
ሐሙስ ነሐሴ 29 ቀን 2017 ዓ/ም
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል የብልጽግና ባለስልጣናት በኤርትራ ላይ እያደረሱት ነው ያሉትን “ወታደራዊ ዛቻ” ቀጥለውበታል ሲሉ ሰሞኑን የብልጽግና ሰዎች ስለቀይ ባሕር ላደረጉት ንግግር አጸፋ ሰጥተዋል።
ባለስጣናቱን የወቀሱት ሚኒስትሩ በዚህም “በዘፈቀደ” ሲሉ በጠሩት አካሄድ የብልጽግና ሰዎች “ዛቻ” በኤርትራ ላይ መቀጠሉን በኤክስ ገጻቸው በይፋ አስታውቀዋል።
ሚኒስትር የማነ ገብረመስቀል ይህን ያስታወቁት ረቡዕ ነሐሴ 28 ቀን 2017 ዓ/ም ሲሆን፣ የብልጽግና ፓርቲ ባለስልጣናትና ”ተሳዳቢዎቻቸው” በኤርትራ ላይ “በዘፈቀደ” ያካሂዱታል ያሉትን “ወታደራዊ ዛቻ” ቀጥለውበታል ነው ያሉት።
ይህን ያሉት ለሰሞንኛው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ንግግር አጸፋ ለመስጠት እንደሆነ ያሳበቀባቸው ሚኒስትር የማነ፣ የብልጽግና ባለስልጣናት የኤርትራን ጥንታዊና ዘመናዊ ታሪክ ያዛባሉ ሲሉም ወንጅለዋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከማኀበራዊ ጉዳዮች አማካሪያቸው ዳንኤል ክብረት ጋር ሰሞኑን ባደረጉት “የጉባ ላይ ወግ” ቀይ ባሕር ከ30 ዓመት በፊት በኢትዮጵያ እጅ እንደነበር አስታውሰው፣ “ቀይ ባሕር ቀላል ነው” ሲሉ በቀላሉ መመለስ እንደሚቻል ገልጸው ነበር።
“ቀይ ባሕር የዛሬ 30 ዓመት በኢትዮጵያ እጅ ነበር፤ የተፈጠረው ስህተት የትናንትና ነው” ሲሉ የተደመጡት አቢይ፣ “ነገ ይታረማል፤ ብዙ ከባድ አይደለም” ነበር ያሉት።
የኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገ/መስቀል የብልጽግና ሰዎችን “ወታደራዊ ዛቻ” እያደረሱ ነው በሚል የወነጀሏቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ንግግር፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ሜጀር ጀነራል ተሾመ ገመቹም ከቀይ ባሕር ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ከተናገሩ በኋላ ነው።
ጀነራል ተሾመ ገመቹ፣ “ቀይ ባሕር እኛ ጋር ነበር፡፡ ቀይ ባሕር አሰብ ነው የነበረው፡፡ አሰብ ደግሞ ራስ ገዝ ነው የነበረው” በማለት ሰሞኑን ተናግረዋል።
“ብዙ ነገር ማለት ይቻላል፤ ወደ ሚዲያ ባናመጣውም እነኝህን ነገሮች በጓዳ በደንብ ማውራት ጀምረናል ከእነርሱ ጋራ” ሲሉም ተደምጠዋል።
የኢትዮጵያ ቀይ ባሕር ጉዳይ የመፈለግ ጉዳይ “የሕልውና ጉዳይ ሆኗል”፣ የህልውና ጉዳይ ደግሞ “ማንኛውም ዋጋ የሚከፈልበት ብሔራዊ ፍላጎት ነው” ያሉት ጀነራል ተሾመ፣ ቀይ ባሕርን አሳልፎ የሰጠው” የሽግግር መንግስት ነው፤ በሕዝብ ያልተመረጠ መንግስት ባሕር አሳልፎ የመስጠት መብት የለውም” ብለዋል።
ጀነራሉ፣ “አሰብ የኢትዮጵያ የቀይ ባህር ግዛት ነው” ብለው፣ “ብዙ ሀገራት ‘በእናንተ ድክመት ነው እስካሁን ያልተመለሰው እንጅ እስካሁን መቆየት ያልነበረበት ነው’ ይሉናል” ሲሉም ተደምጠዋል፡፡
የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የማነ ገብረ መስቀል በበኩላቸው፣ የብልጽግና ባለስልጣናት ንግግር የቀይ ባሕርን ጉዳይ ከሽግግር ፍትህ ጋር እንደሚያያዝ መናገራቸውን በተመለከተ በሰጡት አጸፋ፣ ኤርትራን በወረራ የያዘችው አገር በቅድሚያ ፍላጎቷ ሊጠየቅና ሕዝበ ውሳኔውን እንድትቀበል በቅድመ ሁኔታ የሚቀርብበት ሁኔታ ሊኖር እንደማይችልና እንዳልነበረ አስረድተዋል።
ኤርትራ እአአ ከ1940 ጀምሮ ነጻነቷን ለማግኘት መታገሏን የገለጹት የማነ፣ “ይህ በማንም ውድቅ የማይደረግ፣ የማንም ሌላ አገር ወይም ዓለም አቀፍ አካል ይሁንታ የማያስፈልገው ነው” ብለዋል።
ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ጽኑ ፍላጎት እንዳላት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ ካሳወቁ በኋላ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጨምር ጉዳዩን አጀንዳ ያደረጉት ሲሆን፣ ኤርትራና ኢትዮጵያ በጉዳዩ ዙሪያ አጸፋ ሲሰጣጡ ከመስተዋላቸውም ባሻገር ውጥረቱ አይሏል።
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






