
ቦርከና ደስክ
ለሁለት ሳምንት ገደማ ታፍነው የቆዩ ጋዜጠኞች ነጻ ቢወጡም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ጠይቋል።
ከሕግ አግባብ ውጪ የታፈኑት ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ እና ጋዜጠኛ አብዱሰመድ መሐመድ፤ ከሁለት ሳምንት ገደማ በኋላ ከስወራ ነጻ መውጣታቸውን ማኅበሩ አረጋግጧል። ጋዜጠኛ አብዱሰመድ ከ12 ቀናት በኋላ፤ ጋዜጠኛ ዮናስ ደግሞ ከ10 ቀናት ስወራ ነጻ ወጥተው ወደ ቤታቸውን ማኅበሩ ጠቁሟል።
ጋዜጠኞቹ ከስወራ ነጻ ወጥተው የተጠረጠሩበት ወንጀል ካለ በሕግ አግባብ እንዲዳኙ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር በመግጫ መጠየቁ ይታወሳል። ምንም እንኳን የተፈጸመው ሕገ ወጥ ድርጊት አሳሳቢ ቢሆንም፤ ጋዜጠኞቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከሚያስከትል ስወራ ነጻ መውጣታቸውን ለቤተሰቦቻቸው እፎይታ ተሰጥቷል ተብሏል።
ጋዜጠኞቹ ያሉበት በማይታወቅበት ሁኔታ ሁለት ሳምንት ገደማ ተሰውረው መቆየታቸው ሕገ ወጥ ተግባር በመሆኑ፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ማኅበሩ ጠይቋል።
ጋዜጠኞች የሚያስጠይቃቸው ወንጀል ቢፈጽሙ እንኳን በሕግ አግባብ ከመጠየቅ ይልቅ፤ ማፈን እና ማዋከብ ተቀባይነት የሌለው አካሄድ ነው ተብሏል። መሰል ድርጊቶች አንደ አገር የሚዲያ ምህዳሩን የሚያጠቡና የዜጎችን ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት የሚገድቡ ስለሆነ፤ ጋዜጠኞች የአገርና የሕዝብን ጥቅም መሰረት አድርገው በነጻነት እንዲሰሩ ባለድርሻ አካላት አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ተጠይቋል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ለጋዜጠኞች መብት ጥበቃ እና ለፕሬስ ነፃነት መጎልበት አዎንታዊ ኃላፊነቱን መወጣቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል።
የሪፖርተር ጋዜጣ አርታኢ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረም ነሐሴ 7/2017 ዓ.ም ምሽት ላይ ጭንብል በለበሱ ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ተይዞ መሰወሩ ይታወሳል። በተመሳሳይ በአሐዱ ራዲዮ የሚተላለፈው ቅዳሜ ገበያ ፕሮግራ አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱሰመድ መሐመድ ነሐሴ 5/2017 ዓ.ም ተይዞ ተሰውሮ ነበር።
ጋዜጠኞቹ በስወራ ነጻ የወጡት የኢትዮጵያ መገናኛ ባለሙያዎች ማኅበር፣ ፖለቲካ ፓርቲዎችና የተለያ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተቆርቋሪዎች የተቃውሞ ድምጽ ካሰሙ በኋላ ነው ተብሏል፡፡
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






