
ቦርከና ዜና
05/02/2018
ጦርነት፣ ግጭትና የተለያዩ ደጋዎች በሚፈራረቁባት ኢትዮጵያ በአንድ ሆስፒታል ባለው መረጃ ብቻ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በዓመት 15 ሺሕ መጨመሩን ቦርከና ተረድቷል፡፡
ቦርከና ከአማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ገለጻ እንደተረዳው፣ ወደ ሆስፒታሉ የሚያቀኑት የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር በ2016 ከነበረው አንጻር ሲታይ በ2017 ዓ/ም ከ10 ሺሕ እስከ 15 ሺሕ ጨምሯል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ወደ ሆስፒታሉ ለህክምና ያቀኑት ሕሙማን ብዛት 130 ሺሕ ገደማ እንደነበር ያስታወሱት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ኃይሌ፣ በ2017 በጀት ዓመት ግን እስከ 15 ሺሕ መጨመሩን ተናግረዋል፡፡
ቦርከና የተመለከተው የሆስፒታሉ የ2017 ዓ/ም ዓመታዊ ሪፖርት፣ በበጀት ዓመቱ ለ141 ሺሕ 864 ዜጎች በአዕምሮ ህመምና እና ተያያዥ ጉዳዮች የህክምና አገልግሎት ተሰጥቷል።
በዚህም፣ በአስተኝቶ የአዕምሮ ህክምና ለ1 ሺሕ 793፣ በተመላላሽ የአዕምሮ ህክምና ለ136 ሺሕ 89፣ በድንገተኛ የአዕምሮ ህክምና ለ1 ሺሕ 793 በድምሩ ለ141 ሺሕ 864 የአዕምሮ ህመም ታካሚዎች ህክምና መሰጠቱን ይሄው መረጃ በዝርዝር ያስረዳል።
መቶ ሺሕ የሚቆጠሩት እነዚህ ዜጎች ህክምናውን የወሰዱትም፣ ሆስፒታሉ በ2017 በጀት ዓመት በአዕምሮ ህመምና ተያያዥ ጉዳዮች ለመስጠት ካቀደው 155 ሺሕ ዜጎች ውስጥ መሆኑን መረጃው አስፍሯል፡፡
በ2016 ዓ/ም ወደ ሆስፒታሉ ለህክምና ያቀኑት የአዕምሮ ህሙማን ብዛት 130 ሺሕ ገደማ እንደነበር በወቅቱ መነገሩ የሚታወስ ሲሆን፣ የሆስፒታሉ የ2017 ዓ/ም ሪፖርት ደግሞ በበጀት ዓመቱ ለ155 ሺሕ ዜጎች ህክምናውን ለመስጠት አቅዶ ነበር፡፡ ከዚህ መረጀ በመነሳትም የህሙማኑ ቁጥር በዓመት ውስጥ ከ15 ሺሕ በላይም መጨመሩን መረዳት ይቻላል፡፡
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ጦርነት፣ ግጭት፣ የመሬት መንቀጥቀጥ፣ መፈናቀል፣ የመሬት ናዳ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከፈተና መውደቅ ሌሎች መሰል ሰው ሰራሽና ተፈጥሮዊ አደጋዎች ለአዕምሮ ህሙማኑ መጨመር የራሳቸው የሆነ ድርሻ እንዳላቸው ቦርከና ያነጋገራቸው የሆስፒታሉ የአዕምሮ ህመም ህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡
የአማኑኤል ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ኃይሌ በበኩላቸው፣ ኢትዮጵያ እየተፈራረቁ የተስተዋሉ እንደ ግጭት፣ ድርቅ፣ ጦርነት፣ መፈናቀልና መሰል አደጋዎች ወደ ሆስፒታሉ ለሚያቀኑ የአዕምሮ ህሙማን ቁጥር መጨመር በምክንያትነት ይጠቅሳሉ፡፡
እንደ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገለጻ ከሆነ፣ በተለይ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ህሙማን ወደ ሆስፒታሉ የማያቀኑበት አጋጣሚ ስለሚኖር በአማኑኤል ሆስፒታል እየጨመረ የመጣው የህሙማን ቁጥርም ትክክለኛውን በኢትዮጵያ ያለ የህሙማን ብዛት የማይገልጽ ሲሆን፣ ቁጥሩ ከዚህ ሊያሻቅብ ይችላል፡፡
እንደ እሳቸው ምክረ ሀሳብ ድግሞ፣ ወደ ሆስፒታል የማያቀኑ ህሙማን የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ልክ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚጓጓዙት ሁሉ የዘርፉ የህክምና ባለሙያዎችም ህሙማን ባሉበት አካባቢ ሊሰማሩ ይገባል፡፡
በሌላ በኩል፣ በተለይ የህጻናት አዕምሮ ህሙማንና የሱስ ታካሚዎች ሀኪሞች በጣም ትንሽ መሆናቸው ለዘርፉ ትልቅ ተጋዳሮት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የታማሚዎች ብዛት ግን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ለአብነትም፣ በ2017 በጀት ውስጥ 490 የሚሆኑት የህፃናት የአዕምሮ፣ በሱስ ህክምና 777 ለሚደርሱ ዜጎች የሱስ ህክምና መስጠቱን ቦርከና የተመለከተው የአማኑኤል የአዕምሮ ህሙማን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ሪፖረት ያስረዳል፡፡
በኢትዮጵያ የሚስተዋሉት ጦርነትና ግጭቶች በቀጥታ በሰዎች ላይ ሞት፣ በመሰረተ ልማት ላይ ውድመት፣ ከማድረሳቸው ባሻገር በተዘዋዋሪ ለዜጎች የአዕምሮ ህመም መጋለጥ ምክንያት ሆነዋል፡፡
__
ቦርከናን ይደግፉ :- እዚህ ገጽ ላይ
የቦርከናን ዮቲዮብ ቻናል ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






