግሎባል ፒስ ኢንዴክስ (The Global Peace Index) ሪፖርት ‘…ለኑሮ ምቹና ሰላማዊ፣ ዜጎችም ደስተኛ ናቸው’ ብሎ የለያቸውን ሀገራት የሚጋሩትን የጋራ ጠባይ ሲያስረዳ፣‘ሃይማኖተኛ ሕዝብ ስላለባቸው ነው’ አይልም፡፡ይልቁንም “ባለጸግነት፣ ማኅበራዊ ዋስትና፣ትምህርት፣ወንጀልን ማረቂያ ጠንካራ የሕግ ሥርዐትና መንግሥትና ዜጎች ‘አንተ ትብስ፣ አንቺ ትብሽ’ መባባላቸው” እንደኾነ ሹክ ይለናል፡፡ሪፖርቱ የሚነግረን አንድም፣ ሰው መሰሉ ሰውን ከመግደሉ በፊት መግደል ‘ፋይዳው ምንድር ነው?’ ብሎ እራሱን የሚጠይቅ ብቻ ሳይኾን ከፋ ቢባል ‘በሕግ አምላክ!፣እረ በባንዲራው!’ ሲባል ከክፉ ሥራው የሚታቀብ ዜጋ አፍርተዋል ማለት ነው፡፡ አለያም ሰው ወንጀልን የተጠየፈው፣ እስር ቤትን ፈርቶ እንጂ ‘ገሃነም እገባለሁ፣ፈጣሪ አይወደውም’ በማለት አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር “ጽድቅና ኩነኔ ቢኖርም ባይኖርም፣ከክፋት ደግነት ሳይሻል አይቀርም” ብሎ ነው፡፡
አምና 131ኛ የነበረችው ሀገራችን፣ ከ98 በመቶ አማኝ ያለባት ኢትዮጵያ፣ ላለፉት 12 ዓመታት በተከታታይ አሽቆልቁላ፣ ከ163 ሀገራት 144ኛ መኾኗ ሊገርመን አይገባም ማለት ነው? ሰው ሕግን ፈርቶ እንጂ እግዜርን ፈርቶ ክፉ ሥራ መጠየፍን ትቷል ማለት ነው? ‘እገሌ የተባለ ሰው ወድቆ ያገኘውን ገንዘብ ለባለቤቱ መለሰ’ በሚለው ዜና ወቸ ጉድ! ብለን መገረማችንም ይቀጥላል ማለት ነው?
በዓለም ላይ ወደ 10ሺ የሚጠጉ ሃይማኖቶች እንዳሉ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ (የትኛው ይኾን ትክክል? በእርግጥስ የቱ ነው ትክክል?) የሃይማኖት ተከታይ እያሽቆለቆለ ሲመጣ የሃይማኖቶች ቁጥር ደግሞ ማሻቀቡ የሚገርም ነው፡፡ ሁሉም ‘የኔ ሃይማኖት ነው ትክክል፣…እኔ ነኝ ልክ ፣የኔ ልክ ነው’ ይላል፡፡ሁሉም በቆመበት ማዕዘን ልክ ሊኾን ይችላል፡፡ ‘ልክ ነኝ’ ባይ ውስጥ ሃይማኖቱ የሚከለክለው እራስ ወዳድነት አላደፈጠም? ትኅትና አልታፈነም? እውነትስ አንድ አይደለችም?
ሁሉም ሃይማኖቶች ሰው ተኮር ከኾኑ፣ ሰላምን ከሰበኩ፣ ‘ሰላም ሆይ ወዴት ነሽ?’ አንልም፡፡ “Peace come from within-do not seek it without” እንዲል ቡደሃ፣ ኢየሱስ ክርስቶስ “The kingdom of God is within you” (ሉቃ 17:21) እንዲል ሰላም የሚመነጨው ከውስጥ ነውና የሃይማኖት ሚና ያንቀላፋውን የውስጥ ሰላም መቀስቀስ ይመስለኛል፡፡ ሃይማኖት ይሄን ሥራ ከሠራች ታድያ ችግሩ ያለው ከሃይማኖቱ? ከተከታዮች ወይስ ከሃይማኖት መሪዎቹ? ስብራታችን ከመንጋው ወይስ ከእረኛው? ከመንጋው መካከል ከተከለከለው እሸት ለመቅጠፍ የምትደፍረው በግ እረኛው ሲዝል አለያም ዐይኑን ከመንጋው ሲነቅል ይመስለኛል፡፡ሃይማኖት ‘የሰላም መንገድ ጠራጊ ናት፣ በመንግሥትና በዜጎች መካከል የምትቆም ድልድይ ናት’ ይባላል፡፡ድልድይ መኾኗ ቀርቶ ወዳንዱ ያዘነበለች ጊዜ ከሁለቱም ወገን ሞጓሷን ትገፈፋለች፤ መፈራቷም ያበቃል፡፡ ‘ድሃ ተበደለ፣ፍርድ ተጓደለ’ ማለት በመንግሥት ሥራ ጣልቃ መግባት ሳይኾን ‘ያገባኛል’ ማለት ነው፡፡ ‘ለምን?’ ቢሉ ጉዳዩ ከፖለቲካ አልፎ ሰዋዊ ኾኗልና፡፡
“…እስካልተያዝክ ድረስ ሌብነትም ሥራ ነው” የሚለውን ሳያፍር፣ሳይፈራ መቀበል ከቻለ፣ተቀብሎም ከተገበረው ችግሩ ከተናጋሪው ብቻ ነው? ይህ መልእክት ጆሮ አግኝቶ ከኾነ የሚነግረኝ አንድ ቁም ነገር ቢኖር፣ ‘አትስረቅ’ ከሚል የሃይማኖት መሪ ይልቅ ለፖለቲካ መሪ ጆሮ መስጠቱን ነው፡፡”ገንዘብ የሃጢአት ስር ነው” ብላ የምታስተምር ሃይማኖት፣ ደም ስሯ ገንዘብ ከኾነ የሃጢአት ስር ሃይማኖት መኾኗም አይደል?ተበድሮ የሰጠውን እጅ መንሻ ለመክፈል ሃብታምን በሙላትና በስፋት ማገልገሉ፣ ለሃብታም መስገዱ ሳይታለም የተፈታ ነውና ስለ ሚዛናዊነት ለማስተማር የሞራል ብቃት ይኖረዋል? ‘ፊት ዐይታችሁ አታድሉ! ‘ፈጣሪ አይወደውም’ ለማለት ይችላል? ከመንጋው መካከል ጥል ቢነሣ ‘አንተም ተው፣አንተም ተው’ ለማለት ይቻለዋል? ያምርበታል? እጅ መንሻ ሰጥቶ የሚሾም የሃይማኖት አገልጋይ ‘በሚዛን አትበድሉ!፣አትስረቁ!…’ ብሎ ለማስተማር እንዴት ይቻለዋል? እጅ መንሻ ለመስጠት የደፈረ፣ ለመቀበልም አይፈራም ብቻ ሳይኾን የሰጠውን እጅ መንሻ ለመመለስ ሃብታምን እጅ መንሣቱ፣ለሃብታም ማደሩ የታወቀ ነው፡፡እጅ መንሻ መስጠት ያልቻሉቱ ወይም ያልፈለጉቱ በር ላይ፣ እጅ መንሻ የሰጡቱ ማኅሌት ቆመው በየት በኩል ፈጣሪ ይቅረበን?! ይህ እኩይ አዙሪት የት ላይ እንደሚቆም መገመት የሚችል እርሱ ነብይ ነው! ሃይማኖት ያለ ምግባር፣ ከ’ኩርንችት በለስ፣ ከአጋም ወይን’ ለመልቀም እንደመሞከር ያለ ‘ከንቱ፣የከንቱ ከንቱ’ ይመስለኛል፡፡
የቀብር ሰዓት በማርዘም ጽድቅ ይገኝ ይመስል፣ ድሃ ሲሞት ‘እንግዲህ አፈር ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ’ ብሎ አፈር ለማልበስ መጣደፉ (እንደ ድሃ ቀብር አታጣድፈኝ የሚለውን ስላቅ ልብ ይሏል)፣ ሃብታም ሲሞት ‘አይ እንዴት ያለ ሰው!፣ የአባ መስጠት ዘር ነበር…’ እያሉ ማሽቃበጡ ይቀጥላል፡፡ እናም በሰው ሰውኛ ስሌት ‘ድሃ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢገባ ይቀላል’ መባሉ እውነት ይኾናል፡፡
ሃይማኖት በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ እንደኾነ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለይ በአውሮፓና በአሜሪካ ቤተ እምነቶች ወደ መሸታ ቤት እየተለወጡ መኾኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
የዘርፉ ምሁራን በዳለስ በአሜሪካን ፊዚካል ሶሳይቲ ጉባኤ (American Physical Society ) ላይ ወደ አንድ ክፍለ ዘመን ለሚጠጋ ጊዜ ከተሰበሰበ ዳጎስ ካለ መረጃ ተነሥተው “አውስትራሊያ፣ኦስትሪያ፣ ካናዳ፣ቼክ ሪፐብሊክ፣ፊንላንድ፣ አየርላንድ፣ ኔዘርላንድ፣ ኒውዚላንድና ስዊዘርላንድ ሃይማኖት ከነጭራሹ ይጠፋባቸዋል” የተባሉ ሀገራት መኾናቸውን ቢቢሲ (March 22 በ2011-እኤአ) አትሞታል፡፡ ( … that religion will all but die out altogether in those countries….and in all the countries, the indications were that religion was headed toward extinction)፡፡ “እንደምነህ ስለው እንደምነህ አለኝ፣እግዚአብሔር ይመስገን ሊቀር ነው መሰለኝ” የሚለው ስንኝ ለ’ነዚህ ሀገራት ልከኛ ነው፡፡ ገቢ ሲጨምር፣ ሃይማኖትን ችላ የማለት ዝንባሌ ዓለም ዐቀፋዊ እውነታ ነው፡፡’ሀብት በበር ሲገባ፣ ሃይማኖት በመስኮት ትወጣለች’ ዓይነት፡፡ ካርል ማርክስ “ሰብአዊነት በቴክኖሎጂ፣በሳይንስና በኢኮኖሚ ሲደገፍ፣ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ሃይማኖት ትቀዘቅዛለች፣ በፈጣሪ መመካት ይቀንሳል” ይላል፡፡ ጠግባ ማደር ያቃታት ሀገር የዚህ ስጋት የለባትም፡፡ ከሰርክ ወተግ ዐርፎ ‘ከየት መጣሁ? ወዴትስ እሔዳለሁ?’ የሚሉትን ትልቅና ጥልቅ ሀሳቦችን ማሰብ ቅንጦት ነው፤ የሰማይ ያህል ሩቅ፤ የሥላሴን ያህል ረቂቅ ነው፡፡
‘ሃይማኖት ቀየረ እንጂ ሃይማኖቱን ተወ’ ሲባል የማንሰማው፣ ከሃይማኖት ጋር ያለን ቁርኝት ጥብቅ በመኾኑ ነው ከሃይማኖት እራስ ላይ የማልወርደው፡፡እንደ ፍጥርጥራቸው ብለን የምናልፈው ቢኾን እሰየው፤ እዳው ገብስ ነበር፡፡ችግሩ በብዙኃኑ ዘንድ እንደ ‘ሞራል’ ምልክት (ምሰሶ) የሚታዩትን ተቋማት በማየት አጥር ላይ ተንጠልጥሎ የሚያመነታውን፣ ፈራ ተባ የሚለውን “እነሱ እንኳ እንዲህ እያደረጉ…እኔ ምን ቤት ነኝ?” በሚል ስለሚያደፋፍር ብቻ ሳይኾን በምግባር ከተጠገነ፣ በአንድ ጠጠር ብዙ ችግሮቻችንን መትተን እንጥላለን የሚል ቅን ምልከታ ስላለኝ ነው፡፡ ከሃይማኖት እራስ ላይ የማልወርደው ብናድግ፣ ብንመነደግ እንኳ ከጥይትና ከረሃብ ብናመልጥ ‘ነፃ ፈቃዳ’ችንን ተጠቅመን እራሳችንን ከማጥፋት ስለማንመለስ ነው፡፡ ከሃይማኖት እራስ ላይ የማልወርደው እንደ broadspecrum antibiotics ያለ፣ ለብዙ ደዌያችን መድኅን የመኾን እምቅ ዐቅምም ስላለው ነው፡፡ መፍትሔውም ልክ እንደ ክትባት ከዚህ የሚወለድ ይመስለኛል፡፡ 98 በመቶ በላይ አማኝ ባለባት ‘ጦቢያችን’ ስለምን ሰላም አጣን? ነው ወይስ 2 በመቶ የማይሞሉት “ጥቂቶች ቆራጦች ያልተንበረከክነው…” ብለው በመፈከራቸው በፍርሃት ርደን?
ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ ከዐምስት ዓመት በፊት በሜይ 9/2019 (እኤአ) በጦቢያ ግጥምን በጃዝ ተጋብዞ፣ “…የሃይማኖት ሰባኪ ነን የምንል ሰዎች ስብከቱን ላልተወሰነ ጊዜ ብንተወው” ማለቱ ችግራችን ከሃይማኖት እንደሚወለድ ፍንጭ አይሰጥ ይኾን? ምክንያቱን ሲያስረዳ “የማልኖረውን ሕይወት፣ያልገባኝን እውነት በመስበክ ሕዝብንም ሀገርንም መበደል ስለማልፈልግ…” ነበር ያለው፡፡
ዶ/ር ሳምሶን እስጢፋኖስ ከአንድ ዓመት በፊት በኦክቶበር 22/2023 (እኤአ) በዚሁ በጦቢያ ግጥምን በጃዝ ተጋብዞ፣ “…ኢትዮጲያችን በ3ሺ ዘመን ታሪኳ ስም ያላቸው 2ሺ ጦርነቶች አድርጋለች…” ይለናል፡፡ ልብ በሉ ‘ስም ያላቸው ጦርነቶች’ ነው የተባለው፡፡ በሌላ አነጋገር ጠብመንጃችንን ወልውለን “ውረድ እንውረድ ተቁልቁለቱ፣የሞተው ይሙት ታልቅስ እናቱ” ለመባባል! ሁለት ዓመት የ2መቶ ዓመት ያህል ይረዝምብናል! ማለት ነው፡፡ አቤት ጥድፊያ! መጥኔ እቴ!
አሁን ከከፍታ እንጂ ከመውረድ ምን ይገኛል? ከተራራ እንጂ ከቁልቁለት ምን ይገኛል? ከሕይወት እንጂ ከሞት ምን ይገኛል? ከሳቋ እንጂ ከእናት ለቅሶ ምን ይገኛል? ይህን ስንኝ ትንኝ በለጠችው!
‘የመጣንበት መንገድ’ ብቻ ሳይኾን እየሔድንበት ያለው መንገድ ያሳዝናል! ምን ኾነናል? በእርግጥም በጣም ታምመናል! በእርግጥም ቀለብ መሸመት ሲገባው ቅባትና ሽቶ እንደሚገዛው አባወራ ግራ ገብቶናል፡፡”ምግባር ከሌለው ሃይማኖት፣አንድ ፊቱን ሃይማኖት የለሽነት ሳይሻል ይቀራል?” ያስብላል፡፡ ለባልንጀራችን እሾህ ኾነን፣ለገዢዎች ወለላ ከኾንን ‘ሃይማኖት’ ያለጥርጥር እስካሁን የጠቀመው ለ’ኛ ሳይኾን ለገዢዎች ይመስለኛል፡፡ ሃይማኖት ኖሮን እንዲህ ከኾንን ባይኖረን ምን ልንኳኳን ነበር? ‘ወይ ውረድ፣ወይ ፍረድ’ ለማለትም እኮ ጠግቦ ማደር ያስፈልጋል፡፡ “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች…” እንደተባለ ሰምተናል፡፡እኛ ልጆቿ እጆቿን እንዳትዘረጋ ሰንክለነዋል ወይስ ቆርጠነዋል?
“የገደለው ባልሽ፣ የሞተው ወንድምሽ
ሐዘንሽ ቅጥ አጣ፣ከቤትሽ አልወጣ”፡፡ የሚለው ሙሾ አይሰለችም? ይሰለቻል እኮ፡፡
ራሔሏ ኢትዮጵያ ስለልጆችዋ አለቀሰች፡፡ ልጆችዋ ግን እምባዋን ሊያብሱላት ቀርቶ ማልቀሷን ልብ ያሉት አይመስልም፡፡ ምን ኾነናል?! ምንም፡፡ ልማዳችን ነዋ! ጭር ሲል አንወድም!!
ከነሕመማችን ያሰንብተን!
እንኳን ለ25ኛ ዓመት ልደት አደረሳችሁ፣ አደረሰን!
ምንጭ፡-
ለአርታኢ ወይም አዘጋጅ /ዋና አዘጋጅ ብቻ …. i.e NOT to be published publicly)
- Zuckerman, Phil. (2015, Oct. 30). Op-Ed: Think religion makes society less violent? Think again. Los Angeles Times. https://www.latimes.com/opinion/op-ed/la-oe-1101-zuckerman-violence-secularism-20151101-story.html
- Institute for Economics & Peace. Global Peace Index 2024: Measuring Peace in a Complex World, Sydney, June 2024. http://visionofhumanity.org/resources (accessed 10 January 2025).
__
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






