
መርሻ
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ – መንግሥት የዘጋውን የሞጣ-ባህር ዳር መንገድ ለማስከፈት በሚል የአማራ ፋኖ በጎጃም የጣለውን ክልከላ ተከትሎ፣ የአዲስ አበባ-ባህር ዳር ዋና መንገድ መዘጋቱ ተሰምቷል፡፡
የፋኖ ኃይሎች መንግሥት የዘጋውን መንገድ ለማስከፈት በጣሉት ክልከላ የአዲስ አበባ ጎጃም መስመር የተዘጋው ከትላንት ነሀሴ 1/2017 ዓ.ምጀምሮ ነው፡፡ የፋኖ ኃይሎች የጣሉትን የተሸከርካሪ እንቅቅቃሴ ገደብ ተከትሎ፣ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃምም ይሁን ከጎጃም ወደ አዲስ አበባ በሁለቱም አቅጣጫ ተሸከርካሪዎች ባሉበት ቆመዋል ተብሏል፡፡
በጎጃም ቀጠና የሚንቀሳቀስ የፋኖ ክንፍ ክልከላውን የጣለው በመንግሥት የተዘጋውን መንገድ ለማስከፈት መሆኑን አስታውቋል፡፡ መንግሥት ከሐምሌ 5/2017 ዓ.ም ጀምሮ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከሞጣ ከተማ ወደ ባህር ዳር የሚወስደው ዋናው መንገድ መዝጋቱን ተከትሎ እንድከፈት የፋኖ ኃይሎች ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሲሰጡ ነበር፡፡
የመንገዱ መዘጋት በማኅበረሰቡ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተከትሎ፣ የአማራ ፋኖ በጎጃም የመንገዱን መዘጋት በመቃወም እንዲከፈት መጠየቁ ይታወሳል፡፡ መንግሥት መንገዱን እንዲከፍት የፋኖ ኃይሎች የሰጡትን ማስጠንቀቂያ አልመቀበሉን ተከትሎ ነው አዲስ አበባ-ጎጃም መስመር የተዘጋው፡፡
መንገዱ ከአንቡላንስ በስተቀር ለማንኛውም አይነት ተሽከርካሪ ዝግ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በአማራ እና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በርካታ ተሸካሪዎች ለመቆም ተገደዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃም በመግባት ላይ የነበሩ የከባድ ጭነት ተሽከርካሪዎች ኦሮሚያ አዋሳኝ ላይ ቆመዋል፡፡ እንዲሁም ከተለያዩ የጎጃም አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ የነበሩ ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎችም በተመሳሳይ አዋሳኝ ቦታዎች ላይ ቆመዋል ተብሏል፡፡
መንግሥት የፋኖን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚል መንገድ መዝጋቱን ተከትሎ፣ ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ እንግልት መጋለጡ ሲገለጽ ነበር፡፡ በተለይ ከባህር ዳር እሰከ ሞጣ ያለው መስመር የፋኖ መንቀሳቀሻ ቀጠና ነው በሚል መንግሥት ከምሌ 5/2017 ዓ.ም ጀምሮ ዘግቶት ቆይቷል፡፡
በፋኖ የተጣለው የተሸከርካሪዎች እንቅስቃሴ መንግሥት የዘጋው መስመር እስከሚከፈት ድረስ ሊቀጥል ይችላል ተብሏል፡፡ መንገድ በተዘጋባቸው አካባቢዎች ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ ችግር መጋለጡን የሚያመለክቱ መረጃዎች በተደጋጋሚ ሲወጡ ነበር፡፡
__
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






