
እነሆ ባሕርዳር ተከስተናል፡፡
ባሕር ዳር ከወትሮው በተለየ በሰው ወበቅ የታፈነች ትመስላለች፡፡ ዕለቱ ቅዳሜ ስለኾነ? ወይስ ከከተማዋ ዳርና ዳር ከሚንጣጣው የጥይት ድምፅ ለመሸሽ? ብቻ ለወትሮው ቱሪስት የሚርመሰመስባቸው ጎዳናዎች በሀገሬው ተጥለቅልቀዋል፡፡
…በትክሻቸው ሻንጣ ብጤ ያዘሉ ጎልማሶች፣በጀርባቸው ከረጢት፣ በክንዳቸው ቁልጭ ቁልጭ የሚሉ ሕፃናት የታቀፉ እናቶች፣ነጠላ ዘቅዝቀው በደቦ የሚጓዙ ወይዛዝርት፣ ዶክመንት በጉያቸው ሸጉጠው የሥራ ማስታወቂያ ለማንበብ የሚጋፉ ወጣቶች፣ፌስታል ያንጠለጠሉ አዳፋ ጋቢ የለበሱ አዛውንቶች፣ በአንድ እጃቸው ደቦት (ችቦ) በሌላኛው ቄጠማ፣ ጨፌ የያዙ ነጫጭ የለበሱ ምእመናን ፣ አዲስ ማስታወሻ ደብተርና የታሸገ ውኃ በጃቸው ይዘው የሚወዛወዙ ኮትና ‘ሌዘር’ ለባሾች (ለስብሰባ የከተሙ ሳይኾኑ አይቀሩም)፣ ባታቸው እንደ መስታወት የሚያብረቀርቅ ቁምጣ ለባሽ ጎበዛዝት፣እንደ ዐይናቸው ብሌን የሚጠብቁትን ሚዛን ከፊት ለፊት አስቀምጠው በሳንቲም እየቆረቁሩ ‘ጋሸ ተመዘን’ የሚሉ ሕፃናት፣ የ’ተመዘን’ ጥያቄው ሲበዛባቸው ‘ምን ተበልቶ?” ሲሉ የሚነቁሩ ዐዋቂዎች፣ ከጠጉራቸው ጋር የተሰፋ የሚመስል ቁና በአናታቸው ሰክተው “ጋሸ ማንጎ፣ማንጎ፣ዘይቱን” የሚሉ ልጅ እግር ሴቶች…ጎዳናውን ሞልተው፣ “አንተ ጎዳና እንዳይከፋህ! ቱሪስት ቢቀር እኛ አለንልህ” የሚሉ ይመስላሉ፡፡
“The world is a book and those who do not travel read only one page” የሚለውን የቅዱስ ኦውግስቲንን ምክር ሰምቼ አንድም በታክሲ አለያም በባጃጅ፣ደግሞም በእግሬ እጓዛለሁ፡፡ ከመቀመጥ ምን ይገኛል? ወንበር ለቦለቲከኛ ይመስለኛል (ቂቂቂ…ይመስለኛል ነው ያልኩት)፡፡
‘ዲፖ’ ላይ እንደ ጅብራ እንደተገተርሁ፣ ከላይ ከጥንት ከጥዋቱ ካቴድራል ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን የተንደረደረው ታክሲ አጠገቤ ሲደርስ እንደመቆም ካለ በኃላ አናቱ ላይ ሻሽ ብጤ ሸብ ያደረገ ወጣት አንገቱን አስግጎ “ሆስፒታል፡፡ ሆስፒታል፣ ሆስፒታል” እያለ መጣራት ጀመረ፡፡ “ሆስፒታል፣ ሆስፒታል፣ሆስፒታል፡ሆስፒታል ነሽ? ሃሎ ሆስፒታል ነህ? ሃሎ ሆስፒታል ናችሁ?” አብሮኝ ሊሻገር የመኪናውን እንቅስቃሴ የሚሰልልን ሰው ተኩሮ “ሆስፒታል ነህ? ሆስፒታል ነህ?” ሲለው ድምፁን ከፍ አድርጎ “መች አመመኝ?” አለ፡፡ ወቸ ጉድ!ረዳቱ መስሚያ የለውም፡፡ “ሆስፒታል፣ ሆስፒታል፣ሆስፒታል፡ሆስፒታል ነሽ? ሃሎ ሆስፒታል ነህ?
መንገዱን ተሻግሬ “ገበያ ገበያ” በሚለው ታክሲ ለመግባት በር ላይ ቆሜ የታክሲውን ውስጥ በዐይኔ ስበረብር ፣ ረዳቱ “ሦስት ሰው ነው የሚያዘው ከፈት አድርጊለት” አለ፡፡ ዐራተኛውን ወንበር ትቼ ሦስተኛ ተደርቤ ከተቀመጥኩ በኋላ ረዳቱ ሌላ ተሳፋሪ ይዞ መጣና “ክፈችለት እንጂ…” ሲል “ከዚህ ወዲያ?” አለች ትእዛዙ የደረሳት ተሳፋሪ፡፡ ረዳቱ ደግሞ “ክፈቺለት” ብሎ ገና ሳይጨርስ ቀሚሷን እያስተካከለች “አንተዬ ክፈቺ ክፈቺ አትበል! ሌላ ያስመስልብሃል” ስትል ታክሲው ውስጥ ያለው ሰው ሁሉ ባንድነት አውካካ፡፡
‘ተመሰገን ሣቃችን በቦታው አለ’ አልኩ በሆዴ፡፡
ከመቀመጥ ምን ይገኛል? አይባልም፡፡ ሣቅ በተወደደ ሀገር…ይሄው እንዲህ መሣቅ አለ፡፡ ሴትዮዋ የዋዛ አይደለችም፡፡ “የዓባይ ዕዳ አለብን ጠጋ ጠጋ በሉ ትሉ አልነበር? ይሄው ዓባይ ተገደበ አሁን ምን ትሉ?”
“ምን ?”
“ሰምተሃል ባክህ…አሁን ቸኩለናል እንሒድበት”
ረዳቱ “መብታችሁ ትዝ የሚላችሁ ታክሲ ውስጥ ስትገቡ ነው” እያለ እያጎተመተመ ሹፌሩን “ቆስቁሰው” አለ፡፡
እየተጓዝኩ ነው፡፡
በመሃል ‘ይከራያል’ የሚል ማስታወቂያ ሳልፈልገው እያደናቀፈኝ፣ በእንግሊዝ አፍ የተጣፉትን ወፈ ሰማይ ንግድ ቤቶች እንደዘበት እያነበብኩ፣ ‘ከተማውን የሞላው ባጃጅ ብቻ ነው እንዴ?’ እስክንል ድረስ ነዳጅ ለመስፈር አስፋልቱ ግራና ቀኝ የተሰለፉትን ባጃጆች እያየሁ፣ “በባጃጆች ፈንታ ሹፌሮች ቢሰለፉ ቃል የተገባልን ነዳጅ አይፈልቅ ይኾን?” እያልኩ ሳላበቃ በወረፋ ተጣልተው የተፈናከቱትን ሁለት ሹፌሮች እየታዘብኩ … እጓዛለሁ…እጓዛለሁ…እጓዛለሁ…
ውሉን የሳተ የሐሳብ ማግ ስፈትል…ከዛ ታክሲ ወርጄ እንደኑሮ የማይሞላ ሌላ ታክሲ ውስጥ ራሴን አገኘሁት፡፡ ወድያው ግን ሰው ከየጎሬው እየወጣ ወንበሩን ይሞላው ጀመር፡፡
‘ሞት ብቻ ነው የሚለየን’ ያሉ የሚመስሉ ጥንዶች ወደ ታክሲው ሲቀርቡ ረዳቱ ሴቷን ለይቶ ፡-“ብቻሽን ነሽ?”
ወንዱ ልጅ ጠጉሩን በጣቶቹ እየፈተለ “ምንሼ? (በአራድኛ ምን ፈልገህ ነው? እንደማለት ያለ ሳይኾን አይቀርም) እኔ ሰው አይደለሁም?” ሲል መለሰለት፡፡ “እረ ወንድሜ ያንድ ሰው ቦታ ብቻ ስላለኝ ነው፡፡” ሹፌሩ ‘አንለያይም’ እያለ የሚቀውጠውን ታምራት ደስታ ዝም አሰኝቶ፡- “አ…ሉ እንዴ?” (እነዛ ትራፊክ ፖሊሶችን መኾኑ ነው ) ሲል ረዳቱን ይጠይቀዋል፡፡
“አዋዋዋ!”
ሁለቱ ጥንዶች ታክሲው በር ላይ “ምን ተሻለ?” በሚል ሐሳብ ሲወዛገቡ ፣ ረዳቱ በርካታ የነተቡ የብር ኖቶችን በጣቶቹ እያተለተለ “ታክሲ ሁሉ እየሞላ ስለሚመጣ አንዳችሁ ብተሔዱ ይሻላል፡፡ ዛሬ መንገድ ተዘጋግቷል” ሲል አከለ፡፡ “ዛሬ ደግሞ ማን መጥቶ ነው?” ሲል ወንዱ ጠየቀ ፡፡መልስ የለም፡፡ እሱም ምላሽ ፈልጎ የጠየቀ አይመስልም፡፡
ጥቂት ቆይቶ ሴቷ “በቃ እኔ ልቅደም” ብላ ዘላ ታክሲ ውስጥ እንደገባች፣ ታክሲው መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ግን ጥቂት እንደተፏንቀቀ ወዲያው ቆመ፡፡ ወዲያው ልጅቱ ወረደችና ከወጣቱ መሳፈሪያ ፈረንካ ወስዳ ተመልሳ ገባች፡፡ እንደገባች “እዛው እጠብቅሃለሁ” አለች፡፡
ድፍን ሁለት መቶ ብር ነበር የሰጣት…፡፡ ኪሱ ውስጥ ለመሳፈሪያ የሚኾን ቀሪ ብር አለው ይኾን? አልመሰለኝም፡፡ ‘እዛው እጠብቅሃለሁ’ ስትለው… ‘እደውላለሁ’ ነበር ያለው፡፡ እነሆ ‘እኔና አንቺን ሞት ብቻ ነው የሚለየን’ በሚለው ላይ ቦተሊካ ይጨመርበት ብለናል፡፡
የነደደውን ጉሮሮዬን ለማርጠብ ወደ አንድ ግሮሰሪ ጎራ አልኩ፡፡እግሬንም ልጠፈው እንጂ!
ግሮሰሪው ውሉ ባልለየለት ሙዚቃ ተመሳቅሏል፡፡ሐሳብ የሚያናዛውታትን አስተናጋጅ እጄን አውለብልቤ ጠራኋት፡፡ ያዘዝኩት ሲመጣልኝ ፉት ብየ እንዳስቀመጥኩ በቀኜ የተቀመጠው ሰው፣ አሻግሮ የተቀመጠውን ሰው “ለምን አትተወኝም ግን?…” አለ በምሬት፡፡ የኔን መግባት ተከትሎ ጨዋታቸውን እንዳቆሙ ገባኝ፡፡
ጥያቄዬ ከብዶህ ነው? ምነው ‘ናኖ’ ሳይንስ ኾነብህሳ… ”ይቺ ሀገር ወዴት እየሔሔ…ደች ነው?”
“እኔ’ንጃ ወንድሜ እኔ ምም…..ንም የማውቀው ነገር የለኝም፡፡ ምናልባት የሚነዷትን ብትጠይቅ…”
ስካር በያዘው አንደበት ስቅታ እያደናቀፈው” የሚ…ያ…ነዷትን አትልም?” ሃሃሃ….
ያ ሰው “ሆሆ…ማነሽ እናቱ ሒሳብ! …” አለና ከግሮሰሪው ለመውጣት ይቁነጠነጥ ጀመር፡፡
ጠያቂው ሰው ሊፋታው ነው፡፡ “ጆሮ እመስላለሁ እንዴ? አይዞህ አት….ፍፍራ !”
ሰውየው ሒሳብ እየከፈለ ደምፁን ቀንሶ “ጆሮማ ብትኾን ያልኩትን ትሰማ ነበር” አለ፡፡ ሞቅታ የተጫነው ጠያቂ የመልስ ምቱን የሰማ አይመስልም፡፡ ሣቁን ሊያቆም አልቻለም….. ሃሃሃ…ፍርሃታችንን ለፖለቲከኞች እስከ አከራየን ድረስ እያከክን፣እየታመስን መኖራችን የታወቀ ነው፡፡ ሃሃሃሃ…
ሰውዬው ሒሳቡን ከፍሎ እንደወጣ፣ ከጥግ በኩል የተቀመጠው “መቦትለኩን ትተህ ለምን ሥራ አትሠራም?”ሲለው “ምን ሥራ አለ?”
“እና የምትጠጣበትን ብር የት አገኘኸው? ዘርፈህ ?” ሲለው “የለም ሎተሪ ደርሶት ነው” አለ ሌላው፡፡
ግሮሰሪዋ በሣቅ ፈላች፣ተንተከተከች፣ፈነዳች፡፡ …ሣቅን የፈጠረ የተመሰገነ ይኹን!
ከዛ ግሮሰሪ ለመውጣት ቸኮልኩ፡፡ ቸኩየም አልቀረሁ፣ሒሳብ ከፍዬ ጎዳናውን እንደያዝኩ “ዓባይ፣ ዓባይ፣ ዓባይ፣ ዓባይ” እያለ የሚጣራ ሰላላ ድምፅ ተቀበለኝ፡፡ “ዓባይ ነህ? ዓባይ ነሽ? ልትሔድ ነው?” ከማለቱ ወደ ታክሲው ሆድ ተንደርድሬ ገባሁ፡፡ ‘ወደግድቡ ከኾነ እገባለሁ’ አልኩት፡፡ የሰማኝ አይመስለኝም፡፡ “ዓባይ ነህ? ዓባይ ነሽ? ልትሔድ ነው?” መንገዱን ለማቋረጥ የሚያመነታ አርሦ አደርን “ዓባይ ነህ? ዓባይ ነህ?” ማለቱን ሲደጋግም አርሦ አደሩ ግራ ገብቶት እየተገላመጠ፡-
“እኔን ነው?”
“እንግዲያ እኔን ነው?” ሲል ጥያቄውን በጥያቄ መለሰለት፡፡
“እሯ ምን አልኩህ አያ! እናቴ ያወጣችልኝ ስም እያለ?”
ረዳቱ ሣቁን በጉንጩ ሸሽጎ ግና ፊቱን ደግሞ አቀጭሞ፣ አነጋገሩን እንደ አርሦ አደሩ አስማምቶ ፡- “እናሳ ማን ትባላለህ?”
“ሞላ ነዋ!”
“ሞላ ?”
“እንግዲያስ”
“ኤዲያ አሁን ምን ሞልቶልህ ነው ?”
አርሦ አደሩም ትክሻው ላይ ጣል ያደረጋትን ቋጠሮ በአጋደመው ዱላ አሾልኮ በእጁ እያልመዘመዘ “ቸር አስመሸኝ!” አለ በለሆሳስ፡፡ አሜን!
ወደ ማረፊያዬ ስጠጋ ጨለማው ውስጥ ጠንከር ያለ ንግግር ይኹን ጭቅጭቅ ጆሮዬን ጠለፈው፡፡አንዲት ውሻ ምን እንደሸተታት እንጃ ክፉኛ ታክላላለች፡፡
“አሁን እነነነነ….ናንተ ወንድማችሁን ገድላችሁ ጀግና ልትባሉ ነው?” ይላል ስካር ያዳከመው ሰው፡፡ከወዲያኛው ጥግ… “ቀርቀጭ… ቀርቀጭ….” መሳሪያ ተቀባበለ፡፡ “ምን አልክ አንተ? አሁን ያልከውን ድገመው!” ሲል በርከክ እንደማለት አለ፡፡
“አንዱ ወንድሜ በዚህኛው ነው፤ ሌላኛው በዛኛው፡፡ ለማን ልወግን? ንገሩኝ እስኪ? ኣ? አሁንስ አይበቃንም? እንጀራ ነው እንዳትሉኝ! ሳይበ….ሳይ…በበበላ ይቅር! ቱፍፍፍ…”
“ምንድነው የሚል አንተ! ቁም ብየሃለሁ! ቁም!” ቀርቀቀቀቀጭጭ….
“ተወው ሰክሮ ነው፡፡ ደግሞ ሰካራም ልትመታ ነው? በል!በል! በል!… ምን ያለው ነው አያ… ?” ይላል ሌላኛው፡፡
“አሄሄሄ …ምን ሰክሮ ነው ትለኛለህ? እብድና ዘመናይ አሉ…”
‘ተደናገጥኩልሽ ጥይት እንደሳተኝ’ የተሰኘውን ዜማ የቆሰቆሰው ይህ ዓይነት ገጠመኝ መኾን አለበት፡፡ ሐዘኔታ ያሳየው ሰው “አተ(አንተ) ቤትህ አትገባም ? ምን ያንዘላዝልሃል?” ከማለቱ ሰካራሙ ሰው ጨለማው ውስጥ ገብቶ ተሰወረ፡፡ የተዘጉ በሮች ከግራም ከቀኝም መከፈት ጀመሩ፡፡ ግን በስሱ ነው፡፡ ገርበብብብ… ትንኝ ቢገባስ?






