
ቦርከና ዜና
አርብ መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ/ም
የወለጋ ክፍለ ሀገር ፋኖ ዕዝ ወይም ቢዛሞ ተብሎ ሲጠራ የነበረው ኃይል የስም ስያሜውን ወደ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ቢዛሞ ዕዝ መቀየሩን ይፋ አድርጓል።
በዚህም የወለጋ ክፍለ ሀገር ፋኖ ዕዝ ወይም ቢዛሞ የስም ስያሜው ወደ አማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ቢዛሞ ዕዝ የቀየርን መሆኑን እያሳወቅን ሲልም ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
የቀድሞው “ቢዛሞ ዕዝ” የአሁኑ “አፋብኃ ቢዛሞ ዕዝ” የአማራን ህልውና ለማረጋገጥ በሚያደርገው ሁሉን አቀፍ ትግል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አፋብኃ በሚፈልገው መስመር ለመሰለፍ ዝግጁ ነኝ ብሏል።
የአማራ ህልውና የሚረጋገጠው ሁሉም ታጋይ በአንድ አታጋይ አማራዊ ድርጅት ስር ሆኖ ሲታገል እንደሆነ በፅጹ እንዲሚያምንም በመግለጫው አስፍሯል።
የ70 ሚሊዮን አማራን ህልውና ለማረጋገጥ የተመሰረተው የጋራ ቤታችን አፋብኃ ሌላኛው የቤቱ ግርግዳ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል ቢዛሞ ዕዝ መሆኑን እውቁልኝ ነው ብሏል።
“ለአንድነት ሲባል የምናስቀምጠው ቅድመ ሁኔታ የለም” ያለው ዕዙ፣ “ታሪካዊ ጠላቶቻችን አማራ የሚባል ጠላት በምናባቸው ፈጥረው እና ልብወለድ ፅፈው ላለፉት 50ና 60 ዓመታት አማራን ሲገድሉት ኖረዋል” በማለት ከሷል።
“ተረኛው ገዳይ” ሲል በጠራው ብልፅግና “ላለፉት 8 ዓመታት አማራ ላይ የሞት አዋጅ አውጆ ወገናችን ተጨፍጭፏል፤ ከጭፍጨፋ የተረፈው ለቀጣይ 40 ዓመታት እንዳያገግም ሁሉን አቀፍ ውድመት ደርሶበታል” ሲል ዕዙ በመግለጫው በብርቱ ወንጅሏል።
“በተለይ በወለጋ ክፍለ ሀገር የሚኖረው አማራ ላይ የደረሰው ግፍ ከአዕምሮ በላይ የሆነ የበደል ጥግ ነው” የአፋብኃ ቢዛሞ ዕዝ፣ “የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ባሉበት ዓለም አማራ ላይ የደረሰውን ስቃይ ሰበር ዜና ብለው መሞታችንን ከማረጋገጥ ባለፈ ምንም አለማድረጋቸውን ስናይ ለአማራ ሞት ይቺ ዓለም ተባባሪ ናት አስብሎናል” ሲልም ወቅሷል።
“አማራ ከፈጣሪ በታች መዳኛው ክንዱ ብቻ መሆኑን ባሳለፍናቸው አምስት ዓመታት” አስተውለናል ሲል ገልጾ፣ በወለጋ የሚኖረውን አማራ ከፈፅሞ መጥፋት ለመታደግ የወለጋ ክፍለ ሃገር ፋኖ ዕዝ ወይም ቢዛሞ ተደራጅቶ ዱር ቤቴ ከከተመ ሰነባብቷል በማለትም አስታውሷል።
ከመንግስት ጋር የተኩስ ትልግ እያደረገ የሚገኘው ፋኖ አደረጃጀቱ እርስ በእርሱ የተበታተነ ነው በሚል ብርቱ ትችት ሲሰነዘርበት መስተዋሉ ይታወሳል።
ሆኖም ፋኖ ግንቦት 1 ቀን 2017 ዓ/ም የአማራ ብሔራዊ ኃይል የሚል አደረጃጀት መሰረትኩ ካለ በኋላ ኃይሉን ወደ አንድ አደረጃጀት አመጣሁ ሲል በተደጋጋሚ እያሳወቀ ይገኛል።
_
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena







በስም ብዛት ቢሆን ይኸኔ አራት ኪሎ ገብተው ነበር።