Homeዜናከ3 ሺሕ በላይ የመንግስት ወታደሮች ሲገደሉ፣ ከ600 በላይ ተማርከዋል ሲል አፋብኃ አስታወቀ

ከ3 ሺሕ በላይ የመንግስት ወታደሮች ሲገደሉ፣ ከ600 በላይ ተማርከዋል ሲል አፋብኃ አስታወቀ

Advertisement
World Wide Travel Group

ከ100 ሺሕ የሚልቁ መሳሪያ እና ተተኳሾችን ገቢ አድርጌያለሁ ብሏል

ማክሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2018 ዓ/ም

የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) ምሥራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ ከ3000 በላይ በሚሆኑ የመንግስት ወታደሮች ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰዱንና ከ600 የሚልቁትን መማረኩን አስታውቋል።

የአፋብኃ ምስራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ አርበኛ በለጠ ሸጋው ይህን ያሉት፣ የዕዙን የሁለት ሳምንታት ዘመቻ አስመልክተው ትላንት ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ/ም በሰጡት መግለጫ ነው።

የመምሪያው ኃላፊ አርበኛ በለጠ፣ ለሁለት ሳምንታት በተደረገው ውጊያ 3 ሺሕ 3 የመንግስት ወታደር ሲደመሰሱ፣ 679 ደግሞ ምርኮኛ ሆነዋል ብለዋል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

እንዲሁም፣ 62 ሺሕ 479 የክላሽ፣ 34 ሺሕ 570 የብሬን፣ 15 ሺሕ 614 የዲሽቃ ተተኳሾች ገቢ መደረጋቸውን በዝርዝር ተናግረዋል። ሁለት ሳምንታት በዘለቀ ውጊያ በአጠቃላይ ከ100 ሺሕ በላይ ተተኳሽና መሳሪያዎች ገቢ መደረጋቸውንም ገልጸዋል።

እንዲሁም፣ የመንግስት ወታደሮች ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 24 ተሽከርካሪዎች፣ የወታደራዊና የፖለቲካ አመራሮች ኦራል፣ አምቡላንስና ፓትሮል በፋኖ ታጣቂዎች ተማርከዋል ሲል አፋብኃ አረጋግጧል።

“አገዛዙ ወታደራዊ መጠቀሚያ አድርጓቸው የነበሩትና የተማረኩት አምቡላንሶች ለሕዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ተደርጓል” ሲልም ገልጿል።

እንዲሁም፣ የ16 ቀኑ ያልተቋረጠ የዘመቻ አባናደው ዘመቻ፣ የመንግስት ታጣቂ 5 ኮሮች የተበታተኑበት፤ አቅደው የሚመሩ መሃንዲሶችን ጨምሮ መስመራዊ መኮንኖችን ድል የተደረጉበት ነው ተብሏል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በሌላ በኩሌ፣ ከ40 በላይ ከተሞች ሕዝባዊ ውይይት ማካሄዱን፣ የህዝብ አስተዳደር መዋቅር በሰፊው መዘርጋቱን ያስታውቀው ምኒልክ ዕዝ፣ በቀጣይ አፋብኃ በሚያውጀው ዘመቻ ምን ሊፈጠር እንደሚችል አቅማችንን ያሳየንበት ነበር ሲል የ16 ቀናቱን ተከታታይ ውጊያ ውጤት አስረድቷል።

ዘመቻው፣ መስከረም 14 ቀን 2018 ዓ/ም ከጠዋቱ 12 ሰዓት በአምስቱም ኮሮች በተመሳሳይ ሰዓት መጀመሩን አስታውሷል። በዚህም ምስራቅ አማራ ኮር 1 እና 2፣ ላስታ አሳምነው፣ ልጅ ዕያሱ እና ንጉስ ሚካኤል አሊ ኮሮች፣ በዕዙ ልዩ ዘመቻ እንዲሁም በሌሎች ጥምረት የኃልውና ትግሉን ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ውስጥ ማስገባት ተችሏል ብሏል።

የአማራ የኀልውና ትግል ከጀመረበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ መንግስት ካስተናገዳቸው ኪሳራዎቹ ሁሉ እጅግ የከበደውን ኪሳራ በምሥራቅ አማራ ቀጠና ምኒልክ ዕዝ በዘመቻ አደም አሊ አስተናግዷል ሲል የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ኃይል (አፋብኃ) አስታውቋል።

“አማራን ሰበርነው እያሉ ጠላቶቻችን ቢያወሩም ታላቁ አማራ እንደማይሰበር ጠላቶቹን በሰዓታት እድሜ መደምሰስና ማጥፋት የቻለበት ዘመቻ ነው” ሲልም ምኒልክ ዕዝ በመግለጫው ገልጿል።

- Advertisement -

በሌላ በኩል፣ የአማራ ፋኖ ትግል ዓለማቀፍ የጦርነት ህጎችን እንደሚያከብር በምርኮኛ አያያዙ ለዓለማቀፉ ማኀበረሰብ በማሳየት ትግሉ እንዲጠፋ የተፈረደበትን ሕዝብ ኀልውና የማዳን ተልዕኮ እንደሆነ በተግባር ማስመስከር ችለናል ሲል አፋብኃ ምኒልክ ዕዝ አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ሕግ በሚደነግገው መሰረት ሰብዓዊ ክብራቸውን በጠበቀ ሁኔታ የያዝናቸው የቀድሞ የብልጽግና ሰራዊት አባላት ይህን በዓለማቀፉ ማኀበረሰብ አባላት ፊት መስክረዋል ያለው ዕዙ፣ “ይህ አዲሱ የአማራ ኀልውና ትግል የታሪክ ምዕራፍ ነው” በማለትም አክሏል።

ዋርካው ምሬ ወዳጆ በይፋ ባቀረቡት ጥሪና አፋብኃ ከአለማቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር ጋር በውስጥ ባሳወቀው መሰረት በውጊያ የቆሰሉ የብልፅግና ሰራዊቶችን ለቀይ መስቀል አስረክበናል፤ በተጨማሪም ምርኮኞችን ጎብኝተዋል ነው ያለው።

“ይህ ተግባራችን የፋኖን የህልውና ታጋይነት በሰፊው ለዓለምቀፉ ማህበረሰብ ያስመሰከረ ነው” ያለው ፋኖ፣ “በቀጣይ በሚደረጉ ዘመቻዎችም ለዓለም አቀፍ የሰብዓዊነት ህግ ተገዢ ሆነን እስከ አራት ኪሎ ድረስ እንደምንዘልቅ ዳግም ማረጋገጥ እንወዳለን” ብሏል።

መከላከያ ሠራዊት በበኩሉ፣ በፋኖ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው ሲል ትላንት ጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ/ም አስታውቋል።

በኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ምዕራብ ዕዝ፣ የተሰጠውን ሀገራዊ ተልዕኮ አጠናክሮ ቀጥሏል፣ በፋኖ ላይ እርምጃ እየተወሰደ ነው ሲሉ የዕዙ ዋና አዛዥ ሜጄር ጄኔራል አማረ ባህታ ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ለሁለት ዓመታት የዘለቀው ጦርነት መቋጫ ርቆት ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና በተለይ ገፈት ቀማሽ የሆነው የአማራ ህዝብ ጦርነቱ እንዲቆም እየተማጸኑ ይገኛሉ።

ጠቅላይ ሚኒስቴር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በባሌ ባደረጉት ንግግር ደግሞ፣ “ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት መቶ አመታት ሰላም አልነበረም” ሲሉ በአሁኑ ወቅት ጦርነት ቢኖርም የልማት ስራቸውን እንደሚያስቀጥሉ ሲናገሩ ተደምጠዋል።

አቢይ አሁን ያለው ጦርነት የገነነው “ፌስቡክና ዩቱብ ስላለ ነው” በማለት ምክንያት የደረደሩ ሲሆን፣ ይህንኑ ንግግር የተመለከቱ አስተያየት ሰጭዎች በበኩላቸው፣ “መንግስት በህዝብ ላይ በግልጽ ያወጀውን ጦርነት ሊያቆም ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።

…………………

የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News