
ጠገናው ጎሹ
እንደ እኛው የዘመን ቀመር አቆጣጠር ከዓመት ወደ ዓመት የተሻገርንበትን (ከ2017 ወደ 2018) ባከበርን በ16ኛው/17ኛው ቀን ታላላቅ ከምንላቸው ሃይማኖታዊ በዓላት መካከል አንዱ የሆነውን የመስቀልን በዓል አከበርን (ማክበር ከተባለ) ።
አዎ! እጅግ ፈታኙ ጥያቄ ተከበረ የሚል ዜና ማስነገሩ ሳይሆን በምን አይነት የሃይማኖት አመራር አካል/እረኛ? ቃል ህይወት የመሆኑ ሚስጢር ከተገለጠባቸው ታላላቅ ሃይማኖታዊ በዓላት አንዱ የሆነውን የመስቀሉን በዓል ቢያንስ ብዙውን ጊዜ ራሳችንን ለማታለል ቢሆን በምንጠቀምበትና አንፃራዊ ሰላም በሚያሰኝ አኳኋን አክብረን ለመዋል ያልቻልነው ለምንድን ነው? ወደየቤታችን ስንመለስ ደርሸ መጣሁ ወይም ደርሰን መጣን ከማለት ያለፈ ስሜት እውን ተሰምቶናል? የሃይማኖት መሪዎች ተብየዎች ጠብቁና አሰማሩ ተብለው በአደራ ከተሰጡት አማኝ/የበግ መንጋ በላቀ ሁኔታ በሃይማኖታዊ አርበኝነት ስሜትና ሃላፊነት ይወጣሉ ተብለው ሲጠበቁ ራሳቸውን ወደ የእኩያን ገዥዎች የወዮላችሁ ማስጠንቀቂያ አመላላሽነት/ተላላኪነት ያወረዱትና ራሳቸውን ብቻ ሳይሆን አማኙን/ተከታዩን ጨምረው ያሸማቀቁት ለምንድን ነው? ወዘተ የሚለው ነው።
በእውነተኛ አማኝነት ይዘትና አቋም ላይ ሆነን የምንዘክራቸውና የምናከብራቸው እስከሆነ ድረስ እንኳንስ በጎና ታላላቅ ኩነቶች የተከናወኑባቸውን የሃይማኖታዊ እምነት በዓላት የትኛውንም ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ትውፊታዊ፣ ማህበራዊ ፣ ወዘተ በዓል ደምቀንና አድምቀን ብናከብር የሚቃወም ወይም የሚያጣጥል እንኳንስ የሃይማኖቱ ተከታይ ማነኛውም ባለ ጤናማና ሚዛናዊ ህሊና የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም።
በእጅጉ አሳዛኙና አሳፋሪው ጉዳይ የፈጣሪ ቁጣ ወይም ያለመታደል ሆኖብን ሳይሆን በገዛ ራሳችን ልክ የሌለው ስንፍና እና ውድቀት ምክንያት በሥልጣነ መንበር ላይ ከሚፈራረቁ ሴረኛና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖች ፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ሰብረን ለመውጣት ባለመቻላችን ይኸውና የሃይማኖታዊ እምነት በዓሎቻችንን እንኳ በቅጡ ዘክረን/አክብረን ለመዋል የማንችልበት ሁኔታ ላይ የመገኘታችን ግዙፍና መሪር እውነታ ነው።
“ቃል ነበረ፥ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፥ ቃልም ህይወት ሆነ ፣ወዘተ “ የሚለውና በዮሐንስ ወንጌል የተጠቀሰው ረቂቅና ጥልቅ ሃይማኖታዊ አስተምህሮት በፈጣሪ አምሳል ከተፈጠረው የሰው ልጅ ህይወት ምንነትና እንዴትነት ተለይቶ የሚንሳፈፍ አንዳች አይነት መንፈስ አይደለም ። ሊሆንም አይችልም። የእውቀትት አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ይህንን ለመረዳት ቅንና እውነተኛ አማኝነትን እንጅ የተለየ/የረቀቀ እውቀትን ግድ አይልም። ሃያል ቃሉን ወደ ሃያል ተግባር ተርጉሞ ያሳየበትን መስቀሉን ስናከብር ለዘመናት ከመጣንበትና አሁንም ተዘፍቀን ከቀጠልንበት የገዛ ራሳችን የውድቀት አዙሪትና አረንቋ (በእጅጉ የተጎሳቆለ ህይወት) እንዴትና መቼ ሰብረን መውጣት እንዳለብን ከምር እየተናገርንና እየተናጋገርን ካልሆነ ነገረ ሥራችን ሁሉ ትውፊታዊና ልማዳዊ ብቻ ይሆንብንና ከክፉው አዙሪት ሰብረን ለመውጣት እንቸገራለን።
በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን አብዛኛው የሃይማኖት መሪ፣ ሰባኪና አማኝ ነኝ ነይ ባይ ቃል ህይወት የመሆኑን ሃያልነት በአገራችን ውስጥ ከሆነውና እየሆነ ካለው ፖለቲካ ወለድ የመከራና የውርደት ህይወት (ህይወት ከተባለ) ምንነትና እንዴትነት ጋር በአግባቡና በሃይማኖታዊ አርበኝነት መንፈስ እየተረጎመና እያስተማረ ሃይማኖቱንና ተውልድን ለመታደግ ያለመቻሉ መሪር እውነት ቅንና ሚዛናዊ ህሊና ያለውን የአገሬ ሰው በእጅጉ ይረብሻል።
አዎ! ከመጣንበት የዘመን ርዝማኔም ሆነ የመከራ አስከፊነት አንፃር ስናየው ዛሬም በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረ ወገን/ህዝብ እኩያን ገዥዎችና ግብረ በላዎቻቸው በሚፈፅሙት ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ምክንያት ቃልና ተግባር ተዋህደው የመልካም ህይወት ትሩፋትን ሊያስገኙለት ባለመቻላቸው ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች እንዲኖር (ኑሮ ከተባለ) በተገደደበት መሪር እውነታ ውስጥ የባለጌና የጨካኝ ገዥዎችን እጅግ አስከፊ/ፀያፍ የወዮላችሁ ትእዛዝ ተቀብለው የወዮላችሁ ትእዛዝ ያስተላለፉ የሃይማኖት መሪዎች ነን ባዮች የመስቀልን በዓል በሰላም፣በነፃነትና በድምቀት አከበርነው በሚል ሊያሳምኑን ሲሞክሩ ራስን ከማታለል አልፎ የመስቀሉን ክብር ዝቅ ማድረግ ነውና ይልቁንም ከቻላችሁ ንስሃ ግቡ ብንላቸው ትክክል እንጅ ከቶ መዳፈር ሊሆን አይችልም።
ሃጢአት ማለት ለምድራዊውም ሆነ ለመንፈሳዊ ህይወት ፈፅሞ የማይበጅ እኩይ/ክፉ ባህሪና ተግባር እንጅ በአየር ላይ የሚንሳፈፍ አንዳች አይነት ክፉ መንፈስ ይመስል ለገዛ ራስ የቀውስና የውድቀት መሸፈኛ ማድረግ እንኳንስ ቃል ህያው እውነት ይሆን ዘንድ ክርስቶስ ለተሰቀለበት መስቀል ለየትኛውም መንፈሳዊና ዓለማዊ በዓልም ፈፅሞ አየመጥንም።
ሰፊና ጥልቅ የሃይማኖታዊ ዶግማ እውቀት አስፈላጊነት እንደተጠበቀ ሆኖ ክርስቶስ ለመስቀል ላይ ስቅላት የበቃበት መሠረታዊው ምክንያት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረው ሰብአዊ ፍጡር ለፈጣሪው ምስጋና እያቀረበና የአምላክነቱን በጎ እገዛ እየጠየቀ ደህንነት፣ ነፃነት፣ ፍትህ፣ ሰብአዊ መብት፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ሥልጣኔ፣ የጋራ እድገት ፣ ወዘተ በሰፈነበት ሥርዓተ ህይወት ውስጥ ይኖር ዘንድ የተከፈለ ድንቅ አምላካዊ ዋጋ መሆኑን ለመረዳትና ለመቀበል የሚያስቸግር አይመስለኝም።ይህንን መሠረታዊ አስተምህሮት ለመረዳት የሚጠይቀው አስተዋይ የሆነ ፣ ሚዛናዊነት ያለው እና ወደ ህይወትነት የሚተረጎም ቃልን የውስጠ ህሊናው አካል ያደረገ ማንነትን ነው።
የመስቀሉ እውነተኛ አማኝነት መገለጫው በእኩያን ገዥ ቡድኖች ነፍስና ሥጋው ጭንቅ ውስጥ የገቡበትን መከረኛ ህዝብ ለመታደግ ይቻል ዘንድ ቃል ህይወት ዘርቶ (የተግባር ሃይል ሆኖ) የመገኘቱ ድንቅ እሴትነት ነው ። ለዚህም ነው “መስቀል ሃይላችንና ቤዛችን ነው” የሚለው እጅግ ሃያል አገላለፅ የሆነው። ይህ ግዙፍና ጥልቅ የሆነ የእምነት መርህ ቃል ወደ ተግባር ተተርጉሞ ለሁለንተናዊ የህይወት (ለመንፈሳዊና ለሥጋዊ ህይወት) ዋስትና እንዲሆን እውነተኛ የግልና የጋራ ጥረት ስናደርግ ብቻ ነው የእውነተኛው መስቀል ትሩፋት ተሳታፊዎች የምንሆነው።
ይህንን ሆነንና አድርገን ለመገኘት አስፈላጊውንና እልህ አስጨራሹን ጥረት/ተጋድሎ ባለማድረጋችን ምክንያት ይኸውና የዘንድሮውን የመስቀል በዓል የመንግሥት ተብየውንና የግብረ በላዎቹን የወዮላችሁ/የሽብር ማስጠንቀቂያ/አዋጅ እንደ ወረደ እየተቀበሉ ይህንን ወይም ያንን አይነት ምልክት ወይም ምስል ይዛችሁ ብትገኙ እና በአንደበትም ሆነ በሌላ ዘዴ ለገዥዎች የማይመች ቋንቋ ትንፍሽ ብትሉ ወዮላችሁ ብለው ካስጠነቀቁን የሃይማኖት አባቶች ተብየዎች ሥር ሆነን “በድምቀት አከበርንና እኛም ከበርንበት” ማለት ቃል ህይወት ሆነ ለሚለው ሃይለ ቃል አንዱና ታላቅ ማሳያ ለሆነው ለመስቀሉ ምንነትና እንዴትነት ፈፅሞ አይመጥንም። ለምን? ቢባል የትኛውም ሃይማኖታዊ አተምህሮት በፈጣሪ አምሳል ከተፈጠረው የሰው ልጅ ሁለንተናዊ የህይወት ስኬት ተገንጥሎ የሚተረጎምና የሚተገበር አይደለምና ነው። ከዚህ ወጭ ያለው መከራከሪያ የውድቀታችንን ድግግሞሽ ለመሸፋፈን ካልሆነ በስተቀር ከትናንትና ከዛሬ ስህተት ተምረን የተሻለ ለምናደርገው የነገ እኛነታችን ፈፅሞ አይጠቅመንም።
በአንድ በኩል ሃይማኖትን ከቤተ መንግሥት ፖለቲካ ሥልጣን ጋር በሚያቀላቅሉ ገዥዎች እና በሌላ በኩል ደግሞ የእነርሱ ሰለባዎች ለመሆን ራሳቸውን አሳልፈው በሰጡ የሃይማኖት መሪዎች ምክንያት ከሚፈጠሩ ፈታኝ ሁኔታዎች ነፃ የሆነበት ዘመን አልነበረም። ተሳክቶልን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ለማድረግ ብንችል እንኳ የሚፈጠሩ ተመሳሳይ ችግሮች ከህግ ፣ ከደንብና ከፍትህ ቁጥጥር ውጭ እንዳይሆኑ ማድረግ እንጅ ፍፁም በሆነ ደረጃ ማስወገድ አንችልም። ለምን? ቢባል እየተነጋገርን ያለነው አስቸጋሪና ውስብስብ ስለሆነው የሰው ልጅ ባህሪ ነውና።
ሃይማኖትን ጨምሮ መሠረታዊ መብቶቻችን ዘመናትን ካስቆጠሩበትና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ ከሚገኙበት እጅግ ለመግለፅ የሚከብድ አስከፊ ሁኔታ መንጥቀን ማውጣት ካለብን መፍትሄው አንድና አንድ ብቻ ነው። እርሱም የፖለቲካ ወለድ መከራና ውርደት ዋነኛ ማዕከልና ማከፋፈያ የሆነውን የእኩያን ገዥ ቡድኖች አገዛዝ ሁለገብ በሆነና እና የውድቀት አዙሪት ፖለቲካ ታሪክን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመለወጥ እና ዴሞክራሲያዊት የሆነች የጋራ አገር ዜጎች ለመሆን የሚያስችል የለውጥ ተጋድሎን አጠናክሮ ማስኬድና ለድል ማብቃት ብቻ ነው!
ለዚህ ደግሞ ይበልጥ አበረታች እየሆነ የቀጠለውን የአማራ ፋኖ እና የመነሻ ምክንያቱን፣ የትግል ዲሲፕሊኑን፣ የትግል ፅዕናቱን፣ ዴሞክራሲያዊት የጋራ አገር እውን የማድረግ ዓላማውንና ግቡን የሚጋሩ ወገኖች የሚያካሂዱትን ትግል ጊዜን፣ ህይወትንና ማተሪያላዊ አቅምን ግምት ውስጥ በሚያስገባ ሁለንተናዊ ድጋፍ እያጠናከሩ ለድል ማብቃትን ከምር መውሰድን ግድ ይላልና ከምር እንውሰደው።
ስለሆነም ልብ ያለው ልብ ይበል!
_
የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በነጻ አስተያየት መድረድ ላይ የሚወጡ ጽሁፎች የጸሃፊውን እንጂ የቦርከናን አቋም አያንጸባርቁም፡፡
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






