Homeነፃ አስተያየትየተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ብቸኛው መንገድ ዉይይትና ድርድር ነው!!!

የተደቀነብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ ብቸኛው መንገድ ዉይይትና ድርድር ነው!!!

Advertisement
World Wide Travel Group

ኤፍሬም ማዴቦ (emadebo@gmail.com) 

እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1950ዎቹ አጋማሽ የተጀመረውና ለ1966ቱ አብዮት መፈንዳት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው የኢትዮጵያ ተማሪዎች እንቅስቃሴ ከቀዳማዊ ኃ/ሥላሤ ሥርዓት ጋር ከፍተኛ ትንቅንቅ አድርጓል። ይህ ባለፉት ሃምሳ አመታት ውስጥ በተለያየ ጎራ ተሰልፈው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ያደረጉ ብዙ የትግል ሰዎችን ያፈራው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ዉስጥ የፊውዳል ሥርዓት ማብቃት አለበት ብሎ ለአመታት የታገለ ቢሆንም፣የፊውዳሉ ሥርዓት ካበቃ በኋላ ምን አይነት ሥርዓት መምጣት አለበት ለሚለው ጥያቄ መልስም ድርጅታዊ ዝግጅትም አልነበረውም። ይህ በመሆኑ የቀኃሥ ሥርዓት በየካቲቱ አውሎነፋስ መነቃነቅ ሲጀምር፣አጋጣሚውን ተጠቅሞና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ከሥልጣን አውርዶ በቦታው የተተካው፣ በወቅቱ ድርጃታዊ አቋም የነበረውና እራሱን “ግዜያዊ ወታደራዊ መንግስት” ብሎ የሰየመው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ነበር።

የበረሃውን አንበሳ ጄኔራል አማን አንዶምን ሊቀመንበር አድርጎ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ኢትዮጵያን መምራት የጀመረው ደርግ፣ከውስጥም ከውጭም ውስብስብ የሆኑ ችግሮች ውስጥ የገባውና “ያለምን ደም” ብሎ እየዘመረ ደም በገፍ እያፈሰሰ ልዩነቶችን በጡንቻ መፍታት የጀመረው ብዙም ሳይቆይ ነበር። በትውልድ ኤርትራዊ የሆኑት ጄኔራል አማን አንዶም በሥልጣን ላይ በነበሩበት አጭር ግዜ በተደጋጋሚ ካደረጓቸው ሙከራዎች አንዱ፣ የኤርትራን ችግር ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት ያደረጉት ጥረት ነበር፣ ይህ ጥረት በአንድ በኩል ጄኔራል አማንን የህይወት ዋጋ ያስከፈላችው ሲሆን፣በሌላ በኩል ደሞ የደርግን ጭካኔና ደም የማፍሰስ ጥማት በግልጻ ያሳየ ነበር።

በደርግ የመጀመሪያዎቹ አመታት በተቃዋሚው ጎራ የኢትዮጵያን የፖለቲካ መድረክ የተቆጣጠሩት መላው ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) እና የኢትዮጵያ ህዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ነበሩ። ደርግ ለእነዚህ ሁለት ሶሻሊስ ርዕየተ ዓለምን ለሚከተሉ ድርጅቶች የአብረን እንስራ ጥሪ ሲያቀርብ፣ የኢህአፓ የመጀመሪያው መልስ፣እንዴት ነው አብረን የምንሰራው ወይም አብረን የምንሰራቸው ስራዎች ምንድናቸው የሚል ሳይሆን፣ እኛ ከፋሺስት ጋር አብረን አንሰራም የሚል ነበር። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የኢትዮጵያ ህዝብ ደርግን ለማስወገድ በተለያየ መልኩ መራራ ትግል አካሂዷል፣ሆኖም በ1983 ዓ.ም. ደርግን ከሥልጣን አስወግደው አራት ኪሎን የተቆጣጠሩት ኢትዮጵያን በዘር የከፋፈሏትና የኢትዮጵያ ህዝብ ለሚቀጥለው ህያ ሰባት አመት የታገላቸው ህወሓቶች ነበሩ። ህወሓቶች ሥልጣን ከተቆጣጠሩ በኋላ የኢትዮጵያ ህዝብ በተለያየ ግዜ አገራዊ ጉባኤ ተካሂዶ ብሔራዊ እርቅ ይደረግ ብሎ ሲጠይቅ፣ የህወሓቶች መልስ የተጣሉ ግለሰቦች እንጂ የተጣላ ህዝብ የለም የሚል የፌዝ መልስ ነበር።

የአገራችንን የኢትዮጵያን ያለፉት 150 አመታት ታሪክ ወደኋላ ዞር ብለን ስንመለከት ሦስት ኩነቶች ወለል ብለው ይታዩናል፣ አንደኛ- እኛ ኢትዮጵያዊያን ድንበር ጥሶ በሚመጣ ወራሪ ኃይል ወይም ቅኝ ገዢ ላለመገዛት የማናደርገው ምንም ነገር የለም፣የአገር ዉስጥ ገዢዎቻችን መብታችንን ገፍፈው እንዳሰኛቸው ረግጠው ሲገዙን ግን ከሚገባው በላይ እንታገሳለን፣ሁለተኛ- ጨቋኝ የፖለቲካ ሥርዓትን ማስወገድ እንችልበታለን፣ ሁላችንንም የሚያቀፍ የተሻለ ሥርዓት መገንባት ግን አናውቅበትም፣ ሦስተኛ- የፖለቲካ ችግሮቻችንን በጉልበትና በኃይል እንጂ በውይይት፣በድርድር ወይም በሽምግልና መፍታት አናውቅበትም። 

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ወደ ሥልጣን ሲመጣ በዘመናዊ ኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ህዝባዊ ድጋፍ ነበረው፣ጠሚሩ ይህንን ህዝባዊ ድጋፍ ወይም የፖለቲካ ካፒታል ተጠቅመው ብዙ የአጭርና የረጂም ግዜ ስራዎችን መስራት ይችሉ ነበር። ለምሳሌ፣አኩርፎ መቀሌ የገባውን ህወሓት “የቀን ጅብ”፣’ጁንታ’፣”አገር አፍራሽ” እያሉ ከፖለቲካው ማዕከል ከማራቅ፣ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገውና መሄድ የሚችሉትን ርቀት ያክል ሄደው ህወሓት የጦርነት አማራጭን ትቶ ልዩነቶችን በውይይት እንዲፈታ ማድረግ ነበረባቸው። ይህንን በተመለከተ ጠሚ አቢይ የሰሩት ስራ እዚህ ግባ የማይባል ስለሆነ፣ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዋጋ ከፍላለች፣አሁንም እየከፈለች ነው። 

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ከህወሓት ጋር ያደረገው ሁለት አመት የፈጀ ጦርነት፣ የኢትዮጵያ ጥምር ኃይሎች በከፈሉት ከፍተኛ መስዋዕትነት ህወሓት በታሪኩ ለመጀመሪያ ግዜ መሸነፉን አምኖና ትጥቄን እፈታለሁ ብሎ ጦርነቱ በስምምነት ቢቋጭም፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በፕሪቶሪያው ስምምነቱ መሰረት ህወሓት ትጥቁን እንዲፈታ ከማድረግ ይልቅ፣ ከህወሓት መሪዎች ጋር ሰርግና ምላሽ ዉስጥ በመግባቱ፣ዛሬ ህወሓት ለሚያደርገው ለሌላ ዙር የጦርነት ዝግጅትና ባጠቃላይ ትግራይ ዉስጥ ለሚታየው ረሃብ፣ወንጀልና ህገወጥነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

ሌላው በፍጹም ይቅር የማይባል የጠሚ አቢይ አህመድ አገራዊ ክህደት፣ በአለም አቀፍ ስምምነት ትጥቁን ይፍታ የተባለውን ህወሓትን አቅፈው እየሳሙ፣ የሰሜኑ ጦርነት ሲጀመር አገርህን አድን ብለው ጥሪ ሲያደርጉለት፣ጨርቄን ማቄን ሳይል ጥሪውን ተቀብሎ ከጉድ ያዳናቸውን ፋኖን ትጥቅህን ካልፈታህ ብለው ጦር ይዘው አማራ ክልል መዝመታቸውና ዛሬ ሁለተኛ አመቱን ጨርሶ ወደ ሶስተኛ አመት የተሸጋገረውን የርስ በርስ ጦርነት መጀመራቸው ነው። 

ዛሬ ኢትዮጵያ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በማወቅም ባለማወቅም በፈጠራቸው ነገር ግን በፍጹም ብቻውን መፍታት በማይችለው አምስት ቀውሶች መሰረቷ እየተናጋ ነው። አንደኛ- ትግራይ ክልል ትሁን ወይም አራሷን የቻለች አገር ምንም የሚታወቅ ነገር የለም።  ህወሓቶች የክልሉን ግዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳን በኃይል አስወግደው እነሱ የፈለጉት ሰው በቦታው እንዲቀመጥ አድርገዋል፣ አሁን ደሞ ጭራሽ የፕሪቶሪያው ስምምነት ተግባራዊ ካልሆነ ሌላ ዙር ጦርነት የማይቀር መሆኑን በግልጽ እየተናገሩ ነው። ሁለተኛ- አማራ ክልል በ15 ቀን ትጥቅ አስፈትተን እንመለሳለን ተብሎ የተገባበት ጦርነት ከ15 ቀን ወደ ሁለት አመት ማደጉ ብቻ ሳይሆን፣ትጥቁን እያስረከበ ሁለት እጁን ከፍ እያደረገ እራሱን ለፋኖ የሚሰጠው የአቢይ አህመድ ሰራዊት ሆኗል። ሦስተኛ- ኦሮሚያ ክልል ዉስጥ በአንድ በኩል የሸኔ ኃይሎች የትጥቅ ትግሉን አፋፍመው ይዘውታል፣ በሌላ በኩል ደሞ ክልሉ መሳሪያ ያነገበ ሁሉ ግለሰቦችን እያፈነ ገንዝብ የሚጠይቀበትና ህገ-አራዊት የነገሰበት ክልል ሆኗል። አራተኛ- የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት አንዴ የባህር በር፣ ሌላ ግዜ ደሞ የባህር ኃይል እያለ የጀመረው ዘመቻ የጎረቤት አገሮችን አስቆጥቶ የአፍሪካ ቀንድ ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ የተለያዩ ኃይሎች የሚፈነጩበት የፍጥጫ ቀጣና እየሆነ ነው። አምስተኛ- የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ተው ይቅርብህ ተብሎ አገር ውስጥም ውጭ አገርም ባሉ ኢትዮጵያዊያን የኤኮኖሚ ጠበብቶች ሲነገረው ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ ከአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ጋር ያደረገው ስምምነት፣ኢትዮጵያ ዉስጥ መካከለኛ ገቢ ያለውን የማህበረሰብ ክፍል አጥፍቶ አገራችንን በጣት የሚቆጠሩ ኃብታሞችና የእልፍ አእላፋት ደሃዎች አገር አድርጓታል። የኢትዮጵያ ብር ዋጋው በገበያ እንዲወሰን ከተደረገ በኋላ የተፈጠረው የዋጋ ንረት ለወትሮው መጽዋች የነበረውን የማህበረሰብ ክፍል የሰው እጅ እንዲመለከት አድርጎታል።

የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት አንዴ የኮሪዶር ልማት፣አንዴ በስንዴ ምርት እራሳችንን ቻልን ሌላ ግዜ ደሞ ኢትዮጵያ ያለጥርጥር እያንሰራራች ነው እያለ የኢትዮጵያን አስከፊ ገጽታ ለመደበቅ ቢሞክርም፣ የዛሬዋ ኢትዮጵያ ሁኔታ እንኳን በቃላት ጋጋታ በብረት መጋረጃም ሊደበቅ አይችልም። የኤኮኖሚውን ዘርፍ ካየነው የኢትዮጵያ ህዝብ በልቶ ማደር የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፣የማህበራዊውን ዘርፍ ካየነው ቂሚያው፣ዝርፊያውና አፈናው ባጠቃላይ የወንጀሉ ብዛትና አይነት ከቤት ወጥቶ መመለስን ብርቅ አድርጎታል። ፖለቲካችን የገባበት ችግር ተዘርዝሮ የሚያልቅ አይደለም። ህወሓቶች ትግራይን ለአራተኛ ዙር ጦርነት እያዘጋጇት ነው፣ ኦሮሚያ ውስጥ ሰባት አመት ያስቆጠረ የትጥቅ ትግል፣ዝርፊያ፣አፈናና በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸም ግዲያ ያለምንም ክልከላ እየተካሄደ ነው። አማራ ክልል ዉስጥ የተጀመረው ጦርነት ሁለት አመቱን ጨርሶ ሦስተኛውን ተያይዞታል። አፋር፣ሱማሌና ኦሮሚያ ክልሎች በግዛት ይገባኛል ጥያቄ ጦር ለመማዘዝ እየተዘጋጁ ነው። የደቡብ ክልል ወጣቶች አሁንስ መረረን ብለው እራሳቸውን የደቡብ ፋኖ ብለው ሰይመው ለትጥቅ ትግል እየተዘጋጁ ነው። እነዚህን መራራ እውነቶች የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በፕሮፓጋንዳ ጋጋታ ሊሸፍናቸው አይችልም፣ወታደራዊ ጡንቻውን ተጠቅሞ በየአካባቢው የሚካሄድውን ጦርነት ማሸነፍም አይችልም። ያለ ምንም ማጋነን እውነቱን እንናገር ከተባለ፣ የኢትዮጵያን ውስብስብ ችግሮች በጦርነት መፍታት በፍጹም የማይቻልበት ቦታ ላይ ደርሰናል። 

ከላይ ለተዘረዘሩት የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ኤኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ግዜ ወስደን፣አስበንና ተወያይተን ወቅቱና ሁኔታው የሚፈለገውን የመፍትሄ ሃሳብ ይዘን የማንመጣ ከሆነ፣ ወይ አገረ-መንግስቱ ይፈርሳል፣አለዚያም አይናችን እያየ ኢትዮጵያ ወደ ብዙ ትናንሽ አገሮች ትቀየራለች እንጂ፣ በ1966፣በ1983 እና በ2010 እንዳየነው የዛሬው ተፋላሚዎች አንዱ ሌላውን አሸንፎ ሥልጣን መቆጣጠር የሚችልበት ሁኔታ አይኖርም። ኢትዮጵያ እንደ ሶማሊያ አገረ-መንግስት አልባ (State Less) አገር ትሆናለች ሲባል፣በተደጋጋሚ የምንሰማው መልስ ታዲያ ሶማሊያኮ አሁን መንግስት አላት የሚል ነው። ለኔ ይህ ጀልባና አውሮፕላን ተሸካሚ መርከብን ማወዳደር ይመስለኛል፣ በሌላ በኩል ደሞ፣ ኢትዮጵያ ትፈርሳለች ሲባል፣ ኢትዮጵያ የቃል ኪዳን አገር ናት አትፈርስም የሚባል ድምፅ በስፋት ይሰማል። ከማን ጋር ነው ኢትዮጵያ ቃልኪዳን የገባችው? ከእግዚአብሔር ጋር ነው ለምትሉ እግዚአብሄር ከሰው ልጆች ጋር ነው ቃል ኪዳን የገባው እንጂ ከአገር ጋር አይደለም፣ደሞም ለእግዚአብሔር ኢትዮጵያም፣ሶማሊያም፣ሶሪያም፣ቻይናም አንድ ናቸው። 

- Advertisement -

በኔ ዕምነት ሙሉ ፈቃደኝነቱ፣መቻቻሉ፣መደማመጡና መከባበሩ በመካከላችን የሚኖር ከሆነ፣ኢትዮጵያን ለማዳንና የኢትዮጵያን የፖለቲካ መሰረት ላንዴና ለመጨረሻ ግዜ በነፈሰ ቁጥር በማይነቃነቅ ጠንካራ መሰረት ላይ የማቆም ዕድሉ አሁንም እጃችን ላይ ነው ያለው ባይ ነኝ። ዛሬ ኢትዮጵያን ወጥረው የያዟት ችግሮች በአንድ መንግስት ዉስጥ የተፈጠሩ ችግሮች አይደሉም፣በመንግስት ብቻ የተፈጠሩ ችግሮችም አይደሉም። ድርሻችን ይለያያል እንጂ በማድረግም ባለማድረግም የኢትዮጵያን ችግሮች የፈጠርነው እኛ ልህቃኖቿ፣ምህሮቿ፣የተለያዩ መንግስታትና በእያንዳንዱ መንግስት ዉስጥ የነበረው የማህበረሰብ አካል ነው፣ ችግሩን መፍታት ያለበትም ይሄው አካልና መንግስት ነው። 

በ1960ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ የዲሞክራሲ መብቶች ያለገደብ አሁኑኑ ብለን ኢትዮጵያ ውስጥ ከዳር ዳር  ጮኸናል፣ ህዝባዊ መንግስት ይመስረት፣ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ፣የኢትዮጵያ አንድነት ለድርድር አይቀርብም የሚሉ መፈክሮች በደርግም፣በህወሓትም አሁን በሥልጣን ላይ ባለው የጠሚ አቢይ አህመድ ዘመንም በየቀኑ የሚሰሙ መፈክሮች ናቸው። እነዚህን መፈክሮቻችንን ተግባራዊ ለማድረግ ባለፉት ሃምሳ አመታት የከተማ ውስጥ ትግል አድርገናል፣ጫካ ገብተን የትጥቅ ትግል አድርገናል፣እርስ በርስ ተጨራርሰናል፣ሆኖም በ50 አመት ዉስጥ ሦስት ግዜ የመንግስት ለውጥ ማድረግ ብንችልም፣አንዱን አምባገንነ በሌላ አምባገንነ ከመተካት ውጭ፣ የመንግስት ለውጥ እንድናደርግ ለትግል ያነሳሱንን ዋና ዋና ምክንያቶች ለአንዱም ተግባራዊ ዕልባት መስጠት አልቻልንም።  

እኛ ኢትዮጵያዊያን ዕድለኞች ነን መሰለኝ ታሪክ በ1966፣ በ1983 እና በ2010 የቸረንን የሥርዓት ለውጥ አጋጣሚ አሁንም እንካችሁ እያለን ነው። ከቅድመ 1966 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ድረስ የነበረው ትግላችን ያተኮረው ጨቋኝ ሥርዓቶችን በመጣል ላይ ነው እንጂ የወደቀውን ሥርዓት በምን እንተካለን ለሚለው ቁልፍ ጥያቄ መልስ አልነበረውም። የማይቀረውና ፊት ለፊታችን ላይ ያለው የመንግሥት ለውጥ ግን አንድን የጠገበ ዓምባገነን በሌላ በራበው ዓምባገነን ከመለወጥ ዑደት ውስጥ ወጥተን፣ አዲስ ህዝባዊ ሥርዓት እንዴት እንደምንገነባና ይህንን የሥርዓት ግንባታ ሂደት ማን ይመራዋል የሚለውን ቁልፍ ጥያቄም የሚመልስ ለውጥ መሆን አለበት። የኢትዮጵያ የፖለቲካ ልህቃን፣ምሁራንና የሲቪክ ማህበራት የሽግግሩን ወቅት እንዴት እንወጣዋላን ከሚል አገራዊ ጥያቄ ጎን ለጎን የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባትን የሚለውን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል ውይይት ውስጥ ሳይውል ሳያድር ዛሬውኑ መግባት አለባቸው።

ባለፉት ሃምሳ ዓመታት የተራመድንበት የፖለቲካ ታሪካችን የሚያሳይን ነገር ቢኖር ችግሮችን በጋራ የመፍታትና የፖለቲካ ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ ተወያይቶ የማስወገድ ባህላችን ደካማና ኋላ ቀር እንደሆነ ነው። ሆኖም ይህ የአዲስ ሥርዓት ግንባታ ጅምራችን ከአዲስ የፖለቲካ ባህል ጋር መላመድንም ያጠቃልላልና ልዩነትን ከሚያስቀድም የዜሮ ድምር ፖለቲካ ተላቅቀን የአገራችንን ችግሮች አንድ ላይ ሆነን በጋራ መፍታት አለብን። የወደፊቷ ኢትዮጵያ የፖለቲካ አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት የሚለው ጥያቄ መልስ መገኘት ያለበት ከሁሉም የኢትዮጵያ ልጆች አንደበት ነው። እንደዚህ ሲባል ግን የኢትዮጵያ ህዝብ ስብሰባ ተቀምጦ ለእያንዳንዱ የፖለቲካ ጥያቄ መልስ ይሰጣል ማለት አይደለም።

በቅርቡ የኦሮሞ ልህቃን አሜሪካ ሴያትል ውስጥ ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ ኑና የአገራችንን  ችግር በጋራ የምንፈታበትን መንገድ እንፈልግ የሚል ጥሪ ኦሮሞ ላልሆኑ ኢትዮጵያዊያን አቅርበዋል። በኔ የፖለቲካ ህይወት ዉስጥ የኦሮሞ ልህቃን ስብሰባ ተቀምጠው ለሌላው ኢትዮጵያዊ የአገራችንን የኢትዮጵያን ችግር አንድ ላይ ለመፍታት እንወያይ የሚል ጥሪ ሲያቀርቡ የሴያትሉ ጥሪ የመጀመሪያው ነው። ይህንን በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነውንና የ“አገራችንን” የሚል ቁልፍ ቃል ያለበት ጥሪ ተቀብለን፣ የአገራችንን ችግሮች ወደሚፈታና ወደ ዋናው ውይይት ወደሚወስደን የመጀመሪያ ምዕራፍ የውይይት ሂደት ውስጥ መግባትና መፈታተሽ ነው ያለብን እንጂ፣ያንን ባለፉት ሃምሳ አመታት የሰለቸንን የቃላት ቦምብ መወራወር ለምንም ለማንም የሚበጅ አይመስለኝም። እውነቱን እንነጋገር ከተባለ እኛ እራሳችንን የ”አንድነት ኃይሎች” ብለን የምንጠራ ኢትዮጵያዊያን የኦሮሞ ልህቃን የሚያደርጉትን ጥሪ ጆር ዳባ ልበስ ብለን የኢትዮጵያን ችግሮች ከማን ጋር ሆነን ነው የምንፈታው? ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ቁጥሩ ከ130 ሚሊዮን በላይ እንደሆነ የሚነገረው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በኢትዮጵያ ችግሮች ላይ ተቀምጦ መወያየት የሚችልበት ሁኔታ በፍጹም እንደሌለ የታወቀ ነው፣በሌላ በኩል ደሞ፣ የኢትዮጵያን ችግሮች የኦሮሞ ልህቃን በሌሉበት መድረከ ላይ በፍጹም መፍታት እንደማይቻልም መታወቅ አለበት። ስለዚህ በኔ ዕምነት የኦሮሞ ልህቃን ያቀረቡትን ጥሪ ሃቀኝነት የምናውቀው ጥሪውን ተቀብለን በምናደርገው የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ውይይት ላይ ነው እንጂ፣ጥሪውን ባቀረበው ስብስብ ውስጥ የሚገኙትን ሰዎች የቀድሞ ታሪክ በመዘርዘር አይደለም። አሁንም እውነቱን ለመናገር የትናንት እና የትናንት ወዲያ ፋይላችን ተከፍቶ ከታየ ሁላችንም ጥቁር ነጥብ ብቻ ሳይሆን ብዙ ጥቁር ነጠብጣቦች ያሉብን ሰዎች ነን። እኔ ማንንም አንጠራጠር የመጣውን ሁሉ እንዳለ እንቀበል እያልኩ አይደለም። የኔ ትልቁ ነጥብ የሚደረጉልንን የእንወያይ ጥሪዎች ሁሉ በጥርጣሬ  አንቀበልም ብለን ውድቅ ከማድረግ፣ እንወያይ ካሉን አካላት ጋር በቀጥታ ወይም ቀጥታ ባልሆነ መንገድም(Formally or Informally) ቁጭ ብለን ሃሳብ ከተለዋወጥን በኋላ ነው በውይይቱ ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል መወሰን ያለብን የሚል  ነው። 

ለምሳሌ፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት ዳያስፖራው ወኪሎቹን ይላክና መጥታችሁ እንወያይ ብሎ  ለዳያስፖራው ጥያቄ ቢያቀርብ፣ የዳያስፖራው መልስ መሆን ያለበት የውይይቱ አላማ ምንድነው? ማነው የውይይቱን አጀንዳ የሚቀርጸው? የት ነው የምንወያየው? ማነው ውይይቱን የሚመራው ነው መሆን ያለበት እንጂ፣ ከአቢይ አህመድ ጋር መወያየት ግዜ ማጥፋት ነው የሚል መልስ በፍጹም መመለስ ያለብን አይመስለኝም። አቢይ አህመድ አዲስ አበባ መጥታችሁ እንወያይ ቢለን መልሳችን አዲስ አበባ ከመምጣታችን በፊት እዚሁ አሜሪካ ወይም አውሮፓ ውስጥ ተገናኝተን እንወያይና የአዲስ አበባውን ውይይት እናመቻች የሚል መልስ ነው መመለስ ያለብን እንጂ፣ ዞር በል ካንተ ጋር አንወያይም የሚል መልስ መመለስ ያለብን አይመስለኝም። 

ኢትዮጵያ ዉስጥ የፖለቲካ ልዩነቶችን ወይም ችግሮችን ሁሉ በጉልበት ወይም በመሳሪያ ኃይል ብቻ እፈታለሁ ማለት ኋላ ቀርነት ወይም አይን ያወጣ ድንቁርና ነው ብዬ በድፍረት ስናገር፣መልዕክቴ በሥልጣን ላይ ላለው ለጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት መሆኑ በግልጽ መታወቅ አለበት፣ምክንያቱም ዛሬ በግልጽ እንደምናየው ጉልበትን እንደብቸኛ አማራጭ የወሰደው የአቢይ አህመድ መንግስት ነው። ለምሳሌ፣ አማራ ክልል የሚካሄደውን የመሳሪያ ትግል ብንመለከት፣ የፋኖ ኃይሎች የአማራን ህዝብ ህልውና ለማረጋገጥ ተጎትተው የገቡበት ጦርነት ነው እንጂ እነሱ የጀመሩት ጦርነት አይደለም። 

ኢትዮጵያ ዉስጥ በፌዴራሉ መንግስትና በፋኖ፣በህወሓትና በሸኔ ኃይሎች መካከል ድርድር እንጂ ጦርነት አያዋጣም የሚል መልዕክት አዲስ አበባ ውስጥ ካለው የአሜሪካ ኤምባሲና ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት በተደጋጋሚ ተደምጧል። ከልቡ ስላምና መረጋጋት ፈልጎ ይሁን ወይም ግዜ ለመግዛት በውል የሚታወቅ ነገር ባይኖርም፣ የጠሚ አቢይ አህመድ መንግስትም ከፋኖና ከሸኔ ኃይሎች ጋር የእንደራደር ጥሪ አቅርቧል። ጠሚ አቢይ አህመድ በፍጹም የማይታመን ሙልጭልጭ ሰው መሆኑን ከርቀት ሳይሆን በቅርብ የማውቅ ሰው ነኝ፣ሆኖም ይህ ሰው አደባባይ ወጥቶ እንደራደር/እንወያይ ብሎ ጥያቄ ሲያቀርብና፣ የጦር መሳሪያ፣የዲፕሎማሲና የፋይናንስ ጡንቻ ያለው የአሜሪካ መንግስትም ተደራደሩ ብሎ ሲወተውት፣ መልሳችን መሆን ያለበት አቢይ አይታመንምና አንወያይም የሚል ደረቅ መልስ ሳይሆን፣ ገለልተኛ አገር ላይ ገለልተኛ የሆነ አደራዳሪ አካል ፈልገን እንደራደር የሚልና ከምንም ነገር በላይ ለውይይትና ለድርድር ቅድሚያ እንደምንሰጥ የሚያሳይ መልስ ነው መሆን ያለበት። 

የፋኖ፣የሸኔና የህወሓት ኃይሎች ከአቢይ አህመድ መንግስት ጋር የሚደራደሩ ከሆነ፣ድርድሩ ማተኮር ያለበት ጦርነቱን ለማቆም ብቻ መሆን የለበትም። የፋኖ፣የሸኔና የህወሓት ኃይሎች የአቢይ አህመድ መንግስት ጦርነቱን ከማቆም ባሻገር፣ የወደፊቷ ኢትዮጵያ ምን መምሰል አለባት በሚሉ ትላልቅ ጉዳዮች  ላይ የሚወያይና ውሳኔ የሚያሳልፍ አገራዊ መድረክ እንዴት መፈጠር እንዳለበትም መወያየትና መደራደር አለባቸው፣ ከዚህ በተጨማሪ ከጠሚ አቢይ አህመድ መንግስት በኋላ የሚመጣው መንግስት ምን አይነት መንግስት እንደሆነና፣ይህ መንግስት እንዴት ወደ ሥልጣን መምጣት እንዳለበት ተደራድረው ግልፅ አቋም መያዝ አለባቸው። ለምሳሌ፣ የሽግግር መንግስት የሚፈጠር ከሆነ፣የሽግግሩ መንግስት አባላት እነማን እንደሆኑና በምን መመዘኛ እንደሚመረጡ፣የሽግግሩ መንግስት ምን አይነት ስራዎችን እንደሚሰራ፣እንዴት ውሳኔ እንደሚወስንና ለምን ያክል ግዜ እንደሚቆይ በግልጽ መታወቅ አለበት። ኢትዮጵያ ባለፉት ሃምሳ አመታት ቀይ ሽብርን የመሰለ አሰቃቂ ወንጀል፣ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣የዘር ማጽዳት ወንጀልና የጦር ወንጀሎች የተፈጸሙባት አገር ናት። ይህንን የሃዘንና የሰቆቃ ታሪካችንን በሽግግር ግዜ ፍትህ መዝጋት አስፈላጊ ስለሆነ፣ከአቢይ አህመድ መንግስት ወደሚቀጥለው በቀጥታ በህዝብ ወደሚመረጥ መንግስት የሚደረገው ሽግግር በሽግግር ግዜ ፍትህ መታጀብ ይኖርበታል። እነዚህን ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች አስበን፣ተግባብተን፣ተደማምጠንና ተከባብረን በጋራ ከሰራን ብቻ ነው ኢትዮጵያን ከመበታተን አድነንና የትልቅነት ታሪኳን አድሰን ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ የምንችለው!

_

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡

ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ  

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

1 COMMENT

  1. ውድ ወንድሜ አቶ ኤፍሬም ማዴቦ የምትጽፋቸው ጽሁፎች ሎጂካቸው በፍጹም አይገባኝም። ካርል ማርክስ እንደሚለው ነገሮችን በጭንቅላታቸው እያቆምክና ከዚያ በመነሳት ነው የምትጽፈው። የምትጽፋቸው ነገሮች በሙሉ የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታዎች በፍጹም የሚያንፀባርቁ አይደሉም። ርስ በርሳቸውም የሚጋጩ ናቸው። የተደቀነብን የህልውና አደጋ ከውጭ የመጣ ሳይሆን፣ ወይም የማይታይና የማይዳሰስ ሳይሆን፣ የህልውናችን አደጋዎች ራሱ ፋሺሽቱ የአቢይ አህመድ አገዛዝ፣ በውጭ ኃይሎች የሚጠመዘዘው ያረጀውና የበሰበሰው የህውሃት ስብስብ፣ ኦነግ ሸኔ የሚባለው በራሱ በአቢይ አህመድ የተቋቋመውና፣ መርሲነሪዎችን በሚያሰለጥነውና ኃይልን በሚከፋፍለው ከሲአይኤ ጋር በመተባበር የሚሰራውና ከአሜሪካን መንግስትም ድጋፍ የሚያገኘውና ኮንትራትም የሚሰጠው በብላከ ወተር በሚባለው የአሜሪካን ድርጅት የሚደገፈው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይልና፣ በሌሎችም ለአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ባደሩ ቅጥረኛ ኃይሎች ነው። የኦሮሞ ልሂቃን ብለህ ያቀረብካቸውም እነ ጃዋር መሀመድ፣ በቀለ ገርባና ሌሎችም በሙሉ ምንም ዐይነት የፖለቲካ ቲዎሪና የፍልስፍና መሰረትና ግልጽነት ሳይኖራቸው የኦሮሞ ብሄረሰብ ተጨቁኖ ነበር በማለትና የኦሮሞ ብሄረሰብ የሚባለውን ሽፋን በማድረግ ስልጣን ላይ ብቻ ለመውጣት የሚቅበዘበዙ ስብስቦች ናቸው። ራሳቸውም የውጭ ቅጥረኛ ኃይሎችና በዚያም የሚተዳደሩ ናቸው። አንዳቸውም እየሰራ የሚተዳደርና የሚንቀሳቀስ አይደለም። የአቢይን የሰሞኑን ፉከራ በደንብ ተከታትለህ እንደሆን በደም የተቀባባን ስለሆን ስልጣኔን ብለቅ አንድ ነገር ስለምሆን እንፋጃታለን እንጂ በምንም ዐይነት ስልጣኔን በፍላጎት አልለቅም እያለ ነው የዛተው። በአጠቃላይ ሲታይ ከአብዮቱ መፈንዳት ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሂደት ወይም እንቅስቃሴ በሚገባ ተከታትለህ እንደሆን በጣም ጥቂት ካልሆኑ በስተቀር የፖለቲካ ተዋናይ ነኝ ብለው የሚንቀሳቀሱት በተለይም በግንባር ቀደምትነት ከሚታወቁት ውስጥ የተወሰኑ ኃይሎች የማሰብ ኃይል የሌላቸው ናቸውም። ራሳቸውንም ወደ ውስጥ ለመመልከት የማይችሉና የሚሰሩትንም የሚያውቁ ያልነበሩ ናቸው። ለማሰብና ለመጠየቅ፣ እንዲሁም ድርጊታቸውን ለማረም የሚችሉ አልነበሩም። አብዮቱም ሊከሽፍ የቻለውና እንደዚያም ዐይነት እጅግ የሚዘገንን ደም መፋሰስ ሊከሰት የቻለው እኛ ብቻችንን ስልጣን ላይ ካልወጣን እንሞታለን ብለው በሚቅበዘበዙ ኃይሎች ምክንያት ነው። እነዚህም ኃይሎች በአሜሪካ የስለላ ድርጅት የሚደገፉና ቦዘኔውን በማስታጠቅ የከተማ ውስጥ የሽብር ትግል እንዲካሄድ ያደረጉ ናቸው። በዚህም ምክንያት የተነሳ ለአገራችን ሰላምና ዕድገት አስተዋፅዖ ሊያበርክቱ ይችሉ የነበሩ ግንባር ቀደም ታጋይ ምሁራን፣ የሰራተኛውና የገበሬው ማህበር መሪዎች እየተመረጡ ሊገደሉ ችለዋል። የፖለቲካ ካድሬዎችም የማርክሲስት ሌኒንስት የጥናት ቤተመጻህፍት ውስጥ በማጥናት ላይ በነበሩበት ጊዜ ተገድለዋል፤ መጻህፍቶችም ተቃጥለዋል። ይህንን ሁሉ ያደርጉ የነበሩት ደግሞ ራሳቸው ማርክሲስት ሌኒስት ነን ይሉ የነበሩ የግራን ስም ያንጠለጠሉ አንዳንድ ድርጅቶች ናቸው። ይህ ዐይነቱ የጨቅላ ትግል ደርግን ስላንበረገገውና ስላስቆጣው፣ እንዲሁም ሆን ተብሎ በደርግ ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር በመደረጉ የተወሰነው የደርግ ክፍል በቁጣ ኃይል በመነሳትና በደመ-ነፍስ በመመራት እሱም ዘግናኝ ድርጊቶችን መፈፀም ጀመረ። ባጭሩ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ውስብስነት ስንመለከት አንዳችም ድርጅት ጭንቅላቱ የበሰለና አርቆ የሚያስብ ኃይል ያለው የለም። ሁሉም ስልጣን ላይ ካልወጣሁ ብሎ የሚቅበዘበዝና ትርምስም ለመፍጠር የሚታገል ነው። ሁሉም በፖለቲካ ውስጥ እንሳተፋለን የሚሉና፣ የብልጽግናና የህወሃት ሰዎች፣ እንዲሁም የኦሮሞ ልሂቃን ተብለው የሚጠሩት በሙሉ ከሳይንሳዊ ዕውቀት የራቁና ሳይንሳዊ ትንተናም ለመስጠት የሚችሉ አይደሉም። መንፈሳቸው ውስጥ ምንም ነገር የለም። ሰው መሆናቸውን የሚገነዘቡ አይደሉም። ለምንና ለማን እንደሚታገሉ የሚያውቁት ነገር የለም። ሰለሆነም ካለምንም ፍልስፍናና ርዕይ እዚህና እዚያ የሚራወጡ ናቸው። እንደነዚህ ዐይነት ሰዎች ስልጣን ላስ ሲወጡ፣ እንዳረጋገጥነውም አረመኒያዊ ባህሪያቸውን በግልጽ ያሳያሉ። ህዝብን ከድህነት ከማላቀቅ ይልቅ የባሰ ደሃ ያደርጉታል። ምንም የማይገባቸውን የኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ በማድረግ ሀብትን ያዘርፋሉ፤ በዚያውም አንድን አገርና ህዝብ ያራቁቱታል። ይህ ሁሉ ነገር ባለፉት 35 ዓመታት የተረጋገጠና ህዝባችንም የሚኖርበት ነው። ስለሆነም ጭንቅላት በትክክል ካልታነፀና በሳይንሳዊ ዕውቀት ካልዳበረ አንድ አገር ታሪክ የሚሰራበት ከመሆን ይልቅ ወደ ጦርነት አውድማነት ይለወጣል። የአንድን አገርና ህዝብ ችግር ለመፍታት ደግሞ የግዴታ ሳይንሳዊ ዕውቀት፣ በተለይም የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዕውቀት ያስፈልጋል። ሌሎችም አንድን ህዝብ ሊያሰባስቡና እንደሰው ሊያኖሩት የሚችሉት መሰረታዊ ነገሮች በሙሉ ለፖለቲካ እንታገላለን በሚሉት ድርጅቶችና ግለሰቦች በሙሉ ተጠንተውና ተጽፈው ለክርክር መቅረብ አለባቸው። አንድም ህዝብ የሚፈልገው በፖለቲካ ስም የሚመጻደቁ፣ ይህንን ወይም ያኛውን ስም የያዙ እንዲፈራረቁበት ሳይሆን፣ ዕውነተኛ ነፃነትን የሚያጎናፅፉትንና በሰላምም እንዲኖር የሚያድርጉትን ኃይሎች ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተና ለሰፊው ህዝብ በቂ የስራ መስክ ሊከፍት የሚችል የኢኮኖሚ ፖሊሲ መንደፍና ተግባራዊ ማድረግ በጣም ወሳኝ ነው። ከዚህ አጭር ገለጻ ስንነሳ ስልጣን ላይ ያለውም ሆነ ከስልጣን ውጭ ያሉት በሙሉ እንደ አማራጭ ሊቀርቡ የሚችሉ አይደሉም። በእነሱ መሀከልም የሚደረገው ውይይት በምንም ዐይነት ለኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምን ሊያስፍንለትና ነፃነትንም ሊያጎናጽፈው በፍጹም አይችልም። የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድል ከእነዚህ ዝቃጭና የበሰበሱ ኃይሎች ውጭ መታየት አለበት። የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሰው በሚያስቡና፣ ታሪካዊ ኃላፊነትም በሚሰማቸውና በምንም ዐይነት ለውጭ ኃይሎች በማያጎበድዱ መመራት አለበት። ሊያነቀት፣ ሊያስተምሩትና ሊያደራጁት በሚችሉ ሰፋ ያለና የጠለቀ ዕውቀት ባለቸው መመራት አለበት። ይህ ሲሆን ብቻ ነው በአገራችን ምድር እያንዳንዱ ዜጋ ሙሉ ነፃነትን ሊቀዳጅ የሚችለው። እያንዳንዱም ሰው ከዚኸኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረሰብ የመጣሁ ነኝ በማለት የሚጨቃጨቅበት መድረክ መዘጋትና እያንዳንዱም ሰው እንደሰው መታየት ያለበት ስርዓት መቋቋም አለበት። ለዚህ ደግሞ በአገሪት ውስጥ በሙሉ ሰፋ ያለ የመማሪያ ተቋም መገንባት አለበት። እዚህ ላይ በፋኖዎች የሚደረገው እንቅስቃሴ መደገፍ ያለበትና እንደ አማራጭም መታየት ያለበት ሲሆን፣ አንዳንዶች በመሀክል እየገቡ የከፋፋይነት ስራ የሚሰሩ መቆጠብ አለባቸው። ወንድም በወንድሙ ላይ መነሳት የለበትም። በተለይም ከአማራው ብሄረሰብ የወጡና አርቀው ማሰብ የማይችሉ አንዳንድ ግለሰቦች ችግር እንደሚፈጥሩ የታወቀ ነው። እነዚህ ግለሰቦች ማሰብ ያለባቸው የጠቅላላው ህዝብ ዕድልና የተከታታዩን ትውልድ ዕጣ ነው። አንድ ቦታ ላይ በሚሰራ ስህተት ተከታታዩ ትውልድ ስቃይ ውስጥ ይገባል። እፎይም ብሎ እንዳይኖር ይደረጋል። ስለሆነም ቶሎ ብሎ ከመቆጣት፣ መሳሪያ ከመቀሰርና ከመፎከር መታቀብ አስፈላጊ ነው። የፖለቲካ ትግል አርቆ አሳቢነትን የሚጠይቅ ነው። ለዚህም ደግሞ ተከታታይ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል። ራስን በዕውቀት ማነፅ ያስፈልጋል።
    ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ
    http://www.fekadubekele.com

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News