
ኢክናስ
መግለጫ

የኢክናስ ቦርድ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ የምክክር ኮሚሽን የቀረበውን የተሳትፎ ጥሪ ውድቅ ያደረገው ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ ነው። ኢክናስ ለቋሚ ሰላም፣ ፍትህ፣ እርቅና ደህንነት መርሆዎች በቁርጠኝነት የቆመ ቢሆንም፤ ተአማኒነት፣ ግልጽነት፤ተጠያቂነት እና የሞራል ታማኝነት በሚጎለው ሂደት ላይ መሳተፍም ሆነ ሂደቱን መደገፍ አይችልም፡፡
ዋና ዋና ስጋቶች
1. የዋና ዋና ባለድርሻ አካላት መገለል
የምክክር ኮሚሽኑ በአሁኑ ጊዜ እየቀጠለ ባለው ግጭት ውስጥ ያሉ ዋና ተዋናዮችን — በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች — ለማካተት አለመቻሉ የኮሚሽኑን ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዜጎች ለመፈናቀል፣ ለግፍ እና ለመሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጥ ተጋላጭ ቢሆኑም፤ ጩኸታቸው ሰሚ አላገኘም፤ ድምፃቸውም ተገቢው ውክልና አልተሰጠውም።
2. የምክክር ኮሚሽኑ ገለልተኝነትና ተአማኒነት ማጣት
የኮሚሽን አባላት የተሾሙበት መንገድ እና ከሕዝብ ጋር የተደረጉ ውይይቶች ይዘት፣ የምክክር ኮሚሽኑ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ፖለቲካዊ ቁርኝት እንዳለው በሰፊው ያሳያሉ። ይህም ግንኙነት የኮሚሽኑን
ገለልተኝነት በከፍተኛ ደረጃ አጠራጣሪ አድርጎታል። በመሆኑም ተአማኒነቱ አጠያያቂ በሆነበት ሁኔታ የምክክር ኮሚሽኑ የተጣለበትን ግዴታ በገለልተኝነት ያከናውናል ብሎ ማመን አይቻልም።
3. እየተፈፀሙ ያሉትን ግፍ መከራና በደል መፍትሄ ለመስጠት አለመቻል
ኮሚሽኑ በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የተካሄዱ የጅምላ ግድያዎች፣ የአየር ጥቃቶች እና ስልታዊ ጭቆናዎች መደረጋቸውን እውቅና አልሰጠም ወይም አላመነም። ይህ ዝምታ የነዚህ ማህበረሰቦች ሥቃይ ለኮሚሽኑ ግድ እንደማይሰጠው ወይም ተራ ጉዳይ አድርጎ እንደሚያየው ያመለክታል።
ኮሚሽኑ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች በስፋት እየተፈጸመ ያለውን ግፍና መከራ እውቅና ካለመስጠቱ በተጨማሪ፣ የታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና ገለልተኛ ድምፅ የሚያሰሙ ዜጎች እሥርና እንግልት መቀጠሉ፤ ኮሚሽኑ ውጤት ያለው ምክክር ለማካሄድ አለመቻሉን ወይም ፍቃደኝነት እንደሌለው በጉልሕ ያመለክታል፣ ይህም በኮሚሽኑ የእርቀሰላም መሪነት ሚና ላይ ሕዝቡ የሚኖረውን እምነት የበለጠ ሸርሽሮታል።
4. የሲቪል እና የሚዲያ ምህዳር መጣበብ
ለማንኛውም ተአማኒ ውይይት አስፈላጊ አጋሮች የሆኑት ገለልተኛ ሚዲያ፣ የህዝብ የፖለቲካ ተወካዮች፣ የሃይማኖት መሪዎች እና የሲቪል ማህበረሰብ አካላት ድምፃቸው ይታፈናል፣ ማስፈራርያ ይደርሳቸዋል፣ ታስረውም ይወነጀላሉ። እንደዚህ ያለ ወከባ እና ጭቆና አካታች እና በቅን መንፈስ የሚደረግ ተሳትፎን የማይቻል ያደርገዋል።
5. የስራ ቅደም ተከተል የሳተና ለታይታ የሚደረግ ተግባር
ግጭቶች በተፋፋሙበት ሁኔታ ውይይት መጀመር ክፍፍልን እና ልዩነትን ያባብሳል። እንደ ተኩስ ማቆም፣ የፖለቲካ እስረኞችን መፍታት እና ገለልተኛ አካላት ሂደቱን እንዲቆጣጠሩ ማድረግን የመሳሰሉ መተማመንን የሚገነቡ እርምጃዎች ካልተውሰዱ ሂደቱ እንደ እውነተኛ የእርቀሰላም መንገድ ሊታይ አይችልም።
አገራዊ ምክክሩ ጉዳይ ሆኖ የተከሰተው በየአካባቢው ያለው ቅሬታ እና በመንግሥት ላይ ያለው መከፋት በስፋት በሚታይበት፣ በመንግሥት የሚፈፀም ኢፍትሃዊነት እና ግፍ በሰፈነበት፣ ጭቆና በቀጠለበት እና በመንግሥት እና በዜጎች መካከል ያለው መተማመን በተመናመነበት ጊዜ ነው። የምክክር ኮሚሽኑ እነዚህ አጣዳፊ እውነታዎች ሳይገቱ ወይም እንዲፈቱ በመንግሥት ላይ ተፅእኖ ሳያደርግ ዳያስፖራውን ለማሳተፍ
መሞከሩ፣ የታሰበውን እርቀሰላም እንዲያሳልጥ እና ተጠያቂነትን እንዲያሰፍን የተሰጠውን ዋና ተልእኮ
መፈጸም አለመቻሉን በጉልህ ያሳያል። የመንግሥትን ግፍ ለመጋፈጥ ቸል ማለት፣ የተጎዱ ማህበረሰቦችን አለማካተት እና የሲቪል እና የሚዲያ ምህዳሩ ዋስትና እንዲያገኝ አለመቻል ኮሚሽኑ ግጭቶችን ከመፍታት ይልቅ የውይይት ምናብ በመፍጠር ላይ ያተኮረ እንዲመስል አድርጎታል።
መዝጊያ
ኢክናስ ለፍትህ እና ተጠያቂነት ያለው ቁርጠኝነት የማይናወጥ ነው። በመሆኑም ተጎጂዎችን የሚረሳ፣ ተቃውሞን የሚያፍን እና ወንጀል ፈጻሚዎችን ከመጠየቅ የሚከላከል ሂደት ቅቡልነት እንዲያገኝ ድጋፉን ሊሰጥ አይችልም። በአንጻሩ፣ ከአለም አቀፍ አጋሮች፣ ከሕዝባዊ ንቅናቄዎች እና ከተጎዱ ማህበረሰቦች ጋር ያለውን አጋርነት በማጠናከር በህዝብ ላይ የሚፈጸሙ በደሎች በአፋጣኝ እንዲቆሙ፣ የፖለቲካ እስረኞች ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ እና እውነተኛና ገለልተኛ የሆነ፣ ግልጽ የውይይት ማዕቀፍ እንዲፈጠር ጥረት ማድረጉን ይቀጥላል።
ኢትዮጵያ ተዳክማ በቋፍ ላይ ነች — እውነተኛ ምክክር እና ዕርቀሰላም በአፋጣኝ ትፈልጋለች።
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena





