
ሰኞ መስከረም 2 ቀን 2018 ዓ/ም
የጦር ኃይሎች ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ “2018 ትልቅ ትግል አለብን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ፊልድ ማርሻሉ ይህን ያሉት ለመላው ኢትዮጵያውያን፣ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት የ2018 አዲስ አመትን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሲያስተላላፉ መሆኑ ታውቋል፡፡
2018 ትልቅ ትግል አለብን” ያሉት ኢታማዦር ሹሙ፣ በኢትዮጵያ ይስተዋላሉ ያሏቸው ግጭቶች በውይይት መፈታት እንዳለባቸው፣ እስከዛሬ ግጭቶቹ ለመፍታት መሰናክል የሆነው “የውጭ ኃይል ” ሲሉ በጠሩት ጣልቃ ገብነት ሳቢያ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በተለይ በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች ለአመታት የዘለቀው ፊልድ ማርሻሉ “ግጭቶች” ሲሉ የጠሩት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን “ጦርነት” ሲሉ የሚደመድሙት የተኩስ ልውውጥ እስከሁን በውይይትና ድርድር ባለመፈታቱ የንጹሐን ሕይወት እየተቀጠፈ፣ ቤት ንብረት፣ መሰረት ልማት እየወደመ፣ ኢኮኖሚው እያሽቆለቆለ ቀጥሏል፡፡
ፊልድ ማርሻል ብርጃኑ ጁላ በበኩላቸው፣ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ያሉ ያሏቸውን “ግጭቶች” በውይይት ለመፍታት መሰናክል የሆነው የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ነው ሲሉ በሰሞንኛው መልዕክታቸው መናገራቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህም፣ “የውስጥ ግጭቶችን በውይይት መፍታት አለብን፤ እስካሁን ግጭቶቹን በውይይት ለመፍታት እንቅፋት የሆነው የውጪ እጅ መኖሩ ነው፡፡ ይህ የውጭ እጅ ደግሞ መቆረጥ አለበት መዋጋትም አለብን” ነው ያሉት፡፡
ይሁን እንጅ ኢታማዦር ሹሙ፣ “የውጭ ኃይሎች” ሲሉ የጠሯቸውና “እጃቸው መቆረጥ አለበት” ሲሉ የዛባቸውን አካላትን በግልጽ ይፋ አላደረጉም፡፡ ሆኖም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ለሚካሄደው የተኩስ ልውውጥ የኤርትራና የግብፅ እጅ አለበት ብሎ እንደሚያምን መከላከያ ከዚህ ቀደም በተዳጋጋሚ ሲናገር ተደምጦ ነበር፡፡
በአማራ ክልል ለሁለት ዓመታት የዘለቀው በፋኖ እና መከላከያ ሰራዊት መካከል የሚደረገው የተኩስ ልውውጥ በውይይትና ድርድር እንዲፈታ ያደርጋል የሚል ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የአማራ ክልል የሰላም ካውንስልም እስካሁን ተጨባጭ ውጤት እንዳላገኘ የገለጸ ሲሆን፣ ተኩሱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
በኦሮሚያ ክልል መንግስት “ሸኔ” ብሎ የሚለው ራሱን “የኦሮሞ ነጻ አውጭ ግንባር” ብሎ በሚጠራው ታጣቂ ቡድንና በመከላካያ መካከል ለዓመታት የተስተዋለው የተኩስ ልውውጥ ከዚህ ቀደም በውይይት ለመፍታት ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም ያለውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ታጣቂ ቡድኑ አሁንም በንጹሐን ላይ ጥቃት ማድረሱን እንዳላቆመ በየጊዜው የሚወጡ መረጃዎች የሚያመልካቱ ሲሆን፣ ከኦሮሚያ ክልል አልፎ እንደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ባሉ ቦታዎችም ጥቃቱን እያስፋፋ መምጣቱ ይነገራል፡፡
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






