
በኢዮብ ትኩዬ
የክረምቱ ዝናብ በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ሀብሩ ወረዳ በሚገኘው ጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ከ20 በላይ ተፈናቃዮችን ሲያቆስል፣ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ደግሞ ወደ 10 ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎችን ማፈናቀሉ ተሰምቷል፡፡
የዝናብ እጥረት አጋጥሞት እንደነበር ከሳምንት በፊት በዞኑ መንግስት ባለስልጣናት እና በሃይማት አባቶች ሲለፈፍለት በነበረው ሰሜን ወሎ ዞን ሰሞኑን አውሎ ነፋስ ቀላቅሎ በጣለው ከባድ ዝናብ በጃራ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በመፈራረሱ 23 ተፈናቃዮችን መቁሰላቸውን ተፈናቃዮቹ ተናግረዋል።
ከ360 በላይ ተፈናቃዮች መጠለያ አልባ መሆናቸውን፣ በዚህም ከ60 በላይ የአባወራ መጠለያዎች በአውሎ ነፋሱ ተነቃቅለው መፍረሳቸውን ቦርከና ከተፈናቃዮቹ ገለጻና ከቦታው ከወጡ የምስል ማስረጃዎች የተረዳ ሲሆን፣ የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ በአደጋው የ61 ተፈናቃይ አባወራዎች ቤት በመውደሙ ለጥገና እንየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተነግሯል፡፡
በጃራ መጠለያ ጣቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ፣ ቤት ንብረት የሌላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች የሚገኙ ሲሆን፣ ተፈጥሯዊ አደጋው በሰዎች ላይ ካደረሰው ጉዳት ባደሻገር የተፈናቃዮችን የእለት ምግብና ማብሰያ ማውደሙን የዞኑ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መምሪያም ተናግሯል፡፡
በደረሰው ተፈጥሯዊ አደጋ ከሚደረገው ባሻገር ለተፈያቃዮቹ በዘላቂነት ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው መምሪያው የገለጸ ሲሆን፣ በዚህም “መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም በተለይ ከጸጥታው ችግር ጋር ተያይዞ ወደየአካባቢው የመግባት ፍላጎትም የላቸውም፤ እንዳዶቹም ጭራሹን ከሀገርም የመውጣት ሁኔታ አለ” ሲል የድጋፉን አሳሳቢነት ከወዲሁ አስረድቷል።
በተያያዘ ዜና በክረምቱ ሳቢያ የአዋሽ ወንዝ መሙላቱን ተከትሎ ወደ 10 ሺሕ የሚጠጉ የአካባቢው ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን፣ በኦሮሚያ ክልል የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መግለጹ ተሰምቷል።
እንደ ጽሕፈት ቤቱ ገለጻ ከሆነ፣ እስከ ሐምሌ 30 ቀን 2017 ዓ/ም ድረስ ባለው መረጃ ብቻ ከ9 ሺሕ በላይ ነዋሪዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው በትምህርት ቤቶች የተጠሉ ሲሆን፣ የጎርፉ መጠን አሁንም በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ነው።
እንዲሁም በቢሾፍቱ ከተማ ከቀናት በፊት በጣለው አውሎ ነፋስ የቀላቀለ ዝናብ ሳቢያ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ፣ በመሠረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ባለስልጣናት መናገራቸው ይታወሳል።
በኢትዮጵያ ዋናው ክረምት የሚገባው ከሰኔ መጨረሻ ጀምሮ ሲሆን፣ በአንዳንድ አካባቢዎች ዘግይቶ በመግባቱ ድርቅ እንዳያስከትል ተሰግቷል፤ በአንጻሩ ደግሞ ክረምቱ በገባባቸው አካባቢዎች በሰዎችና በመሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል።
የኢትዮጵያ ሜትሮሎጂ ኢንስቲትዩት በበኩሉ ትላንት በሰጠው መግለጫ፣ በቀጣዩ የክረምት ወቅት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑት የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚጠበቅና ማህበረሱቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስቧል።
በቀጣዮቹ ወራት የሚኖረው የዝናብ መጠን
የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት መንሸራተት፣ በማሳዎች የውሃ መተኛት፣ የሰብሎች በጎርፍ መዋጥ፣ የአፈር ውስጥ እርጥበት መብዛትን ሊያስከትል እንደሚችል ኢንስቲትዩቱ ጠቁሟል።
በአንጻሩ፣ “በነሐሴ እና በመስከረም ወር የሚጠበቀው ዝናብ፤ በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ እና በመካከለኛው የኢትዮጵያ ክፍል ሊዘገይ ይችላል” ተብሏል።
__
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






