
ክፍል ሁለት
ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com)
የምርጫ ሥርዓት ግቦች
አገራችን ኢትዮጵያ ከመቶ ሃምሳ አመት በፊት ተጀምሮ ኢትዮጵያዊያንን በሚያስማማ መልኩ ያልተገባደደ አገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት አለ፣ይህ ትውልድ ይህንን ተጀምሮ ያላለቀ አገረ-መንግስት ግንባታ ሂደት ሲያጠናቅቅ እራሱን ጠይቆ መመለስ ያለበት ብዙ ጥያቄዎች አሉ፣ ከእነዚህ ጥያቄዎች ውስጥ አንዱ ምን አይነት የምርጫ ሥርዓት ያስፈልገናል የሚለውና ይህ የምንፈልገው የምርጫ ሥርዓት ምን እንድያደርግልን ነው የምንፈልገው የሚለው ቁልፍ ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ ከዲሞክራሲ ልምዳችን፣ ከማህበራዊ አደረጃጀታችንና፣ ከፖለቲካዊ፣ባህላዊና ታሪካዊ እሴቶቻችን አኳያ ታይቶ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ የሚስማማበት መልስ ማግኘት አለበት። ዛሬ በተለያዩ አገሮች ዉስጥ በስራ ላይ የዋሉ የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፣ እነዚህ የምርጫ ሥርዓቶች እያንዳንዳቸው በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ የሚገኙ ተዋንያንን ባህርይ በመቅረጽ በኩል የየራሳቸውን ሚና ይጫወታሉ። ኢትዮጵያ ዉስጥ ዲዛይን የምናደርገው የምርጫ ሥርዓት ምን እንዲያደርግልን ነው የምንፈልገው የሚለው ጥያቄ የምርጫ ሥርዓቱ ዲዛይን ከመደረጉ በፊት መመለስ አለበት፣ምክንያቱም የምርጫ ሥርዓቱ በተለያዩ ተቋሞች ላይ፣ በድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ ላይ፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይና በሌሎችም በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ተዋንያን ላይ ማምጣት ያለበት የባህርይ ለውጥ ምን መምሰል እንዳለበት በቅድሚያ መታወቅ ስላለበት ነው።
የምርጫ ሥርዓት የተለያየ እይታና አመለካከት ያላቸውን ድምፅ ሰጪዎች ፍላጎት አገናኝቶ የፓርላማ ውክልና እንዲኖረው የሚያደርግ የዲሞክራሲ ተቋም ነው። በተቋማዊ ምህንድስና እና በምርጫ ሥርዓት ጥናትና ምርምር የረጂም ግዜ ልምድ ባላቸው ምሁራን እምነት፣ ከሁሉም የተሻለው የምርጫ ሥርዓት የድምፅ ሰጪውን ማህበረሰብ እይታና አመለካከት በቀላሉና አጥጋቢ በሆነ መንገድ ማንጸባረቅ የሚችለው የምርጫ ሥርዓት ነው። እዚህ ላይ ግን አንድ በፍጹም መረሳት የሌለበት ጉዳይ አለ፤ የትኛውንም የምርጫ ሥርዓት ብንመርጥ የድምፅ ሰጪውን ማህበረሰብ ፍላጎት ፍጹም በሆነ መልኩ ማንጸባረቅ የሚችል የምርጫ ሥርዓት የለም፣ ወይም አንድ አገር የሚፈልጋቸውን ማህበራዊና ፖለቲካዊ ግቦች ሁሉ አንድ ላይ ይዞ የሚመጣ የምርጫ ሥርዓት የለም። የምርጫ ሥርዓት ግቦችንን እና የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶችን ጎን ለጎን አስቀምጠን መመልከት ያለብን፣ የትኛውን የምርጫ ሥርዓት ከነደካማ ጎኑ መቀበል አለብን የሚለውን እጅግ በጣም አሻሚ ጥያቄ መመለስ እንዲያስችለን ነው እንጂ ሁሉም የምርጫ ሥርዓት ይብዛም ይነስ ተሸክሟቸው የሚመጣ የራሱ የሆኑ ዳካማ ጎኖች አሉት። ደግሞም ከምርጫ ሥርዓት ባሻገር በፖለቲካ ፓርቲዎችና በድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ ባህርይ ላይ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ብዙ ኃይሎች አሉና፣ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደርግ እነዚህንም ኃይሎች ከግምት ውስጥ ማስገባት አስፈላጊ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ስድስት የምርጫ ሥርዓት ግቦችን እንመለከታለን።
1. የድምፅ ብዛትና የፓርላማ መቀመጫ ድልድል ተመጣጣኝነት (Proportionality of seats to votes)
የምርጫ ሥርዓትን በተመለከት የፖለቲካ ተዋንያኑን ከሚያስጨንቁ ነገሮች አንዱና ዋናው አገራችው ውስጥ ያለው የምርጫ ሥርዓት ምን ያክል ተመጣጣኝ ነው የሚለው ጥያቄ ነው። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች በአንድ የምርጫ ወረዳ ከተሰጠው ድምፅ ውስጥ 35% ብቻ ድምፅ ያገኘ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ እንዲያሸነፍና፣ 65 በመቶ የሚሆነው የወረዳው ድምፅ ሰጪ ባልመረጠው ተወካይ እንዲወክል ያደርጋሉ። እንዲህ ዓይነት የምርጫ ሥርዓቶች በአንድ በኩል ትላልቅ ፓርቲዎችን ጠቅመው ትናንሽ ፓርቲዎችን ይጎዳሉ፣ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድምፅ ያባክናሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የውክልናን ተመጣጣኝነት ያዛባሉ ወይም የአንዳንድ ማህበረሰብ ክፍሎችን ውክልና ያሳንሳሉ። ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ መታየት ካለባቸው ግቦች ውስጥ አንዱ በምርጫ የተሰጠው ድምፅ ብዛትና የፓርላማ መቀመጫ ድልድል ተመጣጣኝነት ነው።
2.የመንግሥት መረጋጋትና ዘላቂነት
በየትም አገር ዉስጥ ህዝብ ከምርጫ የሚጠብቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ፣አንዱና ዋነኛው የመረጠውን ህዝብ ጥቅምና ፍላጎት የሚወክል የተረጋጋና ቀልጣፋ መንግሥት ተመስርቶ ማየት ነው። ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ዉስጥ ወቅቱን እየጠበቀ የሚደረግ ምርጫ አለ፣ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ደግሞ መንግሥት መመስረቱ አይቀርም፣ ምን ዓይነት መንግሥት ነው የሚመሠረተው የሚለው ጥያቄ ግን እንደየምርጫ ሥርዓቱ ይለያያል። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች አንድ ፓርቲ ብቻውን ከግማሽ በላዩን የምክር ቤት መቀመጫ አሸንፎ መንግሥት የሚመሰርትበትን መንገገድ ያመቻቻሉ፣ ሌሎች የምርጫ ሥርዓቶች ደግሞ ጥምር መንግሥት የሚመሠረትበትን መንገድ ያመቻቻሉ። አንድ መንግሥት ህዝብ የጣለበትን አደራ ለመወጣት የፓርቲዎች ስምምነት፣ በቂ ግዜና የተረጋጋ የፖለቲካ ምህዳር ያስፈልገዋል። ከፍተኛ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነት ያላቸው ፓርቲዎች በብዛት የምክር ቤት መቀመጫ በሚያሸንፉበትና ጥምር መንግሥት ውስጥ የመግባት ዕድላቸው ከፍተኛ በሆነባቸው አገሮች ውስጥ፣ አንደኛ- ጥምር መንግሥት መመስረት ብዙ ግዜ የሚወስድ አስቸጋሪ ሥራ ነው፣ሁለተኛ- የተለያየ ፅንፍ ላይ የቆሙ ፓርቲዎች ያሉበት ጥምር መንግሥት የመፍረስና ሌላ ምርጫ የመጠራት ዕድሉ ከፍተኛ ነው፣እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ሲደጋገሙ የፖለቲካ አለመረጋጋት ይፈጠራል። ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ በቅርብ እይታ ከሚያስፈልጋቸው መመዘኛዎች አንዱ የመንግስት መረጋጋትና ዘላቂነት ነው (ዘላቂነት ሲባል አንድ መንግስት የተመረጠበትን የሥልጣን ዘመን ያለ ውዝግብና ቀውስ መጨረስ መቻሉ ነው)
3.አብዛኛው ህዝብ የተመረጠው ተወዳዳሪ (Condorcet Winner)
በህግ አውጪው አካል ውስጥ ወይም በየትኛውም የሥልጣን እርከን አንድን የምርጫ ወረዳ የሚወክለው ፓርቲ ወይም የግል ተወዳዳሪ አብዛኛው ህዝብ (50% + 1) የመረጠው ተወዳዳሪ ሲሆን የምርጫው ውጤት ዲሞክራሲያዊ ህጋዊነትና ቅቡልነት ይኖረዋል። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች አብዛኛው ድምፅ ሰጪ ያልመረጠውን ተወዳዳሪ አሸናፊ ያደርጋሉ። ለምሳሌ፣ አንድ ተወካይ ብቻ በሚመረጥበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ አራት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩና በቅደም ተከተል 24.8%፣25.6%፣ 25% እና 24.6% ድምፅ ቢያገኙ 25.6% ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ የምርጫ ወረዳውን ያሸንፋል። የዚህ ተወዳዳሪ ማሸነፍ በምርጫ ወረዳው ከተሰጠው ጠቅላላ ድምፅ ውስጥ ሦስተኛ አራተኛው ድምፅ እንዲባክን ያደርጋል፣ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድምፅ በሚባክንባቸው አገሮች ዉስጥ የድምፅ ሰጪው በምርጫ የመሳተፍ ፍላጎት ከግዜ ወደ ግዜ እያሽቆለቆለ ይሄዳል። ስለዚህ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይህ ሲደረግ እነዚህ ችግሮች ከግምት ዉስጥ መግባት አለባቸው።
4. በብሔር፣ በሃይማኖትና በባህል ስብስቦች መካከል ስምምነት እንዲፈጠር ማድረግ
አንድ አገር አንድን የምርጫ ሥርዓት ይበጀኛል ብሎ ሲመረጥ ከምርጫ ሥርዓቱ የሚጠብቃቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ነገር ግን አንድ አገር የሚፈልጋቸውን ነገሮች ሁሉ ይዞለት የሚመጣ የምርጫ ሥርዓት የለም። ለምሳሌ፣ የተለያዩ ማህበረሰቦችን ማቀራረብን፣ ተጠያቂነትን፣ የውክልና ተመጣጣኝነትን፣ መንግሥታዊ መረጋጋትን እና ተጠያቂነትን አንድ ላይ ይዞ የሚመጣ የምርጫ ሥርዓት የለም። ኢትዮጵያ ብዙ ብሔሮች የሚገኙባት አገር መሆኗ ብቻ ሳይሆን የብሔር ጥያቄ የተነሳባትና በተለያዩ ብሔሮች መካከል ግጭት የሚታይባት አገር ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ዉስጥ ዲዛይን የምናደርገው የምርጫ ሥርዓት በተላያዩ የብሔር፣የቋንቋ፣የባህልና የሃይማኖት ስብስቦች መካከል መቀራረብ መፍጠር በሚችልበት መልኩ ዲዛይን መደረግ አለበት።
5- አናሳ ቡድኖች ውክልና ማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት
የአናሳ ቡድኖች ውክልና የተለየ እንክብካቤ ያስፈልገዋል የሚለው ክርክር የሚመጣው በብዙ አገሮች ውስጥ አብዛኛው የማህበረሰብ ክፍል የፖለቲካ ሥልጣን ተቆጣጥሮ የራሱን ኤኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጥቅም ሲያስጠብቅ አናሳ ቡድኖችን ስለሚረሳ ነው። በተለይ ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ አናሳ ቡድኖች የምክር ቤት መቀመጫ አሸንፈው ጥቅማቸውን ለማስከበር ያላቸው ዕድል ዝቅተኛ ነው። አናሳ ቡድኖች ዉክልና የሚያገኙበት መንገድ መመቻቸት አለበት የሚለው አባባል ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚደረገው አንድ ሰው ከአናሳ ብሔረሰብ ስለመጣ ችሎታው ሳይኖረው የብሔር ኮታ ለማሟላት ሲባል ብቻ የመንግሥት ሥልጣን መያዝ አለበት ማለት አይደለም። ስለዚህ አገራችን ዉስጥ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ የአናሳ ቡድኖች ውክልና የዲዛይኑ አንድ አካል መሆን አለበት።
6- ማህበረሰቦችን ማቀራርብና ግጭቶች እንዲወገዱ ማድረግ
በአንድ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ በምርጫ ተወዳድሮ ማሸነፍና መንግሥት መሥርቶ አገር መምራት ብቻ አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ አገር ውስጥ በፓርላማ ተቃዋሚነት ከሚጫወቱት ሚና ባሻገር ግጭቶችን የማብረድ፣እንዳይነሱ የማድረግና ባጠቃላይ አገርን የማረጋጋት ሥራም ይሰራሉ። አንዳንንድ የምርጫ ሥርዓቶች የፖለቲካ ፓርቲዎች የፖለቲካ መሰረታቸው ከሆኑ አካባቢያቸው ወጥተው የምረጡኝ ዘመቻ እንዲያካሄዱ ያበረታታሉ። ለምሳሌ፣ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነጮች ጥቁሮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ጥቁሮችም ነጮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች እየሄዱ የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሄዱ በተደጋጋሚ ታይቷል፣ደግሞም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ነጮች በጥቁሮች ጥቁሮችም በነጮች የተወከሉባቸው አካባቢዎች እንዳሉ የደቡብ አፍሪካ የቅርብ ግዜ ታሪክ ያሳያል። እንዲህ ዓይነቱ አንዱ በሌላው አካባቢ እየሄደ የምረጡኝ ዘመቻ ማካሄድ መቻሉና መመረጡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በነጮችና በጥቁሮች መካከል ያለውን ውጥረት ያለዝበዋል። የኛም አገር የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግ ሊመለከታቸው ከሚገባ ሁኔታዎች ውስጥ አንዱ በማህበረሰብ መካክል ግጭቶች እንዳይነሱ ማድረግን ነው።
የምርጫ ሥርዓት ግቦች ምርጫ
አንድ ምርጫ ሥርዓት ብዙ ግቦች ሊኖሩት ይችላል፣እነዚህ ግቦች ደሞ የተለያዩና አንዳንዴም የሚቃረኑ ሊሆን ይችላል። ለአንድ አገር አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲያደርግ አስቸጋሪ ከሚሆኑ ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሥርዓቱ ማድረግ ከሚችለው በላይ እንዲያደርግ ሲደረግ ወይም ማሳካት ከሚችለው ግብ በላይ እንዲያሳካ ሲደረግ ነው። የምርጫ ሥርዓት በፓርቲ አመሠራረት፣ በፓርቲዎች ባህርይ እና በፓርቲ ሲስተም ልደትና ዕድገት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራል። ስለዚህ አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሲደረግም ሆነ በሥራ ላይ ያለውን የምርጫ ሥርዓት በሌላ መለወጥ ሲያስፈልግ የእያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት ግብና የምርጫ ሥርዓቱ እንዲቀየር የሚፈልገው አካል ግብ ጎን ለጎን ተቀምጠው በጥልቀት መመርመር አለባቸው። ዛሬ በዓለም ውስጥ በተለያዩ አገሮች በሥራ ላይ የዋሉ የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ። የምርጫ ሥርዓት በአንድ አገር ውስጥም ቢሆን በብሔራዊ፣በክልልና በወረዳ ደረጃ ሊለያይ ይችላል። ለምሳሌ፣ አንዳንድ አገሮች ፕሬዚደንታቸውን ለመምረጥ አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን ይጠቀሙና የምክር ቤት አባላትን ለመምረጥ ደግሞ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን ይጠቀማሉ። በአንድ አገር ውስጥ እንደዚህ ዓይነት ልዩነት የሚፈጠረው በተለያየ ደረጃ የሚገኙ መንግሥታዊ ውሳኔ ሰጪዎች የተለያየ ግብና ፍላጎት ስላላቸው ነው። ከዚህ ቀጥሎ ከምርጫ ሥርዓት ግቦች ውስጥ የትኞቹን ግቦች እንዴት እንደምንመርጥና ለምን እንደምንመርጥ በአጭሩ እንመለከታለን። የምርጫ ሥርዓት ግቦች አንዳንዶቹ የሚደጋገፉ ናቸው፣አንዳንዶቹ ደግሞ አብረው የማይሄዱና ጭራሽ የሚጋጩ ናቸው። ለዚህም ነው የምርጫ ሥርዓት ከመመረጡ በፊት ግቦቹ መመረጥ ያለባቸው።
የ”ምርጫ ሥርዓት” ምርጫን በተመለከተ የእያንዳንዱ አገር ግብና ፍላጎት ይለያያል። አንዳንድ አገሮች ዋናው ግባቸው ተጠያቂነትና መረጋጋት ሊሆን ይችላል፣ አንዳንድ አገሮች ደግሞ ብዙ ፓርቲዎችን በፓለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ ማሳተፍ ሊሆን ይችላል። ይህንን የመሳሰሉ የሚጋጩ ፍላጎቶች መኖር ነው የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ሂደትን ውስብስብና አስቸጋሪ የሚያደርገው። ለምሳሌ፣ በአንድ አገር ውስጥ የምርጫ ሥርዓቱ ዋና ዋና ግቦች ተጠያቂነት እና ተመጣጣኝ ውክልና ከሆኑ፣ ሁለቱንም ግቦች ብቻውን ማሟላት የሚችል የምርጫ ሥርዓት የለም። አንዳንድ አገሮች እንደዚህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ድብልቅ የምርጫ ሥርዓቶችን (Hybrid Systems) ተጠቅመዋል። ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት ማለት ሁለት የምርጫ ሥርዓቶችን በማዳቀል የሚገኝ የምርጫ ሥርዓት ነው። ለምሳሌ፣ ጀርመን ውስጥ የፓርላማ ምርጫ የሚካሄደው በአብላጫ ድምፅና በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ነው። በአንድ አገር ውስጥ የምርጫ ሥርዓት በሁለቱ ትልልቅ የፖለቲካ ተዋንያን (በፓርቲዎችና በድምፅ ሰጪው ማህበረሰብ) ባህሪይ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደርጋል። የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያክል ዕጩ ተወዳዳሪዎች እናቅርብ፣ የት ቦታ እንወዳደር፣ ከየትኞቹ ፓርቲዎች ጋር እንጣመር የሚል ውሳኔ ውስጥ እንዲገቡ የሚያደጋቸውና፣ ድምፅ ሰጪው ማህበረስብ ደግሞ ለየትኛው ፓርቲ ድምጼን ልስጥ የሚል ስትራቴጂያዊ ውሳኔ ሲወስን የምርጫ ሥርዓቱ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድርበታል።
አንድ አገር አዲስ የምርጫ ሥርዓት ዲዛይን ማድረግ ከመጀመሩ በፊት፣ የምርጫ ሥርዓቱ በፖለቲካ ሥርዓቱና በፖለቲካ ተዋንያኑ ላይ ይዞት የሚመጣውን ለውጥ አስቀድሞ ካልተገነዘበ በቀላሉ የማይወጣቸው ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ሊገባ ይችላል። ለምሳሌ፣ ኒውዚላንድ ውስጥ በ1993 ዓ.ም. በተካሄደው ውሳኔ ህዝብ አገሪቱ ለረጂም ጊዜ የተጠቀመችበት የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተተካ። ኒውዚላንድ ከዚህ ሽግግር በኋላ በ1996 ዓ.ም. ለመጀመርያ ጊዜ ባካሄደቸው ምርጫ የአገሪቱን ፖለቲካ መድረክ ለብዙ ዓመታት ተቆጣጥረው የነበሩት ሁለቱ የኒውዚላንድ ፓርቲዎች (ብሔራዊና ሠራተኞች ፓርቲ) ፓርላማው ውስጥ አብላጫውን መቀመጫ መያዝ አልቻሉም። ስለዚህ የግድ የጥምር መንግሥት መቋቋም ነበረበት። ሆኖም፣ አሸናፊዎቹ ፓርቲዎች የጥምር መንግሥት ማቋቋም ተስኗቸው፣ አገሪቱ አለልማዷ ለብዙ ጊዜ መንግሥት ሳይኖራት ቆይታለች። ከዚህ በተጨማሪ፣ በቀድሞው አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በፍጹም ወደ ሥልጣን መጥቶ የማያውቀው አንድ አክራሪ ቀኝ ዘመም ፓርቲ ፓርላማው ውስጥ መቀመጫ ከማግኘት አልፎ የጥምር መንግሥቱ ውስጥም መግባት ችሏል።
የወደፊቷ ኢትዮጵያ ከሚጠብቋት ውስብስብ ህገ መንግሥታዊ ምርጫዎች ውስጥ አንዱ የምርጫ ሥርዓት ነው። ኢትዮጵያ አንደኛ- ብዙ ብሔሮች የሚኖሩባት፣ ብዙ ቋንቋዎች የሚነገሩባት እና ብዙ ሃይማኖቶች የሚገኙባት አገር ናት። ሁለተኛ- እራስን በራስ የማስተዳደር እና ለዘመናት የመገንጠል ጥያቄም የተነሳባት አገር ናት። ስለዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲዛይን የሚደረገው የምርጫ ሥርዓት እነዚህንና ሌሎችንም ፖለቲካዊና ማህበረሰባዊ ችግሮቻችንን ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት።
የምርጫ ሥርዓትና የምርጫ ህግ
የምርጫ ሥርዓትና የምርጫ ህግ (Electoral System & Electoral Rules) ጎን ለጎን ሲታዩ ብዙ ልዩነት ያለባቸው አይመስልም። ነገር ግን በእነዚህ ሁለት ፅንሰ ሃሳቦች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ በጣም ትልቅ ነው። የምርጫ ሥርዓት ግንባር ቀደም ሥራ ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ ወደ ፓርላማ ወንበርነት መቀየርና የአንድ አገር የፖለቲካ ሥርዓት በአብዛኛው የፖለቲካ ተዋንያን ተቀባይነት ያለው እንዲሆን ማድረግ ነው፣ሆኖም የምርጫ ሥርዓት ይህንን ዋና ስራውን ሲሰራ የሚከተሉትን ሥራዎችም አብሮ ይሰራል።
1.የድምፅ ሰጪው ህብረተሰብ ጥቅምና ፍላጎት በፖለቲካ ሥርዓቱ ውስጥ እንዲወከል ያደርጋል፤
2. ጠንካራና የተረጋጋ መንግሥት እንዲፈጠር ያደርጋል፤
3. ህዝብ ብቃት ባላቸው ተወካዮች እንዲወከል ያደርጋል፤
4. መንግሥትን ለህዝብ ተጠያቂ ያደርጋል፤
5. የተለያዩ የፖለቲካ ባለድርሻዎችንና ተከታዮቻቸውን ያቀራርባል
እነዚህ አምስት የምርጫ ሥርዓት የሚሠራቸው ሥራዎች፣ በሚቀጥሉት ምዕራፎች በዝርዝር እንደምንመለከተው፣ አንዳንዶቹ የሚቃረኑ ስለሆኑ አምስቱንም ዕሴቶች ይዞልን የሚመጣ የምርጫ ሥርዓት የለም። ጠቅለል ባለ መልኩ፣ ዲሞክራሲ አንድን የፖለቲካ ሥርዓት ተሸክሞ ወደፊት የሚቀዝፍ መርከብ ነው ብንል፣ የምርጫ ሥርዓት የመርከቡ ፓይለት ነው።
ከላይ ከፍ ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው፣ በምርጫ ሥርዓትና በምርጫ ህግ መካከል ልዩነት አለ። የምርጫ ህግ ማን መምረጥና መመረጥ ይችላል (እድሜ፣ ዜግነት፣ የመኖሪያ ቦታ)? ምርጫው መቼና ዬት ይካሄዳል? እጩ ተወዳዳሪዎች እንዴት ይጠቆማሉ? ፓርቲዎችና ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንዴት ነው የምርጫ ዘመቻ የሚያካሄዱት? የድምፅ አሰጣጡና የድምፅ ቆጠራው ሂደት ምን መምሰል አለበት? የሚሉ ጥያቄዎችን ጨምሮ፣ ምርጫውን ማን እንዳሸነፈ እስከማወጅ ድረስ ያሉትን የምርጫ ሂደቶች ሁሉ የሚቆጣጠሩ ደንቦች፣ ህጎችና መመሪያዎች ስብስብ ነው። እነዚህ ህጎችና መመሪያዎች የምርጫ ጣቢያ ድልደላን፣ እጩ ተወዳዳሪዎች የሚጠቆሙበትን ህግ፣ አንድ ዜጋ ለመምረጥና ለመመረጥ መሟላት ያለበትን መመዘኛዎች፣ የምርጫ መመዝገቢያ መመዘኛዎችን፣ የመመዝገቢያ ቦታዎችንና የምርጫ ካርድ ቀረፃን የመሳሰሉ የምርጫውን ውጤት የሚወስኑ ተግባራዊና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን አጠቃልለው የያዙ ዝርዝር ህጎችና ደንቦች ናቸው። እያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት የራሱ ህግ አለው፣ ለምሳሌ፣ የምርጫ ካርድ ምን መምሰል እንዳለበት የሚደነግገው ህግ በአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትና በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓቶች ውስጥ ይለያያል።
የምርጫ ሥርዓት አይነቶች (Types of Electoral Sysytem)
በአለማችን ላይ በሥራ ላይ የዋሉ ብዙና የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፣ በተለያዩ አገሮች ዉስጥ የሚገኙ የምርጫ ሥርዓቶችን ጠጋ ብለን ስንመለክት፣ ፍጹም አንድ ዓይነት የሆነ የምርጫ ሥርዓት የሚጠቀሙ አገሮች አሉ ለማለት ያስቸግራል። ለምሳሌ፣ ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት በብዙ አገሮች ውስጥ አለ፣ሆኖም ይህ የምርጫ ሥርዓት በየአገሮቹ በሥራ ላይ የዋለበት መንገድ ይለያያል። የምርጫ ሥርዓቶችን በውጤታቸው ብቻ ከፋፍለን ስንመለከት፣ በስፋታቸው ግዙፍ የሆኑና በውጤታቸው እጅግ በጣም የተለያዩ ብዙሃንነት (Plurality) እና ተመጣጣኝ ውክልና (Proportional) የሚባሉ ሁለት የምርጫ ሥርዓቶች አሉ። በእነዚህ ሁለት የምርጫ ሥርዓቶች መካከል ደግሞ ሌሎች በጥቃቅን ነገሮች የሚለያዩ ብዙ የምርጫ ሥርዓቶች አሉ። ከላይ የጠቀስናቸውን ሁለት ዋና ዋና የምርጫ ሥርዓቶች ጨምሮ እያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት በስሩ ብዙ የተለያዩ ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶችን ያቅፋል። ይህ ጽሁፍ በዓለም ላይ የሚገኙትን የምርጫ ሥርዓቶች ሁሉ አያጠቃልልም። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ የምንመለከተው ከ12ቱ የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች ውስጥ በዓለም ላይ በስፋት በሥራ ላይ የዋሉትንና ለኛም አገር ብዙ ትምህርት ሊሰጡን የሚችሉትን ዘጠኝ የምርጫ ሥርዓቶችን ነው።
ዛሬ በዓለማችን ውስጥ በሥራ ላይ የዋሉ አሥራ ሁለት የምርጫ ሥርዓት ዓይነቶች አሉ። እነዚህን የምርጫ ሥርዓቶች እንደ ተቀራራቢነታቸውና እንደ ተመሳሳይነታቸው በአራት ዋና ዋና ክፍሎች ከፍሎ መመልከት ይቻላል። የምርጫ ሥርዓት ትልቁ ሥራ ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ ወደ ፓርላማ መቀመጫነት መቀየር ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ የምርጫ ሥርዓቶችን የሚለያያቸው ትልቁ መለኪያ ምን ያህል ተመጣጣኝ ናቸው የሚለው ጥያቄ ነው። አንዳንድ የምርጫ ሥርዓቶች የሚያስገኙት ውጤት ተመጣጣኝ (Proprtional) ነው፣ አንዳንዶቹ ተመጣጣኝ አይደሉም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በሁለቱ መካከል ናቸው።
ዛሬ በዓለም ውስጥ ብቸኛው የፖለቲካ ሥልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን እና ህዝባዊ የሥልጣን ባለቤትነት የሚረጋገጠው ደሞ በምርጫ ብቻ መሆኑን አምባገነኖችም ቢሆኑ ሳይወዱ በግድ የተቀበሉት እውነት ነው፣ለዚህም ነው የምርጫ ሥርዓትን በጥልቀት ማወቅ የሚገባን። ከዚህ ቀጥሎ በሚቀርበው ሠንጠረዥ ላይ የምንመለከተው በተለያዩ አገሮች ውስጥ በሥራ ላይ የዋሉትን ዋና ዋና የምርጫ ዓይነቶች ነው።
የምርጫ ሥርዓት አይነቶች
በሠንጠረዡ አናት በአራቱ ሳጥኖች ውስጥ ያሉት አራቱ ዋና ዋና የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች ሲሆኑ፣ ከእያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት ዝርያ ሥር የሚገኙት ደግሞ በምርጫ ሥርዓቱ ሥር የሚጠቃለሉ ንዑሳን ክፍሎች ናቸው። በዚህ ጽሁፍ ዉስጥ የምንመለከተው በሠንጠረዡ ዉስጥ ከሚታዩት 12 የተለያዩ የምርጫ አይነቶች ውስጥ አምድ ሁለት፣ሦስትና አራት ውስጥ የሚገኙትን 9 የምርጫ አይነቶች ብቻ ነው።
ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት (Plurality/Majoritarian Electoral Sysytems)
ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት በዓለም ላይ በጣም ብዙ አገሮች የሚጠቀሙበት፣ ቀላሉና አጀግ በጣም አሮጌው የምርጫ ሥርዓት ነው። ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ምንም ውስብስብነት የሌለውና ማንም ሰው በቀላሉ ሊረዳው የሚችል የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህንን የምርጫ ሥርዓት በሚከተሉ
| ብዙሃንነት(Plurality) የምርጫ ሥርዓት | ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት | ድብልቅ የምርጫ ሥርዓት | ሌሎች የምርጫ ሥርዓቶች | |
| 1 | አብላጫ ድምፅ | ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ | ድብልቅ ተመጣጣኝ | ዉስን-ድምፅ |
| 2 | ባለ ሁለት ዙር ምርጫ | ፓርቲ-ዝርዝር | ተጓዳኝ ሥርዓት | ቦርዳ-ቆጠራ |
| 3 | አማራጭ ድምፅ | ነጠላ የማይሸጋገር ድምፅ | ||
| 4 | ብዙ-ድምፅ | |||
| 5 | ፓርቲ ብዙ-ድምፅ |
አገሮች ውስጥ የድምፅ አሰጣጡና የድምፅ ቆጠራው ሂደት ጣቢያዎች ከተዘጉ ከጥቂት ሰአታት በኋላ ነው። በብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ሥር የሚገኙ አምስት ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶች አሉ። እነዚህ አምስት ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶች የአንድ ቤተሰብ አባላት በመሆናቸው የሚጋሯቸው ባህሪያት አሉ፣ የሚለያዩበት መንገድም አለ።
1.ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ First past the Post (FPTP)
“ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” የምርጫ ሥርዓት ከብዙሃንነት ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶች ውስጥ ቀላሉና ብዙ አገሮች የሚጠቀሙበት የምርጫ ሥርዓት ነው። ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት በአንግሊዝኛው Plurality electoral system የሚባለው ነው፣ ይህ ቃል ብዝሃነት (Diversity) ከሚለው ቃል የተለየ ነው። ኢትዮጵያ ዉስጥ ያለው አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በዚሁ በብዝሃነት የምርጫ ሥርዓት የሚጠቃለል የምርጫ ሥርዓት ነው። የብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓትን ድምፅ አሰጣጥ ሂደት በስፋት ለመረዳት በመጀመርያ የምርጫ ሥርዓቱን ከሦስት የ”ምርጫ
ሥርዓት” ዋና ዋና ባህርያት ማለትም ከምርጫ ወረዳ መጠን (District Magnitude)፣ ከድምፅ መስጫ ወረቀቱ አወቃቀር እና ከምርጫ ቀመር (Electoral Formula) ጋር በማነጻጸር መመልከቱ የምርጫ ሥርዓቱን በጥልቀት ለመረዳት ይጠቅማል።
1-የምርጫ ወረዳ መጠን (District Magnitude)
ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓትና በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት መካከል ያለው ትልቁ ልዩነት የምርጫ ወረዳው መጠን ነው። ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ምርጫ የሚካሄደው አንድ ተወዳዳሪ ብቻ በሚመረጥበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ ነው። ለምሳሌ አብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን በምትከተለው አገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ 547 የምርጫ ወረዳዎች አሉ፣በእነዚህ ወረዳዎች በእያንዳንዳቸው ዉስጥ የሚመረጠው አንድ ተወካይ ብቻ ነው። የምርጫ ወረዳው መጠን አንድ በሆነባቸውና ከሁለት በላይ ተወዳዳሪዎች በሚወዳደሩበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ አንድ ተወዳዳሪ ምርጫውን ለማሸነፍ ከጠቅላላው ድምፅ ከ50% በላይ የማግኘት ግዴታ የለበትም። የምርጫ ወረዳ መጠን ማለት ከአንድ የምርጫ ወረዳ ተመርጠው የፓርላማ መቀመጫ የሚያገኙትን ሰዎች መጠን የሚያሳይ ቁጥር ነው። ለምሳሌ፣ ከአንድ የምርጫ ወረዳ ተመርጦ ፓርላማ የሚገባው ሰው ቁጥር ሁለት ቢሆን የምርጫ ወረዳው መጠን ሁለት ይሆናል ማለት ነው።
2-የድምፅ መስጫ ወረቀቱ አወቃቀር (Ballot Structrure)
ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ውስጥ በእያንዳንዱ የምርጫ ጣቢያ የሚካሄደው የምርጫ ፉክክር በግለሰብ ተወዳዳሪዎች መካከል ነው እንጂ በፓርቲዎች መካከል አይደለም፣ ወይም ህዝብ በምርጫ ወቅት ድምፅ የሚሰጠው በቀጥታ ለተወዳዳሪ ፓርቲዎች ሳይሆን ለግለሰቦች ነው። በእርግጥ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የፓርቲ አባል ሊሆን ይችላል፣ ላይሆንም ይችላል። እዚህ ላይ መሰመር ያለበት ጉዳይ ቢኖር ድምፅ ሰጪው ህዝብ ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ሳይሆን ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች መሆኑ ነው። ለተጨማሪ ማብራሪያ ከታች የተቀመጠውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ።
የድምፅ መስጫ ካርድ
| 1 | አመንሲሳ መገርሳ | አሮሞ ኮንግሬስ ፓርቲ | አርማ | |
| 2 | ኤልሳቤት ሐጎስ | አረና ትግራይ ፓርቲ | አርማ | |
| 3 | መንግስቱ አለማየሁ | አማራ ብሔራዊ ንቅናቄ | አርማ | |
| 4 | አስቴር ጌታቸው | እናት ፓርቲ | አርማ | x |
| 5 | አቦሴ ሙሊሶ | ኢትዮጵያ ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ | አርማ | |
| 6 | ከዲጃ ማህሙድ | ነፃነትና እኩልነት ፓርቲ | አርማ | |
| 7 | አሳምሩ አመሎ | ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ | አርማ |
ይህ ከላይ የተቀመጠው የድምፅ መስጫ ካርድ የተዋቀረበት መንገድ በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ያሉ የምርጫ ካርዶች ከተዋቀሩበት መንገድ ይለያል። በድምፅ መስጫ ካርዱ ላይ እያንዳንዱ ተወዳዳሪ የትኛውን ፓርቲ ወክሎ እንደመጣ መራጩ ህዝብ በቀለቀሉ መገንዘብ ይችላል። ሆኖም ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲ ሳይሆን ለግለሰብ ተወዳዳሪ ነው። ለፓርቲ በሚሰጥ ድምፅና ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች በሚሰጥ ድምፅ መካከል ያለውን ልዩነት በሚቀጥለው ክፍል ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓትን ስንመለከት አናያለን። ሠንጠረዥ አራት ላይ የተደረደሩት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ሰባት ቢሆኑም አንድ መራጭ ድምፁን መስጠት የሚችለው ለአንድ ተወዳዳሪ ብቻ ነው። ለምሳሌ፣ በሠንጠረዡ ላይ የሚታየውን የምርጫ ካርድ የያዘው ድምፅ ሰጪ ድምፁን የሰጠው እናት ፓርቲ ላቀረባቸው ተወዳዳሪ ለወሮ አስቴር ጌታቸው ነው። በብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ውስጥ የምርጫ ወረዳው መጠን አንድ ስለሆነ አንድ ድምፅ ሰጪ ያለው ዕድል ድምፁን ለአንድ ተወዳዳሪ መስጠት ወይም ማንንም አለመምረጥ ብቻ ነው።
3-የምርጫ ቀመር (Electoral Formual)
የምርጫ ቀመር ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ወደ ፓርላማ መቀመጫነት የሚቀይር ዘዴ ነው። ይህ ቀመር አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ የፓርላማ መቀመጫ ለማሸነፍ ማግኘት ያለበትን የድምፅ መጠን ወይም አንድ ፓርቲ የፓርላማ መቀመጫ ሽሚያ ውስጥ ለመግባት ማግኘት ያለበትን ዝቅተኛውን የድምፅ መጠን (Threshold) ያጠቃልላል። “ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” የምርጫ ሥርዓት እንግሊዝ፣ ካናዳ፣ አሜሪካ፣ ኢትዮጵያ፣ ህንድና ሌሎች ብዙ የቀድሞ የእንግሊዝ ቅኝ ግዛቶችን ጨምሮ በ91 አገሮች ውስጥ በሥራ ላይ የዋለ የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህንን የምርጫ ሥርዓት በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ምርጫ ከተካሄደ በኋላ አሸናፊውን ፓርቲ ወይም ግለሰብ ተወዳዳሪ ለማሳወቅ ብዙ ጊዜ አይፈጅም። አንድ ዕጩ ተወዳዳሪ በምርጫው አብዛኛውን ድምፅ ባያገኝም ከተወዳዳሪዎቹ በአንድም ድምፅ በልጦ ከተገኘ ምርጫውን ማሸነፍ ይችላል። ለምሳሌ፣ 1000 ድምፅ በተሰጠበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ ሦስት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩና በሦስቱ ተወዳዳሪዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ካለ ቀድሞ 334 ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ የምርጫው አሸናፊ ሊሆን ይችላል። ለዚህም ነው ይህ የምርጫ ሥርዓት “ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” በእንግሊዝኛው ደግሞ First Past the Post (FPTP) እየተባለ የሚጣራው። የዚህን ምርጫ ሥርዓት አሠራር ለመረዳት የሚከተለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ።
| ተወዳዳሪ | ድምፅ | መቶኛ | ዉጤት |
| አመንሲሳ መገርሳ | 333 | 33.3% | |
| ኤልሳቤት ሐጎስ | 334 | 33.4% | አሸናፊ |
| መንግስቱ አለማየሁ | 333 | 33.3% | |
| ጠቅላላ ድምፅ | 1000 | 100% |
“ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” የምርጫ ሥርዓት ትናንሽ ፓርቲዎችን ይጎዳል፣ ትላልቅ ፓርቲዎችን ደግሞ አላግባብ ይሸልማል፣ ምክንያቱም ይህ በአንድም ድምፅ ተወዳዳሪዎቹን ላሸነፈ ተወዳዳሪ የምርጫውን ውጤት የሚሸልመው የምርጫ ሥርዓት ትላልቅ ፓርቲዎች በቀላሉ ትናንሽ ፓርቲዎችን አሸንፈው ብቻቸውን መንግሥት መመሥረት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ስለሚያመቻች ነው። በዚህ ዓይነቱ የምርጫ ሥርዓት የአናሳ ቡድኖች ድምፅ ፓርላማ ውስጥ የመሰማት ዕድሉ አነስተኛ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሠንጠረዥ አምስት ላይ በግልጽ እንደሚታየው “ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” የምርጫ ሥርዓት ምርጫውን አሸንፎ የፓርላማ መቀመጫ የሚያገኘው ተወዳዳሪ አብዛኛው መራጭ ያልደገፈው ተወዳዳሪ ነው፣ ይህ ደሞ በተደጋጋሚ ሊያጋጥም የሚችል ክስተት ነው።
2-ባለ ሁለት ዙር ምርጫ (Second Ballot)
“ባለ ሁለት ዙር ምርጫ” የምርጫ ሥርዓት ስሙ በግልጽ እንደሚያመለክተው ምርጫ ተካሂዶ አሸናፊው ካልተለየ አሸናፊውን ለመለየት ሁለተኛ ዙር ምርጫ የሚካሄድበት የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ አንድ ተወዳዳሪ ምርጫውን ለማሸነፍ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ ውስጥ ከግማሽ በላዩን ማግኘት አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ መቶ ድምፅ በተሰጠበት የምርጫ ጣቢያ ውስጥ ሦስት ተወዳዳሪዎች ቀርበው 33%፣ 32% እና 35% ድምፅ ቢያገኙ ማንም ተወዳዳሪ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ ውስጥ ከግማሽ በላዩን ስላላገኘ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ ከምርጫው ይወጣና ሁለቱ ተወዳዳሪዎች እንደገና ለምርጫ ይቀርባሉ። በመገናኛ ብዙኃን በተደጋጋሚ “Run-Off Election” በመባል የሚጠራው እንደዚህ ዓይነቱ የምርጫ ሥርዓት ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ሁለተኛው ዙር ምርጫ እንዲኖር አንደኛ- በመጀመርያው ዙር ምርጫ ላይ የሚቀርቡት ተወዳዳሪዎች ብዛት ከሁለት በላይ መሆን አለበት፣ ሁለተኛ- በመጀመሪያው ዙር ምርጫ ማንም ተወዳዳሪ ከ50 በመቶ በላይ ድምፅ ማግኘት የለበትም፣ ጎረቤታችን ኬንያ፣የአገሪቱን ፕሬዚደንት ለመምረጥ የምትጠቀመው ይህንን የምርጫ ሥርዓት ነው።
3-አማራጭ ድምፅ (Alternate Vote)
አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት እያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ በምርጫው ካርድ ላይ የቀረቡለትን ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከተል እያስቀመጠ ፍላጎቱን (Prefrence) የሚገልፅበት የምርጫ ሥርዓት ነው። አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የምርጫ ወረዳው መጠን አንድ ቢሆንም ይህ የምርጫ ሥርዓት “ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” (FPTP) ከሚባለው የምርጫ ሥርዓት በተለየ መንገድ ለመራጩ ህዝብ አማራጭ የሚሰጥ የምርጫ ሥርዓት ነው። አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ምርጫውን የሚያሸንፈው ተወዳዳሪ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ ከግማሽ በላዩን ያገኘው ተወዳዳሪ ስለሚሆን፣ውክልናው በብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ከግማሽ በታች ድምፅ አግኝቶ ከሚመረጥ ተመራጭ የበለጠ ቅቡልነት ይኖረዋል። አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድምፅ አሰጣጡና በተለይ ድምፅ ቆጠራው ውስብስብ ከመሆናቸው በስተቀር፣ ለድምፅ ሰጪው ህዝብ የተሻለ አማራጭ ሰለሚሰጥና አንድ ተወዳዳሪ ምርጫውን ለማሸነፍ ከ50% በላይ ድምፅ እንዲያገኝ ስለሚያስገድድ ከሌሎቹ የብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች የተሻለ የምርጫ ሥርዓት ነው። አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ዉስጥ በምርጫ ካርዱ ላይ አምስት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ፣ አንድ ድምፅ ሰጪ አምስቱን ተወዳዳሪዎች እንደየፍላጎቱ ከአንድ እሰከ አምስት ያስቀምጣቸዋል።
‘አማራጭ ድምፅ የምርጫ ካርድ
| ፓርቲ | ተወዳዳሪ ስም | ድምፅ |
| ኦፌኮ | አመንሲሳ መገርሳ | 5 |
| አረና | ኤልሳቤት ሐጎስ | 3 |
| ህብር ኢትዮጵያ | መንግስቱ አለማየሁ | 2 |
| እናት | አስቴር ጌታቸው | 1 |
| ኢሶዴፓ | አቦሴ ሙሊሶ | 4 |
ይህንን ከላይ የሚታየውን የምርጫ ካርድ የያዘ ድምፅ ሰጪ የእናት ፓርቲውን ወሮ አስቴር ጌታቸውን በአንደኝነት ሲመርጥ፣አቶ መንግስቱ አለማየሁን፣ወሮ ኤልሳቤት ሐጎስን፣አቶ አቦሴ ሙሊሶንና አቶ አመንሲሳ መገርሳን ሁለተኝ፣ሦስተኛ፣አራተኛና አምስተኛ ምርጫው አድርጎ መርጧቸዋል።
አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድምፅ ቆጠራና የፓርላማ መቀመጫ ድልድል
ጠቅላላ ድምፅ = 72,356
የምርጫ ወረዳው መጠን = 1
የተወዳዳሪ ስም | 1ኛዙር ድምፅ ቆጠራ | አማራጭ ድምፅ 1ኛ ዙር | 2ኛ ዙር ድምፅ ቆጠራ | አማራጭ ድምፅ 2ኛ ዙር | 3ኛ ዙር ድምፅ ቆጠራ | አማራጭ ድምፅ 3ኛ ዙር | 4ኛ ዙር ድምፅ ቆጠራ | አማራጭ ድምፅ አራተኛ ዙር | 5ኛዙር ድምጽ ቆጠራ |
| አመንሲሳ መገርሳ | 13,739 | +61 | 13,800 | +157 | 13,957 | +441 | 14,398 | አራተኛተሸናፊ | |
| ኤልሳቤት ሐጎስ | 1,139 | +48 | 1,187 | ሁለተኛተሸናፊ | |||||
| መንግስቱ አለማየሁ | 26,471 | +45 | 26,516 | +211 | 26,727 | +710 | 27,437 | +8877 | 36,314 አሸናፊ |
| አስቴር ጌታቸው | 29,021 | +39 | 29,060 | +341 | 29,401 | +526 | 29,927 | +4862 | 34,789 |
| አቦሴ ሙሊሶ | 309 | የመጀመሪያተሸናፊ | |||||||
| ከዲጃ ማህሙድ | 1,677 | +116 | 1,793 | +430 | 2,223 | ሦስተኛተሸናፊ |
ይህ ከላይ የተቀመጠው ሠንጠረዥ የተለያዩ የምርጫ ሥርዓቶች ውጤታቸው ምን ያክል እንደሚለያይ በግልጽ ያሳያል። በሠንጠረዡ ላይ የሚታየው ምርጫ የተካሄደው በአማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ሲሆን፣ምርጫውን ያሸነፉት አቶ መንግስቱ አለማየሁ ናቸው። ይህ ምርጫ የተካሄደው “ቀድሞ የማሸነፊያውን ድምፅ ያገኘ” (FPTP) በሚባለው የምርጫ ሥርዓት ቢሆን ኖሮ ወሮ አስቴር ጌታቸው በመጀመርያው ዙር የምርጫው አሸናፊ ይሆኑ ነበር፣ ሆኖም ወሮ አስቴር በመጀመሪያው ዙር ያገኙት ድምፅ ከ50% በታች ስለሆነ ምርጫውን ማሸነፍ አይችሉም። ሠንጠረዡ ላይ በ2ኛው አምድ ውስጥ የሚገኙት ቁጥሮች የሚያሳዩት እያንዳንዱ ተወዳዳሪ ከመራጩ ህዝብ ያገኘውን ድምፅ ብዛት ነው። በአማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት እያንዳንዱ መራጭ የተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ያለበት የምርጫ ካርድ ይሰጠዋል፣በምርጫ ወረዳው ዉስጥ 6 ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ ድምፅ ሰጪው በምርጫ ካርዱ ላይ የሉትን ተወዳዳሪዎች እንደፍላጎቱ ከ1-6 በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ድምፁን ይሰጣል። ለምሳሌ፣ ቡኖ ቦሬ የተባለ ድምፅ ሰጪ በዚህ ምርጫ ተሳታፊ ቢሆንና የመጀመሪያ ምርጫው አቶ መንግስቱ አለማየሁ ቢሆኑ ከ”መንግስቱ አለማየሁ” ስም ጎን አንድ ቁጥር ይጽፋል። የቡኖ ሁለተኛ ምርጫ ወ/ሮ ከዲጃ ማህሙድ ቢሆኑ ከ “ከዲጃ ማህሙድ” ስም ጎን ባለው ሳጥን ውስጥ ሁለት ቁጥር ይጽፋል። የቡኖ ድምፅ መስጠት ሂደት በስድስቱም ተወዳዳሪዎች ስም ጎን ከ1-6 ቁጥር አስገብቶ እስኪጨርስ ድረስ ይቀጥላል። ቡኖ ደምጽ ለመስጠት በተመዘገበበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ ድምፅ ለመስጠት የተመዘገቡ 72,356 ድምፅ ሰጪዎች አሉ። እነዚህ ድምፅ ሰጪዎች ድምጻቸውን የሚሰጡት ቡኖ ድምጹን በሰጠበት መንገድ በድምፅ መስጫው ወረቀት ላይ ያሉትን ተወዳዳሪዎች ከ1-6 በቅደም ተከተል በማስቀመጥ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ የድምፅ አሰጣጡ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የድምፅ ቆጠራው ሂደት ይጀመራል። በአማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ከድምፅ አሰጣጡ ሂደት በላይ ውስብስብ የሆነው የድምፅ ቆጠራው ሂደት ነው። አማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን በተመለከተ አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ጉዳይ አለ፣ እሱም በአማራጭ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት መራጩ ህዝብ ድምፅ የሚሰጠው አንድ ግዜ ብቻ ነው። የምርጫው አሸናፊ እስኪለይ ድረስ የሚቆጠረው፣በየዙሩ እየተሸነፈ የሚወጣውን ተወዳዳሪ በአንደኝነት የመረጡ ሰዎች በሁለተኝነት የሰጡት ድምፅ ነው። ቀጥለን የምንመለከተው ይህንን ቆጠራ ይሆናል።
ከላይ በሚታየው ሠንጠረዥ ላይ “የመጀመርያው ዙር ቆጠራ” በሚለው አምድ ውስጥ የሚገኙት ቁጥሮች መራጩ ህዝብ ለእያንዳንዱ ተወዳዳሪ የሰጠው ድምፅ ብዛት ነው። ለምሳሌ፣ ወሮ አስቴር ጌታቸው በምርጫ ያገኙት ድምፅ ብዛት 29,021 ነው። እዚህ ላይ መታሰብ ያለበት እነዚህ ወሮ አስቴርን የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገው የመረጧቸው 29,021 ሰዎች ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛና ስድስተኛ ምርጫቸው አድርገው የመረጧቸው ተወዳዳሪዎች አሉ። ይህ ተወዳዳሪዎችን በቅደም ተከተል የማስቀመጡ ሂደት ነው የምርጫ ሥርዓቱን “አማራጭ ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት የሚል ስም ያስሰጠው። ወሮ አስቴር በአንደኝነት ከመረጣቸው ህዝብ ያገኙት ድምፅ ብዛት 29,021 ነው። ይህ ድምፅ ብዛቱ የተቀሩት ተወዳዳሪዎች ካገኙት ድምፅ ብዛት ቢበልጥም ወሮ አስቴር በመጀመርያው ዙር ያገኙት ድምፅ ብዛት በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ 40.1 % ብቻ ስለሆነ ለአሸናፊነት አያበቃቸውም።
የመጀመሪያው ዙር ድምፅ ቆጠራ ሲጠናቀቅ ከስድስቱ ተወዳዳሪዎች ዝቅተኛ ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ ከምርጫው ውጭ ይሆናል። በዚህ መሠረት በጠቅላላ ከተሰጠው 72,356 ድምፅ ውስጥ 309 ድምፅ ያገኙት አቶ አቦሴ ሙሊሶ ከምርጫ ውጭ ይሆኑና ለአቶ አቦሴ የተሰጠው አማራጭ ድምፅ ለተቀሩት ተወዳዳሪዎች ይከፋፈላል። አቶ አቦሴን የመጀመሪያ ምርጫቸው አድርገው የመረጧቸው 309 ድምፅ ሰጪዎች ከአቶ አቦሴ በተጨማሪ ሌሎቹ አምስት ተወዳዳሪዎችን ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛ፣ አምስተኛና ስድስተኛ ምርጫቸው አድርገው መርጠዋል። ለምሳሌ፣ ሠንጠረዡ ላይ “አማራጭ ድምፅ አንደኛ ዙር” በሚለው አምድ ውስጥ ከአቶ አመንሲሳ መገርሳ ስም ጎን በሦስተኛው አምድ ውስጥ የሚታየው ቁጥር (+61) የሚያሳየን ከምርጫው የወጡትን አቶ አቦሴን በአንደኝነት ከመረጧቸው 309 ድምፅ ሰጪዎች ውስጥ ስልሳ አንዱ ድምፅ ሰጪ ሁለተኛ ድምፁን የሰጠው ለአቶ አመንሲሳ መሆኑን ነው። ይህ አቶ አመንሲሳ መገርሳ ከአቶ አቦሴ ያገኙት 61 ድምፅ እሳቸው እራሳቸው በመጀመርያው ዙር ካገኙት 13,739 ድምፅ ጋር ተደምሮ ወደ ሁለተኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ ይተላለፋል።
አቶ አለማየሁ መንግስቱ በመጀመሪያው ዙር 26,471 ድምፅ አግኝተዋል፣እሳቸውም ልክ እንደ አቶ አመንሲሳ መገርሳ ተሸንፈው ከምርጫው ከወጡት ከአቶ አቦሴ ሙሊሶ 45 ድምፅ እግኝተዋል። ይህ 45 ድምፅ አቶ አለማየሁ መንግስቱ በመጀመርያው ዙር በቀጥታ ከመራጩ ህዝብ ካገኙት 26,471 ድምፅ ጋር ተደምሮ ወደ ሁለተኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ ይተላለፋል። ይህ ሂደት አምስቱም ተወዳዳሪዎች ከአቶ አቦሴ የሚያገኙት ድምፅ ተደምሮላቸው ድምሩ ወደ ሁለተኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ እስኪተላለፍ ድረስ ይቀጥላል።
ሠንጠረዥ ሰባት ላይ አራተኛው አምድ የሚያሳየው የሁለተኛውን ዙር ድምፅ ቆጠራ ውጤት ነው። አራተኛው አምድ ላይ አምስቱም ተወዳዳሪዎች ያላቸው የድምፅ መጠን ከአቶ አቦሴ ሙሊሶ ባገኙት የድምፅ መጠን ልክ ከፍ ብሏል። ነገር ግን አሁንም ማንም ተወዳዳሪ ከጠቅላላው ድምፅ ከግማሽ በላዩን ስላላገኘ ዝቅተኛ ድምፅ ያለው ተወዳዳሪ ከምርጫው ሂደት ይወጣና የዚህን ከምርጫው የወጣውን ተወዳዳሪ አማራጭ ድምፅ ለተቀሩት ተወዳዳሪዎች እንደየድርሻቸው የማከፋፈሉ ሂደት ሁለት ተወዳዳሪዎች እስኪቀሩ ድረስ ይቀጥልና ከሁለቱ አንዱ 50%+ 1 አግኝቶ ምርጫውን ያሸንፋል።
እስካሁን ባየነው የድምፅ ቆጠራና አማራጭ ድምፅ ማስተላለፍ ሂደት እስከ አራተኛው ዙር ቆጠራ ድረስ ወሮ አስቴር ጌታቸው ምርጫውን የሚያሸንፉ ይመስል ነበር። ደግሞም ብዙ ድምፅ ሰጪ በአንደኝነት የመረጠው ወሮ አስቴርን ነው። አቶ አለማየሁ መንግስቱ አሸናፊ ለመሆን የበቁት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ድምፅ ሰጪ ከወሮ አስቴር ይልቅ እሳቸውን እንደ ሁለተኛ አማራጭ አድርጎ ስለመረጣቸው ነው። ወሮ አስቴርን 29,021 ድምፅ ሰጪ በአንደኝነት መርጧቸዋል፣አቶ መንግስቱን ደሞ 26,471 ድምፅ ሰጪ በአንደኝነት መርጧቸዋል፣ በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት 2,550 ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተሰጠ ድምፅን በተመለከተ አቶ መንግስቱን 9,843 ድምፅ ሰጪ ሁለተኛ ምርጫው አድርጎ መርጧቸዋል፣ወሮ አስቴርን ሁለተኛ ምርጫው አድርጎ የመረጣቸው ድምፅ ሰጪ 5,768 ነው። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት 4075 ነው። ይህ ከፍተኛ ልዩነት ነው አቶ መንግስቱ አለማየሁ ምርጫውን እንዲያሸንፉ የረዳቸው።
በሠንጠረዡ ላይ ሁለተኛው፣ ሦስተኛው፣ አራተኛውና አምስተኛው ድምፅ ቆጠራ ተብሎ የተጠቀሰው በየዙሩ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙ ተወዳዳሪዎች ከምርጫው ሂደት ሲወጡ ለእነሱ የተሰጠው አማራጭ ድምፅ ለተቀሩት ተወዳዳሪዎች ከተላለፈ በኋላ ያለውን ድምፅ ቆጠራ ለማሳየት ተብሎ ነው እንጂ መራጩ ህዝብ በየዙሩ ድምፅ ይሰጣል ማለት አይደለም።
3-ብዙ-ድምፅ (Block-Vote)
ብዙ-ድምፅ/Block Vote የምርጫ ሥርዓትን በብዙሃንነት (Plurality/Majority) የምርጫ ሥርዓት ሥር ካሉት የቅርብ ጓደኞቹ የሚለየው በምርጫ ወረዳው መጠን (District Magnitude) ነው።
ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ከአንድ የምርጫ ወረዳ የሚመረጠው የህዝብ ተወካይ አንድ ብቻ ነው፣ ወይም የምርጫ ወረዳው መጠን አንድ ነው። ብዙ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ግን ከአንድ የምርጫ ወረዳ የሚመረጠው የህዝብ ተወካይ ቁጥር ከአንድ በላይ ነው፣ ድምፅ ሰጪው ህዝብም ድምፁን የሚሰጠው ከአንድ ጊዜ በላይ ነው። ለምሳሌ፣ ሦስት የህዝብ ተወካዮች በሚመረጡበት የምርጫ ጣቢያ ውስጥ አንድ ድምፅ ሰጪ በምርጫ ካርዱ ላይ ከተዘረዘሩት ዕጩ ተወዳዳሪዎች ውስጥ ለሦስቱ ድምጹን መስጠት ይችላል። በ”ብዙ-ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት አንድ ተወዳዳሪ ምርጫውን ለማሸነፍ በጠቅላላ ከተሰጠው ድምፅ ከ50 በመቶ በላይ ማግኘት የለበትም። ለምሳሌ፣ በአንድ 3 ሰዎች በሚመረጡብት የምርጫ ወረዳ ውስጥ ስድስት ተወዳዳሪዎች ቢኖሩ ምርጫውን የሚያሸንፉት ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ የመጀመርያዎቹ ሦስት ተወዳዳሪዎች ናቸው።
4-ፓርቲ ብዙ ድምፅ (Party Block Vote)
ብዙ-ድምፅ የምርጫ ሥርዓትና ፓርቲ-ብዙ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ተመሳሳይ የሆኑ የምርጫ ሥርዓቶች ናቸው። ሆኖም በመካከላቸው ሁለት ጉልህ ልዩነቶች አሉ፣ አንደኛ፣ በ”ብዙ-ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች ሲሆን በ”ፓርቲ ብዙ-ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት ግን ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ነው፣ ሁለተኛ- “ፓርቲ ብዙ- ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ የምርጫ ወረዳው መጠን ከአንድ በላይ ቢሆንም ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለአንድ ፓርቲ ብቻ ነው፣ በ”ብዙ-ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ግን አንድ ድምፅ ሰጪ ድምፁን የሚሰጠው ከምርጫ ጣቢያው በሚመረጠው ተወዳዳሪ መጠን ነው። “ፓርቲ ብዙ-ድምፅ” የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ በአንድም ድምፅ አሸናፊ የሚሆነው ፓርቲ ለምርጫ ወረዳው የተመደበውን የፓርላማ መቀመጫ ሁሉ ይወስዳል ማለት ነው። ለምሳሌ፣ የምርጫ ወረዳው መጠን ሦስት ቢሆን አሸናፊው ፓርቲ ሦስቱንም የፓርላማ መቀመጫዎች ይወስዳል። አሸናፊውን ፓርቲ ወክለው ፓርላማ የሚገቡትን ግለሰቦች የሚመርጡት የፓርቲ መሪዎች ናቸው።
ክፍል ሦስት ሰኞ ሐምሌ 28 ይቀርባል
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






