
አክሎግ ቢራራ (ዶር)
የአማራ ፋኖ የቆመበት መርህ፤ የሚንቀሳቀስበት፤ የሚታገልበት፤ ከፍተኛ መስዋእት የሚከፍልበት፤ የአማራው ተራ ሕዝብ ቀን ከሌት ዋጋ የሚከፍልበት መሰረታዊ ምክንያት ለአማራው ሕዝብ ህልውና መሆኑ አያከራክርም። መሰረታዊ ምክንያቱ ግልጽ ከሆነና ባለቤት ካለው የአማራ ፋኖ ለምን እርስ በእርሱ ይናከሳል? ዋናው ዓላማ ከጠላት ላይ በመሆን ፋንታ ሁሉም ነው ለማለት ባልችልም፤ የአማራ ፋኖ ጎራ ለይቶ ለምን እርስ በእርሱ ይገዳደላል? ለምን ለግል ጥቅምና ዝና ይታገላል?
ለመሆኑ ለአማራው የህልውና ፍትሃዊ ትግል የግለሰቦች ፍላጎት፤ “እኔ ብቻ ነኝ መሪነት”፤ ወገንተኛነት፤ እብሪተኛነት እና ጎጠኛነት የአማራውን ሕዝብ ይመጥናል? የአማራ ዲያስፖራስ የሞራል ግዴታውን እየተወጣ ነው? ለምን የመፍትሄው አካል አይሆንም? ለምን የአማራ ፋኖ መሪዎችን አደብ ግዙ፤ ተባበሩ አይልም?
በአማራ ፋኖ መካከል የተከሰተውን ልዩነት በጥበብና በትግግስት ለመፍታት ካልተቻለ፤ የአማራ ፋኖ ድል አድርጎ አዲስ አበባ ቢገባ ይህ የእርስ በእርስ ትንቅቅንቅና የሥልጣን ሺሚያ ሊያስከትለው የሚችለው አንደምታ ምን ይሆናል?
እነዚህና ተዛማጅ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። ልክ እንደ ሌሉ ሁሉም ነገር አማን ነው የሚለውን በበኩሌ አልቀበልም። በተለይ የአማራ ምሁራንና ልሂቃን ድምጽ የምናሰማበት ወቅት አሁን ነው። ምክንያቱም፤ ይህ እድል ካመለጠን ሌላ እድል አይኖረንም።
አንድ ምሳሌ ላቅርብ። በጎንደር ክፍለ ሃገር በአማራ ፋኖ ስም የሚንቀሳቀሱት እርስ በእርሳቸው እየተዋጉ ስንት ጀግኖችን አጥተናል? በዚህ ምክንያት ወንድም ወንድሙን መግደሉ ባስቸኳይ ካላቆመ፤ ይህ ቀጠና የወደፊቱ ዳርፉር የሚሆን ይመሰለኛል። ይህ መሰረታዊ ተግዳሮት ሆኗል። የአማራውን የውጭና የውጭ ጠላት የሚረዳ ተግዳሮት። በጎንደር የተከሰተው ልዩነት ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል። ግን፤ የሚሰማ የለም። ይህ የሚያስታውስኝ ብሂል አለ። “ምክረው! ምክረው! አለያ መከራ ይምክረው1” ይህ ድንቁርና ነው። የአማራው ሕዝብ መከራ አይደለም የፋኖን እንቅስቃሴ የቀሰቀሰው? ሰው እንዴት አንዱን መከራ በሌላ መከራ ይተካል?
እኔ እንደሚገባኝ የአማራ ህልውና ሲባል ክፍለ ሃገር፤ ጎጥና መንደር፤ ጾታ፤ እድሜ፤ ወጣት፤ ሽማግሌ፤ መነኩሴ፤ ሃብታም ወይንም ድሃ፤ ገጠሬ ወይንም ከተሜ፤ ክርስቲያን፤ ይህዲ ወይንም ሙስለም፤ የተማረ ወይንም ያልተማረ፤ በአገር ቤት የሚኖር ወይንም ዲያስፕራ ወዘተ ለይቶ አይደለም። አማራው ለእልቂት፤ ለእስራት፤ ለስደት፤ ለእንግልት፤ ለመፈናቀል፤ ለድህነት፤ ለውርደት፤ ለአገር አልባነትና ለተዛማጅ መከራ የተጋለጠው በአማራነቱ ተለይቶ ነው።
ይህ ጭካኔ የተሞላበት ሰቆቃ የሚካሄደው ደሞ በመንግሥት ደረጃ ነው። ይህንን ጨካኝ መንግሥት የሚደግፉና አገልጋይ ሆነው የሚተባበሩ ልዩ ልዩ አካላት መኖራቸው የአደባባ ምስጢር ነው። ከእነዚህ መካከል የአማራ ፋኖን ሰርገው ገብተው የአማራ ፋኖ እርስ በእርሱ እንዲጨራረስ፤ ወንድም ወንድሙን እንዲገድል የሚያመቻችቹና በቀጥታ የጭካኔው አካል የሆኑ መኖራቸው በተደጋጋሚ ታይቷል። በተለይ ዘግናኝና የአማራው ሕዝብ ይቅር የማይለው በአማራ ፋኖ ስም የጭካኔ ተባባሪ የሆኑትን ነው። ይህ በመሆኑ፤ የአማራው ሕዝብ ጠላት ብዙ ነው ለማለት እችላለሁ። ወዳጁ ግን ገና ብዛት አለው ለማለት አልችልም። እኛም ውጭ የምንኖረው ተቆርቋሪዎች በዚህ ጉዳይ ላይ የድርሻችን አልተወጣነም።
አማራው እንደማንኛውም የሰው ፍጥረት በመሆኑ፤ መሬት፤ ንብረት፤ሃብትና ጥሪት፤ የስራ እድል፤ እምነት፤ ተቋም፤ ድርጅትና መሪዎች ያስፈልጉታል። ህያው ለመሆን የሚበላው ያስፈልገዋል። ይህ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው መሬት፤ ሃብትና ንብረት ሲኖረው ነው። ቤትም ሆነ ንብረት፤ መሬት ላንተ አይገባህም ከተባለ፤ ይህ አይገባህምነት ከአማራው ህልውና ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው። ለይተን አንየው።
የአማራው ሕዝብ በልዩ ልዩ ቦታዎች ግፍና በደል ተካሂዶበታል። አሁንም እየተካሄደበት ነው። ያለው አማራጭ የአማራ ፋኖን አንድ እንዲሆን ጫና በማድረግ ማሸነፍ ብቻ ነው።
አለያ አማራው በመሰረታትና በደማላት አገር ባሪያም ሆኖ የሚኖርባት ኢትዮጵያ አትኖርም። የኦህዴድ ብልጽግና አላማ ኦሮማዊ አገር የመመስረት ህልሙ ስኬታማ ይሆናል፤ በሌላ አነጋገር የአንድ ብሄር የበላይነት በማያሻማ ደረጃ መሰረት ይይዛል። ይህ አደገኛ ሁኔታ ሁሉንም በሰብአዊነታቸውና በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑትን ሁሉ ይመለከታል።
የአማራው መሰረታዊ አደጋ ምንድን ነው?
በአማራው ሕዝብ ላይ የተደቀነበት ሴራ በምን በምን መልኩ ይታያል? የሚለውን መሰረታዊ ጥያቄ በማጠቃለል ላቅርበው።በተደጋጋሚ ለማሳሰብ እንደሞከርኩት በአማራው ላይ የሚካሄደው የህልውና ጥቃት የሚካሄደው ቢያንስ በሚከተሉት ስድስት ክፍሎች ነው።
- በፖለቲካው ሚና እንዳይኖረው፤ ድምጹ እንዳይሰማ፤ተወካይ እንዳይኖረው መደረጉ፤
- በኢኮኖሚው ቤት፤ ንብረት፤ መሬት፤ ሃብት፤ ስራ፤ የግል ንብረት እንዳይኖረው መደረጉ፤
- በእምነቱ፤ በተለይ በኢትዮጵያ ተዋህዶ ኦርቶዶክስ፤ በእስልናና ሌሎች እምነት አባቶችና ተከታዮች ላይ ስር ነቀል የሆነ የተቋም መናድ ጫና መደረጉ፤ እየለያዩ ማምከን የመንግሥት መርህ መሆኑ፤
- በባህሉ ላይ፤ አንተ መጤ ነህ፤ ነፍጠኛ ነህ፤ ወራሪ ነህ፤ ቅኝ ገዢ ነህ፤ “ጡት ቆራጭ ነህ” በሚል ሰው ሰራሽ ትርክት የስነልቦና ጦርነት መካሄዱ፤
- በሚይያኮራውና ዓለም በመሰከረለት ታሪኩ፤ ጀብዱና ጀግንነቱ፤ በአድዋ፤ በማይጨው፤ በካራ ማራ፤ በኮርያ፤ በኮንጎ ባካሄደውና ሚና፤ ሌላው ቀርቶ ፊደል ቀርጾ፤ ተከታታይ ትውልድ አስተምሮ ባዳበረው በአማርኛ ቋንቋው እንዳይተማመን የስነ ልቦና ጦርነት በመካሄድ ላይ መሆኑ፤ እና
- የጥንት አያቶቹ በኖሩበትና ባለሙት መሬት ላይ እንዳይመካ በተከታታይ መፈናቀሉ ይገኙበታል።
እነዚህ ሁሉን የማህበረሰባዊ ኑሮና ህይወት የሚነኩ ተግዳሮቶች ስርዓታዊ፤ ተቋማዊና መዋቅራዊ ናቸው። ተነጣጥለው ሊታዩ አይችሉም።
ለዚህ ነው፤ በአማራው ላይ የሚካሄደው እልቂት ፍጹም የሆነ የማክመክን ስልት ነው የምለው። በመሆኑም፤ የህልውና ትግል የሚለውን የእንጊሊዝኛው ቋንቋ በበለጠ ይገልጸዋል በሚል የማቀርበው። ስለሆነም፤ ይህንን እርህራሄ የሌለበት እልቂት Total Amhara annihilation እለዋለሁ። በብሄርና በቋንቋ የተዋቀረው ሕገመንግሥት እና የክልል አስተዳደር በሕዝቡ ላይ የተጫነው ለከፋፍለህ ግዛውና ከፋፍለህ ብላው ስለሚያገለግል ነው። ይህ ስርዓት እስከ ቀጠለ ድረስ በኢትዮጵያ ሰላምና እርጋታ አይታሰብም።
የኢኦህዴድ ብልጽግና አጀንዳ ምንድን ነው?
በአሁኑ ወቅት፤ ኢትዮጵያ መንግሥት አላት ለማለት አልችልም። በአሁኑ ወቅት፤ በሁሉም ዘርፍ ኢትዮጵያ ሃሰትን እንደ እውነት በሚያስታገባ፤ እልቂትን በእልቂት የሚተካ፤ በሰው ሰራሽ ትርክት የምትስተዳደር አገር ናት። ይህች አገር ወደማትወጣው ዘርፈ ብዙ ቀውስ ገብታለች። የብልጽግና አገዛዝ ይህንን ዘርፈ ብዙ ተግዳሮት ሊወጣው አይችልም። ችግሩን የፈጠረውና እንዲቀጥል የሚያደርገው ራሱ ነው። ኢትዮጵያን ወደ አጣብቂኝ ያስገባት ገዢው የብልጽግና አገዛዝ ነው። ይህ አገዛዝ ተገዢነቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አይደለም። ለሕዝቡ ኑሮ ደንታ የለውም። ለኢትዮጵያም ግዛታዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ግድ የለውም። ለዚህ የጎንደርንና የጋምቤላን አካባቢ ሁኔታ ብቻ ማየት በቂ ነው። የዐብይ አህመድን መከላከያ አድሏዊ፤ ዘውጋዊ፤ ወገንተኛና ተረኛውን ፓርቲ አገልጋይ ሆኗል ተብሎ የሚያስተቸው ይኼው ነው።
ለመሆኑ የኦህዴድ ብልጽግና አጀንዳ ምንድን ነው? ብላችሁ ብትጠይቁዩኝ፤ በኔ ግንዛቤ አማራውን ጨፍጭፎ’፤ በሙሉም ሊገድለው ባይችል ቀንሶና አምበርክኮ የኦሮሞውን የበላይነት እንዲቀበል አድርጎ፤ እትዮጵያን የኦሮሞ አገር ለማድረግ ነው። ታሪክን ወደ ኋላ ብንመለከት ዐብይ አህምደ፤ ሺመልስ አብዲሳና ግብረ አበሮቻቸው የሚያደርጉት ግራኝ ሞሃመድ ካደረገው የባሰ ነው። ታየ ደንድዓ የተናገረውን ብቻ በጽሞና ብታዳምጡት ከዚህ የተለየ አይደለም።
በመሬት ላይ የተከሰተውን ባጭሩ ልጥቀስ። የኦህዴድ ብልጽግና አገዛዝ የአማራው ገበሬ ጥሮ ግሮ፤ አርሶ፤ አምርቶ ለራሱ፤ ለቤተሰቡና ለህብረተሰቡ እንዳያደርስ በድሮንና በሌላ መሳሪያ ሲያወድመው ምን እንለዋለን? ማዳበሪያ ሲከለክል፤ መህር ሲያወድም፤ ከብቶችን በጥይት ሲገድል ወዘተ ለኔ ከህልውናው ጋር የተያያዘ የአረመኔዎች ሽብርተኛነት ስራ ነው።
አማራው ከቀየው ሲፈናቀልና ቤት አልባ፤ መሬት አልባ እንዲሆን ሲገደድ ህይወቱ ሙሉ በሙሉ ተናጋ ማለት አይደለም? ይህ በራሱ የሞት ሞት ነው።
ወጣቱ ትውልድ በአገሩ ስራ ስለሌለው የስራ እድል ለመፈለግ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ሲጓዝ ጀልባው እየሰመጠ ብዙ የአማራ ወጣት ሞቷል።
በአማራው ክልል ብቻ ከስድስት እስከ ሰባት ሚሊየን የሚገመት የአማራ ወጣት የትምህርት እድል ሲከለከል ተከታታይ እድል እንዳይኖረው ተደርጓል።
የአማራው የተማረና የነቃ ክፍል በገፍ እየታሰረ በእስር ቤት ሲሰቃይ በአማራው ሕዝብ ላይ የሚካሄድ ግልጽ አምካኝነት መሆኑን ያሳያል።
በአማራው ተራ ሕዝብ ላይ በጉራ ፈርዳ፤ በሻሸመኔ፤ በወለጋ፤ በወልቃይት፤ በራያ፤ በደራ ወዘተ በተከታታይ የተካሄደው እልቂት፤ መፈናቀል ወዘተ ሆነ ተብሎ የሚካሄድ አማራውን ኢላማ ያደረገ ወንጀል መሆኑ አያከራክርም። በአማራው ላይ ጀኖሳይድ ወይንም የሕዝብ እልቂት ተካሂዷል ለማለት እንችላለን።
በጠቅላላው ስገመግመው የአማራው ሕዝብ በአንድነት ለመነሳት ካልወሰነና የአማራ ፋኖ አንድ ካልሆነ ጠላቱ የተመኘውን ስኬታማ ያደርጋል። የተደራጀን አጥቂ ኃይል ለመከላከልና ለማሸነፍ የሚቻለው አንድ ወጥ የአማራ ተቋም መመስረት፤ አንድ ወጥ የአማራ ጦር ሰራዊት እዝባ አመራር መመስረት፤ አንድ ወጥ የሕዝብ ግንኙነትና የሜድያ ማእከል መመስረት፤ በአንድ ቋት ቁሳቁስ ስብስቦ ሁነኛና ግልጽነት ባለው መልክ ለተንቅስቃሹ አካል መለገስ። ባጭሩ የአማራ ፋኖ በአንድነት ተባብሮ ለመስራት ወስኖ ሲተገብር ብቻ ነው።
ታዲያ ምን እናድርግ?
በአማራው ሕዝብ ላይ በተከታታይ የሚካሄደው በመንግሥት ደረጃ የተቀነባበረውና ፍጹም የሆነው እልቂት የአማራ ፋኖ እንዲመሰረት ምክንያትና መስረት ሆኗል። የዛሬ ሁለት ዓመት የአባቶቻችንን የፋኖን መንፈስ ይዞ የተጀመረው እንቅስቃሴ ታሪካዊና ተአምራዊ ትግል መሆኑን አሳይቷል። በጎንደር፤ በወሎ፤ በጎጃምና በሸዋ ሲካሄድ የቆየውና አሁንም የሚካሄደው ጀብዱ በራሱ ለአማራው ሕዝብ የተስፋ ጭላንጭል ሆኗል። የዚህ እንቅስቃሴ የማህብረሰብ መሰረት ሕዝቡ ነው። በዋናነት የሚመግበው፤ መረጃ የሚሰጠው፤ ደጀን የሆነው ሕዝቡ ነው።
ይህ እንቅስቃሴ በአንድነት ሆኖ የአማራውን ሕዝብ ከተጋረጠበት የህልውና አደጋ ከመከላከልና ከማጥቃት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። በዚህ ላይ እንስማማ። ተገዢነታችን ለማንም ሳይሆን ለአማራው ሕዝብ ብቻ ይሁን እላለሁ። ይህንን ካደረግን ማንም ሃይል የአማራ ፋኖን ሊገታው አይችልም። ምክንያቱም፤ እምነቱና አንድነቱ ከብረት የጠነከረ ስለሆነ ነው።
የአማራ ፋኖን ምን መሰናክል ገጠመው?
- በአራቱም ክፍለ ሃገሮች ያሉት የፋኖ መሪዎች በግለሰባዊ ሥልጣን ይገባኛልነት/የመሪነት ፍላጎትንና ችሎታን ማጋነን፤ ስር መስደዱ፤ ገንዘብና ደጋፊዎች ማግኘታቸው፤ይህ ነው ዋናው ተግዳሮት ተብሎ የሚነገረው፡፡
- በውጭ የሚገኙ የአማራ ሜድያዎች፤ የማህበረሰብ አንቂዎችና ምሁራን አንዱን ፋኖ ከሌላው እየለዩ መገምገማቸው፤ መለየታቸው፤መደገፋቸው የጋራውን የአማራውን የህልውና ትግል ዓላማ በክሎታል ተብሎ ይነገራል።
- ሁሉም ናቸው ባይባልም፤ የፋኖ አመራሮች፤ ልሂቃን፤ ምሁራን፤ ሜድያዎች የጎጠኛነት ዝንባሌ ማሳየታቸው፤ ለምሳሌ ጎጃምና ጎንደር የሚል አንድነትን የሚጎዳ አካሄድ መስተጋባቱ፡፡ ይህንን ህወሃትና የኦህዴድ መንግሥት ሰርገው ገብተውና ገንዘብ ፈሰስ እያደረጉ አማራውን ከአማራው ጋር እያጋጩት፤ እንዲገዳደል እያደረጉት ነው ተብሎ ይነገራል። ይህ ጎልቶ የተከሰተው በጎንደርና በሸዋ ነው የሚሉት ብዙ ተቆርቋሪዎች ናቸው።
- የአማራውን ዘርፈ ብዙ ጥቃቶች ለመወጣት የዓላማና የተግባር አንድነት ግዴታ መሆኑን መገንዘብ አለመቻሉ፤ የተማከለ የአማራ ፋኖ ድርጅትና አመራር ክፍተት መኖሩ፤ በአማራው ላይ የእልቂት ጦርነት የሚካሄድ መሆኑን እንደ ተራ ነገር ማየታችን በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
- የአማራው ትግል ለህልውናና ለፍትህ ብቻ ሳይሆን ለአማራውና ለሌላው መከራ መሰረት የሆነውን ዘውጋዊና አምባገነን ስርዐት ገርስሶ ሕዝቡ የስልጣኑ ባለቤት እንዲሆን ማመቻቸት መሆኑን አለመገንዘብ፤ ይህንን ሌሎች እንዲጋሩት አለማድረጋችን በተደጋጋሚ እንደ ድክመት ይነሳል።
- በአማራ ምሁራን፤ ልሂቃን፤ ጫና ፈጣሪዎችና በፋኖ አመራሮች መካከል ብዙ የማይነገር የፖለቲካና የርእዮተ ዓለም ልዩነት አለ እየተባለ ይጠቆማል፤ ለምሳሌ፤ አብዛኛው የአማራ ምሁር እኔ በአማራነቴ ሳይሆን የማምነው በኢትዮጵያዊነቴ ነው የሚለው መኖሩ፡፡
- የአማራ ፋኖን የጠለፉ ግለሰቦች አማራው ባንድነት እንዳይቆም ከፍተኛ ውዢንብር እየፈጠሩ ነው የሚሉም ተቆርቋሪዎች አሉ።
- የአማራው ዲያስፖራ አንድ ወጥ የሆነ መርህ ለመከተል አለመቻሉ፤ የተበታተነ መሆኑ፤ ገንዘብ በአንድ ቋት ለመላክ አለመቻሉ በተደጋጋሚ ይነሳል።
- ኦህዴድ፤ ህወሃት ወዘተ ብዙ ገንዘብ ፈሰስ በማድረግ ለሆዳቸው ተገዢ የሆኑ አማራዎችን ጣልቃ እንዲገቡና የአማራ ፋኖን እንዲበክሉ መደረጉ፤ የአማራ ፋኖ እርስ በእርሱ መነታረኩ፤ መገዳደሉ፡፡ ተአመኔታ አለመኖሩ ችግር ፈተና እንደሆነ ይጠቀሳል።
- የአማራ ፋኖ እርስ በእርሱ በመጋጨቱ የአማራው ሕዝብ ተስፋ እንዲቆርጥ መደረጉ፤ የጎሳ ፌደራሊዝም ይመቸናል የሚሉ ምሁራንና ልሂቃን በጎን እየሰሩ ማዘናጊያ መሆናቸው አማራጭ የሆነ የሽግግር መንግሥት እንመስርት ማለታችው ይነገራል።
- የአማራ ጫና ፈጣሪዎች፤ ምሁራን፤ ልሂቃንና ስብስቦች ለግል ዝናና ሥልጣን የቆሙ የፋኖ መሪዎችን ለመተቸት አለመቻላቸው ለአማራው ፋኖ አንድነት መስናክል ሆኗል የሚሉ ብቅ ብቅ በማለት ናቸው የሚለው ይነገራል።
- የአማራው ሕዝብ የውጭ አገር ወዳጅና ደጋፊ ለማግኘት አለመቻሉን የአማራ ፋኖ መሪዎች እለመገንዘባቸው መሰረታዊ ተግዳሮቶች ናቸው የሚሉት ሁሉ በሰፊው በልዩ ልዩ መድረኮች ይነገራሉ።
ባጠቃላይ ስገመግመው የአማራ ፋኖን ተአምራዊ ጀብዱ ብዙ መሰናክሎች እንደ ተከሰቱበት የሚያሳይ ሁኔታ አለ። ለአንድነት መሰናክል የሆኑትን ችግሮች ሁሉ ለመፍታት የሚቻልበት እድልም አለ።
መጀመሪያ ልዩነትን በአማራ ጨዋነት ተመካክሮ መፍታት ወሳኝ ነው። ልዩነት ፈጣሪዎችን አደብ ግዙ ብሎ ማስጠንቀቅ የመጀመሪያው እርምጃ ነው። ሽምግልናን እንደ በጎ ነገር የማይመለክት የአማራ ፋኖ እንዴት አድርጎ የአማራውን የህልውና ትግል ስኬታማ ለማድረግ ይችላል? ልዩነትን በጥበብ ለመፍታት ካልተቻለ ልዩነቱ እየከረረ ወደማይታረቅበት ደረጃ ይሸጋገራል። ይኼ ደሞ የሚረዳው ስርዓቱን ነው።
የአማራ ፋኖ እንቅስቃሴን በመመካከር፤ በብልሃት፤ በመቻቻል፤ በአንድነት ለመምራት የማይችሉ ግለሰቦች እንዴት የብዙ ብሄረሰቦችና እምነቶት አገር የሆነችውን ኢትዮጵያን ለመምራት ይችላሉ? ብለን የምንጠይቅበት ወቅት አሁን ነው። ለዚህ መሰናክል የሆኑትን ግለሰቦችም ለመተቸትና ለመምከር የምንገደድበት ወቅት ዛሬ ነው። /6
የአማራው ሕዝብ ፍላጎት መሰረት ስለሆነ፤ የአማራው ሕዝብ የሚመኘው ምንድን ነው? የሚለውን በአጭሩ ልመልሰው።
አንደኛ፤ የአማራው ሕዝብ እልቂት በቃኝ ብሎ ተነስቷል። ስለዚህ የአማራ ፋኖ ባንድነት ድሉን በፍጥነት መቀዳጀት ወሳኝ ነው። አለያ ሕዝቡ ጦርነቱ ይሰለቸዋል፤ ከሚሽከመው በላይ ይሆንበታል።
ሁለተኛ፤ እስካሁን የተካሄደው የአካባቢ ጦርነት አመርቂ ውጤት ማስገኘቱ ባይካድም፤ የአማራ ፋኖ ፋሺስታዊውን ስርዓት ለመገርሰስ ባንድነት የተቀነባበረና ስልታዊ ውጊያ ማካሄድ አለበት። ጦርነቱ ከአማራው ክልል አልፎ መላውን ኢትዮጵያን ማናጋት አለበት።
ሶስተኛ፤ በቅርቡ አንድ አንድ የፋኖ አመራሮች የዐብይን ጦር ለማዳከም የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ይበል የሚባል ሆኖ አገኘዋለሁ። የዐብይ ጦር ሰራዊት ፊት ለፊት የሚያሰማራውና የጥይት ማብረጃ የሚያደርገው ሚሊሺያውን፤ ልዩ ኃይሉንና ፖሊስ ሰራዊቱን ነው። በብዛት የሚሞተውና የሚማረከው ይህ ክፍል ነው። እየከዳ ከመሳሪያው ጋር የአማራ ፋኖን እንዲቀላቀል መጎትጎቱ የምስራች የሚባል ነው። ቀጥሉበት እላለሁ። ያልተቀላቀለው ክፍል እንዲቀላቀል ጥሪ አደርጋለሁ።
ለማጠቃለል፤
- የአማራ ፋኖ አመራር የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር የጅዖፖለቲካው ሁኔታ በፍጥነት እየተለዋወጠ መሄዱን መገንዘብ አለበት። ይህ እድልም ነው፤ አደጋም ነው።
- በግልጽ የሚታየው ክስተት ህወሃት የተለመደውን ባህሪውንና መርሆውን ተከትሎ ከሱዳን አንድ ክፍል፤ ማለትም ከጀኔራል አልቡርሃን ጋር ስትራተጂክ ግንኙነት መስርቷል። የዚህ ቡድን ዋና አላማ ወልቃይት ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያን ጠቅልሎ ታላቋን ትግራይን እንደ አዲስ አገር ይፋ ማድረግ ነው።
- ጎንደሬው፤ ብሎም መላው አማራም፤ ብሎም መላው በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነው ሁሉ፤ ኦሮሞውን ጨምሮ፤ በአንድነት ለዚህ ጥቃት ያጋለጠውን የኦህዴድ ብልጽግናን አገዛዝ ለመገርሰስና ሁሉን ዜጎቿን የምታስተናግድ ዲሞክራሳዊ ኢትዮጵያን መልሶ እንድታብብ የማድረግ ግዴታ አለበት። ለዚህ ደግሞ የአማራ ፋኖ ትግል ፍትሃዊና ዲሞክራሳዊ መሆኑን መቀበል ያስፈልጋል።
- ህወሃት ከአልቡርሃን ጋር አብሮ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያን ቢቆጣጠር ተጠቃሚው የትግራይ ሕዝብ ይሆናል የሚለው አከራካሪ ነው። ዋናው ተጠቃሚ ሱዳንና አጋር የሆነችው ኤምሬትስ እንደምትሆን አምናለሁ። በመሆኑን ጉዳዩ የጎንደር አማራ ብቻ ሳይሆን፤ የመላው አማራና የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። ጉዳዩ የኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ሉዐላዊነት ይሆናል። ስለዚህ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ትግሉን ከዳር ማየታቸውን አቁመው ድጋፍ እንዲሰጡ ጥሪ አደርጋለሁ።
- የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ የአማራ ፋኖ የዐብይ አህመድ አገዛዝ የፈጠረውን ብሄራዊ ጠንቅ (National crisis) እንደ አጋጣሚ እድል የመጠቀም ግዴታ አለበት። ሕዝቡ ዝም እስካለ ድረስ ስር ዓቱ ተቀብሎታል፤ ምንም አያደርግም የሚል እምነት ይኖረዋል። ይህ ሁሉንም ዜጋ ይጎዳዋል። ሸክሙ በቃን በሉ።
- የአማራ ፋኖ ጥንቃቄ ያድርግ የምለው በደርግ ጊዚ ያየሁትን “የጠላቴ ጠላት ወዳጀ ነው” የሚለውን በጭፍን እንዳያስተናግድ ነው። የአማራ ፋኖ እውነተኛ ጠላቱን ከእውነተኛ ወዳጁ የመለየት ግዴታ አለበት። ህወሃት የአማራውን፤ ብሎም የኢትዮጵያን አንጡራ መሬት ቀምቶና ለጠላት አስተላልፎ ወዳጅ ሊሆን አይችልም። ቢያንስ ቢያንሥ በዚህና ተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ቀይ መስመር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።
- የአማራ ፋኖ ዋናው ወቅታዊ ትኩረት አንድነቱን ለመላው የአማራ ሕዝብና ለመላው ዓለም ይፋ ማድረግ ነው። ይህንን ሲያደርግ በችሎታቸው እንከን የሌላቸውን መሪዎቹችን በየዘርፉ ሰይሞ የአማራውን የህልውና ስኬታማ ማድረግ አለበት ማለቴ ነው። ችሎታና ብቃት ያላቸው ምሁራን፤ የጦር መኮንኖች፤ የፖለቲካ ጠበብቶች፤ የሕዝብ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ፤ የቁሳቁስ፤ የሜድያ መሪዎች መሪዎች አሉት። ከአገር ውጭም አጋሮች አሉት። የአማራው ሕዝብ ዋናው ደጀኑ ነው። የዚህ ሕዝብ ድጋፍ እንዳያቆም ከፈለገ የአማራ ፋኖ ከአንድነት ውጭ ሌላ አማራጭ የለውም። እርስ በእርሱ መናከሱና መገዳደሉ ባስቸኳይ መቆም እለበት።
- የአማራ ፋኖ አንድነት ለህልውና ወደ ድል ምእራፍ ሊሸጋገር የሚችለው በግለስቦች የስልጣን ወይንም የዝና ግብግብ ወይንም የእልኸኛነት ባህርይ፤ ወይንም እኔ የምለውን ብቻ እመኑና ተከተሉ በሚሉ ብሂሎች ሊሆን አይችልም። በተደጋጋሚ አንድነት ለድል የሚል መርህ ጠቃሚ መሆኑን አሰምርበታለሁ።
ለአማራው የህልውና ትግል በአንድ ራስ ሁለት ምላስ አያዋጣም። ባንድ በኩል ባንድነት እንስራ እያሉ በጀርባ ወገንን ማጥቃት ለማን ሊያዋጣ ይችላል? ማንን ይረዳል? ያላማ ጽናት ለትግሉ ወሳኝ መሆኑን አሰምርበታለሁ።
- ዝንጀሮ መጀመሪያ መቀመጫየን እንዳለችው ሁሉ፤ የአማራ ፋኖ በውስጡ ሰርገው ገብተው እርስ በእርሱ የሚያናክሱትን ግለሰቦችና ስብስቦች ባስቸኳይ ማጽዳት አለበት።
- የአማራ ፋኖ የእርስ በእርስ ገመድ ጉተታውን ባስቸኳይ ያቁም፤ ወንደም ወንድሙን አይግደል። ይህ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
- ወጣት ሆኘ የማስታውሰው አንድ ምክረ ሃሳብ ትዝ አለኝ። በህጻንነቴ በአካባቢው ዳኛ ወይንም ፖሊስ አልነበረም። ግለሰቦች ሲጣሉ፤ ለምሳሌ ነፍሰ ገዳይ ወይንም ሌባ ወይንም በትዳር የተጋጩ ግለሰቦች፤ አባቴና ሌሎች ሽማግሌዎች ከጸሎት በኋላ ከዛፍ ስር ቁጭ ይላሉ። ባለጉዳዮችን ጥርተው ይመክራሉ። ይህ ዝግ ችሎት ነው። ምስጢርም ነው። በፈቃደኛነት የሚስራ ጉዳይ ነው። በአብዛኛው በጽሞና ካዳመጡ በኋላ ችግሩን ይፈቱታል። መመካከር፤ መደማመጥ ክፍተኛ ጥቅም አለው። የፋኖን መሪዎች ዝግ ችሎት አድርጉና ችግራችሁን ራሳችሁ ፍቱ እላለህ።
- በመጨረሻ፤ የአማራውን ዲያስፖራ የምመክረው ሌላውን ሁሉ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን የሁላችንም ዋና ትኩረታችን የአማራ ፋኖ እንድ እንዲሆን መረባረብ ነው።
ይህንን ካደረግን የአማራው ሕዝብ ያመሰግነናል፤ የዓለም ህብረተሰብ ለአማራ ፋኖ እውቅና የሚሰጡበት ቀን እሩቅ አይሆንም።
__
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






