Homeዜናየኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ታጣቂዎች እስካሁን የሰጡኝ ምላሽ የለም” አለ

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን “ታጣቂዎች እስካሁን የሰጡኝ ምላሽ የለም” አለ

Advertisement
World Wide Travel Group
  • በትግራይ ክልል የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራ በዚህ ወር ይጀመራል ብሏል

ቦርከና ዜና
08/02/2018

ዋናውን ሀገራዊ ጉባዔ ለማካሄድ አጀንዳ ለመቅረጽ እየሰራሁ ነው ያለው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን አጀንዳቸውን ማቅረብ የሚጠበቅባቸው በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉ ወገኖች እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጡት ገለጸ፡፡

ኮሚሽኑ በፓርላማ የተሰጠውን ተጨማሪ የአንድ አመት ጊዜ ለማጠናቀቅ ወራት ቢቀሩትም፣ በትግራይ ክልል አጀንዳ ካለማሰባሰቡ በተጨማሪ ከታጣቂዎችም እስካሁን አጀንዳ አልመረከቡንም ተናግሯል፡፡

የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ አቶ ጥበቡ ታደሰ፣ ታጣቂዎች ለኮሚሽኑ የሰጡት ምላሽ እንደሌለ የገለጹት የኮሚሽኑን ተግባራትና ቀጣይ ሂደቶች በተመለከተ ዛሬ ለሚዲያዎች ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡት ወቅት ነው፡፡

ታጣቂዎች አጀንዳ ማቅረብና አለማቅረባቸውን በተመለከተ ያለውን ሁነት እንዲያብራሩ ሲጠየቁም፣ “የታጠቁ ኃይሎች እስካሁን ይፋዊ በሆነ መንገድ የሰጡን መልስ የለም” ብለዋል፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በተለያዩ ክልሎች በትጥቅ ትግል የታገዙ ግጭቶች መኖራቸው ይታወቃል ያሉት አቶ ጥበቡ፣ አጀንዳዎችን ወደ ምክክር ሂደቱ እንዲያመጡና ሰላማዊ የሆኑ አራጮችን ተከትለው ችግሮችን ለመፍተት ጥረት ማድረግ እንዲቻል ኮሚሽኑ ጥሪዎችን አቅርቧል፤ አሁንም ያቀርቧል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የተለያዩ ጥረቶችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ጠቁመው፣ “ነገር ግን ይሄ በኮሚሽኑ ብቻ የሚፈታ ጉዳይ አይደለም፤ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይጠይቃል” ብለዋል፡፡

መንግስትንም ሆነ ታጣቂዎች የያዙት አማራጭ ሀገር እንደሚያከስርና ብዙ ጉዳት እንደሚያደርስ ያስገነዘቡት ቃል አቀባዩ፣ ለምክክር ሂደቱ እድል እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ በክልሉ ያሉ ግጭቶችን ለማርገብ በድርድር መፍትሄ ለማምጣት እየተሰራ መሆኑን ሰሞኑን ማስታወቁን ገልጸው፣ “እነዚህ ጥረቶች ናቸው መጠናከር ያለባቸው፡፡ ኮሚሽኑ ብቻውን ሰርቶ የሚያመጣው ውጤት ስለሌለ” ነው ያሉት፡፡

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በሌላ በኩል፣ ከኮሚሽኑ ያገለሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጦርነት ውስጥ ሆነው ምክክር ያካሄዱ ሀገራት በምክክር ውጤት እንዳላመጡ በመጥቀስ፣ በኢትዮጵያም ቢሆን ኮሚሽኑ ምክክር ከማካሄዱ በፊት ጦርነት እንዲቆም መስራት እንዳለበት፣ ይህን ካላደረገ ግን ውጤት አይመጣም የሚል ትችት ሲያቀርቡ ይደመጣሉ፡፡

ኮሚሽኑ በበኩሉ፣ ጦርነት፣ ግጭት፣ አስቸጋሪና ፈታኝ ሁኔታዎች አሉ ተብሎ የምክክር ሂደት የሚቆምበት ሁኔታ አማራጭ አይሆንም ሲል ዛሬ መግለጫ በሰጠበት ወቅት ተናግሯል፡፡

አንዳንድ ሀገራት ምክክርን በተለያየ ሁኔታ ውስጥ ያስኬዳሉ ያለው ኮሚሽኑ፣ ይሄ ማለት አንጻራዊ ሰላም ባለበትና በግጭት ውስጥ የሚካሄድ ምክክር አካሄዱም ውጤቱም አንድ አይነት ይሆናል ማለት አይደለም፤ በዚያ ሁኔታ ውስጥ ባይካሄድ ይመረጣል፣ ግን እነዛ ሁኔታዎች አልተሟሉም ተብሎ ምክክሩን እንዲቆም ማድረግ ይበልጥ የተወሳሰበ ችግር ውስጥ ይከታል ብሏል፡፡

የትግራይ ክልል አጀንዳ ማሰባሰብ ሂደትን በተመለከተ በሰጠው ማብራሪያ ደግሞ፣ “ኮሚሽነሮቹ በሁለት ዙር ወደ መቐሌ በመጓዝ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ጨምሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶችን አድርገዋል፤ በክልሉ ምክክር ለማስኬድ እንዲቻል የቀረቡ ጉዳዮች አሉ” ብሏል፡፡

- Advertisement -

ይህን ያሉት የኮሚሽኑ ቃል አቀባይ፣ “አብዛኛዎቹ ፌደራል መንግስቱና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ፖለቲካዊ ውይይቶች ተደርገው መፈታት እንዳለባቸው የጠቆሟቸው ጉዳዮች ናቸው” ሲሉም አክለዋል፡፡

ኮሚሽኑም እነዚህን ግብዓቶች ወስዶ ከፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አርድጎበታል ሲሉ አስረድተው፣ በክልሉ በኩል ፓርቲዎች ጭምር ያነሷቸውን ጉዳዮችን ለፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ቀርበዋል፤ ውይይት ተደርጎ አመቺ ሁኔታ ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

የክልሉ ፕሬዚደንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ጋር ውይይቶች እየተደረጉ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጥበቡ፣ “እሳቸው ባቀረቡት መረጃ መሰረት ከጥቅምት አጋማሽ በኋላ ባለው ጊዜ የምክክር ሂደቱን በትግራይ ክልል መጀመር የሚቻልባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ ገልጸዋል” ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ጎን በጎን ለአጀንዳ ቀረጻው ሥራ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ፣ አጀንዳዎቹ ይፋ ከተደረጉ በኋላ ዋናው የምክክር ጉባዔ እንሚጠራ፣ በምክክር ጉባዔውም ከ4500 በላይ ተሳታፊዎች ተገኝተው ለቀናት እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡

ሆኖም፣ አጀንዳውን ቀርጾ ይፋ ለማድረግና ዋናውን ጉባዔ ለመጀመር የትግራይ ህዝቦችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሳተፍ ስላለባቸው የሚመለከታቸው አካለት ርበርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

……………..

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News