• ያለፉት 48,929 ብቻ ሲሆኑ የትምህርት ሚኒስትሩ “ስንጠብቅ የነበረው ይህን ውጤት ነው” ብለዋል

ሰኞ መስከረም 5 ቀን 2018 ዓ/ም
በ2017 የትምህርት ዘመን የ12 ክፍል ፈተና ወሰዱ ከተባሉ 558 ሺሕ 893 ተማሪዎች መካከል 536 ሺሕ 964 የሚሆኑት ፈተናውን አለማለፋቸውን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የሚኒስቴሩ መረጃ እንደሚያሳው፣ ለፈተና ከተመዘገቡ 309 ሺሕ 547 የተፈጥሮ ሳይንስ እና 299 ሺሕ 041 የማህበራዊ ሳይንስ በድምሩ 608 ሺሕ 588 ተፈታኞች መካከል 297 ሺሕ 540 የሚሆኑት በተፈጥሮ ሳይንስ እንዲሁም 288 ሺሕ 353 ማህበራዊ ሳይንስ ሆነው በአጠቃላይ 585 ሺሕ 893 ተማሪዎች ለፈተና ተቀምጠው ነበር።
ከእነዚህ ለፈተና ተቀምጠዋል ከተባሉ 585 ሺሕ 893 ተፈታኞች መካከል ከ50 በመቶና ከዚያ ባላይ የሆነ ውጤት በማምጣት ያለፉት በተፈጥሮ ሳይንስ 11 ነጥብ 4 በመቶ፣ በማህበራዊ ሳይንስ ደግሞ 5 ነጥብ 2 በመቶ በድምሩ 8 ነጥብ 4 በመቶ ወይም 48 ሺሕ 929 ተማሪዎች መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ትላንት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
በሌላ አገላለጽ፣ ፈተናውን ወሰዱ ከተባሉ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ውስጥ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት ያመጡት 48 ሺሕ 929 ብቻ ሲሆኑ፣ 536 ሺሕ 964 ወይንም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ተማሪዎች ግን ወድቀዋል ማለት ነው፡፡
ፕሮፌሰር ብርሃኑ፣ በተያዘው ዓመትም የአቅም ማሻሻያ ወይም የሪሜዳል የትምህርት ፕሮግራም እንደሚሰጥ፣ ሆኖም ግን መግቢያው ከባለፈው ዓመት ከፍ እንደሚል አስታውቀው፣ “ዘንድሮ ሪሚዳል የሚሰጣቸው ተማሪዎች ቁጥር አልተወሰነም፣ ከ40 እስከ 50 በመቶ የሚለው በውይይት ላይ ነው” ብለዋል፡፡
የበርካታ ተማሪዎች ፈተናውን አለማለፍ በበርካቶች በኩል እንደ ትልቀ ውድቀት ተደርጎ እየጠቀሰ የሚገኝ ሲሆን፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ግን “ስንጠብቅ የነበረው ይህን ውጤት ነው፡፡ የፈተና ስርዓታችን ሊያመጣው የሚፈልገው ውጤት እየመጣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ መግቢያ ወጤት ያላመጡት “መኮራረጅን ማስቀረት ስለተቻለ ነው” በሚል የሚያምኑት ሚኒስትሩ፣ የፈተና ሥርዓት ውጤት “ትክክለኛው መስመር መሆኑን የተረዳንበት ነው” ብለዋል።
አክለውም፣ “ይህንን ሀገር የሚጠበቅበት ቦታ ለማድረስ የሚያበቃ ትውልድ እያፈራን ነው፡፡ በዚሁ እንዲቀጥል ነው የምንሰራው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
“ከ15 እስከ 20 በመቶ የሚሆን ተማሪ እንዲያልፍ ነው የምንሰራው፤ ሁለትና ሦስት ዓመታት ይፈጅብናል ግን እንደርስበታለን” ሲሉ በልበ ሙሉነት የተናገሩት ብርሃኑ፣ “ዘንድሮም ጥሩ ውጤት ነው የመጣው ነገር ግን የሚያኩራራ አይደለም፣ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የተሻለ ውጤት ይመጣል” በማለት በአንጻሩ ደግሞ ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል፣ በ2017 ዓ/ም የ12ኛ ክፍል ፈተና አስፈትነው ከፍተኛ ተማሪዎችን አሳለፉ ከተባሉ ክልሎች መካከል ከሁለት ዓመታት በላይ የጦር ሜዳ የሆነው አማራ ክልል በሦስተኛ ደረጃ ሲካተት፣ አዲስ አበባ አንደኛ ሀረሪ ክልል ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ረገድ ደግሞ፣ ከ500 በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች አጠቃላይ ብዛት 2 ሺሕ 384 ሲሆን፣ ይሄውም 2 ሺሕ 215 በተፈጥሮ ሳይንስ፣ 169 ደግሞ በማኅበራዊ ሳይንስ ነው ተብሏል።
ይሄው ከ500 በላይ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ብዛት በክልሎች ደረጃ ሲተመን ደግሞ በአዲስ አበባ 888፣ በኦሮሚያ 794፣ እንዲሁም በአማራ 385 መሆኑ ተመልክቷል።
እንዲሁም፣ በ2017 ዓ/ም የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ካስፈተኑ ትምህርት ቤቶች መካከል 1 ሺሕ 249 የሚሆኑት ምንም ተማሪ እንዳላሳለፉ፣ መቶ በመቶ ተማሪዎቻቸውን ያሳለፉትም 50 ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን ሚኒስትሩ አልሸሸጉም፡፡
በ2017 የትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎች፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ከዶዶላ ኢፋ ቦሩ ትምህርት ቤት 591 ከ600፣ እንዲሁም ከብስራተ ገብርኤል ትምህርት ቤት 579 ከ600 ሲሆን፣ በማህበራዊ ሳይንስ 562 ከአምቦ አዳሪ ትምህርት ቤትና 548 ከቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት መሆኑን ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
በ2016 የትምትርት ዘመን ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ከተቀመጡ 674 ሺሕ 823 ተማሪዎች መካከል ያለፉት 36 ሺሕ 409 መሆናቸው የሚታወስ ሲሆን፣ በትምህርት የሚወድቁ ተማሪዎች “ወደ ጦር አውድማ ይማገዳሉ” ወይም “ብርሃኑ ነጋ የጣለውን፣ ብርሃኑ ጁላ ያነሳዋል” የሚል ትችት በተደጋጋሚ ሲሰነዘር ይደመጣል።
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






