Homeነፃ አስተያየትየምርጫ ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው? (  ክፍል ሦስት)

የምርጫ ሥርዓት ማለት ምን ማለት ነው? (  ክፍል ሦስት)

Advertisement
World Wide Travel Group

       

                                ክፍል ሦስት

     ኤፍሬም ማዴቦ(emadebo@gmail.com) 

        ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት (Proportional Representation)

ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት መራጩ ህዝብ በምርጫ የሰጠውን ድምፅ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ወደ ፓርላማ ወይም ምክር ቤት መቀመጫነት የሚቀይር ሥርዓት ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ የሚያገኙት ድምፅና ፓርላማ ውስጥ የሚያገኙት መቀመጫ ተመጣጣኝና ተቀራራቢ እንዲሆን የሚያደርግና በጠባዩና በውጤቱ ከብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት እጅግ በጣም የሚለይ የምርጫ ሥርዓት ነው። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ልክ እንደ ብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ጥቃቅን ልዩነት ያላቸውን ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶችን በውስጡ ያቀፈ የምርጫ ሥርዓት ነው። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በክፍል ሁለት በዝርዝር የተመለከትናቸው የብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች ትኩረት፣ ለመረጠው ህዝብ ተጠያቂ የሆነና የተረጋጋ መንግሥት እንዲኖር ማድረግ ሲሆን ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር የምንመለከተው ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ደግሞ በይበልጥ የሚያተኩረው ውክልናን ሚዛናዊ በማድረግ ላይ ነው። የተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተቀዳሚ ግብ አንድ ፓርቲ ከመረጠው ህዝብ ያገኘውን ድምፅ ተመጣጣኝ በሆነ መልኩ ወደ ህግ አውጪው አካል፣ ምክር ቤት ወይም ፓርላማ መቀመጫ መቀየር ነው። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ተግባራዊ የሚሆነው ከአንድ በላይ የህዝብ ተወካዮች በሚመረጡበት የምርጫ ወረዳዎች (Multi-Member Dtrictrict) ባለባቸው አገሮች ውስጥ ነው።

ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ሲቀረጽም ሆነ በሥራ ላይ ሲውል ከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግበት የሚገባ የምርጫ ሥርዓት ነው። በዚህ ጽሁፍ ውስጥ በተደጋጋሚ እንደተገለጸው እያንዳንዱ የምርጫ ሥርዓት የራሱ የሆኑ ጠንካራና ደካማ ጎኖች አሉት። ይህ የሚያሳየን ሁሉንም የፖለቲካ ተዋናይ የሚያስደስት የምርጫ ሥርዓት እንደሌለ ነው። ስለዚህ አንድን የምርጫ ሥርዓት ከሌሎቹ የምርጫ ሥርዓቶች የተሻለ ነው ብለን ስንመርጥ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ለአንድ አገር የሚመረጠው የምርጫ ሥርዓት ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ከሆነ ደግሞ መወሰድ ያለበት ጥንቃቄ እጥፍ ድርብ መሆን አለበት። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት የተሻለ የምርጫ ሥርዓት ነው ተብሎ ሲመረጥ የምርጫ ሥርዓቱ ይዟቸው የሚመጣ ሌሎች ብዙ በቅድሚያ መታየትና በጥሞና መመርመር ያለባቸው ዕሴቶች አሉ። እነዚህ ዕሴቶች በመዋቅራዊ አሰራራቸውና በስነልቦና ይዘታቸው የፖለቲካ ተዋንያኑን አስተሳሰብ የመቀየር ኃይል አላቸው። በእርግጥ እነዚህ ጥቃቅን ዕሴቶች በየግላቸው በፓለቲካ ተዋንያኑ ላይና ባጠቃላይ በፖለቲካ ሥርዓቱ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ትናንሽ ለውጦች ሲጠራቀሙ በምርጫው ውጤት ቅቡልነት ላይ፣ በፓርላማው ጥንቅርና በመንግሥት ምሥረታ ሂደት ላይ የሚኖራቸው ተፅዕኖ እጅግ በጣም ከፍተኛ ነው።

በመርህ ደረጃ የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት ልዩ መታወቂያ፣ አንድ የምርጫ ወረዳ ፓርላማ ውስጥ የሚኖረው ውክልና መራጩ ህዝብ ከሰጠው ድምፅ ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት የሚለው መርሁ ነው። ሆኖም በተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ሥር የተለያዩ ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶች ስላሉ ይህ መርህ በተግባር ሲተረጎም እንደየንዑስ የምርጫ ሥርዓቱ ይለያያል። አንዳንድ የተመጣጣኝ ውክልና ምርጫ ሥርዓት አቀንቃኞች ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ፓርቲዎች በምርጫ ያገኙት የድምፅ መቶኛ በቀጥታ ወደ ፓርላማ መቀመጫ መቶኛ መቀየር አለበት የሚል ጠንካራ አቋም አላቸው። እንደነሱ አባባል አንድ ፓርቲ 40% ድምፅ ካገኘ ፓርላማ ውስጥም 40% መቀመጫ ማግኘት አለበት። ይህ አሠራር ሲያዩት ቀላል ይምሰል እንጂ ችግር አለበት። ለምሳሌ፣ አንድ ፓርቲ 25.6% ድምፅ ቢያገኝ ፓርላማ ውስጥ0.6% መቀመጫ ስለሌለ ያገኘውን ድምፅ እንዳለ ወደ ፓርላማ መቀመጫ መቀየር አዳጋች ይሆናል። ተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት እንደነዚህ ዓይነት ችግሮችን የሚያቃልሉና እጅግ በጣም በረቀቀ ቀመር በምርጫ የተገኘን ድምፅ ወደ ፓርላማ መቀመጫነት የሚቀይሩ ሁለት ንዑሳን የምርጫ ሥርዓቶች አሉት። አንደኛው የፓርቲ-ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ሲሆን ሁለተኛው ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ (Singel Transferable Vote/STV) ናቸው።

1-ፓርቲ-ዝርዝር (Party List) የምርጫ ሥርዓት

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በፓርቲ-ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ውስጥ መራጩ ህዝብ ድምፁን የሚሰጠው ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች ሳይሆን ለፓርቲዎች ነው። በምርጫ ካርዱ ላይ የሚጻፈውም የፓርቲ ስምና ፓርቲው ያቀረባቸው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት “ፓርቲ-ዝርዝር” የሚባል ስም የተሰጠውም በምርጫ ካርዱ ላይ የሚቀርበው የተወዳዳሪ ፓርቲዎች ስምና የየፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ስለሆነ ነው። ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በምርጫ ካርዱ ላይ የተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ቢኖርም በተለይ “ዝግ- ፓርቲ” ዝርዝር ባለባቸው አገሮች ውስጥ መራጩ ህዝብ ምርጫ ካርዱ ላይ ለቀረቡለት ተወዳዳሪዎች በቀጥታ ድምፁን መስጠት አይችልም፣ ደግሞም ፓርቲዎቹ ምርጫውን ሲያሸንፉ ፓርቲውን ወክለው ወደ ፓርላማው የሚገቡ ተወካዮችን ማንነት በመወሰኑ ሂደት ላይ ከፍተኛውን ሚና የሚጫወቱት የፓርቲ መሪዎች ናቸው። የፓርቲ-ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ሦስት የተለያዩ የድምፅ አሰጣጥ ዓይነቶች አሉት።

ሀ) “ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር (Closed Party List)

“ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ከተመጣጣኝ ውክልና የምርጫ ሥርዓት ዝርያዎች ውስጥ በጣም ቀላሉና በዓለም ላይ ብዙ አገሮች የሚጠቀሙበት የድምፅ አሰጣጥ ዓይነት ነው። በ”ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር አሠራር መራጩ ህዝብ በድምፅ መስጫ ካርዱ ላይ ከቀረቡለት የተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ውስጥ ይወክለኛል ብሎ የሚተማመንበትን ተወዳዳሪ መርጦ ድምፅ መስጠት አይችልም፣ ወይም ፓርቲው ያቀረበውን የዕጩ ተወዳዳሪዎች ስም ዝርዝር ቅደም ተከተል መለወጥ አይችልም። ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ነው። በ “ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር የምርጫ ካርድ ላይ የሚታየው ስም ዝርዝር ቅድም ተከተል በዘፈቀደ ወይም ባጋጣሚ የተቀመጠ ቅደም ተከተል አይደለም። የፓርቲ መሪዎች ዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ያላቸውን የመሪነት ችሎታ፣ በህብረተሰቡ ውስጥ ያላቸውን እውቅና፣ ተወዳጅነትና ተሰሚነት እያዩና ባጠቃላይ የትኛው ዕጩ ተወዳዳሪ ነው የመመረጥ ዕድሉ  የሰፋው  እያሉ  ነው  ቅደም  ተከተሉን  የሚሰሩት።  ለምሳሌ፣  ስሙ  በቁጥር  አንድ ላይ የተቀመጠ ዕጩ ተወዳዳሪ ከላይ በተጠቀሱት ዕሴቶች ከተቀሩት ተወዳዳሪዎች የተሻለ ነው ማለት ነው። ይህ አባባል ሁልግዜ ትክክል ላይሆን ይችላል፣ አንዳንዴ በምርጫ ካርዱ ላይ ስማቸው በአንደኝነት የሚቀመጠው ዕጩ ተወዳዳሪዎች ለፓርቲ መሪዎች ባላቸው ታማኝነት ሊሆን ይችላል።

አንድ ድምፅ ሰጪ ያለው ድምፅ አንድ ብቻ ሲሆን ድምፁን የሚሰጠው ፓርላማ ውስጥ እንዲወክለው ለሚፈልገው ፓርቲ ነው። አንድ ፓርቲ አንድ የፓርላማ መቀመጫ ብቻ ካሸነፈ ፓርቲውን ወክሎ ፓርላማ የሚገባው ስሙ በተራ ቁጥር አንድ ቦታ የተቀመጠው ተወዳዳሪ ይሆናል ማለት ነው።ዝግ ፓርቲ ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት የሚሠራው የምርጫ ወረዳ መጠናቸው ሁለትና ከሁለት በላይ በሆኑ የምርጫ ጣቢያዎች ውስጥ ስለሆነ እንደየሁኔታው የምርጫ ወረዳው በአንድ፣ በሁለት ወይም በሦስት ፓርቲዎች ሊወከል ይችላል። ለምሳሌ፣ ከታች በሚታየው የዝግ-ፓርቲ ዝርዝር ምርጫ ካርድ ባለበት የምርጫ ወረዳ ውስጥ እናት ፓርቲ ብቻውን ምርጫውን ቢያሸንፍና የምርጫ ወረዳው መጠን 3 ከሆነ፣ እናት ፓርቲ ለወረዳው የተመደበውን ሦስት የፓርላማ መቀመጫ በሙሉ ይወስዳል። በምርጫ ካርዱ ላይ በሚታየው የተወዳዳሪዎች ቅደም ተከተል መሠረት እናት ፓርቲን ወክለው ፓርላማ የሚገቡት ስማቸው ከአንድ እስከ ሦስት የተቀመጠው አቶ ከበደ አደራ፣አቶ ሸምሱ በረደድና ወ/ሮ አስቴር ገመቹ ናቸው።

- Advertisement -

“ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር ምርጫ ካርድ

የምርጫ መመሪያድምፅ መስጠት የሚችሉት ለአንድ ፓርቲ ብቻ ነውመምረጥ ከሚፈልጉት ፓርቲ ስም በታች ባለው ሳጥን ዉስጥ ምልክት ያድርጉ

ለ)ክፍት ፓርቲ ዝርዝር (Open Party List)

        እናት ፓርቲ    ህብር ኢትዮጵያ      ፓርቲ  ኦሮሞ ፌዴራሊስት    ኮንግሬስ ፓርቲ  ባልደራስ ፓርቲ




ከበደ አደራ    አለሚቱ ገመዳ  ሠላማዊት አሽኔ  መሰረት አንዱአለም
ሸምሱ በረደድ    ሃሰን መሀመድ  በሪሶ አያኖ  ኡጁሉ ኦሞድ
አስቴር ገመቹ    ኤርበሌ አቡቶ  አሊጋዝ ሃንፍሬ  ሃብታሙ ወዳጆ
መታሰቢያ ተክሌ    ትግሮ ቲቦ  ገብራይ ሀጎስ  ጳውሎስ ጃግሶ

በክፍት ፓርቲ ዝርዝር ድምፅ አሰጣጥ ዘዴ መራጩ ህብረተሰብ ያሰኘውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን፣ ፓርቲው ካቀረባቸው የተወዳዳሪዎች ዝርዝር ውስጥ የሚፈልገውን ተወዳዳሪ መርጦ ድምፅ መስጠት ይችላል፣ ወይም እያንዳንዱ ድምፅ ሰጪ ፓርቲው ያቀረበውን የስም ዝርዝር ቅደም ተከተል መለወጥ ይችላል። ለምሳሌ፣ፓርቲው አራተኛ ተራ ቁጥር ላይ ያስቀመጠውን ዕጩ ተወዳዳሪ ድምፅ ሰጪው አንደኛ አድርጎት ድምፅ መስጠት ይችላል። ይህ ማለት ደግሞ፣ በክፍት ፓርቲ ዝርዝር አሠራር መራጩን ህዝብ ወክሎ ፓርላማ የሚገባው ግለሰብ ማን መሆኑን የሚወስነው አሸናፊው ፓርቲ ሳይሆን መራጩ ህዝብ ነው ማለት ነው።

        እናት ፓርቲ    ህብር ኢትዮጵያ      ፓርቲ  ኦሮሞ ፌዴራሊስት    ኮንግሬስ ፓርቲ  ባልደራስ ፓርቲ




ከበደ አደራ አለሚቱ ገመዳ ሠላማዊት አሽኔመሰረት አለሙ
ሸምሱ በረደድሃሰን መሀመድበሪሶ አያኖኡጁሉ ኦሞድ
አስቴር ገመቹኤርበሌ አቡቶአሊጋዝ ሃንፍሬሃብታሙ ወዳጆ
መታሰቢያ ተክሌትግሮ ቲቦገብራይ ሀጎስጳውሎስ ጃግሶ
የምርጫ መመሪያድምፅ መስጠት የሚችሉት ለአንድ ፓርቲ ወይም ለአንድ ዕጩ ተወዳዳሪ ነውድምጾን ለፓርቲ ለመስጠት ከፓርቲው ስም በታች ባለው ሳጥን ዉስጥ ምልክት ያድርጉድምጾን ለሚፈልጉት ዕጩ ተወዳዳሪ ለመስጠት ከዕጩ ተወዳዳሪው ስም ጎን ምልክት ያድርጉ

ክፍት ፓርቲ ዝርዝር የምርጫ ካርድ

2-ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ (Single Transferable Vote)

ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ ከአንድ በላይ የምክር ቤት ተወካይ በሚመረጥባቸው የምርጫ ወረዳዎች (Multi Member District) ውስጥ መራጩ ህብረተሰብ ተወዳዳሪዎችን እንደየፍላጎቱ በቅደም ተከተል እያስቀመጠ የሚመርጥበት የምርጫ ሥርዓት ነው። ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት በሥራ ላይ በዋለባቸው አገሮች ውስጥ መራጩ ህዝብ ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ሳይሆን ፓርቲያቸውን ወክለው ለሚወዳደሩ ተወዳዳሪዎች ነው። ለምሳሌ፣ ምርጫ ካርዱ ላይ አራት ፓርቲዎችን የሚወክሉ አራት ተወዳዳሪዎች ካሉ አንድ ድምፅ ሰጪ አንደኛ፣ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ እና አራተኛ ምርጫዬ እያለ አራቱን ተወዳዳሪዎች በቅደም ተከተል ከአንድ እስከ አራት ያስቀምጣቸዋል። የነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ዋናው ግብ የምርጫው ውጤት በይበልጥ ሚዛናዊ እንዲሆን ማድረግ ነው። ይህ የምርጫ ሥርዓት ‹‹ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ›› የሚለውን መጠሪያ ስም ያገኘው ከድምፅ ቆጠራውና ከፓርላማ መቀመጫ ድልደላ ሂደት ነው። ይህንን ሂደት በሚቀጥለው ክፍል እንመለከታለን።

ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ መራጩ ህዝብ ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ሳይሆን ለግለሰብ ተወዳዳሪዎች ነው። ይህ ማለት ደግሞ ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች ውስጥ ህዝብን ወክሎ ፓርላማ ውስጥ መቀመጫ የሚይዘውን ግለሰብ የሚወስኑት የፓርቲ መሪዎቸ ሳይሆኑ ድምፅ ሰጪው ነው ማለት ነው። ለምሳሌ፣ “ዝግ-ፓርቲ” ዝርዝር የምርጫ ሥርዓት ባለባቸው አገሮች ውስጥ ድምፅ ሰጪው ድምፁን የሚሰጠው ለፓርቲዎች ብቻ በመሆኑ ምርጫውን አሸንፎ የፓርላማ መቀመጫ የሚይዘው ሰው ማንነት የሚወሰነው በፓርቲ መሪዎች ነው። መራጩ ህዝብ ፓርላማ ውስጥ የሚወክሉትን ግለሰቦች ማንነት ይወስናል ወይም አይወስንም ሲባል ጉዳዩ እንደ ቀላል ነገር መታየት የለበትም። ምክንያቱም የአንድ አገር የዲሞክራሲ ጥልቀትና ስፋት ከሚለካባቸው መለኪያዎች ውስጥ አንዱ በድምፅ በድምፅ ሰጪው ህዝብና በተወካዮቹ መካከል ያለው ግንኙነት ነው። የዚህ ግንኙነት ስፋትና ጥልቀት ደግሞ መራጩን ህዝብ ፓርላማ ውስጥ የሚወክለውን ግለሰብ ማንነት ፓርቲዎች ሲወስኑና መራጩ ህዝብ እራሱ ሲወስን ልዩነቱ ትልቅ ነው። ከዚህ ቀጥሎ ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ በሥራ ላይ ሲውል ምን እንደሚመስል በዝርዝር እንመለከታለን።

ነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ካርድ

አርማ(ይህ ግዴታ አይደለም)የዕጩ ተወዳዳሪው ስምና የሚወክለው              ፓርቲየዕጩ ተወዳዳሪው ፎቶ(ይህ ግዴታ አይደለም)በምርጫ ያገኘው ድምፅ
አርማአለባቸው ደጄ -እናት ፓርቲ      ፎቶ  3      
አርማእምሻው ኪዳኔ- ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲ      ፎቶ  2   
አርማቶሎሳ ቆቱ- ኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ      ፎቶ  1    
አርማአየለ ማሞ- ኢህአፓ      ፎቶ  5
አርማይመሹላ ታከለ- ባልደራስ       ፎቶ  4

ይህ ከላይ የሚታየው የምርጫ ካርድ እያንዳንዱ መራጭ ወደ ድምፅ መስጫ ጣቢያው ሲሄድ የሚሰጠው ካርድ ነው። የምርጫ ካርዱ የፓርቲ ዓርማ፣የፓርቲ ስም፣ ፓርቲውን ወክሎ የሚወዳዳረው ሰው ስምና አድራሻ አለው። ይህንን የምርጫ ካርድ የያዘው መራጭ የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ፓርቲውን አቶ ቶሎሳ ቆቱን በአንደኝነት የመረጠ ሲሆን ከአቶ ቶሎሳ ቀጥሎ በቅደም ተከተል በሁለተኛነት፣ በሦስተኛነት፣ በአራተኛነትና በአምስተኛነት ለሌሎች ተወዳዳሪዎች ድምጹን ሰጥቷል። 

ከላይ ከፍ ሲል በብዙሃንነት የምርጫ ሥርዓት ሥር ያየነው “አማራጭ ድምፅ” የምርጫ ሥርዓትና አሁን የምናየው የ”ነጠላ ተሸጋጋሪ” ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድምፅ አሰጣጥ ይመሳሰላል፣ደሞም በሁለቱም የምርጫ ሥርዓቶች ድምፅ አሰጣጥና ቆጠራው ላይ ውስብስብ ናቸው፣የ”ነጠላ ተሸጋጋሪ” ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድምፅ ቆጠራ በጣም ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ የኮምፒተር እርዳታ ይፈልጋል። በነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት አሠራር ውስጥ እጅግ በጣም ወሳኝና አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ውስጥ አንዱ ኮታው ነው። ነጠላ ተሸጋጋሪ ደምፅ የምርጫ ሥርዓት ከሚጠቀምባቸው የኮታ ዓይነቶች ውስጥ አንዱ ‹‹ድሩፕ›› ኮታ (Droop Quota) በመባል ይታወቃል፣ ኮታው ይህንን ስያሜ ያገኘው ኮታውን ለመጀመርያ ጊዜ ከቀመረው እንግሊዛዊ ሄንሪ ድሩፕ ነው።

          ድሩፕ ኮታ = [ጠቅላላ ድምፅ / (የመቀመጫ ብዛት + 1)] + 1

በ‹‹ድሩፕ›› ኮታ አሠራር አንድ ተወዳዳሪ በመጀመርያው ዙር ምርጫ ከህዝብ ያገኘው ድምፅ ከኮታው ጋር እኩል ከሆነ ወይም ከበለጠ፣ የፓርላማ መቀመጫ ያሸንፍና የሱ ስም ከፓርላማ መቀመጪያ ሽሚያ ውጭ ይሆናል። ከኮታው በላይ ያገኘው ድምጽ ካለ ግን በቀጣይ ዙር ለሚወዳደሩ እጩዎች ይተላለፋል፣ ይህ የሚተላለፈው ድምጽ ሰጪዎቹ በሁለተኛ ደረጃ ላስቀመጧቸው የሁለተኛ ዙር ተወዳዳሪዎች ነው። የ‹‹ድሩፕ›› ኮታን አሠራር ለመረዳት የሚከተለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ።

ወሮ አይሻ ዘይኑ-ህብር ኢትዮጵያ ፓርቲአቶ ብስራት ድልነሳ-እናት ፓርቲአቶ አሊ ሃቢብ- ነጻነትና እኩልነትወሮ ሊሊ አበባው- እናት ፓርቲአቶ አቡሌ ነጋ-ባልደራስ
  ውጤት
1ኛ ዙር      20       18  46ተመረጠ      10      6አሸናፊ- አቶ አሊ ሃቢብ



2ኛ ዙር
  

   25
    

   22
   

   16



   10
በ2ኛው ዙር አሸናፊ የለም፣ዝቅተኛ ድምፅ ያገኘው ተወዳዳሪ ከውድድሩ ይወጣል(አቶ አቡሌ ነጋ)
3ኛ ዙር  26 ተመረጠ    25    21 ከውድድር  ውጭአሸናፊ- ወሮ አይሻ ዘይኑ 
4ኛ ዙር  –    27  ተመረጠአሸናፊ- አቶ ብስራት ድልነሳ 

ጠቅላላ ድምፅ= 100

የወረዳው የፓርላማ መቀመጫ ብዛት = 3

ኮታ (ድሩፕ ኮታ) = [ጠቅላላ ድምፅ/ (መቀመጫ + 1)] + 1 = 100 / (3 + 1)] + 1 = 26

በሠንጠረዡ ላይ ድምፅ አሸናፊውን ለመለየት የተጠቀምነው ኮታ 26 ሲሆን የዚህን ኮታ ያህል ወይም የበለጠ ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ በመጀመርያው ዙር የፓርላማ መቀመጫ ያሸንፋል። ስለሆነም የነፃነትና እኩልነት ፓርቲው አቶ አሊ ሃቢብ  46 ድምፅ ስላገኙ የመጀመሪያውን የፓርላማ መቀመጫ ያገኙና ከመቀመጫ ሽሚያው ይወጣሉ። ሌላ የኮታውን ያክል ድምፅ ያገኘ ተወዳዳሪ ስለሌለ ቀሪዎቹን ሁለት የፓርላማ ወንበሮች ለማከፋፈል ነጠላ ድምፅ የማሸጋገሩ ሂደት ይጀምራል።

አንደኛ ዙር ውጤት

አቶ አሊ ሃቢብ ከኮታው በላይ ድምፅ ስላገኙ አንድ የፓርላማ መቀመጫ ያገኛሉ፣በአንደኛው ዙር የፓርላማ መቀመጫ ያሸነፉት አቶ አሊ ሃቢብ ብቻ ናቸው። አቶ አሊ ከኮታው በላይ ያገኙት ድምፅ 20 ሲሆን ይህ ትርፍ ድምፅ ለዚህ ጉዳይ በተቀመረው ቀመር እየተቀመረ ለቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች ይተላለፋል።

ሁለተኛ ዙር ውጤት

አቶ አሊን በአንደኝነት የመረጧቸው 46 ድምፅ ሰጪዎች ናቸው፣ እነዚህ ድምፅ ሰጪዎች አቶ አሊን ሲመርጡ በሁለተኝነት የመረጧቸው ተወዳዳሪዎች አሉ፣ይህ ድምፅ ለ2ኛ ደረጃ የተሰጠ ድምፅ ነው፣በዚህ መሰረት የአቶ አሊ ሃቢብ ትርፍ ድምፅ ለቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች የሚከፋፈልበት ቀመር ይህንን ይመስላል- 

(ለ2ኛ ደረጃ የተሰጠ ድምፅ÷ለአቶ አሊ የተሰጠው ድምፅ) * ትርፍ ድምፅ

አቶ አሊን 46 ሰዎች በ1ኛነት መርጠዋቸዋል፣ ከእነዚህ ሰዎች ውስጥ ወሮ አይሻን (12 ሰዎች)፣  አቶ ብስራትን  (10  ሰዎች)፣  ወሮ ሊሊን  (14  ሰዎች)፡  አቶ  አቡሌን (10  ሰዎች) በሁለተኝነት ደረጃ መርጠዋቸዋል 

ለአቶ አሊ ሃቢብ የተሰጠው ድምፅ = 46

 ትርፍ ድምፅ = (ድምፅ- ኮታ)= (46-26) =20

በቀመሩ መሠረት . . . . . . .

ለወሮ አይሻ የተላለፈ ድምፅ =(12/46)*20 = 5 

ለአቶ ብስራት የተላለፈ ድምፅ = (10/46)*20 = 4 

ለወሮ ሊሊ የተላለፈ ድምፅ = (14/46)*20 = 6 

ለአቶ አቡሌ የተላለፈ ድምፅ = (10/46)*20 = 4

ከአቶ አሊ ሃቢብ የተላለፈው ትርፍ ድምፅ ለቀሪዎቹ 4 ተወዳዳሪዎች ተከፋፍሎና ከህዝብ በቀጥታ ካገኙት ድምፅ ጋር ተደምሮ የሁሉም ተወዳዳሪዎች ድምፅ ከኮታው በታች ስለሆነ በ2ኛው ዙር የፓርላማ መቀመጫ የሚያገኝ ተወዳዳሪ የለም። ስለዚህ በሁለተኛው ዙር ቆጠራ ዝቅተኛ ድምፅ ያገኙት ተወዳዳሪ (አቶ አቡሌ) ከውድድሩ ይወጡና ሦስተኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ ይቀጥላል (ከላይ ያለውን ሠንጠረዥ ይመልከቱ)።

ሦስተኛ ዙር ውጤት

በ3ኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ ከውድድር የወጡት የአቶ አቡሌ ድምፅ ከላይ በተጠቀምነው ቀመር መሠረት ለቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች ይከፋፈላል። ሆኖም የአቶ አቡሌ ድምፅ ከኮታ በታች ስለሆነና ትርፍ ድምፅ ስለሌለ ቀመሩን መጠቀም አንችልም። ስለዚህ ለሌሎቹ ተወዳዳሪዎች የሚተላለፈውን ድምፅ የምናገኘው አቶ አቡሌን በአንደኝነት የመረጡ ሰዎች ለተቀሩት ተወዳዳሪዎች በሁለተኛ ደረጃ የሰጡትን ድምፅ በመቁጠር ነው። በዚህ መሠረት ወሮ አይሻ አንድ አንድ ድምፅ፣አቶ ብስራት ሦስት ድምፅ፣ ወሮ ሊሊ ደግሞ ሁለት ድምፅ ያገኛሉ። ወሮ አይሻ ከአቶ አቡሌ ያገኙት አንድ ድምፅ በሁለተኛው ዙር ካላቸው ድምፅ ጋር ሲደመር 26 ይሆናል። ይህ ቁጥር ከኮታው ጋር እኩል ስለሆነ ወሮ አይሻ ሁለተኛውን የፓርላማ መቀመጫ ያገኛሉ- በ3ኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ የወሮ አይሻ ድምፅ ከኮታው ጋር እኩል ስለሆነ ለቀሪዎቹ ተወዳዳሪዎች የሚተላለፍ ትርፍ ድምፅ አይኖርም። 

አራተኛ ዙር ውጤት

3ኛው ዙር ድምፅ ቆጠራ ሲጠናቀቅ ሳይከፋፈል የቀረው የፓርላማ ወንበር አንድ ብቻ ሲሆን የፓርላማ ወንበር ሳያገኙ ውድድሩ ውስጥ የሚገኙት ተወዳዳሪዎች ሁለት ናቸው። ስለዚህ ከእነዚህ ሁለት ተወዳዳሪዎች ውስጥ ዝቅተኛ ድምፅ ያለው ተወዳዳሪ ከፓርላማ ወንበር ሽሚያ ይወጣና የዚህ ተወዳዳሪ ድምፅ ለሚቀረው ተወዳዳሪ ይተላለፋል። በዚህ መሠረት ወሮ ሊሊ አበባው ከውድድሩ ይወጡና የሳቸው ድምፅ በውድድሩ ውስጥ ለቀሩት የመጨረሻው ተወዳዳሪ ይተላለፋል። ወሮ ሊሊን በአንደኝነት ከመረጡ 10 ድምፅ ሰጪዎች ውስጥ 2ቱ አቶ ብስራትን፣3ቱ አቶ አሊን፣ 4ቱ አቶ አቡሌን፣አንድ ሰው  ደሞ ወሮ አይሻን በሁለተኝነት መርጠዋል። ሆኖም አቶ አሊ በ1ኛው፣ወሮ አይሻ ደሞ በ2ኛው ዙር ስለተመረጡና አቶ አቡሌ ደግሞ በ2ኛው ዙር ከውድድር የወጡ ስለሆነ አራተኛው ዙር ላይ የምንቆጥረው ለአቶ ብስራት የተሰጠውን ድምፅ ብቻ ነው። አቶ ብስራት ድልነሳ ከወሮ ሊሊ ያገኙት 2 ድምጽ 3ኛው ዙር ላይ ካላቸው 2 ድምጽ ጋር ሲደመር ውጤቱ (27) ከኮታው በላይ ስለሚሆን አቶ ብስራት የመጨረሻውን የፓርላማ መቀመጫ ያሸንፋሉ።

ከላይ በሠንጠረዡ ላይ የተመለከትነው ምሳሌ ቀላልና አንባቢው በቀላሉ እንዲረዳው ተደርጎ የተሰራ ነው። የነጠላ ተሸጋጋሪ ድምፅ የምርጫ ሥርዓት ድምፅ አሰጣጥ በተለይ ድምፅ ቆጠራው በመሣርያ ካልታገዘ በቀር ከባድና ውስብስበ ነው። በአንድ ዙር፣ ሁለት ተወዳዳሪዎች ኮታውን አሟልተውና የፓርላማ መቀመጫ አሸንፈው ከውድድር ቢወጡ ነጠላ ድምፅ የማሸጋገሩ ሂደት በጣም ውስብስብ ይሆናል። በክፍል አራት ላይ ድብልቅ የምርጫ ሥርዓትንና እስካሁን ያየናቸውን የምርጫ ሥርዓቶች ጠንካራና ደካማ ጎን እንመለከታለን።

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡

ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ  

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News