
ቦርከና ዜና
21/02/2018
-ሌሎች ተቋማትም ግድያውን በጽኑ አውግዘው ተጨማሪ ጥቃት እንዳይደርስ ለመንግስት አሳስበዋል
የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) በአርሲ ዞን የፈጸመውን ግድያ በተመለከተ፣ “የብልጽግና መንግስት ተጠያቂነቱን እንዲያምን እና ወንጀሉን የፈጸሙት አካላት በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ” ሲል ጠይቋል።
“የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይን ንጹሐን ዜጎችን በግፍ መግደል ያብቃ፤ ዜጎች በህይወት የመኖር ዋስትና ያግኙ” ሲልም አሳስቧል።
ኢሕአፓ ይህን ያለው፣ ሰሞኑን አርሲ ዞን የተፈጸመውን ዘግናኝ ግድያ በተመለከተ ዛሬ ጥቅምት 21 ቀን 2018 ዓ/ም ባወጣዊ መግለጫ ነው።
በዚህም፣ ከጥቂት አመታት ወዲህ የተባባሱት በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ መጠነ ሰፊ በእምነትና በዘር ልዩነት ላይ የተመሰረቱ ግድያ፣ እገታ፣ ማፈናቀል፣ የንብረት ውድመቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ አሳስቧል።
በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ አርሲ ዞን በጥቅምት 2018 ዓ/ም 25 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ምዕመናን በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የጠየቀው ፓርቲው፣ ለጉዳዩ ገዢው ብልጽግና ፓርቲን ተችቷል።
“ገዳዮቹ የኢትዮጵያዊነትና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ዕምነት ጠል ስብስቦች፤ የፈጸሙትን ግድያና ያደርሱትን አካላዊ ጉዳት ለሁሉም ዜጎች የሚቆምና የሚቆረቆር መንግስት ቢኖር ወይም መንግስት እጁ ባይኖር አያደርጉትም፤ ወንጀል ሰርተውም ያለተጠያቂነት አይፏሉሉም ነበር” ነው ያለው።
ድርጊቱን፣ ለሰብዓዊ መብት መከበር፤ ለእኩልነትና ለሕግ የበላይነት መስፈን የሚታገሉ ኃይሎች ሁሉ ሊያወግዙት የሚገባ ኢሰብዓዊ፣ እኩይና አፍራሽም ተግባር መሆኑን ገልጾ፣ የገዳዮችና የአሰማሪዎቻቸው ዓላማም የህዝቡን አንድነት በማናጋት ሀገርን ማፍረስ ነው” ሲል ወንጅሏል።
በምዕመናኑ ላይ የተፈጸመውን ግድያና ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት በጽኑ ያወገዘው ኢሕአፓ፤ “መንግስት ቢያንስ የዜጎችን በህይወት የመኖር መብት እንዲያከብር አጥብቀን እናሳስባለን” ሲል በመግለጫው አስፍሯል።
ሕይወታቸውን ላጡና የጥቃቱ ሰለባ ለሆኑት ሁሉ ሃዘኑን በመግለጽ፤ አካላዊ ጉዳት ለደረሰባቸው ምዕመናን እና ለሟቾቹ ቤተሰቦች ስለደረሰው በደልና ጉዳት ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ አስፈላጊውን ካሳ እንዲከፍል ኢሕአፓ በመግለጫው መንግስትን አሳስቧል።
“ያለጥርጥር የሕዝብን ሰላምና አንድነት የሚያናጉ በርካታ ተግባራት ተፈጽመዋል” ሲል አያይዞ የገለጸው ፓርቲው፣ “ዜጎች አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያለውን ሰንደቅ ዓላማ ለምን ያዛችሁ፣ ለምን አረንጓዴ ቢጫና ቀይ ቀለማት ያላቸው ልብሶች ለበሳችሁ በሚል ድብደባና ወከባ ተፈጽሞባቸዋል” ብሎ፣ “ዜጎች የመረጡትን ቀለም ቢለብሱና ቢከናነቡትስ፣ መንግሥትን ምን ያገባዋል?” ሲልም ጠይቋል።
የዜጎች በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል የመኖርና ሃብት የማፍራት መብት ተጥሶ፣ በተለይ ባለፉት ሰባት ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ በዘር እና ሃይማኖት ላይ ያተኮረ ግድያ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በፖሊሲ የሚመሩ በሚያስመስላቸው ደረጃ ተፈጽመዋል ሲልም ከሷል።
ወንጀሎቹ በተፈጸሙባቸው ቦታዎች የነበሩ የፀጥታ አካላት የሚጠበቅባቸውን የዜጎችን ህይወትና ደህንነት የመጠበቅ ግዴታቸውን እንዳልተወጡ የገለጸው ፓርቲው፣ “ወንጀሉ ሲፈጸም በዝምታ ማሳለፋቸውና ከገዳዮቹ ጋር ተባባሪነታቸውን ማሳየታቸው በርካቶች በጉዳዩ ላይ የመንግሥት እጅ አለበት ብለው እንዲደመድሙ አድርጓል” ብሏል።
“በገዥው ድርጅትና በወቅቱ መንግስት ላይ ዜጎች ከፍተኛ ጥርጣሬቸውን እየገለጡ ነው” ሲልም በመግለጫው አስፍሯል።
“መንግሥት ስልጣን የሚይዘው የዜጎችን በህይወትና በሰላም መኖር እንዲሁም አገራዊ አንድነትን ለማስጠበቅ ነው” ሲል ገልጾ፣ የህዝቡን ደኀንነት እንዲጠብቅ አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት በበኩሉ፣ የአርሲውን የአማኞች ግድያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፣ የ25 ኦሮቶዶክሳዊያን ከሰቃቂ ጭፍጨፋ እንዳሳዘነው ገልጿል። ባለፉት ዓመታት በኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ያነጣጠረ ግድያ ሲደጋገም መታየቱን የጠቀረው ምክር ቤቱ፣ ባለፈው ሰኔ በደብረ ከዋክብት ዝቋላ ገዳም የሚገኙ መነኮሳት መገደላቸው አስታውሷል።
የሚመለከታቸው አካላት ምዕመናንን በሃይማኖት እና በብሔር ለይተው ከሚያንገላቱና ነፍስ ከሚያጠፉ እንዲጠብቋቸው አሳስቦ፣ “ሃይማኖትን በነፃነት እየተከተሉ መኖር ከሰብዓዊ መብቶች ዋነኞች መካከል በመሆኑ ሊጠበቅ ይገባል” ሲልም አሳስቧል።
የኢትዮጵያ ሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል በበኩላቸው በግድያው ላይ መግለጫ አውጥተው፣ ድርጊቱን አግዘዋል። ጉባዔው፣ በአርሲ በኦርቶዶክሳዊያን እየደረሰ ያለው ግድያና ስቃይ በየጊዜው እየጨመረ መሆኑን ተረድቻለሁ ብሏል።
መንግስት የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት ነፃነት የማረጋገጥ ዋንኛ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የጠቀሰው ጉባዔው፣ ችግሩ ከዚህ በላይ ተባብሶ ተጫማሪ ሰቆቃ ከመከሰቱ በፊት አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሰራ አሳስቧል።
……………………………………………….
የቦርከናን ዮቲዮብ ቻናል ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ
የቴሌግራም ቻናላችን ይቀላቀሉ ፡ t.me/borkena
ፌስቡክ ገጻችንን ላይክ ያድርጉ ፡ Borkena
Ethiopian News – Borkena English
ኤክስ ፡ @zborkena






