Homeዜናመንግስት 7ኛው ዙር ምርጫ ይካሄዳል ቢልም ጦርነቱ አስቻይ እንዳልሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

መንግስት 7ኛው ዙር ምርጫ ይካሄዳል ቢልም ጦርነቱ አስቻይ እንዳልሆነ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ገለጹ

Advertisement
World Wide Travel Group

ቦርከና ዜና
21/02/2018

ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድ ሰባተኛው ዙር ምርጫ በተያዘው ዓመት ይካሄዳል ቢሉም፥ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ግን በኢትዮጵያ የሚስተዋሉ ጦርነቶችና አለመረጋጋቶች ምርጫ ለማስኬድ አስቻይ እንዳልሆኑና ቅድሚያ ሊቆሙ እንደሚገባ ለቦርከና ገልፀዋል።

እውነተኛና ፍትሃዊ ምርጫ ለማካሄድ ቅድሚያ አስቻይ ሁኔታዎች መረጋገጥ አለባቸው የሚሉት ፓርቲዎቹ፥ ይህ ካልሆነ በይስሙላ ምርጫ ላለመሳተፍ ሊወስኑ እንደሚችሉም ከወዲሁ እየተናገሩ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ አህመድ በሰሞንኛው የፓርላማ ውሏቸው ሰባተኛው ዙር ምርጫ እንደሚካሄድ እርግጠኛ ሆነው ሲናገሩ የተደመጡ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በበኩሉ፥ ምርጫው በግንቦት 2018 ዓ/ም እንደሚካሄድ ዝርዝር መርሃ ግብሮችን በማውጣት ሰሞኑን አሳውቋል።

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን ምርጫው መደረጉን በመደገፍ ዝግጅት እያደረጉ ቢሆንም፥ መንግስት ቅድሚያ ጦርነት ካላስቆመ ለምርጫው አሳቻይ ሁኔታ አይኖርም ሲሉ ለቦርከና ተናግረዋል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢህአፓ) ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ጉዳዩን አስመልክተው ለቦርከና በሰጡት አስተያየት፥ “ሰባተኛው ዙር ምርጫ ከዚህ በፊት ከነበሩት ምርጫዎች በጣም አስቸጋሪ እንደሚሆን እናምናለን” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ (ዶ/ር)፥ ሰባተኛው ዙር ምርጫ ከዚህ ቀደሞቹ የተሻለ ይሆናል ሲሉ ተደምጠው የነበረ ሲሆን፥ ኢህአፓ ግን ግንቦት ወር ይካሄዳል የተባለው ምርጫ እንዳውም ከእስከዛሬዎቹ ይበልጥ አስቸጋሪ እንደሚሆን ከወዲሁ ስጋቱን አስቀምጧል።

ቅድሚያ መሰራት የነበረባቸውን የምርጫ አስቻይ ሁኔታዎች ቅድሚያ አለመሰራታቸው ለስጋታቸው ምክንያት መሆናቸውንም የኢህአፓ ፕሬዚዳንት ለቦርከና ተናግረዋል።

በዚህም “ለምሳሌ ምርጫው አንድና ሁለት ዓመት ሲቀረው ቢያንስ እንኳ ለይስሙላም ቢሆን በየክልሎች እተዞረ ማደራጀትና ህዝብ ማወያየት ይገባ ነበር” ብለዋል።

- Advertisement -
Advertise here _ borkena

በመሆኑም “እስካሁን ምርጫ ለማካሄድ ምንም አስቻይ ሁኔታ የለም” ነው ያሉት። “ሰላማዊ ትግሉ ከባድ የሆነ ፈተና ውስጥ ነው ያለው፥ ሚዲያዎች ለመዘገብ እየተሸማቀቁና እየፈሩና እየተዘጉ ነው፥ ጋዜጠኞችና ፖለቲካኞች ታስተዋል፤ ጠንካራ የሚባሉ ሲቪክ ማህበራት ተግተዋል“ ያሉት አቶ አብርሃም፥ እነዚህ ድርጊቶች ባሉበት ኢህአፓ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት የለውም ሲሉም ስጋታቸውን ተናግረዋል።

“ሆኖም ከዚህ ወዲያ ህጋዊ መብታችንን ከመንግስት ብቻ አንለምንም፤ ህዝባችንን አንቅተን አደራጅተን ህገ መንግስታዊ መብታችንን ራሳችንም ማስከበር እንችላል በሚል ከፍተኛ ዝግጅት ላይ ነው ያለነው ትብብር ለኢትዮያ አንድነት የሚል ቅንጅት ፈጥረናል” ሲሉም አስረድተዋል።

“በይስሙላ ምርጫ መሳተፍ ስለማንፈልግ አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር እንታገላለን። ከምርጫ አንወጣም እስካሁን ድረስ ባለው ሂደታችን ዝግጅት ላይ ነን በምርጫ የምናምን ሰላማዊ ታጋዮች ነን” ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ “ሆኖም በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች ያሉት ጦርነቶች ቁመው በድርድር መፈታት፣ የፖለቲካ እስረኞችም መፈታት አለባቸው። እነዚህ ለምርጫው በጣም ወሳኝ ናቸው” ሲሉም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጠዋል።

ጠንካራ አባላት ፈጥረናል የማሉት አቶ አብርሃም፣ “መንግስት የሆነው ብልፅግና ምንም ቅቡልነት የለውም። በህዝብ የተጠላና ተፈትሾ የተጣለ ነው። አቅምም ብቃትም፣ ማህበራዊ መሰረትም ህዝባዊ ተቀባይነትም ያለን ፓርቲዎች እኛ ነን” ሲሉም መንግስትን አጣጥለዋል።

- Advertisement -

“በምንም መንገድ ብልፅግና እኛ ጋር ሊገዳደር የሚችል እንዳልሆነ እንውቃለን። ያለጥርጥር እናሳካዋለን። ነገር ግን ምናልባት ምርጫውን አጭበርብሮ አሁን በሚሄድበት አካሄድ ሂዶ በማጭበርበር ሊያሸንፈን ይችላል። ያ ማሸነፍ ሳይሆን ማጭበርበር ነው። ስለዚህ እውነተኛ ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄድ” ነው ያሉት።

መንግስት ይካሄዳል እያለው ላለው ሰባተኛው ዙር ምርጫ አስቻይ ሁኔታ ስለመኖርና አለመኖሩ፥ አስቻይ እንዲሆን ምን መደረግ እንዳለበት፥ ቦርከና አስተያየት የጠየቃቸው የእናት ፓርቲ ዋና ጠሐፊና የፖለቲካ ዝርፍ ሃላፊ አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) በበኩላቸው)፥ በተወሰነው የጊዜ ገደብ ውስጥ ምርጫ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስረድተው፥ “ግን የህዝብ ተወካዮችን፥ የሀገር መሪዎችን የመምረጥ ያክል ትልቅ ነገር ቅድሚያ ሰላምን ይፈልጋ” ብለዋል።

“ሰላም በሌለበት ሁኔታ ምርጫን ማድረግ የሚቻል አይደለም፤ እንኳን የሰላም እጦት ከዚህ ቀደም የነበረው የኮቪድ ችግርም ምርጫን ለማድረግ አስቻይ አልነበረም፤ ምርጫው ተራዝሞ አሁን ድረስ ለቀጠለው ቀውስ ተዳርገናል” ሲሉም አስታውሰዋል።

“የዘንድሮው ምርጫ ይካሄዳል የሚል እምነት አለን” ያሉት አሰፋ (ዶ/ር)፥ “ቅድሚያ ግን ሰላም መኖር አለበት። ምንም እንኳ በፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱ የቆመ ቢሆንም አሁንም በትግራይ ክልል ከፍተኛ የጦርነት እንቅስቃሴ አለ፤ በዚያም በዚህም ፉከራዎች መኖራቸውን መረጃ ያመለክታሉ” ብለዋል።

እንዲሁም በአማራ ክልል ከፍተኛ ጦርነት መኖሩን የጠቀሱት የእናት ፓርቲው አሰፋ (ዶ/ር)፥ “የአማራ ክልል ጦርነትም ምርጫን ለማድረግ አስቻይ ሁኔታ አይደለም፤ በኦሮሚያ ክልልም ከፍተኛ የሆነ አረመረጋጋት አለ፤ መንግስታና በኦነግ ሸኔ መካከል ጦርነት አለ” ብለው ምርጫ ለማካሄድ ጦርነቱን ማስቆም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

“ምርጫ ለማድረግ ፕሮግራምን ማሳወቅ ያስፈልጋል፤ ፕሮግራምን ለማሳወቅ ደግሞ ህዝብን መሰብሰብ መቻል አለበት’’ ብለው፥ “ህዝብን ለመሰብሰብ ግን የሰላም ዋስትና ያስፈልጋል፤ የምርጫ እጩዎችንና የምርጫ ታዛቢዎችን መመልምልም ያስፈልጋል፥ እነዚህን ሁሉ ለማድረግ ደግሞ አሁን ያለው ሁኔታ እጅግ በጣም አስቸጋሪ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።

መንግስት ወደ ሰላም መጥቶና ሁሉን ነገር አረጋግቶ ለምርጫ ሊሆን የሚችል ድባብ ከፈጠረ እናት ፓርቲ በሰባተኛው ዙር ምርጫ ለመሳተፍ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል። የፓርቲው አካላት ግን በምርጫው እንሳተፋለን ወይም አንሳተፍም የሚለውን ውሳኔ ላይ እንዳልደረሱና ሁኔታዎችን እተከታተሉ ስለመሆኑም የእናት ፓርቲው አሰፋ አዳነ (ዶ/ር) ለቦርከና ተናግረዋል።

የኢህአፓ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት በበኩላቸው፥ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለፁት አይደለም ኢህአፓ በሀሳብም ቢሆን በሁሉም ጠንካራ ሀሳብ በፖሊሲም በሰው ሀይልም ዝግጁ ነው። ድርጅታችን አስቻይ ሁኔታ እንዲኖር፣ ምህዳሩ እንዲሰፋ፥ እውነተኛ፥ ገለልተኛና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ተካሂዶ ይች ሀገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ትረፍ። እውነተኛ ምርጫ ካልተካሄደ ግን እንደምትፈርስ ጭምር ነው የምንናገረው” ብለዋል።

በሌላ በኩል፥ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ ዝግጅት ከማደረግ በተጫሪ ግትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ከወዲሁ መሞገትም አለበት ተብሏል። የኢሕፓ ፕሬዚዳንት አቶ አብርሃም ሃይማኖት ቦርዱን በተመለከተ ለቦርከና በሰጡት አስተያየት፥ “ምርጫው ራሱ ፖለቲካ ምህዳሩ እንዲሰፋ የሚያደርግ እውነተኛ ድርድር ከተቃዋሚ ፖርቲዎች ጋር መንግስት ማድረግ አለበት” ሲሉም አክለዋል።

…………………………………………………

የቦርከናን ዮቲዮብ ቻናል ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena

ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English

ኤክስ ፡ @zborkena

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisement -spot_img

የቅርብ ጊዜ

- Advertisement -spot_img

Related News