Homeአበይት ዜናጋዜጣዊ መግለጫየዐማራ ዲያስፖራ ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የአቋምና ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ መግለጫ

የዐማራ ዲያስፖራ ሁለተኛ ዓለም አቀፍ ጉባኤ የአቋምና ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ መግለጫ

Advertisement
World Wide Travel Group

  መግቢያ 

እኛ በዓለም ዙሪያ የምንገኝ ከተለያዩ የዐማራ ማህበራት ፣ምሁራን ፣የፖለቲካ አንቂዎች ፣ የሚዲያ ተቋማትና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት የተውጣጣን የዐማራ ዲያስፖራ አባላት እ.አ.አ ኦገስት 16 ቀን 2025 በአርሊንግተን ቨርጂኒያ ዩናይትድ ስቴትስ ተሰብሰበን በዐማራው የህልውና ትግል ባለፉት ሁለት ዓመታት በተገኙ ድሎች ፣ባጋጠሙ መሰናክሎችና የትግሉን የወደፊት አቅጣጫ በተለይም የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ በሆነው የዐማራው ህብረት መመሥረትና መጠናከርን በተመለከተ ሰፊ ውይይት አድርገናል። የወቅቱን የኢትዮጵያን ፣ የአካባቢውንና ዓለም አቀፍ ሁኔታዎች በዐማራው ትግል ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ ጥልቅ ግምገማ አካሂደናል። በተጨማሪም እ.አ.አ ከኦክቶበር 19 -20 ቀን 2024 በስፕሪንግፊልድ ቨርጂኒያ ተካሂዶ በነበረው የዐማራ ዲያስፖራ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተወሰነው መሰረት የዐማራ ዲያስፖራ ግሎባል ፎረም ባከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ የቀረበውን ሪፖርት አዳምጠን ውይይት በማካሄድ የሚከተለውን የአቋም መግለጫና የቀጣይ ድርጊቶች መርሃ ግብር አውጥተናል። 

1. የዐማራ የህልውና ትግል ዓላማና መርሆዎች  

የዐማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ሃገረ- መንግሥት ምሥረታና ነፃ አገር ሆኖ ለዘመናት መቀጠል ፣ ለሥልጣኔና አኩሪ ባህል መስፋፋት ግንባር ቀደም አስተዋፅዖ ያደረገና ከሌሎች የአገሪቱ ነገዶች ጋር በወንድማማችነትና በሰላም ለዘመናት የኖረ ነው። እውነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ከአለፉት አርባ አመታት በላይ በዐማራው ላይ የሃሰት ትርክትን በማራመድ በማንነቱ ላይ ተመርኩዞ የዘር ማጥፋት (Genocide) የተፈፀመበትና አሁንም እየተፈፀመበት የሚገኝ ፣ ከአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ህይዎት እንዲገለል ተደርጎ ለመፈናቀል መሰደድና እስር የተዳረገ፤ አፅመ እርስቱን፣ሃብቱንና ንብረቱን እየተቀማ ሰብአዊ ክብሩንና መሰረታዊ የዜግነት መብቱን በሆነ የተገፈፈ ሲሆን፤ በተለይም አሁን በሥልጣን ላይ ባለው የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ በአዋጅ ጦርነት ተከፍቶበት ጭፍጨፋ እየተካሄደበት ይገኛል።በመሆኑም፣ እየተካሄደ ያለው የዐማራው የህልውና ትግል ይህን የጥፋት አደጋ በመመከት፣ ሰብአዊ ክብሩንና ህልውናውን ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም የተነጠቀውን መብትና ጥቅም ለማስመለስ የሚደረግ ፍትሃዊ፣ ህጋዊ፣ ታሪካዊና አማራጭ የሌለው ትግል ነው።  

የዐማራው ትግል ተቀዳሚ ዓላማ የተገፈፈ ሰብዓዊ መብቱን ማስከበር ፣የተጋረጠበትን የህልውና አደጋ መቀልበስና የተቀማውን ጥቅሙን ማስመለስና ማረጋገጥ ሲሆን፤ ይህም እውን የሚሆነውና ዘላቂነትም የሚኖረው፡ በወቅቱ በአገሪቱ እየተሰራበት ያለው በዘር ላይ የተመሰረተ ከፋፋይ ስርአትና ህገመንግሥት ከስሩ ተነቅሎ ሲወገድ ብቻ ነው።ይህንም ለማሳካትና በኢትዮጵያም፤ ዘላቂ ሰላም፤ ፍትህ፡ እኩልነትና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ፡ ዐማራው ተመሳሳይ አላማ ካላቸው ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ ጋር ተባብሮ ይቆማል።  

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

2. የፋኖን እንቅስቃሴ በተመለከተ  

የዐማራውም ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ታሪክ እንደሚያረጋግጠው ፋኖ የህዝብንና የአገርን ክብርና ነፃነት ለማስጠበቅ የቆመና ይህንኑም በተግባር ያስመሰከረ፤ የሁሉንም እውቅናና አክብሮት ያገኜ ህዝባዊ ሃይል ነው። በአሁኑ ወቅትም በዐማራው ላይ የሚካሄደውን ስርአታዊ የዘር ማጥፋት ዘመቻ: መገፋትና መከራ ለመከላከልና ህልውናን ለማስጠበቅ የሚካሄደው የመላው ዐማራ ትግል ግንባር ቀደም መሪ ነው። ይህንኑ ታሪካዊና ህዝባዊ ሃላፊነት ለመወጣት፡ ፋኖ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ራሱን አደራጅቶ፡ አሰልጥኖና አስታጥቆ እጅግ ግዙፍና አስተማማኝ ሃይል በመገንባት በጦር ሜዳ በኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ ሰራዊት ላይ ከፍተኛ ድል እየተጎናፀፈ ይገኛል። ይህ የፋኖ ድል፡ ለበርካታ አመታት አንገቱን ደፍቶ ግፍና በደል ሲቀበል የነበረው የዐማራ ህዝብ ቀና ብሎ እንዲሄድ ያስቻለው ሲሆን፡ ትግሉን በድል ለመቋጨትና ዘረኛውን ሥርአትም በመገርሰስ የዐማራውን ህልውናና መብት በአስተማማኝ ደረጃ ለማረጋግጥ ብሩህ ተስፋን የሚጥል ነው።  

በመሆኑም የፋኖ ትግል የመጨረሻ ግቡን እንዲመታ፡ የጠንካራ ድርጅታዊ ህብረትና ህዝባዊ የትግል መመሪያ አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አይደለም። ይሁን እንጂ፡ የፋኖ ሃይሎች አደረጃጀታቸውን እያሳደጉና እያሻሻሉ የመምጣታቸዉን ያህል ፣ በመርህና በህዝባዊ ተጠያቂነት ላይ ተመስርቶ በአንድነት የመስራቱ ሂደት በተገቢው ደረጃ እየተከናወነ ካለመሆኑም በላይ በተለይም በአንዳንድ አካባቢዎች የርስ በርስ የጎንዮሽ ውዝግቦች መታየታቸው አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ይህም በህብረት ቆሞና ሃይልን አስተባብሮ በአገዛዙና በስርአቱ ላይ በማተኮር ትግሉን በአጭር ጊዜ ዉስጥ በድል ለመቋጨት በሚደረገው ጥረት ላይአሉታዊ ተፅዕኖ ከማሳደር በላይ፡ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተነሱ ፀረ-ዐማራ ሃይሎችም ትግሉን እንዳይጠልፉትና የአገዛዙንም ሆነ የስርአቱን ዕድሜ በማራዘምና የዐማራውንም ተስፋ በማጨለም ለከፋ አደጋ እንዳያጋልጡት ያሰጋል።  

ስለሆነም፡ ሁሉም የፋኖ ሃይሎች በትግሉ ላይ ያንዣበበውን አደጋ በመገንዘብ በመካከላቸው ያሉትን መለስተኛ ልዩነቶች በዉይይት በማስወገድና ከሁሉም በላይ የህዝባቸውን ህልውና መከበር በማስቀደም በመርህ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ አንድነት በመርህ እንዲፈጥሩ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በዚህ ረገድ፡ በዐማራው ባህል መሰረት፡ በአባት አርበኞችና በዲያስፖራውም የፋኖን አንድነት ለማምጣት የዐማራ ምሁራንና ታዋቂ ግለሰቦች ለሚያደርጓቸው ጥረቶች ድጋፋችንን እየገለፅን ሁሉም የፋኖ ሃይሎች ከእነዚህ በጎ ጥረቶች ጋር እንዲተባበሩ በአፅንዖት እንጠይቃለን። 

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

3. ስለዐማራ ዲያስፖራ ድርሻና ግዴታ  

በዓለም ዙሪያ የሚገኘው የዐማራ ዲያስፖራ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ፣ የዕውቀትና የሃብት አቅምንም ያካበተ በመሆኑ ይህን ዕድል ተጠቅሞ የህልውና ትግሉ እንዲሳካ የማድረግ ታሪካዊና ህዝባዊ አደራ የተጣለበት ባለድርሻ አካል ነው። በዚህ ረገድ ዲያስፖራው ምንም እንኳን ያለውን አቅም የመጠነና የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም፤ በጥቂት ድርጅቶችና በተገቢው ደረጃ ባልተቀናጀ ሁኔታ በዐማራው ላይ እየተፈፀመ ያለውን ግፍ በዓለም አቀፍ ደረጃ በማጋለጥ የህልውና ትግሉ እንዲቀጣጠል በማድረግ በኩል አስተዋፅኦ ማድረጉ አይዘነጋም:  

ሆኖም፡ ከፋኖ የትጥቅ ትግል መጀመር በኋላ በዲያስፖራው ውስጥ የሚገኘው ዐማራ ቁጥራቸው በበዛና ጥቃቅን የሆኑ ልዩነቶችን በፈጠሩ ድርጅቶች ስር በመሰለፉ ለህልውና ትግሉ ሊሰጥ የሚገባውን የዲፕሎማሲና የገንዘብ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ ካለማድረጉም በላይ፡ ጎራን በመለየት መሬት ላይ ያለውን ትግል በሚከፋፍልና በሚጎዳ መልኩ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርግ ይታያል። ይህ ተግባር በታሪክ ፊት የሚያስወቅስና የህልውና ትግሉ ቢሰናከልም ሆነ አላስፈላጊ ዋጋ ቢያስከፍል የዲያስፖራው አባላትን ከቁጭት አልፎ በማህበረ ሰባችን ፊት ተጠያቂ የሚያደርግ ሁኔታ ነው። በመሆኑም፤ በዲያስፖራ የሚገኙ ድርጅቶች፡ የፖለቲካ አንቂዎች፡ ምሁራን፡ ታዋቂ ሰዎች፤ የሚድያው አካላት እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻዎች በሙሉ ቅንነትና ሃላፊነት በተሞላው መንፈስ በመነጋገር በአላማና መርህ ላይ የተመሰረተ አስቸኳይ ቅንጅት እንዲፈጥሩ ጥሪ እናቀርባለን። 

በዲያስፖራው የሚገኘው ዐማራ እንዲያከናውን ከሚጠበቁበት ቁልፍ ተግባራት መካከል የዐማራውን ህዝብ ሁኔታና የፋኖን እንቅስቃሴ ለዓለም ማህበረሰብ ማሳወቅ፤ በአገዛዙ ላይ ጫና እንዲደረግ ማስቻልና፤ ዐማራው እያካሄደ ያለው የህልውና ትግል እውቅናና ድጋፍ እንዲያገኝ ማድረግ ናቸው። በዚህ ረገድ፤ የተቀናጀና አመርቂ ሥራ ለመሥራት እንዲቻል፡ እ.አ.አ ኦገስት 9/2025 በተካሄደው ዓለም አቀፍ የዐማራ ዲፕሎማሲ በይነመረብ ጉባኤ የዐማራ ቀን በአለም አቀፍ ደረጃ በየአመቱ እንዲከበርና፤ የዐማራውን ትግልና መልሶ መቋቋም ለማገዝ ገንዘብ አሰባሳቢ አካል እንዲቋቋም ለተደረሰው ስምምነትና እነዚህንና ሌሎችን ተግባሮችን ለማስተባበር ለተሰየመው የዐማራ አለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ግብረሃይል ድጋፋችንን እየገለጽን፤ ሁሉም የዲያስፖራ አባላትና ባለድርሻ አካላትም ለዚሁ አንገብጋቢና ወቅታዊ እርምጃ ድጋፍና ትብብር እንዲያደርጉ እንጠይቃለን።  

- Advertisement -

4. የሚድያዎች ተግባርና ግዴታ  

በዐማራው ላይ በህወሃት ቀጥሎም በኦሮሙማው ዘረኛ አገዛዝ የተፈፀሙትን ግፎች በማጋለጥ መላው ህዝብ በቃ ብሎ እንዲነሳ እንዲደራጅና እንዲታገል በማነቃቃት ረገድ የዐማራ ሚድያዎችና የፖለቲካ አንቂዎች ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርገዋል፣ ሆኖም ፣ የትጥቅ ትግሉ ከተጀመረበትና ወሳኝ ደረጃ ላይ ከደረሰበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ፤ አብዛኛዎቹ ሚድያዎች ጎራ በመለየት ክፍፍልና የጎንዮሽ ውዝግብን በማራገብ የአፍራሽነት ሚናን በመጫዎት ላይ ይገኛሉ። ይህን አሉታዊ ድርጊት አስቁሞ፡ በትብብርና አግባብ ባለው ስነምግባር እንዲመራ ጥረቶች ቢደረጉም የተፈለገውን ዉጤት አላስገኙም። ትግሉ አሁን በደረሰበት ወሳኝና ውስብስብ ሁኔታ በሚድያው ዘርፍ እየታዩ ያሉ ችግሮች ሳይስተካከሉ በጎራ ተከፍሎ ውዝግብ የማራገቡ ተግባር ካልተገታ ዐማራውን ለበለጠ መከፋፈልና ለትግሉም አደጋ ላይ መውደቅ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ። በመሆኑም፡ ሁሉም ሚድያዎች፡ በመሬት ላይ ባሉ ሃይሎችም ሆነ በዲያስፖራው መካከል ክፍፍልን ከሚፈጥሩ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ጉባኤው አጥብቆ ጠይቋል::  የዲያስፖራው አባላትም የሚዲያዎቹን እንቅስቃሴ በቅርብ በመከታተል ተገቢውን ጫና እንዲያደርጉ እናሳስባለን።  

5. ስለ ወቅታዊው የኢትዮጵያ አሳሳቢ ሁኔታ  

በኢትዮጵያ በሥልጣን ላይ የሚገኘው የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ በሁሉም የአገሪቱ ማዕዘናት በተለይም በዐማራው ህዝብ ላይ ጦርነት አውጆ ህፃን፡ ሴት ሽማግሌ ሳይለይ ጭፍጨፋ እያካሄደ አገሪቷን ወደ ከፍተኛ ጥፋት እየወሰዳት ይገኛል። ባለፉት ሰባት አመታት፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ተገድለዋል፤ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፤ ለረሃብና ስደት ተጋልጠዋል። ብዙዎችም በአደገኛ የስደት ጉዞ ላይ ህይዎታቸውን አጥተዋል። በብዙ ሽህ የሚቆጠሩ በማንነታቸውና በፖለቲካ እምነታቸው የተነሳ ለአስክፊና አዋራጅ እስርና ሰቆቃ ተዳርገዋል። ወጣቱ ትውልድ ለጦርነትና ለስደት ተጋልጦ ስራ አጥነትና መንግስት መራሽ ወንጀል ተንሰራፍቷል። በአጠቃላይ፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ዉርደትና እንግልት ስር ወድቆ፤ ስለጦርነት፡ ወንጀል፡ ፍትህ መጓደል፡ ረሃብና ስደት ሲነሳ በምሳሌነት ተጠቃሽ ሆኗል። በተቃራኒው፡ የወቅቱ የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ፡ የአገሪቱን መጠነ ሰፊ ሃብት ተጠያቂነት በሌለው ሁኔታ ጠቀሜታ በሌላቸው የታይታ ፕሮጀክቶች ላይ እያጠፋ ለሙስናና የተበላሸ ገፅታውን ለመገንባት እያባከነ ነው::  

ኢትዮጵያንና ህዝቧን አዋርዶ ሃገራችንን መመለሻ ወደማይኖረው ፍፁም ቀውስ እየወሰደ የሚገኘው የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ ካለፉት 30 አመታት በላይ በህገመንግሥት ታውጆ በአገሪቷ የተንሰራፋው በዘር ላይ የተመሰረተው ከፋፋይ ስርአት ዉጤትና አራማጅ ነው። ይህ ስርአት ለጠንሳሾቹ ጥቂት የጎሣ መሪዎችና የቅርብ አጋሮቻቸው የስልጣንና ሃብት ምንጭ ሲሆን እንወክለዋለን ወይም ነፃ እናወጣዋለን ያሉትን ህዝብ፡ማለትም ቀደም ሲል የትግራይን አሁን ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ወይም በሰላምና ክብር እንዲኖሩ አላስቻሏቸውም ።በተቃራኒው ሁለቱንም ህዝብ በታሪካቸው አይተውት ለማያውቁት ውርደት፡ ጦርነትና ጥፋት፡ ጭፍጨፋ፡ ረሃብና፡ መፈናቀል ዳርጓቸዋል። ይኽው የአፓርታይድ ስርአት፡ ለረዥም ዘመናት በጋብቻና በትውልድ ተሳስረው በሰላምና በመከባበር ይኖሩ የነበሩትን ኢትዮጵያዊያን ለያይቶና በጠላትነት እንዲተያዩ አድርጎ አገራዊ የጋራ እሴቶችን በማጥፋት የህዝብን መከራ የአገርን ጥፋት እያፋጠነ የሚገኝ የጥቂት ወንጀለኞች ጥቅም አስጠባቂ መሆኑን በተግባር ያሳየ፡ የዐማራውም ሆነ የሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላት ነው። በመሆኑም፡ የዐማራውን ህልውና በዘላቂነት ለማረጋገጥ፤ የሌላውም የኢትዮጵያ ህዝብ አስከፊ ችግርና መከራ እንዲወገድ የኢትዮጵያም እንደ አገር መቀጠል እንዲረጋገጥ፡ዘረኛው ስርአት ከስር መሰረቱ ተነቅሎ መወገድ አለበት። ከዚያ ውጭ፡ የአሁኑን አገዛዝ በሌላ የዘር ፖለቲካ አራማጅ ሃይል መተካት ብቻውን የዐማራውን ህልውና ሊያረጋግጥ፡ በአገሪቷም የሚፈልገውን ዘላቂ ሰላም፡ ፍትህና የሁሉንም ህዝብ እኩልነት ዕውን ሊያደርግ አይችልም።  

6. ጂኦ– ፓለቲካዊ ሁኔታና የዐማራ ዲፕሎማሲ  

ኢትዮጵያ የምትገኝበት አካባቢና አጠቃላዩ አለም አቀፍ ሁኔታና የሃይል አሰላለፍ ተለዋዋጭነትን እያሳየ ነው። የኦሮሞ ብልፅግና አገዛዝ ሁሉም በሚባል ደረጃ ከኢትዮጵያ ጎረቤት አገሮች ጋር ያለው ግንኙነት አለመተማመንንና ዉጥረትን የፈጠረ: ሃገራችን በአፍሪካም፡ የነበራትን መሪ ሚና ያሳጣት ነው። በአለም አቀፍ ደረጃም፡ አገዛዙ የሚታወቀው በጠብ አጫሪነት፡ ጦርነት አራማጅነት፡ የህዝቡን መብትና ህልውና በመጣስና በሙስና ነው። በተለይም፡ በቀጠናውና በአጠቃላይም በአፍሪካና በዓለም ከፍተኛ ክብርና ተቀባይነት የነበራት ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት፡ የፈረሱ አገሮች (failed states) ተብለው በሚታወቁት ሳይቀር ግዛቶቿ ሲያዙ፤ ዜጎቿ ሲዋረዱ፤ ለእስርና የግፍ ሞት ሲዳረጉ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ ቀርቶ በይፋ ተቃውሞ ማሰማትና መንግስታዊ ሃላፊነትን ለመወጣት በማይችል ደካማ አገዛዝ ስር የወደቀች አገር ሆናለች። ይህም ሆኖ፡ በአፍሪካም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ በአገዛዙ ላይ የጎላ ተፅእኖ አልተደረገበትም።ለዚህም ዋናው ምክንያት የዐማራም ሆነ ሌላው ኢትዮጵያዊ ህዝብ የተቀናጀና ቀጣይነት ያለው የዲፕሎማሲ ስራ መሥራት ባለመቻላችው ነው። በዚህ ረገድ የዐማራውን ትግል የዲፕሎማሲና አድቮካሲ እንቅስቃሴ በተቀናጀ መልክ ለማካሄድ ኦገስት 9 ቀን 2025 ለተደረገው የዐማራ ዲያስፖራ የዲፕሎማሲና አድቮካሲ ቅንጅት ጉባኤና በዚሁ ወቅት ለተቋቋመው አለም አቀፍ አስተባባሪ ግብረሃይል ሙሉ ድጋፋችንን እየገለጽን፤ በዲያስፖራ የሚንቀሳቅሱ የዐማራ ድርጅቶች፤ ምሁራን፡ የፖለቲካ አንቂዎችና ባለድርሻ አካላት ሁሉ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ተባብረው እንዲሰሩ ጥሪ እናቀርባለን።  

7. ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ሃይሎች ጋር ተባብሮ ስለመስራት  

ለዐማራው ትግል ቀዳሚ መሠረት ጥለው የተሰውት ቀደምት መሪዎች እንዳስገነዘቡት፡ ዐማራው ከተጋረጠበት ዉስብስብና መጠነ ሰፊ ሰፊ የህልውና ጥፋት አደጋ በአሸናፊነት ሊወጣ የሚችለው በራሱ ሃይል፡ ተደራጅቶና ተባብሮ ሲታገል ብቻ ነው። ይህም፡ ባለፉት ሁለት አመታት በተገኙት ውጤቶች ተረጋግጧል። ይህ እውነታ እንደተጠበቀና ለዐማራው አንድነት መመስረት ቅድሚያ በመስጠት፡ የዐማራው ድል ዘላቂ የሚሆነው በሁሉም የአገሪቷ ህዝብ ተሳትፎ በኢትዮጵያ የሥርአት ለውጥ ሲመጣና በዜጎች እኩልነት፤ በፍትህና ተጠያቂነት መስፈንና በጋራ ተጠቃሚነት ሲረጋገጥ ነው። እነዚህን አላማዎች እውን ለማድረግም፡ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተባብሮ መቆምና መታገል ለነገ የማይባል አስፈላጊ ተግባር ነው። ከዚህ ዉጭ፡ በአማራው ህብረት ዙሪያ በሚታዩ ክፍተቶች ተደብቀው፡ ወደ ትግሉ ሰርጎ በመግባት አጋር የሆኑ መስለው የሚቀርቡ ባለፈው ድርጊታቸው ያልተፀፀቱና የጥገና ለውጥ በማምጣት አሁንም ዘረኛውን ስርዓት የማስቀጠልና ዐማራውን በድጋሜ በአጫፋሪነት ለማሰለፍ ከሚሞክሩ ሃይሎች መጠንቀቅ አስፈላጊ ነው። አሁን በሚታየው ነባራዊ የፖለቲካና የትግል አቅም አኳያ ይህንን ቁልፍ ሚና መጫወት አቅምና አመኔታን የገነባው የዐማራ ፋኖ መሆኑ ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት የማስተባበርና የመሪነት ሚና እንዲጫወት ተጨባጭ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። 

8. በቀጣይ የሚከናወኑ አጣዳፊ ተግባሮች. 

➢ የፋኖን አንድነት ለማመቻቸት በአባት አርበኞችና በዲያስፖራው ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች በመካሄድ ላይየሚገኙ ጥረቶችን ድጋፍ መስጠት፡ በመርህ እና በጋራ አጀንዳ ላይ ተመርኩዘው ሁሉም የአዐማራ ፋኖ ሃይሎች በትብብርና በአንድነት መንፈስ ትግሉን እንዲመሩት ማስቻል:  

➢ የዲያስፖራው አንድነት እንዲፈጠር ከሁሉም የዐማራ ድርጅቶችና ባለድርሻዎች ጋር ምክክር መቀጠል: በቅርቡ በተቋቋመው የዓለም አቀፍ ዐማራ ዲፕሎማሲ ግብረሃይል የሚከናወኑ ስራዎችን በትብብርና በመተጋገዝ መንፈስ መስራትና ዐማራው በአንድ የጋራ ድምፅ እንዲናገር ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ. 

➢ የዐማራ ፋኖ አመራር ስርዓታዊ ለውጥ እውን ለማድረግ ታሪካዊ አደራ ትከሻው ላይ የወደቀ መሆኑን በአፅንኦት በመገንዘብ በመላው ኢትዮጵያ ያሉ የለውጥ የፖለቲካ ሀይሎችን በማስተባበር የመሪነት ሚና እንዲጫወት ማስቻል፤ ለተግባራዊነቱም ተጨባጭ እርምጃዎችን መውሰድ. 

➢ የዐማራው ማህበረሰብ የደረሰበትን የኢኮኖሚ ቀውስ፣ የስራ አጥነት ችግር፣ የድህነት መንሰራፋትና የማህበራዊ አገልግሎት በጦርነት መውደም በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ: መልሶ ግንባታና የረጅም ጊዜ የልማትና የፅናት ስትራቴጂ ነድፎ በሂደት ወደ ስራ መግባት. 

➢ በሚዲያው የሚታየውን አፍራሽ ዝንባሌን በተመለከተ፤ የዐማራ ሚድያ አካላት ከውዝግብና ትግሉን ከሚጎዱ ተግባሮች ተቆጥበው በትግሉ የጋራ አጀንዳ ላይ በማተኮር የዐማራው ህዝብ በሚያደርገው ተጋድሎ አዎንታዊ ሚና እንዲኖራቸው ማበረታታትና ጠንካራ ግፊት ማድረግ።  

አንድነታችን ለህልውና ትግላችን ድል!  

ድል ለዐማራ ፋኖ፤ ድል ለዐማራ ህዝብ፤ ድል ለኢትዮጵያ!  

የዐማራ ዲያስፖራ ሁለተኛ አለም አቀፍ ጉባኤ አርሊንግተን / ቨርጅኒያ 

ዩናይትድ ስቴትስ 
ኦገስት 16 ቀን 2025

__

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ  

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News